Saturday, 14 January 2012 10:56

የዘመን ሐሳብ ጥያቄ

Written by  ሰሎሞን አበበ ቸኮል (Saache43@yahoo.com
Rate this item
(0 votes)

እነሆ ይሄው ገና የተባለው በዓል ሆነ፡፡ ይህን ተገን ያደረገው የፈረንጆች ዘመን መለወጫም ሆነ፡፡ ዘመንን ለመቁጠር መነሻ ከሆኑት ጥንታትም (Epochs) አንዱ የሆነው ይሄው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያውያን ያሉት ከሌሎቹ በተለየ ቀን የሚያከብሩበትና ከልደቱ ተጀምሮ የሚቆጠረውን የዓመት ቁጥር በሰባትና በስምንት ዓመት ተለይተው የሚገኙበት መሠረትም ይሄው አንዱ ዕለት ነው፡፡ለዚህ ለኢትዮጵያውያኑ የቁጥር መለየት ሌሎች የቀረባቸውን አንድ ምክንያት ሲያሰሙ ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በብሔራዊ ደረጃ የምትጠቀምበት ሐሳበ ዘመን የጁሊያን ካሌንደር በመሆኑ ነው ብለው ይዘጋሉ፡፡

ይህንኑ የተመለከቱ ሙግቶችና ሥራዎች እስኪታክቱ ድረስ “የኢትዮጵያ ሚሌኒየም” የተባለ በዓል መንግሥት በአዋጅ ባከበረበት ጊዜ ተነስተው ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያ መቁጠሪያ ጁሊያን ያለመሆኑን በተጨባጭ የገለጡት ባይስተዋሉ፣ በዓሉን ሊያስከብር የተሰየመው አካል እንዲከናወን ባደረገውና በቀጥታ በቲቪ ይተላለፍ በነበረ የምሁራን ጉባዔ ከጁሊያንነት ወደ አሌግሳንድሪያንነት የተቀየረበት ጥናት ቀርቦ ነበር፡፡ ይህ መቁጠሪያ የታላቁ አሌክሳንደር ስም እንዲያዝበት የፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ጥናታዊ ወረቀት አስገንዝቦ ነበር፡፡ያም ሁሉ ዋጋ አልነበረውም፡፡ ዘንድሮ ከሳምንታት በፊት በተከናወነው “ታሪካዊ”ው የአይካሳ ስብሰባ ላይ የተለቀቁ የቱሪዝምና ባህል ሚኒስቴር መፅሄትና ዲቪዲ ያንኑ ነባር ስሙን የያዙ ነበሩ፡፡ “ኢትዮጵያ - ዘ ክራድል ኦፍ ማንካይንድ“ ተብሎ የተጠራው ዲቪዲ “ለየት ያለው ጁሊያን ካሌንደር” ብሎ በሦስት የውጭ ቋንቋዎች ያስተዋውቀዋል፡፡ “ዲስከቨር ኢትዮጵያ” የተባለው መጽሔትም እንዲሁ ይጠራዋል፡፡ ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ብዙ ተብሏል፡፡ አሁንም ይኼው ጉዳይ እንዲነሳ ግድ የሚለው፣ ስለ አገሪቱ ቅርሶች የሚመለከተው ሚኒስቴር በበተነው ፅሁፍ ያንኑ በሌላ መንገድ ይበልጥ ገባ ብሎ አመጣው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ መቁጠሪያ ሊጠናባቸውና ሊመረመርባቸው በሚችሉ መመልከቻዎች መሞገትን ያዝን፡፡ በቀጥታ ወደዚያው እንለፍ፡-

1. ከአገላለጡና ከአከፋፈሉ አንፃር

አንድ “ካሌንደር” በቅድሚያ የሚለካውንና የሚቆጥረውን ጊዜ ምንነት ተረድቶ - አስረድቶ፣ በዚያው ፍቺውና ግንዛቤው መሰረት ዘመናቱን ከፍሎ ዓመት፣ ወር፣ ዕለት…. በማለት መሰረታዊ የሆኑ ክፍሎቹን ይይዛል፡፡ መሰረታዊ አሐዶችን (units) በመያዝም፤ የእነዚያኑ ዓውዶች ወደመለየቱና ወደመለካቱ - መቁጠሩም ያመራል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ ከዚያ ወዲህ፣ አንድን መቁጠሪያ ‘የተሟላ’ እና ‘የተጠናቀቀ’ (complete & full) የሚያስብሉ መመልከቻ ነጥቦችም ከነዚህ መሠረታውያን ጉዳዮች በመነሳት የሚጠየቁ ናቸው፡፡ ማለትም፡- ‘የሚቆጠረውን ጊዜ ወይም ዘመን እንዴት አድርጐ ይፈታዋል?’ እንዲሁም፣ “ዘመኑንስ እንዴት አድርጐ ይከፍለዋል?’ በሚሉዋቸው ጥያቄዎች፡፡ ከነዚሁ ተከትሎ የሚመጣው ጥያቄ ደግሞ የየመቁጠሪያው አሐዶች (ክፍላተ ዘመን) ብዛትና አይነት ናቸው፡፡

እነዚህ ነጥቦች አንዱን ካሌንደር ከአንዱ ለመለየትና አንዱን ራሱን ለማወቅና ለማጥናትም መነሻና መሠረታዊ ጉዳዮች ይሆናሉ፡፡ አሁንም እያንዳንዱን መሰረታዊ ጉዳይ ቀዳሚ አድርገን፣ በጥቅል - ጥቅሉ፣ በማነሳሳት የኢትዮጵያውያንን ከጁሊያን ዓይነቱና ሌሎች በርሱ ከሚለጠፉ ካሌንደሮች ጋር እያናፀርን እንመለከታለን፡፡

የዘመን አገላለጽ (አፈታት)፡- ጊዜ ወደሚቆጠርበት ደረጃ ወርዶ ሲገኝ ዘመን ይባላል፡፡ ግር ሊያሰኝ ቢችልም፣ ‘ዴት’ የሚሉትም ይኼንኑ ነው፡፡ ይህን በሌላ አገላለጽ፡- “ቁጥር (መለያ፣ መቁጠሪያ፣ …) ያለው ጊዜ ዘመን ይባላል” ሲል ጋዜጠኛውና የሐሳበ ዘመን መምሕር የሆነው ሄኖክ ያሬድ ገልፆታል፡፡ (በቅንፍ ያሉት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ተጨማሪ ማብራሪያዎች ናቸው፡፡) ይበልጥ አንድ ባንድ በመጥራት ስንገልጻቸው፡- ዓመት፣ ወቅት፣ ወር፣ ዕለት፣ … እያልን የምንጠራቸው የጊዜ ክፋዮች ሁሉ የዚሁ የዘመን ክፍሎች፣ ዓይነቶች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

“ካሌንደሮቹ ይህን ዘመን የተባለ ምንት ምን ብለው ይገልጿቸዋል?” የሚለው ጥያቄም ለያንዳንዱ መቁጠሪያ ቁልፍ ጥያቄ ይሆናል፡፡ ወይም መሆን አለበት፣ አሊያም ነበረበት፡፡ ምክንያቱም ይህንኑ ሊለኩ፣ ሊቆጥሩ፣ ለይተው ሊጠቁሙ ነውና በቅድሚያ ምንነቱን ማወቅ አለባቸው፡፡ ምናልባትም ከዚሁ መረዳታቸው ጀምሮም ይሆናል አንድነቱም ይሁን መለያየቱ የሚጀምረው፡፡

የኢትዮጵያ ሐሳበ ዘመን ቁልጭ ያለ ፍቺን አስቀምጦለት ይነሳል፡፡ በሐሳበ ዘመኑ መምሕራን ዘንድ በአቀራረቡ ተወዳጅነት የተነሣ መጽሐፉ በደራሲው ስም እየተጠራ የሚገኘው “አቡሻክር”፤ በተለይ በምክር መልክ የጻፈው በመሆኑ የሱን እንዳለ በመጥቀስ የሐሳቡ የዘመን አገላለጥ እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን፡፡

“ወንበል ፍካሬሁሰ ለዘመን በውስተ ልብ ወሰነ ጊዜ ውእቱ በኩሉ ጊዜ፡፡”

“በልባችን የዘመን ትርጓሜስ በመላው ጊዜ ውስጥ ያለ የቀጠሮ ጊዜ ነው እንበል” ይላል፡፡

ከዓለም መፈጠር ጀምሮ፣ “(የፈጣሪ) የሥራው መቁጠሪያ የሆነ ጊዜ” (ብርሃኑ አድማሱ፣ በዓላት) ውስጥ የሚገኝ “ወሰነ ጊዜ” ወይም “የቀጠሮ ጊዜ” ነው ይለዋል፡፡ በሌላ ስሙም “ጊዜ ዕድሜ” ብሎ ይጠራዋል፡፡ የኢት/ሐሳብ እንዲህ አድርጐ በመግለጽና በዚሁ ገለጻ ላይ በመመሥረት የተዋቀረ፣ የተሠራ ሐሳበ ዘመን ነው፡፡

በሌሎቹ፣ ከዚህ ከኢትዮጵያ ሐሳበ ዘመን ጋር በማይጠፉ ስሞች፣ በተለይም በዚህ ሐ.ዘ ላይ እንደ ንግድ ምልክት እየተለጠፉ ከሚገኙት የጁሊየስ ቄሣራዊውም ሆነ የታላቁ እስክንድር መቁጠሪያዎች ላይ ግን ቀድሞ ነገር ምን ማለት እንደሆነ በቀጥታ ፈትተው የሚጀምሩት ሆነው እንኳን አናገኛቸውም፡፡ በቀጥታ ዘመኖች የተባሉትን በመያዝ ወደ ልኬታቸው እና ቆጠራቸው ሲገቡ ብቻ እናገኛለን፡፡ ዓመት፣ ወርና ዕለት የተባሉትን እንዳሉ አንስተው ወደ መለያ - መቁጠሪያቸው ሲገቡ ነው የምናገኛቸው፡፡

- ይህ ምንን ያመላክተናል? …

እነዚህ ሐሳባት አስቀድሞ ከተመሠረተ ሐሳብ ላይ ተነሥተው የተሠሩ፣ የተጠሩና የታወጁ መሆናቸውን ያመለክተናል፡፡ በእርግጥም ከልደት በፊት በ319ኛው ዓመት ላይ፣ ራሱ የነገሠበትን ዘመን የዓመት ዘመን ቁጥር መነሻ (epoch) ያደረገው  የአሌክሳንድሪያን ሐሳብ አምጭ ታላቁ እስክንድርም ሆነ፣ ከልደት በፊት በ46ኛው ዓመት ጂሊያን የተባለውን የዘመን መቁጠሪያ ሐሳብ አሠርቶ ያወጀው የሮማው ጄኔራል ጁሊየስ፤ ዓመት፣ ወር እና ዕለት የሚባሉትን ዘመኖች እንዳሉ ይዘው የተነሡ መቁጠሪያዎች ነበሩ፡፡ ከሥር ከመሠረቱ የራሳቸውን የዘመን አፈታት ገልጸው የተነሡ አልነበሩም፤ ሊሆኑም አይችሉም …  ግና በቃለ ነቢብ ባይገልጹት፣ እያንዳንዱ ሐሳብ ስለየትኛውም ዘመን ያለውን ግንዛቤ፣ ዘመን/ዘመናት ብለው መርጠው በያዟቸው ላይ ያላቸው አያያዝ ምን ዓይነት የዘመን አገላለጥን እንደያዙ ለመረዳት ያስችለናል፡፡ ዓመታቸው ምንድነው? ወራቸውስ? … ብለን ለመጠየቅ ስለሚቻል፣ በቀጥታ ገልጸው ያላስቀመጡትን የዘመን/ዘመናት ግንዛቤያቸውን እንገልጥባቸዋለን፡፡

ዓመትም ይሁን ወር፣ ዕለትም ይሁን ሌላ፣ በነዚህ ዕድሜ ልክ ኢትዮጵያዊው የዘመን መቁጠሪያ ላይ ተለጥፈው በኖሩት ሐሳባት ዘንድ በምድርና በብርሃናት (ፀሐይ፣ ጨረቃ …) ሥርዓት ወይም ከነዚህ አንዱ በሌላው ዓውድ በሚያደርገው ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴ (ዑደት) የሚፈጠር የጊዜ መጠን ነው፡፡ ሳይንስ ዘዋሪቷ ምድር እንጂ ፀሐይ አይደለችም እስካለበት ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ በተቃራኒው ዘዋሪቷን በማስቀመጥ፣ ወራቸውንና ዕለታቸውን ከተፈጥሮዓዊያኑ አካላት እንቅስቃሴ ጋር አያይዘው የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ የነዚያኑ ውጤት የሆነ የጊዜ ርዝመት “ዓመት/ዓውደ ዓመት”፤ ምድሪቱ ገጿን ተራ በተራ ለፀሐይ የምትሰጥበትን ሹረት ደግሞ “ዕለት” የተባለ ዘመን (ዴት) እያደረጉ ወደ መቁጠር-ማስቆጠሩ እንደገቡ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ የትኛውም ይሁን፣ በነሱ ዘንድ ዘመን የተባለው ምንት የሰማይ አካላትና ምድር ባላቸው ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴ አማካኝነት የሚከሠት የጊዜ መጠን ነው ማለትን ብቻ የሚያውቁ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሐሳበ ዘመን ግን እንዲህ ካለ የወረደና የቀረበ፣ የጊዜንና የዘመንን ተፈጥሮ ከተወሰኑ ዓለማት እንቅስቃሴ የሚያይዝ፣ ጊዜ ከዓለማቱ እንቅስቃሴ የሚወለድ አድርጐ አይነሳም፡፡ ዓለማት ከጊዜም ሆነ “ከዘመን የቀደሙ አያደርግም፡፡ የጊዜና ዘመን ወላጅ አባት - እናቶች የምድሪቱ በፀሐይ ዙሪያ መዞር ወይም በራሷ ዛቢያ መሾር በማድረግ የሚነሳ ተራና ምሉዕነት የሌለው ሐሳብ አይደለም፡፡ (ከብርሃናት አንፃር በምናነፃፅርበት ጊዜ የምንመለከተው ስለሆነ፣ ከአፈታታቸው ጀምሮ እየቅል መሆናቸውን ለመያዝ ያህል የጠቆምነው ይብቃን፡፡)

ከዘመን አከፋፈል አንጻር፡-

ሀ. ሦስቱ ክፍላተ ዘመን፡-

ዘመን የተባለን ምንት ከላይ በተጠቀሰው መልክ፣ ደረቅ ዘላለማዊና ፍፁማዊ ባልሆነ (ኒውተን እንዳሰበው external & absolute ሳያደርግ) የሚፈታው የኢት/ሐ/ዘመን ቀጥሎ ዘመን የተባለውን ክፍሎች ወደመቁጠሩ፣ ከፍሎ ወደ መመልከቱ ይገባል፡፡

“ይህ ወሰነ ጊዜ የተባለ፣ ጊዜ ዕድሜም የሚባል ዘመን (በመጀመሪያ) በሦስት “መንገላት” ይወሰዳል፣” ይላል፡፡

“መንገላት” የሚለው አቅጣጫዎች፣ መንገዶች በሚሉ ቃሎች የሚተካ ነው፡፡ ዘመን “በሦስት መንገዶች/አቅጣጮች ይወሰዳል፣ ይከፈላል” ካለ በኋላ፡-

“እነዚህም፡- ዘኃለፈ (ያለፈው)፣ ወዘይመጽእ (የሚመጣው)፣ ወዘሀሎ (ያለው) ይላል፡፡ ይህ ማለት ትናንት፣ ዛሬና ነገ” ማለት ነው፡፡ ወይም “ያለፈው ጊዜ፣ ያለው (የአሁን) ጊዜና የሚመጣው (የወደፊት) ጊዜ” ማለቱን ያስተውሏል፡፡

ይህንን ቀዳሚ አከፋፈል፣ እንደ አንድ መሠረታዊ የዘመን ክፋዮች አድርገው ለማስቀመጥ “ጁሊያን” እና “አሌግዛንደራዊው”ን ሐሳባት የሚበቁ አድርገን ካሰብን ቀድሞ ነገር የያዝነው ጉዳይ ገና አልተገለጸልንም እንደ ማለት ይመስላል፡፡ እነዚህ ሐሳባት እንደ መሠረተ ሐሳብ እነዚህን ሦስት ክፍላት ገልጸው ለማስቀመጥ ከመነሻቸው በተፈጥሮአዊዎቹ አካላት ላይ የወደቀ ዘመንን መያዝ የለባቸውም፡፡ በሌላ ግንዛቤ፣ በሳይንሳዊው አገላለጽ “ሊኒየር” የተባለ ኒውተናዊ ጊዜን ሊቆጥሩ የተነሡ መሆናቸውን ስናስብ፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ጊዜን በእነደነስቴፊን ሆውኪንግ ዓይነቱ፣ (“ሊኒየር” ያልሆነ ባለሦስት አቅጣጫ፡- the past, present & future) በሥዕልም የተገለጸውን ዓይነት አለመሆናቸውን ሠርሥረን ስናይባቸው ከዚህ ዓይነቱ አገላለጽ የማይደርሱ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡

እንዲህ ሳንመራመርም፣ ዓመት፣ ወር … ተብለው የተጠሩትን አንጠልጥለው የገቡ እንደሆነ ስናውቅ፣ ከዚህ አስቀድሞ የነበሩትን እነዚህን ሦስት አከፋፈሎችን እናገኝባቸዋለን ብለን አናስብም፡፡ በእርግጥም፣ በሚገባው ስፋትና ብዛት በተጠናውና በተገለጸው ጁሊያን ካሌንደር ላይ እንዲህ “በሦስት መንገላት ይወሰዳል” የሚለውን አገላለጽና አከፋፈል አታገኙበትም፡፡ የዚህን ያህል ባይጸናም፣ እንደ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ያሉት በወረቀቶቻቸው አዲስ ሊለጥፉት የሞከሩት “አሌግዛንድሪያን”ም ቢሆን ይህን ያህል የተጠበበ መቁጠሪያም አይደለም፡፡ …

የኢ/ሐ/ዘመን ይህን ዘመንን እንዲህ በሦስት መንገድ ከፍሎ የመገኘቱን ነገር እንደዋዛ ዐይተን የምናልፈው ጉዳይ አለመሆኑን ተከታዮቹን ሁለት ሳይንሳዊ ጥቅሻዎችን ስናገኝ እንረዳዋለን፡፡

ጊዜን በዘመን ከፍሎ መለየት መቁጠር እንዴት ተጀመረ? - ሳይንሳዊ የሆኑ፣ ስለ ጊዜ አጠቃላይ ገለጻን የሚሰጡ ድረገጾችንም፣ የታተሙ መዝገበ ዕውቀቶችን (ኢንሳይክሎፔዲክ ቡክስ/ራይቲንግስ) ክፈቱና የሰው ልጅ ጊዜን በዘመን መቁጠርን እንዴት እንደጀመረ የሚገልጹትን ልቀሙ፡፡ ሁሉም አንድ ሐሳብን ነው በመላ የሚያቀርቡላችሁ፡- የጥንቱ ሰው “ያለፈው፣ ያለው(ያሁኑ) እና የሚመጣው (የወደፊቱ)” የሚሏቸውን ከመገንዘቡ የተነሣ ጊዜውን በዘመን ከፍሎ የመለየትና የመቁጠር ሐሳቡ ጐነቆለበት! ይሏችኋል፡፡

በእርግጥ የሰው ልጅ እነዚህን ሦስት የዘመን መንገዶች ከተረዳ በኋላ ዘመን በሚባል መቁጠሪያ ጊዜውን መለየት - መቁጠር ጀመረ ወይ? የሚለውን ማጣራት ጉዳያችን አይደለም፡፡

እዚህ ላይ፡- እነዚህ ሦስቱ አከፋፈሎች ወይም ግንዛቤዎች ጊዜን በዘመን የመከፈሉና የመቆጠሩ መሠረት ተደርገው መወሰዳቸው፤ ብቻ የምንረዳቸውን ነጥቦች እንጥቀስ፡-

የሰው ልጅ ዘመንን መቁጠር በጀመረበት ጊዜ እነዚህ አከፋፈሎች የነበሩ ብቻ ሳይሆኑ ጥንታዊ አከፋፈልም መሆናቸውን፤

ይህ አከፋፈል ደግሞ የመላው የሰው ዘር የጋራ ግንዛቤ መሆኑ (ዓለምዓቀፋዊና ከመላው የሰው ዘር የጋራ ከሚሆን አንድ ቤት የነበረ መሆኑን) እናጤናለን፡፡ ጥንታዊነቱንና የጋራ መሆኑን ከተገለጸው እንደምንረዳ አስተዋይ ልቡና ይገነዘበዋል፡፡

እንዲህ ተረድተን ስናበቃ ይህን የመሠለው ጥንታዊና የጋራ የሆነ ግንዛቤ ዛሬ ካሉት ካሌንደሮች ሁሉ በሌሎች የትኛውም ዘንድ ያለመገኘቱ፤ በዚሁ በኢት/ሐ/ዘመን ላይ ብቻ ተገልጾ ስናገኘው ደግሞ ምን ይሆን የምንለው …

የጁሊየን ነው! - የአሌክሳንድሪያን … እየተባለ እንዳይገለጥም፣ እንዳይጠናም የተደረገው ይህ ሐሳብ ምን ያህል የራቀ፣ የረቀቀ፣ የሰው ልጆች የጋራ ኃብትም እንደነበር፣ አንመለከትም? በእርግጥም በሳይንሳውያኑ እንደ መላምት የቀረበውንም ለማስረዳት ሕያው መቁጠሪያ ሆኖ እንደሚገኝም ሁሉ ልብ ያለው ልብ ያደርገዋል!

 

2. የስቴፈን ሆውኪንግ ሦስት የጊዜ ገጾች

በሌላ በኩል ደግሞ፣ በዘመናዊው ሳይንስ ጊዜ በነዚህ ሦስት ገጾች የተወሰደበትን ስንመለከት ደግሞ ይህ ሐሳበ ዘመን ከሺ ዓመታት በፊት ይዞት እንደነበረ ስናውቅ የበለጠ ግራሜ ይፈጠርብናል፡፡ ከላይ የቀረበው ከነ አልበርት አነስታይን በፊት ለዘመናት ተገልጾ የቆየ ነው፡፡ ያን ጊዜ በሦስት የተከፈለበትን ግንዛቤ “የጥንቱ ሰው ግንዛቤ” ብቻ አድርጐ የሚተወው ነው፡፡ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ግን ሳይንስ ስለጊዜ ከነበረው የተለየ አገላለጽ ይዞ ተገኘ፡፡ ያም ስቴፈን ሆውኪንግን የጊዜ አጭር ታሪክ የተባለ መጽሐፉን ለመጻፍ አስገደደው፡፡  በዚያ ጽሑፉ ጊዜን ለመግለጽ ቀዳሚዎች አድርጐ ያቀረባቸው እነዚህኑ ሦስት አቅጣጫዎችን ሆነ፡፡ ስለነሱም ሳይንሳዊ መግለጫዎችን ጻፈና ጊዜ በነዚህ ሦስት “መንገላት” የሚወሰድ ተፈጥሮ ወይም “ጠባይዓት” እንዳሉት አቀረበ፡፡

እንግዲህ ምን እንላለን? ከሺዎች አመታት በፊት ይህ ሐሳበ ዘመን አጥብቆ ይዞት የነበረውን አይደለም በሳይንሱም የተደረሰበት?

እዚህ ላይ አንድ ሌላ ነጥብ እንጠያየቅ፡- ኢትዮጵያውያኑ በተለየ አገላለጥ ያቀረቡት መግለጫ ስለጊዜ አንጻራዊነት አስቀድሞ የተገለጸ ሐሳብ እንደሆነ አጢነዋል?

 

ለ. አምስቱ ክፍላተ ዘመኖችን በአሐዶች -የኢ/ሐ/ዘመን አስቀድሞ በ3ቱ “መንገላት” የሚወስደውን ዘመንን፣ እንደገና በ5 የዘመን ክፍሎች ከፍሎ፣ በስም ስማቸው በመለየት ወደ ተግባራዊ ዒላማው ይጠጋል፡፡

“ትልቁ ዓመት ነው፤ ሁለተኛው ወር (ኀ) ሦስተኛውም ዕለት፤ ዓራተኛው ሰዓት፤ አምስተኛውም ኬክሮስ” ይላል፡፡

ሌሎቹ አብዛኞቹ ካሌንደሮች ግን ከነዚህ ሦስቱን ክፍላተ ዘመኖች፤ ማለትም፡- ዓመትን፣ ወርኅንና ዕለትን ብቻ ይዘው እንደሚገኙ ነው የምንረዳው፡፡

እነዚህኑ አምስቱን ክፍለ ዘመንም ነው ሐሳበ ዘመኑ መሠረታዊ አሐዶች ያደረገው፡፡ ለሌሎቹ ደግሞ ሦስቱ ብቻ ለምሣሌ በበርካታ ጽሑፎች ውስጥ ጁሊያንና ግሪጐሪያን “ሰዓት” የተባለውን ክፍለ ዘመን (አሐድ) የየመቁጠሪያው መሠረታዊ አሐድ (fundamental unit) አድርገው አለመያዛቸው ይገለጻል፡፡  ሲጠቀሙበት መገኘታቸውን ግን አልደበቁላቸውም፡፡ …

- “ኬክሮስ” የተባለውንስ የቱ ይሆን ከሐሳበ ዘመኑ ጋር አቆራኝቶ የሚያስበው? …

- በጁሊያን፣ በአሌክዛንድሪያንና ከነዚህ ወዲህ ከተሠሩትም ላይ የማናያቸው ናቸው፡፡ በተለይ በዛሬው ዓለም ብቸኛው ባለ አምስት መሠረታዊ አሐድ የቀን መቁጠሪያ ቢኖር ይህ የኢትዮጵያ ሐሳበ ዘመን ብቻ እንደሆነም መታወቅ አለበት፡፡

ሐ. ደቂቃን አሐዶች፡- በፈረንጆቹ “ሚሊኒየም” ምክንያት ዴቪድ ዱንካን በተባሉ ጸሐፊ “History of calendar” የሚል መጽሐፍ በ1999 ኤ.ዲ ወጥቶ ነበር፡፡ በዚያ መጽሐፍ “ግሪጐሪያን” የሚባል የዘመን መቁጠሪያ ያስፈለገበትን ወይም የጁሊያኑ ላይ ምን እንከን ተገኝቶበት ማሻሻል እንደተፈለገ ይገለጻል፡፡ የአንድ ፀሐያዊ ዓመት ርዝማኔ በጁሊያን 365.25 ቀኖች ሆኖ መገኘቱ እንደነበር ይጠቁምና ይህም ከዓመታት በኋላ (በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ) የ11 ቀን እላፊ ጊዜን አስቆጥሮ እንደተገኘ በማስላት ማሻሻያው እንደተሠራ ያስረዳል፡፡ ማሻሻያው፡- ግሪጐሪያን የተባለው ሲሆን በዚህ መቁጠሪያ መሠረት አንድ ዓመት 365.2324 መሆን እንዳለበት እና እላፊ የተሄደበት የ11 ቀን ጊዜም ቀኑን በ11ቀን ወደ ኋላ፣ ወስዶ በመቁጠር እንዲስተካከል አደረገ፡፡ እዚህ ላይ ተለይቶ መጠቆም የተፈለገው ጁሊያን የተባለው ያንድ ዓመት ርዝመቱን 365.25 ብቻ ለምን አደረገው ተብሎ የተጠቀሰውን ነው፡፡ ጸሐፊው ዋቢዎችን በማስቀመጥም የገለጹት ጁሊያን በተሠራበት ወቅት የሰው ልጅ ሩብና ግማሽ ከማለት ሌላ ከነጥብ በኋላ ሊቀመጡ የሚችሉትንም ከሁለት አኃዞች በላይ ማስቀመጥ ገና ያልቻለበት ዘመን ስለነበር ነው ይላሉ፡፡ አጠቃላይ ድምዳሜው ልክ ባይሆንም ጁሊያን ግን ይበልጥ የደቀቁ ቁጥሮችን የሚያስታምምበት ብልሃት የሌለው መሆኑ ትክክል ነበር፡፡ ከዚህ ስህተት የሆነ አጠቃላይ ድምዳሜ የምንረዳው አንድ ዕውነትም ጁሊያን የደቀቁ መጠኖችን የሚቆጥርበት ደቂቃን አሐዶችንም የማያውቅ መሆኑን ነው፡፡ የሰው ልጅ ደቂቃን የጊዜ መጠኖችን ከጁሊያን በፊት ከ5ሺ ዘመኖች አስቀድሞ፣  በመቁጠሪያ ቁጥሮች ቀይሮ ይቆጥርባቸው የነበሩ መስፈሪያዎች እንደነበሩት የሚያሳውቁ በርካታ ትውፊታዊ የሃይማኖትና ሌሎች መጽሐፎች አሉ፡፡ (ለምሣሌ ክንድ፣ ስንዝር፣ ጋትና …) ባለማስተዋል የተሰነዘረውን ሐሳብ የኢ/ሐ/ዘመንን ለመሰለው አለመሥራቱን በዚሁ ሐሳበ ዘመን በሚገኙት “ደቂቃን” አሐዶች እንረዳለን፡፡  የኢት/ሐሳበ ዘመን ከማይክሮ ማይክሮ ሰከንዶች በታችም እጅግ የደቀቁ የረቀቁ የጊዜ መጠኖችን በመቁጠሪያ ቁጥሮች ቀይሮ የሚቆጥርባቸው ደቂቃን አሐዶች ያሉት ነው፡፡   እነዚህ ደቂቃን የተባሉት፡- ካልዒት (12 ሰከንዶች ያህል ነው)፣ ሣልሲቲ (0.2 ሰከንዶች)፣ ራብዒት (0.003 ሰከንድ)፣ ኃምሴት (የራብዒት አንድ ሳልሰኛ)፣ ሳድሲት (የኃምሲት አንድ-ስልሳኛ) ይባላሉ፡፡ እነዚህም በሐሳበ ዘመኑ ተቆጥሮባቸው የተገኙትን ብቻ በመያዝ እንጂ፣ ከዚህ በታች የወረዱትን መጠኖች በሙሉ ቁጥሮች ለመቁጠር ክፍት ሆኖ የሚገኝ መሆኑን እንመለከታለን፡- ሳብዒት፣ ሳምኒት … እያለ የሚቀጥል ይመስላልና፡፡

***

አንባቢ ሆይ! የዚህ ሐሳበ ዘመን ጁሊያንም፣ አሌግዛንድሪያን አለመሆን እንዲህ  ሳይታይ በድፍኑ የተነገረ መሆኑን ለማሳየት እስካሁን የቀረበው ሁሉ የመቁጠሪያዎች መሠረቶች በሆኑት የዘመን አገላለጥ፣ አከፋፈልና አሐዶች ላይ ባተኰሩ ነጥቦች የታዩ ናቸው፡፡ ከአዕዋዳቱ፣ ከብርሃናቱ፣ እንዲሁም ከአቆጣጠራቸውና ከመለያ-መቁጠሪያቸው አንፃር ደግሞ ከነዚህ የበዙ ልዩነቶችን የምንቆጥርለት ሆኖ እንደሚገኝ እንዲሁ ዕድሉን ካገኘን እንመለከታቸው ይሆናል፡፡

ግና እንዲሁ በመላ ብቻ ይህ ዘመን መቁጠሪያ የጁሊያንና የእከሌ እገሌ መባሉ እስከመቼ ይሆን? የሚመለከተው አካልስ ማን ይሆን? በየቱሪስት መጽሐፉና በሌሎችም በየአጋጣሚው እየተቀባበሉ የሚገልጹት ሰዎችስ ለምን ይሆን የዚህን ሐሳበ ዘመን ልዩነትና ዓለም ዓቀፋዊ ቅርስነት የሚያጠፉት?

… የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃና ጥናትስ ይህ አይመለከተው ይሆን?

 

 

Read 3122 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 10:59