Tuesday, 14 April 2015 08:40

የፖለቲካ ጥግ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

በትዳራቸው ላይ
የቀበጡ የአፍሪካ ቀዳሚ እመቤቶች

    እንኳንስ በቤተመንግስት ቀርቶ በደሳሳ ጎጆም ቢሆን በአብዛኛው በትዳር ላይ ሲማግጡ የምንሰማው ወንዶች ነበሩ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ነገሮች የተለወጡ ይመስላሉ። አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ቀዳሚ እመቤቶች በትዳራቸው ላይ (ያውም የቤተመንግስት ትዳር!) እንደሚቀብጡ እየሰማን ነው። Africa Cradle የተባለው ድረገፅ፤ 5 በትዳራቸው ላይ የቀበጡ ወይም እስካሁንም የሚቀብጡ የአፍሪካ ቀዳሚ እመቤቶችን ይፋ አድርጓል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የስዋዚላንድ ንጉስ ሙስዋቲ 12ኛ ሚስት የሆነችው ኖታንዶ ተጠቅሳለች፡፡ (ልብ በሉ 12ኛ ልጅ አላልኩም!)
ኖታንዶ ከማን ጋር መሰላችሁ የቀበጠችው? ከአገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር ንዱሚሶ ማምባ ጋር ነው (ፍትህ ቀጠለች!) ሚስትየዋ በዚህም ተወንጅላ ከቤተመንግስት ተሰናብታለች (ደግ ንጉስ ስለሆኑ እኮ ነው!) ኖታንዶ ግን ብቻዋን አይደለችም፡፡ በ2004 እ.ኤ.አ የሙስዋቲ ሌሎች ሁለት ሚስቶችም በትዳራቸው ላይ ቀብጠዋል ተብለው ከቤተመንግስት የሞቀ “ጎጆአቸው” ተባርረዋል፡፡
ለነገሩ እኮ በሴቶቹም መፍረድ ያስቸግራል። እንግዲህ ንጉሱ 13 ሚስቶች ናቸው ያሏቸው፡፡ በየዓመቱም ድንግል ልጃገረድ ይበረከትላቸዋል - በባህላዊ የዳንስ ትርዒት፡፡ ከዚህ ሁሉ የምንረዳው ንጉሱ ለሚስቶቻቸው ጊዜ እንደሌላቸው ነው፡፡ ሴት ቤተመንግስት ውስጥ በድሎት እየኖረች ሥጋዊ ፍላጎት ቢያድርባት አይገርምም፡፡ እናም የንጉስ ሙስዋቲ ሚስቶች ቢቀብጡና ዓይናቸው ውጭ ውጭውን ቢያይ ሊወቀሱ አይገባም ይላሉ - የስነ ልቦና ተንታኞች። ጥፋተኛው ሰውየው ናቸው ሲሉ ንጉሱን ይወቅሳሉ - ተንታኞቹ፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት የጃኮብ ዙማ ሁለተኛ ሚስት ኖምፑ ሜሌሎ ንቱሊ ዙማም እንዲሁ ፊንዳ ቶሞ ከሚባለው ጠባቂዋ  ጋር ትቀብጥ ነበር ብሏል - ድረ ገፁ። (“ቦዲጋርድ” የሚለውን ፊልም አይታ ይሆን?) በእርግጥ ቦዲጋርዷ አሁን በህይወት የለም፡፡ ራሱን አጥፍቷል፡፡ ኖምፑ ሜሌሎ ንቱሊ ዙማ፤ ለፕሬዚዳንቱ 21ኛውን ልጅ አርግዛ በነበረ ወቅት ታዲያ የወላጅ አባት ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም። (አይገርምም የ13 ሚስቶችና 21 ልጆች ነገር!) ጉዳዩ ያሳሰባቸው የዙማ ቤተሰቦች በዙሉ ቋንቋ ለሚታተም ጋዜጣ በወቅቱ በፃፉት ደብዳቤ፤ ከሦስቱ የፕሬዚዳንቱ ሚስቶች አንደኛዋ፣ ፊንዳ ቶሞ ከተባለው ጠባቂዋ ጋር እንደምትማግጥ ገልፀው ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ማንም ወህኒ የወረደ የለም ተብሏል፡፡ “የፕሬዚዳንቱን ገፅታ ለመጠበቅ” ሲባልም ነገሩ እንዲቀዛቀዝ መደረጉ ታውቋል፡፡
ከዚያው ከደቡብ አፍሪካ ሳንወጣ ሌላ በትዳሯ የማገጠች ቀዳሚ እመቤት እናገኛለን፡፡ የኔልሰን ማንዴላ ሚስት ዊኒ ማዲኪዜላ ማንዴላ፡፡ ዊኒ በትዳሯ ላይ መማገጥ ጀመረችው ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ከተፈቱ ከሁለት ዓመት በኋላ ነበር፡፡ የፍቅር ግንኙነት የጀመረችው ደግሞ በዕድሜ ከሷ በግማሽ ከሚያንሰው ዳሊ ምፖፉ ከተባለ የህግ ባለሙያ ጋር ሲሆን የድፍረቷ ድፍረት እሷ በምትመራው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረንስ ፓርቲ የማህበራዊ ደህንነት ክፍል ውስጥ ምክትል ኃላፊ አድርጋ ሾማው ነበር፡፡ እናም ዊኒ፤ ማንዴላን እቤት ጎልታ ከድብቅ ፍቅረኛዋ ጋር በኮንኮርድ አውሮፕላን አሜሪካ ትንሸራሸር ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ማንዴላ ወሬ ሳይደርሳቸው ቀርቶ አልነበረም፡፡ በእሷ ላይ የሚወራውን ሁሉ ለመስማት ስለማይሹ እንጂ፡፡ ብዙም ሳትቆይ ግን ዊኒ የእጇን አገኘች፡፡ የዘራችውን አጨደች፡፡ እ.ኤ.አ በ1992 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ዳሊ ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት እንዳለው አወቀች፡፡
በነገሩ አንጀቷ የተቃጠለው ዊኒ ለዳሊ በፃፈችለት ደብዳቤ፤ “ለአምስት ወራት ያህል ከታታ (ኔልሰን ማንዴላ) ጋር አለመነጋገሬ ላንተ አያሳስብህም፡፡ ቤት ውስጥ ሁኔታዎች እየተበላሹ መምጣታቸውን ስነግርህ ቆይቻለሁ፡፡ አንተን ግን ምንም አላስጨነቀህም፤ ምክንያቱም በየማታው ሴት እያቀፍክ ትተኛለህ። ከአሁን በኋላ ግን ሞኝህን ፈልግ” ብላዋለች፡፡ ይሄ ደብዳቤ በኋላ ላይ በደቡብ አፍሪካው “ሰንደይ ታይምስ” ጋዜጣ ላይ ታትሟል፡፡
ከወር በኋላም የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረንስ (ANC) ከነበራት የኃላፊነት ቦታ ላይ ያነሳት ሲሆን ማንዴላም “ትዳራችን አብቅቷል” ሲሉ በአደባባይ ይፋ አደረጉ፡፡ ዊኒ በአንድ ጊዜ ሁሉ ነገሯን አጣች፡፡
African Cradle በትዳራቸው የቀበጡ ወይም አሁንም እየቀበጡ ያሉ “የአፍሪካ ቀዳሚ እመቤቶች” በሚል ከጠቀሳቸው ውስጥ የዚምባቡዌዋ ቀዳሚ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ይገኙበታል፡፡ የ50 ዓመቷ ግሬስ፣ ከሙጋቤ ጋር የ40 ዓመት የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ሲሆን ይቀብጣሉ የተባለውም ከዚምባቡዌ ሪሰርቭ ባንክ ገዢ ጊዲዎን ጎኖ ጋር እንደሆነ ድረገፁ ይጠቁማል፡፡ ክፋቱ ደግሞ የባንኩ ገዢ የፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ  የቀኝ እጅ መሆናቸው ነው፡፡
ይሄ ግን ግሬስና ጎኖን በወር ሦስቴ ከመገናኘት አላገዳቸውም - አንድም በግሬስ የወተት ተዋፅኦ እርሻ ውስጥ አንድም ደግሞ በጎረቤት አገር ደቡብ አፍሪካ ሆቴሎች ውስጥ እየተገናኙ ዓለማቸውን ይቀጫሉ ተብሏል፡፡ (ሙጋቤ እንዴት አስቻላቸው? …)
ግሬስ በትዳራቸው ላይ ሲቀብጡ ይሄ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ ፒተር ፓሚሬ የተባለ ፍቅረኛ የነበራቸው ሲሆን ፍቅረኛቸው አሁንም ድረስ መንስኤው ባልታወቀ የመኪና አደጋ ህይወቱ አልፏል። ጄምስ ማካምባ የተባለ ሌላ ፍቅረኛም ነበራቸው፡፡ እሱ ደግሞ ከአገሪቱ ወጥቶ ተሰውሯል ተብሏል፡፡
ግሬስና የባንኩ ገዢ ከድብቅ የፍቅር ግንኙነታቸው በተጨማሪ ላለፉት 15 ዓመታት የቢዝነስ ሸሪኮች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ለነገሩ ሚ/ር ጎኖ ከግሬስ አጠገብ መሆናቸውን ሮበርት ሙጋቤ ይፈልጉታል፡፡ ሚስቴን እንዳትቀብጥ በዓይነ ቁራኛ ይጠብቅልኛል በሚል እዚህ ድረስ ነው ፕሬዚዳንቱ የባንክ ገዢውን የሚያምኑት። እሳቸው ግን አልታመኑላቸውም፡፡ ምክንያቱ ባይታወቅም እስካሁን ሙጋቤ የ55 ዓመቱን የባንክ ገዢ ምንም አላሏቸውም። ሰውየው ግን ምን ዓይነት የስጋት ህይወት እንደሚመሩ መገመት አያዳግትም፡፡ (ሚስትየዋ እንኳን አመላቸው እንደሆነ ይታወቃል!) በነገራችሁ ላይ ግሬስ ቀዳሚ እመቤት ከመሆናቸው በፊት የፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋ ፀሐፊ ነበሩ፡፡ 

Read 3559 times