Friday, 06 January 2012 11:19

ሙሽራ የገና ስጦታ

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(0 votes)

ቅዳሜ ዕለት ገናን እናከብራለን፤ ታህሣሥ 28 ቀን 2004 ዓመተ ምህረት ወይም እሁድ ዕለት ታህሣሥ 29 ቀን 2004 ዓ.ም፡፡ ለምሣሌ በላሊበላ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ሁልጊዜ ገናን ታህሣሥ 29 ቀን ነው የሚያከብሩት፡፡ ሌሎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ከዘመን መለወጫ ጋር በተያያዘ ገናን በየአራት ዓመቱ ታህሣሥ 28 ቀን ያከብሩታል፡፡ ሁልጊዜ ገናን ታህሣሥ 29 ቀን የሚያከብሩት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችም አሉ፡፡  ኢየሱስ ክርስቶስ ከተመሰለባቸው አገላለፆች አንደኛው የዚህ ፅሁፍ ርዕስ የሆነው ሙሽራ የሚለው ነው፡፡

ሙሽራው፡- የሚመጣ ወይም የሚጠበቅ ነው፤ በክርስቲያን ሥነ መለኮት ሊቃውንት አተናተን፡፡ የገና በዓል የሙሽራውን መወለድ ምክንያት አድርጐ በያመቱ በበርካታ የመላው ዓለም ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በተድላና በደስታ የሚከበር ደማቅ የክርስቲያኖች ዓውደ ዓመት ነው፡፡ በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ የሙሽራውን መወለድ የሚያበስረው፡- እነሆ አዳኛችሁ በዳዊት ከተማ ተወለደ … ብሎ ነው፡፡ ዶክተር ደረጀ ከበደ የሚባል ዓለም አቀፍ የዝማሬ አገልግሎት የሚሠጥ ኢትዮጵያዊ፡- የሚመጣ … የሚል መዝሙር አለው

የሚመጣ የሚነግሥ

ኢየሡሥ . . .

ቅድስት ድንግል ማርያምና እጮኛዋ ዮሴፍ በመንገድ ላይ ጉዞ እያደረጉ ሣሉ ስለመሸባቸው ወደ አንድ መንደር ጐራ አሉ፤ የመንደሩ አሳዳሪዎች በርካታ እንግዶች ስለነበሩባቸው ማርያምና ዮሴፍን በእንሥሣት ማደሪያ የከብት በረት ውስጥ አሳደሩዋቸው፡፡ በዚያ ሌሊት በመንፈሥ ቅዱስ ኃይል ከድንግል ማርያም ተፀንሶ ዘጠኝ ወር በድንግሊቱ ማህፀን የቆየው ህፃን ተወለደ፡፡ ከብቶቻቸውን ሲጠብቁ የነበሩ እረኞች (ሠባ ሠገሎች) በክዋክብት ተመርተው የሙሽራውን ልደት (መወለድ) በታላቅ ብሥራት ለመረዳት ቻሉ፡፡ እዚህ ጋ ኢየሡሥ ክርስቶስ ህፃኑ ሙሽራ ነው፤ በጥንት ነቢያት በኦሪት መፃህፍት የተስፋ ቃል የተፃፈለት ህዝቡን አርነት ያወጣ ዘንድ ይመጣል ተብሎ ለአያሌ ሺህና መቶ ዘመናት ሲጠበቅ የኖረ ህጻን ሙሽራ፡፡

በጥናት ላይ የተመሠረተ ግምት ካልሆነ በቀር በመሠረቱ ኢየሡሥ ክርስቶስ የተወለደበትን ትክክለኛ ቀን የሚያውቅ ማንም እንደሌለ የነገሩኝ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ካርዲናል ጳውሎስ ፃድዋ ናቸው፡፡ ይሁንና፡- ሮማውያን ከክርስቶስ መወለድ በፊት በያመቱ December 25 የፀሀይን አምላክ በማምለክ ያከብሩት ነበር፤ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከርሱ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚበልጥ ፀሀይ እና ብርሀን የለም ብለው ለፀሀይ አምላክ የሚያመልኩበትን ዕለት የክርስቶስ ልደት አደረጉት፡፡

መነሻችን ገና ሆነ እንጂ ሙሽራ የሚለው ቃልና ፅንሠ ሃሣብ በሌላም የተለያየ አገባብና አቀራረብ አለ፡፡ ይኸውም እንዲህ ነው፡-

ፍልቅቅ ብሎ ያልተዘረጋው የእንሠት መሀከለኛው ክፍል፡- ሙሽራ ነው የሚሰኘው፡፡ ጥቂት ቀናት ከጠበቅነው ሙሽራው ፍልቅቅ ብሎ በሠፋፊ ቅጠሎቹ ግራና ቀኝ ይዘረጋል፡፡

ሙሽራ፡- የኢየሱስ ክርስቶስ ተምሣሌት ነው ተብሏል፤ እንዲሁም ደግሞ በሌላ አተያይና አቀራረብ ሙሽራ አለ ብሎ መቀጠል … የዘንድሮውን ገና ወይ ሙሽራ ለየት ባለ አገላለፅ ለማየትም ጭምር ይጠቅማል፡፡

በሠብዕና (Personality) እውቀትና ጥበብ ትንታኔ የአንድ ሠው ትክክለኛው ወይም እውነተኛው ተፈጥሮአዊ ማንነት (Natural Identity) ሙሽራ ነው፤ የሥነ ልቦና ጠበብት ውስጣዊ ማንነት (Inner Core) የሚሉት፤ ወይም የመለኮት ዕውቀት ባለቤቶች ደግሞ፡- ከፈጣሪ ባህሪ ይጋራል የፈጣሪ ክብርና ቅድስና በጐነትና ፍቅር … ይገለፅበታል የሚሉት የሠው ልጅ እውነተኛው ማንነት፡፡ ለምሣሌ አንድ ሌላውን ሰው ለመግደል አቅዶ የጦር መሣሪያውን ደግኖ በመንቀሳቀስ ሊገድለው ያሠበው ሠው ዘንድ ደርሶ መሳሪያውን በማነጣጠር ላይ እያለ አንድ ሌላ የማያውቀው (ሶዎስተኛ) ሠው እጁን ድንገት ቢይዘውና የጦር መሳሪያውን አፈሙዝ አቅጣጫ አስቀይሮ (አስቶ) እጁን እንደያዘ አሥርና አሥራ አምስት ደቂቃዎች ቆይቶ  ቢለቀው ባለመሳሪያው ሊገድለው ባሰበው ሰው ላይ ለመተኮስ በጭራሽ አይሞክርም፤ ለመግደል የነበረውን እቅድና ሃሣብ ሽሮ ወደ ቤቱ ይመለሣል ወይም ወደሚሄድበት ይሄዳል እንጂ፡፡ ሁለቱንም ተቃራኒ ተግባራት ለማድረግ ያሠበው ያቀደውና የሞከረው አንድ አእምሮ ወይም አንድ ሠው ነው፡፡ የመግደል ሃሳቡን የሰረዘው ማንነት፡- እርሱ የዚያ ሠው ሙሽራው ሠብዕና ነው፤ ወይም ድንግል ሠብአዊ ማንነቱ ነው፡፡

ሙሽራ፡- የሠው ልጅ ተፈጥሮአዊ ክቡር ማንነት ነው፤ ማንኛውም ሠው በመጨረሻ የሚደርስበት ድንግል ተፈጥሮአዊ ሠብዕናው፡፡ እዚህ ጋ ፈፅሞ የማይሻሩ ሊሻሩም የማይችሉ ሁለት የዘላለም እውነቶች ላክል፡፡ ይኸውም፡- የሠው ልጅ ከአንድ ታላቅ ፍቅርና እውነት ከአንድ ታላቅ የማይወሰን ዕውቀትና ጥበብ … መጣ፤ ይሄ አንደኛው የዘላለም እውነት ነው፡፡ በመጨረሻ የሰው ልጅ ወደ አንድ ታላቅ የፍቅር ሙላት እና የሚደነቅ ጥበብና እውቀት ይሄዳል፡፡ እርሡም የከፍታዎች ሁሉ ከፍታ የምንለው የላቀው ልቀት ነው፡፡ ይሄንን (እኒህን) የዘላለም እውነቶች ህያውነት፡- የሂንዱም ሆኑ የቡድሃ የክርስትናም ሆኑ የእሥልምና … ሊቃውንት በየራሳቸዉ አቀራረብ ያረጋግጣሉ፡፡ የእኔ ዘር ሥረ መሠረት (root) ከሁለት ምንጮች ይቀዳል፤ አንደኛው ከላይ ከዋቃ (ከእግዚሃር) ነው፤ ሌላኛው ከአገሬ ከኢትዮጵያ ህዝቦች ነው፡፡ መፅሀፍ ቅዱስ ላይ በትንቢተ ኤርሚያስ ምዕራፍ አንድ አምሥት ላይ፡- በሆድ ሣልሠራህ አውቄሃለሁ በማህፀን ሣለህ ቀድሼሃለሁ … የሚል ከባዮሎጂ ሳይንስ ከፍ ያለ ልቀት ተፅፎአል፡፡ በአጭሩ፡- የሠው ልጅ በእናቱ ማህፀን ውስጥ ከመፀነሱ በፊት በህያውነት ነበር ወይም አለ ለማለት ነው፡፡ እንደገና በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ሁለት ሠባት ላይ፡- እግዚአብሄር አምላክ ሰውን ከጭቃ አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የህይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሠውም ህያው ነፍስ ያለው ሆነ … ተብሎ ተፅፎአል፤ በአጭሩ፡- ሠው በባዮሎጂ ሳይንስ አወቃቀርና ቅንብር በእናት ማህፀን ውስጥ ከመታሰቡ አስቀድሞ በእግዚአብሔር ህልውና ውስጥ ነበር ወይም አለ ማለት ነው፡፡ የአምላክ እስትንፋስ ወደ ሰው ውስጥ በገባ ጊዜ የሠው ልጅ ህያው (Eternal) በመሆን የአምላክ ባህሪ ተጋሪ ሆነ ማለት ነው፡፡ በሂንዱ ብሀቫጋድ ጊታ እና በቡድሃ ፒታካስ እንዲሁም በሌሎች ቅዱሣን መፃህፍት የሠው ልጅ ነፍስ እድገት (በተክሎች፣ በእንስሣት፣ በሰው አካል አማካይነት) እስከ ኒርቫና (ፍፅምናና ሀሴት) ድረስ እንደሚቀጥል ተፅፎአል፡፡ አቀራረቡና አገላለፁ ይለያይ እንደሆን እንጂ ይሄ ንድፈ ሃሳብ (Theory) በሌሎችም ሃይማኖቶች እንደዚሁ … ነው፡፡

የሙሽራ ነገር ከተነሣ ከተወሣ አይቀር፤ ሙሽራ፡- እንደ ንጉሥ (King) ሙሽሪት እንደ ንግሥት (Queen) የምትታየው እዚሁ በአገራችን በሶማሌ ብሄር ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ በሶማሊ ብሄር ውስጥ ማንኛውም ለአካለ መጠን የደረሠ የብሄሩ ተወላጅ በህይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ ንጉሥ ይሆናል፡- ይኸውም በሠርጉ ቀን ነው፡፡ ሴትም ከሆነች በህይወት ዘመኗ ቢያንስ አንድ ጊዜ ንግሥት ትሆናለች፡- ይኸውም በሠርጓ ቀን ነው፡፡ ይሄንን ከአዲስ አበባ ደቡብ ምሥራቅ 194 ኪሎ ሜትር መተሀራ አካባቢ በአካል ተገኝቼ፤ ከመቶ ዓመታት በፊት የባቡር ሀዲድ ለመሥራት ከሶማሊ ክልል ወደ ምሥራቅ ኦሮሚያ መጥተው ወልደው ከብደው በተባዙ የሶማሌ ተወላጆች ዘንድ ሆኜ በዓይኖቼ አይቻለሁ፡፡

በጋብቻ ወይ በሠርጓ ቀን ሴት ልጅ ወደቀደመው ህያው አካሏ ትገባለች፤ ጥምረቱ ትክክል ከሆነ ወንድና ሴት እንደ አንድ አካል ይሆናሉ፡- የአንዱ ደስታ ለሌላው፤ የአንዱ ህመም ለሌላው … እስኪሰማ ድረስ አንድ ይሆናሉ፡፡ ሁለት አካል አንድ አእምሮና ልብ ማለት እስኪቻል ድረስ፡፡ …

አንድ ሠው ሙሽራ በሆነ ቀን ለመብረር የሚያስችል የተሟላ ክንፍ ኖረው ማለት ነው፡፡ ካህሊል ጂብራን The Broken Wings (የተሠበሩ ክንፎች) የሚል መፅሀፍ አለው፤ ይሄ ሰው ክንፎቹ እስካልተጠገኑ ወይም ሌላ ክንፍ እስካልኖረው ድረስ ለመብረር አይሞክርም፡፡

The Seven Vallies & The Four Vallies የተሰኘውን መፅሀፍ ከአንድ መቶ ሥድሣ ዓመታት በፊት በኢራን ፋርሥ ፐርሺያ የፃፈው የእግዚሃር መልዕክተኛ (The Messenger of God)   ባሃኡ’ላህ፡- ክንፍ ከሌለህ ለመብረር አትሞክር … ይላል፤ እንዲሁም በሌላ ሥፍራ ደግሞ፡- ትዳር የሌለው ሠው በተገነጠለ ክንፍ እንደሚበር አሞራ ነው … ብሎ ፅፎአል፡፡ ባሃኡላህ በፋርሥ ቋንቋ፡- የእግዚአብሄር ክብር (The Glory of God) ማለት ሲሆን፤ ዛሬ በመላው ዓለም የሚገኙ ባሃኢዎች ሰላምታ ሲለዋወጡ፡- አላህ ኡ አብሃ … ተባብለው ነው፤ ትርጓሜውም He is the most Glorious ወይም እርሱ ከተከበሩት ሁሉ በላይ እጅግ የተከበረው ነው … ማለት ነው፡፡ ባሃኡላህ በአጠቃላይ 110 መፃህፍት ፅፎአል፡፡

ሙሽራው በተሟላ ጥንድ ክንፍ መብረር የሚጀምረው በሠርጉ ቀን ነው፤ ስለ ክንፍ ከተነሳ አይቀር ትንቢተ ኢሣያስ ስምንት ስምንት ላይ፡- የክንፉ መዘርጋት ምድርን ይሸፍናል ይልና አክሎ አርባ ሠላሣ አንድ ላይ፡- እግዚአብሄርን ተስፋ በማድረግ የሚጠባበቁ ሁሉ ኃይላቸውን ያድሣሉ፤ እንደ ንሥር በክንፍ ይወጣሉ ይሄዳሉ፤ አይታክቱም ይሮጣሉ አይደክሙም

በሠው ልጆች የብዙ ሺህ ዘመናት ታሪክ ውስጥ ሙሽራ ሆነው ከማያውቁ ታላላቅ ሠብእናዎች አንዱ ሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡- … እንደኔ እንደኔ … ይላል ጳውሎስ በመልዕክቱ … እንደኔ እንደኔ ባታገቡ ይመረጣል፤ በምኞት ከመቃጠል ግን ማግባት የተሻለ ይሆናል፡፡

Birds of the same Feather fly together የሚል አውሮጳዊ ይትበሃል አለ፡፡ ተመሣሣይ ላባ ያላቸው ወፎች በአንድነት ይበራሉ፡- ይሄ ሠሙ ነው፡፡ ወርቁ፡- በጣም የሚግባቡ ትክክለኛ ጥምረት ያላቸው ሙሽራና ሙሽሪት ሁለት አካል አንድ ልብ እስኪመስሉ ድረስ የሠመረ ቅንጅት ይኖራቸዋል … የሚለው ነው፡፡

ከማናቸውም ታላቅ ሠብዕና ካለው ወንድ ጀርባ ሁልጊዜ ጠንካራ አንዲት ሴት አለች ይላሉ ፈረንጆች፤ ለሥኬቱና ለታላቅነቱ ወሣኙን ሚና የምትጫወተው እርሷም ናት እንደ ማለት፡፡ ይህም እርሡ  ያ ታላቅ ሠብዕና ሙሽራ በሆነበት ቀን እውን መሆን ይጀምራል፡፡

ኢየሡሥ ክርስቶስ ሲወለድ፡- ህፃን ሙሽራ ነው፤ ከተሠቀለ ከሞተና ከተቀበረ በኋላ ሞትን አሸንፎ  እንደሚመጣ ሲጠበቅም ሙሽራ ነው፣ ከሞት ከተነሣ በኋላ አርባ ቀን በምድር ላይ ቆይቶ ወደ አባቱ ካረገና ከአብ በቀር ሌላ ማንም (ኢየሡሥ ራሱም ቢሆን)  በማያውቀው ጊዜያትና ቅፅበት ተመልሶ በኃይል በደመናት እንደሚመጣ ሲጠበቅም፡- ሙሽራ ነው፡፡ ዛሬ በመላው ዓለም የሙሽራውን ዳግም ምፅአት በታላቅ ተስፋ የሚጠባበቁ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያኖች አሉ፡፡

ሙሽራው ተመልሶ እንደሚመጣ የሚያምኑ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ሃይማኖቶችም አሉ፡፡

ለአገሬ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ክርስቲያን ምዕመናን በብዙ ፍቅር በከበረ ክብር፤ እጅግ ከፍ ባለ ትህትና እንኳን ለገና በዓል አደረሠዎ፤ መልካም ገና ይሁንልዎ ለማለት ያህል፡፡

ሠላምዎ ይብዛ! በፍቅር!

Soli.Deo.Glorai!

 

 

Read 3634 times Last modified on Friday, 06 January 2012 11:31