Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 January 2012 09:53

41 ተጓዦች ያለቁበት የዓባይ በረሃ ገደል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድ እናት ከሶስት ልጆቻቸው ጋር ህይወታቸው አልፏል

በሐረር ከተማ የተወለደችው ኢንጂነር ትዕግስት ደጉና በጐንደር ከተማ የተወለደው ኢንጂነር ጋሻው የአምስት አመት የፍቅር ጓደኝነት የነበራቸው ሲሆን በዚሁ ዓመት ህዳር ወር ላይ ነው ጋብቻ የመሰረቱት፡፡ ጐንደር የሚገኙት የጋሻው ቤተሰቦች ጥንዶቹን መልስ ለመጥራት ሲያስቡ የጥምቀት በዓልን ያስታከኩት ሆን ብለው ነው - በጐንደር በድምቀት የሚከበረውን የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ላይ እንዲሳተፉ በማሰብ፡፡ ሆኖም ጥንዶቹ ከአባይ አላለፉም፡፡ አባይ በረሃ ላይ ቀሩ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ 47 ተሳፋሪዎችን ይዞ ሲጓዝ የነበረው ስካይ ባስ የጐንደር ጉዞውን በማለዳ ነበር የጀመረው፡፡

በመሃል መንገድ ላይ ግን ጉዞው ተሰናክሎ አውቶብሱ 80 ሜትር ርቀት ያለው የአባይ ገደል ውስጥ የገባ ሲሆን በደረሰው አሰቃቂ አደጋ 41 ሰዎች ወዲያው ህይወተቸው አልፋል፤ ስድስቱ አውቶብሱ ተፍቷቸው ህይወታቸው ሊተርፍ ችሏል፡፡ አዲሶቹ ሙሽሮች ኢንጂነር ትዕግስት ደጉና ኢንጂነር ጋሻው ፈረደ በአደጋው ህይወታቸውን ካጡት ተሳፋሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ወ/ሮ ወርቅአበባሁ አለማየሁ ደግሞ ለሀያ አመታት በአውስትራሊያ የኖሩትን ሁለት ልጆቻቸውንና በአዲስ አበባ ቴሌኮም የሚሠራውን የመጀመሪያ ልጃቸውን ይዘው ነበር ወደ ጐንደር ጥምቀተ ባህር ለመሔድ ከድሬዳዋ የመጡት፡፡ በሚያዝያ ወር ለማግባት እየተዘጋጀ የነበረው የመጀመሪያ ልጃቸው የ27 ዓመቱ ቴዎድሮስ ጌታቸው፤ ለጉዞው ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ እናቱ ደስ እንዲላቸው ሲል ብቻ አለቃውን በማስፈቀድ ለመሄድ እንደተነሳ ቤተሰቦች ተናግረዋል፡፡ በአውስትራሊያ የሚኖሩት የወ/ሮ ወርቅአበባሁ ልጆች እህትማማቾቹ ሰብለ ጌታቸውና መዓዛ ጌታቸው ወደ አገራቸው የመጡት ከብዙ ዓመታት የውጭ አገር ቆይታ በኋላ ነበር፡፡ የ24 ዓመቷ ሰብለ በአውስትራሊያ የዶክትሬት ዲግሪዋን ለማግኘት ጥቂት ጊዜያት ቀርቷት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከሊስትሮነት ተነስቶ በመገናኛ አካባቢ የሞባይል መሸጫ ሱቅ የከፈተው በሱፍቃድ ተገኘወርቅም ከጓደኛው ከተክለማርያም ጋር ስካይ ባስ የተሳፈረው በጐንደር የጥምቀት በአል አከባበር ላይ ለመገኘት ነበር፡፡ ተክለማርያም የጐንደር ልጅ ሲሆን ቤተሰቦቹን ለማየት እቅድ ነበረው፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የነበረው በሱፍቃድ ሁለት ወንድሞቹንና አንድ እህቱን ያስተዳድር እንደነበር በህይወት የተረፈው ተክለማርያም ይናገራል፡፡ በሱፍቃድ በአደጋው ህይወቱን አጥቷል፡፡

የ55 ዓመቷ ወ/ሮ ሰጠሽኝ አቸነፍ የአምስት ልጆች እናት ሲሆኑ ወደ ጐንደር ያቀኑት ከአስራ ሦስት አመት በፊት የተለዩትን ወንድማቸውን ለማግኘት ነበር፡፡ እንዲህነው አዘነ የተባለውን የወንድማቸውን ልጅ አስከትለው የተጓዙት የቤት እመቤቷ ወ/ሮ ሰጠሽኝ፤ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን የወንድማቸው ልጅ ግን ከአደጋው ከተረፉት 6 ተሳፋሪዎች አንዱ ሆኗል፡፡

ባለፉ ማክሰኞ ማለዳ ላይ ከመስቀል አደባባይ 47 ሰዎችን አሳፍሮ ጉዞ የጀመረው ስካይ ባስ ቸርቸል ጐዳና ጋ ሲደርስ ትራንስሚሽኑ በመበጠሱ በአደጋው ህይወቷ ያለፈው የአውቶቡስ አስተናጋጅ ወ/ሮ ዝላይ ወደ መ/ቤቱ ስልክ ደውላ ተለዋጭ ባስ እንደተላከላቸው የስካይ ባስ ድርጅት ሠራተኞች ይናገራሉ፡፡ ሁሉም በተለዋጩ ባስ ላይ ተሳፍረው ከጠዋቱ አንድ ሠአት ላይ ከአዲስ አበባ ወጡ፡፡ አደጋው ከመድረሱ በፊት ባሱ ለእረፍት ቆሞ እንደነበረ የነገረን ከአደጋው የተረፈው ተክለማርያም ሁሉም ተሳፋሪ ወርዶ ንፋስ ከተቀበለ በኋላ ጉዞ እንደጀመሩ ያስታውሳል፡፡ ለ30 ደቂቃ ያህል እንደተጓዙ መኪናው የመንጓጓት ድምፅ እንዳሰማ የሚናገረው በአውቶብሱ መቀመጫ ቁጥር 38 ላይ ተቀምጦ የነበረው የ30 አመቱ ወጣት ተክለማርያም፤ ስድስቱ ተሳፋሪዎች ህይወታቸው የተረፈው ባሱ ሲገለባበጥ ተፍቷቸው እንደሆነ ይገልፃል፡፡ እሱ ባሱ ተፍቶት ህይወቱ ሲተርፍ ከጐኑ ተቀምጦ የነበረው ጓደኛው ግን በእሳት ተቃጥሎ ህይወቱ አልፏል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን መረብ ኳስ ፌዴሬሽን በስራ አስፈፃሚነት እና በም/ፕሬዚዳንትነት ረጅም አመታት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ፋሲል እጅጉ በዚሁ ባስ ተሳፍረው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በ1970ዎቹ በቦሊቦሊ ስፖርት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ለጐንደር ምርጥ ቡድን ተሰልፈው ተጫውተዋል፡፡ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሸን ማስትሬት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን ባለትዳር እና የ3 ልጆች አባት ነበሩ፡፡አደጋው የደረሰበትን ስካይ ባስ ሲያሽከረክር የነበረው የ37 ዓመቱ ሰለሞን ተገኝ በአደጋው ህይወቷ እንዳለፈ የታወቀ ሲሆን፤ ሟች በህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ ለ10 ዓመት እንደሰራና ላለፉት ሦስት ዓመታት በስካይ ባስ ውስጥ እንደሰራ የድርጅቱ ሃላፊዎች ነግረውናል፡፡

በአውቶብሱ ውስጥ አስተናጋጅ የነበረችው የ26 ዓመቷ ወ/ሮ ዝላይ ዳኜም የአደጋው ሰለባ በመሆን ህይወቷ አልፏል፡፡ በአደጋው ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስባት የተረፈች አንዲት ተሳፋሪ መኖሯን የጠቆሙን የስካይ ባስ ድርጅት ኃላፊዎች፤ ጉዳት የደረሰባቸው አምስቱ ተሳፋሪዎች በገብረ ጉራቻ ሆስፒታል ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን በአዲስ አበባም በጳውሎስና የካቲት 12 ሆስፒታል ህክምና አግኝተዋል፡፡

ከአደጋው የተረፈው ተክለማርያም አውቶብሱ ገደል ውስጥ ከመግባቱ በፊት ከኋላው በእሳት ተቀጣጥሎ እንደነበር ይናገራል፡፡ ገደል ከገባ በኋላ እሳቱ ተባብሶ በአውቶብሱ ውስጥ የነበሩትን 41 ተሳፋሪዎች በሙሉ ያቃጠላቸው ሲሆን ለቀብር የሚያመች አስከሬን ሊገኝ ባለመቻሉ ሟቾቹ እዚያው ባህር ዳር የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር በተገኙበት ባለፈው ረቡዕ በደጀን ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን የቀብር ስነስርዓታቸው ተፈፅሟል፡፡

 

 

Read 13039 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 11:32