Saturday, 27 December 2014 10:21

“...ልጆችን በተገቢው መንገድ ማስተማር...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

“...በሴቶች ላይ የሚፈጸመው የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በአብዛኛው ቅርብ በሆኑ     ወይንም በሚታወቁና እምነት በተጣለባቸው ወንዶች አማካኝነት ነው፡፡  ይህም     በስነተዋልዶ ጤና በኩል በከፍተኛ ሁኔታ የጤናን ችግር ከሚያስከትሉና የሴቶችን የሰብአዊ መብት ከሚገፉ ድርጊቶች የተመደበ ነው፡፡” - WHO
ከላይ ያነበባችሁት እውነታ በመላው አለም ከግምት ውስጥ የገባና ሀገራት ችግሩን ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ የሚስተዋልበት ነው፡፡ የአለም የጤና ድርጅት መረጃውን በማከልም የሚከተሉትን ነጥቦች ለንባብ ብሎአል፡፡
በቅርብ በአለም ላይ የተገኘው መረጃ እንደሚገልጸው፡-
በአለም አቀፍ ደረጃ 35% የሚሆኑ ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው በሚያውቁትም ይሁን በማያውቁት ሰው የወሲብ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ በአማካኝ 30% የሚሆኑት ሴቶች በቅርባቸው ካለ ወይንም አብሮአቸው በሚኖር ሰው ድርጊቱ እንደተፈጸመባቸው መስክረዋል፡፡
በአለም 38% የሚሆኑ ሴቶች ሕይወት የጠፋውም በሚያውቁዋቸው ወይንም በኑሮ ተጋሪዎቻቸው መሆኑን የአለም የጤና ድርጅት ይመሰክራል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በአካል፣ በአእምሮ፣ በወሲብ የሚፈጸም ሲሆን ይህም ለስነተዋልዶ ጤና ወይንም ሌላ ተያያዥ ለሆኑ የጤና እክሎች (ኤችአይቪ) ሊያጋልጥ ይችላል፡፡
በሴቶች ላይ የወሲብ ጥቃቱን የሚፈጽሙት ወንዶች ምናልባትም ዝቅተኛ ትምህርት ያላቸው ወይንም በቤተሰቦቻቸው ዘንድ ለሕጻናት በቂ ትኩረት ወይንም እንክብካቤ ሲደረግ ማየት ያልቻሉ ወይንም በቤተሰብ ዘንድ ጥቃት ሲፈጸም፣ ጎጂ የሆኑ አልኮሆል የመውሰድ ልምድ፣ የስርአተ ጾታ ክፍፍል ሲደረግ መመልከት፣  የሴቶች እኩልነት ዝቅ ማለትን እያዩ ያደጉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ዘገባው ያስረዳል፡፡
ባለፈው ሳምንት እትም የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በመቀሌ ከተማ ሐይደር ሆስፒታል ያቋቋመውን ተገደው የተደፈሩ ሴቶች የሚታከሙበትን ሞዴል ክሊኒክ በንባብ ማስጎብኘታችን ይታወሳል፡፡ በዚያም ያገኘናቸውን ባለጉዳዮች ማብራሪያ አቅርበን ለዚህ እትም ቀጣይ እንደሚኖረው ገልጸናል፡፡ በመግቢያው ላይ “...መምህርማ አባት ወይንም እናት...” የሚለውን ርእስ የተጠቀምነውም ምክንያት ስላለው ነው፡፡ ለዚህ እትም ማብራሪያ ያገኘነው በሞዴል ክሊኒኩ ከምትሰራው ከሲ/ር አበባ ከበደ ነው፡፡
በመቀሌ የተከሰተ አንድ ታሪክ እናስነብባችሁ፡-
ሰውየው በመቀሌ ከተማ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት አስተማሪ ነው፡፡ ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች መካከል የተወሰኑትን ጥናት አስጠናችሁዋለሁ በማለት በየቀኑ በተራ በተራ ከእርሱ ጋር እንዲቆዩ ያደርጋል፡፡ የመምህሩ አላማም ሕጻናቱን ማስተማር ሳይሆን አስገድዶ መድፈር ነበር፡፡ ድርጊቱን ከፈጸመ በሁዋላም ልጆቹ ለማንም ይህንን ታሪክ እንዳይ ናገሩ ...ከተናገሩም ጉዳት እንደሚያደርስባቸው እያስጠነቀቀ ነበር የሚለቃቸው፡፡ በስተመጨረሻውም ከእርሱ ጋር ለመቆየት ተረኛ የነበረች በእድሜዋ ወደ አስራ ሁለት አመት የሚሆናትን ሕጻን በፊንጢጣዋ ጭምር ስለደፈራት ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል፡፡ ሕጻኑዋ እንደተለመደውም በማስጠንቀቂያ ቢለቃትም ...እርስዋ ልትደብቀው የማትችለው በመሆኑ ሰውየው ይጋለጣል፡፡  የህጻኑዋ ቤተሰቦች ልጅቱን ወደሐኪምቤት በማድረስ ወደህግ ቦታም ሄደው ጉዳዩን በመከታተል ላይ ናቸው፡፡
“...እዚህ ላይ አንድ የሚያሳዝን ክስተት ተፈጽሞአል፡፡ ሰውየው ሕጻኑዋን ከጥቅም     ውጭ     አድርጎ በመድፈሩ ምክንያት የልጅቱ ገላ እንዳይሆን ሆኖአል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ     ...መምህሩ ኤችአይቪ ቫይረስ በደሙ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ህጻኑዋንም በቫይረሱ እንድትያዝ አድርጎአታል፡፡ መምህሩ ዛሬ በህግ የተያዘ ቢሆንም የህጻኑዋ የወደፊት የህይወት እጣ ፈንታ ግን ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ እጅግ ...ያሳዝናል፡፡ መምህርማ በእናትና አባት የሚመሰል አይደለምን? ይህንን ድርጊት ይፈጽማል ብሎ መገመት እጅግ ያስቸግራል፡፡ እንደዚህ ያለው መምህር የሌሎች     መልካም ስነምግባር ያላቸውን መምህራን በጎ ተግባር የሚያጠፋ ስለሆነ ተገቢው እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፡፡”ሲስተር አበባ እንደገለጸችው ...ይህች ልጅ ጉዳትዋ ስለከፋ ወደህግና ሕክምና ቀረበች እንጂ ይህ መምህር ጥቃት ያደረሰባቸው ሌሎች ህጸናትም አሉ፡፡ ማንኛውም ቤተሰብ ልጆቹን ግልጽ ውይይት ማስተማር እንዳለበትንና ልጆች ከማንኛውም ሰው የሚሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ወደጎን በመተው እውነቱን ለወላጆቻቸው መንገር እንዳለባቸው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሲስተር ሳራ በአይደር ሆስፒታል ያነጋገርናት ባለሙያ ናት፡፡ እሱዋም እንደምትመሰክረው ወላጆችም ይሁኑ ትምህርትቤቶች እንደዚህ ያለውን አስጸያፊ ተግባር ህጻናቱ አስቀድሞውኑ እንዲያውቁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
“...በተለይም ወላጆች በግልጽ ልጆቻቸውን ተገዶ በመደፈር ሁኔታ ላይ የሚያስተምሩ     አይመስለኝም፡፡ እንዲሁ በደፈናው ሴት ልጆቻቸውን ለምን በሰአቱ ከትምህርት ቤት     አትመጪም ወይንም ለምን ከወንድ ጋር ትሄጃለሽ የመሳሰሉትን ተግባራዊ የማይደረጉትን ቁጣዎች ሊሰነዝሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን ትክክለኛው የማስተማሪያ መንገድ     አይደለም፡፡
ልጆቹ ከትምህርት ቤት መውጫ መግቢያ ሰአታቸውን መጠበቅ የሚገባቸው ለምን ድነው? ምን ችግር እንዳይገጥማቸው ነው?
ሕጻናቱ ከወንድ ጋር አትሂጂ የሚለውን ቁጣ በደፈናው ሊቀበሉት የማይችሉትን መሰንዘር ትክክለኛው መንገድም ስላልሆነ... ከሱ ይልቅ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በተሳሳተ መንገድ በልጆ ላይ ምን ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ እና ይህ ግን የሁሉም ወንዶች እና ሴቶች ተግባር እንዳ ልሆነም ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም ተገዶ መደፈር ምን ማለት እንደሆነና በልጆቹ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት እና የመብታቸውን ሁኔታ በትክክል እንዲያውቁ ማድረግ ከወላጆች፣ ከትምህርት ቤቶች እንዲሁም ከመላው ሕብረተሰብ የሚጠበቅ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡”
ሴቶች የወሲብ ጥቃት ወይንም ትንኮሳ ደርሶባቸዋል ሲባል የግድ የወሲብ ግንኙነት ተደርጎአል ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን ወሲብ ለመፈጸም ሙከራ ማድረግ፣ በእጅ ወይንም በአይን በመሳሰሉት ሁሉ የተለያዩ ትንኮሳዎችን ማድረግ፣ በንግግር በመሳሰሉት ሁሉ ሴቶችን መተንኮስ፣ መብትን መጋፋት መሆኑን ከግምት የማያስገቡ አሰራሮች ሴት ልጆችን እየጎዱ መሆኑን ሲ/ር አበባ ገልጻለች፡፡
“...ታካሚዋ የመጣችው መስከረም ወር ላይ ነው፡፡ እድሜዋ አስራ ሁለት አመት     ይሆናል፡፡ ልጅቱዋ በአሳዳጊዋ አራት ጊዜ የወሲብ ጥቃት ተፈጽሞባታል፡፡ ያች ልጅ     ወደሐኪም ቤት መጥታ ሕክምና ከተደረገላት በሁዋላ የተሰጣት ምስክርነት ክብረ ንጽህናዋ እንዳልተነካ እና የመደፈር ምልክት እንዳልታየባት ነው፡፡ ይህንን ይዛ ወደህግ     ቦታ ስትሄድ ግን ልጅትዋ የምትናገረውን ምስክርነት ከምንም ሳይቆጠር ክብረ ንጽህናዋ ስላልተወሰደ ለክስ መሰረት የሚሆን ነገር የለም ከሚል ፋይሉም ተዘግቶአል... ሰውየውም     በነጻተለቅቆአል፡፡”
ልጅትዋ በአሳዳጊዋ አራት ጊዜ የወሲብ ጥቃት ከተፈጸመባት እንዴት ክብረንጽህናዋ አልተወሰደም የሚል ጥያቄ በአንባቢዎች ዘንድ የሚጭር ነው፡፡ ሲ/ር አበባ እንደገለጸችው፡-
“...የድንግልና ቀለበቱ በተፈጥሮ የተለያየ አፈጣጠር አለው፡፡ አይነቱ አራት አይነት     ሲሆን ከዚያ ውስጥ አንደኛው ቅርጽ በራሱ ጊዜ የመለጠጥ ባህርይ ያለው ነው፡፡ ይሄ     አይነቱ ሲሆን ከግንኙነት በሁዋላ ተመልሶ ወደቦታው የሚገጥም ነው፡፡  እንደዚህ አይነት ተፈጥሮ ከሆነ የመድማት ወይንም የመቁሰል ምልክት ስለማያሳይ ክብረንጽህና አልተነካም ሊባል ይችላል፡፡  ነገር ግን ልጅትዋ በሰውየው ተደጋጋሚ የወሲብ ጥቃት እንደደረሰባት ከገለጸች እና ሌሎች መረጃዎች ከተሰባሰቡ ሐኪም     የክብረንጽህና መወሰድ ምልክት በገላዋ ላይ አይታይም በማለቱ ብቻ መረጃው በሐኪም     ካልተረጋገጠ ክስ ለመመስረት አያበቃም በሚል ጥፋተኛውን መልቀቅ በልጅትዋ     ሞራልና የወደፊት ሕይወት ላይ ጠባሳ እንደሚጥል መገመት አያዳግትም፡፡”  
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በመቀሌ ሐይደር ሆስፒታል ባቋቋመው ሞዴል ክሊኒክ የሚመጡ ታካሚዎች ከሌሎች ታካሚዎች ጋር በመደባለቅ ወረፋ ሳይጠብቁ በቀላልና በፍጥነት አስፈላጊው ምርመራና ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ከተጠቃሚዎች ለመረዳት ተችሎአል፡፡ ተገዶ መደፈር የደረሰባቸው ሴቶች እርግዝና መኖር ያለመኖሩ፣ ከኤችአይቪ ቫይረስ ነጻ መሆን ያለመሆናቸው እና የመሳሰሉትን ሕክምናዎች በነጻ ከማግኘታቸውም በላይ ጉዳያቸው በህግ እንዲታይላቸው አስፈላጊው ሕክምናና መረጃ ካለምንም ክፍያ ይሰጣቸዋል፡፡ በመሆኑም በቅርብ ጊዜ  ስራውን የጀመረው ክሊኒክ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ከ75/ያላነሱ ባለጉዳዮችን ማስተናገዱን ሲ/ር አበባ ገልጻለች፡፡

Read 4633 times