Saturday, 22 November 2014 12:55

“...በእርግዝና ወቅት የሰውነት የአይረን ፍላጎት ይጨምራል...” ዮዲት ባይሳ ከኢሶግ

Written by  ዮዲት ባይሳ ከኢሶግ
Rate this item
(31 votes)

     ብረት ወይም አይረን ለሰውነታችን ከሚያስፈልጉ ንጥረነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በተመሳሳይ አንዲት ሴት ስታረግዝ ጤንነቷ የተሟላ እንዲሆን ከሚያስችሉ ንጥረ ነገሮች መካከል አንዱ አይረን ወይም ብረት ነው፡፡
በዛሬው ፅሁፋችን አንዲት ሴት በሰውነቷ ሊኖር የሚገባው የብረት መጠን፣ ለእናቲቱ እንዲሁም ለፅንሱ የሚኖረው ጠቀሜታ፣ በማነሱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና እክሎች እንዲሁም ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ከባለሙያ ያገኘነውን ምላሽ ጨምረን እንዲህ ልናስነብባችሁ ወደናል፡፡
ዶክተር ሊያ ታደሰ የማህንና ፅንስ ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ብረት ለሰውነታችን የሚኖረውን ጠቀሜታ እንዲህ ሲሉ ይገልፁታል፡፡
“...አይረን ወይም ብረት ለሰውነታችን ህዋሶች በጣም ወሳኝ የሆነ ንጥረነገር ነው፡፡ በዋነኛነት በቀይ የደም ሴሎች ላይ ሄሞግሎቢን የሚባል ኦክስጅን በሰውነታችን ውስጥ እንዲመላለስ የሚያደርግ ህዋስ አለ፡፡ ይህ ህዋስ ኦክስጅንን የሚያመላልሰው አይረን ወይም ብረት በተሰኘው ንጥረ ነገር አማካኝነት ነው፡፡ ስለዚህ በሰውነታችን ላይ በቂ የሆነ ኦክስጅን እንዲኖር የሚያደርገው ይህ ንጥረነገር ነው ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ሴላችን ውስጥ ማይቶኮንድሪያ የሚባል ኢነርጂ ሴል ወይም power house አለ እዛም ውስጥ ደግሞ ወሳኝ የሆነ ስራ አለው ስለዚህ ባጠቃላይ ብረት ለሰውነታችን ወሳኝ የሆነ ንጥረ ነገር ነው፡፡”
ከላይ የተገፀለው አይረን ወይም ብረት በማንኛውም ሰው ላይ የሚኖረው ጠቀሜታ ሲሆን አንዲት ነብሰጡር ሴት በእርግዝና ወቅት የብረት ንጥረነገር በበቂ ሁኔታ በሰውነቷ ውስጥ መኖሩ ለእናቲቱ ብሎም ለፅንሱ የሚኖረው የተለየ ጠቀሜታ እንዳለ ዶክተር ሊያ ይልፃሉ፡፡
“...በእርግዝና ወቅት የሰውነታችን የአይረን ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ይህም የራሱ የሆነ ምክንያት አለው በአንደኛ ደረጃ ፅንሱ በምያድግበት ግዜና እርግዝናው እየገፋ በሚሄድበት ወቅት ከሰውነታችን የሚጠቀመው የአይረን መጠን አለ፡፡ አንደኛው ምክንያት እሱ ነው ሁለተኛው ደግሞ በእርግዝና ግዜ የሰውነታችን የደም መጠን ይጨምራል፡፡ ከዛ ውስጥ የተወሰነውን የሚይዙት የደም ሴሎች ሲሆኑ ፕላዝማ የምንለው የደም ሴል የሌለው የደም ክፍሉም ይጨምራል ነገርግን የሚጨምረው በእኩል መጠን እይደለም ይህም ማለት የደም ሴሉቹ ከደም መጠኑ እኩል አይጨምሩም ስለዚህ dilute የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ፅንሱና የእንግዴልጁ ተጨማሪ አይረን ስለሚፈልጉ እነዚህ ነገሮች የሰውነታችን የአይረን ፍላጎት እንዲጨምር ያደርጉታል፡፡”
ይህ ንጥረነገር በሰውነታችን ያለው መጠን አንሶ ሲገኝ አኒሚያ ወይም በተለምዶ የደም ማነስ የምንለውን ችግር ሊያስከትል ይችላል ነግር ግን እንደ ባለ ሙያዋ አገላለፅ ሁሉም የደም ማነስ ችግሮች የሚከሰቱት ከብረት እጥረት የተነሳ ነው ለማለት አይቻልም፡፡
“...በሰውነታችን ያለው የአይረን ማነስ ደም ማነስ የምንለውን ችግር ያስከትላል ነገርግን ደም ማነስ ሁልግዜም በአይረን እጥረት የሚከሰት ነው ማለት አይቻልም በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ደም ማነስ ሊከሰት ይችላል፡፡ ግን ብዙውን ግዜ በተለይ በእርግዝና ወቅት አብዛኛው የደም ማነስ ምክንያት  በተለይ ደግሞ እንደኛ አይነት ታዳጊ በሆኑ ሀገሮች ላይ የተለመደው ከአይረን እጥረት የሚመጣው የደም ማነስ ነው፡፡”
ደም ማነስ መኖሩ በምን ይታወቃል ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር ሊያ ሲመልሱ...
“...ደም ማነስ መኖሩን ለማወቅ የተለያዩ ምርመራዎቸ ያስፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌም የደም ምርመራ ለምሻሌ ምኄሞግሎቢን መፀን ምጵበ ውስጥ የአይረን መጠን የመሳሰሉትና የአይነ ምድር  ምርመራ በማድረግ ማወቅ ይቻላል፡፡”     
በፈረንጆቹ 2005 በሀገራችን የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከሶስት ሴቶች መካከል አንዷ በአይረን እጥረት ምክንያት ለሚከሰት የደም ማነስ ተጋላጭ ነች፡፡ ለመሆኑ የሄሞገግሎቢን ምርመራ ውጤት አተረገጓጎም ምን ይመስላል?
“...እርጉዝ ላልሆነች ሴት normal የሚባለው ከአስራ ሁለት በላይ ነው፡፡ በእርግዝና ወቅት ደግሞ ወደ አስራ አንድ ዝቅ ይላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቀይ የደም ሲል እንደገለፅኩት በእርግዝና ወቅት ከደማችን መጠን መጨመር ጋር ተያይዞ የደም ማነስ ስለሚኖር ነው፡፡ ስለዚህ በሰውነታችን ያለው የአይረን መጠን ከአስራ ሁለት እስከ ስምንት ግራም (ፐር ዴሲሊትር) ከሆነ መጠነኛ የደም ማነስ አለ ማለት ነው፡፡ ከስምንት እስከ ስድስት ከሆነ ደግሞ የደም ማነሱ መካከለኛ ሊባል ይችላል፡፡ ነገርግን ከስድስት በታች ከሆነ የደም ማነሱ እጅግ ከፍተኛ ስለሚሆን ደም መሰጠት የሚያስፈልግበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡”
በደማችን ውስጥ ያለው የሄሞግሎቢን መጠን መቀነስ ለደም ማነስ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም በሰውነታችን ውስጥ ያለው የአይረን ንጥረነገር ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የተለያዩ የጤና ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ዶክተር ሊያ ይገልፃሉ፡፡
“...እናትየው ላይ ሊከሰቱ የሚችሉት ችግሮች እንደ አጠቃላይ የደም ማነሱ መጠን ይለያል ለምሳሌ የደም ማነሱ መጠነኛ ከሆነ  እንደ የልብ ምት መጨመር፣ መድከም እንዲሁም ማዞር የመሳሰሉት ችግሮች ይኖራሉ፡፡ የደም ማነሱ ከፍተኛ ከሆነ ግን የሰውነት ማበጥ ከዛም አልፎ የልብ ድካም ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህ እንግዲህ በእርግዝናው ወቅት ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ከባዱ ችግር የሚመጣው በወሊድ ወቅት ነው፡፡ ማንኛዋም ሴት በወሊድ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ ሊያጋጥማት ይችላል ነገር የደም ማነስ ያላት ሴት ይህንን መቋቋም አትችልም ይህ ደግሞ እስከ ሞት ሊያደርሳት ይችላል፡፡ እንደሚታወቀው በወሊድ ግዜ የሚኖር የደም መፍሰስ አንዱና ትልቁ የእናቶች ሞት ምክንያት ነው፡፡ ፅንሱን በሚመለከት ደግሞ ፅንሱ ክብደቱ አነተኛና እድገቱም ዘገምተኛ እንዲሆን ወይም በበቂ ሁኔታ እንዳያድግ ሊያደርግ ይችላል አንዳንዴ ደግሞ ካለቀኑ ምጥ እንዲጀምርም ሊያደርግ ይችላል ከዛ ውጪ ልጁ ሲወለድም የደም ማነስ ያለበት ሆኖ ሊወለድ ይችላል፡፡”  
አንዲት እርጉዝ ሴት ይህን መሰል ችግሮች እንዳያጋጥማት በምን መንገድ ልትከላከል ትችላለች? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ተከታዩን ሰፋ ያለ ሞያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡-
“...የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ብዙ የብረት መጠን ላያስፈልጋት ይችላል ነገርግን  ከዛ በኋላ በተለይ እርግዝና እየገፋ ሲመጣ በፊት ከሚያስፈልጋት ስምንት ወይም ዘጠኝ እጥፍ  በላይ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛዋም እርጉዝ ሴት ከምግብና ከምግብ በተጨማሪ ደግሞ icon supplement እንድትወስድ የሚመከረው ለዚህ ነው ምክንያቱም ከምግብ  የምታገኘው አይረን በእርግዝና ወቅት ያለውን የሰውነት ፍላጎት አያሟላም፡፡ ስለዚህ ከምግብ በተጨማሪ  ሌሎች እንደ ፎሊክ አሲድ ያሉ ንጥረ ነገሮች አብረው መሰጠት አለባቸው፡፡ ፎሊክ አሲድም በፅንሱ ጤንነት ላይ እንዲሁም አኒሚያ ወይም ደም ማነስን በመከላከሉ እረገድ የሚያመጣው ተፅእኖ ስላለ ማንኛዋም እርጉዝ ሴት በእርግዝናዋ ወቅት በለተይ ከሶስት ወር በኋላ ባለው ግዜ ውስጥ አይረንና ፎሊክ አሲድ እንድትወስድ ይመከራል፡፡”
ይህ እንዳለ ሆኖ በህክምና ከሚሰጠው የአይረን ንጥረ ነገር በተጨማሪ አንዲት እርጉዝ ሴት አመጋገቧን እና በሰውነቷ ያለውን የአይረን መጠን በማስተካከል የእራሷን ብሎም የፅንሱን ጤንነት መጠበቅ ትችላለችም ብለዋል ዶክተር ሊያ፡-
“...ማንኛዋም እርጉዝ እናት ወደ ህክምና ተቋም ስትመጣ በቅድሚያ በደሟ ውስጥ ያለው የሂሞግሎቢን መጠን ተለክቶ መጠኑ አነስተኛ ከሆነ icon supplement እንድትወስድ ይደረጋል፡፡ በአመጋገብ በኩል ደግሞ ከእንስሳት ተዋፅኦ የሚገኘውን ..ጉበት፣ኩላሊት፣ቀይ ስጋና እንቁላል.. የመሳሰሉት ወይም ደግሞ ከአትክልትና ፍራፍሬ በአይረን የበለፀጉ ምግቦችን በመመገብ በሰውነታችን ያለውን የአይረን መጠን መጨመር ይቻላል፡፡”
ከእዚህ በተቃራኒ ደግሞ በሰውነታችን ያለውን የአይረን መጠን እንዲቀንስ የሚያደርጉ እንደ ቡና፣ሻይ የመሳሰሉትን መቀነስ በሰውነታችን የሚኖረው የአይረን መጠን ተመጣጣኝ እንዲሆን እንደሚያደርግ ዶክተር ሊያ ይገልፃሉ፡፡
በመጨረሻም ዶክተር ሊያ በእርግዝና ወቅት ከአይረን እጥረት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የደም ማነስ በሚመለከት መደረግ አለበት ያሉትን ሀሳብ የፅሁፋችን ማጠቃለያ አድርገነዋል፡፡
“...ከላይ...ከደም ማነስና ከአይረን ጋር የተያያዙት ጉዳዮች በደንብ ተነስተዋል፡፡ ነገርግን አስቀድሜ ፎሊክ አሲድ ብዬ የጠቀስኩትም ንጥረ ነገር ልክ እንደ አይረን ሁሉ ከደም ማነስ ጋር በተያያዘ በሰውነታችን የሚኖረው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ተመሳሳይ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል፡፡ ይህ ንጥረ ነገር ልክ እንደ አይረን ሁሉ ከሶስት ወር በኋላ መውሰድ ይቻላል፡፡ ፎሊክ አሲድ እርግዝና ከመከሰቱ አስቀደሞ ፅንሱ ጤንነት ላይ ትልቅ ተጽእኖ  አለው፡፡ ስለዚህ አንዲት እናት ቢቻል እርግዝና ከመፈጠሩ በፊት ብትወስድ... ይህም ሳይሆን ከቀረ በእርግዝና ወቅት እስከ ሶስት ወር ባለው ግዜ ውስጥ ብትወስድ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡”

Read 27631 times