Saturday, 28 January 2012 12:08

መድረክና ኢራፓ የሊዝ ዐዋጁን ተቃወሙት

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

ኢሕአዴግ ሕዝቡን ጭሰኛ እያደረገ ነው

የዜጐችን ንብረት የማፍራት መብት ይጥሳል

ሕዝብ በነፃነትና በግልፅነት እንዲወያይበት አልተደረገም

በደርግ ዘመን የወጣው አዋጅ የከተማ ቦታን የባለቤትነት ክብር ያጐናፀፈ ነበር

መንግሥት የትኛውንም ዓይነት ሕግ ሲያወጣ ማዕከል ማድረግ ያለበት የዜግነት መብትን ለማስጠበቅ እንጂ መብት በመግፈፍ አንገት ለማስደፋትና ለማሸማቀቅ መሆን የለበትም ያለው መድረክ ፓርቲ፤ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው ዐዋጅ የዜጐችን ንብረት የማፍራት፣ የመሸጥ፣ የመለወጥ እና የመጠቀም መሰረታዊ መብት የሚጥስ ነው ሲል ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ተቃውሞታል፡፡የሊዝ ዐዋጅ አወጣጥ እና የአፀዳደቁ ሂደት የተለመደውን የፓርላማ አሠራር የተከተለ አልነበረም የሚለው ፓርቲው፤ ሁለት መሰረታዊ ግድፈቶች እንዳለበት ይገልፃል፡፡

ሕገ መንግስቱ “የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሉአላዊነታቸው የሚገለፀው በዚህ ሕገ-መንግሥት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸው እና በቀጥታ በሚያደርጉት ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ ይሆናል” እንደሚል የጠቆመው መድረክ፤ በአዲሱ የሊዝ ዐዋጅ ግን ይሄ ተግባራዊ አልሆነም ሲል ይተቻል፡፡ “መሬትን በመሰለ መሰረታዊ ጉዳይ ላይ የሉአላዊ ሥልጣን ባለቤት የሆነውና በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከተው ሕዝብ ጉዳዩ ቀርቦለት በነፃነት እና በግልፅነት እንዲወያይበት አልተደረገም” ብሏል - ፓርቲው፡፡

በፓርላማው የወጣው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሥነ ምግባር ደምብና አሠራር፤ የአንድ ዐዋጅ ረቂቅ ለም/ቤቱ አባል ከስብሰባው 48 ሰዓት በፊት መድረስ እንዳለበት ይደነግጋል ያለው መግለጫው፤ የሊዝ አዋጁ ሲፀድቅ ግን የስነምግባር ደምብና አሠራርን የተከተለ አልነበረም ብሏል - ረቂቅ ዐዋጁ ለፓርላማ አባላት ማምሻውን 12 ሰዓት ላይ ታድሎ ጧት 3 ሰዓት ዐዋጅ ሆኖ እንዲፀድቅ መድረጉን በመጥቀስ፡፡

የሊዝ ዐዋጁ የዜጐችን ንብረት የማፍራት ሕገ መንግስታዊ መብት ይጥሳል የሚለው የፓርቲው መግለጫ፤ በኢሕአዴግ መንግሥት የሚኮነነው ደርግ እንኳን የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግሥት ንብረት ለማድረግ ባወጣው ዐዋጅ፤ ዜጐች እስከ 500 ካሬ ሜትር የሚደርስ ቦታ ለቤት መስሪያነት ሊሰጣቸው እንደሚችል፤ እንዲሁም “ባለይዞታ የሟች ሚስት ወይም ባል ወይም ልጆች በቦታው ተተክተው የመጠቀም መብት ይኖራቸዋል” እንደሚል አስታውሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የከተማ ቤት ማስተላለፍን በተመለከተ በደርግ ዘመን የወጣው ዐዋጅ “አንድ ቤተሰብ፣ ግለሰብ ወይም ድርጅት በከተማ ቤቱ የመጠቀም ወይም ይህንኑ ቤት የማውረስ የመሸጥ ወይም የመለወጥ መብት አለው” እንደሚል የመድረክ መግለጫ ያወሳል፡፡

ከዚህ አንፃር ሲታይ ደርግ ያወጣው ዐዋጅ የአገሪቱን የከተማ ነዋሪዎች ከግለሰብ ጭሰኝነት ነፃ ያወጣ፤ የከተማ ቦታን የመሸጥ የመለወጥ እና የባለቤትነት ክብር እንዲጐናፀፉ ያስቻለ ነው ሲልም ያወድሳል - መድረክ፡፡ በሌላ በኩል ኢሕአዴግ በየጊዜው የሚያወጣቸው ዐዋጆች ገዢዎችን የሚጠቅም፣ ሕዝብና ሀገርን የሚጐዳ፤ የዜጐችን መብትና ጥቅም የሚጋፋ ነው ሲል ኮንኗል፡፡

የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በቅርቡ የወጣው ዐዋጅ ክፍል ሁለት፣ አንቀፅ ስድስት፤ ነባር ይዞታዎች ወደ ሊዝ ስሪት ስለሚቀየሩበት ሁኔታ በዝርዝር መቀመጡን የጠቆመው ፓርቲው፤ የኢሕአዴግ ሹመኞች ግን ዐዋጁ የነባር ይዞታዎችን አይመለከትም፤ ዝርዝር መመሪያ አልወጣም፤ ተረጋጉ እያሉ በሕዝብ ላይ ውዥንብር ይፈጥራሉ ሲል ነቅፏል፡፡ የኢሕአዴግ ሹመኞች ዐዋጁ ነባር ይዞታዎችን አይመለከትም ይበሉ እንጂ ሲሸጥ ሲለወጥ ሊዝ ውስጥ እንደሚገባ በግልፅ ደንግጓል ይላል - መግለጫው፡፡

“አንድ ነባር ይዞታን ሲገዛ ለባለንብረቱ ከሚከፍለው ክፍያ በተጨማሪ ለመንግሥት ያንኑ ቦታ የሊዝ ዋጋ ይከፍልበታል፡፡ ይህ አሠራር ብዙ ምርምር ሳይጠይቅ ንብረት በማስተላለፍ ላይ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ለማንም ግልፅ ነው፡፡ የነባር ይዞታው ባለቤት ቦታውን ሸጦ ሌላ አነስተኛ ቦታ ገዝቼ በተረፈችኝ ገንዘብ ህይወቴን ልምራ ቢል የሚገዛው በሊዝ ነው፡፡ ነባር ይዞታዎች ከሊዝ የሚያመልጡት እንዴት ነው?” በማለት የሚጠይቀው መድረክ፤ “ይዞታው ሳይሸጥ ሳይለወጥ፤ የንብረት ዋጋ ሳይኖረው እንደ ጉልቻ በመቀመጡ ብቻ ከሊዝ አመለጠ ማለት ነውን?” ሲል ተሳልቋል - በመግለጫው፡፡

የሊዝ ዐዋጁ የሀገሪቱን ሕዝብ ከይዞታ ባለቤትነት አሽቀንጥሮ በመጣል መንግሥትን የመሬት ባለቤት የሚያደርግ ነው ያለው ፓርቲው፤ ሕገ መንግስቱ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ቢልም ኢሕአዴግ ግን ራሱ ጠቅልሎ ሕዝብን ጭሰኛ እያደረገ ነው ሲል ተችቷል፡፡

ኢሕአዴግ ዐዋጁ ከወጣ በኋላ ከሕዝቡ ጋር ያደረገውን ውይይት አስመልክቶም መድረክ “ለይስሙላ የተደረጉ ስብሰባዎች” ሲል አጣጥሎታል፡፡

በዚህም ውይይት ቢሆን በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ከሚተላለፈው በተለየ ሕዝቡ በዐዋጁ ላይ ተቃውሞውን በመግለፅ ትክክለኛ አቋም ወስዷል ሲል ድጋፉን ጠቁሟል፡በዐዋጁ ዙሪያ በመንግሥት ባለስልጣናትና ካድሬዎች የሚሰጠው መግለጫና ከሕዝብ ለሚቀርበው ጥያቄ የሚሰጡ መልሶች የፌዝ መሆናቸው እንዳስገረመውም መድረክ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

“ነባር ይዞታ እስኪሰጥ እና እስኪለወጥ ድረስ ሊዝ ውስጥ አይገባም ማለት ‘ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት’ ዓይነት ነው” ሲል የተረተው መድረክ፤ ነባር ይዞታዎች ወደ ሊዝ ሥርዓት የሚቀየሩበት ሁኔታ ዝርዝር ጥናት ተደርጐ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን መገለፁም ዐዋጁ ከመውጣቱ በፊት ተገቢው ጥናት አለመካሄዱን ያሳያል ብሏል፡፡

በመድረክ እምነት ዐዋጁ ከመውጣቱ በፊት ተገቢው ጥናት መካሄድ ነበረበት ይላል - የፓርቲው መግለጫ፡፡ ሕዝብ የመደመጥ መብት አለው፤ መንግሥት በተቆጣጠራቸው የሚዲያ ተቋማት በሕዝብ ስም የሚያስተላልፍው ፕሮፓጋንዳ ለራሱም ለሕዝቡም ለሀገርም እንደማይጠቅም አውቆ ሊያስብበት ይገባል ሲልም አሳስቧል፡፡

አርሶ አደሩ የይዞታው ባለቤት መሆን እንዳለበትና የከተማ ነዋሪውም መኖርያ ቤት የሠራበት መሬት ባለቤትነቱን እንዲያረጋግጥ መድረክ በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ ማስፈሩን ያወሳው መግለጫው፤ ይሀንን እውን ለማደረግ በጀመረው የተቃውሞ ትግል እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

የመሬት ሊዝ ዐዋጁን እንደሚቃወም የገለፀው ሌላው ፓርቲ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ነው፡፡ ፓርቲው በላከው መግለጫ ላይ እንደገለፀው፣ መንግሥት እንደ መንግሥት ሕዝብን ወይም ዜጐችን በአገልጋይነቱ እና አስተዳዳሪነቱ ከመታወቅ በስተቀር የአንድ ሀገር ዜጐችን መሰረታዊ ንብረት በሆነው የገጠር የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት የባለቤትነት መብት ላይ የይገባኛል ክርክር ሊያነሳ እንደማይገባ ያትታል፡፡

ዐዋጁ የዜጐችን ሕገ-መንግሥታዊ ነፃነት የማፈታተን፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚጎዳ እና የዲሞክራሲ ግንባታን ጥያቄ ላይ የሚጥል በጥቂት ሀብታሞችና ብዙሃኑ ድሃ ዜጐች መካከል ከፍተኛ የኑሮ እና የኢኮኖሚ ክፍተት የሚፈጥር፣ ማኅበራዊ ችግሮችን የሚያባብስ፣ ቤተሰባዊነትን የሚሸረሽር ዛሬም ሆነ ነገ ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ ዐዋጁና አፈፃፀሙ እንዲፈተሽ የጠየቀው ፓርቲው፤ የከተማ መሬት ባለቤትነትን የመንግሥትና የሕዝብ ተደርጐ ከመውሰድ ይልቅ የሕዝብና የመንግሥት ተብሎ እንዲጠራ እና ሕዝብ ባለቤትነቱ ያለአንዳች ችግር እንዲረጋገጥ በመግለጫው ጠይቋል፡፡ በሌላ በኩል አንድነት ፓርቲ በነገው ዕለት በእየሩሳሌም ሆቴል ከምሑራኖች ጋር በሊዝ ዐዋጁ ላይ እንደሚወያይ ታውቋል፡፡

 

 

Read 3199 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 12:14