Saturday, 14 January 2012 10:31

“ቻይናው ኢህአዴግ - ስንት ዓመት ይኖራል?”

Written by  አብዲ መ.
Rate this item
(1 Vote)

የተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን ጊዜ በጣም ገና ነው

አቶ በረከት ስምኦን መልሱን በመጽሃፋቸው ቢነግሩን ምን ይገርማል?

የአቶ አላዛር ኬ. ጽሁፍ የዋህ ይመስላል

ይሄን ጽሑፍ ለማዘጋጀት “እንደ አጣዳፊ” ሰበብ ያገለገለኝ ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ አላዛር ኬ. የተባለ ጸሃፊ ያስነበቡን “ኢህአዴግ ተአምረኛው የአላዲን ፋኖስ!” የሚል ጽሑፍ ነው፡፡ ጸሃፊው በቅርቡ ለንባብ የበቃውን የአቶ በረከት ስምኦንን መጽሃፍ “እንደ ኢትዮጵያዊ” አንብበው በዋናነት የተረዷቸውን ፍሬ ሃሣቦች በሶስት መሠረታዊ ጉዳዮች (ማንሳት ካለባቸው መካከል ነው ያሉት እሳቸው) ከፍለው በዝርዝር ሊያብራሩልን ሞክረዋል፡፡ መሠረታዊ ጉዳዮቹ ላይ ብዙም ልዩነት የለኝም፡፡ በተለይ በጥያቄ የተገለፀው  የመጀመሪያው መሠረታዊ ጉዳይ በርእስ ደረጃ በጣም ተመችቶኛል፡፡

ሁሉም መሠረታዊ ጉዳዮች የተብራሩበት መንገድ ግን የጸሃፊውን ፖለቲከዊ አረዳድ እንድሞግት አደረገኝ፣ የጽሑፋቸውን መነሻና መድረሻ አዘበራረቀብኝ፡፡ መጽሃፉን ያነበቡበትን ስሜት እስከዛሬ ኢህአዴግ ላይ በሚሰነዘሩት የተቃውሞ አስተያየቶች እንዳባዛው አስገደደኝ፡፡ እባክዎ አቶ አላዛር ኬ. የሂስ ጽሑፍዎን ለማዳበር የተጠቀሙባቸው ምክንያቶች በሙሉ እርስ በእርስ ከመጋጨታቸውና በቀላል (በየዋህ) ፖለቲካዊ አተያዮች ከመታጀባቸው በላይ “የአቶ በረከት ስምኦንን መጽሃፍ ተከትለው ነበር ወይ መነሳት የነበረባቸዉ?” ብለው  ለራስዎ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ላስቸግርዎት፡፡

 

“ነባር ሂስ” ያውቃሉ? ጽሑፍዎ በነባር ሂሶች የተሞላ ነው ማለቴ ነው፡፡ ሽሙጥ፣ የዋህነት፣ ግራ መጋባት፣ ስሜታዊነት፣ አሁንታን መካድ ወዘተ … የነባር ሂስ መገለጫዎች ናቸው፡፡ እርስዎ ሁሉንም ተጠቅመዋቸዋል፡፡ “ኢህአዴግ ራሱን እንደተአምረኛው የአላዲን ፋኖስ ማየት የለበትም” ለሚለው ወቀሳ አዘል ምክርዎና ሽሙጥዎ እንደማረሚያ ያቀረቡት ምክንያት “በሀገሪቱ ውስጥ ለታዩ ለውጦች ሌላውም አስተዋጽኦ አድርጓል ግን ተዘነጋ” የሚል ነው፡፡ ለመሆኑ ሌላው አካል ማነው? “ሕዝብ ነዋ!” እንዳይሉኝ ብቻ እንደጽሁፍዎ፡፡ እርግጠኛ ይሁኑ “ተቃዋሚዎቹ ኢትዮጵያን መምራት አይችሉም!” ይላል ባሉት የአቶ በረከት ስምኦን ኢህአዴጋዊ አስተሳሰብ ስላልተስማሙ ብቻ “ሕዝብና” “ተቃዋሚ” የሚባሉትን ሁለት የተለያዩ ፖለቲካዊ ስሞች በአንድ ትርጓሜ የመጠቀም ስህተት ሰርተዋል፡፡ ስለዚህ የሆነ ቦታ “ሕዝቡ” ኢህአዴግ አመጣሁት ለሚለው ለውጥ ድርሻ አለው፤ ይሉንና የሆነ ቦታ ደግም የሀገራችን ተቃዋሚዎች የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሰለባዎች መሆናቸውን ማንም አይክድም ይሉናል፡፡ በዚህ ሁሉ የጽሑፍዎ ሂደት ይህቺ ሀገር ላመጣቻቸው ለውጦች በየዋህነትም፣ በስህተትም፣ አንዳዴ ደግሞ በቅንነት እውቅና ይሰጣሉ፡፡ (አደራ እውቅና ለምን ሰጡ?  እንዳላልኩ ይረዱኝ)፡፡

ልክ የኢህአዴግን አደገኛ አተያይ ከተዛነፈ የሸሚዝ አቆላለፍ ጋር እንዳመሳሰሉት ሁሉ ኢህአዴግ ራሱን የለውጦች መሀንዲስ ነኝ ብሎ አረፈው ብለው መገረምዎን ግን ራስዎ የዜሮ ድምር ፖለቲከኞች ካሉዋቸው አካላት ጋር ማነፃፀሩን ረሱት፡፡ ለምን?፡፡ ስለዚህ አንድ ጥያቄና እምነት እዚህ ጋ ተዘለሉ፡፡ “አዎ ከኢህአዴግ በስተቀር የዛሬይቱን ኢትዮጵያ የሚመራ የለም!” የሚል እምነትና “ግን እስከመቼ?” የሚል ጥያቄ፡፡

“አዎ ከኢህአዴግ በስተቀር ኢትዮጵያን የሚመራ የለም” አለ ባሉት የአቶ በረከት መጽሃፍ ሃሣብ በጣም እስማማለሁ!” ብዬ የጽሑፌን ጭብጥ በግልጽ ፈር ለማስያዝ ልሞክር፡፡ “እስከመቼ?” የሚለውን ጥያቀ ማስከተሌ ግን ልብ ይባልልኝ፡፡ የአቶ በረከትን ሃሣብም ዕብሪት፣ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ፣ አደገኛ ሀገራዊ አተያይ ወዘተ … በሚሉ ስሞች እንደማልጠራውም ጭምር፡፡ ታዲያ የጽሑፌ መንገድ በቀጥታ ለአቶ አላዛሬ ኬ. በሚሰጡ ግለሰባዊ ምላሾች የተሞላ እንዳይሆንብኝ በቀጥታ ምክንያቶቼን ወደ ማቅረቡ  ልግባ፡፡ እግረ መንገዴን ከአቶ አላዛር ኬ ጽሑፍ ጋር እየተቃረንኩ ለመሄድ እሞክራለሁ፡፡ ሙከራዬ ከእነዚህ ሶስት መሠረታዊ ጉዳየች ሥር የሚመዘዝ ነው፡-

የደሀ ሀገር ፖለቲካ እና ዲሞክራሲ

የደሀ ሀገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና መንግስት

ቻይናዊዉ ኢህአዴግ

የደሀ ሀገር ፖለቲካና ዲሞክራሲ

“ምነው የጥቁሩ ፕሬዚዳንታችሁ ሥራ እንደወሬው፣ እንደንግግሩ፣ እንደምርጫ ዘመቻው አላምር አለ” ፡፡ ፀጉሩ ሁሉ እኮ በወራት ውስጥ ሸበተ፡፡” ሲባሉ “ታዲያ እሱ ምን ያድርግ ጆርጅ ቡሽ ደህና አድርጐ የበጠበጣትን አገር ተቀብሎ!” ይላሉ አሉ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ደጋፊዎች፡፡ የበርካታ ደሀ ሀገራትን (አሜሪካ ደሀ ነች አላልኩም) ፖለቲካዊ መልክ ስለምትገልጽ ጥያቄና መልሷን በጣም እወዳታለሁ፡፡

ቡሽ አሜሪካንን ደህና አድርገው የበጠበጧት እንዴት ይሆን? አፍጋኒስታን ድረስ ጦር ልከው፣ ባግዳድ ድረስ ወታደር እያዘመቱ፣ ሃይማኖትን ከሽብርተኝነት በቀላቀለው ዝኑፍ አተያያቸው፣ ጉልበት ተኮር በሆነው የአመራር እውቀታቸው ወዘተ … የሚሉ አይነት ናቸው የተለመዱት መልሶች፡፡ ስለዚህ “ዲሞክራሲ ጠገቡ” የአሜሪካ ህዝብ በምርጫ አስወገዳቸው እና የፈለገውን ሾመ፡፡ ጥያቄው ግን ቀጥሏል “ምነው ኦባማ?” እያሉ የተቃውሞ ድምፃቸውን የሚያሰሙ አሜሪካውያን ቁጥር ዛሬም በሚሊዮኖች ነው፡፡ ቁጥራቸው እየበዛ ከሄደም እድሜ “ለምርጫ” ከዓመት በኋላ ኦባማን አጨብጭበው  ይሸኛሉ፡፡ እነቡሽ ደግሞ ይመጣሉ፡፡ ስህተት ያሉትን ይቆርጡና ትክክለኛውን ይቀጥላሉ፣ የሚስማሙባቸውንም እንደዚያው፡፡ ግዙፏ አሜሪካና ህዝቦቿም ከየትኛውም ሀገር በሚሻል ደረጃ መኖራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ነጩ ቤተመንግስትም ህዝቡ ያቀበለውን መሪ እያስተናገደ ይኖራል፡፡ በክፍለ ዘመናት ብእር የተፃፈውን ህገመንግስት እያስጠበቀ ይኖራል፡፡ ደስ ሲል!፡፡ አሁን በጣም ትመቸኛለች ወዳልኳችሁ የኦባማ ደጋፊዎች ምላሽ እንመለስ “ታዲያ እሱ ምን ያድርግ ቡሽ ደህና አድርጐ የበጠበጣትን ሀገር ተረክቦ”

ይህቺ መልስ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሀ ሀገራት ፖለቲካ ውስጥ የምትነገርበትን ጊዜ በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡ ምክንያቱም መልሷ ብዙ ሚስጥር አዝላለች፡፡ ቀድሞ ስለተዘረጋ ስርአት፣ ለዘመናት በቆየ መዋቅር ስለምትመራ ሀገር፣ ስለዳበረ የዲሞክራሲ ስርአት ወዘተ … ታወራለች . መልሷ፡፡ “የሆነ የተደራጀ ነገር ነበረን ቡሽ መጥቶ አጨማለቀብን ስለዚህ ይለወጥ፣ አሜሪካ የተባለች ሲስተም እንዳማረባት እንደትቀጥል፣ እያማረባት እንድትሄድ ሌላ መሪ ይለወጥ!” የሚል ትርጉም አለው የአሜሪካውያኑ ጥያቄና መልስ፡፡ ደሀ ሀገራት እንዲህ ለማለት አልታደሉም፡፡ ሀገራዊ መዋቅር ስለሌላቸው አሊያ የተደራጀ ስላልሆነ ተወቃቅሶ የመደጋገፍ - እንደ ሀገር የማውራት እድሉን አያገኙም፡፡ በነገራችን ላይ እስከአሁን የማውቀው የፖለቲካ መዝገበ ቃላት “ደሀ” የሚባሉትን ሀገራት ሶስት ምድቦች ያስቀምጥልኛል፡፡ ሀገራዊ መዋቅር ፈጽሞ የሌላቸው፣ ሀገራዊ መዋቅራቸውን መምረጥ ያቃታቸው እና ሀገራዊ መዋቅራቸውን የመረጡ፡፡ ሶስቱም ደሀ ናቸው፣ ሶስቱም ከአለማችን ካርታ ሰፍረዋል፡፡ የድህነታቸዉ መጠንም ሀገራዊ መዋቅር በማጣታቸዉ ልክ ይመዘናል፡፡ ሀገራዊ መዋቅር ማለት በሳይንሱ ቋንቋ “ፖለቲካል ኢኮኖሚ” የሚለውን እንዲወክልልኝ የምጠቀምበት መጠሪያ ነው፡፡ የአንድ ሀገር መንግስት የሚመራበት ፖለቲካዊ ፍልስፍና ሀገራዊ መዋቅርን ይወልዳል፡፡ የህዝብ ንቃተ ህሊና፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማንነት፣ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ታሪክ፣ “የገዢ ፓርቲው (የመንግስት) እድገት” ደግሞ ሀገራዊ መዋቅሩን በዋናነት ውጤታማ ያደርጉታል፡፡ ያኔ ሀገር ማለት ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ሲስተም ትሆናለች፤ ሳይንሳዊ የሆነ መስመር ይኖራትና እየተራረሙ፣ እየተደጋገፉ እየተወቃቀሱ ሲያሻም በመሠረታዊ ቅንጣቶች ላይ ለውጥ እያካሄዱ መጓዝ ይቻላል፡፡ መወቃቀሱ እስከ ጠብ ሊደርስ እንደሚችል ይታመን፡፡

የአለማችን ደሀ ሀገራት መገለጫ ጦርነት፣ ብጥብጥ፣ ድህነት ወዘተ የሆነበት ምክንያት በቀጥታ ከላይ ከጠቀስኳቸው ሀገሮችና የሀገራዊ መዋቅራቸው ዝምድና ይመዘዛል፡፡ ወይ ሀገራዊ መዋቅር የላቸውም አሊያ አልመረጡም (የተደራጀ ሀገራዊ መዋቅር አለመኖሩም እዚህ ውስጥ ይካተታል)፡፡ ኢትዮጵያ ደሀ ነች ግን ሀገራዊ መዋቅር አላት፡፡ ወደድንም ጠላንም ሀገራዊ መዋቅሯን የሰራላት የዛሬው “መንግስታችን” ኢህአዴግ ነው፡፡ የፓርቲው ፖለቲካዊ ፍልስፍና ግራም ይዝመም ወደ ቀኝም ያጋድል፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ያቀንቀንም አያቀንቅን፣ ግብርና-መርን ይስበክም አይስበክ፣ ዲሞክራሲን ይሰርም ይፍታ (እንደ አቶ አላዛር ኬ አባባል)፣ የምርጫ ኮሮጆ ይቅደድም አይቅደድ፣ የታክሲ ስምሪትን ይተግብርም አይተግብር ወዘተ… የኢህአዴግ አስኳል ፌደራላዊ ስርአቱ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ መዋቅር መኖር የመጀመሪያው ተመስጋኝ ፌደራላዊ ስርአቱን እውን ያደረገው አካል ነው፡፡ ሀገራዊ መዋቅር ሳይንሳዊ መንገድ ነው ብለናል - በጊዜ እየተወቀረ፣ በእውቀት እየተፈተነ፣ ሕዝብ በተሰኘ ቤተ ሙከራ (አቶ አላዛር ኬ. በሚሉት ቃና ሳይሆን) እየተመዘነ እውን የሚሆን ሂደት ነው፡፡ ይህዊን ሀገር ዘውድም፣ ጠመንጃም እንደየጊዜያቸው መርተዋታል፡፡ ያኔም ድህነት አብሯት ነበር፡፡ “አንድ ኢትዮጵያ-ያለልዩነት” በተባለው አዝማች ስር የተዜሙ ሀገራዊ ስንኞች ግን ሁሉንም ድምጽ ስላለመወከላቸው እኔም አቶ አላዛር ኬም እናምናለን፡፡ ከማመን ወደ ተግባር ያሸጋገረን ግን የኢህአዴግ አብዮታዊ ትግል ነው፡፡ ታጋዮቹ በሙስና ይዘፈቁም ምርጫ ያጭበርብሩም፣ ኢትዮጵያ ዛሬ ላስመዘገበችው “አንዳንድ እድገቶች” ተመስጋኞቹ እኛ ነን ይበሉም ወዘተ … ለትግላቸው ግን ልዩነት-የለሽ ክብር አለኝ (ታጋይ አይደለሁም በነገራችን ላይ)፡፡ ሀገራዊ መዋቅሩ የተሰመረበትን ፌደራሊዝም የተባለ ሰሌዳ ስላበረከተልን ብቻ፡፡

አይደለም ደርግን የሚያህል ግዙፍ ወታደራዊ መንግስት ከበታተኑ በኋላ፤ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በምርጫ የተረከቧትን ሀገር እንኳን መምራት ባቃተበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያን ቢያንስ እንደ ሀገር ቅርጽ ይዛ እንድትራመድ ያደረጋት የኢህአዴግ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ምርጫ ነው፡፡ አቶ በረከት ስምኦን ይህንን እውነት በመጽሃፋቸው ባይናገሩ ነበር የሚገርመኝ፡፡ በእያንዳንዱ የመጽሃፋቸው መስመር “ትክክለኛውን፣ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርስ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የሚከተለው ፓርቲዬ ኢህአዴግ ነው!” የሚል ሃሣብ ቢያስተጋቡ ፕሮፖጋንዳም፣ እብሪትም፣ የተዛነፈ የሸሚዝ አቆላለፍም አልለውም፡፡ ተቃዋሚዎቻችንስ??

የደሀ ሀገር ተቃዋሚ ፓርቲዎችና መንግስት

በዛምቢያ ሀገራዊ ምርጫዎች በአንደኛው ሰሞን ነው ይህ ጽሑፍ የተነበበው፡፡ “ዛምቢያን ኢኮኖሚስት” በሰኞ ጥቅምት 6/2008 እትሙ “Are Opposition Parties doomed in Africa?” (የአፍሪካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እየጠፉ ነውን?) ይላል በተለይም የደቡብ አፍሪካ ሀገራት መንግስታትንና የተቃዋሚዎቻቸውን የመምራት አቅም ባነፃፀርበት ጽሑፉ የተወሰኑ የደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት መንግስታትን (በአብዮት ስልጣን የጨበጡትን) በስም በመጥቀስ ተቃዋሚዎቻቸው ለምን በሀገራዊ ምርጫ እንዳሸነፏቸው ወይም “እንደተገዳደሯቸው” በአጭር አረፍተ ነገር ሊያስረዳን ይሞክራል፡፡ “በአብዮታዊ መንግስታቱ ሁለንተናዊ ድክመት በተለይም በኢኮኖሚያዊ እንጂ በተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ጥንካሬ አይደለም” (Contemporary history of former liberation movements that have ascended to power reveals that their downfall from power was necessarily precipitated by their mismanagement of the economy and not their political opponents)

በርካታ እንዲህ አይነት ስሜት ያላቸው ጽሑፎች ለማገላበጥ ስሞክር ሁለት ነገሮች ነው ያስታወሱኝ፡፡ ኢህአዴግን እና ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችንን፡፡ እነ ቅንጅት፣ እነ መድረክ፣ እነ ኢራፓ፣ እነ ኦፌዴን ወዘተ… እና ኢህአዴግ ትውስ አሉኝ፡፡ የአቶ  በረከት እና የአቶ መለስ ዜናዊ ሀገራዊ ናዳ፣ የመስቀል አደባባዩ ቅንጅታዊ ሰልፍ፣ የእነ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የፓርላማ ወጎች፣ የእነ አቶ ልደቱ መፈረጅ፣ የእነ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እስር፣ የኢቲቪ አኬልዳማ፣ እነ ሰይፈ ነበልባል ወዘተ … እየተደራረቡ ታዩኝ፡፡ የመደምደሚያ ጥያቄዬ ግን አንድ ብቻ ሆነ፡፡ “እውነት የሀገሬ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን መምራት አይችሉም?” የሚል፡፡ መልሱን ከዚህ ቀጥሎ እንዲህ ሞከርኩት፡-

በመልስ ፍለጋዬ የመጀመሪያ ሙከራ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ምንነት በአለም አቀፍ ደረጃ መጠየቅ ቀደመ፡፡ ከወደ ካናዳ አካባቢ ያገኘሁት “የተቃዋሚ ፓርቲነት” ፍቺና ሚና በጥቅሉ አለምአቀፋዊ መልክ ስላለው መረጥኩት፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና ይላል የካናዳዎች ትርጓሜ “የመንግስትን ፖሊሲዎች በመተቸት መንግስትን ይቃወማል፣ አማራጭ መንገዶችን ያስቀምጣል፣ ስለ መንግስት አስተዳደራዊ ጉዳዮች ለሕዝብ መረጃ ያቀብላል”፡፡ ይህን ትርጓሜ እንደ አግባቢ መነሻ በመውሰድ፣ የበርካታ ሀገራትን መንግስታትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግንኙነት ፈተሽኩ፡፡ ብዙ ዓይነት መልክ አላቸው፡፡ በብዝሃ ፓርቲ እንመራለን፣ አይ በአንድ ፖርቲ ከተመራን መች አነሰን?፣ ሁለት ሶስት ግዙፍ ፓርቲዎች ካሉን ይበቃል? ወዘተ … ይላሉ የአለማችን ሀገራት፡፡ ዴሞክራሲያቸው ዳብሯል፣ የኢኮኖሚ ዋልታቸው በቀላሉ አይናወጥም ስልጣኔያቸው ጫፍ ነክቷል የሚባሉት ሀገራት ግን በመርህ ደረጃ የብዝሃ ፓርቲ ፖለቲካን እናራምዳለን ይበሉ እንጂ እውነታው በሁለት አሊያ በሶስት አውራ ፓርቲዎች ሥራ መውደቃቸው ነው፡፡ የእያንዳንዱ ፓርቲ ዲሞክራያዊ ብዝሃነት እንዳለ ሆኖ እንደ ሀገር ሲቃኙ ግን ቁጥራቸው ከሁለትና ከሶስት አይበልጥም፡፡ እንደውም በርካታ ጽሑፎች የእነዚህን ሀገራት የፓርቲዎች ልዩነት “ሁለት አይነት መሳይ ግን አንድ የሆነ” ይሉታል፡፡ ሮጀር ኮኸን የተባለ ፀሐፊ በ `The New York Times` የጥር 21 2010 እትም የአንድ ፓርቲ ዲሞክራሲ” (Single-Party Democracy) ሲሉ ባስነበቡበት ጽሑፍ፤ “ታላቁን” የአሜሪካ ፖለቲካ የአንድ ፓርቲ ዲሞክራሲ መገለጫ በማድረግ Oxymoron ሲሉ በአንዲት እምቅ ቃል ይገልፁታል፡፡ ተቃራኒ የሚመስሉ ሁለት ቃላትን የያዘ አረፍተ ነገር እንደ ማለት ነው፡፡ “የአሜሪካ ምርጫም በሁለት ተቃራኒ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ የሚመስል ግን በአንድ ፓርቲ ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ ነው” ማለታቸው ነው ፀሃፊው፡፡ ለጽሑፌ እንደዋና ማጠንጠኛ የሚሆን ሀሣብ ስለሰጡኝ ፀሃፊውን አመስግኜያለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ጸሃፊው የአንድ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚባል ፖለቲካዊ ፍልስፍና በይፋ አለ ብለው አያምኑም፡፡ ግን ይላሉ የአሜሪካን ፖለቲካዊ ፍልስፍና በመጥቀስ ብዝበዛ ፓርቲ ዴሞክራሲ ተሸፍኖ ምናልባትም 21ኛውን ክፍለ ዘመን እየመራ ያለው እሱ ነው - የአንድ ፓርቲ ዲሞክራሲ፡፡

በተለይም ከመግቢያዬ ለመጥቀስ የሞከርኩትን የፕሬዚዳንት ኦባማ ደጋፊዎች ወቀሳ ፍካሬያዊ ትርጉም ከሮጀር ኮኸን ጽሑፍ ጋር አዋህጄ ለመረዳት ስሞክር “አንዲትን ሀገር በሰላም የሚመራት፣ ወይም በዲሞክራሲ ስርአት ውስጥ ነች የሚያስብላት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዛት እና የገዢ ፓርቲው በምርጫ መሸነፍ ብቻ አይደለም፡፡ የተደራጀው ሃገራዊ መዋቅሯ፣ በየትውልዱ የተፈተነው ፖለቲካል ኢኮኖሚዋ እንጂ” የሚል ጎምዛዛ እውነት አገኛለሁ፡፡ በተለይ ለሀገሬ ምላስ እውነቱ ጐምዛዛ ነው፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ይልቅ በቅድሚያ ሀገሪቱ የምትመራበት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በሕዝብ አመራር (የመንግስትም የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ማለት ናቸው ሕዝብ ማለት) እንዳይፈርስ ሆኖ መገንባት አለበት፡፡ ከዚያ በኋላ ዲሞክራቶችም መጡ ሪፖብሊካኖች ሀገር በአንፃራዊ ስም “የዴሞክራሲ መገለጫ” እየተባለች ትቀጥላለች፡፡ ይህ ማለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገዢው ፓርቲ አጨብጫቢዎች ይሁኑ የሚል የዋህ ፍቺ እንዳይሰጠው አደራ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን ለፌደራላዊ ስርአቱ ተአማኒ እውቅና ይስጡ፣ ኢህአዴግ በተባለው መንግሥት ሥር ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ስለተገነባችው ደሀዋና - ሀብታሟ ኢትዮጵያ እውቀት ይኑራቸው፡፡ ከፋፍሎ በመግዛት፣ በብሔርተኝነት፣ በጎሰኝነትና በፌደራሊዝም መካከል ስላለው ልዩነት ግንዛቤ ይኑራቸው - ቢያንስ ከኢህአዴግ የሚሻል ግንዛቤ፡፡ የአቶ አላዘር ኬ እና የአቶ በረከት ስምኦንን (የኢህአዴግን ቋንቋ ልጠቀመውና) ከዜሮ ድምር ፖለቲካቸው ይውጡ፡፡

እስቲ በአንድ ቀላል ጥያቄ ስር የሀገራችንን ተቃዋሚ ፓርቲዎት ሁለንተናዊ አቅም አስቀምጠን እንፈትሸው፡፡ “ለመሆኑ ከተቃማዊ ፓርቲዎቻችን መካከል የትኛው ነው ኢህአዴግ የሰራትን የዛሬይቱን ኢትዮጵያ መምራት የሚችለው” የምርጫ 97ቱ የመስቀል አደባባይ ሰልፈኛ “ኢትዮጵያውያንን” የመወከል አቅም ነበረውን?፣ በወቅቱ መስታወት ከሰበሩ፣ ጎማ አቃጥለው መንገድ ከዘጉ ወጣቶች መካከል ዛሬ ስንቶቹ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተዋል?፣ ጥይት ከበላቸው ወጣቶች መሀል ስንቶቹ ነበሩ ቅንጅት ስለተባለው ፓርቲያቸዉ ፖለቲካዊ ፍልስፍና እውቀቱ የነበራቸው?፣ ወዘተ … የሚሉ ጥያቄዎችን እናንሳና የሀገራችንን የመቃወም ፖለቲካ ቀለም ዓይነቱን እንለይ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎቻችንን ተቋማዊ አቅም ከሀገሪቱ ፍላጎት አኳያ እንቃኘው እስቲ፡፡ “የመንግስትን ደካማ ጎን መተቸት ብቻውን ተቃዋሚ የሚያሰኝበት ሀገር ውስጥ ነን፡፡” በሚሉ ፓርቲዎች ተመርተን የት ልንደርስ እንደምንችልም በድፍረት ራሳችንን እንሞግት፡፡ የዲሞክራሲ ውበቱ፣ የዲሞክሲ ፖለቲካዊ ፍቺው ገዥ መንግስትን ከስልጣን በምርጫ በማውረድ ብቻ አይመዘንም፡፡ መሪዎቹ እኩል መሆን አለባቸው፣ ተፎካካሪዎቹ በቅድሚያ ሀገር በሚባል ጣሪያ ስር መጠለል ይገባቸዋል፡፡ ጣሪያው ከማስተዋል፣ ከእውቀት፣ ከታሪክ ይሰራል፡፡ ዛሬ በዲሞክራሲዊ ምርጫ ይተዳደራሉ፣ ለብዝሃ ፓርቲ መዳበር ቀን ከሌት ይተጋሉ እያልን የምናወድሳቸው ሀገራት ስኬታቸው የፖለቲካን ሳይንሳዊ ጣእም ከቀመሱባት እለት ይጀምራል፡፡ ዲሞክራሲ የሚለውን ቃል እንደ መተዳደሪያ መጥራት ከጀመሩ በርካታ መቶ አመታት አልፈዋል፡፡ በከባባድ ጦርነቶች ውስጥ አልፈው፣ በርካታ የኢንዱስትሪ አብዮቶችን አካሂደው፣ በአያሌ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሽግግሮች ታጅበው ነው በሁሉም ዘንድ የሚታይ ሀገራዊ መዋቅር የዘረጉት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎቻቸው አብዮቱን ከመሩት እኩል እድሜ አላቸው፤ በፋይናንስ፣ በሠው ኃብትና፣ በሀገራዊ አረዳድ ከገዢው ፓርቲ ያላነሰ አቅም አላቸው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ውጣ ውረዶች ውስጥ አብሯቸው የነበረ ሕዝብ ደግሞ በንቃት ይከተላቸዋል፡፡ ሲያጠፉ እየወቀሰ፣ ሲያፌዙበት እየቀጣ፣ ሳይመጥኑት ሲቀሩ እየሸኘ በንቃት ይከታተላቸዋል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ የምርጫ ካርዱን ግብር በአግባቡ ለከፈለላት ሀገሩ፣ ለቋንቋው፣ ለባህሉ፣ ለሉአላዊነቱ ሲል ይጠቀምበታል፡፡ ስለዚህ የዲሞክራሲያዊ ስርአቱ ፍሬ በተቃዋሚዎችና በገዢ ፓርቲ እንኪያ ሰላንቲያና በምርጫ ውዝግቦቻቸው ብቻ አይጎመራም፡፡ በርካታ ሀገራዊ ምእራፎችን የተሻገረ ሕዝባዊ ታሪክና መሠረት ያስፈልጋል፡፡ ይሄን መሰረታዊ የፖለቲካ ግብአት ያሟሉ ተቃዋሚዎችና ዜጎች እስኪፈጠሩ ድረስ ኢትዮጵያም ቅርጿን በሰጣት ኢህአዴግ እጅ መሰንበቷ አያጠራጥረኝም፡፡ ቀደም ሲል የወቀስኳቸው አይነት ተቃዋሚዎችና ዜጎች እንዲፈጠሩ መንግስት ድርሻ የለውም አለማለቴ መቼም ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ የተሻለ ጥረት ማድረግ እንደሚገባውም ጭምር፡፡

አንድ በረዥም የትጥቅም ትግል ስልጣን የያዘ የደሀ ሀገር መንግስት፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በበሬ የምታርስን ሀገር የተረከበ መንግስት ከምንም በላይ ታጋሽ ሕዝብና አስተዋይ ተቃዋሚዎች ስጠኝ ብሎ ነው የፖለቲካ አምላኩን የሚማፀነው፡፡ የራበው ሕዝብ በየሰከንዱ ይበሳጫል፣ ደሀ ሕዝብ በለውጥ ዝግመታዊነት አያምንም፣ ፖለቲካን ከመቃወም ይጀምራል፡፡ ይሄኔ የሚናበቡ ፈጣን ለውጦች ማስመዝገብ፣ አፋጣኝና ችግር ፈች የሆኑ ፖሊሲዎች መቅረጽ የመንግስት ፈተናዎች ይሆናሉ፡፡ የሚሰራ ደግሞ ይሳሳታል፡፡ ሳታፈርስ አትገነባም፡፡ ኧረ እንደውም ቁጣዎችን ሊያፍን፣ በሥራዬ መጡ የሚላቸዉን ሊያስር፣ እንደ አቶ አላዛር ኬ አባባል “ዲሞክራሲን ሊያስር” ይችላል፡፡  እዚህች ጋ የመስከረም 8/2009ኙ የ The New York Times ዘገባ ትዝ አለኝ፡፡ ቶማስ ኤል.ፍሬድማን ይባላሉ ጸሃፊው፡፡ አሁን ቃል በቃል የማስነብባችሁን ገለፃ አርተር ክሮኤበር ከተባሉ ኢኮኖሚስት እንደወሰዱት ተናግረዋል፡፡ “ትልልቅ የሚባሉ የእድገት ታሪኮች ሁሉ ውብ አይደሉም፡፡ በአመት አስር ከመቶ ስታድግ በርካታ ነገሮችን ቁልቁል እየመታህ ነው!” (High Growth stories are not Pretty. If you are growing at 10% a year, a lot of stuff gets knocked down)፡፡ ይሄን የማይካድ ሀቅ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት አይን ስንመለከተው የመንግስትን የቤት ሥራ ያከብድብናል፡፡ አቶ በረከት በመጽሃፋቸው የነገሩን ሀገራዊ ናዳን የመግታት ሩጫ ማለት ይሄው ነው እንግዲህ፡፡ ሳምንት አቶ አላዛር ኬ በ97ቱ ምርጫ ስለነበሩ፣ በኢህአዴግ ስለተቀነባበሩት የጠለፋና የጥምዘዛ ድራማዎች ምነው የአቶ በረከት መጽሃፍ ሳይነግረን አለፈ? የሚለው ጥያቄያቸው የዋህ እሮሮ እና ፖለቲካዊ ለዛውን ያጣብኝ በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ እባክዎ አቶ አላዛር ጥያቄውን ከሃምሳ አመታት በላይ ስልጣን ላይ ለቆዩት ኮሚዩኒስቶቹ ቻይናዎችና፣ ከ60 ምናምን አመታት በኋላ ሥልጣን ለለቀቀው የሜክሲኮው ፒ አር አይ ፓርቲ ያቅርቡላቸው፡፡ ቻይናዊቷ ኢህአዴግማ የበረከት መጽሃፍ ባይፃፍም በገዢ ፓርቲነቷ ገና ለበርካታ አመታት መዝለቋ አይቀርም፡፡ እውነት ኢህአዴግ ቻይናዊ ነው? …

ቻይናዊው ኢህአዴግ

የዛሬው የአለማችን ሁለተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ኮሚኒስታዊ ቅርጿን ከ50 አመታት በፊት ከተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ነው የሳለችው፡፡ በኮሚኒስት ፓርቲዋ መሪነት፡፡ ፓርቲው በመጀመሪያዎቹ አስርት አመታት ያሳለፋቸው እነዚያ መውደቅ መነሳቶች ለዛሬ ስኬቱ አብቅተውታል፡፡ ሕዝባዊት ሪፐብሊካዊት ቻይናን ከመመስረቱ በፊትም ሆነ በኋላ ፓርቲው በሚዋዥቁ የኢኮኖሚ አዋጆቹ፣ በማይበረታቱ ፖለቲካዊ አቋሞቹ (ሸሚዙን አዛንፎ በመቆለፍ) ይታወቅ ነበር፡፡ በርካታ የርእዮት አለም ልዩነቶችን፣ የመደብ ትግሎችን፣ የኃይል ሽሚያዎችንና አወዛጋቢውን የባህል አብዮት ያለመታከት አስተናግዷል፡፡ ከወዳጁ ሶቪየት ሕብረት እስኪያኮራርፈው ድረስ የርዕዮተ አለም እድሳት አካሂዷል ድረስ፡፡ ግን ፈተናዎቹን ሁሉ አልፏቸዋል፡፡ ዛሬ ከግዙፏ ቻይና ፊት ሆነው የመሪነቱን ሚና የሚጫወቱት የፓርቲው ልጆች  ያንን የታሪክ ጊዜ “የሚጠበቅ ነበር” ብለው ነው የሚያስታውሱልን፡፡ አይገርማቸውም፡፡ የሕዝባችን ንቃተ ሕሊና ባልዳበረበት፣ ድህነት ተብትቦ በያዘን በዚያ ሰአት ሀገራችን ከዚያ የተሻለ መልክ እንዲኖራት አንጠብቅም ነበር ባይ ናቸው፡፡ ይልቅስ በወቅቱ ፖለቲካ ማለት “ለቻይና እድገት ብቸኛው መድሃኒት የእኛ ፓርቲ ነው የሚለውን ፍልስፍና በሕዝባችን ዘንድ ማስረጽና ተቃዋሚዎችንንም ባገኘነው ጥበብ ማሸነፍ ነበር” አሉና የሌኒንን ”ምን መሰራት አለበት?” (What is to be done?) ፖለቲካዊ መርህ እየፈከሩ፣ ማእከላዊነትን ዲሞክራሲያዊ በማድረግ ሂደት (Democratic Centralism) ራሳቸዉን እየጠገኑ እዚህ ደረሱ፡፡ 80 ሚሊዮን ደጋፊ ይዘው ነው ከ1.5 ቢሊየን በላይ የሚሆነውን   ሕዝብ እየመሩ ያሉት፡፡

አቶ አላዛር ኬ ከአቶ በረከት መጽሃፍ ተረድቼዋለሁ እንዳሉት ኢህአዴግ ልክ እንደ ቻይናዎቹ ኮሚኒስቶች ከእኔ የተሻለ ኢትዮጵያን መምራት የሚችል ፓርቲ የለም የሚል አቋም ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ እንደእኔ እንደእኔ ኢህአዴግ እውነቱን ነው፡፡ ካድሬ፣ ኮሚኒኬተር፣ ልማታዊ ጋዜጠኛ፣ ተሸላሚ አርሶ አደር፣ ሞዴል ተማሪ፣ የልማት አርበኛ ወዘተ እያለ ማእከላዊነትን የማሰራጨት ፖለቲካዊ አካሄድ በሚገርም ፍጥነት እየተገበረ ነው፡፡ (የጥራቱ ጉዳይ በጥያቄ ምልክት ውስጥ ይግባልኝ) በየትኛውም ስሌት ኢህአዴግን እንደ ፓርቲ መገዳደር የሚችል ተቃዋሚ በአላዲን ፋኖስ እንኳን ቢፈለግ አይገኝም፡፡ በጉልበትም በእውቀትም፡፡ የማይገርመው ነገር ይህ እውነት ለበርካታ አመታት መዝለቁ ነው፡፡ በነዚህ አመታት ውስጥ ታዲያ “የአስገራሚዎቹ” ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን ሚና ያው የሀገራዊ ምርጫ ሰሞን ብቅ እያሉ በፖስተሮቻቸው አጥራችንን ከማዥጐርጐር አይዘሉም፡፡ ግን እስከመቼ?

ኢህአዴግ ከሀገር እኩል ፓርቲ ሆኖ (State Party) እስከ መቼ ይቆያል? ታሪክ በግልጽ ይመልሰዋል፣ ራሱ ኢህአዴግም የሚያውቀው ይመስለኛል፡፡ በበርካታ አገራት አብዮታዊ ትግሎችን መርተው ስልጣን የጨበጡ መንግስታትን ብቸኛው የማሸነፊያ መንገድ የህዝብ ብሶት ነው፡፡ ህዝብ በኢኮኖሚ ድቀት፣ በተስፋ መቁረጥ፣ በለውጥ እጦት ወዘተ … ሲዘፈቅ መንግስትን የመጣል አቅም ያገኛል፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚዎች ቢኖሩም ባይኖሩም፡፡ እነ አቶ አላዛርኬ በኢህአዴግ እብሪታዊ አመራር በርካታ ዜጐች በድህነት ፍዳቸውን እያዩ ነው ቢሉም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው እውነት ግን እሳቸው ባሉት ደረጃ የሚገለጽ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የድህነቱን መጠን አይደለም፣ ድህነቱ በኢህአዴግ የአመራር ግድፈት የመጣ መሆኑን እንጂ፡፡ ይህ የኢህአዴግን 20 አመታት ከአሜሪካውያኑ 20 አመታት ጋር እኩል የማነፃፀር አመክንዮዋዊ ስህተት ያስከትላል፡፡ አዎ የኔልሰን ማንዴላና የአቶ መለስ ዜናዊ 20 አመታት እኩል አይደሉም፡፡ በፍጹም፡፡ የኢህአዴግ የሊዝ አዋጅ አወዛጋቢነት እኮ በኢህአዴግ ስህተት ብቻ መለካት የለበትም፡፡ ግብር መክፈል የሚያመው ባለሀብት የሞላባትን ሀገር የሚመራ መንግስት በየቀኑ ቢደናበር እንኳን አይገርመኝም፡፡

ስለዚህ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ የሚቆይበትን እድሜ ለማስረዘም ብቻ ሙሉ ሀይሉን የሚያባክንበት ጊዜ አልፏል፡፡ ፖለቲካዊ አካሄዶች ቻይናዊ ቀለም አላቸው፡፡ ሙሉ ቻይናዊ ለመባል ግን የእድገት ፍጥነትን ከሀገራዊ ናዳው አመለጥኩ ባለበት ፍጥነት ማስኬድ ይጠበቅበታል - ልክ እንደ ቻይና፡፡ ዛሬ በገሀድ ለምናያቸው ችግሮቹ መፍትሄ እስካልሰጠ ድረስ የውደቀቱ ፍጥነት ይጨምራል፡፡ ኢህአዴግ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ካስመገዘባቸው ደሳስ የሚሉ ለውጦች ጎን ለጎን በአስቀያሚ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ በአደገኛ የሚዲያ አጠቃቀም፣ በሀይል ቀውስ፣ እውቀት በጎደለው የአባላት ምልመላ፣ በሙስና ወዘተ … ተከቧል፡፡ ሺ ፎቅ ቢነገባ፣ ሽንጣም መንገዶች በየገጠሩ ቢዘረጉም ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ችግሮች በጊዜው ካልተፈቱ ነገ የሀገራዊ ናዳ ቅመም ሆነው መምጣታቸው አይቀርም፡፡  ደሀውን የሕብረተሰብ ክፍል ያማከሉ የቅርብ ጊዜ ፖሊሲዎችን በማጠናከር የሚያገኛቸውን ትርፎች ማጠራቀም አለበት፡፡ የገቢ አሰባሰብ ስርአቱን በበለጠ ሕዝባዊ ንቃት ማጀብ፣ ጠንካራና በፈጠራ የሚመራ የሚዲያ ፍልስፍና መከተል እና የትምህርት ፖሊሲውን ችግር ፈቺነት በንቃት መከታተል አለበት፡፡ ትምህርት ብቻውን 1.5 ቢሊዮን ሕዝብን ለ60 አመት መምራት የሚችል ፓርቲ ይፈጥራል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎቻችን  ጊዜ ግን ገና ነው፡፡ በጣም ገና፡፡

 

 

Read 3724 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 10:48