Monday, 13 October 2014 07:12

ጣጠኛው ጋን

Written by  ድርሰት - ሉዩጂ ፒራንዴሎ ትርጉም - ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(3 votes)

           የዘንድሮው የወይራ ፍሬ ምርት የሰጠ ነበር፡፡ ዶን ዚርፋ ሎሎ በፕሪሞሶሌ አያሌ የወይራ ዛፎች ነበሩት፡፡ የዓመቱ የተትረፈረፈ የዘይት ምርቱን አምስቱ ጋኖች መያዝ እንደማይችሉ በመገመት፣ ዲላማስትራ ከሚገኝ የጋን ፋብሪካ ጋን ለማሰራት ወሰነ፡፡ እንዲሰራለት ያዘዘው ቁመቱ የሰው ደረት ላይ የሚደርስ፣ ሰፊና ግርማ ሞገስ ያለው ውብ ጋን ነው፡፡
በዚህ የጋን ሥራ ከሸክላ ሰሪው ጋር ተጨቃጭቆ ነበር፡፡ ለነገሩ ከዶን ሎሎ ጋር የማይጨቃጨቅ ማን አለ? በትንሽ በትልቁ ከማንም ጋር እንደተቧጨቀ ነው፡፡ ከግንቡ ላይ ኮረት ወይም የሳር ዘለላ ወደቀ በሚል ከተማ ሄዶ ለመክሰስ “በቅሎዬን ጫኑልኝ” እንዳለ ነው፡፡ ለረባ ላልረባው እየተመላለሰ ያሰለቸው የሎሎ የህግ ጠበቃ፤ ለእያንዳንዷ ቁርሾ የሕጉን አንቀጽ ራሱ እንዲፈልግ መጽሐፍ ሰጠው፡፡ ይህቺው እንደ ፀሎት መጽሐፍ የነተበች የሕግ መጽሃፉ፤ የመንደሯ ነዋሪዎች ማላገጫ ሆነች፡፡ በፊት ከሎሎ ጋር የተጣሉ ሰዎች “በቅሎህን ጫን” እያሉ እንዳላሾፉበት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “መፅሐፍህን ግለጥ” በማለት ሲያላግጡበት፣ እሱም “የውሻ ቡችሎች! ሁላችሁንም ዶግ አመድ እያለ ያስፈራራቸዋል፡፡”
አራት መህልቅ ወርቅ የተከፈለበት ጋን፣ በማጀት ቦታ እስኪገኝለት ድረስ ለጊዜው በምድር ቤት ተቀመጠ፡፡ የወይራ አተላ ዝቃጭ በሚሰነፍጥበት፣ ብርሃንና አየር በማይገባበት ሸጋታ ስፍራ፣ ያን ውብ ጋን ማየቱ ልብ ይነካል፡፡ የወይራ ፍሬ እየተገለፈፈ መሰብሰብ ከተጀመረ ሁለት ቀን አለፈው፡፡ በሶስተኛው ቀን ከገበሬዎች ሶስቱ የወይራ ፍሬ ሲለቅሙ ውለው፣ መሰላልና ዘንግ ለማስቀመጥ ወደ ቤት ገብተው ነበር፡፡ በዚህ መሃል አንደኛው በስል ቢላዋ የሄደበት ይመስል አዲሱ ጋን ለሁለት ተሰነጠቀ፡፡ ከመሃከላቸው በፍርሃት የራደው ገበሬ፣ ማንም ሳያይ እብስ እንዲሉ ሀሳብ አቀረበ፡፡ ሌላኛው ግን፣ “አብዳችኋል? ዶን ሎሎ እኛ የሰበርነው ይመስለዋል፡፡ ማንም እንዳይንቀሳቀስ” አለና ወጣ ብሎ፣ “ዶን ሎሎ … ኧረ ዶን ሎሎ” ሲል ተጣራ፡፡
ሎሎ የጋኑን ሥብራት ባየ ጊዜ እንደ እብድ አደረገው፡፡ ገበሬዎቹ ላይ አምባረቀ፡፡ አንደኛውን ጉሮሮውን አንቆ ከግንቡ ጋር አጣበቀውና፣ “… ትከፍሉኛላችሁ” ሲል ጮኸ፡፡ ባርኔጣውን መሬት ላይ ወርውሮ ለሞተ ዘመዱ እንደሚያለቅስ መሬቱን እየደቃ፤ “አዲሱ ጋን!... አራት የወርቅ ማህለቅ የተከፈለበት ገና ያልተሟሸ ጋን”! ሲል ሙሾ አወረደ፡፡
… ማን ሰበረው? … ጋኑ ራሱ ነቅቶ (ተሰንጥቆ) ይሆን? … በምቀኝነት ተነሳስቶ አንዱ ሰብሮት ይሆን? … ሰከን እንዲል ይለምኑት ጀመር፡፡ ጋኑ ሊጠገን ይችላል፡፡ አሰነጣጠቁም መጥፎ የሚባል አይደለም፡፡ ሸክላ ጠጋኝ ባለሙያ እንደ አዲስ ሊጠግነው ይችላል፡፡
በማግስቱም የፕሪሞሶሌ የጥገና ባለሙያ የሆነው ዲማ ሊካሲ በማለዳ ደረሰ፡፡ ዲማ ዘመናት እንዳስቆጠረ የወይራ ዛፍ ሰውነቱ የተጠማዘዘ ሽማግሌ ነው፡፡ የወላለቀች መነፅሩን አፍንጫው ላይ ሰካና ጋኑን በጥንቃቄ ከመረመረ በኋላ፣ “በጥሩ ሁኔታ ሊጠገን ይችላል፡፡” አለ፡፡ ሎሎም፣ “በማጣበቅ ብቻ ይጠገናል ብዬ አላምንም፡፡ መስፋትም አለበት፡፡” ሲል ሐሳቡን ገለፀ፡፡
“መሔዴ ነው” አለ ዲማ ብድግ ብሎ፡፡ … ሎሎም “ወዴት! ወዴት!.. የድሃ ቀብራራ … ይህን የሚያህል ስንጥቅ እንዴት በማጣበቅ ብቻ … የግድ መሰፋት አለበት፡፡ የማጣበቂያና የስፌቱን እከፍልሃለሁ፡፡ ስንት ታስከፍለኛለህ?”
“… በማጣበቂያ ብቻ ከሆነ…”
“ስፌቱ የግድ ነው፡፡ ሥራው ካለቀ በኋላ እንነጋገራለን፡፡ ካንተ ጋር የማጠፋው ጊዜ የለኝም፡፡”
ዲማ ንዴትና ንቀት ወጥሮት ስራውን ጀመረ፡፡ ጋኑን በመሰርሰር በበሳም ቁጥር ንዴቱ እየጨመረ ነበር፡፡ የተሰበረውን የጋን ሽራፊ ለመግጠም አስጠጋው፡፡ የበሳቸውን ቀዳዳዎች እኩል ርቀት ትይዩ መሆናቸውን በዓይኑ ለካ፡፡ በጣቱ የሰባራውን ጋን ጠርዝ ቀብቶ ጨረሰ፡፡ ቁርጥራጭ ሽቦና ጉጠቱን ይዞ ጋኑ ውስጥ ገባ፡፡ ለገበሬውም ቀድሞ እንዳሳየው፣ የጋኑን ስባሪ በውጪ በኩል ገጥሞ እንዲይዝለት አዘዘው፡፡ ስፌቱን ከመጀመሩ በፊትም፣ “ሳብ! የበላህ የጠጣኸውን ያህል ግፋ!” አለው፡፡
ጋኑ ግጥም ብሎ ተጣበቀ፡፡
ሽቦውን እየጠላለፈ በጉጠት ይቆለመም ጀመር፡፡ ስፌቱን ለመጨረስ አንድ ሰዓት ፈጀበት፡፡
በመጨረሻም፣ “እንግዲህ ልውጣ… አግዘኝ” አለ ዲማ፡፡ ጋኑ ሆዱ ሰፊ ቢሆንም አንገቱ ጠባብ ነበር፡፡ ዲማ ሥራውን ሲጀምር ቁጣ ውስጥ ስለነበር ይህን ልብ አላለም፡፡ እናም ከጋኑ ለመውጣት የቻለውን ያህል ቢፍጨረጨርም መውጣት አልቻለም፡፡ ገበሬው ዲማን ከመርዳት ይልቅ በሣቅ ይንከተከት ጀመር፡፡
ዲማ ራሱ በጠገነው ጋን ውስጥ እስረኛ ሆነ፡፡ ለመውጣት ያለው ብቸኛው አማራጭ ጋኑን መስበር ብቻ ነው፡፡ ሁካታው በተደባለቀበት ድባብ ዶን ሎሎ ደረሰ፡፡ ዲማ እየጮኸ “አውጡኝ! ስለእግዚአብሔር እርዱኝ!” ይል ነበር፡፡
ሎሎ የሚያየውን ማመን አቅቶት ክው አለ፡፡ እንዴት ከጋኑ ጋር አብሮ ተሰፋ…? ሎሎ ወደ ጋኑ አፍ ተጠግቶም፣ “እርዱኝ? … እ… ደደብ! ለክተህ አትገባም ነበር? … አንድ እጅህን አውጣ… አንገትህን… ቀስ በል የማይሆን ነገር ነው፡፡” ይለው ጀመር፡፡
ሎሎ ጋኑን በጣቱ አንኳኳው፡፡ ንጥር ድምፅ ልክ እንደ ደወል ያቃጭል ነበር፡፡ ጥገናውስ ድንቅ ነበር፡፡ ዲማ በወጥመድ እንደተያዘ አውሬ በንዴት ሲወራጭ፣ ሎሎ ጋኑን ደገፍ ብሎ፣ “… ወዳጄ ይህንን ጉድ ጠበቃዬ ብቻ ነው የሚፈታው፡፡ በቅሎዬን ጫኑልኝ… መብቴን ለመጠየቅ ግዴታዬን እወጣለሁ፡፡ የአንድ ቀን ክፍያህን ይሄው አምስት ሊሬ …” አለው፡፡
ዲማ ግን “ምንም አልፈልግም፤ ከመውጣት በቀር…” አለ እየተነጫነጨ፡፡
አምስት ሊሬ ጋኑ ውስጥ ወርውሮለት በቅሎው ላይ ወጥቶ ወደ ከተማ ጋለበ፡፡
ጠበቃው ጉዳዩን ሲሰማ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ሎሎ በጠበቃው የማያቋርጥ ሣቅ ተቆጥቶ፣
“ምን የሚያስገለፍጥ ነገር አለ?” ቢለውም መንከትከቱን አላቋረጠም፡፡ በዚህ ጉደኛ ገጠመኝ ደጋግሞ ለማሳወቅ ሲል ጉዳዩን መላልሶ እንዲነግረው መጠየቁን ቀጠለበት፡፡
“… አ… ሂሂ… እፎይ ውስጡ ተሠፋ! ታዲያ ዶን ሎሎ የሚፈልጉት ምንድን ነው? … እዚያው እንዲኖር … አሃሃ … ሂሂ… ጋኑ እንዳይሰበርብዎ እዚያው ልታኖሩት?...”
“ታዲያ ልስበረው - በማን ኪሣራ?”
“ይሄ ሰውን ማሰር ወይም ማገት ይባላል፡፡”
“ማሰር? ማን አሰረው? ራሱን አገተ እንጂ!”
ጠበቃው ሰከን ብሎ፣ “ነገሩ ሁለት መልክ አለው፡፡ አንደኛው ሰው በማሰር እንዳይከሰሱ እስረኛውን መልቀቅ፣ ሌላው ጠጋኙ ስራውን ባለመቻሉ ኪሳራ መጠየቅ…”
“ይህ ከሆነ የጋኑን ዋጋ ይከፍለኛል፡፡”
“መቼም እንደ አዲስ ሊከፍል አይችልም!”
“ለምን?”
“ሰባራ ስለነበር!”
“ሰባራ አይደለም፡፡ ፍፁም አዲስ ሆኖ ተጠግኗል፡፡ አሁን ከተሰበረ ግን ዳግም መጠገን አይችልም፡፡ ይሄ ደግሞ እኔ ከሰርኩ ማለት ነው፤ ገባህ ጌታው ጠበቃ!?”
አሁን ባለበት ሁኔታ የጋኑንም ዋጋ ለማስከፈል የሕግ ድጋፍ እንዳለው ጠበቃው አረጋገጠለት፡፡ “እንዲያውም ጠጋኙ ራሱን ዋጋውን ያስገምቱት” ሲል መከረው፡፡ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ገበሬዎች በጋኑ ዙሪያ ፌሽታ እያደረጉ፣ ውሻው ሳይቀር እየዘለለና እየጮኸ የድግሱ አካል ሆኖ ነበር፡፡ ዲማ በደረሰበት ዱብ ዕዳ የምሬት ሣቅ ይስቃል፡፡ ዶን ሎሎ ወደ ጋኑ ጠጋ ብሎ፣ “ተመችቶሃል…” አለው፡፡
“ከቤቴ የበለጠ ተመችቶኛል” መለሰ ዲማ፡፡
“ለጋኑ አራት የወርቅ ማህለቅ ከፍዬበታለሁ፡፡ አሁን ስንት የሚያወጣ ይመስልሃል?”
“ከእኔው ጭምር ነው?” ዲማ ጠየቀ፡፡
ገበሬዎቹ ከት ብለው ሳቁ፡፡
“ዝም በሉ! … ጋኑ አሁን ባለበት ሁኔታ ስንት ያወጣል? አንተው ገምት”
“… የተገዛበትን ሲሶ ሊያወጣ ይችላል፡፡”
ሎሎም ተረጋግቶ፣ “ቃልህን አክብረህ የገመትከውን ዋጋ ክፈለኝ”
“ምን?” አለ ዲማ ግራ ተጋብቶ
“አንተን ለማወጣት ጋኑን መስበሬ ነው፤ ጠበቃውም እንደመከረኝ በገመትከው ልክ ትከፍላለህ፡፡” “እኔ ልከፍልህ - ትቀልዳለህ? እስክበሰብስ ድረስ እዚሁ እኖራለሁ እንጂ …” አለና ፒፓውን ለኩሶ ጭሱን ሽቅብ ይለቅ ጀመር፡፡ ሎሎ ተደናገረ፡፡
 ዲማ “አልወጣም” እንደሚል እሱም ጠበቃውም አላሰቡም ነበር፡፡ ይሄ ምን መፍትሔ አለው? በቅሎዬን ጫኑልኝ ለማለት ከጀለውና የምሽቱ መግፋት ትዝ ሲለው ተወው፡፡ “ልብ አድርጉልኝ፡፡ ላለመክፈል ብሎ ከጋኑ መውጣት አልፈለገም… በህገወጥ መንገድ ንብረትህ ባልሆነ ቦታ ላይ በመቀመጥ ክስ እመሰርትብሃለሁ፡፡” ዲማ ጭሱን ቡልቅ እያደረገ፤ “ይክሰሱኝ… መክፈል? ለምን ተብሎ! ይቀልዳሉ!”
ዶን ሎሎ፤ ቱግ ብሎ ጋኑን ሊረግጥ እግሩን አነሳና መለስ አደረገው፡፡ ከቁጣው ሰከን ብሎ፣ “ጥፋተኛው እኔ ነኝ፡፡ በረሃብ ፍግም ትላታለህ፡፡ ማን እንደሚረታ እናያለን፡፡” ብሎት ጥሎት ሄደ፡፡ ጠዋት የወረወረለትን አምስት ሊሬ አላስታወሰም፡፡
ዲማ በዚህ እንግዳ በሆነ አጋጣሚ አውድማው ላይ አብረውት ለሚያድሩት ገበሬዎች ግብዣ ቢጤ ለማድረግ ወሰነ፡፡ በአምስቷ ሊሬ ከመሸታ ቤት መጠጥ አስገዛ፡፡ ጨረቃዋ ሌሊቱን ቀን አስመስላው ነበር፡፡ ጫጫታና ሁካታው ዶን ሎሎን ከእንቅልፍ ቀሰቀሰው፡፡ ከበረንዳው ላይ ቁልቁል አማተረ፡፡
 በጨረቃዋ ብርሃን አጋንንትን ያየ መሰለው፡፡ ገበሬዎቹ ሰክረው እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋኑ ዙሪያ እየጨፈሩ ነው፡፡ ዲማም ከጋኑ ውስጥ ጉሮሮው እስኪሰነጠቅ እየጮኸ ይዘፍን ነበር፡፡ ዶን ሎሎ ትዕግስቱ ተሟጦ፣ እንደተቆጣ ፊጋ በሬ ተንደርድሮ ጋኑን ቁልቁል አንከባለለው፡፡ ጥንብዝ ብለው የሰከሩት ገበሬዎች ጋኑ ሲንከባለል በሣቅ ከመሸኘት ውጪ ያደረጉት ነገር አልነበረም፡፡ ጋኑ እየተንከባለለ … እ.. የ.. ተ..ን..ከ..ባ..ለ..ለ ሄዶ ከትልቅ የወይራ ዛፍ ግንድ ጋር ተጋጨ፣ ፍርክስክሱም ወጣ፡፡
እናም ዲማ ረታ፡፡

Read 3257 times