Saturday, 14 January 2012 11:01

ሸጋ ወግ ከዚህም ከዚያም

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(1 Vote)

Sir Richard F.Burton

የተከበራችሁ አንባብያን

አንድ ሰው Sir የሚል ማእረግ የሚያገኘው ለታላቅዋ ብሪታንያ ታላቅ አገልግሎት በመፈፀሙ ንጉሱ (ወይም ንግስቷ) በልዩ ስነስርአት ሲሸልሙት ነው፡፡ በርተን ሰላሳ ዘጠኝ ቋንቋ አጣርቶ ያውቃል፡፡ “አንድ ሺ ከአንድ ሌሊት” የሚባለውን የአረብኛ የተረቶች ስብስብ ተርጉሞ በአስራ ሁለት ቅጽ አሳተመ፡፡ በእንግሊዝኛ ሲያነቡት ከማማሩ የተነሳ፣ ትርጉም ሳይሆን፣ መጀመሪያውኑ በእንግሊዝኛ የተፃፈ ፈጠራ እያነበብን ያለን ይመስለናል፡፡ አመታት ካለፉ በኋላ በርተን ወደ ካይሮ  ሄዶ፣ እዚያ Professional story tellers የሚናገሩቸውን ተረቶች ሰብስቦ ተርጉሞ The New Arabian Nights በሚል ርእስ በአስራ ሁለት ቅጽ አሳተመ፡እነዚህ አስገራሚና አስደሳች ስራዎቹ ለሰው ልጆች ያበረከተልን የስነ ጽሑፍ እሴት ናቸው፡፡

እሱ ቢሆን treasure ይላቸዋል፡፡ ይሄ አንዱ በርተን ነው፡፡ ሌላ በርተን አለ፣ ከሞት ጋር እንዲፋጠጥ የሚነዳ ዛር የሰፈረበት (ያ ዛር ግን ይጠብቀዋል፣ እንግሊዝ በመካከለኛው ምስራቅ በምታካሂዳቸው አያሌ የቅኝ ግዛት ሽሚያ ጦርነቶት በአብዛኛዎቹ በርተን ገብቶ በጀግንነት ተዋግቷል፡፡ ሞት እምቢ አለው እንጂ ሞትን በጦር ሜዳ ቢያጣው፣ ምናልባት አገኘው ይሆናል በሚል ይመስላል፡፡ ወደ መካ ከተማ ዘመተ፡፡ “ያልተገረዘ ነጭ ባእድ” መካን ቢረግጥ ይገድሉታል፡፡ አስቀድሞ በርተን ተገቢውን ጥንቃቄ ወሰደ፡፡ አረብኛውን ሲናገር የፊደላቱ መውደቅ መነሳት ወይም የድምፁ ቅላፄ እንዳያጋልጠው፣ ከሩቁ የህንድ አገር የመጣ ሙስሊም መስሎ ተከሰተ፡፡ ለረመዳን ነበር የሄደው፡፡ ያን በአል አክብሮ በሰላም ከወጣ በኋላ፣ እዚያ ያየውንና የሰማውን ጽፎ አሳተመ፡፡

 

ሀረር የእስልምና ሶስተኛዋ ቅድስት ከተማ ናት (ከመካ እና መዲና ቀጥሎ) ዛሬ ለቱሪዝም ክፍት ሆነች እንጂ በርተን በጐበኛት ወቅት እውነተኛ ማንነቱ ቢታወቅባት ኖሮ ይገድሉት ነበር፡፡ ከጉብኝቱ መልስ አንድ መጽሐፍ አሳተመ፡፡ በብዛት ስለ ሀረር ታሪክና ባህል ነበር፣ በጥቂቱ ደግሞ ስለቀረው ኢትዮጵያ፡፡ (በነገራችን ላይ፣ በርተን እጅግ የማማርክ anthropologist ነው)

ይህን ሁሉ ሲጽፍ ስለ ግል ኑሮው (ቤተ-ሰብ፣ የልጅነት ዘመን፣ የጉርምስና ፍቅር፣ ወዘተ) ምንም አይናገር፡፡ ምናልባት ሌሎች ስለነዚህ ጉዳዮች ጽፈው ሊሆን ይችላል)

ጓደኛዬ ጳውሎስ ሚልክያስ

የጉርምስና ዘመን ጓደኛዬ ጳውሎስ ሚልክያስ ታሪክ ከሪቻርድ በርተን ጋር በምን እንደሚመሳሰልና በምን እንደሚራራቅ ለአንባቢያን ልተውና፣ እነሆ በረከት:-

ዶሮ ማነቂያ ሰፈር አንዲት አነስ ብላ ፀዳ ያለች ሆቴል ነበረች፡፡ እዚያ ስኖር ከጳውሎስ ጋር ተዋወቅን፣ ተቀራረብን፡፡ ውቤ በረሃ አብረን መዞር ስንጀምር “ኮከባችን ገጠመ” ጳውሎስ ጽዳት ይወዳል፡፡ ጥቂት መፃሕፍት ሁለት ሱፍ ልብስና ሶስት ሸሚዝ ብቻ ነው ንብረቱ፡፡ አንዱን አንድ ወር ይለብሰውና፣ Laundary ደምበኛው ጋ ሄዶ፣ የለበሰውን አውልቆ ለአጣቢው ትቶለት፣ የፀዳውን ለብሶ ይሰናበታል እስከሚቀጥለው ወር፡፡ በሁለት መቶ አስር ብር ተቀጥሮ ቴሌኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት ያገለግላል (Old Airport አጠገብ፡፡) በሶስት ቁጥር ኦቶቡስ ቢሄድ ቲኬቱ ደርሶ መልስ ሃያ አምስት ሳንቲም ነው፡፡ ጳውሎስ ግን በእግር ነው ደርሶ ሚመለሰው፡፡ ድህነት አለቻ!

ባገራችን አሉ ከሚባሉት ሀብታሞች አንዱ ያክስቱ ባል ራስ መስፍን ናቸው፡፡ እሳቸው ደሞ እንኳን ለዘመድ ቀርቶ ለባዳ ለጋስ ናቸው ይባልላቸዋል፡፡

ጳውሎስ ግን አክስቱን ሊጠይቅ ቤታቸው ይሄዳል እንጂ ከሳቸው “አምስት ሳንቲም እንኳን ቢሆን” አይፈልግላቸውም፡፡ ምክንያቱም ጳውሎስ አብዮታዊ ወጣት ነው፣ ጭቁኑን ህዝብ ከነራስ መስፍን አይነቱ አድሀሪ ስርአት ነፃ ለማውጣት ቆርጦ ተነስቷል፡፡

ጳውሎስ ቀልድ ይወዳል፣ እሱም ራሱ ሲበዛ ቀልደኛ ነው፡፡ ግን እንደሌሎቻችን ከሰው የሰማውን ቀልድ ሲያቀብል ሰምቼው አላውቅም፡፡ ቀልዶቹ ሁሉ ራሱ የሚፈጥራቸው ናቸው፡፡

ለምሳሌ አንድ ፈረንጅ አለ፣ አማርኛ እየተለማመደ ነው፡፡ እና መቀመጥ ሲያሰኘው “ማቁጭ እፈልጋለሁ” ይላል፡፡

ሌላው ደግሞ አማርኛ እጅግም የማይችሉ አስተማሪ ናቸው፡፡ ክፍል ውስጥ አንዱ ተማሪ “አንድ ብር ጠፋብኝ ከዴስኬ ላይ” አላቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ተማሪዎቻቸውን ሞራል (ግብረ ገብ) ሲያስተምሩ እንዲህ አሉ

“ልጆች፣ መሌብ አይጠቅምም፣ ከተያዛችሁ ያስቀጣል እንጂ፡፡ ስለዚህ አትሌቡ፣ አደራችሁን”

ጳውሎስ በሰው ቀልድ ሲስቅ እውነት ሳቁ መጥቶ ይሁን ወይስ ተናጋሪው ሰው ያስሳቀው መስሎት ደስ እንዲለው ይሁን በጭራሽ አያስታውቅም፡፡ ራሱ በፈጠረው ቀልድ ሲስቅም የእውነት ይሁን የይምሰል በጭራሽ ለመለየት ችዬ አላውቅም፡፡ ይህን ስነግረው ጳውሎስ “ምስጢራዊ” ሰው ነው ነኝ ማለት ነዋ! ለስራዬ ይጠቅመኛል” ስራዬ ሲል ሊያካሂድ፣ እና ሁኔታዎች ከፈቀዱ ሊመራ ራሱን እያዘጋጀ ነው፡፡ ይለኛል እንግዲህ፡፡ የምሩን ይሁን እየቀለደ አሁንም ላውቅ አልቻልኩም፡፡

…ጳውሎስ በዶሮ ማነቅያና በቴሌኮሙኒኬሽን መሀል በእግሩ ሲኳን እየኖረ፣ ደስታ የሚያገኘው በወር ሁለት ወይም ሶስት ቀን ውቤ በረሃ እየጨፈረ ሲያመሽ ብቻ ነው፡፡ በቃ፡፡

የኔ ደሞዝ የሱ እጥፍ ነው፡፡ አገር ቤት ለሚኖሩ ወላጆቼ የወር ተቆራጭ እየላክሁ እንኳ በቂ ገንዘብ ይተርፈኛል፡፡ ስለዚህ ለጳውሎ አንድ ጠቃሚ የመሰለኝን ሀሳብ አቀረብኩለት፡፡

“ኑሮህ እንዲህ ቢቀጥል፣ አድካሚ ውሃ ቅዳ ውሀ መልስ ሆኖ ይቀራል፡፡ ስለዚህ እንደኔ ዩኒቨርሲቲ ግባና ተማር፡፡ ለለመድካት የሶስት ቀን ደስታ እኔ ገንዘቡን የወር ተቆራጭ ላርግልህና፣ ተመርቀህ ስራ ስትይዝ ትከፍለኛለህ”

“በጣም ጠቃሚ ስጦታ ነው እያደረግልኝ ያለኸው”

“ለስራህም ይጠቅምሀል” ስለው

“አይደለም? እንዴት ደስ ይላል!” አለና ሳቀ፣ የእውነት ሳቅ ነበር ወይ እላለሁ ሳስታውሰው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጣም ከፍ ባለ ውጤት ያለፈ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲ አዳሪ ተማሪ ሆኖ፣ በነፃ እየተመገበና በየአመቱ አንድ ሙሉ ልብስ እየታደለው፣ ደስተኛ ኑሮ ነጋለት፡፡

ዩኒቨርሲቲው አልፎ አልፎ የሚያዘጋጃቸው፣ ተማሪዎቹ የሚሳተፉባቸው፣ የክርክር ወይም የትምህርታዊ ገለፃ እንዲሁም የስነ ጽሑፍ ንባብ ነበሩ፡፡ አንዱ ውስጥ ጳውሎስ ሚልክያስ ይሳተፍ ስለነበረ፣ እንድመጣ ጋበዘኝ፡፡

ንግግሮች ሲሆኑ በእንግሊዝኛ ነበር፡፡ እና ጳውሎስ በጣም የሚመስጥ ገለፃ ሲያደርግ ቆየና፣ ድንገት ሀሳቡ ብልጭ ያለበት ይመስል “I Know what some of you are thinking. You are saying to yourselves what is this black Lenin trying to tell us?” (ይህ ጥቁር ሌኒን ምን ሊነግረን እየሞከረ ነው?)

ይህን ብሎ ወደ ገለፃው ተመለሰ፡፡ የምሽቱ ዝግጅት ሁሉ አብቅቶ ጳውሎስ ሲሸኘኝ “ስለ ጥቁሩ ሌኒን የተናገርከው አስፈላጊ ነበር?” አልኩት፡፡

“በጭራሽ አስፈላጊ አልነበረም፡፡ እንድያውም አደገኛ ነበር፡፡ ልናገረው አስቤ ሳይሆን አምልጦኝ እንደወጣ አይነት ነበር፡፡ ማታ በእግር ስዘዋወር ታክሲ በምትመስል መኪና ቢያስድጡኝስ? ተደርጐ ያውቃል’ኮ”

“እዚያ ድረስ እንኳን አይሄዱም”

“እንዴት ታውቃለህ?”

“የምሩን ሌኒን የሆነ አብዮታዊ ህዝብ ፊት እንዲህ አፉን አይከፍትማ”

“ትክክል! ቢሆንም መጠንቀቅ ያሻል” አለኝና አጠራጣሪ ሳቁን ለቀቀው፡፡

***

…ለናሙና ያህል ጳውሎስ የፈጠራትን አንዲት ቀልድ ባቀርብ ተገቢ መሰለኝ፡፡ ለከተሜ አንባቢዎች ምናልባት መረጃ (Information) ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ቤተሰቦች “ልጃችሁ ለልጃችን ተባብለው ልጆቻቸውን ከመዳራቸው በፊት በሀብት እርስ በርስ ተመዛዝነው እኩያ የሆኑ ሲመስላቸው ነው፡፡ በተለይ ማን ማንን ወለደ ተባብለው ለሰባት ትውልድ ዝምድና ከሌላቸው፣ ወይም እንደ ቁምጥና፣ እንደ ባርነት፣ እንደ እብደት የመሰለ ጉድለት ከሌለባቸው ነው የሚጋቡት፡፡

አንዲት ትንሽ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ ባልየው በጣም፣ እጅግ በጣም ጽዩፍ ነው፡፡ ምግብ እየበሉ ከውጪ አንዱ አላፊ “አክ እንቱፍ” ሲል የሰማ እንደሆነ፣ ፊቱ ቅጭም ይልና “አንሺው” ብሏት፣ ይህን እስኪረሳ ምግብ ሊበላ አይችልም፤ ቋቅ ይለዋል፡፡

አንድ ከይሲ ቀን ይህን ጽዩፍ እባብ ነደፈው፡፡ መድሀኒቱ የታወቀ ነው፣ ሴት ግብር ውሀ ትወጣና፣ እጣቢውን በጣሳ አምጥተው ያጠጡታል፡፡

አመጡለት፣ እምቢ አልጠጣም አለ፡፡ ይልቅ መርዙ ሳይሰራ ቶሎ ጠጣ፡፡ ከመሞት ይሻልሃል፡፡ ደሞ ይሄ አንተ የምትጠረጥረው አይደለም፡፡ ስራስር ምሰን ያዘጋጀነው ነው፡፡ ብትፈልግ ይኸውልህ እገሌ ታማኝ ጓደኛህ፣ አሉት፡፡

“እውነታቸውን ነው እምልልሀለሁ” አለው

“እንግድያው አምጡ” አለና በአንድ ትንፋሽ ጭልጥ አደረገው፡፡

እና አፉን እያጣጣመ “እቺስ የባርያ ናት” አለ፡፡

…ጳውሎስ የኮሌጅ መመረቅያ ፈተናውን በከፍተኛ ማእረግ አልፎ ተመረቀ፡፡ በበቂ ደሞዝ ለአንድ አመት ሰራ፡፡ በግሉ ተፃጽፎ Scholarship አግኝቶ ወደ ካናዳ ሊመርሽ ሆነ፡፡ እንደ ነገ ኤሮፕላን ሊሳፈር እንደ ዛሬ ማታውን እየጠጣን የባጥ የቋጡን ስናወራ አምሽተን፣ ወደ ማደርያው ልሸኘው በእግር እያዘገምን ግንፍሌ ድልድይ አጠገብ ስንደርስ ቆምን (ነገ ስለማልሸኘው አሁን እዚሁ ልንሰነባበት ሆነ፡፡) “መለያየት አስቸጋሪ ነው” አለኝ “የኔ ውቃቢ መልአክ አንተን ባይልክልኝ ኖሮ ዛሬም ለቴሌኮሙኒኬሽኖች እንከራተትላቸው ነበር፡፡ አሁን ደሞ ከዚያም የበለጠ እንድትውልልኝ ልጠይቅህ ነው፡፡ የምቀርባቸው ታጋይ ጓዶች እንኳ ሊያደርጉልኝ የማይችሉት ነው፡፡ ምክንያቱም ያንን ያህል ለአደጋ ሊያጋልጥህ ቢችልም፣ አንተ ብቻ ነህ ችላ ብለኸው ለጓደኛህ የምትቆምለት ሁነኛ ሰው”

በሙገሳው እያፈርኩም ቢሆን ስሜቴ ተነካ “እሺ የማደርግልህን ንገረኝ” አልኩት፡፡ ቀጥ ብሎ ቆሞ እያየኝ “ምናልባት ለዚህ ጭቁን ህዝብ ስታገል የሞትኩ እንደሆነ ከኔ እጥፍ ቁመት ያለው ሀውልት በነሐስ አሰርተህ፤ እንዲህ ቆሜ ወደ ቅድስት ስላሴ ስመለከት እዚችው ቦታ አቁመኝ!”

ይህን ብሎ ሲጨርስ ሁለታችንም በረዥሙ ሳቅን (ግን የጳውሎስ ሳቅ የእውነት ነበረች ወይ? ሥላሴዎቹ ያውቃሉ!)

James Bruce

ወደ እንግሊዝ አገር እንመለስና፣ ጄምስ ብሩስ በራሱ መንገድ ሪቸርድ በርተንን የመሰለ፣ ሞት የማይፈራ ጀግና ነው፡፡ ስለ ፒራሚዶች ዘመን ግብፅ ሲነገር “Egypt is a gift of the Nile” ይባል ነበር፡፡ ግሪኮችም ሮማውያንም አባይ የት ይሆን የሚመነጨው? ብለው ዘወትር ያስቡበታል እንጂ ደፍሮ ወንዙን ሽቅብ ተከትሎ ለመሄድ የሞከረ አልተገኘም ነበር፡፡ ብሩስ ወደ ግብፅ መጣና አባይን ሽቅብ ሊከተል ተዘጋጅቶ በጀልባ ተነሳ፡፡ በወንዙ ሲቀዝፍ አዞዎች እንዳይበሉት፣ በመሬት ሲጓዝ ደግሞ ሰው የሚበሉ ጐሳዎች እንዳይይዙት፣ ከዚህ ሁሉ በጥንቃቄና በቆራጥነት እያመለጠ ጐንደር ደረሰ፡፡ የአባይን ምንጭ ከማንም ቀደም ያየ ባእድ ሰው በመሆኑ ባስመዘገበው ድል እጅግ በጣም የተኩራራው ጄምስ ብሩስ “ይህን ምንጭ ማየቴ ለኔ ትልቅ ፀጋ ነው” ሲላቸው፣ አገሬዎቹ “ማንም ሰው ከልጅነቱ ጀምሮ ሲያየው የሚኖር ምንጭ ነው ኮ” ብለው ትልቁን ጀብዱ አንኳሰሱበት፡፡ ያገሩ ሰዎች ደግሞ “Travels to Discover the Source of the Nile” ብሎ ያሳተመውን መጽሐፍ አንብበው ተሳለቁበት፡፡ በተለይ የሳቁበት በዚያን ዘመን ስለተመለከተው አንድ የጐንደሬዎቹ ልምድ ነበር፡፡ አንዱን ሰንጋ መርጠው፣ በቁሙ እየሄደ እያለ ቆዳውን በቢላዋ ገፍፈው ከስጋው እየቆረጡ ይበላሉ፡፡ ጥቂት በልተው፣ ያረዱትን አካል ቆዳውን መልሰው ያለብሱትና ይለቁታል፡፡ ሰንጋው ግጦሹን ይቀጥላል፡፡ ካሰኛቸው ሌላ ሰንጋ መርጠው እንደ ቅድሙ በትንሹ ይመገባሉ፡፡ ስለዚህ እርጥብ ስጋ ስለመብላት በተለይ፣ የሚከተለውን ግጥም ጽፈው በብዛት እየጠቀሱ ሳቁበት

Nor have I been to far off lands, alas!

Where men eat half a cow

And lead the other half to grass.

አንድ ቀንማ አንዱ እቤቱ ድረስ መጣ፣ መጽሐፉ ምን ያህል እንዳስገረመውና እንዳስደሰተው ነገረውና አመሰገነው፡፡

“Thank you” አለ በርተን

“But Surely, you will agree with me that it is impossible for human beings to eat raw meat?!” በጨዋ ቋንቋ “እዚህ ላይ ዋሽተሀል፣ ሲለው ነው፡፡

ብሩስ “one moment” ብሎት ወጣ፡፡ እና ሙዳ እርጥብ ስጋና ቢላዋ ባንድ እጁ፣ ሽጉጥ በሌላ እጁ ይዞ ተመለ፡፡

ሽጉጡን እየደገነበት “ይበሉ፣ እያየሁዎት እቺን ስጋ ይብሉዋት” አለው፡፡ ሰውየው ቋቅ እያለውም ቢሆን በልቶ ጨረሳት፡፡

ብሩስ “ይኸው እንደቀመሱት ነው፡፡ ሰው እርጥብ ስጋ ሊበላ ይችላል” ብሎ አሰናበተው ይባላል፡፡

ኡም ካልቱም

የአረብ መንግስታት ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ “እስራኤልን እናወድማታለን” የሚለውን ፉከራና ሽለላቸውን በተግባር ለመግለጽ የደፈሩት የጦር ሀይሎቻቸውን አስተባብረው እስራኤልን ወረሩዋት፡፡ ጦርነቱ ስድስት ቀን ብቻ ወሰደ፡፡ አንድ አይናው ጄኔራል ሞሼ ዳያን “ድባቅ መታቸው”ተኩስ አቁመው፣ የሁለቱም ወገን ወታደሮች በያሉበት ነቅተው መንግስታቱ የሰላም ውል እስኪፈራረም ድረስ እየተጠባበቁ እንዲቆዩ ታዘዙ፡፡ በዚህ ትእዛዝ መሰረት የግብጽና የእስራኤል ወታደሮች አጠገብ ላጠገብ ምሽግ ቆፍረው እየተፋጠጡ መዋል ግድ ሆነባቸዋ፡፡ ከዚህ የሚቀጥል ታሪካቸውን በካይሮ ኗሪዎች ልሳን ይነገራል (የካሪኖ ልጆች የተሰጣቸው በረከት በሌላ ላይ ሳይሆን በራሳቸው ላይ የመሳቅ ፀጋ ነው)

አሊ እና ቤንያሚን trench ውስጥ ቆመው መፋጠጥ ሆነ ውሎአቸው፡፡ እና ከጉድጓዱ ወጥተው፣ ወሰን ሳይጥሱ መንጐራደድ፡፡ በአይን ብቻ ተያይተው እንደ ጓደኝነት አይነት ስሜት ሊያድርባቸው ጀምሯል፡፡ ቢሆንም ቤንያሚን ጠላቱን ከመተንኮስ አይመለስም፡፡ አንድ ቀን ማለዳ ላይ ከእንቅልፍ ቀስቃሹ ጥሩንባ ሊነፋ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ቤንያሚን ጮክ ብሎ ተጣራ “ያ አሊ”

“አይዋ” መልሶ ጮኸ አሊ

“ኩስ ኡመክ” (እናትክን!)

በሚቀጥለው ማለዳም በዚያችው ደቂቃ ቤንያሚን አሊን ጠርቶ ሰደበው፡፡ በነጋታውም እንደዚሁ፡፡

ይኸ ሁሉ ሲሆን፣ ከመጀመሪያው ስድብ በኋላ፣ አሊ ነገ ጧት ቀድሜው እነቃና፣ ጠርቼ እሰድበዋለሁ እያለ ሲተኛ ነው ቀናቱ ያለፉት፡

ስድቡ ሲበዛበት ጊዜ አንድ ማታ “ዛሬስ ሳልተኛ አድራለሁ፣ ቀድሜው ነቅቼ፣ ጠርቼ እሰድበዋለሁ፡፡ ረዥም ሌሊት ካሳለፈ በኋላ

“ያ ቤንያሚን” ብሎ ጮሆ ተጣራ

“አሊ ነህ ወይ?” አለው ቤንያሚን

“አይዋ!”

“ኩስ ኡመክ!”

…አሁን ወደ ኡም ኻልቱም መጣን፡፡ ባለፀጋዎቹ የአረብ ሼኮች (እና የአረብ ህዝብ በሙሉ) የሚስማሙበት “እንደ ዘፋኝዋ ኡም (እማማ) ኻልቱም ለጆሮ የሚጥምና መንፈስ የሚያድስ ድምጽ በአለም ላይ ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ ኡም ኻልቱም ግዙፍ ደርባባ ሴትዮ ናቸው፡፡ በመድረክ ሲከሰቱ በእጃቸው አስር ነጭ መሀረብ ይዘው ነው፡፡ እና እየዘፈኑ አንዱን መሀረብ ከዘፈኑ ስሜት ጋር እየሄዱ ይቀዳድዱታል፣ እንባቸው እየወረደ፡፡

ዘፈኖቻቸው ረዣዥም ናቸው፣ እስከ አንድ ሰአት ከግማሽ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ኡም ኻልቱምን ለመስማት ነው እንግዲህ ባለፀጋዎቹ ሼኮች ተደዋውለው “ታድያስ፣ ወደ ካይሮ በኔ jet እንብረር ወይስ ባንተ?” የሚባባሉት፡፡ እስከሚቀጥለው ቸር ይግጠመን አሜን፡፡

 

 

Read 3423 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 13:47