Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 January 2012 14:51

ላም የሌለው ጉረኛ አፉን በወተት ይጉመጠመጣል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጐልማሣ ፈረስ መጋለብ በጣም ያምረውና ወደ ገበያ ፈረስ ሊገዛ ይሄዳል፡፡ ገበያ ውስጥ ብዙ ፈረስ የያዘና አንድ ፈረስ ብቻ የያዙ ሁለት ነጋዴዎች አሉ፡፡ ወደ ባለ ብዙው ፈረስ ይጠጋና፤

“ይሄ ስንት ነው?” ይለዋል፡፡

ባለብዙው ፈረስ - “ሁለት ሺ”

ፈረስ ገዢ - “ይሄስ?”

ባለብዙው ፈረስ - “ሁለት ሺ ሦስት”

ፈረስ ገዢ - “ይሄኛውስ?”

ባለብዙው ፈረስ  “ሁለት ሺ አራት”

ፈረስ ገዢ - “እንዴ አንዴ አንድ ዋጋ ከተናገርክ መቀጠል ነው ማለት ነው ሥራህ?”

ባለብዙው ፈረስ - “ጊዜው ነው ጌታዬ፡፡ የሚጨምር ነው እንጂ የሚቀንስ ነገር የለም”

ፈረስ ገዢው ይተወውና አንድ ፈረስ ወዳለው ነጋዴ ይሄዳል፡፡

ፈረስ ገዢ - “ይሄ ፈረስ ስንት ነው ዋጋው?”

ባለ አንድ ፈረስ “ስድስት ሺ”

ፈረስ ገዢ - “አሃ እዛኮ በሁለት ሺ አግኝቻለሁ”

“ባለአንድ ፈረስ - “እኔ ሻጭ ነኝ፡፡ ይዤ እመወጣው አንድ ፈረስ ነው እሱን ሸጬ መግባት ነው አላማዬ”

ፈረስ ገዢ - “ታዲያ በጣም አስወደድከዋ?”

ባለ አንድ ፈረስ - “የፈረሱ አይነት ነው፡፡ እንደምታየው ሠንጋ ፈረስ ነው የዚህ ዓይነት ፈረስ የትም አታገኝ”

ፈረስ ገዢ - “ጥሩ፡፡ እገዛሃለሁ፡፡ ግን ልዩ ጥቅሙ ምንድነው?”

ባለአንድ ፈረስ - “እሱን ስትጋልበው ታየዋለህ”

ፈረስ ገዢ - “መልካም”

ፈረሱን ገዝቶ ይሄዳል፡፡

ቤቱ እንደደረሰ የግልቢያ ልብስ ይቀይርና ፈረሱ ላይ ወጥቶ ወደሠፈሩ ገና ብቅ ሲል፤ በሀብታምነቱ የሚያውቁት የሠፈሩ ሰዎች፤

“ፈረስ ማለት ይሄ ነው እንጂ!”

“ለእኛም ቢሆን ለአይናችን እንዲህ ያለ ፈረስ አይተን አናውቅምኮ፤ አለፈልን ዘንድሮ”

“የተጋጋጠ ፈረስ ለጋሪ እያሰለፉ ሲያሰቃዩን ከርመው ዛሬ ዕውነተኛ ፈረስ መጣ”

የማይሰጥ ዓይነት አስተያየት የለም፡፡ ጉድ ተባለ!

ባለፈረሱ መጋለብ ጀመረ፡፡ ለካ ፈረሱ አልተገራ ኖሮ አንዴ ሽቅብ ይዘላል፡፡ አንዴ ሳያስበው ሽምጥ ይሮጣል፡፡ በልጓም ቢለው፣ በእግሩ ቢለው፣ ከኮርቻው ቢነሳ፣ ወደፊት ቢያጐነብስ አልቆም አለ፡፡ ሩጫውን ቀጠለ፡፡

አንድ ጋላቢውን የሚያውቅ ወዳጁ ከቤቱ ሲወጣ አየውና፤

“አያ፤ ኧረ ወዴት ነው የምትሮጠው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡

ጋላቢውም፤

“እኔ ምን አውቃለሁ ፈረሱን ጠይቀው” አለው፡፡

*   *   *

መልክና ቁመናውን ዓይተን ያልተገራ ፈረስ ከመግዛት ይሰውረን፡፡

“ስትጋልበው ታየዋለህ” እየተባልን የወጣንበት ፈረስ መጨረሻው አያምርም፡፡ በጊዜ ያልመከርንበት ገበያ ኪሣራው ብዙ ነው፡፡ ብቸኛ ሽያጫችንን ለማሳመር ብለን ያወዳደስነው ያልተጠና ነገር ጉዳቱ በርካታ ነው፡፡ የዛሬ ባለሀብትነታችንን አይቶ የሚያሞግሰን ሁሉ ዕውነተኛ ደጋፊ ነው ብለን ማሰብ አደገኛ ነው፡፡ ከሚጨምር ዋጋ ያድነን! ካልተገራ መመሪያ፣ ካልተገራ አዋጅና ካልተገራ ተከታይ ይሰውረን!

መተካካት የጊዜው ጥያቄ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ጥያቄው የሚከብደው ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች ላይ ነው፡፡ አንደኛው የመተካኪያው መስፈርት ላይ የሚደረግ ጥንቃቄ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ፤ ይተኬና አይተኬ የሚባሉ (dispensable and indispensable) ግለሰቦች ካሉስ የሚለው ነው፡፡ ያለችሎታ፣ ያለ ዕውቀት፣ ያለ ልምድ እንዳንተካካ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡

የሥልጣን ፖለቲካ ልሂቃን እንዲህ ይላሉ፡፡ መቀበል አለመቀበል እንደየመሪው ይለያያል፡፡

“ብቸኛ ተፈላጊ ለመሆን ህዝብ ባንተ እንዲተማመን እንዲመካ አድርግ፡፡ ህዝቦች ደስታና ብልጽግናን ካንተ ወዲያ ሊያገኙ እንደማይችሉ አድርገህ ቃኛቸው፡፡ ካንተ በላይ ሊያደርጋቸው የሚችል ዕውቀት አትስጣቸው” ታዋቂው የፕሬዚዳንት ኒክሰን አማካሪ ሔንሪ ኪሲንጀር ራሱን ያቆየው እዛም እዛም በሚነሱት ጉዳዮች ውስጥ ስለሚገባ እሱን ማጣት ለፕሬዚዳንቱ በጣም ጐጂ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

አይተኬ በመሆኑ ነው፡፡ አይተኬነት የራሱ ችግር አለው፡፡ አጠቃላዩ ዕምነት ግን አይተኬ ነኝ የሚል ግለሰብ ውሎ አድሮ አይነኬ ነኝ ማለቱ ነው፡፡ ከእኔ በላይ ላሣር ማለቱ ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን!

ፀሐፍት “የኮለምበስ ስትራቴጂ” የሚሉትን አንርሣ፡፡ “ሁሌ ጠንካራ ጥያቄ ይኑርህ፡፡ የራስህን ትልቅ ዋጋ አስቀምጥ፡፡ አታወላውል፡፡ በኩራት ከፍተኛው ደረጃ ካለው ሰው እኩል ቁም፡፡ አንድ ስጦታ ለበላይህ ስጥ” ይህን ስትራቴጂ የሚጠቀሙ አያሌ ናቸው፡፡ አንዱ የሙስና በርም ይሄ ነው፡፡ እኩያ ሙሰኞች እኩያ የፖለቲካ አቅም እየፈጠሩ የሚከስቱት ነው፡፡ ህንፃዎቻችን፣ መኪናዎቻችን፣ መሬቶቻችን በምንና እንደምን ተገኙ ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡

መጠንቀቅ ያለብን፤ ማኪያቬሊ እንደሚለው፤ ከመወደድ መፈራት ይሻላል፡፡ ምነው ቢሉ ፍርሃትን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ መውደድን ግን በፍፁም ለመቆጣጠር አይቻልም፤” ከሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች የሚመኩብን አብረውን ለመሆን ካላቸው ፍቅር ከሚሆን ይልቅ እኛን በማጣት ከሚፈጠርባቸው ፍርሃት የተነሳ ቢሆን ይሻላል - እንደማለት ነው፡፡ ይሄ በራሱ አደጋ እንደሚሆን ልብ እንበል፡፡

ሥልጣን ላይ ለመቆየት ከሚጠቀሱ ዘዴዎች መካከል አንድ ፈረንጆች የሚጠቅሱት አባባል አለ፤ “ኦርጅናሌ ሀሳብህን ለሚቻቻሉህ ጓደኞችና ልዩ ፍጡር መሆንህን ለሚያደንቁ ወዳጆችህ ብቻ አማክር” ይላሉ፡፡ ዕውነቱ ግን ህዝቡ ከልቡ ያልመከረበት ነገር ፍሬ - አልባ መሆኑ ነው፡፡ ህዝብን ማማከር ሲባል፤ ነገር ካለቀ ከደቀቀ በኋላ መሆን የለበትም፡፡ ፈረንጆቹ “የሞተ ፈረስ መጋለብ” የሚሉት ይሆናልና (Riding a dead horse) የተበላ ዕቁብ የሚለው ነው አበሻ፡፡ ባለቀ ጉዳይ ላይ መምከር አንድም “እንዳያማህ ጥራው” ነው፡፡ አንድም “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ነው፡፡

ሞንጐላውያን ቻይናን በወረሩ ጊዜ መሪያቸው ጄንጂስ ካን፤ ከሁለት ሺ ዓመት በላይ የቆየው የቻይና ባህል እሴት፤ አይታየውም ነበር፡፡ ይልቁንም ለፈረሶቹ ግጦሽ የሚሆን በቂ ሣር ያልበቀለባት አገር በመሆንዋ፤ “ቻይናውያንን ከምድረ ገጽ አጥፍቶ ሣር ማብቀል ይሻላል” የሚል አቋም ነበረው፡ ሆኖም ብልሁ አማካሪው ዬሎ ቹሳይ “አገሪቱን ከማጥፋት ይልቅ እዚያ የሚኖረውን እያንዳንዱን ነዋሪ ግብር ብታስከፍለው ያገር ሃብት ትሰበስባለህ” አለው፡፡ ካን አማካሪው ያለውን ፈፀመ፡፡ ቀጥሎ ኬይፌንግ ከተማን ወረረና ነዋሪውን ላጥፋው አለ፡፡ አማካሪው ቹሳይ “አይሆንም የቻይና ጥበበኞችና መሀንዲሶች ተሰብስበው የሚገኙት እዚህ ነውና ከምታጠፋቸው ተጠቀምባቸው” አለው፡፡ ጄንጂስ ካን አማካሪው የነገረውን አደረገ፡፡ ተጠቀመ፡፡ ወገናዊነት በሌለበትና ኢፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ግብር ማስገባት አግባብነት አለው፡፡ ምሁራንንም በአግባቡ መጠቀም ሥልጣኔ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን እንደዬሉ ቹሳይ ያለ አማካሪ ያሻል፡፡ መካር አሳስቶኝ ከሚባልበት ዘመን መውጣት ይጠበቅብናልና!

በሀገራችን ዴሞክራሲ ሙሉ በሙሉ እንደሰፈነ የሚያስመስሉ አያሌ አማካሪዎች ናቸው፡፡ ልማት ያጣጠባት፤ ፍትህ የበለፀገባት፤ መልካም አስተዳደር ቤት ደጁን ያጣበበባት አገር ናት እያሉ፤ ራሳቸው ግን ያልለሙ፣ ከኢፍትሐዊነት ያልፀዱ፣ ያስተዳደር ጉድለት የሚፈጽሙ፣ ግን በአደባባይ ችሎት ስለንጽህናቸው የሚጮሁ አያሌ ናቸው፡፡ “ላም የሌለው ጉረኛ አፉን በወተት ይጉመጠመጣል” ማለት እኒሁ ናቸው፡፡

 

 

 

 

Read 3914 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 14:55