Saturday, 08 November 2014 11:36

ሌሊት እና ሄዋን

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(8 votes)

መንደርደሪያ
ሶቅራጥስ እንደሚከተለው ይላል፡ ‹‹ፍቅር መሀል ቤተኛ መንገድ ነው፡፡ የፍቅር ሃይል የሚያገለግለው ሰውን ወደ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔርን ደግሞ ወደ ሰው ለማድረስ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ፀሎትና መስዋእት ወደ ሰማይ የሰማይን ምላሽ ለሰው ፀሎትና መስዋዕት ወደ ምድር መልሶ የሚተሳሰረው  በፍቅር መንገድ ነው፡፡ በሁለቱ ዓለሞች መሀል ያለው ክፍተት በፍቅር ነው ምሉዕ ሆኖ የሚገጥመው፡፡››
ማለትም ለካ… ፍቅር እግዚአብሔር አይደለም፡፡ ሰውም ፍቅርን በራሱ ሊሆን አይችልም፡፡ ምናልባት ክርስቶስ በሰው እና በእግዚአብሔር መሀል ቆሞ ‹ፍጹም አምላክ እና ፍፁም ሰው›› መሆኑን ስላስመሰከረ፣ እግዚአብሔርን ሆኖ እራሱን እንደ ሰው መስዋዕት ስላቀረበ ክርስቶስ… ፍቅር ነው፡፡
በተረፈ ሶቅራጥስ እንዳለው፤ ፍቅር ያለ ሰውና ያለ እግዚአብሔር ዝም ብሎ መንገድ ነው፡፡ ሞገድ ነው፡፡ ሞገዱ… ሬዲዮው (ሰው) እና ማሰራጫ ጣቢያው (እግዚአብሔር) በሌሉበት.. ለራሱ/እንደራሱ ጉድለት ነው፡፡ መነሻና መድረሻ የሌለው መንገድ፣ መነሻና መድረሻውን እስኪያገኝ ጉድለት ነው፡፡
እግዚአብሔር ያላፋቀራቸው አዳምና ሄዋን ሊፋቀሩ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ያላቆራኛቸው ገፀ ባህርይና ደራሲ… በልብወለድ ፈጠራም ሊስማሙ አይችሉም፡፡
እሸቱ መጀመሪያ ሰው ነበር ወይንስ አዳም? ሁልጊዜ እርግጠኛ መልስ የማያገኝለት ነው፡፡ መጠየቁን ግን አያቋርጥም፡፡ ወይንስ መጀመሪያ ሰውም፣ አዳምም ከመሆኑ በፊት ደራሲ ነበረ… መልስ የለውም፡፡ሁሉንም በአንድ ላይ መሆን ካልቻለ ሙሉነትን የሚጨብጥ አይመስለውም፡፡ መጨበጥ ብቻ ሳይሆን ሙሉነትን የሚረግጥ፡፡ መርገጥና መጨበጥም ለሙሉነት አይመጥኑም፡፡ እሱና በምንም መልኩ እንዳይለያዩ ይመኛል፡፡ ምኞት ፍላጎት ነው፡፡ ፍላጎትን ከሚፈለገው ነገር ጋር የሚያገጣጥመው ፍቅር ነው፡፡
አዳም ሙሉ ለመሆን ሄዋንን አገባ፡፡ አዳም ኢትዮጵያዊ ለመሆን በአባቱ የወጣለትን እሸቱ የሚል መጠሪየ ተቀበለ፡፡ ሄዋንም አይዳ የሚለውን መጠሪያዋን ከተቀበለች ብዙ ዘመን አሳልፋች፡፡ አይዳ እና እሸቱ ሶስት ጉልቻ መሰረቱ፡፡ ሰው ሆኑ፡፡
አዳምም ሄዋንም ሰው ለመሆን መፋቀራቸውን እንጂ መፋቀራቸው በፈጣሪያቸው መፈቀሩን አላረጋገጡም፡፡ እነሱ ከመረጡት ምርጫ ጋር የእግዚአብሔር ምርጫ መግጠውን በጋብቻቸው ወቅት አይጠራጠሩም፡፡
አዳም ደራሲ መሆኑን ያምን ነበር፡፡ አምኖም ድርሰት ፅፏል፡፡ ድርሰቱን ያነበቡ የሀገሩ ሰዎች ደራሲነቱን አፅድቀውለታል፡፡ ሰው ስለ እሱ ደራሲነት የሚያወራውን እግዚአብሔር ሰምቶ ምን እንዳለ አይታወቅም፡፡ ሰዎች በደራሲው ላይ ያላቸው ፍቅርና ደራሲው በድርሰት ፍላጎቱ መሀል ያለው ፍቅር ምድራዊ ብቻ ሊሆን እንደሚችል ማንም አልገመተም፡፡ የምድርን ፍላጎት ከሰማይ ይሁንታ ጋር የሚያገናኘው መስዋዕትነት ነው፡፡ ፍቅሮች በድርሰትም ሆነ በፆታ እደጉ እንዲባሉ መስዋዕትነት መክፈል አለባቸው፡፡ ግን እደጉ ሲባሉ ሁለቱም ፍላጎቶች በአንድ ላይ ላይሆን ይችላል፡፡ እግዜር እንትፍ ሲል መስዋዕቱን ተመልክቶ ነው፡፡ አዳም ለጥበቡ የከፈለውን መስዋዕትነት.. አዳም ለትዳሩ ከከፈለው ጋር አነፃፅሮ የእንትፍታ ምራቁ ወደ አንድ ወይንም ወደ ሌላኛው ሊያደላ ይችላል፡፡ ስኬት በፍቅር መንገድ የተላከ የመስዋዕትነት ውጤት ነው፡፡
አዳም ሙሉ ለመሆን ሄዋንን አገባ፡፡ ግን እንዴ እንደተጋቡ መለስ ብለን እንመለከት፡፡ ሄዋን አንባቢ ናት፤ አዳም ደግሞ ደራሲ፡፡ አዳም የመጀመሪያ ድርሰት የሆነውን መፅሐፉን ሲፅፍ ምኞት ላይ ነበረ፡፡ ምኞቱ በሁለት ጎን የተሳለ ቢለዋ ነው፡፡ አንድ ደራሲ ለመሆን ሁለት ሄዋንን ማግኘት፡፡
ሄዋንን ለማግኘት ስላደረገው ፍለጋ በድርሰት መልክ ፃፈው፡፡ ድርሰቱ ላይ የሰፈረችው ምኞቱ ነበረች፡፡ ስጋ እና ደም አይደለችም፡፡ ግን ስጋና ደም የሆኑ ሁሉ ድርሰቱን አንብበው ተነኩ፡፡ ምኞቱ በስጋና ደማቸው ውስጥ ሰርፆ እውነታቸው ሆነ፡፡
አዳም ሄዋንን አገኛት፡፡ ያገኛት ከራሱ ውስጥ ነው፡፡ ድርሰቱን ፃፈ፡፡ የፃፈውን አግኝታ አነበበች፡፡ እውነቱ ወደ እርሡ ጠራት፡፡ ስጋና ደሙን ሳይሆን ምኞቱን አፍቅራ ቀረበችው፡፡ ተገናኙ፡፡ አንድ ሆኑ፡፡ ከራሱ ቁራጭ ተወስዳ የተሰራች ነች፡፡ ተጋቡ፡፡ ሰው ሆኑ፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ፡፡ ኦጵላስ!
በተለያየ አቅጣጫ የሚበር ወፍ እንዴት በአንድ አቅጣጫ በሚበር ድንጋይ እንደተመታ የጠየቀ አልነበረም፡፡
 ፍቅረኞቹ ለጥያቄ ጊዜ አልነበራቸውም፡፡
የሚፈላለግ ነገር ብቻ ነው የሚገናኘው፡፡ ግና ደግሞ የሚፈላለግ ነገር ብቻም ነው የሚጋጨው፡፡
አይዳ ከጋብቻቸው ብዙ ቆይታ በኋላ አንድ አባዜ አመጣች፡፡ ብቸኛ ፍቅር፣ ተፈቃሪ እና አፍቃሪ የመሆን አባዜ፡፡ እሸቱ በስጋ ከእርሷ  ጋር ሆኖ በመንፈሱ ግን ድርሰቱን የሚያፈቅር መሰላት፡፡
በመጀመሪያ መፅሐፉ ላይ የሰፈረችውን የድርሰት ገፀ ባህርይ ከእርሷ የበለጠ እንደሚወዳት ለራሷ አመነች፡፡ ተፈልጋ ከተገኘችው ከእሷ ይልቅ፣ ፍለጋው የነበረችውን ሴት ይመኛል አለች፡፡  ‹‹ከትዳርህ ወይስ ከድርሰትህ?›› ብላ ሁለት ፍቅሮች መሀል ቆመች፡፡
ለእርሷ እምነቷ እውነት የሆነ መስሏት እንጂ እውነቱ እርሷ እንዳሰበችው አይደለም፡፡ አንድ እውነትን ወደ ሁለት እምነት የሚከፍል ፍቅር፣ በሰዎች መሀል ተበጥሶ የቀረ የእግዚአብሔር ይሁንታ ያልተጨመረበት ብቻ ሲሆን ነው፡፡
ለአይዳ.. ለሚስቱ ሲል ድርሰትን እርግፍ አድርጎታል፡፡ ከእንግዲህ ፍለጋው እጁ ገብታለች፡፡ ‹‹እግዚአብሔር እጄ ያስገባውን ይባርክልኝ” አለ፡፡ አይዳን እጁ ለማስገባት የበኩር ድርሰቱ የሆነውን መፅሐፍ እንደ መስዋዕት ከፍሏልና፡፡
አይዳ ግን በእሸቱ ጉያ ተወሽቃም አዳም የራቃት ይመስላታል፡፡ ለእሷ ወደ እርሱ መምጣት ምክንያት የሆነው መፅሐፍ ላይ የምኞቱ ሴት ታትማ መነበብ እስከቀጠለች ድረስ እሱ የእሷ እንዳልሆነ አረጋግጣለች፡፡ ግጭቱ ይኼ ነው፡፡
ግጭት በሚፈላለጉ መሀል እንጂ… ዝንተ አለም ተቃራኒ ለመሆን በተፈጠሩ ነገሮች ዘንድ አይከሰትም፡፡ ሄዋን ከአዳም የሚቀርብላት ፍቅርን በድርሰቱ ላይ ከሰፈረው የፍላጎቱ  አፍቃሪ ገፀ ባህርይ ጋር ስታነፃፅረው ተጨባጩ ከህልማዊው ያንስባታል፡፡
ግጭቱ ተከሰተ፡፡ መቋጫ ሊበጅለት አልቻለም፡፡ በኑሮአቸውም ሆነ እርስ በራስ ባላቸው ስሜት ምንም ጉድለት የለም፡፡ ጉድለቱ በሁለቱ መሀል ሳይሆን በሰማይና በሁለቱ መሀል መሆኑ አልተገለፀላቸውም፡፡
እሸቱ ጉዳዩን በፅሞና መረመረው፡፡ በድርሰት ቋንቋ ግን በአንደበቱ ሚስቱን ከጉያው አውጥቶ ፊት ለፊቱ አስቀምጦአት ፍቅሩን ገለፀላት፡፡
መፅሐፉ ከገበያ ላይ እንዲጠፋ የተቻለውን እንደሚያደርግ፣ ድርሰቱ ላይ ያለችው ሴት የእውነት እንዳይደለች፣ ፈጠራ እንደሆነች፣ በደምና በስጋ ከማትጨበጥ ሴት ጋር ደምና ስጋ የለበሰው ፍቅራቸውን ማወዳደር ግፍ እንደሆነ ነግሮ ገሰፃት፡፡
ተግሳፁን ሰማች፡፡ ሰማች እንጂ አልተቀበለችውም፡፡ እርሱ ቤት በሌለ ሰዓት ከቤት እንዲያጠፋ የነገረችውን መፅሐፍ ከደበቀችበት አውጥታ ደጋግማ ታነበዋለች፡፡ ከደራሲው የበለጠ ገፀባህሪዋን መውደድ ከጀመረች ሰንበትበት ብላለች፡፡ ደራሲውን ጠልታ ገፀባህሪዋን አመለከች፡፡
ገፀ ባህርይዋን በራሷ መተካት ፈለገች፡፡ ገፀባህርይዋና ደራሲው መሀል ያለው ፍቅር በእሷና በእሸቱ ወይም በአዳምና በሄዋን መሀል ካለው ፍቅር የበለጠ ነው፡፡ ሁሌ እየጨመረ የሚሄድ እንጂ የሚከስም አይደለም፡፡ የእሷና የባሏ ፍቅርም እንደዚያ መሆን ነበረበት፡፡ መሆን ነበረበት ግን እንዳልሆነ ታይቷል፡፡ ‹‹ችግሩ እኔ ነኝ›› ብላ ተፀፀተች፡፡ እሱና ድርሰቱ መሀል መግባቷ ታወቀ፡፡ ‹‹ገፀ ባህርይዋን መሆን ብችል ሚስትም ድርሰትም እሆንለታለሁ …. እሱም ለኔ ደራሲዬና ባለቤቴ ይሆንልኛል” አለች፡፡
የመፅሐፉን የመጨረሻ ኮፒ ለመጨረሻ ጊዜ ከሚነደው እሳት ላይ ቆማ አነበበችው፡፡ አንብባ ስትጨርስ አቃጠለችው፡፡
“ከእንግዲህ ስሜ ሮዜላ ነው” አለች፡፡ የገፀባህርይዋን ስም ደጋግማ ስትጠራ፣ አነጋገሯም በስሟዋ አንፃር ተቀየረ፡፡ እንደ ሮዜላ መልበስ ስለነበረባት፣ እንደ አይዳ የለበሰችውን አውልቃ ጣለች፡፡ እንደ ሮዜላ መሳቅ ስለነበረባት፣ ስቋን የሚያጎላ የከንፈር ቀለም አብዝታ ተቀባች፡፡ እንደ ሮዜላ የሊፒስቲክ ቀለሙ ትንባሆው ቂጥ ላይ መገኘት ስለነበረበት፣ ማጨስ ተለማመደች፡፡
እንደ ሮዜላ በብዙ ወንድ መፈለግ ስለነበረባት፣ ወንድ እንዲፈልጋት ማሳየት አስፈለጋት፡፡ እንደ ሮዜላ ፍቅር መስራትና ስራ ማብዛት ስለነበረባት፣ የቤት እመቤት መሆን ማቆም ነበረባት፡፡
አዳም ከድርሰት መስክ ወጥቶ ከተራው መስክ የወል ስራ ላይ መዋል ጀምሯል፡፡ ከዋለበት ተመልሶ ቤቱ ሲመጣ ቤቱን አጣው፡፡ ቤቱ ድርሰት መስሎ አደናገረው፡፡ ሮዜላ ደራሲውን ነው የምትፈልገው፡፡ ድሮ ደራሲው ሚስት ባጣበት ዘመን፣ እሷን እንደፃፈበት መንፈሱ ሆኖ ከተራው ስራው አልመጣላትም፡፡ ከተራው ስራ ገበታው ደክሞት የመጣው አዳም፣ ተራው ሚስቱን ብቻ የሚፈልግ ነው፡፡
እሸቱ የሚፈልጋት ሚስቱ አይዳ ትባላለች፡፡ ሮዜላ አይዳ አይደለችም፡፡ አይዳ በድርሰቱ ምክንያት ሮዜላን መሆን እንደተመኘችው፣ ሮዜላ ከድርሰቱ ገፆች ወጥታ ስጋና ደም ብትለብስም አይዳን መሆን በፍፁም አትሻም፡፡ ሮዜላ በአይዳ በኩል በህልም ድርሰት ወደ እውነት ተቀይራለች፡፡ ተመልሳ ህልም መሆን አይቻላትም፡፡
እሸቱ ሚስቱን ከገፀባህሪዋ ውስጥ ለይቶ ማውጣት አቃተው፡፡ ገፀባህሪዋ በእሱ ከእለታት አንድ ቀን መሰራቷ ራሱ ያጠራጥራል፡፡ አይዳ እንጂ ሮዜላ የሱን ትዕዛዝ ለመስማት አትሻም፡፡ አይዳ እንጂ ሮዜላ የእሱን ደራሲነት ፈፅሞ አታውቅም፡፡ ደራሲነቱን ሳታምን፣ እሷን ሮዜላን የመሰለች የእኔ ድርሰት ነሽ ሲላት፣ ለሳቅ በተፈጠረው ከንፈሯ አስካክታበት ወጣች፡፡
እሸቱ ማንነቱ አጠራጠረው፡፡ አዳም ነኝ?... ሰው ነኝ? ወይንስ የሚለው ጥያቄ አቅሉን ወደ መሳት አደረሰው፡፡ “ከጎድን አጥንት የወጣች” የሚባለውን … እውነት ይሁን አይሁን… ለመመራመር ጊዜ የለውም፡፡ እቺ ሴት ወጥታ ከሄደች ሁሉንም ነገር አጠቃልላ እንደምትወስድ ቢያውቅም ለማስቆም አልቻለም፡፡ በብዕርም ሆነ በክንዱ ሊያስቆማት አቅም አጣ፡፡ “በድርሰት መፅሐፉ ውስጥ የነበረው ጂኒ ጠርሙሱን ሰብሮ ሲወጣ እንዲህ ይመስላል” አለ በውስጡ፡፡
ወደ ጥንቱ እሱነቱ ለመመለስ መሸጋገሪያው የትናንቱ እሱነቱ ብቻ ነው፡፡ እሱ ደግሞ ያለው በአይዳ .. በሄዋን እጅ ነው፡፡ ሄዋንን ሊሊትዝ በልታት እንደ እባብ በጎዳናው ላይ እየተሳበች ስትሄድ አዳም ቆሞ ተመለከተ፡፡
እግዚአብሔር ሁለት ወፍ በአንድ ድንጋይ የመታበትን ፍቅሩን በአንድ ቅፀበት ወደ ትቢያ ቀየረበት፡፡ ወደ ሰማይ አንጋጥጦ ቀረ፡፡ ለሁለት ነገር ፍላጎት የከፈለው መስዋዕትነት በምርቃት ሳይሆን በእርግማን ተደመደመ፡፡ ሰው ያልማል እግዚአብሔር ይፈፅማል፡፡
***
የድሮዋ ምኞቱ (ገፀ ባህርይዋ) እና የቀድሞ ሚስቱ ከቤት ወጥተው በአንድ ላይ ነጎዱ፡፡ ሄዋን አልተፀፀተችም፡፡ ገፀ ባህርይዋን ሆናለች፡፡
አዳምን  /እሸቱን/ ባሏን /ደራሲዋን/ ፍቅረኛዋን በቆመበት ገፍትራ ጥላው ወደ ጐዳና ወጣችው፤ ሲጋራዋን እያቦነነች፡፡ … ነፃነት ተሰምቷታል፡፡ የአዳም የልጅነት፣ የድርሰት ህልሙ ለሄዋን የጉርምስና ፍላጎቷ ማሟያ ሆኗታል፡፡
ነፃነት ተሰምቷታል፡፡ መጠጥ አምሯታል፡፡ የሚያጫውታትን ትፈልጋለች፡፡ በአንድ አዳምና በአንድ ቤት መገደብ አንገሽግሿታል፡፡ ገፀ ባህሪነትን በእውነተኛ ህይወት … በሚነካ … በሚቀመስ … በሚሰማ … በሚጨበጥ … ከተማ …. በተፃፈችበት መቼት…. አዲስ አበባ ላይ ለመሞከር ጓጉታለች፡፡
ወደ ከተማ ወጣች፡፡ ሴቶች ወዳሉበት … ከሌሎች መሀል በብዙ ወንዶች መመረጥ ወደ ሚቻልበት… ሙዚቃ የጎላበት … ወንድነት የገነፈለበት… ቤት ፈልጋ ጥልቅ አለች፡፡ ከእንስቶቹ ተርታ ተገትራ ቆመች፡፡
ብዙ ወንዶች መጡ፤ ብዙ ጨዋታ ይዘው፡፡ ሄዋን አለም ሆነች፤ አለም ደግሞ ገፀ-ባህርይ፡፡  


Read 8563 times