Tuesday, 21 April 2015 08:22

“...አይነቱን ማብዛት እና ማመጣጠን ያስፈልጋል...”

Written by 
Rate this item
(24 votes)

በርካታ እናቶች በተለይም አዲስ ወላድ እናቶች የአመጋገብ ስርአታቸው ጡት በማጥባት ግዜ ስለሚኖረው ተፅእኖ ሰፊ እውቀት የላቸውም፡፡ ከወሊድ በኋላ ቀድሞ የምንመገበውን የምግብ አይነት ሙሉ በሙሉ መቀየር አስፈላጊ ባይሆንም የሚከተሉት ነጥቦች ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡-
የተመጣጠነ ምግብ መመገብ
የእናት ጡት ወተትን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የእናቲቱ አመጋገብ የተስተካከለ ባይሆን እንኳን ህፃኑ ምንም አይነት ተጨማሪ ምግብ ሳያስፈልገው ማግኘት ያለበትን ንጥረ ነገር ከእናት ጡት ወተት ብቻ የሚያገኝ መሆኑ ነው፡፡
ነገር ግን የእናቲቱ አመጋገብ የተስተካከለ ባልሆነበት ሁኔታም ህፃኑ የሚያስፈልገውን ንጥረ ነገር ያገኛል ማለት እናቲቱ እንዲሁም በህፃኑ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ የእናቲቱ አመጋገብ ያልተስተካከለ ከሆነና ሰውነቷ ማግኘት ያለበትን ንጥረ ነገር በተገቢው መጠን ማግኘት ካልቻለ የምታመነጨው ወተት በብዛትም ሆነ በጥራት ሊቀንስ ይችላል፡፡     
በተመሳሳይ ሰውነታችን የሚያስፈልገውን ምግብ በተገቢው ሰአት ማግኘት ከልቻለ አስቀድሞ ያጠራቀመውን ምግብ መጠቀም ይጀምራል ይህም በሰውነታችን የሚኖረው የምግብ ክምችት እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ በዚህ ምክንያት የእናቲቱ ጉልበት ስለሚዳከም ለልጇ የሚያስፈልገውን እንክብከቤ ላታደርግ ትችላለች፡፡
ብዙ የሚያጠቡ እናቶች ከሌሎች በተለየ መልኩ ቶሎ ቶሎ የእራብ ስሜት ሊኖረቸው ይችላል ይህም እናቲቱ ከምትመገበው ምግብ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወተት ለማመጨት በስራ ላይ የሚውል በመሆኑ ነው፡፡
ልክ እንደ እርግዝና ግዜ ሁሉ ምግብን በሰአቱ በመመገብ እና በመካከሉ ፈሳሽ ወይም ሌሎች ተጨማሪ ምግቦችን በመውሰድ ይህን የእርሀብ ስሜት ለማጥፋት እንዲሁም ጥሩ የሰውነት ጥንከሬ እንዲኖር ለማድረግ ይረዳል፡፡
በሰውነት ውስጥ ያለውን ካሎሪ መጠን መቆጣጠር    
አንዲት የምታጠባ እናት በሰውነቷ ሊኖራት የሚገባው የካሎሪ መጠን ምንያህል ነው? ለሚለው ጥያቄ አንድ መልስ ማግኘት አይችልም፡፡ ነገር ግን ብዙውን ግዜ የሚያጠቡ እናቶች በሰውነታቸው ሊኖር የሚገባው የካሎሪ መጠን ከማያጠቡ እናቶች በ500 ኪሎ ካሎሪ መብለጥት እንዳለበት ይመከራል፡፡ ይህም አንዲት የሚታጠባ እናት በሰውነቷ ሊኖር የሚገባውን የካሎሪ መጠን ከ2000-2500/ ያደርሰዋል ማለት ነው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ አንዲት እናት ከላይ በተጠቀሰው ቁጥር ከመመራት ይልቅ በእለት ተእለት እንቅስቃሴዋ የሚኖራትን የእርሀብ ስሜት ብትከተል ሰውቷ የሚያስፈልገውን ያህል ምግብ ማግኘቱን በቀላሉ መቆጣጠር ትችላለች፡፡
የሰውነት ክብደት፣ የምታደርገው አካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የስልቀጣ ስርአት የሚከናወንበት ፍጥነት እንዲሁም እናቲቱ የምታጠባበት የግዜ ልዩነት ሰውነት የሚያስፈልገውን የካሎሪ መጠን ከሚወስኑ ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የሰውነት ክብደትን ቀስ በቀስ መቀነስ  
አንዳንድ እናቶች ከወሊድ በኋላ የሚኖርን የሰውነት ክብደት በአጭር ግዜ ውስጥ መቀነስ ሲችሉ አንዳንዶች ላይ ግን ይህ ከወሊድ በኋላ የሚፈጠር የሰውነት ክብደት እረዘም ላለ ግዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ ይህም በእናቲቱ የሰውነት ሁኔታ፣ የምግብ ምርጫ፣ በምታደርገው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሁም የስልቀጣ ስርአቱ እንደሚከናወንበት ፍጥነት ይወሰናል፡፡
የሚከተሉት ነጥቦች አንዲት የምታጠባ እናት ጤናማ የሆነ የሰውነት ክብደት እንዲኖራት ለማድረግ ይረዳሉ፡-
የሰውነት ክብደትሽን ቀስ በቀስ መቀነስ (ወደ ቀደመው የሰውነት አቋምሽ  ለመመለስ ቢያንስ ከአመት ያላነሰ ግዜ መውሰድ)
ከወሊድ በኋላ በሚኖሩት ሁለት ወራት ውስጥ ክብደት ለመቀነስ በሚል ቀደም ሲል ከምትመገቢው መጠን አለመቀነስ  
ከወሊድ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ከፍተኛ የካሎሪ መጠን ያላቸውን ምግቦች መቀነስ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ምግቦች የሚመነጨውን ወተት መጠን እንዲቀንስ የማድረግ ባህሪ አላቸው፡፡
በአጠቃላይ ከወሊድ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ክብደት ለመቀነስ በሚል የምግብ መጠን መቀነስ ወይም አመጋገብ ላይ ለውጥ ማድረግ አይመከርም፡፡ ነገርግን የሰውነት ክብደት ከመጠን ያለፈ ከሆነ በቅድሚያ ሀኪም ማማከር ያስፈልጋል
በሰውነትሽ ያለው ፈሳሽ በቂ መሆኑን ማረጋገጥ (አንዳንድ ምግቦች በሰውነታችን ያለው ፈሳሽ መጠን እንዲቀንስ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡)
በዚህ ወቅት የሚኖር ከፍተኛ የሆነ የካሎሪ መጠን መቀነስ በሚመነጨው ወተት ብዛትም ሆነ ጥራት ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ስለሚኖር በተቻለ መጠን አመጋገብ ላይ ገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ጤናማ እና የተስተካከለ አመጋገብን መከተል
የምታጠባ እናት የምትመገበውን ምግብ አይነት በማብዛት እንዲሁም በማመጣጠን ጤናማ የሆነ የሰውነት ክብደት እንዲኖራት ማድረግ ትችላለች፡፡ ፕሮቲን፣ ቅባት እንዲሁም ሀይልና ሙቀት ሰጪ ምግቦችን አመጣጥኖ መመገብም እረዥም ሰአታትን ካለምግብ መቆየት እና ሰውነት የሚፈልገውን ንጥረ ነገር ማግኘት ይቻላል፡፡
የምትመገበው ምግብ ሁሉንም የምግብ አይነቶች ያካተተ ማድረግ ሰውነቷ እንዲሁም የምታጠባው ህፃን የሚያስፈልገውን ቫይታሚን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን እንዲያገኝ ለማድረግ ይረዳል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን የምትመገበው ምግብ በውስጡ በሚይዘው ንጥረነገርም ሆነ በአይነቱ የተለያየ መሆን ይኖርበታል፡፡
ቅባት ያላቸው ምግቦችን መመገብ
የቅባት መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦች የህፃኑ የአተነፋፈስ ስርአት ላይ የሚያስከትሉት ችግር እንዳለ ሆኖ እናቲቱም በልብ ህመም ወይም ሌሎች በሰውነታችን ያለው የኮሌስትሮል መጠን መጨመር ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ የጤና እክሎች ሊያጋልጣት ይችላል፡፡ ስለዚህ አንዲት የምታጠባ እናት አነስተኛ የቅባት መጠን ያላቸውን ምግቦች በመመገብ ሰውነቷ ወተት ለማመንጨት የሚያስፈልጉትን ንጥረነገሮች ማሟላት ትችላለች፡፡ እንደ የወይራ ዘይት፣ አሳ፣ አቮካዶ፣ ኦቾሎኒ የመሳሰሉት ለዚህ ተጠቃሽ የሚሆኑ የምግብ አይቶች ናቸው፡፡
የጡት ወተት እንዳይመረዝ ጥንቃቄ ማድረግ
ማንኛዋም ጡት የምታጠባ እናት የጡት ጫፍ አካባቢ የፀዳ መሆኑን ማረጋገጥ እንዲሁም የምትመገበው ምግብ ወተቱን በሌሎች አላስፈላጊ ኬሚካሎች እንዳይበከል ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባታል፡፡
የሚከተሉት ነጥቦች የጡት ወተት በሌሎች አላስፈላጊ ኬሚካሎች እንዳይበከል ጥንቃቄ ለማድረግ ይረዳሉ፡-
የተለያዩ የምግብ አይነቶችን መመገብ (የምታጠባ እናት አንድን የምግብ አይነት አዘውትራ የምትመገብ ከሆነና ያ ምግብ በውስጡ አላስፈላጊ ኬሚካሎችን የያዘ ከሆነ የጡት ወተት የመበከል እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡)
የትኞቹ ምግቦች ለጡት ወተት መበከል ምክንያት እንደሆኑ መለየት
የአትክልት እና ፍራፍሬ ምግቦችን በሚገባ አጥቦ መመገብ
አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች ምግቦችን በትኩስነታቸው መመገብ
የመጠጥ ውሀን አፍልቶ መጠቀም ወይም የተጣራ ውሀን መጠጣት  
የአልኮል መጠጦችን መቀነስ
የምታጠባ እናት የምትወስደውን የአልኮል መጠን መቀነስ ይኖርባታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እናቲቱ የምትወስደው አልኮል በቀጥታ ወደ ጡት ስለሚሄድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በህፃኑ ጤንነት ላይ የሚያስከትለው ተፅኖ ይኖራል፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት እናቲቱ የአልኮል መጠጥ ከወሰደች በኋላ ባሉት አራት ሰአታት ውስጥ የምታጠባ ከሆነ ወደ ህፃኑ የሚደርሰው ወተት በውስጡ አልኮል የያዘ ነው፡፡ ይህም ህፃኑ ነጭናጫ እና እንቅልፍ አልባ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል፡፡
አልኮሉ ከሰውነቷ ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ሁለት ወይም ሶስት ሰአታትን ሊወስድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ እንደወሰደችው የአልኮል መጠን እና አይነት ይለያያል ስለዚህ አንዲት እናት አልኮል ከመውሰዷ በፊት ለቀጣዩ ሁለት ወይም ሶስት ሰአታት ማጥባት አይኖርባትም፡፡      
ብዙ ውሀ መጠጣት እና የአነቃቂ ንጥረነገሮችን ፍጆታ መቀነስ
ጡት የምታጠባ እናት በቀን ወደ አስራስድስት ብርጭቆ ፈሳሽ ያስፈልጋታል፡፡ ይህም ከምትመገበው ምግብ የምታገኘውን ፈሳሽ የሚጨምር ሲሆን በተለያየ ግዜ የሚኖራትን የውሀ ጥም ተከትሎ መጠጣት የሰውነቷን የውሀ ፍላጎት ለማርካት አይነተኛ መንገድ ነው፡፡ ሽንት ንፁህ እና ፈዛዛ ቢጫ ቀለም ካለው በሰውነቷ በቂ የውሀ ክምችት መኖሩን አመላካች በመሆኑ በሰውነቷ ያለው ፈሳሽ  በቂ መሆኑን በዚህ መከታተል ትችላለች፡፡
በተቃራኒው የህክምና ባለሙያዎች ጡት የምታጠባ እናት በቀን ውስጥ የምትወስደው የአነቃቂ መጠጥ እና ምግቦች ፍጆታ ከ300/ሚሊግራም መብለጥ እንደሌለበት ይመክራሉ፡፡ ይህም እንደ ቸኮሌት፣ ሻይ፣ ቡና እንዲሁም አንዳንድ የለስላሳ መጠጦችን ይጨምራል፡፡ 

Read 19898 times