Saturday, 21 January 2012 10:12

አዲስ አበባ - ላሊበላ - ባህር ዳር አዲስ አበባ የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(1 Vote)

የማስታወሻው ማስታወሻ

የደቡብ አፍሪካ ጉዞዬን ማስታወሻ ጽፌያለሁ፡ የፈረንሳይ ጉዞዬን ማስታወሻ ጽፌያለሁ፡፡ የጀርመን ጉዞዬንም እንደዚያው፡፡ የአሜሪካ ጉዞዬን በረዥሙ ዘግቤያለሁ - ለእኛ ሰው በአሜሪካ ስል፡፡ እግረ መንገዴን የቤልጂየም ጉዞዬን ዳስሻለሁ፡፡ የደቡብ ኮርያ ጉዞዬን ነጥቤያለሁ፡፡ የኢራን መንገዴንም ነቁጫለሁ፡፡ ሁሉም ውስጥ እኔ አለሁ፡ ኢትዮጵያዊ አለ፡፡ ኢትዮጵያ አለች፡፡ “መጓዝ ማወቅ ነው”፤ ነው መርሆዬ (Traveling is knowledge) ማወቅ ብቻውን ዋጋም የለው፡፡ ማሳወቅ መኖር/መከተል አለበት፡፡ ቀጣዩ መንገደኛ ዕውቀቱን ታጥቆ መጓዝ አለበት፡፡ የጉዞው ሰንሰለት ወደተሻለ ህይወት የሚያመራው በዚህ ተከታታይ ሂደት ነው፡፡ ሁላችንም እንጓዝ፡፡ የጉዞ አሻራችንን እናትም፡ እንንቀሳቀስ፡፡ አንድ ታዋቂ የፖለቲካ ሰው ስለአገራችን ሰው ሲናገር፤ “አበሻ የቆመበት ቦታ መቀበር ይችልበታል” ይላል፡፡ ይሄ ዕውነታ መቀየር አለበት፡፡ ከቆምንበት መላወስ፣ መንቀሳቀስ አለብን፡፡

የዛሬው ጉዞዬ የአገር ውስጥ ነበር፡፡ ስለዚሁ ጉዞዬ ላወሳ ነው፡፡ የሄድኩት ወደላሊበላ ነው፡፡ ለገና በዓል፡ በአውቶቡስ፡፡ ከብዙ የማላውቃቸው ሰዎች ጋር፡፡ ያየሁዋቸውን ነገሮች በእኔ ዐይን በኩል እነግራችኋለሁ፡፡ ተከታታይ ጽሑፍ ነው፡፡

ላሊበላ ሄጄ ከፃፍኳቸው ግጥሞች በአንዱ ልጀምር፡፡

ላሊበላ

አገር በመሮ ቆፍሮ

ከአለት ምሰሶ አዋቅሮ

ድንጋይ በድንጋይ ጠፍሮ

መንፈስ እንደ ብረት አጥሮ፤

ከቋጥኝ አነባበሮ

የታሪክን ፍልፍል ቋጥሮ፤

አገር ያቆየ ቅዱስ

አገር የመራ ንጉሥ

አገር ያጠነ መሀንዲሰ

ዕምነቱ እንዴት ይጠና፣ መንፈሱ እንዴት ይታደስ

ጥበቡ እንዴት ያስቀና፣ ህዝቡስ እንዴት ይፈወስ

ሲርቁት የሀገር ሞገስ፣

ሲቀርቡት የጽላት መቅደስ፣

ሲያልሙት የጥበባት ዋስ፣

ሲረሱት የህሊና ክስ፣

ሲጽፉት የዘመን አድማስ፣

ሲያከብሩት የመለኮት ጽንስ፡፡

ከዓለም ተዓምራት አደለም፣ ከዚያ ማዶ ነው ቁጥሩ

ካላፊ - ጠፊ አይፃፍም፣ ከሰማያት ነው ድምሩ፡፡

ልብ እንጂ ዓይን አይመጥነው

ውሃ - ልኩ ማተቡ ነው

ጡቡኮ የአለት ፊደል ነው

በዚህ ካልኮራን እንግዲህ፣ ማንነታችን ምንድን ነው?

ድንጋይ አንደበት አውጥቶ፣ ታሪክ ነኝ ሲለን እንግዲያ

ታሪካችንን ለመሥራት፣ እኛስ ምን ቀን ጣለን አያ

ምን እርግማን ሽባ አረገን፣ ከዚያ ዘመን እዚህ ድረስ

አገር ነው ብለን ለማመን፣ ሣር ቅጠሉን ለመቀስቀስ?!

አለት እየተናገረ፣ የእኛን አንደበት ምን ዘጋው?

ቋጥኝ “አይዟችሁ” እያለ ፣ የኛን ልብ ምን አመከነው?

ተራራው ማተቡን ሲያጠልቅ፣ የኛን ማተብ

ማ በጠሰው?

ዋሻ እንደጐህ ቀዶ ሲታይ የኛን ዐይን ምን አጨለመው?

ጽድቁ በእጃችን እያለ፣ ቅስማችንን ማ ሰበረው?

ላሊበላ የጡብ ምላሽ፣ የጥንካሬ ክር ነው

ልብ ለልብ ካልተሳሰርን፣ ትላንት ለዛሬ ባዳ ነው

ላሊበላ!

አገር ያቆየ ቅዱስ

አገር የመራ ንጉሥ

አገር ያጠነ መሃንዲስ

ጥበቡ ያስቀናል እሱስ

እንዴት ይፈወስ ህዝቡስ?!

ታህሳስ 29/2004  (ለላሊበላና ለማተባችን)

 

***

እንግዲህ ወደ ላሊበላ እንጓዝ፡፡

ዋና ስሙ - የላሊበላ ጉዞ፡፡ የገና ክብረ በዓል፡፡

የመጓጓዣው ዓይነት - የሚካኤል አውቶቡስ

የተጓዥ ዓይነት - ወንድ ሴት ምዕመናን፣ መነኩሲቶች፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶች…

አመራሮች - አባ፣ ዲያቆን - መዘምራን፣ ሹፌርና ረዳቶች

የጉዞ መንገድ ስም - አዲስ አበባ - ደሴ - ላሊበላ - ባህርዳር - አዲስ አበባ ውስጠ ነገሩ - የማተብ ጥንካሬ፡፡ የመንፈስ ጽናት፡ ጠንካራ መስዋዕትነት፡፡ ረዣዥም መንገድ የሚያስኬድ አጭር ጉዞ፡፡

***

ጉዞዬ ባጭሩ

ወደ ላሊበላ ጉዞ መነሻው የቡልጋሪያ ማዞሪያ አካባቢ የሚካኤል ቤተ - ክርስቲያን ነው፡፡ በአብዮት አደባባይ - በመገናኛ - በለገጣፎ-በለገዳዲ-በሰንዳፋ - ሸኖ ማሪያምን መጐብኘት፡፡ ቀጥሎ ደብረ - ብርሃን ሥላሴን መጐብኘት፡፡ ደብረ - ሲና፡፡ ሣር አምባ ደብረ ገነት ኪዳነ ምህረት ገዳም፡፡ ሸዋ ሮቢት - ደሴ (ገብርኤል ቤተክርስቲያን)፡፡ መርሳ - ወልዲያ፡፡ የናኩቶ ለአብ ቤተክርስቲያን (ፍልፍል እንፀት)፡፡ ላሊበላ (ት/ቤት ቅጽር ግቢ፡፡) መርሀነ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን (ፍልፍል)፡፡ መልስ ላይ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን፡፡ አሽተን ማርያም፡፡ ቤተ - ጊዮርጊስ - ውቅር ቤተክርስቲያን (ከላሊበላ አብያተ - ክርስቲያናት ውጪ ያለ) አሥሩ አብያተ - ክርስቲያናት - ቤተ - ማርያም፣ ቤተ መድኃኒአለም፣ ቤተ ሚካኤል…

ከአሥሩ ውጪ ያለው ቤተ - ገብርኤል፣ የዋሻ ቤተ - ክርስቲያን፡፡ ከላሊበላ መልስ መቂት ስንደርስ አቡነ - አሮንን መጐብኘት፡፡ ለወንዶች ብቻ ነው፡፡ ሴቶች፤ ሥላሴና ኪዳነምህረትን ይሳለማሉ፡፡ ጨጨሆ መድኃኒዓለም፡፡ ጋይንት ደብረ - ታቦር - ወረታ፣ ቁሃር፣ ሐሙሲት…ደቡብ ጐንደር አባይ ድልድይን ማቋረጥ ወደ ባህር ዳር፡፡ ፎገራ፡፡ ወርቅ ሜዳ፡፡ ባህር ዳር፡፡ ወደ ደሴት አድባራትና ገዳማት ጣና ሐይቅ ዙሪያ፡፡

የአቡነ በትረ ማርያምና የተቃጠለው ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፡፡ አዝዋ ማርያም ኪዳነ ምህረት ገዳም፡፡ ዑራ ኪዳነምህረት፡፡ ክብራን ገብርኤል (የወንዶች ገዳም) እንጦስ እየሱስ ገዳም፡፡ ደብረማርያም፡፡ በነጋታው ወደ አዲስ አበባ መልስ፡፡ ፍኖተ - ሰላም -ደምበጫ - መቸኮል - ደብረማርቆስ፣ ደጀን ዐባይ በረሃ - ዋሻው ሚካኤል - ምዕራብ ጐጃም - ዐባይ ድልድይ - ፍልቅልቂት - ጐሐጽዮን-ኩዩ-ፍቼ- የመጨረሻው ገዳም ደብረ ሊባኖስ (የቅዳሴ ሰዓት) - አዲስ አበባ፡፡ ዞረን ገጠምን፡፡ )

ዋናው ጉዞ ሲጀመር

የጉዞ ጣዕሙ የሚቀጥለው መድረሻ ሁሌ አዲስ መሆኑ ነው፡፡ አልዳስ ሐክስሌይ የተባለ ታዋቂ ደራሲ፤ “መጓዝ፤ ማንም ሰው ስለ ሌሎች አገሮች መሳሳቱን ለማወቅ ይጠቅማል” ይላል፡፡ ግምትና በዐይን አይቶ ማረጋገጥ ምን ያህል እንደሚለያይ ይሄ ያስረዳናል፡፡

ከአውቶቡሱ መነሻ ከቡልጋሪያ፣ ሚካኤል ቤተክርስቲያን መነሻው ሰዓት ከንጋቱ 11 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ተኩል ነው፡፡ ዕቃ እየተጫነ ነው፤ ገና እኛ 11 ከሩብ እዚያ ስንደርስ፡፡ እኔና ባለቤቴ ነን፡፡ ብርዱ ይፈደፍዳል፡፡ ሻንጣ፣ ከረጢት፣ ፌስታል፣ የተጠቀለለ ምንጫፍ፣ የተቋጠረ ትላልቅ ማዳበሪያ ወዘተ ይጫናል፡፡ ረዳቱ ከመኪናው አናት ሆኖ ከሥር እየተቀበለ ይደለድላል፡፡ ሰው “ይሄን ጫን ይሄን ጫን” እያለ ይራኮታል፡፡ “ታክሲ ላይ ሽሚያ፣ ባዛር ላይ ሽሚያ፣ ሰልፍ ላይ ሽሚያ … እንዲያው ምን ይሻለናል?” አልኩኝ፡፡

አውቶቡሱ ውስጥ ስንገባ የውስጥ መጫኛው ላይ ጧፍ .. ዣንጥላ … መቋሚያ .. ፌስታል … ከረጢት … ስሊፒንግ ባግ … ይጫናል፡፡ እዚህም ሽሚያ አለ፡፡ ምንም እንኳን የአውቶቡሱ መቀመጫ ቁጥር ቢኖረው የመቀመጪያም ሽሚያ አለ - ትኬቱንና ቁጥሩን በእጃችን ይዘን ወንበር እንሻማለን! አርባ ሰባት ሰው ገደማ ነን፡፡ ሴቶች ይበዛሉ፡፡ «ላይ ለተጫነው ዕቃ እኛ ኃላፊ ነን፡፡ ውስጥ ያለውን እናንተ ጠብቁ … ቁልቢ የተደረገ ነገር ኢንፎርሜሽን ስላለኝ ነው” አሉ አባ፡፡ ምን ይሆን? ብዬ ግምት ጀመርኩ፡፡

አባ ቡራኬ ሰጡ፡፡ አባታችን ሆይ ተፀለየ፡፡ አውቶቡሱ መንገድ ጀመረ - የአውቶቡሱ ማይክራፎንም መዝሙር ጀመረ፡፡ ተጓዦቹም ቀስ በቀስ ማጀብ ጀመሩ፡፡ ሆንዳ (HONDA) የሚል ቲሸርት የለበሰው የሹፌሩ ረዳት ከኋላ ወደፊት ከፊት ወደ ኋላ ይመላለሳል፡፡ በሜክሲኮ - በአብዮት-በመገናኛ-አድርገን ከአዲስ አበባ እየወጣን ነው፡፡ ብዙ ሱቆች ቡና ቤቶች እየነጋላቸው ነው፡፡ የተንቀሳቀስነው ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ከአምስት ነው፡፡ … ዐይኔ “መለኛው ግሮሠሪ” የሚል አርዕስት ላይ አረፈና ፈገግ አልኩኝ፡፡ የመዝሙሩ ድምፅም እየተሰማኝ ነው፡፡

“ሚካኤል ወረደ፣ እኛም ከቤት ወጣን

በአውደ - ምህረቱ - ቆሟል ሊባርከን” ይላል፡፡

(ይቀጥላል)

 

 

Read 3825 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 10:17