Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 January 2012 11:01

የአማርኛ ሥነ ግጥም

Written by 
Rate this item
(41 votes)

ይህ ግጥም ስለምን ያወራል? ተብሎ ቢጠየቅ ግጥሙ ስለውበት ስለተፈጥሮ ውብነት ማውራቱን የሚጠራጠር ሰው አይኖርም፡፡ በእርግጥ ግጥሙ ስለውበት ይናገራል፡፡ ስለውበት የሚናገረውም የውበትን ምንነት በማተት ወይም በማብራራት ሳይሆን ውበትን ራሱን በማሳየት ነው፡፡ ገጣሚው ውበት ማለት እንዲህ ነው ብሎ በቀጥታ አልነገረንም፣ በቃላት የሳለልንን ሁነት ተመልክተን የተሰማንን እንናገር ወይም፣ “እንዴ እውነትም!” ብለን እንደመም ዘንድ ጋበዘን፤ አስተያየቱን እንጋራ ዘንድ ጠየቀን እንጂ፡፡ የአቀራረብ ጥያቄያዊነት በእኛና በገጣሚው መካከል ያለውን ተራክቦ በወዳጆች መካከል የሚካሄድ ጭውውት ለዛ ይሰጣል፡፡ ይህ አይነቱ አቀራረብ ከንግግር ስልት ጋር በጣም የሚጠጋጋ ወይም የሚዛመድ በመሆኑ በእኛና በገጣሚው መካከል የመንፈስና የስሜት መቀራረብ እንዲኖር ያደርጋል፡፡

ገጣሚው የተፈጥሮን ውብነት ያሳየን ከአያሌ የተፈጥሮ ገፅታዎች መካከል ጥቂቱንና የተወሰኑትን ብቻ መርጦ በቃላት በመሣል ነው፡፡ ከተፈጥሮ ክስተቶች መካከል፤ ቀስተ ደመና፣ ጨረቃንና ተወርዋሪ ኮከብን፤ ከገጸ-ምድር ለምለም መስክን፣ ከወቅት መጸውን፣ ከጊዜ አብራጃን (አመሻሽን)፣ ከሰው ዘር ደግሞ ጥንድ ወጣቶችን በመምረጥ ውበትንና ውብ ነገሮችን እንዲወክሉ አድርጓል፡፡ የተመረጡት ነገሮችም ኹለንታንና በኹለንታ ውስጥ የሚገኙ የሥነፍጥረት ወገኖችን ይወክላሉ፡፡ ውበት የተገለጸው በነገሮች መካከል ካለው ተፈጥሮአዊ አንድነትና ዝምድና በተፈለቀቀና ጎልቶ በወጣ ኅብርና ስምምነት ነው፡፡ ቀስተደመናው፣ በልዩ ልዩ የቀለማት ኅብር አሸብርቆ ነው በቃላት የተሳለው፡፡ የቀለማቱን ዝርዝርና ኅብራቸውን ማብራራት የግጥም ባህርይ ባይሆንም አንባቢው ከገጣሚው የሚጋራው የህይወት ልምድ አለና የቀስተ-ደመናውን ምስል በምናቡ ሊመለከተው ይችላል፡፡ የቀስደመናውን ጎባባ የብርሃን መስመር፤ የጎባባውን ቅርጽ ጥልቀትና ይህ የብርሃን መስመር ያካለለውንም ርቀት (ባድማስ በሰማዩ ሰፍኖበት ተንጣሎ በሚሉ ቃላት ተመልክቷል) ለመገመትም ይችላል፡፡ ገጣሚው ቀስተደመና በሌለበት ቦታና ጊዜ፣ ግጥሙን ስናነብ፤ በተፃፈው ቃል ኃይል አማካይነት ልዩ ልዩ ቀለማት፣ የቀለማቱን ኅብርና ስምምነት፣ የአድማሱን ርቀት፤ ወርድና ጥልቀት በአይነህሊና  ለመመልከት እንችል ዘንድ ጉልህ (አንድ ለመገንዘብ የሚቻል ቅርጽና መልክ ያለው) የቃላት ስዕል አቅርቦልናል፡፡

ከቀስተደመናው ትይዩ (በታች) ለምለም መስክ አለ፡፡ መስኩ የተገለጸው በልምላሜ ነው፡፡ “ልምላሜ” የሚለው ቃል አረንጓዴ የለበሰን ሜዳ በምናባችን ይከስታል፡፡ መስኩ፣ የልምላሜ ምስጢር የተገለጠበት ሁነት (ልምላሜ) ነው፡፡ የዚህ ውበት ፍጽምና፣ “አምሮ፤ ተሰንግሎ፤ በተፈጥሮ ጠርቶ፤”፣ በሚለው ስንኝ ውስጥ በመጡት የፍቺና የቅርጽ ተመሳሳይነት ባላቸዉ ቃላት ድግግም ተገልጾአል፡፡ ይህ ድግግም ውበቱ ደምቆ እንዲወጣ፣ አንባቢውም በምናቡ ውቡን መስክ ትክ ብሎ (አተኩሮ) ያይ፣ እውነቱንም ማስረገጥ ይችል ዘንድ ያሳስባል፡፡ “የልምላሜ ምሥጢር በልምላሜ ሰልቶ፣ /አምሮ ተሰንግሎ በተፈጥሮ ጠርቶ፣4” በሚሉት ሁለት ስንኞች የተያዘው ስሜት አንድምታም (ትርጓሜም) የተፈጥሮን ምስጢርነት፣ የተፈጥሮ ፍጽምናና ሁለንተናዊነት ቆም ብሎ፣ ይመለከት፣ ያሰላስልና ያደንቅ ዘንድ አንባቢን ማነሳሳት ነው፡፡ ይህን የመሰሉት ሃሳቦችና እውነቶችን መሰንዘር (ማሳየት) አንዱ የስነ ግጥም ሁነኛ ሰብአዊና ኪናዊ ጥቅም መገለጫ ገጽታ ነው፡፡ ስለዚህም፣ በዘወትራዊ የንግግርና የጽሑፍ ማኼጃ ቅርጾች ለመግለጥ ወይም ለማለት የሚጠኑ፣ የሚወሳሰቡና የሚረቅቁ እውነታዎችን፣ እሳቤዎችን፣ ሁነቶችን፣ ገጠመኞችንና ስሜቶችን በሥነግጥም ማሰላሰል፣ ማሰብ ቅርጽ ማስያዝና መተንፈስ፣ ሌሎችም ልብ ይሏቸው ዘንድ መጋበዝ የግጥምና ገጣሚ ሁሉ የጋራ ተግባር ነው፡፡

ሥነ ግጥምና ምናባዊ አስተያየት ነው

ሥነግጥማዊ ተግባቦት ምናባዊና ሕውስታዊ ክስተት ነው፡፡ ሥነግጥም ይህንን የሚያደርገው በተጻፈው ወይም በተነገረው ቃል ኃይል አማካኝነት አንባቢ በዐይንህሊናው የሚያየውን ስዕል በእዝነህሊናው የሚሰማውን ድምጽ በመፍጠር ነው፡፡ ስለዚህ ሥንግጥም ምናባዊ አስተያየት ነው ይባላል፡፡ ሥነግጥም ምናባዊ ነው ስንል፤ መጀመሪያ ነገር ሥነግጥም የሚነቃው ከገጣሚው መቀስቀስ፣ እርሱም ሊቆጣጠረው ከማይችለው ጥልቅ ስሜት፣ ሊያስቀረውና ሊያስወግደው ከሚችለው፣ ቀልቡን ከሚሰርቀውና አዕምሮውን ከነገሰበት … መነገር፣ መዘመር ወይም መተንፈስ ካለበት ኃያል ሃሳብ፣ ስሜት ወይም ገጠመኝ ይመነጫል ማለት ነው፡፡ የአልቃሹዋ ሙሾ ወይም እንጉርጉሮ ከጥልቅ ሐዘን ስሜትና የመንፈስ ስብራት፣ የአቅራሪው ሽለላ ደግሞ ነፍሱን ከሚንጣትና ከሚሰብቃት ወኔን እልክ እንደሚነቃ፣ እንዲሁም የአፍቃሪዋ ጉብል እንጉርጉሮ ለሌላ ሰው (ለአድማጭ)  ሳይሆን ለራስ-የከያኔዋን ነፍስ ለማስታመምና ለማባባል እንደሚዘመር ሁሉ፣ በእውነተኛ ገጣሚ ዘንድ ቃላት የሚፈልጉት ገሞራ እሳት ከነፍስ ውስጥ ገንፍለው ነው፡፡ የገጣሚውም ዓላማ የነፍሱን እውነት ለሌሎች መንገር ሳይሆን የውስጡን ነውጥ ማስታገስ፣ የራሱን እውነት ለራሱ በቃላት ቀርጾ (ቅርጽ አስይዞ) ማቆየት ነው፡፡ ዳሩ ግን፣ ከአልቃሹዋና ከአቅራሪው ግጥምና ዜማ የሚነቃው እውነትና ስሜት አንድም ሰው ናቸውና እንደማንኛውም ሰብዓዊ ፍጥረት ከሌሎች የማህበራቸው አባላት ጋር በስሜትና በግብር ካላቸው ትስስር የሚመነጭ ይሆናል፡፡ ይህም ስሜትና እውነት ለሌሎቻችን የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ እውነትና የወል ዕጣ ፈንታ ወይም ምስጢርና እንቆቅልሽ ስለሚሆን፣ የገጣምኑን ቃላቸውን ማህበራቸው ይዘምረው፤ እውነታቸውን እውነቱ ያደርገው ዘንድ ይሻሉ፡፡ እናም ግጥማቸውን በጉባኤ ይከውኑታል፡፡

(በብርሃኑ ገበየሁ ከተዘጋጀው “የአማርኛ ሥነግጥም” መፅሃፍ የተቀነጨበ)

a

 

 

Read 19416 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 11:04