Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 January 2012 10:04

የአርባ ዓመት የትግል ጉዞ በ”የሁለት ምርጫዎች ወግ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሙሼ ሰሙ   የኢዴፓ ሊ/መንበር

ሰዎች ዘርዘር አድርገው ካልጻፉና ካልተናገሩ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለመረዳት ያዳግታል፡፡ በኢህአዴግ ጎራ እንደተለመደው ተቃዋሚዎችን በተቀጥላ ስምና በጥቅሉ ጠባብ፣ ትምክህተኛ… እያሉ ከመጥራት አባዜ ተላቆ በመጸሐፍ መልክ ለመተቸትም ሆነ ለመተንተን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” አንድ እርምጃ ወደፊት የተራመደ ነው፡፡ አንድ አንድ ቦታዎች ላይ የኢህአዴግን ድክመቶች በድፍረትና በመረጃ እያጣቀሱ ለመናዘዝ የተደረገውም ሙከራ ከተለመደው የሰበብና ምክንያት ፍለጋ ፖለቲካ ወጣ ያለ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መጽሐፉ ከላይ ከጠቀስኳቸው መልካም መነሻዎች ውጭ በአጠቃላይ በመረጃ አቀራረብ፣ በሁነቶች አሰላለፍ፣ በመቼት አደራደር ላይ እጅግ ብዙ የሚቀረው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡የሁለት ምርጫዎች ወግን ስናጤን ከግምት ውስጥ መግባት የሚገባው መሰረታዊ ነጥብ አለ፡፡

አቶ በረከትን በሁለንተናዊ መልኩ ከኢህአዴግ ነጥሎ ማየት እንደማይቻለው ሁሉ “የሁለት ምርጫዎች ወግ”ንም ከኢህአዴግ አንደበትነት ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ግንዛቤ መውስድ ያሻል፡፡ ከሃያ ሶስት ያላነሱ ቱባ የኢህአዴግ አመራር አባላት ተራ ገብተው በርብርብ መጸሐፉ ዛሬ ያለውን ቅርጽና ይዘት እንዲኖረው ያደረጉት አስተዋፅኦ በማያሻማ መልኩ በመጸሐፉ ላይ መጠቀሱ ለዚሁ ነጥብ አጋዥ መረጃ ነው፡፡  መጽሐፉን መገምገም ከመጀመሬ በፊት በመጽሐፉ ቴክኒካዊ ብቃት ላይ ጥቂት ማለት እፈልጋለሁ፡፡ በአጠቃላይ “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የንባብ ፍላጐቴን ባይፈታተንም ከባድ የፊደል ግድፈት፣ ድግግሞሽና የስርዓተ ነጥብ መዛነፍ 40 በሚደርሱ ገጾች ላይ ተከስቷል፡፡ አቶ በረከት በዚህ ረገድ አሌ የማይሉት ተጽእኖ እንዳለባቸውም በገጽ 218 ዶ/ር በየነ ያቀረቡትን “የታይፕና” የቋንቋ አሰካክ የእርምት ጥያቄ በመርህ ደረጃ የሚታረም በሚል ያዘገዩበት ሁኔታ በቂ ምስክር ነው ፡፡በመግቢያነት ሌላው ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ አቶ በረከት በመፅሃፋቸው ላይ ቢያንስ በ1997 ምርጫ ምክንያት ለሞቱ በርካታ ዜጎቻችን ስሜታቸውን አልገለፁምና ይህንን ማድረጉ እንደ መንግስትም እንደ አንድ ታጋይም ሊዘነጉት ያልተገባ ነበር እላለሁ፡፡

“የሁለት ምርጫዎች ወግ” ምረቃ

“የሁለት ምርጫዎች ወግ” ምረቃ በድግስ ደረጃ  እጅግ የተዋጣለትና ምናልባትም በኢትዮጵያ የመጽሐፍት ምረቃ ታሪክ ሂደት ሪከርድ የሚሰብር ነው ፡፡ የድግሱ ወጭ ከመፅሐፉ ሕትመት በላይ እንደሚሆንም መገመት ይቻላል፡፡ መፅሐፍ በራሱ ክቡር ነውና እሰየው፤ ደጋሽን እግዜር ይስጠው ከማለት ውጭ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አቶ በረከት ከያዙት ኃላፊነት አኳያ የድግሱ ሂደትና ወጭው ሌላ ትርጉም ሊያሰጥ እንደሚችል ቅድመ ግንዛቤ ሊወስዱ በተገባ ነበር ያሰኛል፡፡ አቶ በረከት ድግሱን ይመኑበትም አይመኑበትም ሂደቱ ከመፅሐፋቸው ባልተናነሰ መጠን በታሪካቸው ውስጥ አወዛጋቢ ምዕራፍ ሆኖ እንደሚኖር አጠያያቂ አይደለም፡፡

በምርቃው ሂደት ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው ከመፅሐፉ ላይ እየተወሰዱ በምረቃው ላይ የተነበቡት ጥቅሶች ጉዳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ በተለይ በምርጫዎች መባቻና ማግስት በዶክመንትሪ ስም በገሃዱ ዓለም ላይ በርካታ ቲያትሮችን ሲሰራ እናውቀዋለን፡፡ በተለይ እጅግ የተካነበትን ቆርጦ የመቀጠልና የማይገናኙ ጉዳዮችን አጨማዶ የማገናኘት የህዝብ ግንኙነት ስራ በዚህ ተግባር ላልተካነ ተራ ሰው ድርጊቱን አድንቆ ከማለፍ  ውጭ ሌላ አማራጭ አይኖረውም፡፡

በሁለት ምርጫዎች ወግ ምረቃ ላይም ይህንኑ ድራማ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ በርካታ አርቲስቶችና ተዋንያን ወደ መድረክ እየወጡ ከመፅሐፉ ውስጥ እኔን ያስደሰተኝና የወደድኩት በማለት ያቀረቧቸው ጥቅሶች እድሜ ለኢህአዴግና ዶክመንትሪዎች ተሞክሮ፣ መጽሐፍን ሳያነቡ ማወቅ፤ ሳይረዱም መውደድ እንደሚቻል በተግባር አሳይተውኛል፡፡

አስደማሚ ድምዳሜዎች

የሁለት ምርጫዎች ወግ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ኢትዮጵያ በኢህአዴግ ቀመር “መቶ ዓመት”፤ በተቃዋሚዎች ቀመር “ሶስት ሺህ ዓመት” እና ከዛም በላይ የኖረች ሃገር መሆኗን ፈጽሞ የዘነጋ ነው፡፡ ገፋ ሲልም ሃገርንና ህዝብን ኢምንት አድርጎ በማቅረብ “ያለ ኢህአዴግ ማንምና ምንም  የለም” እስከማለት ይዘልቃል፡፡

“… ለሃያ ዓመታት የተጓዝንበት የአገር ግንባታ ሂደትም ትንፋሽ የሚያሳጥር ነበር፤ ብርቱ ኢህአዴጎች ብቻ የሚቋቋሙት…” ገጽ 9

ኢህአዴግ ከመጸነሱ በፊት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በርካታ የሃገር ግንባታና የልማት ስራ ሲያካሂዱ መኖራቸው ተረስቶ፤ የዜጎችና የመንግስት አካላት አጠቃላይና የተናጠል ሚና እንደሌለ ተቆጥሮ፣ የኢትዮጵያ የሃያ ዓመት ጉዞ ብርቱ ኢህአዴጎች “ብቻ” የሚቋቋሙት ነው ሲሉና “ ብቻ ” የሚለውን ቃል በማጋነኛነት ሲጠቀሙበት ሁለት ነገሮችን እንድንገነዘብ ፈልገው  እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

አንደኛው ኢትዮጵያ እንደሃገር እዚህ የደረሰችውና ወደፊትም ህልውናዋ የሚረጋገጠው በኢህአዴግ ብርቱ አባላት ብቻና ብቻ እንደሆነና ቀሪዎቹ በብዙ ሚሊዮኖች የምንቆጠር ልጆቿዋ አለኝታና መከታ ልንሆናት ስለማንችል በቀቢጸ ተስፋ ውስጥ የምትዳክር፣ ተስፋ ቢስና ምስኪን ሃገር እንደሆነች ለማስረዳት ሲሆን ሁለተኛው እነማን እንደሆኑ ባናውቅም የሃገራችን ተስፋ ከኢህአዴግ ውስጥም በተለይ በምርጦቹና በብርቱዎቹ ጫንቃና ጉልበት ላይ የወደቀ መሆኑን ነው፡፡ አቶ በረከት ለዚህ ለየት ያለ ድምዳሜ ያደረሳቸውን መነሻና ፋይዳ እንረዳ ዘንድ አንዳችም መረጃ ወይም ማስረጃ በመጸሐፋቸው ውስጥ አላካተቱም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ድምዳሜቸው “ወይ ኢትዮጵያ ለካስ የዜጎች መካን ነሽ” የሚያሰኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

“…ለህዝብና ለሁሉም ተዋናዮች የምርጫ ገጸ-ባህርይ መነሻ ሆኖ ያገለገለው የኢህአዴግ ተሃድሶ ንቅናቄ ነበር…” ገጽ 10

ኢትየጵያና ሕዝቦቿ ለዘመናት የተጫነብን ድርብርብ ጭቆና፣ ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ ድንቁርናና ማህበራዊ ቀውስ፣ እለት በእለት በሺዎች ወደ መቃብር የሚሰደን በሽታ፣ ዓመታት እየቆጠረ የሚገሸልጠን ረሃብ በራሳቸው ለምርጫና ለትግል በቂ መነሻ መሆናቸው ቀርቶ፣ በአንድ ድርጅት ውስጥ የተፈጠረን ውዥምብርና የስልጣን ሽኩቻ ለህዝብ የምርጫ መነሳሳት መነሻ ምክንያት አድርጎ ማቅረብ፣ ምጥን ለእናት እንደማስተማር ያህል የሚቆጠር ነው፡፡ ቆራጡ መሪያችን ሌት ተቀን ባያስቡልን ኖሮ እዚህ አንደርስም ነበር ከሚለው ዜማም ጋር ብዙም የሚራራቅ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያውያን ለመብታቸውና ለጋራ ጥቅማቸው ሲታገሉ፣ የጋራ ጠላቶቻቸውን በየጦር ሜዳው ድል ሲነሱ የኖሩት ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ከመፈጠሩ በርካታ ዘመናት በፊት መሆኑን ማንም አሌ ሊለው የማይችለው እውነት ነው፡፡ ለብዙ ኢትየጵያውያን ዘመናዊ ዴሞክራሲ አዲስ ቢሆንም በሕዝቦች መካከል ፍትሕና ርትሕን ለማስፈን መንግስት ከማንገስ በመለስ በየአጥቢያው ለማህበራዊ ኑሮው፣ ለሰላሙና ለጋራ ጥቅሙ መሪዎቹን ሲመርጥም ሆነ ሲያስመርጥ መኖሩን በሕዝብ ውስጥ ለታገሉት ለአቶ በረከት ሊገለጥላቸው በተገባ ነበረ፡፡

አቶ በረከት  የኢህአዴግ “የተሃድሶ ንቅናቄ” ይበሉት ወይም በሌሎች እንደሚጠራው “የስልጣን ሽኩቻ” በኢህአዴግ ውስጥ ነግሶ የነበረውን የማን ይበልጣልና ማን በተለይ ይጠቀም የሚለውን መገታተር አለዝቦ ሊሆን ይችላል፡፡

ለአብዛኛው ኢትየጵያዊ ግን እኔንም ጨምሮ እንኳን የምርጫ ገጸ-ባሕርይ ሊሆነን ይቅርና ልዩነቱ መች እንደተጀመረና በምን ዓይነት ሁኔታ እንደተጠናቀቀ የመስማትም ሆነ የማወቅ እድሉን ባልጠራ መልኩም ቢሆን ለማንበብ የቻልነው ዛሬ በአቶ በረከት መፅሐፍ ላይ ነው፡፡ ዛሬም ላይ ሆነን በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ሂደቱ ያበረከተው ነገር ቢኖር ለምርጫ መነሻ የሚሆን ገጸ-ባሕርይ ሳይሆን በተደጋጋሚ መብራት መጥፋትና የስልክ መስመር መቋረጥ፣ ገፋ ካለም ጠንከር ባሉና ልጅ ሊሰማቸው በማይገባ ቃላት መወራረፍን ነው፡፡

“… ጊዜያችንን ያጠፋነው ለመስራት የየበኩላችንን አስተዋጽኦ  በማድረግ እንጂ እንደ ተረት አባት ታሪክ በመናገር… ” አልነበረም፡፡ ገጽ 9

“… ኢህአዴግ በዛሬውና በነገው እንጂ በትናንቱ የሚኖር ድርጅት አይደለም…” ገጽ 9

የሁለት ምርጫዎች ወግ መግቢያ ከላይ በቀረበው መሰረት እንደሚተነትነው ከሆነ በጋራ የምናውቃት ኢትዮጵያ ለአቶ በረከትና ለኛ ፍጹም የተለያዩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ታሪካችን እርሳቸው እንደጠቀሱት ተረት አይደለም፣ አልነበረምም፡፡ የተረት አባትም ቢሆን የሚተርከው ተረት እንጂ ታሪክ ሆኖ አያውቅም፡፡

ኢትየጵያውንም ሆኑ የዓለም ሕዝቦች በሞላ ከትናንት ወድያ ላይ ተንተርሰው፣ ትናንትን ወርሰው፣ ዛሬን  በመኖር ነገን አሻግረው ይመለከቱ ይሆናል እንጂ አዲስ ግኝት ካልተፈጠረ በስተቀር የሃገርን ታሪክ የሚያክል ነገር ከዛሬ ወይም ከነገ መጀመር አይቻልም፡፡ ከትናንት ውጭ ዛሬንና ነገን ማሰብም ሆነ ማየት አዳጋች ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ በገጽ 16 ላይ “…በፍርድ ቤትና በግልግል እንፍታው ማለት ቀደምት የኢትዮጵያ መሪዎች ችግርን ለመፍታት ሲጠቀሙበት ከነበረው የፍጥጫና የግጭት መፍትሔ በዓይነቱ የተለየ ነው፡፡”  የሚለው የሁለት ምርጫዎች ወግ  ሃሳብ ነው፡፡

የኢትየጵያ መሪዎች የግጭት አፈታት ስርዓት በድፍኑ የሁለት ምርጫዎች ወግ   የፍጥጫና የግጭት  ነው እንዳለው ሆኖ አያውቅም፡፡ የኢትየጵያ መሪዎች የግጭት አፈታት ስርዓት በድፍኑ የፍጥጫና የግጭት ነበር የሚለው ሃሳብም ለማንም ሊዋጥ የሚችልና ሚዛን የሚደፋ ድምዳሜ ሊሆን አይችልም፡፡

የአቶ በረከት ድምዳሜ ከላይ ለማቅረብ እንደሞከርኩት የኢትዮጵያ ትንሳኤና መልካም ነገሮች ሁሉ መጻፍና መተረክ የጀመሩት በኢህአዴግ ዘመን አድርጎ ለማቅረብና ባለፉት ዘመናት ስንኮራባቸው የነበሩትን እጅግ፣ ዓለምን ያነጋገሩ አልፎ ተርፎም ሃገራችንንም ከጦርነት የታደጉ ዲፕሎማሲያዊ ድሎቻችንን ታሪካዊ ዳራ ለማሳጣት የተደረገ ሙከራ ይመስላል፡፡

በርካታ የአፍሪካ መሪዎች በስልጣን ላይ ለረጅም ጊዜ እየቆዩ በሄዱ ቁጥር፣ እራስን ከፍ ከፍ እያደረጉ የዛሬንና የፊቱን ብቻ በማሰብ የሃገርንና የህዝብን ታሪክ እንደገና መጻፍ የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አቶ በረከት ገጽ 9 ላይ “…ኢህአዴግ በዛሬውና በነገው እንጂ በትናንቱ የሚኖር ድርጅት አይደለም…” ማለታቸው የሃሳባቸው አዝማሚያ እንደ ቀሪዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ታሪክን እንደገና የመጻፍ፣ የመሰረዝና የመደለዝ ዝንባሌ ተጣብቷቸው ይሆን ብለን እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡

ከዚህ አኳያ የቅርብ ጊዜ የኢህአዴግን ተሞክሮ እንቃኝ፡፡ እንደ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ላሉ መሪዎች በሰላማዊ መንገድ ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር የሚዋጥ ሃቅ ሊሆን ስላልቻለ የፍጥጫና የግጭት መፍትሔን በብቸኛ አማራጭነት እንደ ሃገር ለመውሰድ ተገደናል፡፡ በዚህም ምክንያት እጅግ አሰቃቂ ወደ ነበረው ጦርነት በምርጫ ሳይሆን በግድ ገብተን ቀድሞውኑ ሊከፈል የማይገባውን ውድ ዋጋ ከፍለናል፡፡

ማንኛውም ሃገር ሉአላዊነቱን ለማስከበር የሰላም ሃዋርያ ሆኖ መገኘት ብቻ በቂ እንዳልሆነ  ከዚህ አሰቃቂ ጦርነት ኢህአዴግ ትልቅ ትምህርት ወስዷል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ከእልቂትና ከንብረት ውድመት አኳያ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ሊወቀስ የሚገባው፣ ቅድመ ዝግጅት ባለማድረጉና የመከላከያ ሰራዊታችንን ብቁነትና ዝግጁነት ባለማረጋገጡ ነው፡፡ ተጠያቂነቱም መንግስታዊ ስራውን የመዘንጋትና ለከባድ መስዋእትነት ሃገርንና ሕዝብን የማጋለጡ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ ውጭ ተገደን ለገባንበት ጦርነት የቀድሞ መሪዎችንም ሆነ ኢህአዴግን በጦረኛነትና በዲፕሎማሲ ድክመት መፈረጅ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ይህ ሃቅ ለኢህአዴግ ሽፋን የሆነውን ያህል ጦረኛ ለተባሉትና ሳይወዱ በግድ ወደ ጦርነት ለገቡት የኢትዮጵያ መሪዎች በመላ እኩል በምክንያትነት ሊያገለግል መቻሉን አቶ በረከት ሊስቱት ባልተገባ ነበር እላለሁ፡፡

ለዴሞክራሲ ሲባል አቶ በረከት ባለፉት የኢትዮጵያ መሪዎች ላይ የወሰዱትን ድምዳሜ ማክበር ይቻላል፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ሃገርም፣ ሕዝብም፣ አስተዋይነትም፣ ልማትም፣ ጀግንነትም፣ ሰላምም… የተጀመረው በኢህአዴግ ነው የሚለው አቀራረባቸው ግን ለማንም ሊዋጥ የሚችል “ወግ” ሆኖ አላገኘሁትም፡፡

አቶ በረከት የሁለት ምርጫዎች ወግ ታሪክን በየፈርጁ በማስቀመጥ ረገድ ለተመራማሪ  እንደ ዓይነተኛ ሰነድ በሚያገለግል መልኩ በነጻና ገለልተኛ መንፈስ እንዳበረከቱት በመግቢያቸው ላይ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በይዘት ደረጃ ሲፈተሽ ከፍተኛ የሆነ የስሚ ስሚ ትረካ የታጨቀበትና እንደ ኢህአዴግ አባባል በመረጃ እንጂ በማስረጃ የዳበረ አይደለም፡፡

አቶ በረከት እነእገሌ ወይም እነእገሊት የነገሯቸውን “ ወጎች” ከልብ በመውሰድ የመከራከርያ ሃሳቦቻቸውን መፋረጃና መደምደሚያ አድርገው በርካታ ቦታ ላይ ሲጠቀሙባቸው ለማስተዋል ይቻላል፡፡ አንዳንዴም የተለያዩ ግለሰቦችንና ፓርቲዎችን ቁመና መለኪያ በማድረግ ተገልግለውበታል፡፡ አንዳንዶቹ መረጃዎችም ሃሰተኛ መሆናቸውን አቶ በረከት ሳይረዱ ሊባል በሚችል ደረጃ በጽሑፋቸው ላይ ተገልግለውበታል፡፡ የቤዛ ጋዜጠኛን መረጃ ያጤኗል፡፡

አቶ በረከት በበርካታና መሰረታዊ በሆኑ ማስተዋልንና ማመዛዘንን በሚጠይቁ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጭ ናቸው፡፡ ሲወስኑም እናውቃለን፡፡ በውሳኔያቸው ምክንያት እንደሕዝብ ተጠቃሚም ሰለባም ስንሆን ቆይተናል፡፡ በግለሰብ ቃል አቀባይነት የተገኘና መንስኤው ምን እንደሆነ በቅጡ ለመረዳት የማይቻል ሃሳብን ለውሳኔ መስጫነትና ለድምዳሜ መጠቀም ግን ቅንጅትና ደጋፊዎቹኝ አሳንሶ ለማየት ከመጓጓት ያለፈ ትርጉም ልሰጠው አልቻልኩም፡፡

የመረጃ እጥረት ወይስ …

የሁለት ምርጫዎች ወግ ታቅዶና ታስቦ ይሁን ወይም በሌላ ባልታወቀ ምክንያት በርካታ ቦታ ላይ የተዘለሉና ተዛብተው የቀረቡ መረጃዎች አሉት፡፡

“ከቅኝ አገዛዝ ሃይሎች ጋር የተካሄዱትን ጦርነቶች ትተን  ባለፉት አምሳ አመታት የተካሄዱ ከባድ ጦርነቶችን ብንቆጥር…” ይልና ጦርነቶችን ሲዘረዝር በኢትዮጵያና በሻዕቢያ መካከል የተካሄደውን ከ30 ዓመት በላይ የፈጀ ጦርነት ይዘለዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ የጦርነት ታሪክ  እጅግ ከባድ መስዋእትነትን የጠየቀና በርካታ  ሃብትና ንብረት የወደመበትን ጦርነት መጥቀስ ከተፈለገ  በኢትዮጵያና በሻዕቢያ መካከል የተካሄደውን የ30 ዓመት ጦርነትን መርሳት ከኢህአዴግና ከአቶ በረከት ፈጽሞ አይጠበቅም፤ ነገር ግን አቶ በረከት ትንንሽ ጦርነቶችን ሁሉ ሳይቀሩ ዘርዝረው የ30 ዓመቱን ጦርነት ረስተውታል (ረስተውታል ማለት የሚቻል ከሆነ?)

በዚሁ ገጽና አንቀጽ አቶ በረከት የቅኝ አገዛዝ ሃይሎች ጦርነት በማለት የጠቀሱትን ላለማንሳት የሞከሩት በኢትዮጵያና በሻእብያ መካከል የተካሄደውን የ30 ዓመት ጦርነት ከቅኝ አገዛዝ  ጋር ለመላቀቅ እንደተደረገ ጦርነት ስለሚያምኑ ይሆን ? ወይስ የአመለካከት ለውጥ? አቶ በረከት ሊያብራሩት የሚገባ መሰረታዊ ጉዳይ  ይመስለኛል፡፡

በሁለት ምርጫዎች ወግ፣ አቶ በረከት ጦርነትና ረሃብ ያለፉት ስርዓቶች መገለጫ እንጂ ኢህአዴግን የተፈታተነና አሁንም እየተፈታተነ የሚገኝ ችግር እንዳልሆነ ደጋግመው ያስረዳሉ፡፡ አንዳንዴም ድብልቅልቅ ባለ መልኩ ሲገልጹት:-

“አስራ አራት ሚሊዮን ያህል ህዝብ( ወይስ ሕዝቦች?!) ለአደጋ የተጋለጠበት ድርቅ ተከሰተ…”

“እንደተለመደውም በወቅቱ የተጋለጠው አስራ አራት ሚሊዬን የሚለው ቁጥር የተጋነነ እንደሆነ ሊገመት ይቻላል፡፡ ገጽ 33

“…የእርዳታ ፈላጊው ቁጥር ለመጀመርያ ጊዜ በአስር ሚሊዬን አሻቀበ…”

“…የኢንዱስትሪው ቀሳውስት ለአደጋ የተጋለጠውን ሕዝብ ቢያንስ በግማሽ አሳድገው የለጋሽን ልብ ለማስደንገጥና ለማራራት ይጠቀሙበታል፡፡” ገጽ 33

አቶ በረከት በመጸሐፋቸው ገጽ 15 ላይ “…የደም መፋሰስ አዙሪት ለማስቀረት፣ በኛ ይብቃ ብሎ የተነሳው ኢህአዴግ …” በማለት ኢህአዴግ የተዘፈቀባቸውን ጦርነቶች ሁሉ እራስን ለመከላከል እንደተደረጉና ከጀርባ የመወጋት ሴራ አስመስለው ሃዘኔታን በሚጋብዝ አቀራረብ ተርከዋቸዋል፡፡ አልፈው ተርፈውም የአንድ ሃገርን ሉአላዊነት ማስከበር መንግሥታዊ ግዴታ መሆኑንንና ለዚህም ሲባል በቂና ተመጣጠኝ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ እንደነበር በመዘንጋትና ወይም ተጠያቂነትን በማድበስበስ ሻእቢያን እግዜር ይይለት በሚል ቅላጼና በማስተዛዘን ለማለፍ ይሞክራሉ፡፡

አቶ በረከት ወረድ ብለውም በገጽ 15 ላይ  “… ምን እየተደገሰ እንደሆነ በውል ማወቅም ሆነ መገመት በማይቻልበት [ሁኔታ] ባድመ የኔ ነው በሚል ሽፋን ” እና “…በድንገት በኤርትራ መንግስት የተሰነዘረው ጥቃት…” ገጽ 16  እኛ መቼ ገመትን i? መቼ ተዘጋጀን i? ሻዕቢያ ሳይነግረንና ሳያሳውቀን በድንገት  ወረረን እንጂ በማለትም “ከበረሃ ጀምሮ ሻዕብያን ጠንቅቀን እናውቀዋለን” ሲሉ መኖራቸውን ይዘነጉታል፡ ማንኛውም መንግስት ከስራና ኃላፊነት መዘርዝሮቹ ውስጥ ዓይነተኛውና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የሃገሩ ሉአላዊነት እንዳይደፈር ነቅቶ መጠበቅና አቅም በፈቀደው ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ሲሆን ደፍሮ የሚመጣ ሲኖር ደግሞ በብቃት መመከት ነው፡፡ ይህንን አለማድረግ መንግሥታዊ ግዴታን አለመወጣት ነው፡፡

እራስን መከላከል ሌላ ተቀጥላ የለውም፡፡ ማንኛውም መንግስት እንደዚህ ባሉ መሰረታዊ የሆኑ የህይወት፣ የንብረትና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን በሚያስከትሉ ጉዳዩች ላይ ነጮቹ እንደሚሉት በግምት መመራት (second guessing) አይፈቀድለትም፡፡

“ለልማት ስል እኔ ሰራዊቴን ማደራጀት ስላቆምኩ”፣ “የአፍሪካ ቀንድ መሪዎችን አትውጉኝ ስላልኩ ወይም ሞቅ ደመቅ አድርጌ ስለሰላም ስለዘመርኩ ሰላም ይሰፍናል” በሚል መነሻ ሰራዊትን መበተንና በተበተነው ልክ መልሶ አለማደራጀት ተቀባይነት የለውም፡፡  ያውም  ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላለችና ዙርያዋን በድንበር ጥያቄ በተወጠረች ሃገር ላይ እንደዚህ ዓይነቱ በመላምት መመራት( second guessing) አለመፈቀድ ብቻ ሳይሆን ለተፈጠረው ምስቅልቅልና ለተከፈለው መራራ መስዋእትነት ኃላፊነቱን የሚውስድ ሃይል በግልጽ ሊቀመጥ ይገባል፡

የሁለት ምርጫዎች ወግ በተቃዋሚዎች ላይ በጥቅሉ በተለይ ደግሞ በቅንጅት ላይ ከፍተኛ የማጥላላትና የማሳነስ ዘመቻ አካሂዷል፡፡ ይህንን በምሳሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡

“የቅንጅት ስር ከቀድሞዎቹ የኢትየጵያ ገዢዎች የሚመዘዝ ነው፡፡ ምንም እንኳን አዳዲስ የስልጣን ተስፈኞች የቅንጅትን ሰልፍ የተቀላቀሉ መሆኑ ባይዘነጋም፡፡” ገጽ 59

አቶ በረከት ይህንን ሃሳብ በመጸሐፋቸው ውስጥ ሲያካትቱ ምንን መሰረት አድርገው እንደሆነ ለሰሚ ግራ ነው፡፡ የቀድሞ የኢትየጵያ ገዢዎች ሲባል  ገዢዎቹ ኢትዮጵያውያን አይደሉም ለማለት ነው፡፡ የማንም ስር ካለፈው ስርዓት መመዘዙ የማይጸዳና የማይታጠብ ሃጥያት ተደርጎ መቆጠሩ ነው? እነዚህ የተባሉት ግለሰቦችስ እነማን ናቸው? ኢንጅነር ሃይሉ ናቸው ? ዶ/ር ብርሃኑ ነው ? ፕሮፌሰር መስፍን ናቸው? በቁጥር ቢገለጡስ ስንት ስለሆኑ ነው፤ ቅንጅትን በሞላ በዚህ ደረጃ እንደሚወክሉ ተደርጎ የተገለጸው ? ስራቸው ተመዛዥ የተባለው ከላይ የተጠቀሱት ግለሰቦች ከሆነ እርግጠኛ ነኝ አንዳንዶቹ ኢህአዴግን እንዲያገልግሉ ተጠይቀው እምቢ እንዳሉ ከአንደበታቸውና ከጽሑፋቸው አንብቤያለሁ፡፡ ቀሪዎቹም ኢህአዴግን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ አገልግለው በልዩነት የወጡ ናቸው፡፡

“የስልጣን ተስፈኞች” ማለትስ ምን ማለት ይሆን? የስልጣን ተስፈኛ መሆን የሚንኳሰስ ተግባር መሆኑ ይሆን? አቶ በረከት ጫካ የገቡት  የስልጣን ተስፈኛ ሆነው አልነበረምን? እርግጠኛ ነኝ በረሃ የገቡት ከሃገር ሃገር እየተሰደዱ ጭቁኖችን  ከጭቆና ነጻ ለማውጣት ብቻ እንዳልነበረና ቢያንስ ነጻ ከማውጣት በኋላ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ስልጣን አስፈላጊ እንደነበር ልቦናቸው ይስተዋል ብዬ አልገምትም፡፡

አቶ በረከት ከሽፍትነት ውጭ የስልጣን ተስፈኛ ሳይሆኑ በጫካ ውስጥ ትግል ማካሄድ እንደማይቻል ጠንቅቀው ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የስልጣን ተስፈኝነትን የማንቋሸሽ ዝንባሌ ስልጣኔን “አትንኩ” ብቻ ሳይሆን “አትመኙ” ከሚሉትና ከተቀቡት ነገስታት ተራ የሚያሰልፋቸው አመለካከት  መሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡

በአጠቃላይ ስሩ ከቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ገዢዎች የተመዘዘ ሁሉ ከምድረ-ገጽ ካልጠፋ በስተቀር በቀድሞ ስርዓት ውስጥ ያለፈና ያገለገለ ወይም (በርካታ የቀድሞ ስርዓት “ባለስሮች” በኢህአዴግ ውስጥ እያገለገሉ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡)

የስልጣን ተስፈኛ የሆነን በተቀጥላ ማብጠልጠል በሰላም ከመኖር ጀምሮ በህገ-መንግስቱ ውስጥ የሰፈሩ የመደራጀትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የመለየት መብትን  ፍጹም የዘነጋ  አመለካከት ከመሆን አይዘልም፡፡ ከየትኛውም ስርዓት ስሩ የሚመዘዝ ማኝኛውም ዜጋ በሕግ ከሚሰጠው ቅጣት ውጭ ሌላ ትንታኔም ሆነ ተቀጥላ እያበጁ ማሸማቀቅና ማጥላላት በፖለቲካዊ ትንታኔም ሆነ በሕግ ወይም በሞራል ዓለም ሊደገፍ የሚችል አቀራረብ አይደለም፡፡

ሕገ-መንግስትና ሰላማዊ ትግል

መቼስ አቶ በረከት ተቃዋሚዎች በሕገ-መንግስት ላይ ስላላቸው አቋም በርካታ ጊዜ ከቄሱ ደቀመዝሙሩ ሊያስብል በሚችል ደረጃ ያላሉትን ሲያናግሩ፣ ያልወሰዱትን አቋም ሲጭኑባቸው ማድመጥ የተለመደ ነው፡፡ ይህንኑ ብሒል ተጠቀመው ሕገ-መንግስቱ ይሻሻል ያለን ሁሉ ሕገ-መንግስትን እንደሚንድና እንደሚያፈርስ አድርጎ ማቅረቡን በመጸሐፋቸውም ላይ ቀጥለውበታል፡፡

(ተቃዋሚዎች) “...ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በውድም በግድም መፍረስ አለበት፡፡” ገጽ 62

“…ተቃዋሚዎች በሕገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች ላይ ከመዝመት …” ገጽ 56

“..በሀገራችን የሚገኙ ፓርቲዎች ሕገ-መግስቱን በመቀበልና ባለመቀበል ስርዓቱን በማስቀጠልና በኃይል በመቀየር መካከል የተራራቀ አቋም ያላቸው በመሆኑ..” ገጽ 62

“በሁሉም ሕገ-መንገስታዊ ስርዓት እንደሚደረገው፣ ዜጎች ሕገ-መንግስቱን ወደውና ፈቅደው ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡” ገጽ 177

በመጀመርያ ደረጃ በውዴታ (በስምምነት) ሕገ-መንግስቱን ከመቃወም ጀምሮ እስከ ማፍረስ የዘለቀውን መብት መጻረር ማንም ሊረዳው እንደሚችለው ሕገ-መንግስቱን መጻረር ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ የተገለጹት መብቶች በሕገ-መንግስቱ ውስጥ የሰፈሩ መብት መሆናቸውን አቶ በረከትም በመፅሐፋቸው ገልጸውታል፡፡ የኢትየጵያ ሕገ-መንግስትንም ሕገ-መንግስቱን መለወጥ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ልቆ በመሄድ ሕገ-መንግስቱ እንዴት ሊፈርስ እንደሚችል  አንቀጽ አለው፡፡ አንቀጾቹን  ያጤኗል፡፡

በገጽ 177 ላይ በመውደድና በመፍቀድ ዙሪያ የሰፈረውን ሃሳብ በቅጡ ላጤነው ግን ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ የሚባለው አይነት ነው፡፡ዜጎች ህገመንግስቱን ወደውና ፈቅደው ማክበር ይጠበቅባቸዋል ይላል፡፡ መውደድና መፍቀድ የእምነት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በውስጣቸው አለመውደድና አለመፍቀድም አለ፡፡ ማክበር የሚመነጨው ደግሞ ከመውደድና ከመፍቀድ ነው፡፡ አለመውደድና አለመፍቀድ ካለ ደግሞ መቃወምና መታገል አይቀሬ ነው፡፡ አቶ በረከት ሕገ-መንግስትን የመቃወምና እስከናካቴውም ለመለወጥ የመታገል ጥያቄን ሕገ-መንግስትን ከመናድ ጋር ማስተሳሰራቸው በዚህ ዓይነት ተቃርኖ ውስጥ የተፈጠረ ስሜት ከመሆን አያልፍም፡፡ ሰሞኑን በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ናይጄሪያ በአደባባይ ተቃውሞ ወይም እንደኢህአዴግ አባባል ነውጥ ስትታመስ ከርማ ፕሬዚዳንት ጉድ ላክ ጆናታን የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያቸውን አንስተዋል፡፡በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ተመሳሳይ የመብት ጥያቄን አቶ በረከት እንዴት ነው የሚረዱት? መብትን ለማስከበርና ለመደማመጥ እንደሚደረግ እንቅስቃሴ ወይስ ሕገመንግስቱንና ስርዓቱን ለመናድ እንደሚደረግ ነውጥ? ጥያቄውስ ሕዝባዊ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሕዝቡ በተሳትፎ ያረጋግጠው ዘንድ ምህዳሩ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ሊረጋገጥለት አይገባም ወይ? የመብት ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ሳይውሉ ሳያድሩ ሕገ-መንግስት የመናድና ስርዓት የማፍረስ ስለሚሆን የዳቦም፣ የመሬትም፣ የስራ አጥነትም ሆነ ከሕገ-መንግስቱ በመለስ ያሉ ጥያቄዎች በሙሉ ሁሌም ያንጋጠጡትና ያፈጠጡት እዚሁ ነጥብ ላይ ነው፡፡

ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ትክክል ስለሆነ መቀጠል አለበት የሚለው አስተሳስብ እንዲራመድ የመንግስትነትን መንበር ለመያዝ የሚያስችል ድጋፍ ያቀዳጀውን ያህል  ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ትክክል ስላልሆነ መለወጥ አለበት የሚለው አስተሳሰብም እንዲራመድ ሕገ-መንግስቱ ይፈቅዳል፡፡ ሕገ-መንግስቱ የሚጥላላ ነገር ካለውም ማጥላላት እንደሚቻል ሕገ-መንግስቱ ይፈቅዳል፡፡

ሕገ-መንግስት በተቃውሞ እንዲሻሻልና ብሎም እንዲለወጥ አቶ በረከት በረሃ የተንከራተቱበት ዓላማቸው እንደነበር ከንግግራቸውና ከድርጊታቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ዛሬ ግን በመጽሐፋቸው ላይ ሕገ-መንግስቱን አትቃወሙ፣ አታብጠልጥሉ፣ አትተቹ ሲሉ ቀደምት እምነታቸውን እየተቃረኑና ኑቮ አሪስቶክራትነት በውስጣቸው እየታገላቸው እንደይሆን እሰጋለሁ፡፡

ሕጌንና ሕገ-መንግስቴን አትንኩ፣ የስልጣን ተስፈኛም አትሁኑ ማለታቸው ወቅቱ በመፍቀዱ በዋና ተዋናይነት እርሳቸውና ድርጅታቸው ያረቀቁት፣ የተሳተፉበትና እንዲጸድቅ ያመቻቹትን ሕገ-መንግስት ዓለም ላይ ካሉ ሕገ-መንግስቶች ሁሉ ተለይቶ ሊፈተሸና ሊነካ የማይገባው መለኮታዊ ነው ብለው ማመናቸውን ጠቋሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

አቶ በረከት በተቃውሞ ሕገ-መንግስታዊ መሻሻልን መሻትን  በመናድና በማፍረስ መተርጎማቸው እስከቀጠለ ድረስ  ውጤቱ ከላይ እንደጠቀስኩት ስልጣኔን “አትዩ” ብቻ ሳይሆን “አትመኙ” ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ በሂደት ድርጅታቸውና መሪዎቹ ከተቀቡት ነገስታት ተራ መሰለፋቸው  የጊዜ ጉዳይ እንጂ አይቀሬ ያደርገዋል፡፡

የሰው ልጅ ሁል ጊዜም በለውጥ ሂደት ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ነባራዊ እውነታ ነው፡፡  ይህንን የለውጥ ህግጋት ማቆምም ሆነ ማቋረጥ አይቻልም፡፡ እንኳን ሰው ሰራሽ ሕገ-መንግስትን ማሻሻልና መለወጥ ይቅርና መለኮታዊ ሃይል የተሰጣቸው ቅዱስ መጽሐፍትም በለውጥና በህዳሴ ጎዳና ውስጥ አልፈዋል፡፡

አቶ በረከት ድርጅታቸው ኢህአዴግን ጨምሮ በሕገ-መንግስት አስፈላጊነት ላይ ባላቸው አቋም ላይታሙ ቢችሉም ሕገ-መንግስት ግን ሊሻሻልና ከናካቴውም ሊለወጥ የሚችል ሰነድ መሆኑን ከመቀበል አኳያ ያለባቸውን ቀኖና ግን በመጸሐፋቸውም ላይ መደበቅ አልቻሉም፡፡

ዴሞክራሲን የማስፈንና በሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነትን የማቀዳጀት ስራ በአንድ በሰው ልጅ እድሜ ሊጠናቀቅ እንደማይችል እየታወቀ ይህንን ምክንያት በማድረግ  ለዘመናት በስልጣን ላይ መቆየት ዴሞክራሲን በተግባር ከመጻረር ባለፈ  በሂደት መዛልና ቀጥሎም ከራስ እምነት ጋር መቃረንን ያስከትላል፡፡

እድሜ ክፉ ጠላት ነው፡፡ አቶ በረከትና ድርጅታቸው በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ የተቀረቀሩ ይመስላል፡፡ ከሃያ አመት በፊት ተረቆ የጸደቀው ሕገ-መንግስት ጥያቄ እየተነሳበት ያለው ከጅምሩ ሲቃወሙት ከነበሩት ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን ከኢህአዴግ መስራችና ሕገ-መንግስቱን በማጽደቅ ሂደት ዋነኛ ተዋንያኖች ከነበሩትና  ከአዲሱ የአስተሳሰብና የእድሜ ትውልድ ጭምር ነው፡፡

አቶ በረከት በሕገ-መንግስቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በማጣጣል ስርአት የመናድ  እንቅስቃሴ አድርገው ማቅረባቸው አንድም ሕገ-መንግስቱን መንግስታቸውን የመጠበቂያ ልዩ መሳርያ አድርገው በማመናቸው ወይም ከሂደትና ከለውጥ ለመማር የማፈግፈጋቸው ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡

አንዳንድ ተቃርኖዎች ከራስ ጋር

“ተቃዋሚዎች ተመረቁ ብሏቸው ሲፈጠሩ ጀምሮ ሁሌም በአጭሩ ተዘጋጅተው በአጭሩ ይሮጣሉ፡፡… ረጅም ነገር አይወዱም ፡፡ ቁም ነገር የሚመከርበት ዘለግ ያለ ስብሰባ ይጠላሉ፡፡…. ነገር ሲረዝም በጣም ይሰለቻቸዋል፡፡” ገጽ 197

“የተቃዋሚ መሪዎች አብዛኛውን ጊዜ እስኪመሽ ድረስ መቆየትን አይወዱም፡፡…” ገጽ 170

“ዘለግ ያለ ድርጎ (ኮንሴሽን) እንዲሰጣቸው ይመኛሉ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ከአብዛኛው በተለይም ደግሞ ጽንፈኛ ከሆኑ ተቃዋሚዎች ጋር የሚካሄዱ ድርድሮች ረጃጅም ቀናትን የሚወስዱ፤ አሰልችና በዝባንኬ የተሞሉ ሃሳቦችን የምንሰማባቸው ነበሩ፡፡” ገጽ 170

“…በፓርላማ ህጎች፣ በምርጫ ህግና በምርጫ ቦርድ አወቃቀር እንዲሁም በሚዲያ ህግና በፓርቲዎች ፋይናንስ ላይ በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ ድርድር እንዲካሄድ ተደረገ፡፡” ገጽ 214

“.. አህአዴግ፣ ኢድኃኅና ኦፌዲን ባለፉት ሁለት ወራት በስድስት ጉዳዮች ላይ ሲወያዩ ቆይተዋል..” ገጽ 183

በመግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት ሰፋ ተደርጎ ከተፃፈና ከተነገረ ጥርት አድርጎ ማየት ያቻላል፡፡ አቶ በረከት የመጻፋቸው በጎነት ይኸው ነው፡፡ ከላይ በገጽ 197፣ 170፣  214፣ የቀረበው ሃሳብ እንደሚያብራራው፤ አቶ በረከት ተቃዋሚዎችን የሚያስቀምጡበት ቦታ ግር ያላቸው ይመስላል፡፡ መቼስ ተቃዋሚዎች በአንድ ላይ በአጭር የታጠቁና ረጅም ስብሰባ የሚጠሉ፤ እንደገናም ረጃጅም ቀናት የሚወስድ ስብሰባ መካፈልን የሚሹ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አቶ በረከት ለትንታኔያቸው እስከረዳቸው ድረስ ተቃዋሚዎችን በአንድ ጉዳይ ሁለት ገጸ ባሕርይ መስጠትን ምን ተዳዬ ያሉ ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ በዚህ አይነት ወጥነት የጎደለው የተደበላለቀ፣ ፍረጃና ግንዛቤ ውስጥ ሆኖ ተቃዋሚዎች የምናደርገው ሰላማዊ ትግል ግር ቢለን እንዴት ሊፈረድ ይችላል?

“ከቅንጅት ኢዴፓ፣ ከሌላው የተቃዋሚ ድርጅት ደግሞ ሕብረትና ኦፌዲን መስከረም ላይ የተሰመረው ቀይ መስመር የምር እንደሆነ ተገንዝበው አቤት ወዴት ሲሉ ሰንብተዋል፡፡” ገጽ 182

“ሁለቱም ወገኖች ፀጋዬ ገብረመድህን እሳት ወይ አበባ በሚለው መድብሉ በተስለምላሚነት የገለጻት ቢራቢሮ ያስንቃሉ፡፡” ገጽ 183

እነልደቱና ዶ/ር በየነ ሕግ አክባሪ ለመባል ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል የተዘጋጁበት ስለሆነ ….. ገጽ 183

“…የህዝብ ልጆችን ወደ እሳት ሲማግዱ ከከረሙ በኋላ የነበልባሉ ወላፈን ወደ እነርሱ መጠጋት ሲጀምር እንነጠፍላችሁ ማለት…” ገጽ 188

“ ከዚህ ጋር ተያይዞ ትክክለኛዋን ወቅት መርጠው እጃቸውን መሰብሰባቸው በጎዳና ላይ ነውጥ ወንጀል እንዳይጠየቁ ስላደረጋቸው አከራረማቸው ሕግ አክባሪ የመሆን ወይም መስለው የመታየት ጥድፊያ የበዛበት ሆነ፡፡” ገጽ 182

ኢዴፓ በወቅቱ የወሰዳቸው ጠንካራ አቋሞች እጅግ ከተቆጣ ሕዝብና አቅሉን ከሳተ ሃይል ጋር ያፋጠጡትና ከግራና ከቀኝ ፈታኝ በሆነ አደጋ ውስጥ እያለ እንደነበር ማንም የሚስተው አይመስለኝም፡፡ አቋሞቹም ለሰላማዊ ትግል ከፍተኛ በሚባል መስዋእትነት የተገኙ ድሎችን አጥርቶ ማረጋገጥና በሰላማዊ ትግል የተገኘው ድሉ ላይ ከኢህአዴግ ጀምሮ  ከሁሉም አቅጣጫ በተለያዩ ሃይሎች የተቃጣበትን አደጋ ለመከላከል የሚያስችል አቅጣጫ መቀየስ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ በጅምር የነበረው ሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ አላስፈላጊ ለሆነ አደጋ ተጋልጦ እንዳይዳፈን በህጋዊ መንገድ ምክር ቤት ገብቶ በመታገል ለተሟላ ውጤት ማብቃት ዓይነተኛ ትልሙ ነበር፡፡

አቶ በረከት በሁለት ምርጫዎች ወግ የኢዴፓን አቋም በዚህ መልኩ ማቅረባቸው የወቅቱን የቅንጅት ትግል መልክና ቅርጽ ለማሳጣት የታለመ እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡ ይህም ሆኖ ቢያንስ ቢያንስ ትግሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲጓዝና ያልተፈለገ መስዋእትነት እንዳይከፈልና አልፎ ተርፎም ዛሬ ሕዝብን እያስቆጨ ያለውን ምክር ቤት ገብቶ የመታገል አጀንዳ እዚህ በማድረስ ኢዴፓ የነበረውን ሚና ከማውሳት መቆጠባቸው ወይም መርሳታቸው አስደናቂ ነው፡፡

ኢዴፓ በወቅቱ የተጋረጠበት አደጋ የኢህአዴግ የ11ኛ ሰዓት ማስጠንቀቂያ ሊሆን እንደማይችል አቶ በረከት ሊረዱት የሚገባና ያልተረዱት ጉዳይ ነው፡፡ በወቅቱ ለቅንጅትና አባላቱ ከባድ የነበረውና በርካታ የቅንጅት አባላትም ትግሉን ለማስቀጠል አይነተኛው መንገድ ምክር ቤት መግባት እንደነበረ እየተረዱ ለመወሰን ያንገዳገዳቸው በሕዝቡ ውስጥ የነበረው ቁጣ ነበር፡፡ የኢህአዴግ የ11ኛ ሰዓት ማስጠንቀቂያ የመጣው ከዛ በኋላ ነበር፡፡

ሰላማዊ ትግል ለኢትዮጵያኖች አዲስ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ልጆቿ ሰላማዊ ትግልን  በአስቸጋሪ ሂደት ውስጥ በመማር ላይ ነን፡፡ ዴሞክራሲ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ እንዲሰፍን በመማማር ሂደቱ ውስጥ እያለን በአንድ በኩል እውቅና መሰጣጠት፣ መቻቻል፣ መደማመጥና መከባበር የሰፈነበት፤ በሌላ በኩል መብቶችና ግዴታዎች ለሁሉም በእኩል የሚያገለግሉበት አስተሳሰብና ስርዓት አሸንፎ ሊወጣ ይገባል፡፡

ከዚህ አኳያ ሂደቱን የማስቀጠልም ሆነ የማረጋገጥ ስራ ሁለንተናዊ ትብብር፣ ተሳትፎን፣ ቀና ልቦናና ክፍት አዕምሮን  ይጠይቃል፡፡ በሰላማዊ ትግል ሂደት ውስጥ ዴሞክራሲ ተጠናክሮ እንዲወጣ ቁርጠኝነት ከሚጠይቁት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ልክ እንደጦርነት የአሸናፊና የተሸናፊነት ዝንባሌና ስነልቦና የነገሰበት አለመሆኑ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግል የተረጋጋ ቅርጽና ይዘት እንዲሁም ተገማችነት እንዲኖረው ለማድረግ የመጠንና የቁጥር ካልሆነ በስተቀር ሁሉም አሸናፊ ሆኖ ሊወጣ የሚችልበትን አሰራር መከተል የግድ ይለዋል፡፡

ከላይ በገጽ 182, 183 እና 188 ላይ የቀረቡት ሃሳቦች እንደሚጠቁሙት፤ አቶ በረከት ለሰላማዊ ትግል በተለምዶ ሲሰጡት ከነበረው ትንታኔ መፅሐፋቸው በጣም የራቀ፣ እውቅ የመስጠትንና የመደማመጥን አሰራር የሚያጥላላና እድል የሚነፍግ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ መጽሐፋቸው በአብዛኛው በተሞከሩ ሕጋዊ የድርድር፣ የሎቢ፣ የውይይት መንገዶች ላይ የሚዘባበትና ሰጥቶ የመቀበልን ዴሞክራሲያዊ አሰራር እንደመንበርከክ፣ መስለምለምና መሸነፍ አልያም ማድፈጥ አድርገው አቅርበውታል፡፡

እስከዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደውንና እየተካሄደ ያለውን ሰላማዊ ትግልና  ተቃዋሚዎችን በቅጡ ተንትኖ መታረም በሚገባቸው ቦታ የማረምያ፤ መጠናከር ባለባቸው እንዲጠናከሩ ድፍረት በተሞላበት መንገድ እውቅና የመስጠት አቅጣጫን ለመከተል የተናነቀው ነው፡፡ በአጠቃላይ  ስህተትን በቅጡ የማይተነትን ድጋፍን  በቁርጠኝነት የማይገዳደር ሾላ በድፍን የሆነ የማዳከም ዘመቻ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ለተቃዋሚዎች መዳከም  ዓይነተኛ ተጠያቂው እራሳቸው ተቃዋሚዎች ተጠቃሽ  ቢሆኑም መንግስትና ገዢው ፓርቲ የሚጫወቱት ሚና የአንበሳውንም ድርሻ ይወስዳል፡፡ ደካማ ተቃዋሚ ባለበት ሁሉ አለቅጥ ያበጠ ገዢ ፓርቲ መኖሩ ሃቅ ነው፡፡ አቶ በረከት በተቃዋሚ ፓርቲ ድክመት ሲስቁና ሲሳለቁ ቢያንስ በመንግስታቸው ላይ  እየሳቁና እየተሳለቁ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የመንግስታቸው ሚና ዴሞክራሲን ማስፈን ከሆነ ተቃዋሚ ያልተወከለበት ዴሞክራሲ ትርጉም የሌለው መሆኑን ለማወቅ እንደማይሳናቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡  በሃይል አሰላለፍ ምክንያት በወከባና በመሳደድ የዛለና የደከመ ተቃዋሚ ላይ መዘባበት ዴሞክራሲንም ሆነ ልማትን ወንዝ ሊያሻገሩት እንደማይችሉ ግልጽ ነው፡፡

ዴሞክራሲን ሁለንተናዊ ቅርጽና ይዘት ለማስያዝ አቶ በረከት ሰላማዊ የድርድር ፖለቲካን ከተነተኑበት መስፈርት እጅግ ልቆና ደምቆ መታየት የግድ ይላል፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ በሌለበት ዜጎች ከአምባገነኖች ነጻ መሆናቸውና ገዢዎች ስልጣንን ተላምደው እራሳቸውን ብቸኛ  አማራጭ ከማድረግ አልፈው ተርፈው የተቀባ ከማድረግ የሚያግዳቸው አንዳችም አጥር የለም፡፡  ዴሞክራሲን ጀማሪ ነን በሚሉ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ስልጣን በምርጫና በገደብ ሲሉ እንዳልነበር እድሜ ሲገዳደርና የስልጣን ዘመን በምርጫ ሲያጥር ልጆቻቸውን ለማንገስና የስልጣን ዘመናቸውን  ለማራዘም  ከሕዝብ ጋር ሲፋጠጡ ማየት የተለመደ ክስተት እየሆነ እንደመጣ ልብ ማለት ይገባል፡፡

“በመጀመሪያዎቹ 10 እና 12 ዓመታት በአግባቡ ባልተፈጸሙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት የተነሳ በህብረተሰቡ ውስጥ በተለይ በከተማ ነዋሪዎች ዘንድ እየተባባሰ የመጣው ብሶት፣ ተስፋ መቁረጥና ሌሎችም ተዛማጅ ችግሮች…”  ገጽ 31

“.. በኢህአዴግ አካባቢ የነበረውን ውሱንነት በግልጽ መመልከት ይቻላል፡፡ ” ገጽ 74

“…ዓለም አቀፍ የቀለም አብዮተኞች ከሚከተሉት ስልት አንዱ የሆነውን ብሶትን የማራገብ ስራ ገፉበት፡፡ ህዝቡ በስርዓቱ ላይ እንዲነሳ ለማድረግ ዋነው ጉዳይ ተስፋ እንዲቆርጥ ማድረግ በመሆኑ …” ገጽ 70

አቶ በረከት በገጽ 70 ላይ ተቃዋሚው ብሶትን ማራገቡን ተስፋ እንዲቆርጥ ማድረግ ስራቸው አድርገው ተያያዙት ሲሉ በተናጥል በየገጹ ላይ ለሚከተላቸው ግር ሊል ይችላል፡፡ ወጥነትና ተከታታይነት ባለው መልኩ ስንመለከተው ግን ሃሳባቸው ተቃርኖ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡

የሁለት ምርጫዎች ወግ ኢህአዴግ ከ10 አስከ 12 ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ከድርጅታዊ አቅም ውስንነት ይመንጭ ወይም ሌላ ምክንያት ይኑረው  ስራውን በአግባቡ አለመፈጸሙን ገጽ 31 ላይ በዚህ ባለው መልክ ያስቀምጡታል፡፡ በአግባቡ ባልተፈጸሙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ብሶትና ተስፋ መቁረጥ እንደተከሰተም ለጥቆ ይተነትናል፡፡ ኢህአዴግ ባልሰራው ስራ የተከሰተን ብሶትና ተስፋ መቁረጥ በተቃዋሚ ላይ ማላከክ ለምን አስፈለገ?

ቅንጅት የነበረ ብሶትን ጋልቦ ወይም የነበረ ተስፋ ማስቆረጥን በትግል ስልትነት መከተሉስ እንዴት ስህተት ሊሆን ይችላል? በአቶ በረከት ሃሳብ መሰረት በአግባቡ ያልተፈጸሙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ብሶትና ተስፋ መቁረጥን ካመጡ፣ ብሶትንና ተስፋ መቁረጥን መታገያ ማድረግ ለቅንጅት ልማትንና መልካም አስተዳደርን ለተጠማ ህዝብ መታገል ከመሆን ውጭ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? አቶ በረከት ዘንግተውት ካልሆነ በስተቀር ኢህአዴግ ከጫካ ሲመጣ ብሶት የወለደው ድርጅት አልነበረምን?

 

ምርጫና ቅርጫ

(ኢህአዴግ) “…እንከን የለሽ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ቆርጦ መነሳቱንም በይፋ አወጀ..” ገጽ 51

“…ይህም ኢህአዴግ በሚያራምዳቸው የፓለቲካ ዓላማ ትክክለኝነት፣ በራሱና ድርጅታዊ ጥንካሬና በነበረው የህዝብ ተቀባይነት የነበረውን መተማመን የሚያሳይ ነው፡፡”

“ኢህአዴግ ወደ ምርጫ ክርክሩ የገባው ሁሌም … የሚያራምደው መስመር የተሻው አማራጭ በመሆኑ የመመረጥ እድሉ ሰፊ ነው በሚል እምነት ነው፡፡” ገጽ 63

የሁለት ምርጫዎች ወግ ምርጫ ዓይነተኛ አጀንዳው ነው፡፡ ምርጫ 97 ለተቃዋሚዎች የፈጠረውን ድል  ምክንያት በማፈላለግና እውነታዎችን ቆንጽሎ በማቅረብና የተዛባ ቅርጽና ይዘት በመስጠት አምርሮ እየታገለ፤ ምርጫ 2002ን የምርጫ 97 ተሃድሶ አድርጎ ያቀርባል፡፡

ኢህአዴግ የምርጫ ዝግጅት ማድረግ የጀመረው ከዓመት በፊት እንደነበረና እስከ ደቡብ አፍሪካ ለዚህ ጉዳይ እንደተንቀሳቀሱም ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ገደብ የሌለው የአሸናፊነት ስነልቦና እንዳላቸው ከላይ በቀረቡት ገጽ 51ና 63 እንዲሁም በሌሎች በርካታ ቦታዎች ያገልጻሉ፡፡

ክርክሩም ሰፋ ባለ መልኩ እንዲካሄድና ረጅምና ሰፊ የአየር ጊዜ ተቃዋሚዎች እንዲያገኙ ያደረገው እንደመብት ሁሉም አስተሳሰብ መቅረቡን ከማመን ባሻገር እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ስለነበሩ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ምርጫ 2002 ላይ ግን ኢህአዴግ የመገናኛ አጠቃቀምን በሚመለከት 97 የነበረውን አቋም ለውጦ በቂ ሰዓት ከመደልደል ይልቅ አምስት ዓመቱን ሙሉ የነገረንን ለመድገም ከደለደላት ጥቂት ሰዓት ላይ ትልቁን ሰዓት ለመውሰድ ተሰለፈ፡፡ ድርጊቱም ሚስቱ ወልዳ ከሚጠይቀው ጋር ለገንፎ እንደሚሰለፈውና ሳህን ይጨመር ከማለት ይልቅ ጭልፋ ይዞ የመጣውን አባወራ ተረት ያስታውሰናል፡፡

የሁለት ምርጫዎች ወግ ላይና በተግባርም በ1997 ኢህአዴግ ምርጫውን እንከን የለሽ አደርገዋለሁ በማለት ተንቀሳቅሶ እስከ ቆጠራ ድረስ ምርጫውን እንከን የለሽ ማድረግ ችሏል፡፡ በወቅቱ ምርጫ ተወዳዳሪ እንደመሆኔ ገደብ የሌላቸውን ችግሮች ለመፍታት ምርጫ ቦርድ፣ ፖሊስና በርካታ መንግስታዊ ተቋማት፤ የኢህአዴግ ካድሬዎችን ጨምሮ በርካታ ስራ ተሰርቷል፡፡ ኢህአዴግ ከፈለገ ምርጫን እንከን የለሽ ለማድረግ አቅም እንዳለው በተግባር አስመስክሯል፡፡ 2002 ላይ ደግሞ ይህ ድርጊት የተገላቢጦሽ ሆኖ ምርጫን ባለእንከን ለማድረግ አቅምና ችሎታው እንደነበረው አስመስክሯል፡፡

ምርጫን በሚመለከት ኢህአዴግ በሰፊ ልዩነትና በአስተማማኝ ሁኔታ የተሸነፈው በከተሞች ላይ ነው፡፡ ይህም ሆኖ አቶ በረከት አርሶ አደሩን በሚመለከት  በርካታ ቦታ ላይ የኢህአደግ አቆለጳጳሽ ሊያደርጉት እንደሞከሩት በተግባር ሆኖ እንዳልተገኘ የቅንጅትና የሕብረት ድምር ውጤት መስካሪ ነው፡፡ በቁጥር ደረጃ ኢህአዴግ በርካታ ወንበር ያጣው ከከተማው ይልቅ በአርሶ አደሩ ዘንድ ነው፡፡ እልህ ምላጭ ያስውጣል እንዲሉ ኢህአዴግ የከተማውን ውጤት ሳያንገራግር ለመቀበል የተገደደውና በገጠሩ ማጭበርበር ተካሄዶብኛል ብሉ የዘመተውም ባመነውና ባቆለጳጳሰው አርሶ አደር በመቀጣቱ ሲሆን በተለይ ደግሞ የከተማው ነዋሪ ከምርጫ ጀምሮ እስከ ውጤት ገለጻ ድረስ መብቱን ለማስከበር የሄደበት መንገድ ለኢህአዴግ ፍላጎትና ላቀደው ዓላማ የማይቆረጠም ስለሆነበት ነበረ ፡፡

ምርጫ 97 አርሷአደሩ ለኢህአዴግ ያስተማረው ነገር ቢኖር በትጥቅ ትግል ጊዜ ወዳጅ መሆን ብቻ ዝንተ ዓለም ለመመረጥ የሚያስችል መሳርያ አለመሆኑን ጭምር ነበር፡፡ አርሶ አደሩ ጉዳዩ ያለው ከጥቅሙ ጋር በተሳሰረ እንጂ ደርግን በመጣል ሂደት በፍላጎቱም ቢሆን የኢህአዴግ መሳርያ አንጋችና ቀላቢ ከመሆኑ ጋር የተሳሰረ እንዳልነበረ፣ በገጠሩ “ተቃዋሚ ስር የለውም” የሚለውን የኢህአዴግ ትምክህት በምርጫ በመስበር አረጋግጧል፡፡

አቶ በረከት በሁለት ምርጫዎች ወግ እዚህም እዚያም ነካ ነካ ቢያደርጉትም በተሟላ መልክ ሊደፍሩት ያልፈለጉት አጀንዳ በገጠሩ በምርጫ የተሸነፉበትን ነጥብ ነው፡፡ ከገጽ 71 እስከ 72 መመልከት ይቻላል፡፡

 

ነጭ ካፒታሊዝም ነጻ ገበያ ስርዓትና ባለሃብት

“… የገበያ ስርዓት በራሱ መላውን የሰው ልጅ ከጉልበት ምዝበራ ተላቆ የሚኖርበትና ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል በተሟላ መልኩ የሚረጋገጥበት አይደለም፡፡” ገጽ 30

“…ኢትዮጵያ የገበያ ስርዓትን ከመሰረተች ወዲህ ምናልባትም በብዙ የአፍሪካ ሃገሮች ከሚሰራው ለየት ባለ ስፋትና ፍጥነት ሰፊ አገራዊ ባለሃብት መፍጠር ጀመረች፡፡” ገጽ 58

“…ብዙ ተባዙ እንደተባለ ባለሃብቱ እንደ አሸን ፈላ…” ገጽ 86

“…ራሱ ባለሃብቱም ቢሆን በብርሃን ፍጥነት ያገኘውን አዱኛ ቋሚና ዘላቂ አድርጎ መመልከት ባለመጀመሩ በልፋት ላገኝው ሃብት ከቶም ርህራሄ አያሳይም በቁጥሩ ቀላል የማይባለው ባለሃብትም እንደዋዛ ያገኝውን ብር ሲመዘው አምሽቶ ሲበትነው የሚያድር ነው፡፡…” ገጽ 86

አቶ በረከት ስለነጭ ካፒታሊዝም ያላቸውን አቋምና አስተያያት ለመረዳት ከተለያየ ገጽ የተለቀሙት ሃሳቦቻቸው አመላካች ናቸው፡፡

አቶ በረከት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመቻችነት ወደ ነጭ ካፒታሊዝም እንጓዛለን በሚል ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ አመራር ሆነው የገበያ ስርዓትን የገለጹበት ሶሻሊስታዊ ትንታኔ የተቃርኖዎች ሁሉ ተቃርኖ ነው፡፡በአንድ በኩል የገበያ ስርዓት ባለሃብትን እንደአሸን ያውም ባልተጠበቀ ሁኔታ አፈላ ብለው፣ በሌላ በኩል ነጻ ገበያ የሃብት ክፍፍል አያረጋግጥም ሲሉ እርሳቸው የቱ ጋ ቆመውና የሃብት ክፍፍልን በየትኛው ርዕዮተ ዓለም ሊያመጡት እንደሆነ ለመረዳት ያዳግታል፡፡

[መላው ሰው] … የሰው ልጅ ከጉልበት ምዝበራ ተላቆ የሚኖርበትና ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል በተሟላ መልኩ የሚረጋገጥበት ስርዓት አንድም ተምኔታዊ ወይም በርዕዮተ ዓለም ትንታኔ ደረጃ በኮሙኒዝም ነው፡፡

እርግጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ደረጃ የሚደነቅ ሪኮርድ አለው፡፡ በግብር በሚገኝ ሃገራዊ ሃብትን ተጠቅመው እራሱን ለማብቃትና ግብር ከፋይ ለመሆን አንዳችም ጥረት የማያደርገውን ሃይል፤ ጠዋት ከእንቅልፉ ቀስቅሰው ቁርስ አብልተው፣ ረፋድ ላይ ኮንዶምንየም እየሰጡ፣ ማምሻውን መሬትና ገንዘብ ለግሰው በገበያ ስርዓት የማይመራ ጥበቃ እያደረጉ ንቁና የስርዓቱ ታማኝ መደብ እየፈጠሩ ነው፡፡

በተቃራኒው ደግሞ እራሱን በአስቸጋሪ ሁኔታ በማብቃት ሰርቶ፤ ጥሮ ግሮ የሚኖረው የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛ፣ የህክምና ባለሙያ፣ መምህርና በአንጻራዊነት ቁጥሩ ጥቂትም ቢሆን ነጋዴው ማህበረሰብ ሕይወቱን ሊያሻሽልበት የሚችለውን ደሞዝና የንግድ ገቢ በከፍተኛ ግብር በመምታት ሕይወቱን የማይለወጥ አድርጎታል፡፡ በግብር ከፋይነቱና በሃገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ባለው አይነተኛ ሚና ምክንያት ቅድሚያ የመደራጀትና ቤት የማግኘት መብት ሊኖረው ሲገባው በተቃራኒው ካፈራው ሃብት አጠራቅሞ ወደ መካከለኛ ገቢ መደብ እራሱን እንዳይለውጥ ተደርጓል፡፡

ከፍተኛው ባለሃብትም በአንድ በኩል ከደርግ የንግድ ገደብና ሃብት የማፍራት ማነቆ ስላላቀቅንህ በኛ መኩራት ይገባሃል እየተባለ፣ መለስ ተብሎ ደግሞ ሃብቱን ያፈራበት መንገድ በተዛባ መንገድ ተተንተኖ እራሱን መቆጣጠር እንደማይችልና ኃብቱን የትም እንደሚረጭ አልባሌ ተደርቆ ይቀርባል፡፡ የመንግስት ተጠያቂነትም ተረስቶ በኩራት ሃብቱን በብርሃን ፍጥነት እንደተገኘና ምንጩ እንዳልታወቀ ይተነተናል፡፡

አቶ በረከት ከተሜውን ሲያማርሩ በማን ላይ እየተማረሩ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በጥቅሉ አብዛኛው የከተማ ነዋሪ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛና አነስተኛ ነጋዴው ከነቤተሰቡ ነው፡፡ ይህ ሃይል ደግሞ በተደጋጋሚ ኢህአዴግን በምርጫ ያንበረከከና ያንገዳገደ መደብ ነው፡፡

ይህ መደብ አነሰም በዛም ቋሚ ገቢ አለው፡፡ የራሱን እምነት ለመፍጠርም ሆነ ባመነበት ለመገኘትና የኢህአዴግን ፕሮፓጋንዳ ከእውነቱ ለመለየት አቅም አለው፡፡ በጥቅሉ በቀላሉ የሚቆረጠም አይደለም፡፡ ስለዚህ የኢህአዴግ ቁጣ የሚዘንበው በዚህ መደብ ላይ ነው፡፡  ከፍተኛውን ግብር ይሸከማል፡፡ ለመቀጣጫ የታቀደ በሚመስል ደረጃ በከተማ ውስጥ በማቆምና ባለማቆም መካከል ከሚንገዳገዱት ሆስፒታሎች ውጭ አንድም ሆስፒታል ተሰርቶ አይታወቅም፡፡ የትራንስፖርት ችግሩ ገደብ ያጣ መሆኑ በግልጽ እየታየ ትኩረት አይሰጠውም፡፡ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች አይከፈቱም፡፡ ከተሜውን የኑሮ ውድነት አንገላቶ ባናቱ ሊደፋው እያንደረደረው ቢሆንም ተጨባጭ መፍትሄ አይሰጠውም፡፡ ብቻ ጠዋትና ማታ ሁሉ ነገር ወደ ጦር ግንባር እንዲሉ እኩል ትኩረት ለዜጎች ሳይሆን ሁሉ ነገር ለአርሶ አደሩና ለአነስተኛና ጥቃቅን ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ በረከት ሌላው በአለፍ ገደም የወዮልህ መልዕክት የሚያስተላልፉለት መደብ ከፍተኛው ባለሃብት ነው፡፡

አቶ በረከት ከላይ በገጽ 68 ከፍተኛውን ባለሃብት ያስቀመጡበት መንገድ እንኳን ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ይቅርና ንፋስ ላመጣብህ አዱኛ የምትታመን አይደለህም፤ ስለዚህም ለአሰራር አይመችም እንጂ ቢቻል ሃብትህን ኢህአዴግ እንዲያስተዳድርልህ ማድረግ በተገባ ነበር የሚሉ ይመስላል፡፡

አቶ በረከት ባለሃብቱ ሃብት እንዲያፈራ ያበቃነው እኛ እያለን ድምጽ ለመግዛት በየሆቴሉና በየስብሰባ መገኘቱን ሲተቹ [ባለሃብቱ በምርጫ 97 መሆኑ ነው፡፡]… ወንበር ለማግኘት የሚወዳደሩ ፓርቲዎች በጠሩት ስብሰባ ላይ መገኘት ጀምሯል፡፡” አልፎ ተርፎም “ … ባለሃብቱ በምርጫው ላይ የተራቀቀ ፍላጎት ማሳደር ከጀመረ ወዲህ በገንዘቡ ድምጽን እገዛለሁ ብሎ ማሰብ ጀምሯል፡፡” በማለት ገጽ 86 ላይ ስጋታቸውን በጥርጣሬ ይገልጹታል፡፡ በተለይ ይህንኑ ስጋታቸውን ሲያጠናክሩም  [ባለሃብቱ ] “… ለኢህአዴግ በግራ እጁ ከሰጠ ቀኝ እጁ ለቅንጅት ይሰጣል፡፡ ተቃዋሚ ካሸነፈ የባንክ እዳ ይሰረዝልኝ ይሆናል ብሎ ያስባል፡፡” በማለት በዚሁ ገጽ ላይ  ይገልጹታል ፡፡

ባለሃብቱ ተቃዋሚን የረዳበት ምክንያት እንደ አቶ በረከት አባባል ከሆነ፤ ኢህአዴግ ቢያሸንፍ ምንም እንደማያገኝ ስለሚያውቅና ተቃዋሚ ቢያሸንፍ ግን እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ባይገልጹትም ቢያንስ የባንክ እዳ እንደሚሰረዝለት ግምት ይዞ እንደነበር ይገልጻሉ ፡፡ ይህ ሃሳባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አቶ በረከት መልስ ያልሰጡን ጉዳይ ግን “ቢያንስ እንኳን የባንክ እዳ ለማይሰርዝላቸው”  ኢህአዴግን ለምን ገንዘብ ይረዱ እንደነበረ ነው?

አቶ በረከት በ1997 ምርጫ ባለሃብቱ ወንበር ለመግዛት ሲል ደፋ ቀና ሲል እንደነበረ የታወሳቸውን ያህል በ2002 ምርጫ ቀላል የማይባል ባለሃብት የኢህአዴግን የምርጫ ዘመቻ በባነር፣ በፖስተር፣ በቲ-ሸርትና በእጅ-ሰዓት ሲያደምቅ እንደነበረ የተዘነጋቸው ይመስላል፡፡

ባለሃብቱ ማህበረሰብ እንደማንኛውም ማህበረስብ ሁሉ የ1997 ምርጫ እንከን የለሽ ምርጫ እንደሚሆን በተገለጸለት መሰረት ለመደቡና ለጥቅሙ ከሚቆምለት ፓርቲ ጋር በፈራ ተባም ቢሆን  እንደተቀላቀለ ይታወቃል፡፡  ከስጋትም  የተላቀቀበት ሁኔታ ስላልነበረ  አንድ እጅ ለተቃዋሚ፣ አንድ እጅ ለኢህአዴግ ሲሰጥ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ በመጨረሻም ገፍተው በመሄድ ከመደባቸውና ከጥቅማቸው ጋር ብቻ የተሰለፉት ባለሃብቶች የማታ ማታ ዋጋ መክፈላቸው አይዘነጋም፡፡

የሁለት ምርጫዎች ወግ ኢህአዴግ ከጥገኛ መደብ ትንታኔ ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት ያደረገውን ሽግግርም አቶ በረከት በቅጡ ያስረዱናል የሚል እምነት የነበረኝ ሲሆን አንድም ቦታ ጥገኛ መደብን በኪራይ ሰብሳቢ ኢህአዴግ ለምን እንደተካው የኢህአዴግን ትንታኔ ሳላገኝ ቀርቻለሁ፡፡በእርግጥም ጥገኛ መደብ በሳይንሳዊ ትንታኔው የአዳጊ ካፒታሊዝም ጠንቅ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት በኢህአዴግ የማያባራ ዘመቻ ውስጥ ግን ትርጉም የለሽና የጠሉትን ሁሉ ማከማቻ የማይሞላ ከረጢት ነው፡፡ ኢህአዴግ ጥገኛ መደብን በኪራይ ሰብሳቢ ሲተካ የስም ሽግግሩ ለምን እንዳስፈለገና ትርጉሙ ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡

ጥገኛ መደብ ለመሆን የሚጠጉት ያስፈልጋል፡፡ የሚጠጉት ደግሞ ባለስልጣን ካልሆነ ጥገኝነቱ የመደብ ጉዳይ ሳይሆን ማህበራዊ መጠጋጋት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጥገኛ መደብ ያለባለስልጣን ድጋፍ ትርጉም የለሽ ነው፡፡ አሊያም አንድ ጣትን በጥገኛ መደብ ላይ ሲቀስሩ   ሶስቱ ወደ ባለስልጣናት ይጠቁማል እንዲሉ አጣብቂኝ ስለሆነ ነው፡፡ የጥገኛ መደብ ክስ  በራሱ ጥገኛ ይሻል፡፡ ስለዚህ የጥገኛ መደብ ጉዳይ  የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ተብሉ መታለፉ የግድ ነበር፡፡

በማጠቃለያነት ለማለት የምፈልገው ነገር ጥቂት ነው፡፡ የአቶ በረከት መጽሐፍ በማንኛውም መገለጫው ከፍተኛና ንቁ የሕዝብ ተሳትፎ በታየበት በ1997 ምርጫ ላይ ባነሷቸው ጉዳዮች እጅግ አወያይና አከራካሪ ከመሆናቸው የተነሳ በመጽሐፋቸው ላይ የተሟላ መልስ ለመስጠት የሚቻለው በመጽሐፍ መልክ ብቻ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ታሳቢ የሆነው መጸሐፍ ከመፅፍ በመለስ መልስ ለመስጠት ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ አቶ በረከት በምርጫው ላይ ከነበራቸው ዓይነተኛ ተሳትፎ አኳያ፣ በበቂ ሰነድና መረጃ ላይ የተደገፈ ተጨማሪ ማብራሪያና ትንታኔ ከመስጠት አኳያ ልዩነቶች ጠርተውና ጎልተው በመፅሐፋቸው አልወጡምና ይህ መጽሐፍ በቂ አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ብዙ ሊያብራሩልን የሚገቡ ጉዳዮች አሁንም በእንጥልጥል ላይ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ አቶ በረከትና የሁለት ምርጫዎች ወግ ለውይይት እድል ፈጥረዋልና ምስጋናዬን ሳላስቀምጥ ባልፍ ሃሳቤን ጎዶሎ ስለሚደርገብኝ ምስጋናዬ ይድረስዎት፡፡

 

 

Read 15316 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 11:44