Saturday, 28 March 2015 09:53

“...ይህንን ነው የስሜት መዋዠቅ የምንለው...”

Written by  ዮዲት ባይሳ (ከኢሶግ)
Rate this item
(7 votes)

በእርግዝና እንዲሁም በወሊድ ግዜ በእናቲቱ ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ አካላዊ እንዲሁም ስነልቦናዊ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ ምንም እንኳን ይህ ለውጥ በተለያዩ ሴቶች ላይ የሚኖረው ሁኔታ  ቢለያይም እያንዳንዷ እናት ይህን አካላዊና ብሎም ስነልቦናዊ ለውጥ ማስተናገዷ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ አካላዊ ለውጥ ወይም በህክምናው አጠራር physiologic changes of pregnancy በእርግዝና ወቅት በእናቶች ሰውነት ውስጥ የሚመነጨው የሆርሞን መጠን በይዘትም ሆነ በአይነት ከመለወጡ ጋር ተያይዞ የሚከሰት እንደሆነ የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በተመሳሳይ በእርግዝና ወይም በወሊድ ግዜ በእናቲቱ ላይ የሚስተዋሉ ስነልቦናዊ ለውጦችም ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ ለውጦች መካከል ከወሊድ በኋላ ወይም በአራስነት ግዜ የሚከሰት የስሜት ለውጥ አንዱ ነው፡፡ ይህን የስሜት ለውጥ በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል በድንበሯ የእናቶች እና ህፃማት ሆንፒታል የፅንስና ማህፀን እስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር አብዱ መንገሻ ያስረዳሉ፡፡
“በድህረ ወሊድ ወቅት የሚታዩ የስሜት ለውጦችን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው Baby blues  ወይም በአማርኛው የአራስነት መተከዝ ልንለው እንችላለን፡፡ ሌላኛው ደግሞ postpartum depression  ወይም የድህረ ወሊድ የድብርት ህመም ነው፡፡ ሁለተኛው ከበድ ያለና የህክምና ክትትል የሚያስፈልገው ሲሆን የአራስነት መተከዝ የምንለው ግን በብዙ አራሶች ላይ የሚከሰትና እንደ ጤና መጓደልም የማይታይ የስሜት ለውጥ ነው፡፡”
ይህ በአራስነት ወቅት የሚኖር የስሜት ለውጥ እናቲቱ ከወለደች በኋላ ለጥቂት ቀናት ብቻ የሚቆይ በመሆኑ በእርግዝና ወቅት ከሚታዩት ለውጦች እምብዛም የተለዩ አይደሉም ይላሉ ባለሙያው፡፡  
“ይህ የስሜት ለውጥ ከመቶ ምሳ የሚሆኑ እናቶች ላይ ሊከሰት የሚችልና በጣም ለአጭር ግዜ የሚቆይ ነው፡፡ ልክ በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ላይ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ማቅለሽለሽ ወይም አልፎ አልፎ ጠዋት ጠዋት ማስመለስ እንደሚታየው ሁሉ  ከተገላገለች በኋላ ባሉት ሶስት ቢበዛ ደግሞ ስድስት ቀናት ውስጥም የሚከሰት የስሜት ለውጥ ይኖራል፡፡ እናም ከቤተሰብ ድጋፍና እንክብካቤ የዘለለ ህክምና አይስፈልገውም፡፡”
በእርግዝና ወቅት በሰውነት ውስጥ የሚመነጩት የሆርሞኖች መጠን በይዘትም በአይነት ይጨምራሉ። በአንፃሩ ከወሊድ በኋላ የእነዚህ ሆርሞኖች መጠን ይቀንሳል ይህም በአራስነት ወቅት ለሚከሰት የስሜት መለዋወጥ እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡   
“ለዚህ የስሜት ለውጥ ዋና መንስኤ ተብሎ የሚታመነው በእርግዝና ወቅት በነብሰጡሯ ሰውነት በብዙ መጠን ይመረቱ የነበሩ ሆርሞኖች ከወሊድ በኋላ መቀነስ ነው፡፡ እናትየዋ ከወለደች በኋላ እነዚህ ሆርሞኖች መመረታቸውን ስለሚያቆሙ ወይም ከሰውነቷ ስለሚጠፉ የእነዚህ ሆርሞኖች ከሰውነቷ መጥፋት በአራስነት ግዜ ለሚኖር የስሜት መለዋወጥ እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ ምክንያት ነው ይህ የስሜት ለውጥ ግዜያዊ ወይም  ለአጭር ግዜ ብቻ የሚከሰት ችግር ነው የምንለው፡፡”
ለዚህም ተጠቃሽ የሚሆነው ፕሮጀስትሮን የተባለው ሆርሞን ነው፡፡ ይህ ሆርሞን በእርግዝና ወቅት ስሜትን የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተፅእኖ ስለሚኖረው ነብሰጡሯ የተረጋጋ ስሜት ውስጥ እንድትሆን ያደርጋል፡፡ ነገር ግን አንዲት እናት ከወለደች በኋላ ይህ ሆርሞን ስለማይመረትና በሰውነቷ ውስጥ የዚህ ሆርሞን መጠን ስለሚቀንስ ስሜትን የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ከዚህ ሆርሞን ተፅእኖ ነፃ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የስሜት ሁኔታ ዝቅ እንዲል ያደርገዋል፡፡
ምንም እንኳን በወሊድ ግዜ የሚመረቱት ሆርሞኖች መጠን መቀነስ ለዚህ የስሜት መለዋወጥ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይወሰድ እንጂ ይህን ችግር ሊያባብሱ የሚችሉ ሌሎች ምክንያቶች አሉ ይላሉ ዶክተር አብዱ፡፡
“ዋናው ምክንያት የሆርሞን ለውጡ መከሰቱ ቢሆንም ይህ ችግር የተለያዩ ተጨማሪ ክስተቶች ድምር ውጤት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ለምሳሌ በእርግዝና እና በወሊድ ግዜ ነብሰጡሯ ሲሰማት የነበረው የመደሰት እንዲሁም የፍርሀት ስሜት መገላገሏን ተከትሎ ዝቅ ይላል ስለዚህ ይህ እንደ አንድ ተጨማሪ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በመጀመሪያዎቹ የወሊድ ቀናት ላይ የጡት መወጠርም ወይም ሌሎች የእናቲቱን ምቾት ሊያጓድሉ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በአራስነት ግዜ ለሚኖር መተከዝ ወይም የስሜት መለዋወጥ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡”
ሁሉም እናቶች ላይ ባይሆንም ከወሊድ በኋላ የሰውነት ቅርፅ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም እናቲቱ የትዳር አጋሯን ጨምሮ በሌሎች ሰዎች ዘንድ የምስብ ወይም የምማርክ አይነት አይደለሁም የሚል ጭንቀት ሊፈጠርባት ይችላል። በተጨማሪም በምጥ ወቅት የሚኖር የእቅልፍ እጦትን ተከትሎ የሚከሰት የሰውነት መዛል ወይም መድከም፣ እናቲቱ ከወለደች በኋላ ጨቅላ ህፃኑን ለመንከባከብ ያላትን ችሎታ በመጠራጠሯ ምክንያት የሚፈጠር የጭንቀት ስሜት እነዚህ ነገሮች ሁሉ ቀደም ሲል ከተጠቀሰው መሰረታዊ የሆርሞን ለውጥ ጋር ተደማምረው የአራስነት መተከዝን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡    
ይህ ከወሊድ በኋላ የሚኖር የስሜት ለውጥ ሲከሰት በእናቲቱ ላይ ከሚታዩ የተለያዩ ምልክቶች መካከል፡-
እንቅልፍ ማጣት ወይም መደበት
ሆደባሻ መሆን “አለ ምንም ምክንያት በተደጋጋሚ ማልቀስ”
መጨነቅ
ትኩረት ማጣት “ሀሳብን ለመሰብሰብ መቸገር”
ነጭናጫ መሆን እንዲሁም
የስሜት መዋዠቅ
ዋናወናዎቹ ናቸው፡፡
እነዚህን ምልክቶች በተመለከተም ዶክተር አብዱ ይህን ብለዋል፡-
“ለምሳሌ አንዲት አራስ ሴት በቀን ውስጥ ለተወሰኑ ሰአታት ምንም አይነት ምክንያት ሳይኖራት እንዲሁ ዝም ብላ ስታለቅስ ቆይታ ተመልሳ ደግሞ ወደ ጤናማ ስሜቷ ልትመለስ ትችላለች፡፡ የተወሰኑ ደቂቃዎች ጤናማ የሆነ ስሜት ይኖራታል በሌላ ግዜ ደግሞ ያለ ምንም ምክንያት ልታለቅስ ወይም ልትነጫነጭ ትችላለች እንግዲህ ይህንን ነው የስሜት መዋዠቅ የምንለው፡፡”
ይህ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የስሜት መለዋወጥ ለአጭር ግዜ የሚቆይና ወደ ጤና ተቋም መሄድ ሳያስፈልግ ለእናቲቱ በሚደረግ እንክብካቤ ብቻ መከላከል በመቻሉ ከድህረ ወሊድ የድብርት ህመም ወይም postpartum depression  በእጅጉ ይለያል፡፡   
“ይህ የአራስነት መተከዝ በጣም ለአጭር ግዜ የሚቆይ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ይህ ነገር የሚከሰተው ከወሊድ በኋላ ባሉት ሶስት ወይም ስድስት እንደው ቢበዛ ለአስር ቀናት ያህል የሚቆይ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ከ postpartum depression ወይም ከድህረ ወሊድ የድብርት ህመም የሚለይበት ልዩ ባህሪው ነው፡፡”

Read 10647 times