Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 January 2012 11:51

ማራኪ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንድ ቀን እንደ ወትሮዬ በበረንዳው ላይ ተቀምጬ በመቆዘም ላይ እንዳለሁ ከቤታችን ትይዩ ባለው ጐዳና ላይ የፖሊስ መኪና ለቅኝት ጥበቃ ታሽከረክር የነበረች ፖሊስ እኔን አሻግራ እንዳየች መኪናዋን አዙራ በግቢያችን በር ላይ አቆመች፡፡ በተጠንቀቅ እየተራመደችና ትጥቋን እያስተካከለች በቀጥታ ወደ እኔ በመምጣት ሰላምታ ከሰጠችኝ በኋላ ማንነቴን የሚመለከቱ ጥያቄዎች አቅርባልኝ ትዕቢት በተሞላበት የእልክ አነጋገር መልስ ሰጠኋት፡፡ ልክ ልታስገባኝ እንደፈለገች በሚታወቅባት ቃና “እዚህ ነው የምትኖረው?” አለችኝ፡፡

“አዎ” ብዬ አጭር መልስ ሰጠኋት፡፡

“መታወቂያህን ልታሳየኝ ትችላለህ?”

“ምንም አይነት መታወቂያ የለኝም፡፡”

“እንዴት መታቂያ የለህም?”

“ምክንያቱም ስለሌለኝ ነው፡፡”

በጥያቄና መልስ ተካረርንና ያመላለስ ዘይቤዬ የሚገባትን ክብር የሰጣት ስላልመሰላት ኃይሏን ልታስታውቀኝ መፈለጓን በሚያሳይ አረማመድ ገላምጣኝ በማለፍ የቤቱን በር አንኳኳች፡፡ እሷም እኔም ሁለታችንም እኩል ተበሳጭተናል፡፡ እሷ በነጮች ሰፈርና በነጭ በረንዳ ጥቁር መገኘቱ ከወንጀል ሥራ በቀር ሌላ ምንም ዓይነት ምክኒያት ሊያመጣው አይችልም ከሚል ግምት ተነስታ ባለቤቶቹን ለመጠበቅ ስትል የወሰደችው እርምጃ ነው፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ያነጋገር ዘይቤዬና ሥርዓት የጐደለው አመላለሴ ጥርጣሬዋን ስላባባሰው በይበልጥ ትኩረቷን እስበው ዘንድ ምክንያት ሆኛታለሁ፡፡ እኔ ደግሞ አያሌ ግምቶችን ወስጄ በአቀራረቧ ላይ ጥላቻና ንቀት አሳድሬያለሁ፡፡ ጥቁር አሜሪካዊት እንደመሆኗ ከነጮች በረንዳ ላይ ላየችኝ ሌላው ጥቁር ያሳደረችውን ጥርጣሬ አልወደድኩላትም፡፡ ሌላው ያልገባት ነገር ደግሞ ኢትዮጵያ በነበርኩበትም ሆነ በሱዳን ቆይታዬ ዩኒፎርም በለበሰ ሰው ላይ ያሳደርኩትን ፍርሃትና ጥላቻ ነው፡፡ በጠበንጃ አፈሙዝ ሥልጣን ይዞ እንዳሻው ሲያስር፣ ሲገርፍና ሲገል ከነበረ መንግሥት ጋር ስፋለም ኖሬ የመጣሁ በመሆኔ በዩኒፎርም ላይ ሽጉጥ ታጥቆ ለሚያነጋግረኝ ሰው ከቶውንም ቅን ሆኜ የምመልስበት ትዕግስት ሊኖረኝ አልቻለም፡፡

በመጀመሪያ ጥርጣሬን፣ ቆይታም ጥላቻን ያሳደረችዋ ፖሊስ ወደበሩ ተጠግታ “እዚህ ቤት ሰው አለ” በማለት አቤት የሚል ሰው ለማዳመጥ ጆሮዋን ጣል አደረገች፡፡

ሚስስ ፓርከር ወዲያውኑ ወጥተው ፖሊስ መሆኗን ካረጋገጡ በኋላ “እባክሽን ግቢ፣ የምረዳሽ ነገር አለ” አሏት፡፡

“ይህን ሰው ያውቁታል” አለቻቸው ወደኔ እየጠቆመች፡፡

“አዎ ልጃችን ነው ስሙም ስለሺ ይባላል፡፡ አቤት እንዴት ያለ ጥሩ ሰው መሰለሽ! ከሱዳን የመጣ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ነው፡፡ እኛም ቤተሰቦቹ ነን፡፡” ብለው በተጣደፈ አነጋገር ከመለሱላት በኋላ ወደ እኔ ዞረው “ስለሺ ይህች ወታደር ሊንዳ ብራውን ትባላለች፡፡ በካውንቲያችን ካሉት ጠንካራ ሕግ አስከባሪዎች አንዷ ናት፡፡” ብለው አስተዋወቁኝ፡፡

ወታደር ብራውን እንግዳነቴን፣ ካንፀባረኩት ትዕቢት ጋር ያመዛዘነች ይመስል ከመጀመሪያ አመጣጡዋ ለዘብ አለችና በእጅ ጨብጣ ተሰናብታኝ ወደ መኪናዋ ስትሄድ ከወንበሬ ሳልነሳ በኩራት ገባች፡፡ ሚስስ ፓርከር በኦፊሰር ሊንዳ ብራውን መናደዴ ገብቷቸው ሊያፅናኑኝ ዳድቷቸው ምንና እንዴት ብለው ሊያነጋግሩኝ ግራ የገባቸው ይመስል ጀርባዬን አሸት አሸት አድርገውኝ ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ ከሚስታቸው በስተኋላ ቆመው ከኦፊሰር ሊንዳ ጋር የነበረውን ውይይት አንድም ቃል ሳይተነፍሱ ያዳምጡ የነበሩት አባቴ ሚስተር ፓርከር ግን በተፈጠረው ሁኔታ እንዳተደሰቱ ከፊታቸው ተገንዝቤያለሁ፡፡

ሚስተር ፓርከር ለጥቂት ሰከንዶች ያህል አብረውኝ ተቀምጠው ከቆዩ በኋላ “በዚህ ዓይነት ገጠመኞች ልትበሳጭ አይገባህም፡፡ መጀመሪያውኑ ፖሊሷ ለእርዳታ ሳንጠራት ወደ በረንዳችን ዘላ መውጣት አልነበረባትም፡፡ አለመታደል ሆኖ የዚህ ዓይነት ገጠመኞች ለወደፊቱም ይጠብቁሃልና የኔ ብለህ ያዘው፡፡” ብለው ጉዳዩ እሳቸውንም እንዳናደዳቸው በመግለጽ ሊያጽናኑኝ ሞከሩ፡፡

ነገር ክፉኛ በሆዴ የገባው ስደተኛ፣ የሰው አገር፣ ሰው መሆኔን እያስታወስኩ በብቸኝነቴ ላይ መቋዘሙን መረጥኩና ሚስተር ፓርከርን ይቅርታ ጠይቄ ወደ ምኝታ ቤቴ ገብቼ እራሴን ቆለፍኩ፡፡

 

(“ከደንቢያ - ጐንደር እስከ ዋሺንግተን ዲሲ” ከተባለው ታሪካዊ ልቦለድ የተቀነጨበ)

 

 

Read 4211 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 11:53