Monday, 16 March 2015 10:19

WATCH.... የሴቶችና ጨቅላ ሕጻናቶች ጤንነት...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

WATCH ምህጻረ ቃል ሲሆን በእንግሊዝኛው (women and their children health)  የእናቶችና የልጆቻቸው ጤንነት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በካናዳ መንግስት ድጋፍ የሚደረግለት ነው፡፡ ፕላን ካናዳ እና የካናዳ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር በመሆን ገንዘቡን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በጋራ ፕሮጀክቱን ሲተገብሩ ቆይተዋል፡፡ አቶ ቢንያም ጌታቸው በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የWATCH ፕሮጀክት ኮኦርዲኔተር ናቸው፡፡ የፕሮጀክቱን ማብቂያ መቃረብ ምክንያት በማድረግ ስለፕሮጀክቱ ላነሳንላቸው ጥያቄዎች የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡
ጥ/     WATCH በኢትዮጵያ ውስጥ ስራ የጀመረው መቼ ነው?
መ/    የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ስራውን መተግበር የጀመረው     እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013/ጃንዋሪ ላይ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በ2015 ማርች ላይ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ውስጥ በሶስት ክልሎች ማለትም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል በሲዳማ ዞን ሠበዲኖ፣ ጎርቼ እና ቦና ዙሪያ የሚባሉ ወረዳዎች ላይ በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳ እና ጢሮ አፈታ     ወረዳዎች ላይ እና በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በመቂት፣ ላስታ እና ቡግና ወረዳ     ላይ ነው፡፡
ጥ/ በዋናነት ስራው ምን ላይ ያተኮረ ነው?
መ/    ስራው በዋናነት የእናቶችን እና የሕጻናትን ጤና መንከባከብ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ እርጉዝ እናቶች በእርግዝና፣ በወሊድ እና ከወሊድ በሁዋላ የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት የጤና ባለሙያዎች ሕክምናውን እንዴት መተግበር እንዳለባቸው ስልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን ድጋፋዊ ክትትልም ይደረጋል፡፡ በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮያ በኩል ደግሞ አስፈላጊው የህክምና መርጃ መሳሪያ ይሰጣል፡፡ በመጀመሪ የተደረገው በተጠቀሱት የስራ ቦታዎች ላይ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የዳሰሳ ጥናት ተካሂዶአል፡፡     ጥናቱም ያተኮረው ምን በመስራት ላይ ነው? ምን የጎደለ ነገር አለ? በምን መልክ ክፍተቱ ሊሞላ ይችላል? የሚለውን ማወቅ ሲሆን ከዚያ በሁዋላ በጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህር በኩል ምን ሊደረግ ይችላል? ፕላን ኢንተርናሽናልስ ምን ሊያሟላ ይችላል? መንግስትስ የትኛውን ክፍተት ሊሞላ ይችላል የሚለውን በዳሰሳ ጥናት ተለይቶአል፡፡ በዳሰሳው ጥናት መሰረትም Basic emergency obstetric and new born health care ወይም መሰረታዊ የሆነ የድንገተኛ፣ የወሊድና የጨቅላ ሕጻናቶች ጤና እንክብካቤ ስልጠናዎችን ለጤና ባለሙያዎች በመስጠት ነበር የተጀመረው፡
ጥ/     ስልጠናው ለምን ያህል የጤና ባለሙያዎች ተሰጠ?
መ/    በአጠቃላይ በሁሉም ወረዳዎች ወደ 48 ጤና ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን በነዚህ የጤና ጣቢያዎች ውስጥ የሚሰሩ ወደ 167/የሚሆኑ ባለሙያዎች ስልጠናውን እንዲያገኙ ሆኖአል፡፡ የሰለጠኑት የጤና ባለሙያዎች ከየጤና ጣቢያው እየተውጣጡ ሲሆን በየጤና ጣቢያውም ሶስት እና ከሶስት በላይ የሚሆኑ እድሉን አግኝተዋል፡፡ ስልጠናውም የሶስት ሳምንት ጊዜ የሚወስድ ሲሆን የመጀመሪያው ሳምንት በቲዎሪ የተደገፈ ሲሆን እንዲሁም ቀሪውን ጊዜ በሆስፒታሎች ላይ ተመድበው የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ተደርጎአል፡፡
በጅማ ዞን በጢሮ አፈታ ወረዳ ዲምቱ ጤና ጣብያ ጎራ ብለን አንዲት ወላድ አነጋግረናል፡፡ ወላድዋን ስናገኛት በጣም ጤነኛ እና ጠንካራ ነበረች፡፡ እኛ ባገኘናት ወቅት ገና ከወለደች ሰላሳ ደቂቃ የሆናት ብትሆንም እሱዋ ግን ምንም ምጥ ያማጠች አትመስልም ነበር፡፡  
“...ጠዋት ነው የወለድኩት ደህና ነኝ ጥሩ ነው ያለሁት፡፡ ከመውለዴ በፊት እዚሁ አራቴ የእርግዝና ክትትል እድርጌያለሁ፡፡ አሁንም ደህናነኝ፡፡ ...አሁን ሰባተኛ ልጄን ነው የወለድኩት፡፡ እድሜዬ አሁን ሰላሳ ሰባት አመት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ መውለድ አቆማለሁ ብዬ አስባለሁ ግን ከባለቤቴ ጋር ተነጋግረን ነው የምንወስነው...” አለች፡፡
በአካባቢው ባለው የጤና አሰራር መሰረት አንድ ለአምስት የሚባል አደረጃጀት አለ፡፡ የጤና ኤክስቴንሽኖችም አሉ፡፡ የቤተሰብ እቅድ ዘዴን በሚመለከት ይመካከራሉ፡፡ በእርግጥም  የቤተሰብ እቅድ ላይ ለመወሰን የባልየውም ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ባለቤትዋም በዚያው ባጠገብዋ ስለነበር ሀሳቡን ጠየቅነው፡፡   
“...ያው እንግዲህ ሁሉም በእግዚአብሄር ነው የሚሆነው ግን መውለድ እናቆማለን ብለን እያሰብንን ነው፡፡ ቀደም ሲል የተወለዱት ልጆች እድሜያቸው ከአስራ አራት እስከ አስራ ዘጠኝ     አመት ድረስ ነው፡፡ ሁሉም ቀበሌ ቀጄሎ ትምህርት ቤት እየተማሩ ነው፡፡ ትልቁ የአስራ ዘጠኝ     አመቱ ልጅ አሁን ሰባተኛ ክፍል ደርሶአል፡፡ አንዱ ልጅም አምስተኛ ሌላው ደግሞ     አራተኛ ክፍል ደርሶአል፡፡ እኔ በኑሮዬ ገበሬ ስለሆንኩ ልጆቼም ከትምህርት ሲመለሱ ያው ስራ ያግዙኛል፡፡ እስከአሁን ድረስ ባለው ሁኔታ ንብረትም በበቂ ስላለኝ በምን አሳድጋቸዋለሁ... እንዴት እኖራለሁ ብዬ ሰግቼ አላውቅም፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉንም አሳድጋለሁ፡፡ ምናልባትም በትምህርት የሚነግሩን ነገር አለ፡፡ እሱም ምንድነው ...ሴቶች ብዙ በመውለድ ሊታመሙ ይችላሉ... የሚል ነገር ስለአለ ...ምናልባት በዚህ ምክንያት ባለቤቴ እንዳትጎዳ እያሰብኩ ነው፡፡ ስለዚህም     የወሊድ መቆጣጠሪያ እሱዋ ወይንም እኔ እንድንወስድ ወደፊት አቅጃለሁ፡፡”
ከወላድዋ እና ባለቤትዋ በሁዋላ ያነጋገርናት የህክምና ባለሙያ ሲስተር ባንቻየሁ ትባላለች፡፡ ዲምቱ ከጅማ ወደ 68/ኪሎ ሜትር እንደምትርቅ የነገረችን ሲስተር ባንቻየሁ ጤና ጣብያው በወር ከሀምሳ እስከ ስድሳ ወላዶችን እንደሚያስተናግድ እና ወላዶች ምናልባት ችግር ቢያጋጥማቸው ሪፈራል ሆስፒታሉም ጅማ ሆስፒታል መሆኑን ገልጻልናለች፡፡ ሲ/ር ሌሎች ጥያቄዎችን እንደሚከተለው ነበር ያብራራችው፡፡    
ጥ፡-  በእናቶች ጤና ዙሪያ ይሄ ቢስተካከል የምትይው ችግር አለ?
መ፡-     እናቶች አንዳንዴ በገንዘብ ላይ እራሳቸውን ቢያዘጋጁ፡፡ እሪፈር ስንልካቸው አንዳንዴ አንሄድም ገንዘብ የለንም የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ ላይ እራሳቸውን ቢያዘጋጁ ወይም እሪፈር የምናደርግበት አጋጣሚ ሲኖር ከእራሳችን ከጤና ጣብያው ሰጥተን እሪፈር የምናደርግበት ነገር ቢኖር ብዬ አስባለሁ፡፡
ጥ፡- እሪፈራል ላይ ገንዘቡ ለምንድነው የሚያስፈልገው?
መ፡- በአቡላንስ ነው የምንልካቸው፡፡ እዚህ የሚያገኙት አገልግሎት በሙሉ ነፃ ነው፡፡ ግን ሆስፒታል ሲሄዱ ሆስፒታል ላይ ከግላቭ ጀምሮ እስከ መድሀኒት ለሚገለገሉባቸው ነገሮች ገንዘብ ስለሚያስፈልግ ለዛ ነው ገንዘብ የሚጠየቀው፡፡
ጥ፡- ስለዚህ አንሄድም ገንዘብ የለንም ሲሉ ምን ይደረጋል?
መ፡- አንሄድም ያሉ አንድ አምስት እናቶችን በዚህ ስድስት ወር ሰባት ወር ውስጥ ከራሳችን ገንዘብ ሰጥተን እሪፈር ያደረግናቸው አሉ፡፡ ያው ከውስጥ ገቢ ገንዘብ ላይ ተወስዶ እሪፈር ይደረጋል እንጂ አይቀርም፡፡ መሄድ ያለባቸው እናቶች መሄድ አለባቸው ብለን ከወሰንን ከእራሳችንም ቢሆን ሰጥተን ነው እሪፈር የምናደርጋቸው፡፡
ጥ፡- የአብዛኞቹ ባለቤቶች ገበሬዎች ናቸውና እሪፈር በሚላኩበት ሰአት አብረዋቸው ይገኛሉ?
መ፡- ብዙዎቹ አስቀድሞውኑ መውለጃቸው ሲቃረብ በጤና ጣብያው ተኝተው ያሉ እናቶች ናቸው፡፡ ከስምንት ወር ከአስራ አምስት ቀን የሆናቸው እናቶች እዚህ መጥተው ይተኛሉ እና አጋጣሚ ለሊትም ሆነ ቀን ባለቤታቸው ወይም ቤተሰብ በሌለበት ሰአት አንዳንዴ እሪፈር ያጋጥማል፡፡ ያው ባለቤቶቻቸው ደግሞ ከእሩቅ ቀበሌ ቢያንስ አንድ ሀያ ኪሎ ሜትር ያህል እርቀት ላይ ነው የሚገኙት... እና እነሱ ላይደርሱ ይችላሉ፡፡ አጋጣሚ የደም በጣም መፍሰስ ወይም ምጥ ላይ በሚሆኑበት ሰአት እሪፈር መደረግ ሲኖርባቸው አንዳንዴ ችግር ይገጥመናል፡፡
ጥ፡- እስከሚወልዱ ድረስ እዚህ ሲኖሩ ቀለባቸውና ሌሎች ነገሮች እንዴት ነው የሚሟሉት?
መ፡- እስከሚወልዱ ድረስ አንድ እናት ቢያንስ በቀን ሶስቴ ትመገባለች፡፡ ቁርስ ምሳና እራት ይመገባሉ ቡናም አላቸው፡፡ የእነሱን ምግብ የሚሰራላቸው ሰው አለ፡፡ ሌላው ፅዳት ነው ሳሙና ይሰጣቸዋል ፅዳታቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ምግባቸውን በትክክል ያገኛሉ ምግባቸው አይቋረጥም ችግር ካለም መጥተው ባለሙያ ያናግራሉ፡፡ መታየት ካለባቸው መጥተው ይታያሉ እና ሁሉም እንደፈለጉት ነው፡፡
ጥ፡- በጀቱ ከየት ነው የሚመደበው?
መ፡- በጀቱ አንድ ብር ለአንድ እናት በሚል ከህብረተሰቡ የሚዋጣ ብር አለ፡፡ ያ ገንዘብ እንዴት መውጣት እንዳለበት በኮሚቴ ተነጋግረን የሌለ ነገር ማለትም... ሽንኩርቱም በርበሬውም... ሁሉም እስከ ጤፍ ድረስ መገዛት ያለበት ነገር ይገዛል፡፡ ከእነሱ ጋር የሚሰበሰብ እህል ካለ  እሱንም ገቢ አድርገን አንድ ላይ ነው የምንጠቀመው፡፡
ጥ፡- ህብረተሰቡ የሚያዋጣው በፈቃደኝነት ነው ወይስ ግዴታም አለው?
መ፡- ግዴታ የለውም ፍቃደኝነት እንጂ፡፡ ሁሉም ሰው በፍላጎት አምኖበት መሆን ስለአለበት እኔም በበኩሌ በየቀበሌው እየዞርኩኝ ኮንፈረንስ ስናካሂድ ትምህርት እሰጣለሁ፡፡ ስለዚህ እያመነበት ነው ሁሉም ሰው የሚሰጠው፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ቢያንስ በሳምንት ሁለቴ መጥተው እንዲጠይቁ እንነግራቸዋለን የምናስፈርመው ውልም አለ፡፡ ማለትም እዚህ አምጥተው ጥለዋት እንዳይሄዱ እናደርጋለን፡፡   -   ይቀጥላል   

Read 3093 times