Saturday, 25 October 2014 10:39

በነፍሴ ውስጥ እኔ

Written by  አምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
Rate this item
(3 votes)


        ዕድሜዬ በአርባዎቹ አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባል ነበርሁ፡፡ ኦጋዴን ኖሬአለሁ፡፡ ሰራዊቱ ውስጥ ምድብ ሥራዬ የነበረው ሾፌርነት ነው፡፡ ሰራዊቱን በየግንባሩ አጓጉዛለሁ፡፡ አንድ ቀን በጉዞ ላይ እያለን፣ ትከሻዬ ላይ ከባድ አረር መታኝና በረጅም ጊዜ ህክምና ተረድቼ በፈጣሪ ዕርዳታ ተረፍሁ፡፡ በዚህም የተነሳ ከሰራዊቱ ጡረታ ተገለልሁ፡፡
ይኸውና ዛሬ በአንድ ሲቪል የመንግስት መሥሪያ ቤት በሾፌርነት ሙያዬ እያገለገልሁ ነው፡፡ ለመስክ ሥራ ከቀያሾችና ከሌሎች የሙያ ሰዎች ጋር በየገጠሩ እዘዋወራለሁ፡፡ በዚህ ሥራ የተነሳ የሀገሬን መልክዓ ምድር በአብዛኛው ተዘዋውሬ አይቻለሁ ብል አልሳሳትም፡፡ በትንሽ ነገር ብው ብዬ የምገነፍል ነኝ፡፡ ወዲያው ደግሞ ከእሳት ላይ እንደ ወረደ የሻይ ጀበና እሆናለሁ፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እሳትና ውሃ ያደርገኛል፡፡ ክፋት የለኝም፡፡ ቂም የሚባል ነገር አላውቅም፡፡ ሚስት አግብቼ ልጅ ወልጃለሁ፡፡ እኔ ማለት ይህ ነኝ፡፡
አንድ ቀን ከመሥሪያ ቤቱ አስተዳደር ቢሮ ተጠራሁ፡፡ የኃላፊውን ቢሮ ከፍቼ ስገባ፣ እንደኔው ተጠርተው የመጡ ሁለት የማውቃቸው ሰዎች ተቀምጠው አየሁ፡፡ አንዱ ቀደም ሲል በሰራዊቱ ውስጥ ያገለገለ የመቶ አለቃ ነበር፡፡ ሌላውን ግን ከዚህ በፊት ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት፣ አሁን ግን በመ/ቤቱ አንድ የሥራ ክፍል ውስጥ በቴክኒሻንነት ይሰራል፡፡
“ቁጭ በል አስታጥቄ!” አለኝ፣ የአስተዳደር ኃላፊው፡፡
“እሺ!” ብዬ ተቀመጥሁ፡፡
ኃላፊው ሶስታችንን በየተራ ትክ ብሎ ተመለከተንና፤ የተጠራነው ለምን ምክንያት እንደሆነ ሊያስረዳን መናገር ጀመረ፡፡
“ይኸውላችሁ! … እናንተም በመገናኛ ብዙኃን እንደምትሰሙት ሁሉ ሀገሪቷ ትልቅ ውጥረት ላይ ትገኛለች፡፡ መንግስት ውጊያ ላይ ነው…” ብሎ ንግግሩን ጀመረ፡፡ መግለጫ ይሁን መመሪያ በውል ያልገባኝን ነገር በሰፊው አወራልንና፤
“… እናንተ ሦስታችሁም ቀደም ብሎ በሰራዊቱ ውስጥ ያገለገላችሁ ስለሆነና በሙያችሁም ልምድ ያላችሁ ስለሆናችሁ፣ ሀገራችሁ ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ጠርታችኋለች” ብሎ፣ ንግግሩን ገታ አደረገና እያፈራረቀ ይመለከተን ገባ፡፡ እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን እንተያያለን፡፡ “እ! እህ!” ብሎ ጉሮሮውን ጠራረገና፣ “እናንተን የመሳሰሉ የውትድርና ልምድ ያላቸው በሀገሪቱ ያሉ ሁሉ እንዲጠሩ ከመንግሥት ጥብቅ መመሪያ ስለደረሰን፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተዘጋጅታችሁ ትዘምታላችሁ” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጠን፡፡
“መዝመቱንስ እንዝመት፡፡ ለሀገር ነው፡፡ ግን አንድ ሳምንት አላጠረም ወይ?”
ስል ጠየቅሁ፡፡
“መመሪያ ነው!” አለ፣ አስተዳዳሪው፡፡
“እኔ ያመኛል” ሲል መቶ አለቃ የነበረው ሰው ተናገረ፡፡
“እዚያው ሄደህ ይረጋገጥልሃል፡፡ ይህ የእኔ ሥራ አይደለም፡፡ ይኸው ነው!...”
ብሎ አሰናበተን፡፡
ሁሉም ነገር በአስቸኳይ ተጠናቅቆ ወደ ምድቤ ሄድኩና ከሰራዊቱ ጋር ተቀላቀልሁ፡፡ ከፍተኛ ፍልሚያ ውስጥ ሰራዊቱን ወደተፈለገው የውጊያ ግንባር ሳጓጉዝ ከረምኩ፡፡ ሙሉ ወታደራዊ ልብስ ለብሻለሁ፡፡ አንድ አውቶማቲክ ክላሽ ጠብመንጃ ተሰጥቶኝ ታጥቄአለሁ፡፡ ውትድርናውን በመሃሉ ለረጅም ጊዜ ያቋረጥሁት ቢሆንም፣ ከእሳቱ አረንቋ ስገባ ግን የለመድሁት ወዲያው ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ለስምንት ወራት ያህል እንደ ሰራሁ ሽንፈት መጣና ሰራዊቱ በየአቅጣጫው ተበታተነ፡፡ የበላይ የለ የበታች፣ ሁሉም በቡድን በቡድን እየሆነ ባሻው መንገድ የሽሽት መልስ ሆነ፡፡ እኔም ከአንደኛው ቡድን ውስጥ ተቀላቅዬ ክላሼን እንደያዝሁ የኋልዮሽ ጉዞዬን ጀመርሁ፡፡
አብዛኞቻችን ደረቅ ራሽን ይዘናል፡፡ የተቻኮለና በድንገተኛ ሁኔታው የተደናገጠው ባዶ እጁን መንገዱን ጀምሯል፡፡ ከጀርባችን የሚያሳድዱን ስላሉ ከዚያ ለማምለጥ ሩጫ ነው፡፡ ቆንጥሩ እየቆነጠረን፣ እንቅፋቱ እያነቆረን፣ ሙቀቱና ፀሐዩ እየጠበሰን፣ ውሃ ጥሙ እያነደደን እንጓዘው ተያያዝን፡፡ ብዙ ርቀት ስለ ተጓዝን ወደ አመሻሹ ላይ ደከመንና አንድ ጎድጓዳ መሬት ስንደርስ በየጥሻው ውስጥ ተበታትነን አረፍን፡፡ በየቦታው ወዳደቅን ማለቱ ነው ሁኔታችንን ሊገልጥ የሚችል፡፡ ስንት ሰው በየቦታው ወድቆ እንደቀረ ምንም ልገምት አልችልም፡፡ አብረን ጉዞ ከጀመርነው ሰዎች መካከል ጥቂቱ እየተመታ ሲወድቅ፣ ሌላው ደግሞ ከዓቅሙ በላይ ሆኖበት በየቦታው እየወደቀ ሲለየን ቡድናችን ሳሳ ይላል፡፡ ጥቂት እንደ ተጓዝን ደግሞ ሌሎች ከዚህም ከዚያም እየመጡ ይቀላቀሉናል፡፡
“ከየት ነው የዘመትከው?” ብሎ ከጎኔ የተጋደመው ወታደር ጠየቀኝ፡፡
“ከአዲስ አበባ” አልሁ፡፡
“እኔ ከባሌ ነው የመጣሁ፡፡ ስሜ ቶልቻ ይባላል”
“እኔ ደግሞ አስታጥቄ እባላለሁ”
“የትኛው ምድብ ነበርክ?” በማለት ጠየቀኝ፡፡ ነገርኩት፡፡ እሱም የነበረበትን ነገረኝ፡፡ በውጊያው ግንባር ጎን ለጎን ነበርን፡፡ ዛሬም በሽሽት ዓለም ውስጥ ሆነን ጨለማ ውስጥ ጎን ለጎን ተኝተናል፡፡
ጥቂት ቀርታኝ የነበረችውን ውሃ ተካፈልንና አለቀች፡፡ ጊዜው እየመሸ ነው፡፡ ከፊሉ ጉዞ እንጀምር ሲል፣ እኔና ጥቂቶች ግን እዚያው ማደሩን መረጥን፡፡ በሃሳባችን ያልተስማማው ጉዞ ጀመረ፡፡ እኔና ጥቂቶች ያለንበት ቦታ ከጥቃት ሊከልለን ይችላል ብለን ስላመንን ከቆንጥር መካከል በመግባት ራሳችንን ሰውረን ቦታችንን አመቻቸን፡፡ ድቅድቅ ጨለማ ዋጠን፡፡ ኮሽ የሚል ነገር የለም፡፡ ሁሉም ነገር ድፍን ብሎ ፀጥ ረጭ ብሏል፡፡ የአውሬ ድምፅ እንኳ አይሰማንም፡፡ ለነገሩማ የጦርነት ቀጠና ውስጥ አራዊት እንዴት ሊኖሩ ይችላሉ? እነሱም ይሸሻሉ፡፡ እኛም እንሸሻለን፡፡ የሽሽት ዓለም!
እኔ አይኔ ፈጥጧል፡፡ ከመካከላችንም እንቅልፍ የጣለው ሰው ነበር ለማለት አልደፍርም፡፡ ወይ እንቅልፍ! … “እዬዬ ሲዳላ ነው!” አይደል የሚባል!? በመካከሉ ድም! ድም! የሚል የሰዎች ኮቴ ሰማን፡፡ መሳሪያዬን ጠበቅ አድርጌ ያዝኩና ጆሮዬን ወደ ላይ አቆምሁ፡፡ እኛ ተሸሽገንበት ካለው ጉድባ በላይ የሰዎቹ ኮቴ እየቀረበን መጣ፡፡ ጣቴን ከምላጩ ላይ አድርጌ ተዘጋጀሁ፡፡ የመጨረሻችን መጨረሻ እንደቀረበ አመንሁ፡፡ ምራቄን ዋጥ አደረግሁ፡፡ ከጎኔ ያለው ቶልቻም ልክ እንደኔው ተዘጋጅቷል፡፡ ከመካከላችን አንድም ሰው ድምፅ አያሰማም፡፡ ሁላችንም አድፍጠናል ማለት ነው፡፡ ሁለት የማይታረቅ አመለካከት ያለን የአንድ ሀገር ልጆች የፖለቲካ ቁማር በሚቆምሩ የበላዮቻችን ትዕዛዝ ስንበላላ ይኸው ስንት ዘመን አለፈ፡፡ አሁንም በዚህ ድቅድቅ ጨለማ እንደ ክፉ አውሬ ልንበላቸው፣ እነሱም ሊበሉን እየተቃረብን ነው፡፡ እነሱ እየተሸሸጉ ስናባርራቸው የነበር ዛሬ እኛ እየተደበቅን፣ እነሱ ደግሞ በፊናቸው እያባረሩን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የድብብቆሽ ጨዋታ መሰለኝ፡፡ የመድረክ ተውኔትም እየመሰለ ይታየኛል፡፡
የአንዲት ጥይት ድምፅ ተሰማ፡፡ ወዲያው ሁለት … ሶስት… ድብልቅልቁ ወጣ፡፡ የተኩሱ ድምፅ ከወዴት እንደሆነ መለየት እንኳ ተሳነን፡፡ እኔም ሰው ያየሁ በመሰለኝ አቅጣጫ ሁሉ እተኩሳለሁ፡፡ ቦታ እየቀያየርኩ መሳሪያዬን አንጣጣሁ፡፡ ከላዬ ላይ አንድ ግዙፍ ነገር ዘፍ አለብኝ፡፡ ቅርፁ የሰው ነው፡፡ እግሬንም እጄንም አስተባብሬ የወደቀብኝን ገፍትሬ ከላዬ አስወገድሁ፡፡ ዝርግፍ ብሎ ሲወድቅ፣ “ወይኔ ቶልቻ… ኢጆሌ ባሌ!” ብሎ ፀጥ አለ፡፡ አመሻሹ ላይ ስናወራ የነበረው የባሌ ልጅ ነበር፡፡ ጥቂት እንደ ማዘን ብዬ ወደራሴ ሁኔታ ተመለስሁ፡፡ ማን ማንን መትቶ እንደሚጥል አይታወቅም፡፡ የምተኩሰው ጥይት ሰው ይምታ ወይ ደግሞ ቅጠልና ድንጋዩን፣ አሁንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ጥይቴም እንዳያልቅ በቁጠባ ነው የምተኩሰው፡፡ ስንፏቀቅ ብዙ ሄጃለሁ፡፡ በመካከሉ የጥይቱ ድምፅ እየሳሳ እየሳሳ እየሳሳ መጣና አካባቢው ፀጥ አለ፡፡ ጥቂት ቆይቶም የንጋት ብርሃን ይታየኝ ጀመረ፡፡ አጠገቤ ሰው የለም፡፡ ዙሪያ ገባውን ማየት ጀመርሁ፡፡ በርቀት በደረታቸው ተኝተው ያሸመቁ ሰዎች ስለታዩኝ መሳሪያዬን ወደ እነርሱ አነጣጠርሁ፡፡ የለበስኩት ልብስ በቆንጥሩና በድንጋዬ ተዘነጣጥሎ በግማሽ ተራቁቻለሁ፡፡ እዚህም እዚያም የወደቀ አስከሬን ይታየኛል፡፡ ሰውነቴን ደባበስሁ፡፡ ክንዶቼና ጉልበቴ ላይ ቆስዬ ደም ይፈስሰኛል፡፡ ከተዘነጣጠለው ልብሴ ላይ እየቀደድሁ ቁስሌን አሰርሁ፡፡
“አስታጥቄ!” ሲል አንድ ሰው ጠራኝ፡፡
ከእነዚያ አሸምቀው ከነበሩ ወታደሮች መካከል ነበር ድምፁ የመጣው፡፡ በደንብ ስላልነጋ በርቀት ልለየው አልቻልኩም፡፡ እሱ እንዴት ሊለየኝ እንደቻለ እኔ እንጃ!
“ማነህ አንተ? ራስህን ግለፅ፡፡ ከወገን ነህ?” አልሁ፣ በጥርጣሬ መንፈስ፡፡
“እሱባለው ነኝ” ብሎ፣ ልዩ መጠሪያችን የነበረውን ልዩ የኮድ ስም ተናገረ፡፡ ሌላም አከለበት፡፡ ሁላችንም ካደፈጥንበት ተነሳንና ቅልቅል ሆነ፡፡ የሞቱትን ሰዎች ብንመለከት እንደ እኛው ይሸሹ የነበሩ ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ከመጡብን ሰዎች መካከልም የተረፉ ነበሩና በደንብ ነግቶ ከተያየን በኋላ መጥፎ ስሜት ተሰማኝ፡፡ የተላለቅነው እርስ በርስ ነበር፡፡ እጅግ በጣም አዘንሁ፡፡ በወቅቱ ሁላችንም ጭንቅ ላይ ስለነበርን፣ ምንም ማመዛዘን አልቻልንም፡፡ ሞት ከዚህ ከዚያም በየመልኩ ሆነ፡፡
ምክር ያዝንና አብዛኛው የተስማማንበትን የጉዞ ዕቅድ ነደፍን፡፡ ሌሊት ወደ እኛ ከመጡት ወታደሮች መካከል አንደኛው፣ “መሳሪያችንን ጥለን እንደ ማንኛውም ሲቪል ሰው ብንጓዝ ጥሩ ይመስለኛል” የሚል ሃሳብ በማንሳቱ፣ በዚሁ ተስማምተን ከጥቂት በቀር ብዘዎቻችን ክላሾቻችን በየቆንጥሩ ውስጥ ወረወርን፡፡ ወገቤ ላይ አስሬ የያዝኳትን ትንሽ የጨርቅ ከረጢት ከፍቼ፣ አንድ የጨርቅ ሱሪና ሸሚዝ አውጥቼ ለበስሁ፡፡ ጫማዬን አውልቄ የከተማ ጫማ አጠለቅሁ፡፡ ሁላችንም ራሳችንን ለመለዋወጥ ሞከርን፡፡ ሁለት ሁለት፣ ሶስት ሶስት እየሆንን ዕድላችን በፈቀደችልን በተለያየ አቅጣጫ ጉዞ ወደፊት ሆነ፡፡ ከእኔ ጋር የሚጓዙት ወታደሮች ሶስት ሲሆኑ እኔን ጨምሮ አራት ነበርን ማለት ነው፡፡ ይዤው የነበረ ደረቅ ኮቾሮ እያለቀ ነው፡፡ ውሃም የለንም፡፡ ከንፈሮቻችን ደርቀዋል፡፡ የክንዶቼና የጉልበቴ ቁስል ይጠዘጥዘኛል፡፡ ቀን በየጥሻው እየተሽሎከሎክን፣ ለዓይን ያዝ ሲያሰርግ ደግሞ ወደ ገላጣው ብቅ እንላለን፡፡ ረሃቡና ውሃ ጥሙ ፈታን እንጂ ብዙ ርቀት ሄድን፡፡ በጉዟችን ላይ አልፎ አልፎ ሰዎች ሲገጥሙን ፈጠን ብለን ሰላምታ እንሰጥና ራመድ ራመድ እንላለን፡፡
አንድ ቤተክርስቲያን በርቀት ስላየን ወደ እዚያው በእርምጃ ገሰገስን፡፡ ስለ ሰጋን ወደ ኋላ እየተገላመጥን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ ቦታው እግዚአብሔርን ማምለኪያ ቅዱስ ስፍራ ነውና ክፉ ነገር እንደማይነካን ተማምነናል፡፡ በዚያውም ምልጃ እናቀርባለን፡፡ አንዲት መነኩሲት ስላየን ወደ እሳቸው አመራን፡፡ ሁኔታችንን በመጠኑ ስንነግራቸው፣ “አፈር ይብላኝ! ወይኔ ወገኖቼ!...” ብለው እንድንከተላቸው ነገሩን፡፡ የባቄላ ንፍሮ ሰጥተውን በችኮላ በልተን በላዩ በማውራ (ከቅል የተሰራ ክብ መጠጫ) ውሃ እስኪበቃን ቸለስንበት፡፡ አንደበታችን ተፈታልን፡፡ ዓይኖቻችን ተገለጡልን፡፡ ምንም እንደማያሰጋን መነኩሲቷ ነግረውን ለማደሪያችን አንዲት ደሳሳ ጎጆ አሳዩን፡፡ ወዲያው፣ “መጣሁ! ቶሎ እመለሳለሁ…” ብለው ሄዱ፡፤ ጆሮዬ ቆመ፡፡ የዘመኑ ነገር አይታወቅምና ሥጋት ነገር አደረብኝ፡፡ መነኩሲቷ ተመልሰው መጡና፡-
“ይኸውላችሁ… ይኼ ልጅ ከትናንት ወዲያ እየተጎተተ መጥቶ ከቤተክርስቲያኑ ደጃፍ ሲደርስ ወደቀ፡፡ ምዕመናን ተሯሩጠው ቢሄዱ እጅግ ጠውልጎና ተንገላትቶ ደክሞ አገኙት…” ብለው፣ በእጃቸው የያዙትን የጧፍ መብራት ወደ አናታቸው ከፍ አደረጉና፡-
“… አፈር ይብላኝ፡፡ ምንም ሳንረዳው እዚያው ከወደቀበት ነፍሱ ወጣች፡፡ ትናንት ቀበርነው፡፡ ይኸውላችሁ ከኪሱ ያገኘነው ፎቶ…” ብለው እንድናየው አቀበሉን፡፡ ፎቶግራፉን ሳይ ክው አልሁ፡፡ ግን ወዲያው ራሴን ተቆጣጠርኩ፡፡ የመስሪያ ቤታችን አስተዳዳሪ ለዘመቻ መጠራታችንን የነገረን ጊዜ ቢሮው ውስጥ ከነበርነው ሶስት ሰዎች መካከል ቀደም ሲል ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎ የነበረው የመ/ቤቱ ባልደረባዬ ነው፡፡ እጅግ አዘንሁ፡፡
መሬቱ በደንብ ሳይነጋ ካደርንበት ደብር ተነስተን ጥቂት ራቅ እንዳልን ከወደ ጀርባችን የጥይት እሩምታ ይወርድብን ጀመር፡፡ ወደ ፊቴ ዘልዬ በደረቴ ከመሬት ላይ ተሰፋሁ፡፡ እንደ እባብ እየተሳብሁ ከአንዲት የለመለመች ቁጥቋጦ ውስጥ ገብቼ ተወሸቅሁ፡፡ በርቀት የሰዎች ድምፅ ይሰማኛል፡፡ አሁን ሰማዩ ወለል ስላለ በቅጠሎች ውስጥ አሾልቄ አካባቢውን ተመለከትሁ፡፡ ማንም የለም፡፡ በዝግታ ከቁጥቋጦው ውስጥ ወጣሁና ግራ ቀኙን ከመረመርሁ በኋላ ቁልቁል ወደ ተዳፋቱ ሮጥሁ፡፡ አብረውኝ የነበሩት የጉዞ ጓደኞቼ ይሙቱ ወይ ደግሞ በተለያየ አቅጣጫ ነፍሴ አውጪኝ ብለው እንደሁ የማውቀው ምንም ነገር የለም፡፡ ከያዝኩት የባቄላ ንፍሮ ቃም ቃም አደረግሁና ውሃ ተጎነጨሁ፡፡ ሩጫዬን ቀጥያለሁ፡፡ የጫማዬ ሶል ተገንጥሎ በመውደቁ የውስጥ እግሬ ደም አዝሎ ነፍርቋል፡፡ አማራጭ የለምና ጥርሴን ነክሼ እረግጥበታለሁ፡፡ ዕውር ድንብሬን ነፍሴ በመራችኝ አቅጣጫ ስጓዝ ድንገት መኪና መንገድ ላይ ወጣሁ፡፡
መንገዱ ወዴት ነው የሚወስድ? የት ነው ያለሁት? የሀገሪቱን አብዛኛውን ክፍል በሥራ ምክንያት የማውቀው ቢሆንም፣ እዚህ ቦታ ግን መጥቼ አላውቅም፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ተጋባሁ፡፡ በመካከሉ የመኪና ድምፅ ስለሰማሁ ወደ ጫካ ገባሁና በርቀት መመልከት ጀመርሁ፡፡ መኪናው እየቀረበ ሲመጣ ጭነት የጫነ አይሱዙ ፒካፕ መኪና መሆኑን ለየሁ፡፡ ከጫካው ወጥቼ መኪናዋ ስትቀርበኝ እጄን ለእርዳታ አወናጨፍሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ቆሜ መራመድ ስለማልችል የሚመጣውን ሁሉ በፀጋ ለመቀበል ተዘጋጀሁ፡፡
“ወንድሜ … ምን ልርዳህ?” አለ ሰውየው፣ አጠገቤ ሲደርስ መኪናዋን አቁሞ፡፡
“ዘመድ ጥየቃ መጥቼ ሳለሁ ሀገር በመረበሹ ከዘመዶቼ ተለይቼ ስባዝን ከዚህ አውራ መንገድ ላይ ደረስሁ”
“ዘመዶችህ የት ናቸው?”
“ስንሸሽ ጫካ ውስጥ ተጠፋፋን”
“እሺ አሁን ምን ልርዳህ?” አለ ሾፌሩ፡፡
“ከመንገዱ ብዛት እግሬ አላስረግጥ ስላለኝ ብትረዳኝ ብዬ ነው”
“ወዴት ነው መሄድ የምትፈልገው? እኔ አዲስ አበባ ነው የምሄድ”
“እኔም እዚያው ነኝ” አልሁ፣ ፈጠን ብዬ፡፡
“ግማሽ መንገድ እረዳሃለሁ፡፡ በየቦታው ፍተሻ ስላለ አብረን መዝለቅ አንችልም
ግባ!” አለኝና ከጋቢናው ገብቼ ከጎኑ ተቀመጥሁ፡፡
በግምት ለሁለት ሰዓት ያህል እንደተጓዝን ለተፈጥሮ ጉዳይ መኪናዋን አቆመና ወደ ጫካ ጎራ አለ፡፡ በዚህች ቅጽበት አንድ ነገር በሃሳቤ ውልብ አለብኝ፡፡ ከመኪናው ወጣሁና ሽንት የሚሸና በመምሰል እስኪመለስ ጠበቅሁት፡፡ ተመልሶ አጠገቤ ሲደርስ ከጆሮው ሥር ጠቅ እያደረግሁት፡፡ እራሱን እንዲስት እንጂ ከበድ ያለ አደጋ እንዳይደርስበት የመታሁት በጥንቃቄ ነው፡፡ ተዝለፍልፎ ሊወድቅ ሲል መሬቱ እንዳይጎዳው ደጋገፍኩትና በጀርባው አጋደምኩት፡፡ ፈጠን ብዬ ኪሱ ገባሁና የመኪናዋን ቁልፍ አወጣሁ፡፡ መታወቂያው ላይ ያለውን ፎቶውን ገንጥዬ ደብተሩን ወሰድሁ፡፡ ጥቂት ብሮች ብቻ አስቀርቼለት የቀረውን ያዝሁ፡፡ ጫማውን አውልቄ አደረግሁ፡፡ ከዚያም መኪናዋን አስነስቼ በረርሁ፡፡
የሰው ልጅ ምን ያህል ራስ ወዳድ እንደሆነ የገባኝ አሁን ነው፡፡ ራሴን ጠላሁት፡፡ “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” ሆነ ሥራዬ፡፡ ያም ሆነ ይህ እሱን በእኔ ቦታ ትቼው፣ እኔ የእሱን መኪና ቀምቼ እየበረርሁ ነው፡፡ ሁለት የቆንጥር እሾህ ቆርጬ በቀጭኑ በኩል ቁመቱን በጣም አሳጠርኩና እንዳይታይ አድርጌ ፎቶግራፌን ከደብተሩ ጋር በጥንቃቄ ሰፋሁት፡፡ በዚህ ግርግር ወቅት ብዙ ትኩረት የሚያደርግ ሰው እንደሌለ ገምቻለሁ፡፡ አንዲት አነስተኛ ከተማ እንደ ደረስሁ ሱሪና ሸሚዝ ገዝቼ ለበስሁ፡፡ መታወቂያዬን ለማየት በእጄ እንድሰጠው የጠየቀኝ ሰው ስላልነበር በርቀት እያሳየሁ፣ ምንም እንከን ሳይገጥመኝ በሁለተኛው ቀን አዲስ አበባ መግቢያ ላይ ካለው የፍተሻ ኬላ አካባቢ ደረስሁ፡፡ መኪናዋን ሥራሽ ያውጣሽ ብያት ከመንገድ ገባ አድርጌ አቆምኳትና መንገድ አሳብሬ በእግሬ ወደ ከተማዋ ገባሁ፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ ጥቂት ሰዎች ውር ውር ቢሉባትም በአብዛኛው ፀጥ ብላለች፡፡ በየመንገዱ እያስቆሙ ይፈትሻሉ፡፡ ዋና ዋና ጎዳናውን ትቼ መንደር ለመንደር እየሄድሁ፣ አመሻሽ ላይ ሰፈሬ ደረስሁ፡፡ አካባቢው ረጭ ብሏል፡፡ በሬን አንኳኳሁ፡፡ ቆየት ብሎ በሩ ተከፈተ፡፡ ትልቅ እህቴ ነበረች፡፡ ስታየኝ በእልልታ አካባቢውን ልታቀልጠው ስትል አፏን በመዳፌ ከደንኩት፡፡ በሩን ዘጋሁና አረጋጋኋት፡፡ ልጄ ከጓዳ እየሮጠች መጣችና ተጠመጠመችብኝ፡፡
“ባለቤቴ የት ሄዳ ነው?” ብዬ ጠየቅሁ፡፡
“ተባራሪ ጥይት ገደላት” አለችኝ እህቴ፣ ዓይኖቿ እንባ አዝለው፡፡
እኔ ከዚያ መዓት በተዓምር ተርፌ ብመጣ ባለቤቴ ሞታ በመድረሴ ምነው እዚያው ሞቼ በቀረሁ አሰኘኝ፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ይህ ሁሉ ሥቃይ የደረሰብኝ ምን ያልከፈልከሉት ዕዳ ቢኖር ነው? ሀገሬንስ ምን በድያታለሁ? ሁለት ጭንቅላቶች በአመለካከት ልዩነት ችግር ሲፈጥሩ እኔ ገፈት ቀማሽ መሆን አለብኝ እንዴ? ለማንኛውም ግን እኔ …
እኔ እኮ አሁን የለሁም፡ ከዘመቻ መልስ ጥቂት ከራርሜ ሞትሁ፡፡ እሰራበት ከነበረው መሥሪያ ቤት ላለ ወዳጄ በአፀደ ሥጋ በነበርሁ ጊዜ የነገርኩትን፣ ይኸው ዛሬ ነፍሴ ደግማ በጆሮው እየነገረችው ነው፡፡ እሷ እየነገረችው እሱ ፃፈላችሁ፡፡ ነፍሴም አውልቃ የጣለችውን በድን ቁልቁል እያየች፣ ስለ እኔ ማውራቱን አልተወችም፡፡

Read 4174 times