Saturday, 21 January 2012 10:51

ወግ ሲባል ከፒያሳ እስከ ዛላንበሳ

Written by  አለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(0 votes)

መካከል ላይ ሁለት ሳምንቶች ተሙለጭልጨው አመለጡ እንጂ የቅድሚያ ሃሳቤ ከወግ ጥበብ ጋር ሦስት ሳምንታት እንዘልቃለን ነበር፡፡ በሁለቱ ፅሁፎች ከ”የቡና ቤት ሥዕሎች” ጋር መስፍን ሃብተማሪያምን ይዘን፣ በ”ሁለት ሐውልቶች ወግ” እና በ”ጠጠሮቹ” ዳንኤል ክብረትን ዳስሰን፣ ማክተሚያው ላይ እንደ ዳገት ወጪ “ወገቤን” ብለን ቀርተናል፡እንደ ሃሳባችን ቢያዘልቀን ኖሮማ ማክተሚያው የመሐመድ ሰልማን “ፒያሳ” (መሐሙድ ጋ ጠብቂኝ) ቀደም በቀረበ ነበር፡ ግድ የለም ተንጠልጥሎ ቢቆይም ማክተሚያችን በተቀጠበለት ጊዜ ደርሷልና አክትመን እንለያይ፡፡

“ፒያሳ” (መሐሙድ ጋ ጠብቂኝ) መልካም የአየር ንብረት እንደታደለች አገር “ከሙቀቱም” ሆነ “ከብርዱ” አልቀረበትም፡፡ ከአስጐብኚያችን ከመሐመድ ሰልማን ጋር “ከፍ” ስንል “የጀሚላ መዳፎች” የተሰኘ የስሜት ደጋ አለ፡፡ “ዝቅ” ስንል ደግሞ እንደ “ኬሻ በጠረባ” ያለ ምስለ “ቆላ” ያጋጥመናል፡፡ “ፒያሳ” ሲነበብ “ከፍ” እና “ዝቁ” በተለያየ ከባቢያዊ ስሜት ውስጥ ይከተናል፡ እንደ “ወይናደጋ” ሳያቃጥሉም ሳያንዘፈዝፉም በመካከለኛ የሳቅ አየር ሁኔታ የሚያስተናግዱን ፅሁፎችም አሉ፡፡ እንደ “ጀዝቢtude” ያሉ…

ደራሲው መሐመድ ሰልማን በወግ-ፀሐፊ ደንብ አደግድጐ ከወዳጃዊ ፈገግታ ጋር አብሮን ይዘልቃል፡፡ ያየውን፣ የሰማውን፣ የቀመሰውን፣ ያሸተተውን፣ የዳሰሰውን… አንድም ሳያስቀር ያቀርብልናል፡፡ “በአይን-አዋጅ” እንደመማለን፡፡ የምንጥል የምናነሳው እስኪጠፋን ድረስ “የምስጢር እንቁዎቹን” በአይነት በአይነት ይደረድርልናል፡፡ እንደ ከበረ ድንጋይ የድብቅ ሀብቶቹ የነበሩትን ስሜቶቹን ሳይቀር እንዲህ ያቀርብልናል፡፡

“ትዕይንቱ ከአፍታ በኋላ እኔን በጀርባ ወደ ማጋደም ተዛወረ፡፡ የመሀል ጣቷን ጆሮዬ ውስጥ በመጨመር የተለየ ትርጉም ያለው መልዕክት ልታስተላልፍልኝ ሞከረች፡፡ አንገቴ አካባቢ ጥሩ ስሜት የፈጠረብኝን አንዳች ነገር አድርጋ ወደ ደረቴ ተንደረደረች፡፡ ተመልሳ ደግሞ የመሀል ጣቷን ከጆሮዎቼ በመጨመር ቀድሞ እንዳደረገችው ስሜቴን ለማናር ጣረች” የደረቴን ፀጉሮችና ጡንቻዎች በስሜት ታሻሻቸው ጀመር፡፡ ከክሬሙ በቄንጥ በጣቷ ትጠነቁልና የደረቴ ጡቶች ላይ በማሳረፍ በጥፍሮቿ ጫፉን ብቻ እየነካካች ንዝረት ለመፍጠር ታተረች፤ ተሳካላትም፡፡” (ገፅ 123)

ይሄ ምናባዊ ትርክት አይደለም፡፡ ወግ ነውና ምናብ እዚያ ቦታ የለውም - እውነት እንጂ፡፡ መሐመድ ሰልማን ስለ ወግ ጥበብ ይሄን ያህል እርቃነ-ስሜቱን ቀርቧል፡፡ ትክክል ነው! ፈረንሳዊው የወግ ፅሁፍ ጀማሪ ሚካኤል ዴ ሞንታኝ፤ ወግ እየፃፉ መታበይን፣ መሸፋፈንን፣ መወሻከትን… ያነውራል፡፡ እንዲህ በማለት “አንባብያን፣ መፅሐፌን ሳቀርብላችሁ ዋነኛ አላማዬ ያለምንም ሐፍረትና ማስመሰል እኔነቴን መፅሐፌ ውስጥ እንድትመለከቱት ማድረግ ነው” (Reader, my intention is that everyone see me in my book just as I am, without any sham or artifice)

በመሀመድ ሰልማን ግልፅነት የአማርኛ ወግ ፀሐፊነት ክብርን ብቻ ሳይሆን መጪ ህይወትንም ለአደጋ ማጋለጥ ነው፡፡ ግን ደግሞ መደረግ ያለበትም ይሄው ነው፡፡ ወግ-ፀሐፊነት ግማሽ ሰማዕትነት ግማሽ እብደት ቅልቅል ነውና፡፡ በሞንታኝ ገለፃ-ልኬት መሐመድ ሰልማንን “ፒያሳ” ውስጥ እንመለከታለን፡፡ ያለምንም ሐፍረትና ማስመሰል፡፡ ወግ ከፃፉ አይቀር እንዲህ ነው!!

መሐመድ ሰልማን “ፒያሳ” በሚል ስብስብ 14 ወጐችን አቅርቦልናል፡፡ ወጐቹ በአዲስ ነገር ጋዜጣና ድረ-ገፅ ላይ በተለያዩ ጊዜዎች የተነበቡ ይሁን እንጂ በመፅሐፍ ሲቀርቡልን ገና ምርጊቱ እንደተከፈተ ጠላ ኃይላቸው አልቀነሰም፡፡ አልቸኩም፣ አልመነቸኩም፡፡ የመሐመድ አንድ አካል የሆንን ያህል የሄደበት ላለመሄድ፣ የገባበት ላለመግባት… ሳንችል እንቀራለን፡፡ እይታው ተለዋዋጭ፣ ምርጫው አዲስ፣ አቀራረቡ ባለለዛ… በመሆኑ ከእርሱ ጋር ውለን ማደራችን የማይጠገብ ይሆንብናል፡፡ የማናውቀውን ቦታና ሁኔታ ብቻ ሳይሆን አብሮን የኖረውን ሲያስጐበኘን እንደ አዲስ ይሆንብንና አፋችንን ከፍተን እንቀራለን፡፡ ለምሳሌ “ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ”ን መጥቀስ እንችላለን፡፡

“ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ” 17 ንዑስ ምዕራፎችን በ41 ገፆች ላይ የሰየመ የወግ ዋርካ ነው፡፡ መሐመድ ሰልማን በዚህ ወግ ላይ የተጠቀመው አሮጌውን አዲስ የማድረግ ጉልበቱን ነው፡፡ የፒያሳን ካፌዎች፣ ቡቲኮች፣ ጫት ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች፣ ቡና ቤቶች… እናውቃቸዋለን፡፡ ማወቃችን የበቃ የነቃ ስለሚመስለን ወደ ፒያሳ ስንሄድ ትኩረታችን ይሰንፋል፡፡ ይሁንና መሐመድ በመደጋገም ብዛት የረገበ እይታ ከመወጠር በላይ አክርሮ አዲስ ያደርገዋል፡፡ በሽሙጥ እየኳኳለ ባልቴቷን ፒያሳ እንድትወበራ ይኮለኩላታል፡፡

“ስብሐት (ገብረእግዚአብሔር) ‘ትኩሳት’ ብሎ በጠራው መፅሐፉ ጀርባ ምን አለ? ‘ወጣት ሁን፤’ አለ፡፡ ቢመርህ ‘ሪቮሉሸን’ ታስነሳለህ፤ እጅግ ቢመርህ ራስህን ታጠፋለህ…? ለማንኛውም ወጣት ሁን፡፡ እኔ ግን እልሀለሁ፤ ወጣት መሆኑን ሁን፤ ነገር ግን ራስህን ከማጥፋትህ በፊት ፒያሳ ሂድ” (ገፅ 1)

“ፒያሳ” ከመሞት በፊት ብቻ ሳይሆን ከመኖር አስቀድሞም መጐብኘት ያለባት ቦታ ናት፡፡ ታዲያ ስንጐበኛት ከስድስት ኪሎ በ11 ቁጥር አውቶቡስ ወይም ከመገናኛ በ80 ቁጥር አውቶቡስ ተሳፍረን አይደለም፡፡ በመሐመድ ሰልማን ብዕር እንጂ፡፡ እርሱ ሲያስጐበኛችሁ ነው ፒያሳ ከአዚሟ የምትላቀቀው፡፡ ጣሪያና ግንብ፣ አስፋልትና መብራት ከመሆን በድንገት ተላቃ እንደ አላዛር ከሙታን ተለይታ የምትነሳው በመሐመድ ቃል ነው፡፡ ምናልባት ከቃሉ በኋላ በፒያሳ አውራጐዳናዎችና ጉራንጉሮች መለስ-ቀለስ ብትሉ የመሐመድ እይታ ተሸካሚዎች ናችሁና ያኔ ፒያሳ አዲስ ትሆንላችሁ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ዶሮ-ማነቂያ ሄዳችሁ እንበል፡፡ እንዲህ የሚለው የመሐመድ ዶሮ ማነቂያዊ ገለፃ በእዝነ ልቡናችሁ መምጣቱ ግድ ነው፡፡

“የዶሮ-ማነቂያ ዶሮ አይታነቅም፡፡ ሰው ግን ይታነቃል፡፡ ለምሳሌ ኑሮ አልሞላ ሲለው ወይም ዶሮ እጅግ አምሮት መግዣ ሲያጣ፡፡ ኪስህ ውስጥ 12 ብር ከሌለ ለምን ትኖራለህ? ዶሮ እንኳን በአቅሟ አስራ ሁለት ብልት አላት’ኮ፡፡ ስለዚህ ብትታነቅ አልተሳሳትክም” ይሄን አስታውሰህ አስፈሪ በመሰለህ ዶሮ-ማነቂያ እንብርት ላይ ብትሆን እንኳን ፈገግ ከማለት አትቦዝንም፡፡ ፈገግ ካልክ ደግሞ “ዶሮ ማነቂያዊ” መሰልክ ማለት ነው፡፡ ዶሮ ማነቂያዊ ከመሰልክ ደግሞ አልፈራህምና እንኳን የሚቀማህ “የሚፈልጥህ” ጀዝባ’ኳ አይቀርብህም፡፡

መሐመድ ፒያሳን ለማያውቃት ቀርቶ ለኖረባትም አድሶ ነው የቀረባት፡፡ ድንቅ የደራሲነት ችሎታ ነው፡፡ እንግሊዛዊው ደራሲ ሳሙኤል ጆንሰን (1709-1784) ይቺን የመሐመድን አይነት ተሰጥኦ ማዕከል አድርጐ እንዲህ ይላል:- “የአንድ ደራሲ መማረኪያ ጉልበቶቹ ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም አዲስ ነገሮችን የተለመዱ ማድረግና የተለመዱትን አዲስ ማድረግ ናቸው፡፡ (The two most engaging powers of an author are to make new things familiar and familiar things new.)

መሐመድ ሰልማን በ”ፒያሳ” ብዙ የተለመዱ ቦታዎችን አዲስ ያደርግልናል፡፡ ፒያሳ ብቻ ሳትሆን መርካቶ፣ መቀሌና አዲግራትም በመሐመድ ብዕር ከሚወበሩት አንጋፋ አካባቢዎች የሚመደቡ ናቸው፡፡ መርካቶችን በተለየ-ርዕስ በአለፍ ገደም ያስተዋውቃታል፡፡ “ኬሻ በጠረባ” ላይ መሐመድ እንደ ግሪኮቹ አምላክ እንደ ፕሮሚቲየስ አንባቢዎቹ ያላገኙትን የእውነት ችቦ ለማምጣት እራሱን ለመንፈስ ቅጣት አሳልፎ ሲሰጥ እናየዋለን፡፡ በካርቶን የተከፋፈሉ “ኬሻ በጠረባዎችን” ምንጫቸው ድረስ ሄዶ፣ የሰው ልጅ ምን ያህል በኑሮ አሽቆልቁሎ እንደሚያጣጥር አረጋግጦልናል፡፡ ነክቶ፣ ቀምሶ፣ አሽትቶና አድምጦ ለዘልአለሙ የማናገኘውን የቆልቋላ እውነት አምጥቶልናል፡፡

“…በኬሻ በጠረባ ኢንዱስትሪ ደንበኛ የምር ንጉሥ ነው፡፡ ጫማችንን ከመግቢያው ላይ ጥለን በሰዎች ላይ እየተረማመድን ወደ ቆጡ ላይ በመሰላል ወጣን፤ በዚህ የመኝታ ክፍል አሥር ጐረምሶች በከፍተኛ እንቅልፍ ተውጠው ያንኮራፋሉ፡፡ የቤቱን ግማሽ በምታክለው የቆጥ መኝታ ላይ በአንድ መደዳ ተኝተዋል፡፡ ቆጡ በከባድ ጠረን ተውጧል፡፡ ከጐረምሳ ጠረን ባሻገር ክፍሉ በሰው ጋስ በተበከለ አየር ተጨናንቋል፡፡ በደም የወፈሩ ቁንጫዎች ቁጡና አካባቢውን ወርረው ተቆጣጥረውታል፡፡ ቁንጫዎቹ ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው የሚዘልሉት በከፍተኛ ኩራትና በማንአለብኝነት ስሜት ነው፡፡” (131-132)

በአንዲት ምሽት ያውም በደቂቃ ጉብኝታችን በዚህ ህይወት የተጠመዱ ወገኖቻችንን የእድሜ ልክ ስቃይ በቅጡ እንድናውቅ የሚረዳን ነው፡፡ መቼም የማናገኘው፣ መቼም የማንደፍረው ነገር ግን ስንፈራውና ስንጠረጥረው የምንኖረው ቦታና ህይወት ውስጥ መሐመድ በሰላም አድርሶ በሰላም ይመልሰናል፡፡ የመሐመድ መርካቶ ፀጋዬ ገብረመድህን ካስተዋወቃችሁ መርካቶ እጅግ ትለያለች፡፡ የፀጋዬ መርካቶ:-

…ያንዱን ወስዶ ላንዱ

ያንዱን ገፍፎ ላንዱ አብልቶ

አንዱን ነስቶ ላንዱ አድልቶ

ስንቱን ፈርቶ ስንቱን ሸሽቶ

ባፈ ጮሌ ተሸልቶ

አይ መርካቶ

በቅኔ መፍቻ ስልት ከሄድን የፀጋዬ መርካቶ ሰም ናት፣ የመሐመድ መርካቶ ወርቅ፡፡ ቀን-ቀን ገመናዎቿን ሸካክፋ ብቅ የምትለው መርካቶ የፀጋዬ አለችላችሁ፡፡ ነውሯን ለእኩለ-ሌሊት የሰጠችው፣ ጭለማን ተማምና ሃፍረተ-ሥጋዋን ያላቆተችው መርካቶ ደግሞ መሐመድ “ፒያሳ” ውስጥ መሐመድ የጨለማ ግልድሟን ገፍፎ የብሽሽት እባጭ የሆነባት ህይወቷን ሰልሎ ይመለሳል፡፡ መርካቶ ትታከም ዘንድ መትጋቱ የኛ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡የመሐመድ መርካቶ ከሌሊት ነውረኛ ፒጃማዋ በተጨማሪ ቀን-ቀን የምትጐናፀፈው ማስመሰያ የክት ልብስ አላት፡፡ ይሄንን ደግሞ “ሼ-መንደፈር በመርካቶ” ውስጥ እናያለን፡፡ በቀን፣ በብርሃን፣ በፀሐይ… ውስጥ የተደበቀ የጥፋት አዝማሚያ፡፡ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ “ተቻችሎ” መባሉ ለተራኪው አይዋጥለትም፡፡ እውነቱን ነው፡፡ መቻቻል ውስጥ በተራ-በተራ መጐዳዳት አለ፡፡

መሐመድ የራሱን ህይወት ዋቢ አድርጐ እንደሚለን ሙስሊምና ክርስቲያኑ “አንድ ሆኖ” ነው የኖረው፡፡ በዓሉን፣ ደስታውን፣ ሐዘኑን፣ ችግሩን… በጋራ እየተወጣ፡፡ አሁን ግን አዝማሚያው ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን ሆኗል የሚል ፍራቻውን ተራኪው ጠቆም ያደርገናል፡፡ ፍራቻው እርግጠኝነት አለው፡፡ “የክሩሴድ ጦርነት ክተት የታወጀ እስኪመስል ሁለቱም እምነቶች ዛቻን ያዘሉ ፅሁፎችን በአልባሳት እያተሙ ለአደባባይ አብቅተዋል፡፡ …ይህን መሰሉን ነገር ስመለከት አብሮነታችን በቋፍ ያለ መስሎ ይሰማኛል” ይላል መሐመድ፡፡

የመሐመድ ሥጋት ስር የሰደደ ይመስላል፡፡ “ቁርጥራጭ ታሪኮች” ብሎ በሰየማት “ከአዲግራት እስከ ዛላንበሳ” ውስጥም አንስቶታል “የአዲግራት ኃይማኖት” በሚል ንዑስ ርእስ፡፡ የአዲግራቱን የካቶሊክ፣ የኦርቶዶክስና የሙስሊም ቤተ-እምነቶች ህብረት ለመርካቶ፣ ብሎም በኢትዮጵያ የሚመኘው ይመስላል፡፡ አንጋፋው የካቶሊክ ካቴድራል በ1960 ዓ.ም ተመስርቶ ሲመረቅ የእስልምናና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በግ አርደው ደግሰዋል ይለናል፡፡ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ አባ ወልደሥላሴ ቢሮ ውስጥ በወርቃማ ቀለም የተፃፈ የምስክር ወረቀት ተሰቅሏል - “አላሁ-አክበር” የሚል ቃል በጉልህ የተፃፈበት፡፡ የአዲግራት ሙስሊሞች አንዋር መስጊድን ሲገነቡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የገንዘብ መዋጮ እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረጓ የተሰጣት የምስክር ወረቀት ነው ይለናል፡፡

ይሄ የአዲግራት “በረከት” በብሔራዊ ደረጃ ይበዛልን ዘንድ እንድንመኝ አድርጐ ፅሁፉ፣ አጨራረሱ ላይ ወሽመጥ ቆራጭ ይሆራብናል፡፡ “ኢትዮጵያን ወደፊት የኃይማኖት ግጭት ያሰጋታል?” ብዬ ጠየኳቸው” ይላል የካቴድራሉን አስተዳዳሪ “”በዝምታ ተዋጡ፡፡ ያሳሰባቸው ነገር ያለ ይመስላል፡፡” ስለምን እዚህ ላይ ልበ-ሙሉነታቸውን አጡ? የሁላችንም ጥያቄ ነው፡፡

እንቀጥል…

…የቀጠለው ከአዲግራት ወደ ዛላንበሳ ነበር፡፡ የአሥር ብር ጉዞ፡፡ ጉዞው ቦታ ፍለጋ አይመስልም፡፡ ቁጭት፣ ናፍቆት፣ አንድነት… እንጂ፡፡ እነዚህ ስሜቶች መሐመድ እውስጡ እንዳሉ ይፈትሻል፡፡ እራሱን ተገን አድርጐ የእኛን ቁጭት፣ ናፍቆትና የአንድነት ፍላጐት ይበረብራል፡፡ዛላንበሳ የኢትዮጵያ የኤርትራ መፋጠጫ መድረክ ናት፡፡ ምን መፋጠጫ ብቻ! መፋጃም ነበረች፡፡ ዛላንበሳ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጓሮ የቀማው ተራኪ ኤርትራን በቅርብ እርቀት ይማትራታል፡፡ ድንጋይ ተነባብሮ የተሰሩ የኤርትራ ቤቶች ቁልጭ በለው ይታዩታል - ይታዩናል፡፡ “እንደ ትግራይ እረኛ ሰማእንዶ!” እያልኩ ጮክ ብዬ ብጣራ እንኳ አቤት! ሊሉኝ የሚችሉ ኤርትራውያን አይጠፉም” ይላል፡፡ እንዴት ያለ “መጣራት” እንደምን ያለ “ምላሽ”? ሰምና ወርቅ ይኖረው ይሆን?

የመሐመድ የዛላንበሳ ጉዞ የመሬት ፍለጋ አይደለም፡፡ የሰው ናፍቆት ነው፡፡ እነርሱን (ኤርትራውያንን) እና እኛን (ኢትዮጵያውያንን) የለየችን ቀጭን ሽቦ (38th parallel የሚላት) የቁጭት እሳት ሆናበታለች፡፡ እንደ ኦፕራሲዮን ምላጭ አንዱን አካል ከሁለት ከፍላ የተቀበቀበች ሽቦ “ማዶ ለማዶ የሚተያዩት የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች ህዝቦቻቸው መስመሯን (ሽቦዋን) እንዳያልፍ ይከላከላሉ፡፡”

የእነሱን (የኤርትራውያንን) ባናውቅም የእኛ ቀልብ እነሱጋ ነው፡፡ ዛላንበሳ ላይ ከቆምን “ርቀታችን በሜትሮች የሚለካ ነው፡፡ ዘወትር ምሽት የኤርትራ ወታደሮች ከወዲያ ማዶ በክራር ሲያዜሙ ይሰማል፡፡”

ግን… “ክራሩ ብቻ አይደለም የሚሰማው” ይለናል መሐመድ “ምሽት አልፎ አልፎ የተኩስ ልውውጥም ይሰማል፡፡ ለክፉ የማያደርስ የተኩስ ልውውጥ፡፡ ሚዲያዎች የማይዘግቡት የተኩስ ልውውጥ፡፡ ወንድማዊ የተኩስ ልውውጥ”

ወንድማዊ የተኩስ ልውውጥ እንዴት ያለ ነው? ናፍቆት ለመወጣት ሰበብ ፈለጐ እንደመላፋት? ወይስ? …መሐመድ እንደ አዲግራቱ ዛላንበሳ በተስፋ መቁረጥ አይለያትም፡፡ እንዲህ…

“የማያውቁት አገር አይናፍቅም፤ ከአስመራ በቀር፡፡ ይህቺን ህልም የመሰለች ከተማ ሳስብ ክፍኛ ስሜት ይወረኛል፡፡ ሁሌም እንደማውቃት እንጂ እንደማላውቃት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ የእኔ እንጂ “የእነሱ”” ሆና አይሰማኝም፡፡ ደግሞም የእኔ ነበረች፤ የእኔ ትሆን ይሆናል፤ ማን ያውቃል? ሃምሳ አመት?... መቶ አመት?.... ሁለት መቶ አመት? ምናልባት ለአለም ህዝቦች ድንበር የማያስፈልግበት ዘመን ይመጣ ይሆናል፡፡

መሐመድ ከ”ፒያሳ” ይዞን ሄዶ “ዛላንበሳ” ላይ ይተወናል፡፡ በቀላል ምልከታ ተለምዷዊውን አዲስ እያደረገ በሽሙጥ መንኮራኩር ተሳፍረን አዲሱ ተለምዷዊ የሚሆንበት ድንበር ላይ ከሐቅ ጋር ተፋጥጠን እንቀራለን፡፡ አንመለስም፡፡ እዚያ ሐቅ አለ፡፡ እዚያ ተስፋ አለ፡፡ እዚያ ያልሞተ ስጋት አለ፡፡ “ከወንድማዊ ተኩስ” መካከል ቱር ያለች ምናባችን 140 ኪሎ ሜትር ከበረረች አስመራ ትደርሳለች… ለመሆኑ መሐመድ ሰልማን እንደ ፒያሳ፣ እንደ መርካቶ፣ እንደ ቦሌ… ሁሉ አስመራን ያስሳት፣ ይበዘብዛት፣ ይተርካት… ይሆን? ማን ያውቃል? ሃምሳ ዓመት?... መቶ ዓመት… ሁለት መቶ ዓመት?... ምናልባትም ለዓለም ህዝቦች ድንበር የማያስፈልግበት ዘመን ሲመጣ…፡፡

 

 

Read 4003 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 10:58