Saturday, 20 December 2014 13:01

ቤተ-ሳይንስ እና ቤተ-ሙከራ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(5 votes)

       የእኛ ቤተሰብ ባለ ሁለት ሀይማኖት ነው፡፡ በአባቴ በኩል የቤታችን ሀይማኖት ሳይንስ ነበር፡፡ የሳይንስ ትምህርችን መውደቅ ሀይማኖት እንደመካድ ነው፡፡ በቤቱ ጣራ ስር አያስኖረንም፡፡ ስለዚህ በተቻለን መጠን ሂሳብን ጥሩ ለማምጣት እንታትር ነበር፡፡ በአባታችን ፊት እኔ እና ወንድሜ እንደ ሳይንስ ዲያቆን ሆነን እናገለግላለን፡፡ እናታችን ስትኖር ግን ሳይንስን እንከዳለን፡፡ የእናታችን ሃይማኖት የካቶሊክ ክርስትና ነው፡፡ ዋናው ነገር ማታ ማታ ተንበርክኮ በመፀለይ ይከናወናል፡፡ የእናታችን ሃይማኖት እንደ አባታችን ሃይማኖት ፈተና የለውም፡፡ በሰርተፍኬታችን ላይ ለፀሎታችን ያገኘነው ወጤት ተመዝግቦ አይታይም፡፡ ስለዚህ በማስመሰል እንወጣዋለን፡፡ እሁድ  ከእናታችን ጋር ቤተክርስቲያን ስንሄድ የቅዳሴውን ሰአት በማስመሰል እናሳልፋለን፡፡ ተንበርከኩ ስንባል እንንበረከካለን…ቁሙ ሲባል እንቆማለን፡፡ የተመሰጥን እንመስላለን፡፡ አለመመሰጣችንን ቄሱም ሆነ እናቴ አያውቁም፡፡ ሳይንስ ላይ ግን ተመስጦ ስናጣ የፈተናው ወጤት ላይ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡
 ውጤቱ ኩርኩም ያስከትላል፡፡ በዚህ በተለያየ ሀይማኖት ውስጥ በአንድ ቤት ጥላ ስር ነው እኔ እና ታላቅ ወንድሜ ያደግነው፡፡ አባቴ እና እናቴ ናቸው ያሳደጉን፡፡ የእነሱ ሃይማኖት በእኛ ላይ እንጂ በእነሱ ትዳር መሀል አንድም እክል ሲፈጥር ተመልክተን አናውቅም፡፡ አባቴ ሳይንስ ሲያስጠናን፣ እናቴ ባሏን ተው! ብላው አታውቅም፡፡ እናቴ አንበርክካ ስታስፀልየን…አባቴ ጣልቃ አይገባም፡፡ እሁድ ቤተክርስቲያን አንጠልጥላ ስትወስደን…ሳይንሳዊ አምልኮው ውስጥ ሊያግተን የሚፈልገው አባቴ፤ አንድም ተቃውሞ አያሰማም፡፡ እንዲያውም…መኪናውን ለእሷ ተግባር ይሰጣል- እኛን አድርሶ እሱ ደጀ ሰላሙን እንዳይረግጥ ተጠንቅቆ ወደ ቤት ወይንም ቤተ ሙከራው ይፈተለካል፡፡ በዚህ ግንኙነት ከልጅነት እስከ እድገት አብረን ዘልቀናል፡፡ “Ace” የጐረቤታችን ልጅ ሀይማኖት ላይ ያለው አቋም ምን እንደሆነ አይታወቅም ነበር፡፡ ቤተሰቦቹ የምን ሀይማኖት ተከታይ እንደሆኑ ገልፆልን አያውቅም፡፡ እኛ ቤት ሲመጣ የእኛ ቤተሰብ ሃይማኖት ተከታይ ይሆናል፡፡ ሳይንስን ከእኛ እኩል ያጠናል፡፡ ከእኛ በላይ ፈተናውን ይደፍናል፡፡ ቤተ-ካቶሊክ ከእኛ እኩል እሁድ እሁድ ይሳተፋል፡፡ ምናልባት ከእኛ የበለጠ ሳያስመስልም አይቀርም፡፡ ግን የ ኤስ ነገር በጣም ማስመሰሉ ሲሰለቸው በጣም አማኝም ሆኖ ሊቀለበስ ይችላል፡፡ በልጅነታችን ወቅት በቤተክርስቲያን ተሞክሮአችን የተከሰተ አንድ ትዝ የሚለኝ አጋጣሚ ነበር፡፡ የካቶሊክ እምነት አማኞች ለአቅመ አማኝ መድረሳቸው የሚረጋገጠው ቁርባን ከወሰዱ በኋላ ነው፡፡ ቁርባን ለመውሰድ ደግሞ ዝግጅቶች አሉ፡፡ ትምህርተ ክርስቲያን መማር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ አንዱ ክረምት (ከሶስተኛ ክፍል ወደ አራት ለማለፍ ስንዘጋጅ) ለቁርባን ትምህርት በቤተክርስቲያኗ ግቢ ከረምን፡፡ እኔ፣ ታላቅ ወንድሜ እና ኤስ አንድ ላይ፡፡ ትምህርቱ በአብዛኛው በመሸምደድ የሚከናወን ነው፡፡ የሸመደድንነውን ስለማወቃችን…ያወቅነውን ደግሞ ስለመረዳታችን የፈተነን የለም፡፡
ሽምደዳው ስለ እግዜር ነው፤ ሽምደዳው በጥያቄና መልስ መልክ በአንዲት ትንሽ መፅሐፍ ተደርጐ በነፍስ ወከፍ ታደለን፡፡ ኤስ ሸምድዶ የጨረሰው ገና ትምህርት ሳንጀምር ነው፡፡ ቄሱ በፍጥነቱ አልተደሰቱበትም፡፡ ኤስ መደነቅ ፈልጐ አይደለም፣ ለፈተና ዝግጁ ስለመሆኑ ለቄሱ   የገለፀላቸው…ወደሚቀጥለው ፈተና ለማለፍ ሲል ነው፡፡
ማን ፈጠረህ?
እግዚአብሔር
ለምን ፈጠረህ?
እንድታምነው እንድታውቀው፣ ትዕዛዙንም ፈፅመህ መንግስተ ሰማያት እንድንገባ ፈጠረን
ስላሴ ስንት ናቸው?
ሦስት
ቄሱ ተሳስተሀል አሉት “አንድም ሶስትም ናቸው ተሳስተሃል - ትምህርት ሳይጀመር ፈትኑኝ ማለት ይኼ ነው ችግሩ…አትቸኩል!” ብለው አሰናበቱት፡፡ ኤስ ግን መጨረሱን አምኗል፡፡ እናም እኛ ትምህርቱን ስንከታተል፣ ትምህርተ ክርስቲያኑን ስናነበንብ እሱ ሌላ ነገር ነበር በደብተሩ ላይ የሚለቀልቀው፡፡ አንድ ቀን ደብተሩን ሲያሳየን ስዕል ሳይሆን ፅሁፍ ሞልቶበት አገኘን፡፡ ምን እየፃፈ እንደሆነ ጠየቅነው፡፡ ድርሰት ነው አለን፡፡ ክርስትና አትማርም ወይ? ስለው…ጨረስኩ አለኝ፡፡ እኛ እሱ የደረሰበት ለመድረስ ሽምደዳችንን ሌት ተቀን አደረግነው፡፡ በልጅነታችንም ቢሆን አንዱን ሳንጨርስ ሌላውን መጨበጥ አንወድም ነበር፡፡ …እሱ የሚፅፈውን ነገር ለመረዳት እኛ የያዝነውን፣ እሱ ተረድቶ ያለፈውን ማጠናቀቅ ግድ ነበር፡፡ እሱም መፃፉን ቀጠለ፤ እኛም መሸምደዳችንን፡፡ ሸምድደን ስንጨርስ ምንም ጊዜ አልተረፈንም፡፡ ቁርባን ደረሰብን፡፡ ከቁርባኑ በፊት ሁለት ስነ - ሥርዓቶች አሉ፡፡ አንዱ የትምህርተ ክርስቲያኑ ትምህርት ዘልቆን እንደሆነ ለማወቅ ተፈተንን፡፡ ሁላችንም አለፍን፡፡ ትምህርቱ ዘልቆን ሳይሆን ጥርሳችንን ነክሰን ስለሸመደድን ነው፡፡ ኤስ ከእኛ የሚለየው ሲሸመደድ እንደ ፎቶ ኮፒ ማሽን በጭንቅላቱ እንዳይረሳ አድርጐ በመንቀስ ነው፡፡ የኛ መሸምደድ ለሱ እውቀት ነው፡፡ ተፈተንን፤ ሁላችንም አንድ ላይ አለፍን፡፡ ለኑዛዜ ቀረብን፡፡ ኑዛዜ ሀጢአትን መናገር ማለት መሆኑ ተነገረን፡፡ ለቄሱ ጆሮ የምንናገረው ሀጢአት በቄሱ ጆሮ በኩል ወደ እግዜር ጆሮ እንደሚቀዳ ተገለፀልን፡፡ የእኛ እድሜ በዚያ ወቅት እንጭጭ ስለነበር፣ ሀጢአታችንን ላናውቀው እንደምንችል ቄሱ አስረዱን፡፡ በመሆኑም ኑዛዜያችን በቄሱ ጥያቄ እየተመራ፣ እኛ በመልስ የተደበቀ ሃጢአታችንን እንድንዘረግፍ ሆንን፡፡ በመሠረቱ ከኤስ በስተቀር ሌሎቹ ልጆች አንድ አቋም ይዘን ነው ወደ መናዘዣ ክፍሉ የገባነው፡፡ “ቄሱ ለሚጠይቁን ጥያቄ ሁሉ መልሳችን “አዎ” የሚል ይሆናል” ተባብለን ተስማምተናል፡፡
የተጠየቅነው ጥያቄ ተመሳሳይ እንደነበር፣ ከኑዛዜው ክፍል ከወጣን በኋላ እርስ በራሳችን አመሳከርነው፡፡ ቄሱ እያንዳንዱን ልጅ ለየብቻው እያስገቡ - ለማንም በማይሰማ ሹክሹክታ ይጠይቁታል፡፡ ተጠየቅን - ተራ በተራ፡፡ ተመሳሳይ መልስ ተራ በተራ መለስን፡፡
ዋሽተሀል?
አዎ
ሰርቀሃል?
አዎ
የቤተሰብ ምክር ችላ ብለሀል?
አዎ (ችላ የምትለዋን ቃል ትርጉም         ማናችንም አናውቃትም፤ በዛ እድሜ)
ተሳድበሀል?
አዎ
ዝሙት ፈፅመሀል?
አዎ (ዝሙት የሚል ቃልም ትርጉሙ         አይታወቅም)
ገድለሀል?
አዎ
ክርስቶስን ክደሀል?
አዎ
ለዚህ ሁሉ ሀጢአታችን የሚሆን ቁጥሩ በዛ ያለ “አባታችን ሆይ” እና “ሰላም ለኪ” ለእያንዳንዳችን ታዘዘልን (ተፈረደብን)፡፡ በመደዳ ተደርድረን የቤተ መቅደሱን ወንበሮች ተቆጣጥረን ቀጠልን፡፡ ፀሎትም እንደ ትምህርቱ በማነብነብ የሚከናወን ነው ያኔ፡፡ከሁላችንም መጨረሻ ወደ መናዘዣ ክፍሉ የገባው ኤስ ነበር፡፡ መጨረሻ የገባው እሱ ቢሆንም ፀሎት ጨርሰን ስንዝናናም ኑዛዜውን ጨርሶ አልወጣም፡፡ ቄሱ ዝግ ባለ ድምፅ ከሚናገሩበት አንዳንዴ ጮክ ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ የኤስ ድምፅ ግን አይሰማም፡፡ ምናልባት ሰይጣን አግኝተውበት ሊሆን ይችላል ብለን መፍራታችን አሁን ትዝ ይለኛል፡፡ ብዙ ቆይቶ ወጣ፡፡ የድርሰት ደብተሩን በአንድ እጁ ይዟል፡፡ ትንሽ የተረበሸ ይመስላል፡፡ የተረበሸ ፊት ሲያሳይ ሆዱን የቆረጠው ይመስላል፡፡ (በልጅነታችን እንደ ሆድ ቁርጠት በተደጋጋሚ የሚያሰቃየን በሽታ አልነበረም) ኤስ ወደ እኛ እያዘገመ፣ ቄሱ ከእንጨቷ ሳጥን (ክፍል) በሩን በርግደው ከኋላ እያስተዋሉት መሆኑ ለሱ አልተሰማውም፡፡ እኔ ግን እይታቸው ዛሬም ትዝ ይለኛል፡፡ እንደማይወዱት ያስታውቅባቸዋል፡፡ መነፅራቸውን ወደ አፍንጫቸው ጫፍ ዝቅ አድርገዋታል፡፡ ኤስን እየተመለከቱት የነበረው ግን በመነፅራቸው ሳይሆን በአይናቸው ነበር፡፡ እርስ በርስ ስለ ኑዛዜያችን ተጠያየቅን…አንዱ የተጠየቀው ጥያቄ ሌላኛው አምልጦት ከሆነ በሚል ሳይሆን አይቀርም፡፡ መልስ እና ጥያቄያችንን አወራርደን አንድ አይነት መሆኑን አረጋገጥን፡፡ አንድ አይነት ሀጢያት ፈፅመን አንድ አይነት ማርከሻ ነው የታዘዘልን፡፡ ከኤስ በስተቀር፡፡
ኤስም እንደኛው መስሎን ነበር፡፡ እኛ መሀል የተለየ ልጅ ቢሆንም በእግዚአብሔር ቤት  መቼም አጉል ልፍጠን አይልም ብለን ነበር የገመትነው፡፡ ግን ይሄ የኛ ግምት ነው፡፡
ሰው ገድለሀል ሲሉህ ምን አልክ             (አልነው)
ገድያለሁ
እኛም እንደዚያ ነው ያልነው?
እናንተ መቼ ነው ሰው ገድላችሁ             የምታውቁት?
አንተስ መቼ ገድለህ ታውቃለህ?
ከዚያ ማስረዳት ጀመረ፡፡ በሚፅፈው ልብወለድ ላይ ገፀባህሪው (አሁን ስሙን ዘንግቼዋለሁ) የሚስቱን አባት እንደሚገድል ነገረን፡ እኔ የገደልኩት የፈጠርኩትን ገፀ ባህርይ ነው፤ እናንተ ማንን ነው የገደላችሁት?ሳታውቁ የሰራችሁት ሀጢአት ሊኖር ስለሚችል …ማጥፋታችሁ ትዝ የማይላችሁንም አጥፍቻለሁ ማለት በእግዚአብሔር ፊት ያስወድዳል ብለው አስተምረውናል፡፡ (አልነው መሰለኝ)
እኔም እኮ (የገፀ ባህርይውን) ሚስት አባት አልገደልኩም፤ የገደለውማ ገፀ ባህርዬ ነው፡፡ ግን እኔ ገድያታለሁ ስል ሳላውቀው በምፅፍበት ጊዜ ለግድያው የተወሰነ አስተዋጽኦ አድርጌ ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡
ለቄሱ እንደዚህ አልካቸው?
አዎ…ግን አባ ተቆጡ፡፡ ብዙ ተከራከርን፡፡ እመን ሲሉኝ አላምን አልኳቸው፡፡ ሰይጣን አሉኝ..ተሳደቡ አልኳቸው…አልተሳደብኩም አሉ፡፡ ተሳድበህ ታውቃለህ ወይ አሉኝ …አዎ አልኳቸው…ተሳድበው ያውቃሉ ወይ ስላቸው በፍፁም አሉ፡፡ …እና እንደዚህ እያልን ብዙ ተጨቃጨቅን፡፡ በደንብ ሳያናዝዙኝ ቀሩ፡፡ ለተናዘዝኳቸው ሀጢአቶችም ፍትሀት አልሰጥ አሉኝ፡፡ ምናልባት አትቆርብም ብለው ሊከለክሉኝም ይችላሉ፡፡ ስለ ኤስ ሳስብ ሰይጣን ይሆን? ወይንስ መልአክ? የሚለው ጥያቄ እድሜ ልክ እልባት የሚያገኝ አይመስለኝም፡፡   


Read 4365 times