Friday, 06 January 2012 10:58

የዓለም ታላላቆች ጨዋታErostratos

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(0 votes)

በጥንታዊው ዘመን “The Seven Wonders of the World” ተብለው የተመዘገቡ፣ የሰው ልጅ የሰራቸው “ድንቅ”ቅርሶች ነበሩ፡፡ ከነዚህም መሀል የግብፅ ፒራሚዶች፣ትልቁ የቻይና ግምብ፣ እና የአቴንስ Acropolis በብዛት ይጠቀሱ ነበር፡፡ ሀዋርያቱ ከእስራኤል ወጥተው በየአገሩ እየዞሩ፣ ተአምራት እየሰሩ ሲያስተምሩ፣ ኤፌሶን ወደብ ውስጥ የቆመው መጠኑ በኛ ቋንቋ “የገደል ቅራፊ” የሚባለው፣ የድንግሊቱ የአደግ አምላክት የዳያና ሀውልት ቆሞአል፡፡ እዚህ ላይ ኤሮስትራቶስ የሚባል ሰውዬ ይመጣል፡፡ ገና ከልጅነቱ አንስቶ ምኞቱ፣ ፀሎቱ፣ ተስፋው እና ቋሚ አላማው ስሙን “ለዘለአለም” ተክሎ ማለፍ ነበር፡፡

ግን አማልክቱ የተመቀኙት ይመስል፣ ሁሉም “ዘለአለማዊ ስም የተከሉ” ጀግኖች በሁሉም ጥረት ቀድመውት አልፈዋል፡፡ ለምሳሌ በአፍላ እድሜው በሩጫ ከAchiles መፍጠኑን በታመኙ ዳኞች ፊት ቢያስመሰክር እንኳ፣ የታመኑ ሰዎች አንድ ሁለት ሳምንት በአድናቆት አውርተው፣ ሰልችቷቸው ይተውትና ይረሱታል፡፡ ሌላው ይቅርና፣ እንደ ሳይንቲስቱ Daedalus ልጅ እንደ Ikarus በሰም ክንፍ ሰርቶ ወደ ፀሀይ በረራ ቢያደርግ እንኳ፣ ያው ለአንድ ሁለት ሳምንት በታላቅ አድናቆት ከተወራ በኋላ እንደ ልማዳቸው ይረሱታል፡፡   አንድ ቀን ብልጭ ብሎ ብርሀን ታየው፡፡ ስንት የጉልበት ሰራተኛ ቀጥሮ ወይ አሰማርቶ እንደሆን እንጃለት (ትርጉም “አልተመዘገበም”) ያንን ድንቅዬ ሀውልት አስፈረሰው! እና “ዳያናን ያፈረሳት ማን ነው?” ብሎ አወጀ “እኔ ኤሮስትራቶስ ራሴ ነኝ! ለምን ቢባል “ዳያናን ያፈራረሳት ኤሮስትራቶስ ነው” እየተባለ ለዘለአለም እንዲነገር የነበረኝን እቅድ በስራ ተርጉሜዋለሁ!”

ኤሮስትራቶስ ኢላማውን መታ ወይስ ሳተ?

Dalai Lama

እኚህ ብፁእ ሰው ስለ Buddhism እንድንናገር ያነሳሱናል፡፡ ጌታ ቡድሀ የህይወትና የሞት መቆራኘት ሚስጥር ከተገለፀለት በኋላ፣ መንገዱን አስተማረን፡፡ እና ይህን እዚች ምድር ላይ እየደጋገሙ እየተወለዱ እየሞቱ መመላለሱን አራግፎ Nirvana ገባ፡፡

ጌታ ቡድሀ ባመላከታቸው መንገድ ሄደው ቡድሀ የሆኑ፣ ግን “እዚች ምድር ላይ የሚንከራተቱት ነብሳት ሁሉ (አንድ ሳይቀር) ኒርቫና እስኪገቡ ድረስ፣ እኔም እንደነሱ እየተወለድኩ እየሞትኩ የቡድሀን መንገድ አስተምራቸዋለሁ” ይላል፡፡ ዛሬ እየኖረ ያለው የTibet ዳላይ ላማ፣ የመጀመሪያ ዳላይ ላማ ለአስራ አራተኛ ጊዜ ተወልዶ ነው ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ “በሚስጥር ታሽጎ፣ በሹክሹክታ የታወጀ፣ በእንቆቅልሽ የተጠቀለለ ሀቅ አለ” የጥንት Scotland መኳንንት ሚስጥር

ይህ ሚስጥር በሞት የታጠረ ነበር! ለታሪካዊ መረጃ (information) ያህል፣ ኢንግላንድ እገዛለሁ ስትል፣ ስኮትላንድ በሽምጥ የአርበኞች ውጊያ እየተከላከለች ነበር፡፡ ጦርነት ካለ ደግሞ ሀገሩን የሚሸጥ ሰላይ አይጠፋም፡፡ ሰላዩ ሲጋለጥ፣ መኳንንቱ አድፍጠው ጠብቀው ለብቻው ይከቡታል፡፡ እና እያንዳንዱ መኳንንት ሰይፉን ይከትትበታል፡፡ አንድ (ቢበዛ ሁለት) ጊዜ መውጋት ይበቃ ነበር፡፡ እንድያማ ከሆነማ አንዳቸው በአጉል የድክመት ሰአት “እኔ’ኮ ያን ሰው አልወጋሁትም!” ሊል ይችላላ! ስለዚህ የእያንዳንዳቸው ሰይፍ በደም መነከር አለበት! ሰአሊ ለነ ቅድስት አሜን፡፡

Mark Antony እና ሌሎቹ

አዝማሪው Shakespeare (“ጦር ነቅንቅ”!) በመድረክ ሲያቀርበው፣ ማርክ አንተኒ የጁልየስ ሲዛር ታማኝ ቀኝ እጅ ነው፡፡ የዋህ ሁነኛ ጓደኛ! የታሪክ መዛግብትን ያገላበጡ ሊቃውንት ሲነግሩን ግን፣ ማርክ አንተኒ እና ግብር አበሮቹ የመንግስት ካዝና ባዶ ሆኖ አገኙት፡፡ ስለዚህ ስንት ሚልዮን Sestersis (የቄሳር መልክ የታተመበት የወርቅ እንክብል) እንደሚያስፈልጋቸው ስሌት አወጡ፡፡ ከየት ያምጡት? ዙርያውን ቢመለከቱ፣ ያን ያህል ሚሊዮናት ሊገኝ የሚችለው Senators ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ሚሊዬነር ናቸዋ! (እንደ ዛሬው አሜሪካ ሴነተሮች ማለት ነው) ስሌታቸውን ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ከሁሉ ሀብታም የሆኑት የመጀመሪያዎቹ ሀያ ሴነተሮች  ሀብት በቂ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ምን አደረጉ? ሀያውን ባለፀጋ ሴነተሮች “ሀገር ከዳተኛ ናቸው” ሲሉ ክስ መሰረቱባቸው፡፡ የውሸት ምስክሮች አመጡባቸው፡፡ ክህደታቸው ተረጋገጠ፣ ንብረታቸዉ ተወረሰ፣ እነሱ ተገደሉ፡፡ ይሄ “ቆራጥ” እርምጃ የፖለቲካ ዘግናኝ ሀሁ ያስተምረናል ከሩቅ፡፡

Cardinal Richelieux ሊገድሉህ ከፈለጉ

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ስነ ስርአት መሰረት፣ በመንፈሳዊ ስልጣን ተዋረድ፣ Cardinal የሚቀጥለው እድገቱ ጳጳሳት ነው፡፡ (አንዱ ጳጳስ ሲሞት ካርዲናሎቹ ከየአገሩ ወደ ሮማ ተሰብስበው፣ ከነሱ አንዳቸው በድምፅ ብልጫ ሳይሆን፣ በሙሉ ድምፅ ተመርጦ ጳጳስ ይሆናል፣ የሀዋርያው ስምኦን-ጴጥሮስ ቀጥተኛ ወራሽ፡፡ ካርዲናል ሪሸልየ እኛ በማናውቀው ምክንያት መንፈሳዊውን ህይወት በነብሳቸው ውስጥ እየኖሩትም፣ በምድራዊው ህይወታቸው ግን “ፀሀዩ ንጉስ” የሚባለው የLouis the Fourteenth ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለረዥም ዘመን አገለገሉ፡፡ በመላው ኤውሮፓ ታሪክ ውስጥ ከሳቸው እኩል ብልህ አስተዳዳሪ ታይቶ አይታወቅም ተብሎ ተመስክሮላቸዋል፡፡  በሀገር ደህንነት ጥበቃ ጉዳይ አንዱ ከሀዲ ባለስልጣን ላይ ክስ ሊመሰርቱበት አሰቡ፡፡ “እሱስ ጥሩ ነበር” አላቸው አንዱ ጭፍራቸው “ግን በቂ መረጃ የለንም” “ምንም መረጃ አያስፈልገንም” አሉት “እንኳን እሱን ቀርቶ፣ ማንንም ግለሰብ መወንጀል ይቻላል፡፡ ከፈለግህ ከገጠር መንደር የተላከ ደብዳቤ ከፖስታ ቤት በአቦ ሰጡኝ ስበህ አምጣልኝ፡፡ እዚያ ፅሁፍ ውስጥ ስቅላት የሚያስፈርድበትን ወንጀል ላገኝበት እችላለሁ” አሉ አንድዬ ካርዲናላችን!

ፀሀዩ ንጉስ Louis the Fourteenth

ሰውየው በጣም የተለየ ፍጡር መሆኑ ገና አራስ ልጅ እያለ ያስታውቅ ነበር፡፡ አብዛኛው ልጅ የአንዲት እናቱ ጡት ያሳድገዋል፣ በቂ ነው ይባላል፡፡ ይሄኛው ግን ሶስት አራስ ሴት እየጠባ ማደግ ነበረበት (የንግስት እናቱ ጡት እንዳይወድቅ ተብሎ፣ ሶስቱም አጥቢዎቹ ጡታም ወተታም መሆናቸው ታይቶ ነው የተመረጡለት፡፡ ተመራጮቹ የወለዱት ህፃንስ ምን ይጥባ? የራሱ ጉዳይ!  (ንጉስ ለእንዲህ አይነቱ ጥቃቅን ጉዳይ ጊዜ የለውም፡፡ እኛም የለንም)  ሉዊ አስራ አራተኛ በጉልምስና አመታቱ “የሀገሩን የቆዳ ስፋት” በጦር ሀይል አንድ አስረኛ ጨምሮ አሳድጎታል (አብዛኛው የተነጠቀው ከኢጣልያ እጅ ነበር) በእድሜ እየበሰለ ሲሄድ፣ ሀገር የማስተዳደሩን ጉዳይ Cardinal Richelieu እየተሸከሙለት፣ እሱ ፓሪስን ወደ ማስዋብና ምግቦችን እያጣጣሙ ለመኳንንቱ ከፍ ባለ መድረክ ላይ እየታዩ ለመደነቅ ያውለው ነበር፡፡ ከዚያን ዘመን ፓሪስ ትንሽ ወጣ ብሎ Ve’rrsailles ቤተ መንግስትን አሳነፀ፡፡ በጥንት ዘመን ተገንብቶ ቢሆን ኖሮ፣ ከሰባቱ የአለም ድንቅ ስራዎች እንደ ስምንተኛው ሆኖ በተሰለፈ ነበር፡፡ ሉዊ አስራ አራተኛ dinner (የእለቱ ዋና ምግብ) ሲበላ በጥበብ ነበር፡፡ (ሆዱ ከተራው ሰው ሶስት እጥፍ መብለጡን እያስታወስን፡፡) ለመጡት መኳንንት የምግብ ዝርዝር (Menu) በየቦታቸው ይቀመጥላቸዋል፡፡ ግብዣው በዘጠኝ ሰአት አካባቢ የተጀመረ ሲበላ፣ ሲጠጣ፣ አንዳንዴም ሙዚቀኞች ተስማሚ ዜማ እያስደመጡ፣ እስከ ማታ አንድ ወይ ሁለት ሰአት ሊቀጥል ይችላል (እንደ ወራቱ ይለያያል)

መቸስ ዝምብና ነጋዴ እማይገባበት የለም፣ ከግብዣው አዳራሽ ወጣ ብሎ የመኳንንት ሙሉ ልብስ ይሸጣል፡፡ ነጋዴዎች ልብሱን ተከራይተው ወደ ግብዣው መጥተው፣ ከፀሀዩ ንጉስ ራቅ ብለው ይቀመጣሉ (መልካቸው አዲስ ሆኖበት “ማን ነዎት እርስዎ?” ብሎ እንዳያፋጥጣቸው ይህን ሁሉ አይነት ምግብ የሚያዘጋጀው chef (የወጥ ቤት አዛዥ) ምን አይነት ሰው ነበር ይሆን? አንዲት መረጃ አለች፡፡ ሰውየውንም ፀሀዩ ንጉስንም እንደ ፎቶግራፍ ብልጭ አድርጋ የምታሳየን፡፡ የምግብ ዝርዝሩ ላይ አንድ ከሩቅ ባህር የሚያስመጡት ብርቅ የሆነ አሳ ነበረ፡፡ በባህር ማእበል ምክንያት በተባለበት ሰአት ለጥብስ ሊደርስ አልቻለም፡፡ ጥፋት አላደረሰም ነበር፡፡ ግን የፀሀዩ ንጉስ ቃል እንዴት ሊታጠፍ ይችላል? Chef ንጉሱን ይቅርታ ለምኖ ወጥቶ፣ በገዛ ራሱ ታንቆ ሞተ፣ ነብስ ይማር፣ ሰአሊ ለነ ቅድስት አሜን፡፡

መልካም የገና በዓል!!

 

 

Read 4022 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 13:48