Tuesday, 14 April 2015 08:42

ጠ/ሚኒስትሩ የማንን እግር ይጠቡ? የተቃዋሚ መሪዎችስ?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(11 votes)

ሚኒስትሮች ገጠር ወርደው የአርሶ አደሩን እግር ያጥባሉ

    ሳምንቱ የማማት ቢሆንም መሳሳም እንጂ ማሰብ አልተከለከለም፡፡ በነገራችን ላይ --- የሰው ልጅ ማንም ሊከለክለው የማይችለው ብቸኛ ተፈጥሮአዊ መብቱ (ጸጋው) ማሰብ ነው፡፡ ሌሎች ተፈጥሮአዊ ጸጋዎች በተለይ አምባገነንነት በሰፈነበትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ገና በሁለት እግሩ ባልቆመባቸው አገራት ሁሉ በሰበብ አስባቡ ሊከለከሉ ይችላሉ፡፡ (ይችላሉ ሳይሆን ይከለከላሉ!) ሌላው ቀርቶ መሳሳም፣ (ከማማት ውጪ ማለቴ ነው) መዝፈን፣ መደነስ (ባለፈው ስውዲን ከልክላለች!)፣ ማንበብ፣ መብላት፣ ማውራት፣ ማግባት፣ መወለድ ወይም መውለድ---ወዘተ በቀላሉ ሊከለከሉ ይችላሉ፡፡ (ለህዝብ አደጋ ናቸው ተብለው ሲታሰቡ ማለት ነው!) ማሰብን መከልከል ግን እስካሁን አልተቻለም፡፡ (ተፈጥሮ እንዳይቻል አድርጋዋለች!) እርግጠኛ ነኝ የዓለም አምባገነኖች በዚህ ክፉኛ መብሸቃቸው አይቀርም። የራሳቸው ጉዳይ ነው፡፡ (አምባገነንነት እሽሩሩ አይወድም!)
ወደ ሰሞነኛ ጉዳይ ስንመጣ---ከትላንት በስቲያ በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሊቃነ ጳጳሳት የምዕመናንን እግር በወይራ ቅጠል አጥበዋል (ጌታችን የደቀመዛሙርቱን እግር ማጠቡን ልብ ይሏል)፡፡ በዚህም የተነሳ የትላንት በስቲያው ሐሙስ “ሕፅበተ እግር” ይባላል፡፡ ሌሎች መጠሪያዎችም አሉት- ከሃይማኖቱ ጋር በቀጥታ የተያያዘ፡፡ እናላችሁ---ሊቃነ ጳጳሳት የምዕመናንን እግር ሲያጥቡ ስመለከት ---- አንድ ለየት ያለ ሃሳብ አዕምሮዬን ጎበኘው፡፡ ምን መሰላችሁ? ይሄ እግር መተጣጠብ ከምንም በላይ የሚያስፈልገው በፖለቲካው ንፍቀ ክበብ ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ (ማሰብ አይከለከልማ!) እናንተ ትዕግስት ይኑራችሁ እንጂ እኔ ሃሳቤን በዝርዝር አስረዳለሁ፡፡ ምን ይታወቃል----ተቀባይነት አግኝቶ በዚሁ ዓመት ከምርጫው በፊት መተግበር ሊጀምር ሁሉ ይችላል። (የኛ ነገር “ይሆናል ሲባል አይሆንም፤ አይሆንም ሲባል ይሆናል” አይደል!) አንዳንድ በትግል ያልታሹ የሁለቱም ጎራ ለጋ ካድሬዎች፣ሃይማኖትና ፖለቲካን እንደቀላቀልኩ አድርገው ሊወነጅሉኝ እንደሚችሉ እገምታለሁ (ሰው የሚያስበው የአቅሙን ነው!)
እናላችሁ---ሰሞኑን በአዕምሮዬ ብልጭ ብላ ሳብላላት የሰነበትኳት ሃሳብ፣ ጠንክራና ዳብራ ለአቅመ-ፕሮፖዛል ደርሳለች፡፡ ይሄ ፕሮፖዛል እንደሚለው ከሆነ ታዲያ---ለአገራችንን ዋነኛ የፖለቲካ ችግር “ሕጽበተ እግር” ፍቱን መድሃኒት (ፈውስ) ነው፡፡ በአግባቡ ከተተገበረም አሜሪካ 100 ዓመት የፈጀባትን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የማስፈንና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል የማዳበር ሥራ፣ እኛ በ20 እና 30 ዓመት ውስጥ ልንከውነው እንደምንችል ፕሮፖዛሌ ይጠቁማል፡፡ (ኢኮኖሚውም ፖለቲካውም በአቋራጭ ሆነባችሁ እንዴ?) በነገራችን ላይ ይሄ ፕሮፖዛል በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ተሞክሮ የማያውቅ ሲሆን በጦቢያ ውጤታማ ከሆነ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የማሻገርና የማስፋፋት ራዕይ አለኝ፡፡
ቀደም ብዬ እንደጠቆምኳችሁ መነሻ ሃሳቡ የሊቀ ጳጳሳቱ የምዕመናንን እግር ማጠብ ቢሆንም ፕሮፖዛሌ ግን ሃይማኖታዊ ዓላማም ሆነ ግብ የለውም፡፡ (ልምል እችላለሁ!) “የእግር እጥበቱ” ለፖለቲካዊ ዓላማና ተግባር እንዲሆን ብዙ ማሻሻያዎችና ማስተካከያዎች ተደርጎበታል፡፡ እናላችሁ---ፕሮፖዛሉ በፖለቲከኞች ይጀመር እንጂ ወደ ሲቪሉም ይወርዳል፡፡ ተማሪና አስተማሪውን፣ ቤተሰብን፣ የመንግስት ሠራተኛውን፣ ነጋዴውን፣ በአጠቃላይ ወንድ ሴቱን፣ ህጻን አዋቂውን ወዘተ---የሚያካትት ፕሮጀክት ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ---ወደድንም ጠላንም በፖለቲካው ውስጥ የሚታየው ችግር በሌላው ዘርፍም መከሰቱ አይቀርም፡፡ (ፖለቲካ ለብቻው የተከለለ ደሴት አይደለም!)
በዓመት አንዴ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የእግር አጠባ ሥነርዓት፣ ሁሌም የሚጀምሩት የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ወይም ርዕሰ ብሔር ናቸው ይላል -ፕሮፖዛሌ፡፡ ሥነስርዓቱንም ኢቢሲ በቀጥታ ከቤተመንግስት  ያሰራጨዋል - እንደ ፓርላማ ጉባኤ። ፕሮፖዛሉ እንደሚለው፤ ጠ/ሚኒስትሩ ወይም ርዕሰ ብሄሩ የእግር አጠባ ሥርዓቱን የሚያስጀምሩት እርስ በእርስ በመተጣጠብ ወይም የሚስቶቻቸውን እግር በማጠብ አይደለም ይላል-ፕሮፖዛሉ፡፡ ለዚህ ለዚህማ የቲቪ ቀረጻው ሁሉ ለምን ያስፈልጋል?  እናም ፕሮፖዛሌ፤ ጠ/ሚኒስትሩ ወይም ፕሬዚዳንቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን እግር በወይራ ቅጠል ያጥባሉ ይላል፡፡ (በውክልና ማሳጠብ አይቻልም!)
በመቀጠል ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ቤተመንግስት ተገኝተው በተራቸው የጠ/ሚኒስትሩንና የፕሬዚዳንቱን እግር ያጥባሉ፡፡ በፕሮፖዛሉ የመጨረሻ ረቂቅ ላይ ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚን፣ ተቃዋሚ ገዢ ፓርቲን ለምን ያህል ደቂቃ እንደሚያጥበው ባለሙያ አማክሬ የጊዜ ገደብ አካትትበታለሁ፡፡ የእግር አጠባው ሥነስርዓት ግን በትላልቆቹ የገዢውና ተቃዋሚ አመራሮች ብቻ አያበቃም፡፡ ሚኒስትሮችና የመንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ገጠር ወርደው የአርሶ አደሩን እግር በወይራ ቅጠል እንደሚያጥቡ ፕሮፖዛሉ ያመለክታል፡፡ የኢህአዴግ ካድሬዎችም ደግሞ የተቃዋሚ ደጋፊዎችን እግር ያጥባሉ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በበኩላቸው፤ የኢህአዴግ ደጋፊዎችን እግር ያጥባሉ፡፡
ይሄ ዓመታዊ ራስን ትሁት የማድረጊያ ሥነስርዓት ቀስ በቀስ በእያንዳንዱ ማህበረሰብ ውስጥ ዘልቆ እንደሚገባ የሚጠቁመው ፕሮፖዛሉ፤የቤት እመቤትዋ ዝቅ ብላ የሠራተኛዋን እግር ታጥባለች ይላል፡፡ (ሠራተኛዋማ የእመቤቷን እግር ሁሌ እንዳጠበቻት ነው!) አባወራውም ታዲያ የመኪናውን በር የሚከፍትለትን ዘበኛ እግር  ያጥባል - በዓመት አንዴ፡፡
ፖለቲከኞቹን በተመለከተ የእግር አጠባው ሥነስርዓት ሲያስፈልግ ጃንሜዳ፣ አሊያም ስቴዲየምና መስቀል አደባባይ ሊከናወን ይችላል። ገጠር ከሆነም መስክ ላይ ወይም ወንዝ ዳር ይከወናል። በእርግጥ ይሄም እንደምርጫ ሁሉ የሥነምግባር ኮድ ሊያስፈልገው ይችላል-ከአንዳንድ ያልተፈለጉ ውዝግቦችና ግጭቶች ለመዳን፡፡ ሥነስርዓቱን በተለይ ዘንድሮ ለመጀመር ፖለቲከኞች ከስምምነት ላይ ከደረሱ ከግንቦቱ ምርጫ በፊት ቢካሄድ ሸጋ ነው፡፡ ከምርጫ ጋር ለተያያዙ በርካታ ስጋቶችና ጭንቀቶች መፍትሄ እንደሚሆን ፕሮፖዛሉ ያመለክታል፡፡  
የእግር መተጣጠቡ ዓላማ እስካሁን ላይ ላዩን እንጂ በወጉ አልተብራራም፡፡ መቼም ፖለቲከኞችን ሃይማኖተኛ ለማድረግ የተሸረበ ሴራ ነው ብሎ የሚያስብ ማንም አይኖርም፡፡ ከሃይጂን ጋር የተያያዘ እንደማይሆንም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ይኸውላችሁ…በሃይማኖቱ ከሄድን የእግር እጥበቱ ኃጢያትን እንደማጠብ የሚቆጠር ነው፡፡ ፕሮፖዛሉ እንደሚለው፤ የእግር ማጠቡ ሥነስርዓት ዓላማ፤ በፖለቲካው ውስጥ የሰፈነውን ጥላቻ፣ንቀት፣ትዕቢት፣ዘረኝነት፣ጠባብነት፣መጠላለፍ፣መጠፋት፣ጨለምተኝነት፣ፍረጃ ወዘተ--ጠራርጎ ማጥፋት ነው፡፡ የእግር መተጣጠቡ---ራስን ትሁት ለማድረግ፣ለሌላው አክብሮት ለመስጠት፣ከዚያም አልፎ እርስ በእርስ ለመደማመጥም በር ይከፍታል። እናም እውነት የጥላቻ ፖለቲካ ሰልችቶን ከሆነ ዛሬውኑ የእግር ማጠብ ፕሮፖዛሌ ተግባራዊ ይደረግ እላለሁ፡፡
እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ!

Read 3274 times