Friday, 06 January 2012 10:37

ከጐዳና ተዳዳሪነት ወደ ከተማ ፅዳት ቡችላ በ150 ብር ይሸጣል

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

በዛሬው ፅሁፌ ታሪካቸውን በአጭር ቃለ ምልልስ የማቀርብላችሁ ወጣቶች “ታላላቅ ህልሞች” በሚለው የስኬታማ ሰዎችን ታሪክ የያዘ መፅሃፍ ውስጥ ያነበብኩት አሜሪካዊ ቢሊዬነርን አስታውሰውኛል፡፡ አሜሪካዊው ዌይዝንገር እንደነዚህ ወጣቶች ሰፈር ውስጥ ቆሻሻ በመሰብሰብ ጀምሮ ነው ሥራውን ወደ ትልቅ ቢዝነስ በማስፋት በርካታ የቆሻሻ መጣያ መኪኖች ገዝቶ ትልቅ ኩባንያ ማቋቋም የቻለው፡፡ ስኬት ዘር፣ ቀለምና አህጉር አይልምና በትጋት ጠንክረው ከሰሩ ኢትዮጵያዊ ቢሊዬነሮች የማይሆኑበት አንዳችም ምድራዊ ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡

በቸርችል ጎዳና ከሊሴ ገ/ማርያም ትምህርት ቤት በስተጀርባ ነው አድራሻቸው፡፡ አራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 01/02 (አሁን ወረዳ 1) ለጽዳት ሥራ በ2001 ዓ.ም ሲያደራጃቸው ቁጥራቸው 20 የነበረ ሲሆን በጋራ እየሰሩ ሦስት ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ቡድኑ የጋራ ሥራውን ሲያጠናቅቅ አንዳንዶቹ ተጨማሪ ሥራ እየፈለጉ (እየፈጠሩ) ገቢ ለማግኘት ይጥራሉ፡፡ ከ20ው አባላት አራቱ ቡችላ በመሸጥ ገቢ ማግኘት ከጀመሩ አንድ ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ዘላለም ፍቃዱ በይርጋጨፌ፣ ምትኩ ወርቅነህ በአምቦ፣ ታምሩ ሚሊዮን በሐረር፣ ይሁን አማን በአርባ ምንጭ ነው የተወለዱት፡፡ ወጣቶቹ በትምህርታቸው ከ6ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ደርሰዋል፡፡ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የትውልድ መንደራቸውን ለቀው አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ያገኙትን እየሰሩ ለመኖር ሞክረዋል፡፡ ከሌሎች ጋር ተደራጅተው በጽዳት ሥራ ላይ በመሰማራታቸው ምን ጥቅም እንዳገኙና ወደ ቡችላ ንግድ እንዴት እንደገቡ ይናገራሉ፡፡

 

በአንድ ላይ ተደራጅቶ መሥራቱ ምን ፈየደላችሁ?

የሰበሰብነው ቆሻሻ በሜትር ኪዩብ እየተለካ ይከፈለናል፡፡ ገቢው ያን ያህል የሚያረካ አይደለም፡፡ ሆኖም ያገኘነውን የሥራ ዕድል አክብረንና ነገ ይለውጠናል ብለን በማመን በትጋት እየሰራን ነው፡፡ ተጀራጅተን መንቀሳቀሳችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት አድርጎናል፡፡ ከአባላቶቻችን ሦስቱ ሴቶችና የልጅ እናት ናቸው፡፡ ባለትዳሮች ለየብቻ፣ ያላገባነው 10 ወጣቶች ደግሞ በጋራ የምንኖርበት አንድ ቤት ተሰጥቶናል፡፡ ከጎዳና አንስቶ ለዚህ ያበቃንን መንግሥት እናመሰግናለን፡፡

በትርፍ ጊዜያችሁ ምን ትሰራላችሁ?

በጋራ የምንሰራውን የጽዳት ሥራ ካጠናቀቅን በኋላ ሁሉም አባላችን ያገኘውን ስራ ለመሥራት ይሞክራል፡፡ እኛ አራታችን ደግሞ ቡችላ በማዞር እንሸጣለን፡፡

መነሻችሁ ምን ነበር? ቡችላ በመሸጥ ጀማሪው ማነው?

ሥራውን ማን እንደጀመረው አናውቅም፡፡ እኛ ቆሻሻ በምንሰበስብበት ገንዳ አካባቢ ውሾች ስለሚሰባሰቡ የሚወልዱበትን ጊዜ ጠብቀው እየመጡ የሚገዙን ልጆች ነበሩ፡፡ በቅናሽ ነበር የምንሸጥላቸው፡፡ ገዝተውን ምን እንደሚያደርጉ ስናጠና አዙረው እንደሚሸጡ ተረዳን፡፡ እኛስ ለምን አንሞክርም አልንና … ቡችሎቹን ማዞር ጀመርን፡፡ ይህንን ሥራ ከጀመርን አንድ ዓመት ሞልቶናል፡፡

ቡችሎች መሸጫ ልዩ ቦታ አለ? በሥራውስ ላይ የተሰማሩ ምን ያህል ሰዎች አሉ?

ቡችሎች መሸጫ ዋናው ቦታ ቦሌ ወረዳ ነው፡፡ ሀብታም ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ዜጎች ናቸው የሚገዙን፡፡ ቡችላ በመሸጥ ሥራ ላይ የተሰማሩት እኛን ጨምሮ ከ10 አንበልጥም፡፡ ቡችላ ስናገኝ በእጃችን ይዘን በቦሌ ጎዳናዎች ስንዘዋወር ሰዎች እየጠሩ ይገዙናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የመግዛት ሃሳቡ ሳይኖራቸው እንደማበረታቻ ዝም ብለው የሚገዙን ጊዜም አለ፡፡

የቡችላ መሸጫ ዋጋ ስንት ነው?

በትንሹ 50 ብር ጥሩ ነገር ከተገኘ ደግሞ እስከ 150 ብር የምንሸጥበት ጊዜ አለ፡፡ ቡችሎች በየቀኑ አይኖሩንም፡፡ ቡችሎች ኖረውንም ሳንሸጥ የምንመለስበት ጊዜ አለ፡፡

የቡችላ ምንጫችሁ ምን ይመስላል?

የጽዳት ሥራ በምሰራበት ቦታ አብረውን ያሉ ውሾች አሉ፡፡ ብዛታቸው በውል አይታወቅም እንጂ በአካባቢያችን ባለቤት ያላቸውና የሌላቸው ብዙ ውሾች አሉ፡፡ ሲወልዱ እንክብካቤ እናደርግላቸዋለን፡፡ ቡችሎችን በየመንደሩ እየዞርን በመግዛትም ለሽያጭ እናቀርባለን፡፡

የምታደርጉት እንክብካቤ እንዴት ይገለፃል?

እናትየው ቡችሎቿን በደንብ እንድታጠባቸው ምግብ እናቀርብላታለን፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ቡችሎቹም ራሳቸውን ችለው መመገብ ስለሚችሉ የሚያፋፋቸውን ምግብ እንሰጣቸዋለን፡፡ በየጊዜው እያጠብን ጽዳታቸውን እንጠብቅላቸዋለን፡፡

ቡችላ በስንት ጊዜው ነው ለሽያጭ የሚቀርበው? የፆታ ፍላጎቱ ገበያው ውስጥ ምን ይመስላል?

ቡችሎቹን አንድ ወር ሲሞላቸው ነው ለገበያ የምናቀርበው፡፡ ብዙ ጊዜ ገዢዎች የሚፈልጉት ወንድ ቡችሎችን ነው፡፡

ቡችላ የሚሸጥ ተቋም ስለመኖሩ የምታውቁት ነገር አለ?

በቦሌ ጎዳና ላይ በተንቀሳቃሽ የብረት ማስታወቂያ ላይ ለውሾች የክትባት አገልግሎት እንደሚሰጡና ቡችላ እንደሚሸጡ የሚገልጽ ጽሑፍና ተቋም መኖሩን አይተናል፡፡

እናንተስ ሥራችሁን ተቋማዊ ለማድረግ አላሰባችሁም?

ራሱን የቻለ ሥራ ብናደርገው የሚያዋጣ ይመስለናል፡፡ ሥራውን ወደዚያ ደረጃ ለማሳደግ ግን ብዙ ነገር ያስፈልጋል፡፡ ለሥራው የሚያስፈልገውለ ገንዘብና ሰፋ ያለ ቦታ ብናገኝና ብንሰራው ያዋጣል፡፡

ከቡችላው ሽያጭ ምን ተማራችሁ?

ማንም ሰው ያገኘውን ሥራ ሳይንቅ ለመሥራት ከሞከረ ገቢ የሚገኝባቸው ብዙ ሥራዎች እንዳሉ የቡችላ ሽያጩ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

 

 

 

 

Read 2559 times Last modified on Friday, 06 January 2012 10:53