Saturday, 07 February 2015 12:22

...እድሜ ትልቁና ዋነኛው ምክንያት ነው...”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ልጅ ወልዶ የመሳም ፍላጎት አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ሊያገኛቸው ከሚጓጓላቸው ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ታዲያ ይህ ልጅ የማግኘት ጉጉት በተለያዩ ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ሊስተጓጎል አልፎም መሀንነትን ሊያስከትል ይችላል፡፡   
የአለም የጤና ድርጅት በፈረንጆቹ 2010ዓ/ም ባወጣው ጥናት መሰረት በአለማችን ላይ ቁጥራቸው 48.5 ሚሊዮን የሚገመት ጥንዶች የዚህ የማሀንነት ችግር ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ጥናቱ የተደረገው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1990-2010/ አመተ ምህረት በ190/ የተለያዩ ሀገሮች ነው፡፡ በጥናቱም በ1990/ ዓ/ም 42.2/ ሚሊዮን የነበረው የመሀንነት ችግር ያለባቸው ጥንዶች ቁጥር በ2010/ ዓ/ም 48.5/ ሚሊዮን መድረሱን ጠቁሟል፡፡
በዛሬው ፅሁፋችን በተፈጥሮ ከሚከሰተው መሀንነት ውጪ ከአኗኗር እንዲሁም ከመድሀኒት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ መሀንነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች በሚመለከት የባለሙያ ማብራሪያ አካተን ያጠናቀርነውን ፅሁፍ እንዲህ ልናስነብባችሁ ወደናል፡፡
ለዛሬ ያነጋገርናቸው ባለሙያ ዶክተር አበበ ሀይለማሪያም ይባላሉ፡፡ ዶክተር አበበ በዘውዲቱ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ሀኪም ናቸው ለመሆኑ በህክምናው ሳይንስ መሀንነት እንዴት ይገለፃል? በቅድሚያ ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር፡፡
“...ሁለት ጥንዶች ምንም አይነት የእርግዝና መከላከያ ሳይወስዱ በተገቢው መጠን የግብረስጋ ግንኙነት እያደረጉ ቢያንስ ለአንድ አመት መውለድ ካልቻሉ መሀንነት ይኖራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ነገር ግን መከላከያ ሳይወስዱ መውለድ አለመቻላቸው የመሀንነት ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል እንጂ መሀንነት ነው ብሎ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ መሀንነት መሆኑን ለማረጋገጥ የተለያዩ ምርመራዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ፡፡”
የወር አበባ ኡደት መዛባት፣ ቀደም ሲል ተከስቶ የነበረ የአባላዘር በሽታ በማህጸን ቱቦ ወይንም በህክምናው fallopian tube ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ትቶት የሚያልፈው ቋሚ የሆነ ጠባሳ  መሀንነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ይላሉ ዶክተር አበበ፡-
“በሴቶች በኩል መሀንነትን ሊያስከትሉ ከሚችሉ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የእድሜ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እንቁላል የሚያመነጩት እጢዎች እድሜ እየገፋ በሄደ ቁጥር ቀደም ሲል ያመነጩ የነበረውን ያህል እንቁላል ላያመነጩ ይችላሉ፡፡
ስለዚህ እድሜ ትልቁና ዋነኛው ምክንያት ነው ማለት እንችላለን፡፡ የወር አበባ ኡደት ሲዛባም የሴቷ እንቁላል ላይመነጭ ይችላል ወይም ደግሞ እንዳስፈላጊነቱ ጊዜውን ጠብቆ ላይመጣ ይችላል፡፡ ከዛ ውጪ ከተለያዩ ኢንፌክሽኖች እንዲሁም የአባላዘር በሽታዎች የተነሳ የማህፀን ቱቦ መዘጋት ሊኖር ይችላል ይህም የሴቷን እንቁላልና የወንዱ የዘር ፍሬ በተገቢው መንገድ እንዳይገናኙ ሊያደርግ ስለሚችል ለመሀንነት አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በተፈጥሮ ለመራባት የሚያስፈልጉ አካላት ላይኖሩ ይችላሉ እሱም ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ ሌሎች እንደ ቲቢ ያሉ በሽታዎችም ማህፅን አካባቢ ከሚፈጥሩት ችግር የተነሳ ፅንስ እንዳይፈጠር ሊያደርግ ይችላል፡፡”
በዝርዝ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪም የተለያዩ መድሀኒቶች ከመውሰድ ለምሳሌ ከአእምሮ ህመም ጋር በተያያዘ ለረዥም ጊዜ መውሰዱ መድሀኒቶች በሴቷ በኩል መሀንነትን ሊያመጡ እንደሚችሉ ዶክተር አበበ ይገልፃሉ፡፡
“...ለመሀንነት የሚያጋልጡ የተለያዩ መድሀኒቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የደም ግፊት መድሀኒቶች ለመሀንነት የሚያጋልጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ማለት ሁሉም የደም ግፊት መድሀኒቶች ለመሀንነት ያጋልጣሉ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን አንዳንዶቹ መድሀኒቶች በውስጣቸው የያዙት ንጥረነገር ለመሀንነት የሚኖረውን ተጋላጭነት የሚጨምሩበት ሁኔታ አለ፡፡ አንዳንድ ለአእምሮ ህመም ለረዥም ጊዜ የሚወሰዱ መድሀኒቶችም በተመሳሳይ ለዚህ ችግር ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው እንደዚህ አይነት መድኒቶች በሀኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ ስለሆኑ ይህን አይነቱን ችግር እንደሚያስከትል ከታወቀ ባለሙያው ሌሎች መድሀኒቶችን ሊያዝ ይችላል፡፡
በተለምዶ በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ወይም መርፌ ለዚህ ይዳርጋል የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ ነገርግን በህክምናው ሳይንስ የዚህ አይነት አመኔታ የለም፡፡ ማለትም ይህን በሚመለከት በተደረጉት የተለያዩ ጥናቶች የዚህ አይነት መድሀኒቶች መሀንነትን እንደማያመጡ ተረጋግጧል፡፡”
ቀደም ሲል የተጠቀሱት ምክንያቶች በሴቶች በኩል መሀንነትን ሊያስከትሉ ከሚችሉ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ይሁኑ እንጂ ለመሀንነት ሴቷም ሆነች ወንዱ ተመጣጣኝ የሆነ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው ይችላል ብለዋል ዶክተር አበበ፡፡
“...በአብዛኛው ከወንዱም ከሴቷም በኩል ተመጣጣኝ የሆነ ምክንያት ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ወንዱ ከ30-50% ወይም በአማካኝ 40% የወንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ በተመሳሳይ የተቀረው 40% በሴቷ በኩል የሚከሰት ችግር ነው፡፡ ከሁለቱም ምክንያት ሊሆን የሚችልበት 10% ይሄ ነው ተብሎ የማይገለፅ ደግሞ 10% ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ መሀንነት ምክንያቱ በአንድ ወገን ነው ብሎ መደምደም አይቻለም፡፡”
ቀደም ሲል ባለሙያውም እንደ ገለፁት ምንም እንኳን ወንዱ እንዲሁም ሴቷ ለመሀንነት ያላቸው አስተዋፅኦ በመቶኛ ደረጃ ይለያይ እንጂ መሀንነት በሴቶች ብቻ ሳይወሰን በሁለቱም ፆታዎች ላይ ሊከሰት የሚችል ችግር ነው፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ መሀንነት በሴቶች ላይ ብቻ የሚከሰት ችግር አድርጎ የማሰብ የቆየ ልማድ አለ፡፡ ይህም የህክምናው ሳይንስ ከሚለው ፈፅሞ የራቀ ነው እንደ ማብራሪያው፡፡
“...በተለይ እንደኛ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች መሀንነት የሴቷ ችግር ብቻ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ይህ የሆነበት የተለያዩ ባህላዊ እንዲሁም ሀይማኖታዊ አመለካከቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሌላውና ለዚህ አይነቱ አመለካከት መንስኤ የሚሆነው ደግሞ ችግር ሲኖር ሁለቱም ጥንዶች በጋራ ሆነው ህክምናቸውን ለመከታተል የሚኖራቸው ተነሳሽነት ነው፡፡ በአብዛኛው ይህ የመሀንነት ችግር ሲከሰት ሴቶች ፈጥነው ወደ ህክምና ተቋም ይመጣሉ፡፡ አብዛኞቹ ወንዶች ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አይሆኑም ስለዚህም ሴቷ እንደ ምክንያትነት ትጠቀሳለች፡፡ ነገር ግን መሀንነት በተመጣጣኝ ሁኔታ በወንዱም ሆነ በሴቷ ላይ ሊከሰት የሚችል ችግር ነው፡፡”
መሀንነት በተፈጥሮ እና በአንዳንድ የጤና ችግሮች የሚከሰት ቢሆንም ከአኗኗር እንዲሁም ከመድሀኒት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ መሀንነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች አሉ፡፡
“...ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ተፈጥሯዊና እንደ አባላዘር ያሉ በሽታዎች ለመሀንነት ሚዳርጉ ዋነኛ ምክንያቶች ይሁኑ እንጂ ከዛ ውጪ ሌሎች ከአመጋገባችን ወይም እለትተለት የምናደርገው እንቅስቃሴ ለመሀንነት የሚኖረንን ተጋላጭነት ከፍ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አመጋገብን ብንመለከት አንዳንድ ሴቶች የሰውነታቸው ክብደት በጣም ዝቅተኛ ይሆንና ሰውነታቸው የሚፈለገውን ንጥረ ነገሮች በተገቢው መንገድ ላያገኝ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የወር አበባ መዛባትን አንዳንዴም ጭርሱንም እንዲቀር ሊያደርገው ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ ሁኔታ ልጅ ለመውለድ የሚኖረውን ሁኔታ ሊያዘገይ ወይም መሀንነትን ሊያስከትል ይችላል፡፡”
የሴቷ የሰውነት ክብደት ጤናማ የሚባለው ምን ያህል እንደሆነና የክብደት መቀነስ የሚለው ቀደም ሲል ከተጠቀሰው የወር አበባ መዛባትን ከማስከተሉ ባለፈ መሀንነትን ሊያስከትል የሚችልባቸውን መንገዶች ዶ/ር አበበ እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡   
“..አንዲት ሴት በአማካኝ ሊኖራት የሚገባው የሰውነት ክብደት ሀምሳ ኪሎ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ክብደቷ ከዛ በታች ከሆነ ይህ የክብደት ማነስ ለወር አበባ መዘግየት ብቻም ሳይሆን ከአእምሮ የሚመነጩ የተለያዩ ኬሚካሎች በተገቢው መጠን እንዳይመነጩ ሊያደር ይችላል፡፡ ይህም የሴቷ እንቁላል ከዘር ማፍሪያ እጢ ፅንሱ እስከ ሚፈጠርበት የማህፀን ክፍል የሚኖረው መንገድ ላይ ተፅእኖ ሊፈጥር ስለሚችል በዚህ ሁኔታ መውለድ ሊዘገይ ወይም መሀንነት ሊከሰት ይችላል፡፡”   
መሀንነትን በሚመለከት በህብረተሰቡ ዘንድ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ለዘመናት የመሀንነት መንስኤ ናቸው ተብለው በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ነገሮች መካከል መሀንነትን በዘር የሚመጣ ችግር አድርጎ ማሰብ አንዱ ነው፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ ሰዎች ከቤተሰብ አባላት መካከል አንዳቸው ይህ የመሀንነት ችግር ሲገጥማቸው “ኧረ እኛ በዘራችን መሀንነት የለም...” ሲሉ የሚደመጡት፡
“..ሁሉም የመሀንነት ችግር በዘር የሚመጣ ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም በተወሰነ ደረጃ ከዘር ጋር የሚያያዝበት ሁኔታ አለ፡፡ ቀደም ሲል ጠቅሼዋለሁ ለመሀንነት ሚያጋልጡ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ የተለያዩ genetic disorder ወይንም በዘር የሚወረስ የተፈጥሮ መዛባት የምንላቸው ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡
ይህ ማለት አንዳንድ ጊዜ  በተፈጥሮ ለመራባት የሚያስፈልጉት ህዋሶች (Gene) በሰውነታችን ውስጥ ላይገኙ ይችላሉ ወይም ደግሞ ባላስፈላጊ ሁኔታ ተባዝተው ሊገኙ ይችላሉ፡፡
ስለዚህ የዚህ አይነት ምክንያቶች ለመሀንነት የሚዳርጉበት ሁኔታ አለ፡፡ ነገር ግን ከቤተሰብ አባላት ውስጥ የመሀንነት ችግር ተከስቶ ስለማያውቅ ወይም ይህ አይነቱ ችግር ያለበት ሰው የለም ማለት ፈፅሞ መሀንነት ሊያስከትል አይችልም ማለት አይደለም...” እንደ ዶ/ር አበበ ኃ/ማርያም የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስት፡፡

Read 11920 times