Saturday, 21 January 2012 10:05

“ሎጐ”

Written by  ሌሊሣ ግ.
Rate this item
(0 votes)

“ሎጐ” የሚለው ቃል ከግሪክ ቋንቋ የተወሰደ ነው፡፡ ከግሪክ ቋንቋ የተወሰደ መሆኑን የተወሰድኩት “Man kinds Search for meaning” ከተባለ መፅሐፍ ነው፡፡ መፅሐፉን የፃፈው ሰው ደግሞ በአሁኑ ወቅት በሞት ተወስዷል፡፡ መፅሐፉ ውስጥ ያለው ቁም ነገር መፅሐፉን ለፃፈው ሰውዬ ከእንግዲህ አይጠቅመውም፡፡ የመፅሐፉ እውነትነት፤ እውነታ ላይ አሁን እና ወደፊት ላሉት ብቻ ነው፤ ለሌሉት አያገለግልም፡፡ “ሎጐ” የግሪክ ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም፡- “ትርጉም” ማለት ነው፡፡ meaning … የህይወትን ትርጉም የሚመረምር መፅሐፍ ነው፡፡

የመፅሐፉ ደራሲ በጀርመን ናዚ ካንፕ ውስጥ ከመሰል አይሁዳዊያን ጋር ታጉሮ ከፍተኛ ስቃይ እና አሳር አይቷል ወይንም በልቷል፡፡ የበላውን አሳር በመፅሐፍ ላይ ዘርዝሮ ተርኮታል፡፡ እንደ አጋጣሚ በህይወት ተረፈ፡፡ ዶ/ር ኤፍ ፍራንክል፡፡ በሞያው የስነልቦና ሀኪም ስለነበር … ስቃዩን በአዲስ የስነ ልቦና እይታ ገልፆ አቀረበው፡፡ የስነ ልቦና ቀውስ ያለባቸው ሰዎችን በትርጉም ህክምና (Logo therapy) ማከም ያዘ፡፡

 

መፅሐፉ በእንግሊዘኛ የተፃፈ ስለሆነ ወደ አማርኛ ማስተርጐም አስፈላጊ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ተፅፎ ያነበብኩት መፅሐፍም ከጀርመንኛ የተተረጐመ ሊሆን ይችላል፤ አላውቅም፡፡ … መፅሐፉን ለናንተ ለመተርጐም አልፈልግም፡፡ ዋናው ነገር ለኔ የሰጠኝ ትርጉም ነውና፡፡

ዶ/ር ፍራንክል በናዚ ጅምላ ጭፍጨፋ ካንፕ ውስጥ በህይወት ለመትረፍ የቻለበትን ምክንያት ሲገልፀው “ለሰው ልጆች የማበረክተው እውቀት ስለበረኝ ነው” ይላል፡፡ እውቀቱ በኤግዚዝቴንሻሊዝም ፍሳሽ ቦይ ውስጥ የሚነጉድ ቢሆንም በመጠኑ ግን ይለያል፡፡ ሁሉም የኤግዚዚቴንሻሊስ ፍልስፍና ከሁለተኛው አለም ጦርነት እና እሱን ተከትሎ ጥያቄ ወይንም ግራ መጋባት የመነጨ ነው፡፡

ዣንፖል ሳርተር እና ሴት ገርፍልፍሬንዱ (ሲሞን ደ ቦሹዋ) የሚያራምዱት የኤግዚስቴንሻሊዝም ከዶክተር ፍራንክል ይለያል፡፡ ዣንፖል ሳርተር መጀመሪያ የሚቀድመው በህይወት መገኘቱ ነው ይላል፡፡ በህይወት ሳይገኙ ለህይወት ወይንም ህልውና ትርጉምን ማግኘት አይቻልም ባይ ነው፡፡ ዶክተር ፍራንክል በተቃራኒው የሚቀድመው ትርጉሙ ነው ይላል፡፡ “ሎጐ” ከ “ኤግዚዝተንስ” ይቀድማል እንደ ማለት፡፡ ህይወት ትርጉም ከሌለው ህልውና ትርጉም ያጣል፡፡ በስቃይ ወይንም በስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ይወድቃል፡፡ … የደስታ እጦት፣ የእርካታ እጦት፣ የጤና እጦት ከትርጉም እጦት የሚመነጩ ናቸው ባይ ነው፡፡ … የዶክተሩን መፅሐፍ ከማንበቤ በፊት ይሄንን ነገር አውቀዋለሁ ብዬ አሰብኩ፡፡ ምክንያቱም ባላውቀው በህይወት አልኖርም ነበር፡፡ … የሆኖ የትርጉም ምህዋር ላይ ተንጠልጥዬ ቢሆን ነው በህይወት መቆየቱ የቻልኩ፡፡

ትርጉሙ ከጠፋ በመፅሐፍም አለም ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ የሼክስፒር ትራጀዲዎች በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው የተፃፉት፡፡ ቃላቶቹ መፅሐፉ ላይ እስካሉ ድረስ ህልውና አላቸው፡፡ ግን ቃላቶቹን ከመፅሐፉ አንብቦ መረዳት ወይንም መተርጐም የሚችል አንድም ሰው ባይኖር ቃላቶቹም ከመፅሐፉ ጋር ሞተዋል፡፡ (ሰሞኑን “አሙትህ” የሚል ቃል ሲጠቀሙ የሰፈሬ ልጆች ሰማሁ፡፡ አንበሳ “አሙቶ” ነው  እንጂ የሞተ አይበላም … አይነት) …

ህይወት እስካለ ድረስ ትርጉም አለ፡፡ ህይወትን መሞት ሳይሆን … ህይወትን መኖር እስካለ ድረስ፡፡ ትርጉም ሁሌም አለ፡፡ ግን በሞተ ትርጉም ህያው ህልውናን መኖር አይቻልም፡፡ ትልቁ ችግር ያለው እዚህ ነጥብ ላይ ነው፡፡

ስለዚህም ዶ/ር ፍራንክልን በቀጥታ መተርጐም አልፈልግም፡፡ የዶክተር ፍራክል ትርጉም ለራሱ ህልውና ህያውነት ጠቅሞት ሊሆን ይችላል፡፡ በእሱ ትርጉም ግን የእኔ ህልውና ነብስ ባይዘራስ? … በዶ/ር ፍራንክል መነፅር ውስጥ የራሴን ትርጉም አድኜ መያዝ (“አሙቼ ” መብላት) መቻል የግድ ይኖርብኛል፡፡

በድሮ ትርጉም የዛሬን ህይወት ለመኖር መሞከር አልመጣጣምን ይፈጥራል፡፡ በእምነት እውነታን ለመኖር እንደመሞከር፡፡ እምነት ሁሉ በድሮ ጊዜ ላይ ህያው የነበሩ ትርጉሞች ስብስብ/ክምችት ነው፡፡

“የትላንት ቃላት ለትላንት ታሪክ ለዛሬው ትርጉም አዲስ ቋንቋ” “ለምን ራስህን አታጠፋም?” ብሎ ይጠይቃቸዋል ዶ/ር ፍራንክል በሽተኞቹን ለህልውናቸው ምክንንያትነት የሚሰጡት አንድ ትርጉም እንዳላቸው ለማሳየት በሚያደርገው ሙከራ፡፡ አንዳንዳትን ምክንያቱን በደንብ ሳናተኩርበት ችላ ስላልነው እንጂ በፅሞና ስናስበው የህልውናችን ምክንያት ቁልጭ ብሎ ይታየናል፡፡

ሮሚዮ የሚኖርበት ምክንያት ጂሊየት ነበረች፡፡ ጁሊየትም ምክንያቷ ሮሚዮ፡፡ ለሁለቱም የህልውናቸው ምክንያት … የህልውናቸው ትርጉምም ነበር፡፡ ጁሊየት ከሌለች/ከሞተች ሮሚዮ የሚኖርበት ምክንያት የለውም፡፡ ህልውናውም ትርጉም አይኖረውም፡፡ በሞተ ምክንያት መኖር አይቻልም፤ ለሮሚዮ፡፡ … ደግነቱ ሁለቱም የፈጠራ ገፀ ባህሪዎች ናቸው፡፡

በገሐዱ አለም ላይ ጁሊየት ስትሞት ሮሚዮ በጣም ይሰቃያል … አልካል ጠጪ ይሆናል፤ ራሱንይጥላል፡፡ ከብዙ ቆይታ በኋላ ይሻለዋል … ሌላ ሚስት ያገባል፡፡ የሮሚዮ እና የጂሊየት የህልውና ትርጉም (በሰው ልጆችም ላይ) በእውነታው ላይ ይኖራል፡፡ ግን ትርጉሙ ሲጠፋ ህልውናው አብሮት አይጠፋም፡፡ በጠፋው የድሮ የህልውና ትርጉም ፋንታ ሌላ የህልወና ትርጉም ይወለዳል፤ ይተካል፡፡

… ያለ ትርጉም ህልውና የለም፡፡ ትርጉም እና ህልውና ልዩ የሚያደርጋቸው ግን … ህልውና በግለሰቡ ላይ ከሞተ ተመልሶ ነብስ አይዘራም፡፡ ትርጉም ግን ከሞተ በሌላ ትርጉም ይተካል፡፡ ማንም ሰው የራሱን ትርጉም መፍጠር እና በፈጠረው ትርጉም ህያው ሆኖ መኖር ይችላል፡፡ ተስፋ ራሱ አንድ የህይወት ትርጉም ነው፡፡

ትክክለኛውን ትርጉም በራሱ ህልውና ላይ ዛሬ እና አሁን የጨበጠ ሰው በህይወት ይኖራል፡፡ የተሳሳተ ትርጉም የያዘ ሰው ደግም ተቃራኒውን፡፡ በህልውና ላይ እየኖሩ መኖርም እየኖሩ መሞትም ይቻላል፡፡

… ለምሳሌ፡- ህይወቱ እስከሚጀምር እድሜ ልኩን የሚጠብቅ ሰው አይታችሁ አታውቁም? (… እንዴታ! እናንተው ራሳችሁ ናችሁ!) … ህይወቱ የሚጀምረው የዶክትሬት ዲግሪውን ሲያገኝ እንደሆነ የሚያስብ፤ ህይወቱ የሚጀምረው ዲቪ ሲደርሰው የሚመስለው፣ ህልውና ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ትርጉሙም ያለው ዛሬ ላይ ነው፡፡ ትዝታና ተስፋ ላይ የተቀመጠ ትርጉም፣ ህይወትን እስኪጀምር የሚጠብቁ እና በህይወት ላይ እያሉ የሞተ ትርጉምን የሚያነቡ “ዞምቢዎችን” ይፈጥራል፡፡

ጥያቄው፡- መኖር ወይንም አለመኖር ሳይሆን to realy be or to be with out being real. ጥያቄው ይህ ነው፡፡

የጥበቃ ህይወት፤ ህይወት አይደለም፡፡ የኤግዚስቴንሻሊስት ቦይ አንድ ሆኖ የእያንዳንዱ ገባር የግለሰብ ምንጭ አፈሳሰሱ ይለያያል፡፡ ከዣንፖል ሳርተርን እና ዶ/ር ፍራንክል ኤግዚስቴንሻሊዝም የቢኬት (waiting for //////) ይለያል፡፡ ሳሙኤል ቢኬት ገፀባህሪዎች ቭላድሚርእና ኤስትራጐን … ስለ ህልውናቸው የሚሰጡት ትርጉም የለም፡፡ ከመጠበቅ ውጭ፡፡ የህልውናቸው ትርጉም ጥበቃ ቢመጣም አያውቁትም፤ የሚጠብቁት ምን አይነት ነገርን እንደሆነ ለእነሱም ግልፅ ስላይደለ …፡፡ ሁለቱም ጠባቂዎች የስቃይ ሰለባዎች ናቸው፡፡ አንደኛው ጫማው ይጠነባል፡፡ ሌላኛው አፉ ይሸታል፡፡ ትርጉም የሌለው ጥያቄ እየደገሙ ይጠያየቃሉ፡፡ ትርጉም ያለው መልስ “ጐዶ” ይዛልን ይመጣልናል ብለው ይጠብቃሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ እንዳለው የከተማ ነዋሪ ጥበቃ፡፡ መልስ ትርጉም ነው፡፡ መልስ አግኝተው ህይወታቸው እንዲጀምር (በህይወት ሞተው) ይጠብቃሉ፡፡ “ቀን” ነው የሚጠብቁት “ጐዶ” ለዘንድር ህዝብ “ቀን” ነው፡፡ የሚጠበቅ ቀን፡፡ … ቀን ከሆነ ቦታ ወርዶ የጐደለውን ሁሉ እንዲሞላለት፡፡ “ቀን” ደግሞ፤ የከተማ ነዋሪ የሆነ አብዮት ፈጥሮ ካልነበረበት ወደ ታሪካዊ ሁለት እንዲለውጠው ይጠብቃል፡፡ … ቭላድሚር እና ኤስትራጐን “ጐዶን” እንደሚጠብቁት፤ ጐዶ ደግም ምናልባት ቭላድሚር እና  ኤስትራጐን ወደሱ እንዲመጡ የሆነ ግልፅ ቦታ ላይ ተደብቆ እየጠበቃቸው ሊሆን ይችላል፡፡ “ጐዶ” የሚለውን ስም ደራሲው ቢኬት የተጠቀመው “God” ለማለት ፈልጐ ነው ይላሉ፡፡ ጥበቃ እና ትዝታ ላይ ያለ ትርጉም፤ ህልውናን እንዳይሞት አድርጐ ያደነዝዘዋል፡፡ …

ትዝታ፤ የሞተ ነገርን እንደመብላት … ጥበቃ ደግሞ፤ ያልተጣለ እንቁላልን ለፋሲካ አውራ ዶሮ እስኪሆን ጠብቆ ለማረድ እንደመወጠን …፡፡ ትርጉም የምትወልደዋ ዶሮ  ጭር እንዳለች ልትቀር ትችላለች፡፡ ጊዜአዊ ትርጉምን ፈጥሮ … ጠብሶ መብላት ሳይሻል አይቀርም፡፡

… ግን እዚህ ላይ ከዶ/ር ፍራንክል ጋር የግዴታ የምስማማበት ነጥብ አለ፡፡

… ከማንም ፋብሪካ በተሰራ (ሬዲ ሜድ) ትርጉም፤ ሌላ ህያውን አልብሶ ተሰፋለትን የህይወት ትርጉም እንዲወደው አሊያም እንዲስማማው ማድረግ አይቻልም፡፡ … ትልቅ ትርጉም ለሰው ልጆች ያበረክት፣ የትኛውም የጀግና ሀውልት ጥላውን እንጂ እውነትን በሰው ልጆች ላይ አይጥልም፡፡ ጥላ ደግሞ ከፀሀይ እንቅስቃሴ ጋር የሚያጥር ወይንም ከዋናው ነገር በላይ የሚረዝም አሳሳች ነገር ነው፡፡ ጥንታዊያኑ ስለ ሀገራቸው ያላቸው ትርጉም በሀውልቶቻቸው ላይ ተንፀባርቋል፡፡ የሀውልቶቹ  ጥላ ደግሞ በአሁንና ዛሬው እኛነታችን ላይ ከመጠን በላይ አጥሮ ወይንም ረዝሞ ይጋደማል፡፡ ትርጉማቸው ትርጉማችን አይደለም፡፡ አጥሮ ለማስረዘም አሊያም ረዝም ለማሳጠር የምንሞክረው ትርጉም፤ በእኛ ልክ የተሰፋ አይደለም፡፡ … በእኛ ልክ ተሰርቶ ቢመጣም በእኔ ልክ አሁንም ላይሆን ይችላል? ….

…. የህይወት ትርጉም የግል ነው … አየር የጋራ፡፡

 

 

Read 3977 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 10:11