Monday, 29 September 2014 09:03

ያቺን ቀን ፍለጋ!

Written by  ዮሐንስ ገ/መድህን
Rate this item
(4 votes)

                 ሰለሞን ወደግል ድርጅቴ ያለ ቀጠሮ መጣ፡፡ የሥራ ዲሲፒሊን አለኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ ቀጠሮ ላይ በጣም ጥብቅ ነኝ፡፡ ያለ ቀጠሮ ባለጉዳይ አላነጋግርም፡፡ ነገር ግን ሰለሞን በጣም የምወደው አብሮ አደግ ጓደኛዬ ነው፡፡ አሁን አሁን የኑሮ ሩጫ እንደልብ ባያገናኘንም እወደዋለሁ፡፡ ከሰሞን ባህርይ የማልወድለት ሲበዛ ጠጪ መሆኑን ነው፡፡ በዚያም ላይ ሾፌር ነው፡፡ ደጋግሜ ብነግረውም አልተለወጠም፡፡ “እንዲህ በእግር በፈረስ የፈለከኝ በደህና ነው?” አልኩት ሰላምታ ተለዋውጠን ከተቀመጠ በኋላ፡፡ “ምን ዓይነት ችግር?” ደንገጥ ብዬ ጠየቅሁት፡፡ “መኪናዬ ተበላሽታብኛለች፤ በዚያ ላይ ደግሞ አባባ ታሟል፤ ና ተብዬ ወደዚያው ልሄድ ነው፡፡ አንድ ሳምንት ሙሉ ምንም ሥራ የለም፤ አባባ ጋር ከሄድኩ ደግሞ ባዶ እጄን እንዴት ብዬ ታውቀዋለህ አይደል?” “እና?” “ምን እና ያስፈልገዋል? ገንዘብ እንድታበድረኝ ፈልጌ ነው” በዝምታ ጥቂት አሰብኩ፡፡ ከዚያም፡- “ሶል አጉል ጊዜ ነው የመጣኸው፤ በአሁኑ ወቅት ልሰጥህ የምችለው ገንዘብ የለኝም” አልኩት “እንዴት ገንዘብ የለኝም ትላለህ?” አፈጠጠብኝ “ገንዘብ የለኝምና ልሰጥህ የምችለው ገንዘብ የለኝም ይለያያል፡፡ ልጆቼን ላንጋኖ ላዝናናቸው ቃል ስለገባሁላቸው አሁን ልሰጥህ አልችልም፡፡” አልኩት ፍርጥም ብዬ፡፡

“እኔ አባቴ ታሟል እያልኩህ አንተ ልጆቼን ላንጋኖ ይዤ እ - ቂ! ቂ - ቂ - ቂ!” ከተቀመጠበት ተነስቶ ቁልቁል ከተመለከተኝ በኋላ የምሬት ሳቁን ትቶልኝ ከቢሮዬ ወጥቶ ሄደ፡፡ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ ለህፃናት ልጆች ቢቻል ቃል አለመግባት፣ ቃል ከገቡ ደግ መፈፀም አለበት ብዬ አምናለሁ፤ ይህን በምንም አልለውጠውም፤ ለልጆቼ ከኔ በላይ የሚቀርባቸው ደግሞ ማንም የለም፡፡ መኪናዬ ጋራዥ ገብታ ያለው እውነት ሊሆን ይችላል፤ መኪናው ሰበበኛ ናት፤ አምስት ቀን ከሰራች አምስት ቀን ትቆማለች፡፡ አባቴ ታሟል ያለውን ግን እጠራጠራለሁ፤ ምናልባት ለዚያችው ለሱሱ ለመጠጡ ፈልጎ ይሆናል…” እንዲህ እንዲህ እያሰብኩ ቆይቼ ወደቤቴ አመራሁ፡፡ ፋታ የሌላቸው ቀናት፣ ፋታ ሳይሰጡ ነጎዱ፡፡ ሰሞኑንማ ለጉድ ነው! በሰንበት እንኳ ፋታ የለም፡፡ ቀጠሮዬ ቦታ በጠዋት ደርሻለሁ፡፡ ይኼ ቀጠሮ ቢሳካልኝ እንዴት ጥሩ ነበር? ሰለሞን ያኔ ከኔ ቢሮ ከወጣ ከአንድ ወር በኋላ ጠጥቶ ሲያሽከረክር የመኪና አደጋ ደርሶበት ሆስፒታል ገብቷል፡፡

አንድ ጊዜ ሄጄ ጠይቄዋለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ዛሬ እሄዳለሁ ነገ እሄዳለሁ ስል ፋታ የት ተገኝቶ! ከትናንት በስቲያ ባለቤቱ ሄዋን ስትደውልልኝ እንዴት እንዳፈርኩ! “እባክህን” አለችኝ ሄዋን “ለልጆቼ የደንብ ልብስና የትምህርት ቤት ማስመዝገቢያ እጅ አጠረኝ፤ አንተን ላስቸግር ነው” ምስኪን አልኩኝ በልቤ፡፡ “የምን ማስቸገር ነው ያውም ለሰለሞን! ያውም ላንቺ ለሄዋን ልጆች… ምንስ ቢሆን .. በቃ አታስቢ!” አልኳት፡፡ አቤት ቅብጠት! ምን ተይዞ ነው አታስቢ! ይኸው ሃሳቡ ለኔው ብቻ ተረፈ፡፡ ያውም በመስከረም አታስቢ? እንደሰሞኑ ዝናብ እኝ እኝ የሚል ማለቂያ የሌለው ወጪ ከፊቴ ተከምሮ ያፈጥብኛል፡፡ መስቀል ደግሞ ይኸው መጣሁ እያለ ነው፡፡ ዓይኖቼ መንገድ መንገዱን እየቃኙ የቆጠርኩትን ባለሀብት መኪና ይቃኛሉ፡፡ ከአጠገቤ ካለው መዝሙር ቤት ወደሚሰማው ስብከት ጆሮዬን አዘንብዬ በማድመጥ ላይ ነኝ፡፡

“በሙሴ በኩል ሕዝቤን ልቀቅ እያለ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የተለያዩ ምልክቶችን ቢያሳየውም ፈርኦን ይበልጥ ልቡን እያደነደነ ሄደ፡፡ ይባስ ብሎም ለጡብ መስሪያ ያስቀርብላቸው የነበረውን ጭድ ‹ራሳችሁ ፈልጋችሁ አምጡ› አላቸው፤ ልብ በሉ! ጫፍና ጫፉ ላይ ቅርጫት የተንጠለጠለበት አግዳሚ እንጨት ትከሻቸው ላይ አስቀምጠው፣ ሁለት ቅርጫት ሙሉ የጡብ መሥሪያ ጭቃ ተሸክመው፣ በግራና በቀኝ እጃቸው የተሸከሙትን እንጨት ደግፈው ቀኑን ሙሉ ሲመላለሱ መዋል እንዴት አድካሚ እንደሆነ ይታያችኋል? ይህ ሁሉ ሳያንስ ይህ ሁሉ ሳይበቃ፣ በዚህ ላይ ተጨማሪ ጭድ ሲጨመርበት ጭዱን ለመሰብሰብ የሚፈጅባቸው ጊዜ የሚታሰብ አይደለም፡፡

ከአሁን በፊት ሲሰሩት እንደነበረው እንዲሰሩ ነው የተደረገው፡፡ ትከሻቸው ላይ ያለውን እንጨት በሚደግፉበት በእጃቸው ጭድ ሲታቀፉበት፣ ትከሻቸው ላይ ያለው እንጨት በእጅ መደገፍ ስለቀረ፣ ከትከሻቸው ወደኋላ እንዳይወድቅ ወደፊታቸው አጎንብሰው ጎብጠው መሄድ ጀመሩ፤ ከኋላቸው ደግሞ በፈረጠመ ክንዳቸው ጅራፋቸውን በማስጮህ፣ ጀርባ ጀርባቸውን እያሉ የሚያጣድፏቸው የፈርዖን ወታደሮች ይከተሏቸዋል፡፡ ቀና ማለት አይችሉም፤ ሁሉም አጎንብሶ የየራሱን መንገድ ይጠበጥባል፡፡ ሁኔታቸውን በዓይነ ህሊናዬ ስስለው አስገረመኝ፡፡ ደግሞ ለኔ ጭምር የተነገረ መሰለኝ፡፡ ጎብጫለሁ፡፡ አጎንብሻለሁ፡፡ ምን እኔ ብቻ? ሁላችንም ጎብጠናል፡፡ የምንሸከመው ጡብ ዓይነቱ ይለያይ እንጂ የሁላችንም ቅርጫት አንድ ዓይነት ነው፤ የማናወርደው የማንጥለው ኑሮ የሚባል ቅርጫት! ጊዜ ደግሞ እንደ ጅራፍ ደረስኩ እያለ እየጮኸ ይከተለናል፡፡ “ዛሬ ይሄን ካላደረስክ!”፣ “ዛሬ ይሄን ካልከፈልክ!” “ዛሬ ይሄን ካልጨረስክ” ዛሬ… ዛሬ… አሁን!... የጊዜ ጅራፍ ሳያቋርጥ በቀናቶቻችን ላይ እየጮኸ ፋታ ይነሳናል፤ ለማይሞላ ቅርጫት… ቅርጫቱ… ግራና ቀኝ ትከሻችን ላይ የተሸከምነው ቅርጫት … በቃኝ አያውቅም… የቤት ኪራይ… የመብራት … የውሃ… የስልክ … አገር ውስጥ ገቢ… መዋጮ… የቤት አስቤዛ… የልጆች… ሁሉም ዓይነት ወጪ… የዘበኛ… የቤት ሰራተኛ… የላውንደሪ… የጋራዥ… የወፍጮ… ወዘተ... ወዘተ… ወዘተ ቅርጫቱ ሞልቷል፤ ይከብዳል፡፡

ከኔ ቅርጫት ውስጥ “በቃ አታስቢ!” ብዬ የተቀበልኩት ጭድ፤ ራሴ እፈልገው ዘንድ ግድ የሆነብኝ ጭድ! እናም ይኸው ጭድ ልፈልግ ወጥቻለሁ፤ ከወገቤ ቀና ብዬ ወደ ጎን ሌላውን ለማየት አልችልም፤ አለመፈለግ ሳይሆን አለመቻል ነው፡፡ በየዕለቱ አጎንብሼ የራሴን መንገድ ብቻ እጠበጥባለሁ፡፡ የኑሮ ሸክም አጉብጦኛል፤ አጎብንሼ መንገድ መንገዴን ብቻ አያለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ መሀከል ግን ቀና ብዬ የምቆምበትን ቀን እናፍቃለሁ፡፡ ከጎኔ የኑሮ ሸክም ያጎበጠውን… ሸክሙን አግዤው ቀና እንዲል፤ ቀና ብሎ እንዲራመድ፡፡ ሁላችንም ቀና እንድንል፡፡ ያቺን ቀን እናፍቃለሁ፡፡ ነገር ግን ያቺ ቀን መቼ ናት? ድንገት የቀጠርኩት ሰው ከመኪናው ወርዶ እኔ ወዳለሁበት ሲያመራ ተመለከትኩ፡፡ ያቺ ቀን ዛሬ ትሆን? ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ፡፡

Read 4021 times