Saturday, 11 October 2014 12:37

“በሰንደቅ አላማው ላይ ብሄራዊ መግባባት ያስፈልጋል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

               የዘንድሮው ብሄራዊ ሰንደቅ አላማ ቀን ለ7ኛ ጊዜ “በህዝቦቿ ተሳትፎና ትጋት ድህነትን ድል በመንሳት ብሄራዊ ክብሯንና ሰንደቅ አላማዋን ከፍ ከፍ በማድረግ ላይ ያለች ሃገር ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የፊታችን ሰኞ በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡ አንዳንድ በአገር ውስጥ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በሰንደቅ አላማው (ባንዲራው) ላይ የተቀመጠውን አርማ የሚቃወሙ ሲሆን በሃገሪቱ ሰንደቅ አላማ ላይ ብሄራዊ መግባባት የለም የሚሉም በርካቶች ናቸው፡፡ መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር ህገ-መንግስት፣ ሰንደቅ አላማ እና ብሄራዊ መዝሙር መለዋወጣቸው ስርአቶች በመሳሪያ ኃይል ወደ ስልጣን የመምጣታቸው ሚስጥር ነው ሲሉ የሚገልፁት ተቃዋሚዎች፤ በእነዚህ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ መግባባት ያስፈልገናል ይላሉ፡፡

በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሰንደቅ አላማው ላይ በሚቀመጠው አርማ ላይ ለምንድን ነው ተመሳሳይ አቋም የሌላቸው? በሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራርና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ “የማንስማማበትን እየፈለግን እናጉላ ካልን፣ ብዙ ነገሮችን እየመዘዝን ማውጣት ይቻላል፡፡ ህገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ባንዲራ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ይሆናል ብሎ በግልፅ ደንግጓል፣ ብሄራዊ አርማ ይኖረዋል ሲልም ያክላል” ብለዋል፡፡ “አርማው ለኔ ትርፍ ነገር ነው” የሚሉት የተከበሩ አቶ ግርማ፤ ቁም ነገሩ በሰንደቅ አላማው ቀለማት ላይ መስማማቱ ነው ይላሉ፡፡

“የባንዲራ ቀን የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአዴግን ካሸነፈባቸው ቀኖች አንዱ ነው” ሲሉ የተከበሩ አቶ ግርማ ይገልፃሉ፡፡ ባንዲራ ከጨርቅነት ያለፈ ትርጉም የለውም ሲል የነበረ መንግስት፤ ባንዲራን አከብራለሁ ብሎ መነሳቱ ወደ ህዝቡ ለመጠጋት ያለውን ፅኑ ፍላጎት ያሳያል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ጉዳይ ላይ ለድርድር እንደማይቀርብ አውቆ፣ ወደ ህዝቡ ፍላጎት በመምጣት ጨርቅ ነው ያለውን ባንዲራ ማክበሩ በበጎ የሚታይ ነው ይላሉ፡፡ አርማውን እንጠላለን የሚሉ ወገኖች በትልቁ ሊያዩት የሚገባው ባንዲራው አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ መሆኑን ነው የሚሉት የተከበሩ አቶ ግርማ፤ እኔም ሁልጊዜ የማየው ይሄንኑ ነው ብለዋል፡፡ በባንዲራ ጉዳይ ብሄራዊ መግባባት እንደሌለ ማንም የሚያውቀው ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ “ኢህአዴግ ግትር አቋሙን ትቶ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በዲፕሎማት ፅ/ቤቶች አርማው ያለበትን ማውለብለብ ግዴታ ነው” ቢልና ሌላው የፈለገውን እንዲያደርግ ቢፈቅድ መልካም ነው ብለዋል፡፡ የኮከቡ ፍቅር ያለበት ባለኮከቡን እንዲያውለበልብ፣ ኮከቡን አልፈልግም ያለ ሌላው ዜጋ ግን ሶስቱን ቀለማት ብቻ እጠቀማለሁ ካለ ክብሩን በጠበቀ ሁኔታ መያዝ እንዲችል ተደርጎ ቢፈቀድ የተሻለ ነው ይላሉ የተከበሩ አቶ ግርማ፡፡

አሁን ያለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር ከሁሉም የተሻለ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግርማ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚፈልገውን ሃሳብ የያዘ ነው፣ እንድንወደው ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡ በሶስቱ ቀለማት ላይ ልዩነት ያለ አይመስለኝም የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ በተቀመጠው አርማ ላይ ግን ኢህአዴግን ሊተካ የሚችለው መንግስት ህዝበ ውሳኔ ሊያካሂድ ይችል ይሆናል ሲሉ ይገልፃሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ሰንደቅ አላማው ቋሚ አይደለም ማለት ግን አይደለም ያሉት አቶ ግርማ፤ በአርማው ላይ አለመግባባት ማለት በአጠቃላይ በሰንደቅ አላማው ላይ አለመግባባት አለመሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ በባንዲራ ጉዳይ ያለውን ልዩነት ብዙም ተወያይተንበት አናውቅም የሚሉት የአረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ጸጋዬ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው የብሄር እኩልነትን እንደሚቀበል ጠቁመው፤ “አሁን ያለውን ሰንደቅ አላማም የምንቀበልበት አዝማሚያ ነው እስካሁን ያለው” ብለዋል፡፡ መቼ ይሆን መንግስት በተቀያየረ ቁጥር የማይለዋወጥ ባንዲራ እና ብሄራዊ መዝሙር የሚኖረን ስል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ጎይቶም፤ “ብሄራዊ መዝሙሩም ሆነ ባንዲራው ቋሚ ሊሆን የሚችለው ኢህአዴግ ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ ሲያስረክብ ብቻ ነው” ይላሉ፡፡

በአመፅ ወይም በሌላ መንገድ ከወረደ ግን ስርአቱን ከመጥላት አንፃር ቀጣዩ መንግስት አርማውንም ላይቀበለው ይችላል፡፡ አሁን ባለው አርማ ላይም ሌላ ይበልጥ ኢትዮጵያን ይገልፃታል የሚባል አርማ ከመጣም ተወያይቶ ለመቀበል ኢህአዴግ ዝግጁ መሆን አለበት ይላሉ፤ አቶ ጎይቶም፡፡ አርማውም ሆነ ብሄራዊ መዝሙሩ ቋሚ የሚሆነው አሁን ያለው መንግስት በሰላማዊ መንገድ በህዝባዊ ምርጫ ስልጣን ሲለቅ ብቻ ነው ብለዋል፤ አቶ ጎይቶም፡፡ አረና አሁን ያለውን ባንዲራና አርማ እንደ ብሄራዊ መገለጫ ተቀብሎ እንደሚንቀሳቀስ አቶ ጎይቶም አክለው አስረድተዋል፡፡ የመድረክ አመራር የሆኑት የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ገብሩ ገ/ማርያም በበኩላቸው፤ ንጉሡ ሞኣ አንበሳ ያለበትን፣ ደርግ ሌጣውን፣ ኢህአዴግ ደግሞ የኮከብ አርማ ያለውን ሰንደቅ አላማ መጠቀማቸውን አስታውሰው፤ ባንዲራ ከጨርቅነቱ በስተጀርባ የአገር ሉአላዊነት መገለጫ ነው ይላሉ፡፡ የአሁኑ አርማ የብሄር ብሄረሰቦችንና ሃይማኖቶችን እኩልነት ለመግለፅ ታስቦ የተቀረፀነው የሚሉት አቶ ገብሩ፤ “ይሄን ባንዲራ አንቀበልም የሚሉ የድሮውን ናፋቂ ናቸው፤ እዚህ ሃገር ላይ አሃዳዊ መንግስት መልሰን እናሰፍናለን የሚለው ለኔ አይሰራም ይላሉ፡፡

ባንዲራ የአንድ ሃገር ሉአላዊነት መገለጫ እንደመሆኑ፣ ፓርቲያቸው ውስጥ በባንዲራ ጉዳይ ብዙም ውይይት እንዳልተደረገ አስታውሰው፣ ፓርቲው ፌደራሊዝምን የሚቀበል እንደመሆኑ በቀጣይም ይሄን ባንዲራ የማይቀበልበት ምክንያት እንደሌለ ገልፀዋል፡፡ በባንዲራ ጉዳይ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባሉ ኢትዮጵያዊያን መካከል የተፈጠረው አለመግባባት የብሄራዊ አለመግባባት ውጤት ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ ችግሮቹን ነቅሶ አውጥቶ በጉዳዩ ላይ ተነጋግሮ አንድ አቋም ለመያዝ የሚያስችል ሰፊ የመወያያ መድረክ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አንድ ብሄራዊ ጉዳይ ሁሉንም ማስማማት ባይችል እንኳ አብዛኛውን ህዝብ ማስማማት አለበት የሚሉት የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ ስዩም መንገሻ፤ የባንዲራው ጉዳይም ያለመግባባቱ አንድ አካል ነው ይላሉ፡፡ “ሃገር የምትወከልበት ባንዲራ የእኔነት ስሜት የሚያመጣ መሆን አለበት” የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ በሶስቱ ቀለማት ላይ አሁን ያለው አርማ ሲቀመጥ ምን ያህሉ ህብረተሰብ ነው የተወያየበት? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አንድነት በርካታ ጉዳዮች የህዝቡን ፍላጎት የጠበቁ አይደሉም ብሎ ስለሚያምን መንግስት ቢሆን እንደገና የህዝብ ውሳኔ ሊያሰጥበት ይችላል ያሉት አቶ ስዩም፤ “የሰንደቅ አላማው ጉዳይም ዳግም ለህዝብ ውይይት ከሚቀርቡት አንዱ ነው፣ በጉዳዩ ላይ ህዝብ እንዲወስን ይደረጋል፡፡ በብሄራዊ መዝሙሩ ላይም ተመሳሳይ ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግና የህዝብን ስሜት የጠበቀ እንዲሆን እናደርጋለን” ይላሉ፡፡ በእኛ እምነት አሁን ያለው ህገ መንግስት ብዙ የሚያግባቡ ጉዳዮችን ያካተተ ነው፤ የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ ምናልባት የማሻሻል ካልሆነ በቀር ሙሉ ለሙሉ የሚቀየር ነው ተብሎ አይታሰብም ብለዋል፡፡ የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በበኩላቸው፤ ሰንደቅ አላማ የዜግነት ምልክት ነው ይላሉ፡፡ የሰንደቅ አላማ ቀን መከበሩም በጎ ነው ባይ ናቸው፡፡

እንደ እድል ሆኖ በንጉሱም፣ በደርግም ሆነ በዚህ መንግስት ባንዲራው ላይ የሚቀመጡ አርማዎች ሙሉ ለሙሉ የህዝብ ድጋፍ አላገኙም የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ “መንግስታት በተለዋወጡ ቁጥር የመቀያየሩ ነገር ገና አላበቃለትም፤ ለወደፊትም ይቀጥላል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡” ይላሉ፡፡ የፈረንሳይ ሰንደቅ አላማ ከፈረንሳይ አብዮት ጀምሮ ሳይለወጥ፣ የአሜሪካም እንዲሁ ወጥነቱን ጠብቆ የዘለቀ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ከዚህ አንፃር ሃገሪቷን የሚወክል ሁሉንም ያግባባ፣ ወካይ ሰንደቅ አላማ በሁለት እግሩ ለማቆም ገና ነን ይላሉ፡፡ በአፄው ዘመን ዘውዳዊ ስርአቱን የሚወክል ሞአ አንበሳ፣ በደርግ ህብረተሰባዊ ስርአቱን የሚወክል አርማ፣ አሁን ደግሞ ብሄር ብሄረሰብ በሚል የብሄር እኩልነት የሚወክል አርማ መቀመጡን የጠቆሙት ምሁሩ፤ በዚህ መነሻ “እኔ የእገሌ ብሄር ነኝ ሲል አንድ ሰው በአንፃሩ የእገሌ ብሄር አይደለሁም ማለቱን ስለሚያንፀባርቅ፣ ዜጋ የሚለውን በሚገባ ይወክላል ማለት አይቻልም ባይ ናቸው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ “ዜግነት” የሚለው አንድ ቀን መምጣቱ አይቀርም የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ዜጋ የሚለው ቢወከል እኔ የእገሌ ብሄር ነኝ የሚለው አስተሳሰብ አይኖርም ባይ ናቸው፡፡

መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር የአርማው መቀያየር አንድ የሚያግባባን ሁለንተናዊ የሆነ አርማ እስከዛሬ ስላላገኘን ነው የሚሉት ምሁሩ፤ ሌላ መንግስት ሲመጣ አሁን ያለውም መቀየሩ አይቀርም ብለዋል፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት መሃል ላይ በክብ ሰማያዊ መደብ ላይ ኮከብ ያለበት ሰንደቅ አላማ የአሁኒቷ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቅ አላማ መሆኑን የገለፁት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባልና የህግ ባለሙያ እንዲሁም በብሄራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን በዓል አከባበር ብሄራዊ ኮሚቴ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ዳዊት ተፈራ፤ ቀደም ሲል ግን በተለያዩ አገዛዞች የተለያዩ ብሄራዊ አርማ ያላቸው ሰንደቅ አላማዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ መደበኛ ቀለማቱ ተለውጠው አያውቁም፤ በየጊዜው የሚለያዩት ብሄራዊ አርማዎቹ ናቸው ያሉት አቶ ዳዊት፤ አሁን ያለው ሰንደቅ አላማ ላይ የተቀመጠውን ብሄራዊ አርማ ምንነት ሲያስረዱ ሰማያዊ መደብ መሆኑ ሰላምን፣ እኩል ቀጥታ የሆኑት የኮከቡ መስመሮች የብሄረሰቦች እና የሃይማኖት እኩልነትን እንዲሁም በነዚህ መስመሮች የተዋቀረው ኮከብ፣ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድ የመሰረቱት አንድነትን ለማሳያነት የተቀመጠ ሲሆን ቢጫ ጨረሮቹ የፈነጠቀውን ብሩህ ተስፋ ለመጠቆም ነው፤ በህገ መንግስቱ መሰረት፤ ይሄ የአሁኑ አርማ በህገ መንግስት አርቃቂ ቡድኑ በከፍተኛ ድምፅ የተወሰነ መሆኑን ያጠቆሙት አቶ ዳዊት ከነበረው ቀለማት ላይ አርማው ቢቀመጥ ቀድሞ የነበሩት ቁርሾዎችን፣ የአንድነትና እኩልነት እጦት ሊገልፁና ወደፊት የምትመሰረተው ሃገር ኢትዮጵያ፤ በአንድነትና በእኩልነትና ላይ የተመሰረተች መሆኗን ሊጠቁም ይችላል በሚል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “አይ ይሄን አልቀበልም የሚሉ ወገኖች የራሳቸው ሰንደቅ አላማ ሊኖራቸው ይችላል፤ ነገር ግን ያ የኢትዮጵያ ህዝቦች ነው ማለት አይቻልም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛው የተቀበለው ይሄኛውን ሰንደቅ አላማ ስለሆነ ሰንደቅ አላማውን እንደ ሃገር መቀበል ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

Read 12595 times