Monday, 06 April 2015 09:29

“...መንስኤው ሳይታወቅ ድንገት የሚከሰት ነው...”

Written by  ዮዲት ባይሳ (ከኢሶግ)
Rate this item
(5 votes)

“ሶስት ልጆችን ወልጃለሁ ነገር ግን ይህ ችግር የገጠመኝ የመጀመሪያ ልጄን ስወልድ ነው፡፡ በጣም ነበር የምጨናነቀው፣ በጣም ነበር የሚያመኝ ምኔን እንደሚያመኝ ግን አላውቀውም ነበር እና ለእራሴ በማይገባኝ ሁኔታ ነበር ይህ ችግር የጠፈጠረብኝ። በጣም እጨናነቃለሁ፣ በጣም እራሴን ያመኛል፣ ምግብ አልበላም ወልጄ በተነሳሁበት ሰአት አራስ ሳይሆን ህመምተኛ ነበር የምመስለው፡፡ በዛ ሰአት ወላጆቼ በህይወት አልነበሩም የቅርብ ቤተሰብም ከጎኔ አልነበረም እና ሁለተኛም የምወልድ እስከማይመስለኝ ድረስ በጣም ነበር የተቸገርኩት፡፡ነገር ግን ይሄ ነገር የጤና ችግር መሆኑንና በዚህ ግዜ የሚንከባከብ ሰው እንደሚያስፈልግ ቆይቶ ነው የገባኝ እና ሁለተኛ እና ሶስተኛ በወለድኩ ግዜ ይህ ነገር አልገጠመኝም፡፡”
ይህን ፅሁፍ ስናዘጋጅ ያገኘናት እናት ከሁለት አስርት አመታት በፊት የመጀመሪያ ልጇን በወለደችበት ወቅት የገጠማትን ያጫወተችን ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ፅሁፋችን ከወሊድ በኋላ የሚከሰቱትን የስሜት ለውጦች በሚመለከት በዚህ ወቅት በእናቲቱ ላይ የሚታዩ የባህሪ ለውጦችን፣ ለችግሩ መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን እና መፍትሄዎቻቸውን የባለሙያ ማብራሪያ አካተን ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ ዛሬም የዛን ቀጣይ ክፍል ይዘን ቀርበናል እነሆ፡-
ሳምንት በድህረ ወሊድ ወቅት የሚታዩ የስሜት ለውጦችን በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል አንደኛው Baby blues  ወይም በአማርኛው የአራስነት መተከዝ ሌላኛው ደግሞ postpartum depression ወይም የድህረ ወሊድ የድብርት ህመም መሆናቸውን፡፡ እንዲት እናት የአራስነት መተከዝ ወይም Baby blues  ሲያጋጥማት የምታሳያቸውን ባህሪያት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በዝርዝር አይተናል፡፡
ዛሬ ተራው የድህረ ወሊድ የድብርት ህመም ወይም በህክምናው አጠራር postpartum depression ነው። postpartum depression ወይም የድህረ ወሊድ የድብርት ህመም በአራስነት ወቅት ከሚኖር መተከዝ ጋር ያለው ልዩነት ምንድነው? ስንል ላነሳነው ጥያቄ ዶክተር አብዱ የሰጡትን ምላሽ እናስቀድም፡-
“ሁለተኛውና በድህረ ወሊድ ግዜ የሚከሰተው የስሜት ወይም የባህሪ ለውጥ postpartum depression ወይም የድህረ ወሊድ የድብርት ህመም ነው፡፡ይሄኛው ከመጀመሪያው ማለትም ከአራስነት መተከዝ ወይም Baby blues ካልነው ጋር ፍፁም የተለያየ ነው፡፡ ይህ የድህረ ወሊድ የድብርት ህመም በሌላ ወቅት ማለትም ከእርግዝና እና ከወሊድ ውጪ ባሉት ግዜያት የሚያጋጥመው ድብርት ወይም depression የሚባለው የአእምሮ ህመም አይነት ነው። ከወሊድ በኋላ ከሶስት እስከ ስድስት ወራት ባሉት ግዜ ውስጥ የሚከሰት depression ሲሆን በባህሪውም በምልክቶቹም በሌላ ግዜ የሚታየው የአእምሮ ህመም አይነት ነው ስለዚህ ተገቢው ህክምና ያስፈልገዋል፡፡ እንደ Baby blues  ወይም በአራስነት ወቅት የሚኖር መተከዝ እንክብካቤና ድጋፍ በማድረግ ብቻ መፍትሄ የሚያገኝ አይደለም፡፡”
ይህ በአራስነት ወቅት የሚከሰት የድብርት ህመም በሌላ ግዜ ከሚከሰቱት የድብርት ህመሞች ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ ይህ ነው የሚባል መንስኤ የለውም፡፡ ይህም ከወሊድ በኋላ በሚኖረው የሆርሞን ለውጥ ምክንያት ከሚከሰተው የአራስነት መተከዝ በእጅጉ እንደሚለየው ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡
“ምክንያቱ ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ይሄኛው ልክ ሌላ ግዜ እንደሚታየው የድብርት ህመም ሁሉ መንስኤው ሳይታወቅ ድንገት የሚመጣ የህመም አይነት ነው፡፡”
ምናልባት ይላሉ ዶክተር አብዱ፡-
“ምናልባት አንዳንድ ግዜ ከሌላው በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ እናቶች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ እድሜያቸው ከያዎቹ በታች ወይም በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ሆነው ሲወልዱ፣ ቀደም ሲል የድብርት ህመም ኖሯቸው ከዳኑ በኋላ የወለዱ እናቶች ሲሆኑና የህክምና ታሪካቸው ይሄ ህመም እንደነበረባቸው የሚያሳይ ከሆነ እነዚህ እናቶች በድህረ ወሊድ የድብርት ህመም የመጠቃት እድላቸው በሰላሳ ከመቶ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ እንደዚሁ ቀደም ሲል እንዲህ አይነት የድህረ ወሊድ የድብርት ህመም ኖሯቸው የዳኑ ማለትም በቀደመው የወሊድ ግዜ እንዲህ አይነት የድብርት ህመም ያጋጠማቸው እናቶች በቀጣዩ የወሊድ ግዜ ደግሞ የመከሰት እድሉ በሰባ በመቶ ከፍ ይላል፡፡ በተመሳሳይ አንዲት እናት ቀደምሲል በድህረ ወሊድ የድብርት ህመም ተጠቅታ በቀጣይ የወሊድ ግዜ ላይ የአራስነት መተከዝ ከታየባት ሁለቱ ሲደመር በዚህ በድህረ ወሊድ የድብርት ህመም የመያዝ እድሏ ወደ ሰማኒያ አምስት ከመቶ ከፍ ይላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ከላይ የጠቀስኳቸው አንድን እናት ለዚህ ለድህረ ወሊድ የድብርት ህመም ይበልጥ ተጋላጭ እንድትሆን የሚያደርጓት ሁኔታዎች ናቸው እንጂ ምክንያት ወይም መንስኤ አይደሉም፡፡”
በዚህ በድህረ ወሊድ የድብርት ህመም የተጠቃች እናት የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩባት ይችላሉ፡፡
እረዥም ሰአታትን በትከዜ ማሳለፍ
የምግብ ፍላጎት መቀነስ ወይም መጨመር
ከፍተኛ የሆነ የክብደት መጨመር ወይም መቀነስ
በእለት ተእለት እንቅስቃሴዎቿ ላይ ያላት ፍላጎት ወይም እርካታ በእጅጉ መቀነስ
እንቅልፍ ማጣት ወይም እቅልፍ ማብዛት
ትኩረት ማጣት (ሀሳብን ለመሰብሰብ መቸገር)
ከልክ ያለፈ የመፀፀት ስሜት እንዲሁም
ተደጋጋሚ እራስን የማጥፋት ፋላጎት ወይም ሙከራ    
አንዲት እናት ከእነዚህ ከተጠቀሱት ምልክቶች ግማሽ ያህሉ ከታገዩባት የድህረ ወሊድ የድብርት በሽታ አለባት ተብሎ ይወሰዳል፡፡
በቅርቡ በገራችን የተጠና ጥናት ከመቶ እናቶች መካከል አንዷ በዚህ በድህረ ወሊድ የድብርት ህመም እንደምትያዝ ያሳያል፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በአዲስ አበባ በሚገኙ ሶስት የመንግስት ሆስፒታሎች ሲሆን 277/ እናቶች በጥናቱ ላይ ተካተዋል፡፡ ዶክተር ብርኑ መሀመድ ከአጥኚዎቹ መካከል አንዱ ሲሆኑ ጥናቱን ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲገልፁ፡-
“ይሄ ችግር ከሚታሰበው በላይ ብዙ እናቶችን የሚያጠቃ ነው ነገር ግን ልክ እንደ ሌሎች የጤና ችግሮች ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ያደጉት ሀገሮች ላይ የዚህ ችግር ስርጭት ከአስር ፐርሰንት እስከ ሀያ ፐርሰንት ይደርሳል አፍሪካ ሀገሮች ላይ ደግሞ ከአርባ እስከ አርባሶስት ይደርሳል የሚሉ ጥናቶች አሉ፡፡ እኛስ ሀገር ምን ያህል ነው የሚለው ጥያቄ ለጥናቱ ዋነኛ የመነሻ ሀሳብ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ይህ ችግር እናቲቱ ላይ ብቻም ሳይሆን በህፃኑ እንዲሁም በሌሎች የቤተሰቡ አባላት ላይ የሚያመጣው ተፅእኖ ይኖራል። ከፍ ሲል ደግሞ ማህበረሰቡም ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ይህ አይነት ችግር ላይ ጥናት ማድረግ ተገቢ ነው ብለን በማሰብ ለማጥናት ተነሳን፡፡”
“ጥናቱን የሰራነው በጥቁር አንበሳ፣ ጋንዲ እና ዘውዲቱ ሆስፒታሎች ነው፡፡ መጀመሪያ ጥናቱን ለማድረግ ስንነሳ 200 እናቶችን ነበር አቅደን የተነሳነው ነገርግን በስተመጨረሻ 277 እናቶችን ለማግኘት ችለናል። ጥናቱን በሶስት ወር ግዜ ውስጥ ነው የጨረስነው በአጠቃላይ ውጤቱም ከመቶ እናቶች መካከል ስምንቱ በዚህ በድህረ ወሊድ የድብርት ህመም እንደሚጠቁ ማየት ችለናል፡፡”
ይህም ትልቅ የሚባል ቁጥር ባይሆንም ችግሩ ከሚያስከትለው ጉዳት አንፃር ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት የከፋ ችግር ሳያስከትል አስቀድሞ መከላከል የሚቻልበት መንገድ ቢኖር መልካም እንደሆነ ዶክተር ብርኑ ይገልፃሉ፡፡
የዛሬውን ፅሁፍ የምናጠቃልለው ዶክተር አብዱ በአራስነት ወቅት የሚከሰቱ የስሜት ለውጦችን በሚመለከት ህብረተሰቡ ማወቅ አለበት ብለው ባስተላለፉት መልእክት ይሆናል፡፡
“አሁን ባለው ሁኔታ ይሄ ችግር የለም ተብሎ ሊታሰብ ይችላል ነገር ግን እናቶቹ ወደ ህክምና ተቋም ስለማይመጡ እንጂ ችግሩ በስፋት አለ፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ማወቅ ያለበት ከወሊድ በኋላ ባሉት ግዜያት እንደነዚህ አይነት ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በመገንዘብ እናቲቱን በንቃት መጠበቅ እና መንከባከብ ያስፈልጋል፡፡
በተጨማሪም ለዚህ የድብርት ህመም ምልክት ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ ነገሮች በታዩበት ግዜ እናቲቱን በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም መውሰድና ተገቢውን ህክምና እንድታገኝ ማድረግ ያስፈልጋል። ሌላው መታወቅ ያለበት ነገር ይሄ ህመም ሙሉ በሙሉ መዳን የሚችል በመሆኑ ተገቢው የህክምና ክትትል ከተደረገ እናቲቱን ወደ ቀድሞ ጤንነቷ መመለስ ይቻላል፡፡”

Read 6899 times