Saturday, 13 December 2014 11:14

ራሄል ጉዲት

Written by  ጆኒ
Rate this item
(8 votes)

      የሰው ልጅ ዛሬ ከደረሰበት ወይም ከቆመበት ቦታ ታሪኩ አይጀምርም፡፡ ወደ ኋላ የሚተረተር፣ የሚጎለጎል ቱባ መምጫና መገለጫ አለው፡፡
እነሆ ታሪክ …
አባቴ እናቴን አገባት፡፡ ክብር ዘበኛውና የቤት እመቤቷ ተጋብተው ሲወልዱ - ሲወልዱ - ሲወልዱ - ሲወልዱ - ሲወልዱ … አስራ ስድስተኛ ልጃቸውን እኔን ወለዱ፡፡ ለኔ መወለድ - እናቴ እንቁላሏንና ማህፀኗን ስታዋጣ፣ አባቴ ደግሞ የዘር ፍሬውን አበረከተ፡፡ ከተወለድኩ በኋላም እናቴ ጡቷንና ጀርባዋን ስትቸረኝ - አባቴ ገንዘቡን፡፡ እናቴ - አባቴን አራት ለሁለት ስለምትመራው ነው መሰለኝ -- ለሷ ያለኝ ፍቅር እንደ ምድር ያለ ካስማ፣ እንደ ሰማይ ያለ ባላ የፀና ነው፡፡
ዛሬ አድጌያለሁ …
ያደገ ሰው አባወራ ለመሆን እቤቱ ውስጥ እማወራ ያሳድራል፡፡ እቤቴ የምታድር እማወራ የለችኝም - የምትመላለስ ግን አለችኝ፡፡ ራሄል ስሟ ነው፡፡ ራሄል ቆንጆ ነች፡፡ ራሄል ሁሌም ሌላ ራሄል ነች፡፡ ራሄል ሁሌም ግራ ታጋባኛለች፡፡ በማይለወጥ ቆንጆ መልኳ፣ እንደ እስስት በየሰከንዱ አዳዲስ ሰብዕና  እየተላበሰች፣ ይኼው ግራ ስታጋባኝ አምስት ዓመት ሞላኝ፡፡ ፍቅር ማለት እሷን ለማወቅ የማደርገው ጥረትና በየዕለቱ የምገባው እልህ እስኪመስለኝ ድረስ፡፡
የዛሬ ፊቷን ለጣረ ሞት አምስት ጉዳይ ሲቀረው ነው ይዛው የመጣችው፡፡ እንዲህ ሆና ደግሞ አይቻት አላውቅም፡፡ ደግሞ ዛሬ ምን ገጥሟት ይሆን? ምላሷ ሳይበጠር፣ እንደተንጨፈረረ አፏ ዋሻ ውስጥ ተቀምጧል፡፡ እንደፈራሁት ሳታበጥረው ወሬ ጀመረችበት፡፡
“ካንሰር ይዞኛል!”
“ምን!?”  አልኩ፡፡ ሳልሰማት ቀርቼ አይደለም፡፡ እንኳንስ ድምጿ የሆዷ ጉርምርምታ ሳይቀር በሚሰማኝ ርቀት ላይ ነው ያለሁት፡፡ ግን ያለችው ምንም አልገባኝም፡፡
“አይገባህም!? የጡት ካንሰር ይዞኛል፡፡ እንዴት ይሄ በሽታ ለኔ ይሆናል?  እኔ እኮ ዮዲት ጉዲት ሳልሆን ውቧ ራሄል ነኝ፡፡ ለተቆረጠ ጡቴ መበቀያ - የማቃጥለው ቤተ መቅደስና የማሳድደው ካህን የለኝም…” ወይ ራሄል ጉዲት! ዛሬ ደግሞ እንዴት ያለ ወሬ ነው ይዛብኝ የመጣችው!? አንገትም ሆነ  ጅራት የለውም እኮ፡፡ ምንድነው የምላት? ለሚቆረጥ ጡት የሚሆን ማፅናኛ እንዴት ያለ ነው … ልግጠም ይሆን?
ልጅ እያለሁ፣ አልቅሼ እናቴ ስታፅናናኝ ወይም ተነጫንጬ ስታስተኛኝ፣ በዜማና በግጥም ነበር፡፡ ሞልቶ የገነፈለ የፍቅር እመቤት ስለነበረች፣ ዜማና ግጥም ለማፍለቅ የምናብ ዳረጎት ወይም ብድር አያስፈልጋትም፡፡
ለዚህም ይመስለኛል ለግጥም ቅርብ የነበርት፡፡ ይሄንን ቅርበቴን  ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነዘብኩት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነበር፡፡
እንደ አማርኛ የፊደል ገበታ  - በቀላሉ የማይለመድ ፊት ነበራቸው፡፡ ሀ - ላይ ፈግገው፣ ሁ - ላይ ይዳምናሉ - የአምስተኛ ክፍል የአማርኛ መምህራችን፡፡ እንደ ዛሬ - ለበነጋው ሰርተነው የምንመጣው የቤት ስራ አዘዙን፡፡ የቤት ስራው ግጥም ነበር፤ ግጥሙ ደግሞ ስለ ወፍ የሚተርክ መሆን አለበት አሉን፡፡
በበነጋው ስለ ወፍ የሚተርከውን ግጥም ፅፌ የተገኘሁት ተማሪ እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ምድረ የአምስተኛ ክፍል ውሪ ሁላ …ስለ ትረካ ምንነት የት ታውቅና - እንኳን ስለ ወፍ መተረክ ቀርቶ፡፡
አማርኛ መምህራችን እኔን አመስግነው… አሞጋግሰው …ሌላውን በጉማሬ (በእንስሳው ሳይሆን ባለንጋው) ሶስት ሶስቴ ቂጥ ቂጡን ገሽልጠው ሲያበቁ …ስለ ወፍ የሚተርከውን ግጥሜን ወጥቼ እንዳነብ ጋበዙኝ፡፡
ወጥቼ አነበብኩ…
በጠፍጣፋ ድንጋይ ከተዘጋ በሩ
እናት አትገኝም እንደ ወፍ ቢበሩ፡፡
አንብቤ ሳበቃ የጓደኞቼ ጭብጨባና የመምህሬ ሁለት ኩርኩም ተበረከተልኝ፡፡
ዛሬ አድጌያለሁ ብያለሁ … ያደገ ሰው ነኝ፡፡ ያደጉ ሰዎች አንብበው የሚረዱት፣ የሚወዱትና እኔንም የሚያደንቁበት ግጥም እፅፋለሁ፡፡ ያደጉ ሰዎች በስመጥር ገጣሚነቴ ነው የሚያውቁኝ፡፡ ቤቴ የምትመላለስ እማወራዬ ደግሞ ስለ መሞት እያወራችኝ ነው፡፡ ስለ ህመሟ ግጥም መፃፍ እንጂ ከህመሟ ልፈውሳት እንደማልችል እያስገነዘበችኝ ያለች ትመስላለች፡፡
አውቃለሁ - መፈወስ ፈጠራ ይጠይቃል፡፡ ፈጠራ ከምንም ነገር ውስጥ የሆነ ነገርን ማስገኘት ነው፡፡ እንዲታወቅልኝ የምፈልገው ነገር ግን ፈጠራ አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እግዜሩስ  ቢሆን አዳምን ብቻ አይደለም እንዴ የፈጠረው፡፡ ከአዳም ወዲህ - ከሔዋን ጀምሮ ሰው ፈበረከ እንጂ አልፈጠረም እኮ!? እኔም ገጣሚው - ግጥም የፈጠርኩት ያኔ ነው፡፡ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ - ይኸው እስከ ዛሬ የግጥም መፈብረኪያ ማሽን ሆኜአለሁ፡፡
ራሄል ጉዲት - ባልተበጠረ ምላሷ ማውራቷን ቀጥላለች…
“…ሞቴ በእቅዴ ኩሬ ውስጥ ረግቶ የሚኖር ታዛዤ ነው … ሞቴ እንደ ደራሽ ውሃ ድንገት ከተፍ ባይ አይደለም፡፡ እንድታውቀው የምፈልገው ነገር ግን ጡቴን አስቆርጬ፣ ወንድ ደረት ሆኜ መኖር እንደማልፈልግ ነው…”
ኧረ ቆይ - ጡት ምንድነው!? እስከ ዛሬ ስለ ጡት ምንም አይነት የተለየ ነገር አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ የምር ግን የራሄል ጡት፣ ከጡት የዘለለ ምንነት አለው እንዴ?
አዎ! አለው፡፡
እና ጡት ምንድነው?
ጡትስ ራሄል ነው… ጡትስ ራሄል ነው፡፡
ራሄል እያወራች - እኔ እንዲህ በሀሳብ እዳክራለሁ!!
“…አይዞሽ ራሄል - ይሄ በሽታ ባንቺ ላይ ብቻ የሚደርስ በሽታ አይደለም፡፡ ማለቴ…”
“ባንተ ላይ ይደርሳል!?” አለችኝ  አቋርጣኝ፡፡
“ማለቴ… ያው በሌሎች ሴት እህቶቻችንም ላይ የሚደርስ ነው ብዬ ነው…”
“እኔ ሌሎች ሴት እህቶቻችሁን አይደለሁማ - እኔ ራሄል ነኝ” አለችኝ፡፡    
“ይገባኛል! ይገባኛል ራሄል -- ግን በደንብ አስቢው እስቲ… ለአንድ ጡት ይሄን ያህል መሆን የለብሽም … ደግሞስ - ዘንድሮ ምን ጡት አለና ነው እንዲህ መጨነቅ መጠበብሽ --- የዘንድሮ ሴቶች ከወንዶች የሚለዩት እኮ ደረታቸው ላይ ባለች ብጉንጅ የምታክል አጎጣጉጤያቸው እኮ ነው … እናም…”
አሁንም ሳታስጨርሰኝ “ጡትን እንዴት አባህ ነው ያየኸው አንተ!? ለደነዝነትህ ልክ አጥተህለት አልተገለጠልህም እንጂ ሴት ልጅ እኮ ጡቷን ነች፡፡ ጡት ማለት - ለሴት ልጅ ባሏን ማሰሪያ ገመዷ -- ከስሯ እንዳይወጣ ማድረጊያዋ… የማያልቅ የስኳር፣ የመጣፈጥ ተራራዋ ነው፡፡ በልጆቿ ልቦና ውስጥ ደግሞ እናት አማልክት ሆና የምትኖርበት ነው፡፡ ይገባሃል!? እድሜ ልካቸውን - ማን እንደ እናት - እያሉ እንዲኖሩ ማድረጊያ ምትሃቷ ጡቷ ነው…”
“እምልሽ - ጡት ካሉሽ በርካታ ሴትነትሽን ከሚገልፁ አካሎችሽ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እሱ ቢጎድልም…”
ራሄል ወሬዬን ልታስጨርሰኝ አትችልም
“ባይኖረኝም መኖር እችላለሁ አይደል!? እንዲህ ልትለኝ ነው ያሰብከው? አንተ ደደብ! ደደብ መሆንህን ስታቆም እመጣለሁ” ብላኝ ነበር የምትወጣው - ከላይ ያሰብኩትን ባወራት፡፡ ደግነቱ - የሰው መታደሉ አእምሮው ምላስ አልባ መሆኑም ላይ አይደል፡፡
አንዳንድ እውነት ደግሞ - እውነት ነኝ የሚለው -- እንደ ፈሪ ጀግና መሆን አይነት -- ወቅትና ክስተት ጠብቆ ነው፡፡ እስቲ አሁን ማ ይሙት፣ እኔስ ሆንኩ ራሄል  ከዛሬ በፊት ስለ ጡት እንዲህ አይነት አመለካከት ኖሮን ያውቃል? ጡትስ - ይኼን ያህል የመግዘፍ አቅም እንዳለው ገምተን እናውቃለን? በካንሰር አስታክኮ - ጡት ብቻ ሳልሆን - ሙሉ ራስሽን - ሙሉ አንቺን ነኝ ብሏት እርፍ አለዋ፡፡
እና እኔ ምን አባቴ ላድርጋት!?  ራሄል ጉዲት ከክፉ ቀን ከብዳ እያስጨነቀችኝ ነው፡፡ በህይወቴ የምጠላው ነገር ቢኖር ደግሞ ጭንቀትን ነው፡፡ በእስከዛሬው ሕይወቴ - እንግዲህ የዛሬውንም ጭምር ደምሬ መሆኑ ነው - የማልረሳቸው ሁለት ጭንቀቶች ውስጥ ዳክሬያለሁ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሁለቱም በሴት ሳቢያ የመጡ መሆናቸው ነው፡፡
የመጀመሪያው ጭንቄ የተወለደው፣ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነበር፡፡ ልክ እንደ ራሄል - ቆንጆና ግራ የነበረችዋን ሰብለን አፍቅሬ፡፡ ቤተሰቦቼ ከአስራ አምስት ልጅ ተርፏቸው - ለኔ ለብቻዬ የሚሰጡኝ የተለየ ፍቅር አልነበራቸውም፡፡ እናም በየደረስኩበት እፈልገዋለሁ፡፡ የተለየ ፍቅር የሚሰጠኝን ሰው በታላቅ ሀሰሳ ነበር የማፈላልገው፡፡ ያገኘሁ ሲመስለኝ ሁሉ ነገሬ ወከክ ብሎ ይከፈታል … እናም አፍቃሪ ነበርኩ፡፡
ልጅት ማፍቀሬን አውቃለች፡፡ አጠገቧ ስደርስ - የተቆጣች ቆቅ ትሆናለች፡፡ እንኳን ተቆጥታ ቆቅ እኮ ቆቅ ነች፡፡ የፊቴን ግርታ ስትመለከትና ስትንጨፈረር፤ ልቤ ውስጥ የሆነ … ነፍሴ የምትባለው እረቂቅ ሕዋሴ ውስጥ -- ግዙፍ ያመድ ተራራ ያለ ነበር የሚመስለኝ …መላ አካሌ እንደ አሞሌ ነጥቶ ፊቷ የቆምኩ ያህል ይሰማኛል፡፡ መሸበሬ ይገባታል --- ጅምር ቆቅነቷ መርበድበዴን ሹክ ብሏታል … ከቆንጆ  ለጋ አይኗ ውስጥ እንደ ጅራፍ - አወፍራ በገመደችው የቁጣ መብረቋ -- መንፈሴን ነበር የምትለጠልጠው፡፡ ያ - የመንፈስ ግርፋቴ ያወጣው ሰንበር፣ ዛሬም ድረስ የጠፋ አይመስለኝም፡፡ አሃ! ባይጠፋ ነው እንጂ …እንደውም በራሄል የጡት አስኮርባጅ - የካንሰር ጉማሬ አዲስ ጓደኛም ተጨመረለት፡፡
ጨንቆኝ ነበር፡፡ ጠብቦኝ ነበር፡፡ የምሆነው የምሰራው ጠፍቶኝ ነበር፡፡ በኋላ ላይ በአንድ ጓደኛዬ አይዞህ ባይነት -- መንደራችን ውስጥ ደብዳቤ በመፃፍ ለሚታወቅ  ልጅ - ስፈራ ስቸር ሄጄ ፍቅር እንደያዘኝ ነገርኩት፡፡ ስለ ፍቅሬ ደረጃም ሆነ ስለ ልጅቷ ማንነት መጠየቅ ሳያስፈልገው ደብዳቤውን ፃፈልኝ፡፡
“ሙሴ የያዘው በትር እባብ ሆነ -- የባቢሎን ግንብ ፈራረሰ -- የግብፅ ከተሞች በፒራሚድ አጌጡ -- የዳዊት ወንጭፍ ግዙፉን ጎልያድ ጣለች --- አንዳንዴ - በሕይወት ውስጥ የማይሆን የሚመስለን ነገር ሁሉ ይሆናል፡፡ የኔም አንቺን ማፍቀር እንደዚያው ነው እንዳያልቅ - እንዳይደረስበት ሆኖ የተዘረጋው፡፡ ሰፊ ሰማይ - አገርሽ ነው፡፡ ሰማዩ እንብርት ላይ ብቻዋን እንደረጋች ኩንስንስ ሴት ወይዘሮ --- በክብነቷ ተኩራርታ የተቀመጠችው ጨረቃ አንቺ ነሽ፡፡ ከዋክብት ለክብርሽ ጠብ እርግፍ የሚሉ ደንገጡሮችሽ…” ምናምን እያለ የሚቀጥል ደብዳቤ ፅፎ ሰጠኝ፡፡ ክፍያ ነበረው - ሦስት ኒያላ ገዛሁለት፡፡ ስንቀጠቀጥ ሰነባበትኩና ወስጄ ሰጠኋት፡፡ ከጓደኞቿ ጋ ሆና (ምናለ ብቻዋን ሆና ብታነብበው - የሰጠኋት የግሌን ሕመም) አንብበው ሲያበቁ መውረጃ በሌለው የሳቅ አንቀልባቸው አዘሉኝ፡፡
አስጨነቁኝ፡፡ መግቢያ ቀዳዳ አሳጡኝ፡፡ ሳቃቸው የደረስኩበት ይደርሳል፡፡ የረገጥኩበት - ቀድሞኝ አለሁ ባይ ሆነብኝ፡፡ የምገባበት ሲጠፋኝ --- እቤቴ ገብቼ ግጥም ፃፍኩ፡፡
እኔስ መሞቴ ነው ባንቺ የተነሳ
የምን ሰው ገጠመኝ ጥይት የማይበሳ … (ው)
ያኔ ቤት የማይመታ ግጥም መጻፍ የሚቻል አይመስለኝም ነበር፡፡
 “ው” የምትለዋን ፊደል የጨመርናት ለዚህ ፅሁፍ ማሟያ ከደራሲው ጋር ተመካክረን ነው፡፡
ዛሬ አድጌያለሁ… ብያለሁ፡፡
ሀገር ስሜን የሚጠራው --- የተመሰገነ የግጥም ፋብሪካ ሆኛለሁ፡፡ ዛሬ እቤቴ ለምትመላለስ እማወራዬ ደብዳቤ አልፅፍም -- ሰማይም ሀገሯ አይደለም፡፡ ሀገሯ አዲስ አበባ - ላስፋው ካለች ኢትዮጵያ ነው -- ጨረቃም አይደለች --- ሴት ሆና በየቀኑ ሌላ ሰብዕና የምትይዝ ራሄል ነች -- የከዋክብት ቀርቶ የሰው አሽከር የላትም፡፡
ምን ባድግ -- ምን ሀገር ስሜን ቢጠራ -- ምን ደብዳቤ ባልፅፍላት --- ምንም እንኳን - እሷን ሳይሆን በሽታዋን መነሻ አድርጌ (በበሽታዋ ንሸጣ) -- ከሷ በዘለለ ሁናቴ ለአጠቃላዩ የሰው ልጅ (በሰው ልጅ ቋንቋ ሁሉ እፅፍ ይመስል) የሚናገረው አንዳች ነገር ያለው ግጥም ልወልድ ብችልና - በእውቅናዬ ብርሃን ላይ - ሌላ አንድ አዲስ ችቦ ማንቦግቦግ ብችልም ቅሉ -- መጨነቄን ግን አልክድም፡፡
ራሄል ጉዲት - በጡቷ ወሬ -- በዝባዝንኬ ካንሰሯ -- በሞት መጣ ሰበካዋ ምናምኔም ሳይቀራት በጭንቀት ሰቅዛ ይዛኛለች፡፡  እንግዲህ - መሄጃ ሁሉ ቢበዛ መዳረሻው አንድ ከሆነ -- ስንጀምር ያገኘነው - ስናጋምስ ካገኘነው - አጋማሹም ልናገባድድ ስንል ከምናገኘው በምን ይለያል? የሰባተኛ ክፍል ሁኔታዬም - የዛሬ አኳሃኔ -- መድረሻቸው ጭንቀት እስከሆነ ድረስ፤ የይዘትም ሆነ የቅለትና የክብደት ልዩነት የላቸውም፡፡ ምን አባቴ ላድርጋት!? ጨንቋታል - ፈርታለች - ግራ የሚያጋባ ዕልፍ ሰብዕናዋ ብን ብሎ ጠፍቶ - ልሙጥና የተጨነቀች ራሄል ሆና ከፊት ለፊቴ ተቀምጣለች፡፡ መኖር ግን እንዴት ያለ መጨረሻ አልባ -- ሁሉን መሸሸጊያ ዋሻ ቢሆን ነው? ውበቷን ዛሬ ብቻ ሳይሆን - ሁሌም ነበር… የምታውቀው፡፡ ከዛሬ በፊት መደሰቻዋ --- ሌላውን ማንበርከኪያዋ የነበረ ውበቷ፣ ዛሬ ስጋቷ - ዛሬ ሰቀቀኗ ሆኗል፡፡ እንዲህ እንደሚሆን ማናችንም አልጠረጠርንም፡፡
“… ሞት ለኔ አይገባኝም  --- እኔ መኖር እፈልጋለሁ --- እንዲህ በቀላሉ ሬሳ ልሆን? ለምን ሲባል!? ለምን ሲባል -!? ቆንጆ ነኝ - መኖር አለብኝ --- ከኖርኩ ደግሞ ከነሙሉ ውበቴ እንጂ - መጉደል የለብኝም -- ጡቴ መቆረጥ የለበትም -- ጡቴ ተሰልቦ - መክተፊያ ደረት ከሆንኩማ ምኑን ኖርኩት…?” ራሄል እያወራች ነው፡፡ ወሬዋ ግን ለኔ ሳይሆን ከፊት ለፊቷ ተቀምጦ ለሚያዳምጣት እግዜር እያወራች ነበር የሚመስለው፡፡ ጭንቋን ያወራችው -- አጠገቧ ተቀምጦ --- ግራ መጋባቷን የተነፈሰችለት - ሁሉን ቻይ የሆነው እግዜሩ --- የሆነ ነገር እንዲፈጥርላት የፈለገች ትመስላለች፡፡ አጠገቧ ሆኜ የማዳምጣት --- በጭንቋ ሰአትም ከጎና ያለሁት ግን እኔ ነኝ፡፡ ጭንቋን የተጋራኋት --- ለሚቆረጥ ጡቷ የሚሆን ማፅናኛ ለመውለድ ማጣፊያው ያጠረኝ - እኔ ነኝ፡፡ እኔም ሆንኩ --- ካጠገቧ ተቀምጦ የሚሰማት እግዜሩ --- የቱንም አይነት ፈጠራ ብትፈልግ የምንሰጣት አይነት አይደለንም፡፡ ሁለታችንም ፈጥረን ጨርሰናል፡፡ “… አየህ መኖር እየኖርከው እያለ ምንም ማለት ነው -- ቀላልና የሚያሳስብ አይደለም -- በተለይ --- እንደኔ ቆንጆ ሆነህ ከኖርከው… ሁሉ ሲመለከትህ ደስተኛ የሚሆን እየመሰለህ ከኖርከው --- መኖር ዝም ብሎ ከመኖር የዘለለ ነገር ያለው አይመስልህም --- ለካንስ እንዲህ አይነትም መልክ አለውና ታውቃለህ ---!? ሳያዘጋጅህ --- ሳያስጠነቅቅህ የሚያልቅ ነገር እንደ ኑሮ ምንም የለም” ለኔ እያወራች ለኔ አይመስልም ወሬዋ፡፡ አጠገቧ ተቀምጦ ለሚያዳምጣት እግዜሩ እያወራች ያለች ነው የምትመስለው፡፡ እንዴ--- እንዴ!! እኔ እሆን እንዴ እግዜር!? እኔ እሆን እንዴ --- ለዘመኔ መጀመሪያም ሆነ ፍፃሜ የሌለኝ እግዜር!? ስለ በሽታዋ ግጥም መፃፍ እንጂ ከበሽታዋ ልፈውሳት የማልችል እግዜሯ? ፈጠራዬ አንዴ መንጭቶ የደረቀ -- ዛሬ ላይ ከመፈብረክ ውጪ ሌላ ኪን የማላውቅ እግዜሯ እኔ እሆን እንዴ…!?
ብቻ --- ሁላችን እንዲህ ነን፡፡ ሲጨንቀን ማንነታችን የሚገለጥ - ጭንብላችን የሚወልቅ -- የሆነ ወደ ኋላ የሚተረተር --- የሚጐለጎል፡፡ የዛሬ ሕይወታችን ላይ… የሆነ መምጫው ላይ -- መኖር የማይደፍነው -- ራሳችንን አሳልፈን ሰጥተንለታል የምንለው ስራችን የማያክመው -- አጠገባችን ሆኖ የሚያዳምጠን እግዜር፣ የሚያጠግገው እንጂ ጨርሶ የማይሽረው -- አንዳች ሽንቁር የያዝን --- እንደያዝነውም ለማክተም የምንሮጥ ነን፡፡

Read 5413 times