Saturday, 29 November 2014 11:38

“...የስነ ተዋልዶ አከላት አፈጣጠርና ችግሮቹ...”

Written by  ዮዲት ባይሳ ከኢሶግ
Rate this item
(13 votes)

የሴቶች ስነ ተዋልዶ አከላት አፈጣጠር በምን መንገድ ነው?
ተጉዋደለ የሚባለው ምን ስለጎደለ ነው?
የአፈጣጠር ጉድለት ምን ጉዳት ያስከትላል?
ከላይ በተሰነዘሩት ጥያቄዎች ዙሪያ (Integrated family health program) በተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም ከፍተኛ የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናት ጤና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ሰንደቅ የሰጡንን ማብራሪያ ነው በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው፡፡
ጥ/    የተፈጥሮ ሂደት በምን ይገለጻል?
መ/    “...የሰው ልጅ ሲሰራ ከሁለት ሴሎች ድብልቅ ነው፡፡ እነዚያ ሁለት ሴሎች ሲባዙ ነው      የምናውቃቸውን የተሙዋላ ሰውነት ማለትም አይን እጅ እግር... እንዲሰራ ያደርጋል፡፡ በዚህ የሴሎች አሰራር ሂደት ውስጥም የሴት ልጅ ውጫዊና ውስጣዊ ስነ-ተዋልዶ አካላት ወይንም የመራቢያ አካላት የሚፈጠሩት
ጥ/    ሴሎቹ በደረጃ ይለያያሉ ወይንስ ተመሳሳይ ናቸው?
መ/    ሴሎቹ ሶስት ዋነኛ ክፍሎች (layers) አሉዋቸው፡፡ እነርሱም ኤክቶደርም ሜሶደርም እና ኢንዶደርም የሚባሉ ሶስት ላየሮች አሉ፡፡ የሴት የስነተዋልዶ አካል ማለትም ማህጸን፤     የማህጸን ቱቦዎች     እና ብልት የሚፈጠረው ፓራሜሶነፍሪንክ ወይም ሙለሪያን ዳክት     ከሚባለው ከሜሶደርመም የተገኘ ነው፡፡ በዚህ አፈጣጠር ሂደት ከኩላሊትና ከሽንት ቡዋንቡዋ ጋር ባላቸው ቅርበት የተነሳ አከላዊ ጉድለት ሲኖር ሁለቱም ጋ ሊከሰት ይችላል ስለዚህም በምርመራ ወቅት ይህን ግንዛቤ ወስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
ጥ/    የሴቶች ስነ ተዋልዶ አከላት አፈጣጠር ጉድለት በምን ምክንያት ይከሰል?
መ/    ይህ ነገር በምን ምክንያት ይመጣል ለሚለው ጥያቄ አንድ መንስኤ ብቻ  መስጠት     አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከብዙ ምክንያቶች ሊመጣ ስለሚችል ነው፡፡ ይህ የተፈጥሮ  ችግር     ከአካባቢ ተጽእኖ በዕርግዝና ወቅት ከሚወሰዱ ነገሮች ለአንዳንድ ነገሮች ከሚኖር     ተጋላጭነት... በመሳሰሉት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ይህ የተፈጥሮ ችግር በአጠቃላይ “...ከብዙ ምክንያቶች የሚመጣ...” ተብሎ የሚገለጽ ነው፡፡
ጥ/     ጽንስ የወንድ ወይንም የሴት ስነ-ተዋልዶ አካል እንዲሆን የሚያስችለው ተፈጥሮአዊ     ሂደት ምን ይመስላል?
 መ/    ጽንሱ የወንድ ወይም የሴት ስነ-ተዋልዶ አካል እንዲኖረው የሚለየው ሙለሪያን     ኢነሂቢቲንግ ፋክተር የሚባል ንጥረ-ነገር ሲሆን ወንዶቹ ላይ ገና ከጅምሩ ይህ ነጥረ-ነገር     ስለሚኖራቸው የሴት ስነ-ተዋልዶ አካል አይፈጠርም፡፡ ስለዚህ ሙለሪያን     ኢነሂቢቲንግ ፋክተር መኖሩ ማህጸንና ሌሎች የሴት ብልት አከላት መሰራታቸው ይቀርና ይከስማሉ፡፡ ጽንሱ ሴት ከሆነ ግን ሙለሪያን ኢነሂቢቲንግ ፋክተር የሚባለው ስለማይኖር የማህጸን እድገት የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ እና ብልት የተባሉት ይሰራሉ፡፡  
ጥ/    አንዲት ሴት በማህጸንዋ ወይንም በብልትዋ የተፈጥሮ ችግር ያለባት መሆኑን እንዴት     ልታውቅ ትችላለች?
መ/    እነዚህ አካላዊ ጉድለቶች በአብዛኛው መከሰታቸው አይታወቅም ብዙዎች ምልክት ስለሌላቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ በአጋጣሚ በኦፕራሲዮን ወቅት ወይም የላፓራስኮፒ ምርመራ     ሲደረግ እግረ መንገዱን የሚታይ ሊሆን ይችል፡፡ በብዛት የሚከሰቱት ምልክቶች የወር     አበባ አለማየት፤ በግብረ-ሥጋ ግንኙነት ወቅት ህመም፤ ማርገዝ አለመቻል፤     ተደጋጋሚ ጽንስ መቁዋረጥ፤ ያለጊዜ ልጅ መወለድ፤ የመሳሰሉትን ያከትታል፡፡
ጥ/    ምን ምን አይነት የአካል ጉድለቶች አሉ?
ጉድለቶች ብዙ አይነት ሲሆኑ ለመጠቆም ያክል ሁለት ማህጸን (uterine     didelphis)፤ አርኩዌት ማህጸን (arcuate uterus)፤ ሴፕቴትድ ማህጸን (septated     uterus)፤ ማህጸን አለመፈጠር (uterine agenesis)፤ የብልት መደፈን (imperforate     hymen/ vaginal septum) የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡
ጥ/    ማህጸን ወይንም የሴት ብልት ሁለት ሊሆን የሚችልበት ምክንያት ምንድነው?
መ/    ማህጸን ሲፈጠር በቀኝና በግራ ከሁለት ሙለርያን ዳክት ጥምርታ ሚፈጠር ሲሆን በዚህ ሂደት  በመሀል ሲለዩዋቸው የነበሩ ሴሎች/ቲሽዎች እሲከሰሙ አንድ ማህጸን ይሆናል፡፡     ይሄ     ውህደት ሊኖር ሲገባ ነገር ግን ሳይሳካ ከቀረ በግራና በቀኝ ሆነው የተፈጠሩት የማህጸን ክፍሎች ሁለቱም ለየብቻቸው ስለሚቀሩ ሁለት ማህጸን ሁለት የማህጸን     በር ሁለት ውጫዊ ብልት ሊኖር ይችላል፡፡  ብልት ሲባል ግን ከውጭ የምናየውን አካል ሳይሆን ወደማህጸን በር የሚያገናኘውን ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ተፈጥሮ     ሁለት ማህጸን ወይንም በከፊል የተከፈለ አለዚያም በመሀከሉ ስስ በሆነ ግድግዳ የተከፈለ ተብሎ ይገለጸል፡፡  
ጥ/     የስነ-ተዋልዶ አካላት አፈጣጠር ችግር ያለባቸው በህክምና ሊረዱ ይችላሉ ወይ?
መ/     አዎ፤ እንደ ጉድለቱ አይነት በህክምና ሊታገዙ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ በቀላል ህክምና ሲድኑ  ሌሎቹ ግን ከፍተኛ ህክምና ያስፈልጋቸዋል፡፡
ማጠቃለያ፡-
“...በስተመጨረሻው ለህብረተሰቡ ማስተላለፍ የምፈልገው... ሰዎች ካለምንም ምክንያትና     ምልክት ተፈጥሮአዊ ጉድለትን ለማወቅ ብቻ ሲሉ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ አለባቸው ብዬ አልመክርም፡፡ ነገር ግን ችግሩን ለማወቅ ይረዳሉ የተባሉ ምክንያቶችን ሲያስተውሉ ግን ጊዜ ሳያጠፉ ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ አገልግሎቱን መግኘት ብልህነት ነው፡፡”

Read 12732 times