Saturday, 28 January 2012 13:25

የዶ/ር ጌታቸው ተድላ “የሕይወት ጉዞዬ እና ትዝታዎቼ”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

“መጋቢት 6 ቀን 1963 ዓ.ም ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ይዞ ወደ አባያ ለመብረር ሲነሳ በአውሎ ንፋስ ምክንያት መሰናክል አጋጥሞት የወደቀው ሒሊኮፕተር ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡ “ሒሊኮፕተሩ በአውሎ ንፋስ ምክንያት መሰናክል ደርሶበት የወደቀው፤ ከአዋሳ ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኘው በብላቴ የእርሻ ልማት የተደረገው ንጉሣዊ ጉብኝት ከተፈፀመ በኋላ፤ ወደ አባያ ለመሄድ ሲነሳ መሆኑ ታውቋል፡፡ “ይኸው 28 ሰዎች ሊይዝ የሚችለው በሶቪየት ኅብረት የተሠራው ሒሊኮፕተር ተሰናክሎ ቢወድቅም፤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አንዳችም ጉዳት ሳያገኛቸው ከሒሊኮፕተሩ በደህና በመውጣት ጉዟቸውን በአውቶሞቢል ቀጥለው፣ በሌሎች ሥፍራዎች የተዘጋጀውን የጉብኝት ፕሮግራም ሲያከናውኑ ውለዋል፡፡”መጋቢት 14 ቀን 1963 ዓ.ም አዲስ ዘመን ጋዜጣ በፎቶግራፍ አስደግፎ ያስነበበውን ዜና “የሕይወት ጉዞዬ እና ትዝታዎቼ” በሚል ርዕስ ለአንባቢያን በቀረበ መጽሐፍ ውስጥ በፎቶ ኮፒ ታትሞ ቀርቧል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ የሒሊኮፕተሩ አደጋ በተከሰተ ዕለት በቦታው ነበሩ፡፡ በዘመኑ የ26 ዓመት ወጣት የነበሩት የመጽሐፉ ደራሲ በእርሻ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከስዊድን ይዘው በመምጣት በአካባቢው ተመድበው በሥራ ላይ ይገኙ ነበር፡፡

በ1930ዎቹ አጋማሽ ነው የተወለዱት፡፡ በተወለዱበት መንደር በሚገኘው ራስ ዳርጌ ትምህርት ቤት ተምረው ትልቅ ቦታ ከደረሱ የአርሲ ተወላጆች አንዱ የሆኑት ደራሲው፤ የዶክትሬት ትምህርታቸውን በሀንጋሪ ነው የተከታተሉት፡፡ በትምህርት፣ በሥራ፣ በስብሰባና በጉብኝት ከ60 በላይ የዓለም አገራትን አይተዋል፡፡ የዕለት ማስታወሻ የመያዝ ልምዳቸው በ426 ገፆች ያቀረቡትን መጽሐፍ ለማዘጋጀት ከ9 ወር በላይ እንዳይወስድባቸው ረድቷቸዋል፡፡ በፋኦ፣ በአይ ኤል ኦ እና በተባበሩት መንግሥታት ስር በተለያዩ ቦታዎች፣ ጊዜያትና  አገራት ለ30 ዓመታት ያህል ሲያገለግሉ ያለፉበትን ውጣ ውረድ፣ ያዩትን ደስታና ሃዘን፣ ያስገረሟቸው የሕዝቦች የባሕል መመሳሰልና በአኗኗር መለያየት መዝግበው አንባቢያን በመጽሐፋቸው እንዲጐበኝ ትልቅ ሥራ መሥራት ችለዋል፡፡ “የሕይወት ጉዞዬ እና ትዝታዎቼ” ለደራሲው አምስተኛ መጽሐፋቸው ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ያሳተመው የፀሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ “ማስታወሻ” የእንግሊዝኛውን ትርጉም ብቻውን በመጀመሪያ ያሳተሙት ዶ/ር ጌታቸው ተድላ ናቸው፡፡ የወላጅ አባታቸውን ታሪክና ሥራ “ተድላ አበበ የዘመናዊ እርሻ ፋና ወጊ” በሚል ርዕስ አዘጋጅተው አሳትመዋል፡፡ “ውጥረትን በተስፋ የተወጣች” በሚል ርዕስ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርተው ጽፈው ያሳተሙት መጽሐፍም አላቸው፡፡ የግል ሕይወትና የሥራ ታሪካቸውን የሚያስቃኙ አምስተኛ መጽሐፍ “ልዩ” የሚያሰኙት በርካታ ነገሮች አሉትከቅርፁ ብንጀምር 24 በ17 መጠን በጠንካራ ሽፋን ተጠርዞ ነው የቀረበው፡፡ የመጽሐፉ ወረቀት ባለ 80 ግራም ነው፡፡ ባለ ቀለም ፎቶግራፎች የታተሙበት 10 ገፆች አሉት፡፡ በ13 ምዕራፎች የቀረበውን ታሪክ የሚያግዙ በመቅድም፣ በመግቢያና በፎቶ ማህደር የተለያዩ መረጃዎች ቀርበዋል፡፡ ከነዚህ አንዱ “ስንቱን አሳለፍነው” የሚለው የመልካሙ ተበጀ የዘፈን ግጥም ነው፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ የዘር ሐረግ (Family root) መግለጫ በስዕል ቀርቧል፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ በተለያዩ አገራት ሲያገለግሉ የተሰጣቸው 16 የሚደርሱ መታወቂያዎችና መንጃ ፈቃዶች እንዲሁም ከተለያዩ አገራት የተሰጧቸው ከ30 በላይ ቪዛዎች ከዚህም በተጨማሪ ባለታሪኩ በተለያየ ምክንያት የሄዱባቸውን አህጉርና አገራት በዓለም ካርታ ላይ በተለያዩ ምልክቶች ለማሳየት ይሞክራል - መጽሐፉ፡፡

ከደራሲው የዕለት ማስታወሻ በተመረጠ መልኩ እየተወሰዱ በመጽሐፉ የቀረቡት ታሪኮች እንደ ጉዞ ማስታወሻ ከዶ/ር ጌታቸው ተድላ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴና የሥራ ፀባይ ጋር በተያያዙ የሚነገሩ ናቸው፡፡

ደራሲው እዚህ ገብቼ ወጣሁ፣ ይህንን ሠርቼ ተመለስኩ፣ ይህንን በልቼ፣ ያንን ለብሼ፣ እነዚህን ጐብኝቼ እያሉ አፍሪካን፣ አውሮፓን፣ አሜሪካን፣ አውስትራሊያን ሲያስቃኙ የመጽሐፉ አንባቢ እየተገረመና እየተረጐመ የሚረዳው ብዙ ታሪኮችን ያቀረበ መጽሐፍ ነው፡፡የ1967 ዓ.ም አብዮት ከመፈንዳቱ በፊት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ሀንጋሪ በመሳሰሉት አገራት በትምህርትና በሥራ ላይ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ስለ ለውጡ በስፋት ይወያዩ እንደነበር ዶ/ር ጌታቸው የሚያሳዩን ነገሬና ዋና ዓላማዬ ነው በሚል አይደለም፡፡ በሀንጋሪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የአሜሪካንን መፃሕፍት አስወግደው መደርደሪያቸውን በሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ላይ በሚያተኩሩ ጥራዞች መሙላታቸውን እንዳዩ የሚነግሩን እንደቀልድ ነው፡፡ በሩሲያ በተገኙበት አንድ ስብሰባ ላይ “ፋኖ ተሰማራ” ሲዘመር ሰማሁ ብለው ወደ ሌላው ጉዳያቸው ይዘውን ይሄዳሉ፡፡

በአሁኑ ዘመን ብዙ ሲያነጋግር የሚታየው ኢትዮጵያዊያን ሕፃናትን በጉዲፈቻነት ለማሳደግ ወደ ውጭ አገራት የመሄዳቸው ጉዳይ ከአብዮት በፊት በንጉሡ ዘመንም ተግባራዊ መሆን ጀምሮ እንደነበር የዶ/ር ጌታቸው ተድላ መጽሐፍ ይጠቁማል፡፡ ደራሲው ለመጀመሪያ ጊዜ ለትምህርት ወደ ስዊዲን በሄዱበት ወቅት ነበር በጉዲፈቻ የሚያድጉትን ኢትዮጵያዊያን ሕፃናትን ማየታቸውን የሚነግሩን፡፡

በትምህርት፣ በሥራ፣ በጉብኝት የተለያዩ የዓለም አገራትን የማየት ዕድል ያገኙት ዶ/ር ጌታቸው ተድላ፤ መጽሐፋቸው በአስገራሚ ገጠመኝና ታሪኮች እንዲሞላ ረድቷቸዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ባለስልጣናት ኒልሰን ማንዴላን ከእስር ከመፍታታቸው በፊት “አሸባሪው” ብለው ይጠሯቸው እንደነበር ገጠመኛቸውን የሚነግሩን ዶ/ር ጌታቸው፤ የኢትዮጵያ አብዮት መሪ ኮሚኒስት አይደለም ያላቸው የአፓርታይድ ኢሚግሬሽን ባለስልጣን “ማነው መንግሥቱ ኃይለማርያምን ኮሚኒስት ያደረገው እሱ የወታደር ጁንታ አምባገነን፤ ነው ቦታውን ላለመስጠት ሰው ይገድላል እንጂ ኮሚኒስት ማለት ምን እንደሆነ እንኳን አያውቅም” የሚል ማብራሪያ ሰጠኝ ይላሉ፡፡

ብር የታጨቀበትን ቦርሳ መንገድ ላይ በመጣል ለማንሳት የፈጠነውን ሰው ተከትለው “ብጋራ” በማለት ለዘረፋ የሚያመቻቹና ከአዲስ አበባ ኪስ አውላቂዎች የሚመሳሰሉ የኬኒያ (ናይሮቢ) አራዶችን ተግባር አስቃኝቶ የሚያልፈው የዶ/ር ጌታቸው መጽሐፍ፤ ደራሲው በሄዱባቸው ቦታዎች ሁሉ ካዩት እየቆነጠሩ ያቀረቧቸው ታሪኮች ብዙ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አስተማሪ፣ አዝናኝና አስገራሚ ነገራቸው ይበዛል፡፡

በፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን ዘመን በኢራቅ በሥራ እጦት የተነሳ በሕክምና በዶክትሬት ደረጃ የተመረቁ ሰዎች እንዳልተማረ ሰው  ዝቅተኛ መመዘኛ እያቀረቡ ለቢሮ ተላላኪነት ሥራ አመልክተው ሲቀጠሩ ያዩት ደራሲው፤ ችግሩን ሲረዱ አዝነው፣ ተገርመውና ታሪኩን ለመጽሐፋቸው ግብአት ተጠቅመው ብቻ አለማለፋቸውን እናያለን፡፡ በሥራ እጦት ምክንያት በተላላኪነት ዝቅ ብሎ ያገለግል የነበረውን ኢራቃዊ የሕክምና ባለሙያ በሹፍርና እንዲያገለግል ረድተውታል፡፡

ግለሰብ ቀርቶ ተቋማትም ሆኑ መንግሥት በቀላሉ መፍትሔ ያገኝላቸዋል ተብለው የማይታሰቡ ችግሮች የሞሉባቸው አገራትና ሕዝቦች አሉ፡፡

ዶ/ር ጌታቸው ተድላ ለወራት አስበው ለ5 ዓመታት የቆዩባት ናይጀሪያ ጉቦ፣ ሌብነትና ዘረፋው ሕጋዊና ባሕላዊ በሚመስል መልኩ መስፋፋቱን በብዙ ገጠመኝና ማሳያ ያስቃኛሉ፡፡ የዶ/ር ጌታቸው ተድላ “የሕይወት ጉዞዬ እና ትዝታዎቼ” መጽሐፍ በታሪክ፣ በተለያዩ ገጠመኞችና በብዙ መረጃዎች ከመሞላቱም ባሻገር የደራሲው ቀልድ አዋቂነት ለመጽሐፉ ትልቅ ጉልበት ሰጥቶታል፡፡ በደቡብ ምሥራቅ እስያ በሀብታምነቷ የምትታወቀው ሲንጋፖር፤ ብዙ የአልማዝና የወርቅ መሸጫ ሱቆች አላት፡፡ በሱቆቹ ያሉት አሻሻጮች ልዩ ችሎታ እንዳላቸው የሰሙት ዶ/ር ጌታቸው፤ የአንዷን አሻሻጭ ልዩ ችሎታ በዚህ መልኩ አሟጣ እንድትጠቀም አድርገዋታል፡፡

“ለሚስትህ አልማዝ ወይም ወርቅ ገዝተህ ልታስደስታት ትፈልጋለህ?” አለችኝ

“አላገባሁም”

“ለሴት ልጅህ ለአንተ ትልቅ ከበሬታ እንዲኖራት አልማዝ ግዛላት”

“አልወለድኩም”

“ለእጮኛህ ገዝተህ ልቧን ንካው”

“ሚስት አላገባም”

“ለእናትህ ስላሳደግሽን አመሰግናለሁ በልና ሰጣት”

“እናቴ በሕይወት የለችም” ስላት ትንሽ ተናደደችና

“መቼም እዚህ ድረስ መጥተህ ለራስህ ሳትገዛ አትሄድም” አለችኝ፡፡

“እኔ ለሁለቱም አለርጂክ ነኝ፣ አሠራራችሁን ለማየት ብቻ ነው የመጣሁት” ስላት ወዲያውኑ ጥላኝ ሄደች፡፡

ታህሳስ 21 ቀን 2004 ዓ.ም በጣሊያን የባህል ተቋም የተመረቀው “የሕይወት ጉዞዬ እና ትዝታዎቼ” መጽሐፍ ደራሲ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ፤ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ሲሆኑ አሁን ወደ አገራቸው መጥተው የጡረታ ዘመናቸውን የተለያዩ መፃሕፍት እየፃፉ በማሳተም ላይ መሆናቸውን በመጽሐፉ ምረቃ ዕለት ተናግረዋል፡፡

 

 

Read 3000 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 13:30