Saturday, 08 November 2014 11:42

“...ግልፅነት ይጎድላል... መደባበቁ ጥቅም የለውም...”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ መንግስት በጤናው ዘርፍ የምእተ አመቱ ግብ ብሎ ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል እንደውጭው አቆጣጠር በ2020/ዓም ከኤችአይቪ ነፃ የሆነ ትውልድ ማፍራት የሚለው አንዱ ሲሆኑ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው በተግባር ላይ ውለዋል ከእነዚህም መካከል፡-
በጤናው ዘርፍ ከሚሰሩ ፖሊሲ አውጪዎች ጋር በጋራ መስራት፣
የህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የPMTCT አገልግሎትን እንዲሰጡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ፣
አገልግሎቱን በሚመለከት ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ፣
የሚሉት ዋናዋናዎቹ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን የህክምና ክትትል የPMTCT (Prevention of mother-to-child transmission) አገልግሎት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ የግል እንዲሁም የመንግስት የህክምና ተቋማት እንዲሰጥ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በተለይም ከግል የህክምና ተቋማት ጋር በመተባበር ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን ተግባር በመከወን ላይ ያለ ሲሆን በዛሬው ፅሁፋችን የምንመለከተው ግን በደሴ ከተማ ተገኝተን አገልግሎቱ በመንግስት የህክምና ተቋማት በምን መልኩ እንደሚሰጥና ለግል የህክምና ተቋማቱ ከመንግስት የሚደረግላቸውን ድጋፍ የሚመለከት ነው፡፡
ሮዛ ሽፈራው በደሴ ከተማ አስተዳደር ጤና ጥበቃ መምሪያ የአገልግሎቱ አስተባባሪ ኦፊሰር ናቸው፡፡ ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የግል የህክምና ተቋማት ከመንግስት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ይገልፃሉ፡፡ ምንም እንኳን በተወሰነ መልኩ የህክምና ቁሳቁስ እጥረት ቢኖርም መንግስት ከተቋማቱ ለሚደርሰው የቁሳቁስ እንዲሁም የሙያ ድጋፍ ጥያቄ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡ ምን ያህል እናቶች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
“...አሁን ባለው ሁኔታ በግል የህክምና ተቋማቱ አገልግሎቱን የሚጠቀሙት ታካሚዎች ከተለያየ ቦታ ነው የሚመጡት አንዳንዶቹ ምጥ ይዟቸው በመጡበት ሰአት ፖዘቲቭ የሚሆኑበት ግዜ አለ አንዳንዴ ደግሞ ፖዘቲቭ ሆነው መጥተው የሚወልዱበትም ሁኔታ አለ፣ ብዙዎቹም ከተለያየ ቦታ ይመጣሉ፣ ከአፋር ክልል ጀምሮ ከሰሜን ወሎ ከሌላም     ቦታ ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎቹን ቁጥር በውል ለማወቅ  ያስቸግራል፡፡”
ለህክምና ተቋማቱ የምታደርጉት የቁሳቁስም ሆነ ሌሎች ድጋፎች በትክክል ለተጠቃሚዎቹ መድረሳቸውን በምን መንገድ ታረጋግጣላችሁ? ቀጥለን ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር፡፡
“...ያው ምርመራ ያደረጉትን ታካሚዎችን ለማየት እንሞክራለን ግን ምርመራን ያደረጉት ሁሉ ፖዘቲቭ ላይሆኑ ይችላሉ በዋናነት ግን ምን ያህል ሰዎች ተመርምረው ውጤታቸውን አውቀዋል የሚለውን እናያለን፡፡ ምን ያህሉን PMTCT አገልግሎት ላይ አዋሉት የሚለውንም እንመለከታለን፡፡ አንዳንድ ግዜ እጥረት የሚፈጠረው ለሌላም     ስለሚጠቀሙበት ይሆናል ብለን እንገምታለን።”
አያይዘውም በመንግስት የህክምና ተቋማት ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን የህክምና ክትትል በሚመለከት ማንኛዋም አገልግሎቱን ፈልጋ የምትመጣ እናት የነፃ ህክምና ታገኛለች ብለዋል፡፡
“አንዲት እናት እኛ ጋር ስትመጣ ነብሰጡር ናት ተብሎ አገልግሎቱን ከጀመረችበት ግዜ አንስቶ እስከምትወልድ ግዜ ድረስ ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነ አገልግሎት ታገኛለች፡፡ የቤተሰብ ምጣኔ እንዲሁም ሌሎች ከእናቶችና ህፃናት ጋር ተያያዥ የሆኑ     አገልግሎቶችም በአብዛኛው ነፃ ናቸው፡፡”  
በመንግስት በኩል አገልግሎቱ ደረጃውን የጠበቀና በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተመርምሮ እራስን በማወቁ እንዲሁም እራስን ካወቁም በኋላ በግልፅ ለሌሎች በማሳወቁ እረገድ በርካታ ችግሮች አሉ ያሉን ደግሞ በደሴ ከተማ የቧንቧ ውኀ ጤና ጣቢያ የነብሰጡር ክትትልና የማዋለጃ ክፍል ውስጥ ሲሰሩ ያገኘናቸው ሲስተር ካሳነሽ ግዛው ናቸው፡፡
“...ብዙዎቹ እራሳቸውን አውቀውም እንኳን ቢሆን ግልፅ መሆን አይፈልጉም እራሳቸውን አውቀው መድሀኒት እየወሰዱ እኛ ጋር መጥተው ሲመረመሩ እንደ አዲስ ነው የሚሆኑት ቀድመው እያወቁት ይደብቃሉ፡፡”
በቅርብ የገጠመጥ ብለውም የሚከተለውን አጫውተውናል፡፡
“...አንዲት እናት ...ቀደም ሲል በወለደችበት ወቅት አሁን ያለው ኦፕሽን ቢ ፕላስ ስላልተጀመረ በምጥና በወሊድ ግዜ የሚሰጠውን መድሀኒት ሰጥተው ነው ያዋለዷት፡፡ ጤና ጣቢያ  ስትመጣ ኤችአይቪ መመርመር አለብሽ ብዬ የምክር አገልግሎት ስሰጣት ቫይረሱ በደሟ እንዳለ ነገረችኝ፡፡ ከመቼ ጀምሮ ... ስላት ከሁለት ሺህ አመተምህረት ጀምሮ እንደሆነ ነገረችኝ፡፡ ስለዚህ አሁን ቫይረሱ ወደ ልጅሽ እንዳይተላለፍ ጤነኛ ልጅ እንድትወልጂ መድሀኒቱን መጀመር አለብሽ ስላት ሲዲፎርሽ ዘጠኝ መቶ ነው ስላሉኝ መድሀኒት አልጀምርም ነው ያለችኝ፡፡ ይህ እንግዲህ ከዚህ በፊት የነበረው አሰራር ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ይህ መድሀኒቱን ለመጀመር መመሪያ ወይም ቅድመሁኔታ አይደለም፡፡ ሲዲፎር ቢወርድም ባይወርድም ኤችአይቪ በደምሽ ውስጥ እንዳለ ከታወቀና ነብሰጡር ከሆንሽ... ወዲያው ነው መድሀኒቱን መጀመር ያለብሽ ብዬ ስላት ባለቤቴን አማክሬ እመጣለሁ ብላ መድሀኒቱን ሳትይዝ ሄደች፡፡ ለእኔ ግልፅ ላለመሆን እንጂ መድሀኒቱን የምትወስድ ይመስለኛል፡፡ እንደዚህ አይነት ችግሮች በተደጋጋሚ ይከሰታሉ ብዙዎቹ የመኖሪያ አድራሻቸውን ካርዳቸው ላይ እንኳን ማስመዝገብ አይፈልጉም፡፡”
ምን ቢደረግ ነው ይህን ችግር ማስቀረት የሚቻለው ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲ/ር ካሳነሽ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
“...እንግዲህ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በየጊዜው በሚዲያ ይነገራል፡፡ በእኛም በኩል ምርመራውን ከማድረጋቸው በፊት በደንብ ነው የምክር አገልግሎት የምንሰጣቸው፡፡ መድሀኒቱ የእድሜ ልክ እንደሆነና ተጀምሮ መቋረጥ እንደሌለበት... ከተቋረጠ የቫይረሱ መጠን እንደሚጨምር እንዲሁም ወደ ልጁ የመተላለፍ እድሉም በዛው ልክ እንደሚጨምር እንነግራቸዋለን፤ ግን አሁንም ወደ ፊትም እኔ ለውጥ ያመጣል የምለው የmother support  ቡድኑ የሚሰራው ስራ ነው ምክንያቱም እነሱ ናቸው እታች ወዳለው የህብረተሰቡ ክፍል ወርደው ብዙውን ስራ የሚሰሩት ስለዚህ ያለን አማራጭ እነሱን ማጠናከር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡”
ከሁሉም በላይ ግን ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የትዳር አጋሮች የሚኖራቸው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ባለትዳሮች በጋራ ተመርምረው ውጤታቸውን ቢያውቁ አሁን እየታየ ባለው ለውጥ ላይ የበለጠ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ሲሉ ሲ/ር ናሳነህ ተከታዩን ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡
“...ሚስቱ ለእርግዝና ክትትል ወደ ጤና ተቋም ስትሄድ ባልዋ ሀላፊነት ተሰምቶት ከእሷ ጋር አብሮ     ሄዶ የምክር አገልግሎት ሲደረግላት ስለ ኤችአይቪ ብቻም ሳይሆን ስለ    አመጋገብ ስለ ንፅህና ሌሎችንም ነገሮች እንመክራለን፡፡ ኤችአይቪም አብሮ ይመረመራል እዚሁ አብረው ተመርምረው ሚስት እንኳን ቢገኝባት የምክር አገልግሎት አግኝቶ ከሄደ ለመድሀኒቱ እንኳን ጫና አያሳድርባትም፡፡ አንቺ ነሽ ያመጣሽብኝ ምናምን     የሚለው ነገር አይኖርም፡፡ ዲስኮርዳንት ከሆኑም ወደፊት እንዴት አብረው መኖር እንዳለባቸው፣ አንዱ አንዱን እንዴት ከኤችአይቪ መጠበቅ እንዳለበት በዛው እናስተምራለን፡፡ እንደገና በእርግዝና ወቅት ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዲሁም     እናቲቱ ነፃ ሆናም ከሆነም ከባል ወደ እሷ እንዳይተላለፍ ጥንቃቄ አድርገው አንዱ ለአንዱ እንዲተሳሰቡ አብረው ስለሚመከሩ የትዳር አጋርም አብሮ ወደ ጤና ጣቢያ     ቢመጣ ለኤች አይቪ     ስርጭት መቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡”
የባልና ሚስት ውጤት መለያየት በሚገጥምበትም ወቅት ተገቢውን የህክምና ክትትል በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት መግታት ይቻላል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ተከታዩን መልእክት አስተላልፈዋል፡-
“...ኤችአይቪ በደም ውስጥ ባይገኝ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከተገኘ መንግስት አሁን አገልግሎቱን በነፃ እየሰጠ ነው፡፡ ስለዚህ ወላጆች ክትትል አድርገው ጤነኛ ልጅ ወልደው እንዲያሳድጉ ይመከራል ...መደባበቁ ጥቅም የለውም... በተለይም በደሴ ከተማ ኤችአይቪን በሚመለከት ግልጽነት ይጎድላል፡፡ ለመመርመር የሚመጡ እናቶች ሳይደብቁና ሳይሳቀቁ ግልፅ ሆነው መጥተው ቢስተናገዱ ለወደፊቱ ከኤችአይቪ ነፃ ሆነ     የሆነ ትውልድ ለማፍራት ይረዳል።”        

Read 3577 times