Saturday, 16 May 2015 11:22

“...ሁለቱም ፆታዎች በእኩል ሊጠቁ ይችላሉ...”

Written by  ዮዲት ባይሳ (ከኢሶግ)
Rate this item
(14 votes)

 በመራቢያ አካላት ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች እንዲሁም ኤችአይቪን ጨምሮ በግብረ ስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚተላለፉ የተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች ሰፊውን የስነተዋልዶ ጤና ችግር ይሸፍናሉ፡፡
በየአመቱ በአለማችን ላይ ቁጥራቸው 500/ ሚሊዮን የሚገመት ሰዎች በጎኖሪያ፣ ሲፊሊስ እንዲሁም ትራይኮሞኒያሲስ በሚባሉ በግብረስጋ ግንኙነት አማካኝነት በሚተላለፉ የአባለዘር በሽታዎች እንደሚጠቁ 290/ ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶች ደግሞ በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ እንደሚያዙ የአለም የጤና ድርጅት በ2013/ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በመራቢያ አካላት ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖችን እና የአባላዘር በሽታዎችን በተመለከተ የኢንፌክሽኖቹን አይነት እና ምልክት እንዲሁም የትኛውን የመራቢያ አካል ያጠቃሉ በሚለው ዙሪያ አንድ ፅሁፍ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡
ዛሬም ሳምንት በይደር ያቆየነውን በመራቢያ አካላት ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖችን እንዲሁም የአባላዘር በሽታዎችን እንዴት አስቀድሞ መከላከል ይቻላል? ተከስቶስ ሲገኝ ምን መደረግ አለበት? የሚለውን እናያለን።
አብዛኞቹ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጡት ኢንፌክሽኖች ከግል ንፅህና ጉድለት ወይም ተገቢውን የንፅህና አጠባበቅ ባለመከተል የሚከሰቱ በመሆናቸው ተገቢውን የንፅህና አጠባበቅ በመከተል መከላከል እንደሚቻል በብራስ የእናቶች እና ህፃናት ሆስፒታል የፅንስና ማህፀን እስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር መብራቱ ይገልፃሉ፡፡
“...ባክቴሪያ በማንኛውም ሰአት ይከሰታል፡፡ የሚመጣውም የግል ንፅህና አጠባበቅ ስልትን ባለማወቅ ብቻ ነው፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ወደ ሰውነታችን የሚገቡ ባክቴሪያዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ባክቴሪያዎች በመነካካት እና በመተሻሸት ወይም በላብ አማካኝነት ወደ ሌላ የሰውነታችን ክፍል በመሄድ እና በመራባት ኢንፌክሽን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ነው እነዚህን በባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች የግል ንፅህናን መጠበቅ ብቻ መከላከል ይቻላል ያልኩት፡፡...”
የአልኮል መጠጦችን እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ ሱሶችን መቀነስ በግብረስጋ ግንኙነት ከሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች እና የአባላዘር በሽታዎች የሚኖረውን ተጋላጭነት መቀነስ ይቻላል፡፡ ይህም የአልኮል መጠጦችን አብዝቶ መውሰድ እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ ሱሶችን መጠቀም በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት ሊደረጉ ከሚገባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች ስለሚያዘናጉ እንደሆነ ዶክተር መብራቱ ይናገራሉ፡፡
“...ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የግል ንፅህናን መጠበቅ እና ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነትን አለማድረግ ዋነኛው የመከላከያ መንገድ ነው፡፡ በግብረ ስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚከሰቱትን ኢንፌክሽኖች በተመለከተ ደግሞ ጥንቃቄ የተሞላበት የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ክፍተቶች በሚያጋጥሙበት ግዜ ኮንዶም መጠቀም በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ጥንቃቄ ማድረግ እና ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ አለመፍቀድ ነው። በተለያየ አጋጣሚ ክፍተት እንዲፈጠር ከሚያደርጉት ውስጥ ነገሮች መካከል አንዱ ሱሰኝነት ነው፡፡ መጠጥ፣ ጫት እና ሌሎች ሱሶችም አሉ እነዚህ ሱሶች ነገሮችን የማገናዘብ አቅምን ስለሚያጠፉ ከግንዛቤ ውጪ የሆኑ ስሜታዊ ነገሮችን ለማድረግ ሊገፋፉ እና ሊያደፋፍሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ከእነዚ ሱሶች መራቅ ተገቢ ነው፡፡...”
በግብረ ስጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚከሰቱትን ኢንፌክሽኖች በተመለከተ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል ያሉትም አለ፡፡
“...ግብረስጋ ግንኙነት ላይ አሁንም ደግሜ ትኩረት እንዲሰጥበት እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው ትዳር ከያዘ በኋላ ከትዳሩ ውጪ ሌላ ቦታ መሄድ የለበትም። ያ ትዳርም ጤናማ ትዳር መሆን አለበት፡፡ በዚህ በምንነጋገርበት የጤና ጉዳይም ይሁን በሌላ ጤናማ እና ሰላማዊ የትዳር ህይወት እንዲኖረን ከፈለግን እነዚህ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡...”
ቀደም ሲል ከተጠቀሱት የመከካላከያ መንገዶች በተጨማሪ የአመጋገብ ስርአታችን በሽታን በመከላከል እረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል  ባይ ናቸው ዶክተር መብራቱ፡፡  
“...ለሰው ልጅ ዋነው መድሀኒት ምግብ ነው፡፡ በተቻለ መጠን ከሁሉም የምግብ አይነት ትንሽ ትንሽ መመገብ ያስፈልጋል፡፡ በእኛ ሀገር በባህል ስጋን አዘውትሮ መመገብ ልክ እንደ ጤነኛ የአመጋገብ ስርአት ይወሰዳል፡፡ ነገርግን ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ስጋ ከፍተኛ የሆነ ፕሮቲን ስላለው ለሰውነታችን ጠቃሚ ቢሆንም ሌሎችንም የምግብ አይነቶች መመገብ ሰውነታችን ብዙ አይነት ንጥረገነሮችን በተመጣጠነ መልኩ እንዲያገኝ ያደርጋል። ስለዚህ በእለት ተእለት አመጋገባችን ላይ ከሁሉም የምግብ አይነቶች ትንሽ ትንሽ ማካተት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይ ቫይታሚን ሊሰጡ የሚችሉ አትክልት እና ፍራፍሬ ምግቦችን ማዘውተር ይመረጣል፡፡
በሀገራችን ውድ ያልሆኑ ብዙ የአትክልት እና ፍራፍሬ አይነቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጎመንን መጥቀስ ይቻላል። ጎመን በጣም ውድ አይደለም ግን ብዙ ሰው ከጎመን ይልቅ ውድ የሆነውን ስጋን ይመርጣል፡፡ ልክ እንደ እስፒናች፣ ቲማቲም፣ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ብርቱካን እና ሙዝ ያሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎች በውስጣቸው ከፍተኛ የቫይታሚን እንዲሁም የአይረን መጠን ስላላቸው ጠቀሜታቸው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ሙዝን ብንመለከት ሙዝ በውስጡ ካልሺየም፣ አይረን  እና ቫይታሚን ስላለው ከፍተኛ ሀይል ይሰጣል፡፡ ለዚህ ነው እስፖርት የሚሰሩ ሰዎች ሙዝን የሚያዘወትሩት። ስለዚህ መጀመሪያ ፋርማሲ ሄዶ መድሀኒት ከመግዛት ይልቅ ምግብ ላይ ማተኮር ተገቢ ይመስለኛል፡፡...”
በእርግዝና ግዜ የሰውነት የበሽታ መከላከል አቅም ስለሚቀንስ እርጉዝ ሴቶች ለእነዚህ ኢንፌክሽኖች የሚኖራቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ ነው ይላሉ ዶክተር፡፡
“...እርጉዞች እና ወላድ ሴቶች ለእንደዚህ አይነት ኢንፌክሽኖች የበለጠ ተጋላጮች ናቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በእርግዝና ወቅት የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም በእጅጉ ስለሚቀንስ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ እና የእርግዝና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ሰአት እርግዝናን እንዲሁም በአጠቃላይ ሌሎች የጤና ጉዳዮችን በተመለከተ ብዙ ፅሁፎች እየወጡ ነው ስለዚህ እነሱንም ማንበብ ጥሩ ነው፡፡ ነገርግን አንዳንድ ግዜ ከሙያ ውጪ የሚነበብ ነገር በጣም ሊያደናግር እና ሊያስደነግጥ ስለሚችል ጥያቄ ሲኖር ከባለሙያ ጋር መመካከር ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ በሚያነቡት ነገር ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡...”
አንዳንድ ግዜ ይህ አይነቱ ችግር በባለትዳሮች ላይ ሲከሰት ባል ሚስትን ሚስት ባሏን ለችግሩ ተጠያቂ አድርገው አንዳቸው አንዳቸውን ሲወቅሱ ይስተዋላል። ለመሆኑ እንዲህ አይነት ኢንፌክሽኖች በአንድ ወገን ብቻ የሚከሰቱ ናቸው ወይንስ ሁለቱንም ፆታ በእኩል ያጠቃሉ? ስንል ላነሳንቸው ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡   
“...ሴቷ ብቻ የምትጠቃ ከሆነ ይህንን ነገር ማን አመጣው? የሄ ነገር ከየት መጣ? በግረስጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ነው ካልን አስተላላፊ ከሌለ የሚተላለፍበት ሰው እንዴት ሊይዘው ይችላል? ስለዚህ ለዚህ አጭሩ መልስ ሁለቱም ፆታዎች በእኩል ሊጎዱ እና ሊጠቁ ይችላሉ ነው፡፡...”
እንዲህ አይነት ኢንፌክሽኖች ወይም ተመሳሳይ የጤና ችግር ሲያጋጥም የህክምና ተቋም እስኪደርሱ አንዳንድ ህመሙን ሊቀንሱ የሚችሉ ነገሮችን ከማድረግ ባሻገር ያለ ሀኪም ትእዛዝ መድሀኒት መውሰድ ለሌላ ችግር ሊዳርግ ይችላል ይላሉ ባለሙያው፡፡
“...ህክምናውን በተመለከተ ያሉት ነገሮች ለባለሙያ ቢተው ጥሩ ነው፡፡ እራስን በእራስ ማከም ፈፅሞ አይመከርም፡፡ በዚህ ጉዳይ እረጅም አመት የተማሩ እና በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ከባለሙያዎቹ ጋር ተመካክሮ መድሀኒት መውሰድ ነው እንጂ እራስን በራስ ማከም የበለጠ አደጋ አለው፡፡ መድሀኒት በመድሀኒትነቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ የጎንዮሽ ጉዳትም እንዳሉት መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለዚህ ህክምናውን በተመለከተ ለባለሙያ መተው ጥሩ ነው፡፡...”
ነገር ግን ይላሉ ዶክተር፡-
“...ነገር ግን ህክምና ጋር እስኪደርሱ ድረስ ለጊዜው የሚደረጉ አንዳንድ  ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ፈንገስ እና ተመሳሳይ ኢንፌክሽኖች ተከስተው ከሆነ በጨው ውሀ ወይንም በሎሚ ውሀ መታጠብ ሀኪም ጋር እስኪደረስ ድረስ ትንሽ ትግስት እና ፋታ ይሰጣል፡፡...”
የዛሬውን ፅሁፍ የምናጠቃልለው ዶክተር መብራቱ በመራቢያ አካላት ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖችን እንዲሁም የአባላዘር በሽታዎችን በተመለከተ መታወቅ አለበት ብለው በሚያስተላልፉት መልዕክት ነው፡፡
“...እንዲህ አይነት የጤና ችግር በሚፈጠርበት ግዜ ወንዶች ሴቶቹን መኮነን ወይም ሴቶች ወንዶቹን መኮነን የለባቸውም፡፡ ሁለቱም አብረው የሚኖሩ ጥንዶች ናቸው። እርስ በእርስ በመተሳሰብ ምን ሆኖ ይሆን? ምን ሆና ይሆን? የሚለውን ቀና ነገር በማሰብ እስከ መጨረሻው ድረስ መረዳዳት እና ለችገሩ መፍትሄ መፈለግ እንጂ መጨቃጨቅ ወይም መጣላት ነገሩን ስለሚያባብሰው ቶሎ መፍትሄ አያገኝም፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ ፅኑ የሆነ የመተሳሰብ ስሜት  እንዲኖር እመክራለሁ፡፡...”  




Read 10672 times