Saturday, 03 January 2015 10:45

“...የደም ግፊቱ ቀለል ካለ ጉዳቱ ከጤና መቃወስ አንስቶ እስከ ሞት ድረስ የሚያደርስ ነው...”

Written by  ዮዲት ባይሳ ከኢሶግ
Rate this item
(16 votes)

    ፕሪክላፕዚያ ወይም በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደምግፊት አንዲት እርጉዝ ሴት በእርግዝናዋ ወራት ሊያጋጥሟት ከሚችሉ የጤና እክሎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት
በእናቲቱ ብሎም በፅንሱ ላይ የተለያዩ ችግሮችን የሚያስከትል ሲሆን በግዜ ታውቆ ተገቢው ህክምና ካልተደረገ
የከፋ የጤና መቃወስ ባስ ሲል ደግሞ ህይወት እስከማጣት ሊያደርስ ይችላል፡፡በዛሬው ፅሁፋችንም ለመሆኑ ይህ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት ምን አይነት የጤና እክል ነው? በሽታው በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ምን አይነት ጉዳት ያስከትላል፣ በሽታው ከመከሰቱ አስቀድሞ የሚታዩ ምልክቶች ምን ይምስላሉ እንዲሁም እንዴትስ የከፋ ጉዳት ሳያስከትልስ መከላከል ይቻላል ለሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች ከባለሙያ ያገኘነውን ማብራሪያ አክለን እንደሚከተለው ልናስነብባችሁ ወደናል፡፡ዶክተር አሳየ መዝገቡ በኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ህክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ላነሳናቸው እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ጥያቄዎች ተከታዩን ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል በቅድሚያ ግን ለመሆኑ ይህ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት ምን አይነት የጤና እክል ነው? የሚለውን ጥያቄ እናስቀድም፡፡     
“በእርግዝና ወቅት የሚከሰትን የደም ግፊትን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል አንደኛው  ለመጀመሪያ ግዜ
በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቀደም ብሎ የነበረ የደም ግፊት ከእርግዝና ጋር አብሮ የሚቀጥል ነው፡፡ ሰባ ፐርሰንቱ የደም ግፊት በእርግዝና ግዜ ለመጀመሪያ ግዜ የሚከሰተው የደም ግፊት ሲሆን ይሄ አይነቱ የደም ግፊት በእናቶች ላይ ሰፋ ያለ የጤና ችግር የሚያስከትል ነው፡፡ የደም ግፊቱ ቀለል ካሉ ጉዳቶ አንስቶ እስከ ሞት ድረስ ሊያደርስ የሚችል ነው ይህም እንደ በሽታው መጠንና የእርግዝናው እድሜ ይለያያል፡፡ ስለዚህ በእርግዝና ወቅት ለእናቶች ሞት ቀዳሚ ከሚባሉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ይህ በእርግዝና ወቅት የሚከሰትን የደም ግፊት ነው ለማለት ይቻላል፡፡”የህክምናው ሳይንስ እስካሁን ድረስ የዚህን በሽታ መንስኤ ለይቶ ለማወቅ እንዳልተቻለው ይሁንና በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶች እንደተካሄዱ አሁንም በመካሄድ ላይ እንዳሉ ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡ “በአሁኑ ሰአት ለበሽታው ምክንያት ይሄ ነው ተብሎ የተቀመጠ ምክንያት የለም፡፡ በተለያየ ግዜ የተደረጉ ጥናቶች ነበሩ በአሁኑ ግዜም የዚህን በሽታ መንስኤ ለይቶ ለማወቅ እየተደረጉ ያሉ ጥናቶች አሉ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ምክንያቱ በግልፅ የታወቀ አይደለም፡፡ በየትኛው የእርግዝና ደረጃ ላይና በየትኛው የእድሜ ክልል ላይ በብዛት እንደሚከሰት እንዲሁም ሌሎች ለዚህ በሸታ የሚኖረውን ተጋላጭነት ከሚጨምሩ ነገሮች ውጪ የበሽታው መንስኤ ይሄ ነው ብሎ መለየት አልተቻለም፡፡”
ለመሆኑ አንዲት እርጉዝ ሴት የደም ግፊቱ አለባት ማለት የሚቻለው የደም ግፊት መጠኑ ምን ያህል ሲሆን ነው?“የላይኛው የልኬት መጠን ወይንም ደግሞ በህክምናው አጠራር ሲስቶሊክ የሚባለው መቶ አርባና ከመቶ አርባ በላይ ከሆነ የታችኛው ዲያስቶሊክ ደግሞ ዘጠናና ከዛ በላይ ሲሆን ደም ግፊት ተከስቷል ማለት ነው፡፡ ወይም ቀደም ተብሎ የደም ግፊት መጠኑ ከታወቀ ደግሞ ከመጀመሪያው ሀያ ሳምንት በፊት ከነበረው የግፊት መጠን እየጨመረ ከሄደ ለምሳሌ የላይኛው በሰላሳ ከጨመረ የታችኛው ደግሞ በአስራ አምስት ከጨመረ ወይም ከዛ በላይ እየጨመረ ከሄደ የደም ግፊት ተከስቷል ይባላል፡፡  ስለዚህ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ

ነው የደም ግፊት አለ ወይንም የለም የሚባለው፡፡”
በሽታው ከመከሰቱ አስቀድሞ የተለያዩ ቅድመ ምልክቶች ይኖሩታል ተከስቶም ሲገኝ የበሽታው ምልክቶች እንደ ግፊቱ ደረጃና የእርግዝናው እድሜ ይለያል፡፡ አንዳንዴ ድንገተኛ በሆነ መልኩ የደም ግፊት ከፍ ብሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን በአብዛኛው የራስምታት፣ እይታ ላይ ብዥ ብዥ ማለት፣ እይታን የመጋረድ፣ ከፍተኛ የሆነ የክብደት መጨመር ለምሳሌ በሳምንት ከአንድ ኪሎ በላይ መጨመር እንዲሁም ደግሞ ባጠቃላይ ሰውነት የማበጥ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ በሆድ የላይኛው ክፍል አካባቢ አህመም ሊያጋጥም ይችላል፡፡ እነዚህ እንግዲህ የደም ግፊቱ ከመከሰቱ አስቀድሞ የሚስተዋሉ ምልክቶች ናቸው ከተከሰተ በኋላ ደግሞ የሚመጡ ሌሎች ችግሮች አሉ፡፡ ስለዚህ ማንኛዋም ነብሰጡር እንደዚ አይነት ምልክቶች በታዩ ግዜ በአቅራቢያዋ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና ማድረግ ይኖርባታል፡፡” አብዛኛው ይህ የደም ግፊት ከሰላሳምስተኛው የእርግዝና ሳምት ጀምሮ የሚከሰት ቢሆንም ማንኛዋም እርጉዝ ሴት በየትኛውም የእርግዝና ደረጃ ላይ ይህ የደም ግፊት ሊያጋጥማት እንደሚችል ዶክተር አሳየ ይገልፃሉ፡፡ ይህ በእርግዝና ግዜ የሚከሰተው የደም ግፊት ወይንም ደግሞ በህክምና ስሙ ፕሪክላምፕሲያ ተብሎ የሚጠራው የተለያዩ ደረጃዎች አሉት፡፡ ይህም የግፊቱን መጠን እንዲሁም በእናቲቱ ላይ የሚታዩት ምልክቶች ታሳቢ አድርጎ የሚሰጥ ነው፡፡   “የበሽታው ደረጃ እንደ ግፊቱ መጠን እንዲሁም ደግሞ እንደሌሎች ተጓዳኝ ምልክቶች መኖር አለመኖር መለስተኛና ከፍተኛ ተብሎ በሁለት የሚከፈል ነው፡፡ ለእነዚህ መስፈርት የሚሆነው ደግሞ አንደኛ የደም ግፊቱ መጠን ነው፤ የደም ግፊቱ የላይኛው ከመቶ አርባ እስከ መቶ ስልሳ የታችኛው ደግሞ ከዘጠና እስከ መቶ አስር ሲሆን መለስተኛ የደም ግፊት ይባላል፡፡ ከዛ በላይ ሲሄድ ግን ከፍተኛው የደም ግፊት ነው፡፡ እንዲሁም አይን ብዥ ብዥ ማለት፣ የእይታ መጋረድ፣ ማንቀጥቀጥ፣ ከፍተኛ የሰውነት የክብደት ሲኖር፣ በሽንት ውስጥ የሚለቀቀው የፕሮቲን መጠን ከአምስት ግራም በላይ ሲሆን ከፍተኛ የደም ግፊት ነው ተብሎ ይወሰዳል፡፡ ይህም ኢክላፕሲያ ተብሎ የሚጠራውንና ለእናቶች ሞት ከፍተኛ አስተዋፅ  ያለው ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ ስለዚህ በዚህ መልኩ ከፍተኛ፣ መለስተኛና ዝቅተኛ ተብሎ ይከፈላል፡፡”
ዋነኛው መመዘኛም ይላሉ ባለሙያው፡-  “ዋነው መመዘኛው የደምግፊት ልኬቱ ነው፡፡ ሆኖም ግን አብረው ሌሎች ተጨማሪ የላብራቶሪ ምርመራዎች አሉ አንዱ መመዘኛ በሽንት ውስጥ የሚለቀቅ የፕሮቲን መጠን ነው፡፡ በእርግዝና ወቅት ከሽንት ጋር አብሮ የሚወጣው የፕሮቲን መጠን ይጨምራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወደ ኩላሊት የሚሄደው የደምፍሰት መጠን እንዲሁም ደግሞ ኩላሊት ውስጥ እያመለጠ የሚሄደው የፕሮቲን መጠን ስለሚጨምር ነው፡፡ ሆኖም ግን ሶስት መቶ ሚሊግራም ፕሮቲን በሀያ አራት ሰአት ውስጥ የሚለቀቅ ከሆነ ይህ ከደም ግፊት ጋር የሚያዝና ጤናማ ያልሆነ ነው፡፡ ይህ አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ በሚወሰድ ናሙና ላይ የሚደረግ ላብራቶሪ ምርመራ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የደምግፊት በሽታ በእርግዝና ወቅት በእያንዳንዱ የሰውነታችን ክፍሎች ላይ የተለያየ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተለይ ኩላሊት፣ አንጎል፣ ጉበት እንዲሁም ልብ የመሳሰሉት ላይ ከባድ ተፅእኖ ያመጣል፡፡ በደም ውስጥ የደም አለመርጋት ችግር ሊያስከትልም ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁሉ የላብራቶሪ ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ጉበት ላይ የሚደረጉ የተለያዩ የኢንዛይም ልኬቶች አሉ፣ በሽንት ላይ ያለው ፕሮቲን በሀያ አራት ሰአት ውስጥ ምን ያህል ነው የሚለው ይለካል፣ በተጨማሪም  ደም ላይ ያሉ ለመርጋት የሚያገለግሉ ንጥረነገሮችም እንደዚሁ ይለካሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን የመሳሰሉ ተጨማሪ ምርመራዎችም በማድረግ የደም ግፊቱ መኖር ለመኖሩን ማወቅ ይቻላል፡፡”
የደም ግፊቱ ተከስቶ ሲገኝ በእናቲቱ እንዲሁም በፅንሱ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ባለሙያው እንደሚከተለው
ያብራሩታል፡-“እናትየዋ ላይ ሊመጡት የሚችሉ የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኩላሊት ሙሉ በሙሉ የማጣራት ስራውን እስኪያቆም  ይታወካል ጉበት ላይም ደም የመቋጠርና እስከ መተርተር እንዲሁም ጉበት ስራ እስከማቆም ሊደርስ ይችላል፡፡ አንጎል ላይ ደግሞ የአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ ይከሰታል ይህም እራስን እስከመሳትና ኢክላምፕሲያ ተብሎ የሚጠራው ደረጃ ላይ ያደርሳል፡፡ ካልታከመና የመጨረሻው ደረጃ ላይ ከደረሰ ደግሞ ህይወት እስከ ማጣት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ስለዚህ እንደ በሽታው ደረጃ አስከፊ ውጤቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ልጁ ላይ ደግሞ የእንግዴ ልጁ ሳይወለድ አስቀድሞ እንዲላቀቅ፣ ፅንሱ ካለቀኑ እንዲወለድ እንዲሁም ደግሞ ውስጥ እያለም እንዲሞት  ሊደርግ ይችላል፡፡” በሽታው ከመከሰቱ አስቀድሞ ሊደረግ የሚገባውን ቅድመ ጥንቃቄ በሚመለከት የሚከተለውን ብለዋል፡-“ቅድመ ጥንቃቄውን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ አንደኛው የደም ግፊቱን እንዳይመጣ መከላከል ይቻላል ወይ ሚለው ነው፡፡ የራስምታት፣ ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ክብደት መጨመር አንዲሁም በሆድ የላይኛው ክፍል ህመም ሲኖር ወደ ጤና ተቋም ሄዶ የደም ግፊት መጠኑን መለካት እንዲሁም ሌሎች ተገቢ ምርመራዎችን ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሽታው ከተከሰተ በቧላ ከፍተኛ የሚባለው ደረጃ ላይ ሳይደርስ ወደ ህክምና ተቋም ከመጡ የከፋ ችግር ሳያስከትል ለመከላከል የሚያስችለው ህክምና ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ግፊቱን ለማውረድ የተለያዩ መድሀኒቶን እንጠቀማለን፣ ልጁ ከቀኑ በፊት የሚወለድ ከሆነ ለልጁ የሚያጠነክር መድሀኒት ይሰጣል፡፡ እንዲሁም ደግሞ ኢክላፕሲያ የሚባለውና እራስን እስከማሳት የሚያደረትሰው ደረጃ ላይ እንይደርስ ለማድረግ የሚሰጥ መድሀኒት ይኖራል ስለዚህ እነዚን ቅድመ ጥንቃቄዎች በማድረግ በሽታው አስከፊ ችግር ሳያደርስ ከቆጣጠር ይቻላል፡፡”በመጨረሻም ባለሙያው ህብረተሰቡ ስለበሽታው ማወቅ አለበት ያሉትን የፅሁፋችን መዝጊያ አድርገነዋል፡፡  “ህብረተሰቡ በዋናነት ማወቅ ያለበት ከእርግዝና ጋር የተያያዘ የደም ግፊት የእናቶችን ህይወት በመቅጠፍ ቀዳሚ ከሚባሉት ምክንያቶች አንዱ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ አንደኛ ነብሰጡሯ የቅድመ ወሊድ ክትትል እንድታደርግ ማበረታታት ሁለተኛ ደግሞ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊትን ቅድመ ምልክቶች ምንድናቸው የሚለውን ህብረተሰቡ እንዲያውቅ ማድረግ ነው፡፡ አንዳንድ ግዜ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ የደምግፊቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ሲያንቀጠቅጣቸውና አእምሯቸውን ሲያስታቸው ወደ ባህላዊ ህክምና የሚሄዱ ነብሰጡር ሴቶች በተደጋጋሚ ያጋጥማሉ፡፡ ይህን አይነቱን ነገር ለመከላከል ደግሞ ህብረተሰቡ ስለ በሽታው ያለውን ግንዛቤ ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የቅድመ ወሊድ ክትትሉ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ተደርጎበት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡..         

Read 19849 times