Monday, 20 October 2014 08:27

የተጨፈነና … የተገለጠ ዐይን

Written by  ዮሐንስ ገ/መድህን
Rate this item
(8 votes)

      የታላቄ ታላቅ እህቴ ድሮም ግዴለሽ ነበረች፡፡ አሁንም ያው ነች፡፡ እንዲያውም ሳይብስባት ይቀራል? ከአሥራ አንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደሀገሯ ስትመለስ እስቲ ማንን ገደለ… መጥቻለሁ ብላ ቢያንስ ቢያንስ ስልክ ብትደውል፡፡ ትናንት ደውላ “ከመጣሁ አንድ ሳምንት ሆኖኛል” አትለኝም? አቤት የተናደድኩት መናደድ! “አብረውኝ የመጡ እንግዶች አልለቅ ብለውኝ ነው ይቅርታ” ስትለኝ ነው ቀዝቀዝ ያልኩት፡፡ ዛሬ ደግሞ ለምሳ አንድ ቦታ አብረን እንሄዳለን ብላኝ ይኸው እየጠበቅኋት ነው፤ ያዘዝኩትን ማኪያቶ ፉት እያልኩ፡፡
ብዙም አልቆየች መጣች፤ ተቃቅፈን ተሳሳምን፡፡ ተላቀስን፡፡ የአስራ አንድ ዓመቱን ናፍቆት በቁም ልንወጣው ስላልቻልን ቁጭ ብለን ብዙ አወጋን፡፡ ደርባባ የሴት ወይዘሮ ሆናለች፡፡ ቴክኖሎጂው ተራቆ በፌስ ቡክና በቲዩተር መገናኘት እየተቻለ እንዴት ይህን ያህል ዓመት አስችሎሽ ድምፅሽ ጠፋ ህሊናዬ?” ስል ጠየቅኋት፡፡
“ነገ ተነገ ወዲያ ረጋ ብለን ሁሉንም እንጫወታለን፤ አሁን ተነስና ወደ ተጠራንበት የምሳ ግብዣ እንሂድ”
“አንቺን አጅቤ መሄድ አለብኝ?”
“ኖ  ኖ! አንተም ስለተጠራህ ነው”
“እኔንም አንቺንም የሚያውቅ ሰው?”
“አዎን እያልኩህ”
“ማን ነው?”
“ማን ናት አይሻልም?”
“እሺ ማን ናት?”
“አልነግርህም! እዚያው ስትደርስ…”
በታክሲ ተሳፍረን  ወደ መገናኛ ጉዞ እንደጀመርን አሁንም በድጋሚ ጠየቅኋት፤
“በእናትሽ ህሊና ማን ናት?”
“አይቻልም አልኩህ … ሳይሞቅ ፈሌው!”
ሁለታችንም በሳቅ ፈረስን፡፡ በታክሲው ውስጥ ያለው ተሳፋሪ ሁሉ እስኪገረም ስንስቅ … ስንስቅ የህሊና ስልክ ጥሪ አሰማ፡፡ በሳቅ ድባብ ውስጥ ሆኖ ታወራ ጀመር፡፡ “አዎን … እየመጣን ነው፤ ፍስሃም አብሮኝ አለ … እህ ልክ ነሽ… ከአሁኑ መስመር ማስያዝ… ማፍጠን ነው የሚበጀው …” ስትጨርስ ጥያቄዬን  ጀመርኩ፤ “ዕሌኒ ናት አይደል?”
“አይደለችም!”
እሷ ለመሆኗ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ቅድም የተሳሳቅንበት “ሳይሞቅ ፈሌ” ያለችኝ የኋሊት አስራ ሰባት ዓመታት በትዝታ አስጓዘኝ፡፡ ህሊና ስልኳን ጆሮዋ ላይ ደቅና መነጋገር መጀመሯ ለኔ የትዝታ ጉዞ ተመቸኝ፡፡
የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ፡፡ ለአዲሱ ዓመት ትምህርት መዘጋጀት በጀመርንበት የመስከረም ወር የመጀመሪያ ቀናት በአንደኛው ምሽት አሥራ ሁለት ሰዓት አካባቢ የግቢያችን በር ተንኳኳ፡፡ በረንዳ ላይ ነበርኩና “ማን ነው?” አልኩኝ
“እኔ ነኝ!” የሚጣፍጥ የሴት ድምፅ፡፡
“እኔ ማን?” እያልኩ መልስ ሳልጠብቅ ወደ በሩ ሄድኩና ከፈትኩት፡፡ ጠይም፣ ሰልካካ አፍንጫ ያላት፣ የሳይት መነፅር ያደረገች፣ ሰማያዊ ጅንስ በጥቁር ሹራብ የለበሰች፣ ነጭ ስኒከር የተጫማች፣ በዕድሜዋ ከኔ ከአስር እስከ አስራ አራት ዓመት የምትበልጥ ቆንጅዬ ወጣት ቆማለች፡፡
“እንደምን አመሸህ … ህሊና ትኖራለች?”
መናገር አልቻልኩም፤ በሩን በሰፊው ከፍቼ እንድትገባ መንገድ ለቀቅሁላት፡፡
“እባክህን ልትጠራልኝ ትችላለህ?”
አቤት ትህትና፡፡ ድምጿ እንዴት ይጣፍጣል፡፡ ወደ ቤት አመራሁ፡፡
“ህሊና ህሊና… ሰው ይፈልግሻል!”
“ማን ነው የሚፈልገኝ?” ከክፍሏ እየወጣች ጠየቀችኝ
“ማን እንደሆነች እንጃ… ብቻ ቆንጅዬ ናት”
“ቁንጅናዋን ንገረኝ አልኩህ… ደደብ! ስሟ ማን ነው?”
“አልጠየኳትም!”
“ሂድና ጠይቃት ከርፋፋ፤ አንተ አሁን የኔ ወንድም ነህ?”
“መጠርጠሩስ!”
ልትመታኝ ዕቃ ስትፈልግ በሩጫ ወጣሁ፡፡
“ማን እንደሆነች ስሟን ጠይቀህ ና ብላኝ ነው” አልኳት፤ ከግቢያችን በር ላይ የቆመችውን ቆንጅዬ ወጣት፡፡
“ዕሌኒ … ዕሌኒ ነኝ በላት”
ተመልሼ ለእህቴ ነገርኳት፡፡
ፀጉሯን የምታበጥርበትን ሚዶ አስቀምጣ፣ እንዴት በፍጥነት እንደወጣች ዛሬም ድረስ ፍንትው ብሎ ይታየኛል፡፡ ተያይዘው ገቡ፡፡ መጀመሪያ ኩሽና ድፎ ዳቦ እየጋገረች ወዳለችው እናቴ ዘንድ አምርተው ከእናቴ ጋር አስተዋወቀቻትና፣ ሳሎኑን አልፈው ወደ ህሊና መኝታ ቤት ገቡ፡፡ “ምናለበት ሳሎን ከሶፋው ላይ ቢቀመጡና ይቺን ቆንጅዬ ልጅ ዓይን ዓይኗን እየተመለከትኩ ባመሽ… ወይ ህሊና፤ ይሄ እውን ደግ ስራ ነው?” አልኩኝ በልቤ፡፡ ሲነጋገሩ ለመስማት ጆሮዬን ወደ እህቴ መኝታ ቤት ቀሰርኩ፡፡ የሚሰማ ድምፅ ቢኖርም የጠራ ነገር መስማት አልቻልኩም፡፡
ለረዥም ሰዓት ከመኝታ ቤት አልወጡም፡፡ መሸ፡፡ አባዬም ወንድሞቼም መጡ፡፡ የራት ሰዓት ደረሰ፡፡ እህቴና ዕሌኒ ለእራት ታደሙ፡፡ ራቴን ስበላ ዐይኖቼን ከዕሌኒ ላይ መንቀል አልቻልኩም፡፡ ከእራት በኋላ ብዙም አልቆየችም፤ ለመሄድ ተነሳች፡፡ ህሊናና ታላቅ ወንድሜ ሊሸኟት ተነሱ፡፡ እኔም ብድግ አልኩና “ወንድም ጋሼ፤ አንተ ደክሞሃል እኔ እሸኛታለሁ” አልኩት ድርቅ ብዬ፡፡
“እንዲህ እንደምታስብልኝ አላውቅም ነበር” አለኝ እየሳቀ
ከእህቴ ጋር ተያይዘን ቆንጅዬዋን ልጅ ልንሸኛት ወጣን፡፡ ብዙም አልሄድንም፡፡ ከኛ ቤት የአራት ግቢ ያህል ርቀት እንደተጓዝን የሚቀጥለው ግቢ ስትደርስ ቻው ብላን ገባች፤ እነ አብቹ ቤት፡፡
“የነ አብቹ ዘመድ ናት እንዴ?” አልኳት ህሊናን፤ ወደ ቤት እየተመለስን፡፡
“አይደለችም፤ ተከራይታ ነው”
“እዚህ ልትኖር?”
“አትለፍልፍብኝ … አዲስ የመጣች አስተማሪ ናት፤ አሁን ዝም በልና ሂድ”
“ይቺን የመሰለች ቆንጅዬ የምን አስተማሪ ትሆን? ምን አለበት የኔ አስተማሪ ብትሆን?” እያልኩኝ ቤት ስንደርስ፣ ሁለቱ ወንድሞቼ በኔ ላይ ሙድ ይዘው ሲሳሳቁ ደረስኩ፡፡ እኔን ሲያዩማ ባሰባቸው፡፡
“ራቱንኮ አልበላም … ስማ እንጂ … የልጅቷ ከለር እስኪለቅ እንደዚያ አፍጥጠህ ስታያት አታፍርም?” ታላቅ ወንድሜ
“አንተ ደክሞሃል፤ እኔ እሸኛታለሁ… እ” ሌላኛው ከሣቅ ጋር
ኧረ… ሁሉም ሳቅ በሳቅ፡፡ እንዲህ ከተረባረቡብኝ ሳያስለቅሱኝ እንደማይተውኝ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ … ወደ መኝታዬ አመራሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ያለዚያች ቆንጅዬ ልጅ ማሰብ አቃተኝ፡፡ ገና እንዳየኋት ነው የሆነ ነገር የተሰማኝ፡፡ ጎበዝ! የዓይን ፍቀር የሚባለው ይኼ ነው እንዴ?
ዕሌኒ ህሊናን ፍለጋ ወደ ቤት አዘውትራ ትመጣለች፡፡ አይቼ አልጠግባትም፡፡ ድንገት ከቀረች መነጫነጭ አበዛለሁ፡፡ ወደምትኖርበት ግቢ አመራና ዙሪያውን አንጃብባለሁ፡፡ እንዳልገባ ከአንድ ወር በፊት ይመስለኛል ኳስ ስንጫወት ተጣልተን ስለተደባደብን ከአብቹ ጋር ተኮራርፈናል፡፡ ሁለት ቀን ዕሌኒን ሳላያት ቀረሁ፡፡ ፍጥጥ ብዬ ሄጄ አብቹን ይቅርታ ጠየቅሁት፡፡ መጀመሪያ ላይ ተጀነነብኝ፡፡ የኋላ ኋላ እርቅ ፈጠርን፡፡ ምን ይደረግ አንዳንዴም እጅ መስጠት ጥሩ ነው፡፡  በወሬ ወሬ “እናንተ ጋ የተከራየች ልጅ አለች አይደል?” አልኩት ሳላስነቃ፡፡
“በምን አወቅህ?”
“የህሊና ጓደኛ ናት‘ኮ … ሁሌ እኛ ቤት ትመጣለች” አልኩት
“አሁን ግን የለችም” አለኝ አብቹ
“የት ሄደች?”
“ደሴ የማመጣው ዕቃ አለ ብላ … ግን ለምን ጠየከኝ?”
“አይ ይኸን ሁለት ቀን እኛ ቤት መጥታ ስላላየኋት እንጂ…”
“አስተማሪ ናት”
“ኧረ ባክህ … የት?”
“መለስተኛ መሰለኝ”
“የኛ አስተማሪ ናታ”
“እንደዛ መሰለኝ” አለኝ አብቹ በመሰላቸት፡፡ የአብቹን መሰላቸት አየሁና ሌላ ሌላ ጨዋታ  ጥቂት ከተጫወትን በኋላ ወደ ቤቴ አመራሁ፡፡
ዕሌኒ አምስት ቀን ያህል ከርማ መጣች፡፡ እነዚያ አምስት ቀናት እንዴት ረዣዥምና አታካች እንደነበሩ እኔ ነኝ የማውቀው፡፡ ገና ሳያት ሁለመናዬ እንደ መስከረም ዐደይ አበበ ፈካ፡፡ የኛ ሱቅ ደንበኛ ሆነች፡፡ ዕቃ ልትገዛ ስትመጣ ሁልጊዜ ስለምንገናኝ ተቀራረብን፡፡ የሆነ ቦታ ለመሄድ ስትፈልግ ትጠራኛለች፡፡ አጃቢዋ ሆንኩኝ፡፡ ባገኘኋት ቁጥር ማስቲካ ወይም ከረሜላ እሰጣታለሁ፡፡ አመስግና ትቀበለኛለች፡፡ ፍቅሬን እየገለጥኩ ነበር፡፡ ገብቷት ይሆን?
እንደማይደርስ የለምና ጊዜው ደርሶ ትምህርት ተጀመረ፡፡ እውነትም እንደተባለው የመለስተኛ አስተማሪ ናት፡፡ አንድ ቀን ጧት ወደ ትምህርት ቤት እየሄድኩ ሳለ “ፍስሃ” የሚል ጥሪ ሰማሁና ዘወር አልኩ፡፡ እሌኒ ነበረች፤ የሷ ድምፅ መሆኑን አላጣሁትም፡፡ አብረን ጉዞ ጀመርን፡፡ ከዚያም በኋላ ሁሌ ጠዋት ጠዋት ቲቸር ዕሌኒን ጠብቄ፣ የተለመደውን የከረሜላ ወይም የማስቲካ ስጦታ አበርክቼ አብረን መሄዳችንን ቀጠልን፡፡ በመጀመሪያው ሳምንት ደውል ተደውሎ የሚቀጥለው አስተማሪ እስኪገባ በር በሩን እመለከት ነበር፤ እሷ በሆነች እያልኩ፡፡ ሌላ መምህር… ሌላ መምህር… በቃ ሌላ መምህር ብቻ!
ትምህርት በተጀመረ በሁለተኛው ሳምንት ሰኞ ማለዳ የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ ላይ ቲቸር እሌኒ ወደኛ ክፍል ገባች፡፡ 7B! ስም ከጠራች በኋላ የ7B የክፍል ኃላፊና የሂሳብ መምህራችን መሆኗን ገለፀችልን፡፡ ከዚያም የክፍል ሞኒተር ምረጡ አለችን፡፡
 እንደተለመደው እኔና አብቹ ተመረጥን፡፡ በሚቀጥለው ቀን ትምህርት እንደምንጀምር ነግራን ወጣች፡፡ ማክሰኞ ጠዋት በሶስተኛው ክፍለ ጊዜ ገብታ ማስተማር ጀመረች፡፡ “ዛሬ የምንማረው የሂሳብ ዓይነት ሴት፣ ሳብ ሴትና ፕሮፐር ሳብ ሴት ይሆናል፤ ይኸም ምልክት ሴት ይባላል” ስትል፤
“መምህር ዕሌኒ ሆይ፤ ሴት አንቺ ብቻ ነሽ” እላለሁ በልቤ
“ይኸኛው ደግሞ ሳብ ሴት” ነጩ ሰሌዳ ላይ ምልክቱን አስቀመጠች
“መምህር ዕሌኒ ሆይ፤ የምስባትም ሆነ የምጎትታት ሴት የለኝም፤ አንቺንም ከተፈቀደልኝ እስምሻለሁ እንጂ አልስብሽም”
ሶስተኛው ምን ነበር?” አልኳት አጠገቤ የተቀመጠችውን ቅድስት፡፡
“ፕሮፐር ሳብ ሴት!”
“የኔ ፕሮፐር አንቺ ብቻ ነሽ ቲቸር!” አልኩ በልቤ፡፡
እሷን እሷን እያሰብኩ እኔና ሂሳብ ተለያየን፡፡ ትምህርቱም ተዘነጋ፡፡ ከዚያ በፊት በጉብዝናዬ ነበር የምታውቀው፡፡ ያኔ ግን ተፈታሁ፡፡
እንደምንም ተንጠልጥዬ በደካማ ውጤት አለፍኩ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ቲቸር ዕሌኒ “ፍስሃ ችግርህ ምንድን ነው? ካሁን በፊት ጎበዝ እንደነበርክ ነግረውኛል፡፡ ከኔ የማስተማር ዘዴ ጉድለት ይሆን?” ብላ ጠይቃኝ ነበር፡፡
የሷን ጉብዝና ግን ተማሪው ሁሉ ይመሰክራል፡፡ አሪፍ አስተማሪ መሆኗን፡፡ እኔ ነኝ የተጠለፍኩት፡፡ ለጠየቀችኝ ጥያቄ ምላሽ ሳልሰጣት ተለያየን፡፡ እቤት ገብቼ ግን ከራሴ ጋር ሙግት ገጠምኩ፡፡ “እስከ መቼ?”
ያበጠው ይፈንዳ ብዬ ልነግራት ቆረጥኩ፡፡ ለማንኛውም ይንጋልኝ ብቻ!
በነጋታው ግማሹ የትምህርት ክፍለ ጊዜ እንደተጠናቀቀ፣ በቀጥታ ወደ መምህራን መዝናኛ ክበብ ሄጄ ቲቸር እሌኒን አስጠራኋት፡፡ ወዲያው መጣች፡፡
“ፍስሃ ምነው ችግር አለ?”
“አዎ!”
“ምንድን ነው ያጋጠመህ?”
“ትምህርቴን መከታተል አልቻልኩም”
“ለምን?”
“ፍቅር ይዞኝ”
“እንዴ ፍስሃ?” በድንጋጤ እጇን አፏ ላይ አድርጋ “አይ ማለቴ … በአሁኑ ወቅት አንተ ወደ ትምህርትህ የምታተኩርበት ጊዜ እንጂ ስለ ፍቅር ገና‘ኮ ነህ … ግን እንዴት … ”
“ሁሌ ሳገኛት ከረሜላ ማስቲካ እሰጣታለሁ”
“እንደምትወዳት ነግረሃታል?”
“አልነገርኳትም ብቻ ያው ከረሜላና ማስቲካ ሁሌ ስሰጣት ታውቃለች ብዬ ነው”
“እንዴት ታውቃለች አንተ እወድሻለሁ ብለህ ካልነገርካት፡፡ ግን እኔ የምልህ አሁን ወቅቱ አይደለም … ገና ነህ ቀስ ብለህ ስታድግ ትደርስበታለህ … የምክር አገልግሎት ብታገኝ ጥሩ  ይመስለኛል፤ ለመሆኑ ልጅቷ ማን ናት?”
“አንቺ ነሻ!” አልኳትና ዞር ብዬ ሳልመለከታት በሩጫ የትምህርት ቤቱን ግቢ ጥዬ ወደ ቤቴ ከነፍኩ፡፡
ከሠዓት በኋላ ከቀበሌ 03 ጋር የእግር ኳስ ግጥሚያ ነበረን፡፡ 3 ለ 0 ተሸነፍን፡፡ ድክምክም ብሎኝ ወደ ቤቴ ሄድኩ፡፡ መሽቶ ነበር፡፡ አባዬም እማዬም፣ ወንድሞቼም ጭምር ገና ሲያዩኝ ሳቅ አፈናቸው፡፡ “ሳይሞቅ ፈሌው ግባ እንጂ!” አለችኝ እማዬ፡፡ አልገባሁም፡፡ በረንዳ ላይ ቁጭ አልኩኝ፡፡
 አይ ቲቸር ዕሌኒ! ከመቼው? ግን እሷ ምን ታድርግ? ለህሊና ጓደኛ ብላ ነገረቻት፡፡ የኔው እህት ህሊና ለመላው ቤተሰብ ተናገረች፡፡ እኔ ግን ይበልጥ … እብሰለሰል ጀመር፡፡
“አንተ ሰው ምን ነክቶሃል ደርሶናል‘ኮ!” ከገባሁበት የቅዠት ዓለም ዲያስፖራዋ እህቴ ቀሰቀሰችኝ፡፡
“ምን እያሰብክ ነው?”
“እርግጠኛ ነኝ… የዛሬው የምሳ ግብዣ ዕሌኒ ጋ ነው!” አልኳት ለጥያቄዋ ምላሽ ሳልሰጥ፡፡
“እንዴት ተገለጠልህ እባክህ?”
“ሳይሞቅ ፈሌ ስለሆንኩ!” ተሳሳቅን፡፡
ወደ አንድ ሆቴል ቅጥር ግቢ አመራን፡፡
“ሆቴል ቤት ነው እንዴ የምሳ ግብዣው?!”
“እና … የት መስሎህ ነበር?”
“አይ መኖሪያ ቤት”
“እሷም እንደኔው ዲያስፖራ ናት … ከአንድ ወር በፊት ነው ቀድማኝ የመጣችው … ተመልሳ ሂያጅ ናት፤ ወደ ጀርመን … ምናልባት ልቧ የወደደውን ካገኘች አግብታ ….”
ከፊት ለፊቴ ወደኛ ስታመራ አየኋት፤ “ትክክል ነኝ!” ብዬ ጮህኩ፡፡ ህሊና እያየችኝ ትስቃለች፡፡ ትንሽ ፊቷ ፈካ ብሏል፡፡ ያቺ የሳይት መነፅር… ጅንስ ሱሪዋ… ራሷ ዕሌኒ! ተሳሳምን፤ እንደገና ተቃቀፍን፡፡ ህሊና አላቀቀችን፡፡ መነጋገር የለም መተያየት ብቻ፡፡
ምሳው ጣፋጭ ነበር፡፡ የድሮውን እያነሳን እየተሳሳቅን ተበላ ተጠጣ፡፡ ከምሳ በኋላ ቡና እየጠጣን ጨዋታው ቀጠለ፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ እኔ ምሳ ልጋብዛቸውና ቤቴንም ሊያዩ ቀጠሮ ያዝን፡፡
“በነገራችን ላይ አግብተሃል?” ዕሌኒ ነበረች
“የዚህ ምላሽ ቅዳሜ ነው” አልኩና ተነሳሁ
“በነገራችን ላይ ካላገባህ ዕሌኒ ….” እህቴ ነበረች
“ዕሌኒ ምን … ጨርሽዋ!”
“አግብታህ ይዛህ ለመሄድ ያሰበች ይመስለኛል”
“ለማንኛውም ቅዳሜ ሩቅ አይደለም!”
ወደ ቤቴ በማምራት ላይ ነኝ… የምወዳት ባለቤቴና ሁለት ልጆቼ ይጠብቁኛል፡፡ “ትዳር ስትይዝ አንድ አይንህን ጨፍን፤ አንዱ አይንህም መመልከት ያለበት የትዳር ጓደኛህን ብቻ ነው፡፡” የሚል አባባል አስታወስኩ፡፡
እናም ለትናንት ትዝታዎቼ አይኔን ጨፈንኩ፡፡ የተገለጠው ዐይኔም ውዷ ባለቤቴን ፀደይን ብቻ ነው የሚመለከተው፡፡

Read 3843 times