Saturday, 28 January 2012 11:39

ከሁለት ምርጫዎች ወግ ምረቃ ጀርባ “ሌላ ወግ”

Written by  ናርዶስ ጂ
Rate this item
(0 votes)

በአቶ በረከት “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ላይ የሂስ ጦሩን የሚመዘው ምነው በዛሳ? ብዬ ጠየቅኩና ወዲያው ምላሹ በአንጐሌ ተንቆረቆረ፡፡ የመንግሥት ባለስልጣን ሆኖ የወግ መፅሐፍ፣ ያውም “የፖለቲካ ወግ” መፃፍ ብርቅ ነው እንዴ? የሚል ጥያቄያዊ ምላሽ ከመስጠቴ በፊት አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ የመፅሐፉ ምረቃ እለት እንድገኝ ምክንያት የሆነውን ባልንጀራዬን ፈጣሪው፣ ውሻ በቁልቁለት የማይጐትተው እንጀራ ይስጠውና ከመፅሐፉ ወግ የበለጠ “ሌላ ወግ” እንድኮመኩም ምክንያት ሆኖኛል፤ እናም፣ ከምረቃው ጀርባ ምን ነበረ? የሚለውን በስሱ ብናወጋስ…

የሀገሬ ሰው “ፖለቲካና ወግ” ይሁን “የፖለቲካ ወግ” (የመስኩ ባለሙያዎች አጥንተው ቢነግሩን መልካም ነው) እየወደደ መጥቷል፡፡ ለነገሩ እኔም እንዳቅሜ፣ “ሰው የፖለቲካ ወግ፣ ጨዋታ እንዴትና ከማን ለመደ?” የሚል የፍልስፍና ጥያቄ አንስቼ ነበር፡፡ እህ! አሁን ይሄ ጥያቄ ግን “ፍልስፍናዊ” ይባላል? ለነገሩ፣ “ፈላስፋ በሌለበት ሀገር፣ አንድም ፍልስፍናዊ ጥያቄ ብርቅ ነው!” ልል ነበር፤ ምላሴ ሳይሆን አእምሮዬ ተንሸዋሮ፡፡

ህዝቡ በፖለቲካ ወግ ፍቅር እያበደ ነው የሚል መላምት ለማርቀቅ የበቃሁት ሸራተን ስደርስ ነው፡፡ አንድ ባልንጀራዬ የመጥሪያ ወረቀቱን ከመቶ ብር ጋር ሰጠኝና፣ “የአቶ በረከት መፅሐፍ ዛሬ 11 ሰዓት ስለሚመረቅ፣ ሸራተን ሂድ… ሸራተንንና ታላላቅ ሰዎችን በቅርበት ማየት ደስታ ይፈጥርልሃል፤ በህይወት ታሪክህም ላይ ይሰፍርልሃል…” ብሎ በሳቁ አጀበው፤ “ሌላማ ምን ታሪክ አለኝ…” በማለት ሳቁን ተጋራሁት፡፡ “መቼም ከመቶ ብር አይበልጥም… መፅሐፉን አደራ ግዛልኝ!” የሚል ትእዛዝም አከለበት፡፡ ሰአት አልፏል ብለው እንዳይመልሱኝ እሮጥኩ - ወደ ሸራተን፡፡ ደረስኩ፣ ሸራተን በር፡፡ ፈራሁ ፍተሻውን፤ አሳየሁ መጠሪያውን፡፡ በርግጥ የፈራሁት አለባበሴን ነው፤ የገረጣው ፊቴ እንኳ፣ ለሀገሩ አሳቢ “ልማታዊ” ወጣት ነው ቢያስብለኝ ነው - ግፋ ቢል አልኩ፡፡

ወግ አብዝቼ ውሌን የምረሳ እንዳይመስላችሁ… እ.እ.. እንዴት ሆኖ! እናም የሸራተኑ ትልቁ አዳራሽ የሚባለው ላሊበላ፣ በታዋቂ ሰዎች፣ በዘፋኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ደራሲዎች፣ ባለሀብቶች… ተሞልቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ነው፣ “ይኼ ሁሉ ወፈሰማይ እዚህ የተገኘው በአቶ በረከት ወይም በኢህአዴግ ፍቅር ነው? ወይስ የፖለቲካ ወግ መጠረቅ ስለሚወድ?” ብዬ ጠይቄ፣ የፖለቲካ ወግ መውደዱ ነው የሚል በህይወት ልምድ የተቀሸረ ምላሽ ሰጠሁ፤ ለራሴ ጥያቄ እራሴ አስቤ መለስኩ፡፡

ወዲያው የመፅሐፍ ምረቃ ዝግጅቱ በአቶ ሴኮ ቱሬ መድረክ መሪነት ተጀመረ፡፡ ታዋቂ የመድረክ ተዋኒያኖች ሳይቀሩ፣ “በዚህ መድረክ ላይ የአቶ በረከትን ሥራ ካላነበብኩ ሞቼ እገኛለሁ እያሉ ነው!” አይነት ቅድመ ጥቆማ በአቶ ሴኮ አስነግረው፣ አቶ በረከት ነፍጥ አንግተው ጫካ በገቡ ጊዜ የገጠሟትን አንድ ርዮታለማዊ ግጥምና ከመፅሐፉ የተቀነጫጨቡ ፅሁፎችን ሲያንበለብሉ አየሁ፡፡ አያችሁ… ህዝቡ የፖለቲካ ወግ ይወዳል የሚለው መላምቴ ልክ ነበር፡፡

በነገራችን ላይ፣ ህዝቡ “የፖለቲካ ወግ ለምን ወደደ?” የሚል ጥያቄ አንስታችሁ ወጌን እንዳታሸብሩ፡፡ በርግጥ “ህዝብ” አስኳሉ ፖለቲካ የሆነ ጭውውት፣ ወግ፣ ወዷል አዎ ወደደ፡፡ ለምን? ኑሮ ስለተወደደ፡፡ እንዴት? መራራ የኑሮ ውድነቱን በሳቅ የሚሸነግልለት አሽሙራዊ የፖለቲካ ወግ ስላለመደ፤ ሰማይ የነካ የኑሮ ውድነት እስከመቼ? ብሎ የማያስጠይቅ ኮሜዲ ፊልም ወደደ፤ መራራን እውነት ለመቀበል ከከበደ… ወዘተ ለመላምቴ ማብራሪያ መስጠት አይቻልም - በርግጥ በተሰጠው ማብራሪያ ላይ “ተሰብስቦ መወያየት” ይቻላል (መወያየት ላይ “መወያየት ብቻ” ተብሎ ተሰምሮበታል)… “የመላምት” እጦት ለገጠማችሁ ተመራማሪዎች፣ ባፀደቅኩት “የመላምት ሊዝ አዋጅ” መሰረት እሸጥላችኋለሁ… አይዟችሁ!

ወዳጆቼ! የወጌን ውል እንዳትረሱ… አሁንም ሸራተን ላሊበላ አዳራሽ ውስጥ ነን፡፡ ከ”የሁለት ምርጫዎች ወግ” ምረቃ ጀርባ… ህዝቤ “ሌላ ወግ” ይመራረቃል… እኔ ከምድረ ታዋቂ ሰው መሃል ስገባ፣ ጨነቀኝ፤ ዘፋኝና ጋዜጠኛ በነቂስ የተገኘ ነው የመሰለኝ፡፡ አንድ ቦታ መቆሜን ትቼ እዘዋወራለሁ፤ የሸራተን ስልጡን አስተናጋጆች ከለስላሳ እስከ ሸካራ መጠጥ አይነት እያዞሩ ነው - ለወጉ ማጣፈጫ፡፡ እኔም ከየአይነቱ እያነሳሁ ጐርጐጭ እያደረግኩ ነው፤ ሌላ ጊዜ እንደማላገኘው ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ በርግጥ ከታዋቂ ሰዎቹ መካከል ከኔ በላይ አሯሩጠው የሚጨልጡ ነበሩ - የጠላት ገንዘብ ይመስል፡፡ በኋላ ግን፣ ተሸወድን! “እንዴት?”… አወጋችኋለሁ…

ስሙኝማ ወገኖቼ… ሰበር ወግ ላውጋችሁ፣፣ እኔ የምለው ግን.. በዚህ እለት “ኢትዮጵያዊያን ምቀኞች፣ ቅናተኞች… ነን!” የሚባለውን ጉዳይ በራሴ እንዳረጋገጥኩ ብነግራችሁ ምን ትሉ ይሆን? እዚህ ላይ የብዙዎቻችንን መላምት ነው ለማረጋገጥ የሞከርኩት - ኢትዮጵያዊያን ምቀኞች ናቸው የሚለውን፡፡ እናም እነዛ ታዋቂ ተዋኒያን እየወጡ የአቶ በረከትን ወግ እየቀነጨቡ ሲያነቡና ሲጨበጨብላቸው ለምን አልቀናም መሰላችሁ? “ኮምፔ” ነው የተንጫጫው… እኔም ወጥቼ “ደስ የሚለኝን” ምዕራፍ ባነብ ደስ ይለኝ ነበር፤ አሆሆ! እንድደሰት ማን አድርሶኝ!? ለማንበብ “መታደል” ያስፈልጋል፤ ታዋቂ ተዋናይ መሆን ብቻ አይበቃም - መመረጥን ይጠይቃል፡፡ በተለይ ለኔ፣ በዚህ መድረክ ለማንበብ ከመመረጥ፣ ለመንግስተ ሰማያት መመረጥ ይቀለኛል… ኧረ ቆይ! ቆይ! ቆይ!... መንግስተ ሰማያትን የት አባቴ አየሁትና እናንተ?... መፅሐፉ፣ ባለፀጋ መንግስተ ሰማያት ከሚገባ እንደኔ አይነቱ መናጢ ድሀ ቢገባ ይሻላል፤ ግመልም ያላበሳው በመርፌ ቀዳዳ ሹለክ አይባልም ይላል ብዬ እንጂ! እንዳልኳችሁ፣ አርቲስቶቹ ሲያነቡ ጊዜና የቅናት ዛሬ ቢነሳ፣ እኔስ ከማን አንሳለሁ አልኩና ለባልንጀራዬ የገዛሁለትን መፅሐፍ መሀል ላይ ገልጬ ከንፈሬን እያንቀሳቀስኩ ማንበብ ጀመርኩ፤ በርግጥ እኔ ወደ መድረኩ አልወጣሁም፡፡ እዚች ላይ ደግሞ አንድ ሃቅ ላክል… እንደ ብዙዎቹ ታዳሚዎች ሞቅ ብሎኛል፡፡ ለካ መፅሐፉን ገልጬ፣ ያላለውን ነው ያነበብኩት፤ የራሴን ፍልስፍናዊ ጥያቄዎች! (ወይ ጉድ! “ፍልስፍናን” እንደ መላሾ ካልጨመርኩ መጠየቅ አልችል አልኩሳ፤ እናንተ ደግሞ በዚህም እንዳትቀኑብኝ፤ ፈላስፋ ለመሆን ካለኝ ጉጉት ነው… “ወግ አይቀር… እያወጉ ማልቀስ” እንዳትሉኝ እንጂ!)

እዚያው መፅሐፉን እንደገለጥኩ፣ ዘወር ስል በዙሪያዬ ብዙ ታዋቂ ዘፋኞችና የፊልም ባለሙያዎች መድረክ ላይ የሚነበበውን ወግ ትተው የራሳቸው የሞቀ ወግ ይተረትራሉ… እውነቴን ነው የምላችሁ፣ ታዘብኳቸው፣ ወዲያው “ኮምፔ” ተንጫጫ፤ እርግጥ ነው እነሱ እኔን አያዩኝም፤ ከነሱ በምን አንሳለሁ፣ ሥራ አግኝቼ ባልቀጠርበትም ዲግሪ አለኝ አይደል እንዴ? ብዬ ድምፄን ከፍ አድርጌ፣ “የፖለቲካ ወግ ለመፃፍ… ፖለቲካ ነው ማወቅ የሚገባው ወይስ የወግ አፃፃፍ ክህሎት? ወይስ ሁለቱንም?” የሚል ጥያቄ አነበብኩ… እነሱ እናቴ የደራ ወግ ይዘዋል፡፡ ለካ አቶ በረከት ምስጋና ማቅረብ ጀምረው ስለነበር ታዳሚው ያጨበጭብ ይዟል…

አቶ በረከት፣ “ትልቁን ምስጋና የማቀርበው ለኢህአዴግ ነው…” ታዳሚው አጨበጨበ፡፡ “…ሁለተኛ ደረጃ ለአቶ መለስ ዜናዊ…” ተጨበጨበ፡፡ “[ሶስተኛ ደረጃ] ለብአዴን…” ጯ! ጯ! ጯ! ጯ! ጯ! ታዳሚው ሞቅ አርጐ አጨበጨበ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? የብአዴን ጭብጨባ፣ ከአቶ መለስም መብለጡን ታዘብኩ፤ ያኔ ነበር ለካ “እናንተ ነፍጠኞች… ዛሬም አትለቁንም!” የሚለው የአንደኛው ከያኒ በሳቅ የታጀበ ቀልድ፣ ሌሎቹን ሞቅ አርጐ ያሳቃቸው፡፡

በዚህ ጊዜ ነው፣ ከ”ሁለት ምርጫዎች ወግ” ጀርባም “ሌላ ወግ” አለ እንዴ? ያስባለኝ፤ የምር ሳይሆን የቀልድ ወግ፤ የሚግባቡ ባልንጀሮች “የፉገራ ወግ” ጆሮዬ ውስጥ ጥልቅ ያለው…

በነገራችን ላይ የአዳራሽ ውስጥ ጭብጨባ አንደምታው ብዙ ነው፡፡ በኛ ሀገር አንዳንዱ ጭብጨባ በኩራት ወጥሮ ያስተኛናል፡፡ አንዳንዱ ጭብጨባ፣ በስጋት ቀብትቶ ያነቃናል፡፡ አንዳንዱ ጭብጨባ ከአንጀት ይንጣል፤ አንዳንዱ ጭብጨባ ከአንገት ይወልቃል፡፡ “ጭብጨባ” በኢትዮጵያዊኛ ወግ ልማድ ሲመነዘር አንድም “ሰም” ነው፣ አንድም “ወርቅ” ነው፡፡ በብዙ አዳራሽ በሚስተጋቡ ጭብጨባዎች ላይ የበሰለ የህይወት ልምድ ያካበቱ ብዙ ኢትዮጵያዊያን (“ብዙ” ማለት ምን ያህል ነው? ብሎ ወጌን ያቆረፈደ ከሽብርተኛ ለይቼ አላየውም) እንደሚያስተነትኑት፣ “የሃበሻ ጭብጨባ” ቅኔ ነው፡፡ የጭብጨባውን ወርቅ ያወቀ በርግጥም የምር ሊያስጨበጭብ ይችላል፡፡

ወዳጆቼ፣ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለባችሁ፣ በሌላው የጭብጨባ “ሰም” ምን ያህል እንደተዘናጋሁ ነው፡፡ “ወርቁ” ጭብጨባ ለኔ ቢቀርብልኝማ አሁን የለሁም…

ሳምንት ከምረቃው ጀርባ ያለውን፣ የጭብጨባ “ሰም” ሳይሆን “ወርቁን” እናወጋለን፤ በሽጉጥ ማስፈራሪያነት ሁሉ የረቀቁ ሌሎች ወጐችን እንሰልቃለን፡፡

 

 

 

Read 12317 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 15:26