Monday, 11 May 2015 09:22

ልባችን እንደ ኮምፒዩተር “ሴቭ” ያደርግ ይሆን?

Written by  ኑርሁሴን
Rate this item
(6 votes)

ኬሊ የስምንት አመት ታዳጊ ነች፡፡ ወደ ሆስፒታል የገባችው የልብ ዝውውር ቀዶ ጥገና (ትራንስፕላንት) ለማድረግ ነው፡፡ የተቀየረላት ልብ የተወሰደው ደግሞ አንዲት በሰው ከተገደለች የ10 ዓመት ልጅ ነበር፡፡ ኬሊ የተሳካ የልብ ዝውውር አድርጋ ከሆስፒታል ከወጣች በኋላ ግን ህይወቷ በአስፈሪ ህልሞች ተዘበራረቀ። በህልሞቿ የምታየው ደግሞ ልብ የሰጠቻትን የ10 ዓመት ልጅ ገዳይ ነበር። የኬሊ አስጨናቂ ህልሞች እውን መሆናቸው የተረጋገጠው ግን እናቷ ወደ ስነልቦና ባለሙያ ከወሰደቻት በኋላ ነው፡፡ እስከዚህ ቅጽበት ድረስ የልብ ሰጪዋ የ10 ዓመት ታዳጊ ገዳይ አይታወቅም ነበር። ነገር ግን የኬሊ የሌሊት ህልሞች ተሰባስበው ስለገዳዩ አስገራሚ መረጃዎችን ሰጡ፡፡ ጊዜውን፣ መሳሪያውን፣ ቦታውንና የገዳዩን ልብስ ሳይቀር የኬሊ ህልሞች አጋለጡ። በመሆኑም ፖሊስ በዚህ መረጃ ተንተርሶ ገዳዩን በቀላሉ አድኖ በመያዝ ለፍርድ ሊያቀርበው ቻለ፡፡
በሜይ 29፣ 1988 ዓ.ም ክሎር ሲልቪያ የምትባል አንዲት አሜሪካዊት በያሌ ሆስፒታል ውስጥ የልብ ዝውውር ተደረገላት፡፡ ልቡ የተሰጣት እዚያው አሜሪካ፣ ማይን ውስጥ ከሚኖር የ18 ዓመት ወጣት ነበር፡፡ ይህን ጨምሮ በሞተር ሳይክል አደጋ እንደሞተም ለሲልቪያ ተነግሯታል፡፡ ሲልቪያ ቀዶ ጥገና ካደረገች ከቀናት በኋላ ግን ያለ ልማዷ ቢራ የመጠጣት ፍላጐት እንዳደረባት ተናገረች፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ልትቆጣጠረው ያልቻለችው የዶሮ ስጋ አምሮት አሰከራት፡፡ በዚህ ምክንያት KFC የተባለው የዶሮ ሬስቶራንት ማዘውተር ጀመረች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማትወደውን ቆስጣ መብላትና ቲም ኤስ ስለተባለ ግለሰብ ዘወትር ህልም ታይ ነበር። ሲልቪያ ራሷ ባደረገችው ጥረትና ማይን ውስጥ በሚታተም ጋዜጣ አማካኝነት እየተረዳች ልብ የሰጣት ሰው ቲም እንደሚባል አረጋገጠች፡፡ የቲም ቤተሰቦችን ከተዋወቀች በኋላ፤ ልብ የሰጣት ቲም የዶሮ ስጋ፣ ቆስጣና ቢራ እንደሚወድ አወቀች። በኋላ ላይ ሲልቪያ ይህንን ጨምሮ አጠቃላይ ታሪኳን “A Change of Heart” በሚል መጽሐፍ አሳተመችው። የልብ ዝውውር የተደረገላቸው በርካታ በሽተኞች ከልብ ተከላ በኋላ አጠቃላይ ሰብዕናቸው፣ ባህሪያቸው፣ ፍላጐታቸውና አመጋገባቸው እንደተቀየረ ራሳቸው መስክረዋል፡፡ በቬና ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ውስጥ የቀዶ ጥገና ክፍል ሐላፊ የሆኑት ዶ/ር ቤንጃሚን በንዝል እንደተናገሩት፤ 47 የልብ ተከላ ካደረጉ ህሙማን ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት ሰብዕናቸው ተቀይሯል፡፡ በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች ደግሞ ከሶስት ህሙማን መካከል አንዱ የልብ ተከላን እንደሚፈራ ጠቁመዋል፡፡ በ1999 ዓ.ም አንዲት እንግሊዛዊት ወጣት እሷ ሳትፈልግ በዶክተሮችና በቤተሰቦቿ አማካኝነት ልብ ተከላውን እንድታደርግ መገደዷ ተገልጿል፡፡ የልጅቱ እንቢተኝነት የመነጨው ደግሞ በልብ ዝውውሩ ምክንያት የራሷን ማንነት እንዳታጣ ከመፍራት ነበር።
በልብ ተከላ ታሪክ ውስጥ በጣም አስገራሚ የሆነው የአሜሪካዊው ሶኒ ግራሐም ነው፡፡ ግራሐም የሌላ ሰው ልብ እንደሚያስፈልገው በዶክተሮች ከተነገረው በኋላ፣ ቴሪ ኮተል ከተባለ ራሱን በሽጉጥ ካጠፋ ግለሰብ ልብ ተወስዶ ተተከለለት፡፡ ግራሐም በ1995 ዓ.ም የልብ ተከላውን ቀዶ -ጥገና ካደረገ በኋላ ልብ ከሰጠው ኮተል ሚስት ጋር ተገናኘ፡፡ ግራሐም፣ ቼርሊ ከተባለችው የኮተል ሚስት ጋር በፍቅር ስለወደቀ እርሷን አግብቶ መኖር ጀመረ። ከ12 ዓመታት በኋላ ግን ግራሐም ልክ እንደ ኮተል ራሱን በሽጉጥ አጠፋ፡፡ የሚያስገርመው ግን ቼርሊ ለሁለተኛ ጊዜ የህይወት አጋሯን ማጣቷ ሳይሆን፣ ልብ የተቀያየሩት ሁለቱ ባሎቿ ራሳቸውን በተመሳሳይ መንገድ አጥፍተው መሞታቸው ነበር፡፡ የብሪታንያው “ዴይሊ ሜል” ጋዜጠኛ በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ታሪክ ዘግቦ ነበር፡፡ በጣም ደካማ ክህሎት የነበረው ዘገምተኛ ማናጀር ከሌላ ሰው ልብ ተወስዶ ከተተከለለት በኋላ ድንቅ የሚባል የአርት ችሎታን ተጎናፅፏል፡፡ ታሪኩን አስገራሚ ያደረገው ደግሞ ልብ የሰጠው ሰውዬ አርቲስት መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነበር፡፡ ይህን የሰብዕና መለዋወጥ በተመለከተ በርካታ ሀኪሞች የተለያዩ አስተሳሰቦችን አንፀባርቀዋል፡፡ አንዳንድ የስነ ልቦና ባለሙያዎች የተቀየረው ልብ “አንድ አካል” መሆኑን መርሳት የለብንም ይሉናል፡፡ ይህ አካል (ልብ) በሰጪው ሰውዬ ውስጥ ከሚገኙ ማንኛውም አካል በላይ የሳይኪክ ኢነርጂን የያዘ ነው። ባዮሎጂ ባለሙያዋ ሊያል ዋትሰን እንደምትለው የሰውነት ክፍላችን አንዱ አካል የሆነው ልባችን፤ የባህሪያችንን አሻራና ስሜታችንን የያዘ ነው፡፡ ሊያል ዋትሰን ጨምራ ስትናገር፤ ከኛ ጋር ንክኪነት ያላቸው የሰውነት ክችሎቻችን በሙሉ ባህሪያችንን የሚይዙበት እድል አላቸው፡፡
ብዙዎቹ የህክምና ሰዎችና የስነ - ልቦና ባለሙያዎችን ያስማማው ግን “ሴሉላር ሜሞሪ” የሚለው ነው፡፡ ሴሉላር ሜሞሪ ራሱን የቻለ ፅንሰ - ሐሳብ ሲሆን ሰብዕናችንንና ማስታወሻዎቻችንን መዝግቦ የሚይዘው አእምሯችን ብቻ አይደለም ይላል፡፡ ማስታወስ ራሱን የቻለ ሒደት እንደመሆኑ መጠን በሌሎች የሰውነታችን ሲስተሞች ውስጥም ሊፈጠር ይችላል፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ልባችን ያሉ የሰውነት ክፍሎች የአእምሮ ተግባር የሆነውን ማስታወስን በውስጣቸው ሊይዙ ይችላሉ ይላል - የሴሉላር ሜሞሪ ፅንሰ - ሐሳብ፡፡ በእርግጥ ይህ ፅንሰ ሐሳብ አዲስ አልነበረም። በምናባዊ የስነ ጽሑፍ ስራዎቹ የሚታወቀው ማውሪስ ሬናርድስ፣ በ1800ዎቹ ዓ.ም የሴሉላር ሜሞሪ ፅንሰ ሐሳብን በልቦለዱ ውስጥ አንፀባርቋል። በእርግጥ የሬናርድስ አስተሳሰብ፣ እንደ እግርና እጅ ባሉ የውጭ አካሎቻችንም የሴሉላር ሜሞሪ ፅንሰ - ሐሳብ ይሰራል ባይ ነው፡፡ ሬናርድስ “Les mains d’orac” በተባለው ልቦለዱ ውስጥ አንድ የፒያኖ ተጨዋች ገፀ ባህሪ ይገኛል፡፡ ይህ ሰው አንድ እጁን ካጣ በኋላ የሌላ ሰው እጅ ተገጠመለት። የተገጠመለት እጅ ገዳይ ከነበረ ሰው የተወሰደ በመሆኑ ፒያኖ ተጨዋቹም ሰው የመግደል ዝንባሌን ሲያሳይ ሬናርድስ በልቦለዱ ውስጥ አሳይቷል፡፡ በእርግጥ ይህ ታሪክ እኛ ከላይ ከጠቀስናቸው እውነተኛ ታሪኮች ጋር የሚመደብ ባይሆንም (ልቦለድ በመሆኑ) ሴሉላር ሜሞሪን በቀላሉ ለመግለፅ ተስማሚ ሊሆን ይችላል፡፡ አብዛኞቹ የሴሉላር ሜሞሪ ጥናቶች በሳይንቲስቶች የተረጋገጡ ናቸው፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ ሆስፒታሎች የልብ ሰጪዎችን  ቤተሰቦች በመደበቃቸው አብዛኛዎቹ ታሪኮች ምስጢር ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ታሪኮቹ ቢገኙ እንኳን ስምና አድራሻቸው አብረው አልሰፈሩም፡፡ በዘመናዊ የህክምና አለም ውስጥ ልብን ጨምሮ ሌሎችን የሰውነት ክፍሎች ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ማዘዋወር የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡ ልክ ከላይ እንደጠቀስናቸው አይነት ታሪኮች፣ አሁንም ቢሆን ቀዶ ጥገና አድርገው የሚነሱ በርካታ ህሙማን የተለየ ባህሪ፣ ጣዕም፣ አስተሳሰብና ሌሎች እንግዳ ሰብዕናን እንደሚያንፀባርቁ በሴሉላር ሜሞሪ ጥናት ተደርሶበታል። ይህ ደግሞ ህክምናው ከሞት ሊያድን ይችል ይሆናል እንጂ ተፈጥሯዊ አለመሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በተጨማሪም የእያንዳንዱ ሰው የሰውነት ክፍል የራሱ ባህሪ፣ ሰብዕና እና ስሜት እንዳለው ከማረጋገጡ በላይ የሁሉም ሰው የሰውነት ክፍሎች የተፈጠሩት በልካችን ተሰፍተው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
በአንድ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች የተሰበሰበው የጣት አሻራ አንድም መመሳሰል እንደሌለው ተገልፆ ነበር፡፡ አንድ ሚሊዮን ሰዎች፣ አንድ ሚሊዮን የተለያየ የጣት አሻራ እንዳላቸው ስንመለከት ማንም፣ ማንንም እንደማይመስል እንገነዘባለን፡፡ የልብ ተከላ ታሪኮችም የሚናገሩት ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ የልብ አሻራ እንዳለው ነው፡፡ በእርግጥ ታሪኮቹ ያስተማሩን ትልቁ ነገር በልቦቻችን ውስጥ ትንንሽ አእምሮዎች መኖራቸውን ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ከልብ ተከላ በኋላ የሚከሰቱት የባህሪ ለውጥና የሰብዕና መዘበራረቅ መንስኤ፣ ምናልባት የሰዎች ትክክለኛ የልብ አሻራ ተወግደው በምትኩ የማይመለከታቸው አሻራዎች በመግባታቸው ይሆናል፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ልባችን የራሱ አእምሮ እንዳለው መገንዘባችን ነው። የሐገሬ ሰው “ይሄ ልበ ቢስ!” የሚለው ቀደም ብሎ የሴሉላር ሜሞሪ ሳይንስ ገብቶት ይሆን? - ሰላም!!

Read 3972 times