Saturday, 28 January 2012 13:32

በአሜሪካ ምርጫ እየተጧጧፈ ነው ሃይማኖትም እንደ መስፈርት ይወሰዳል

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(0 votes)

ከዛሬ አራት አመት በፊት በአሜሪካ በተካሄደ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከበርካታ እጩ ተወዳዳሪዎች ውስጥ ጐልተው ይታዩ የነበሩት ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ነበሩ፡፡ በተለይም አብዛኞቹ እጩዎች ከውድድሩ ከወጡ በኋላ፣ ኦባማና ሂላሪ ክሊንተን ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ፉክክር አይዘነጋም፡፡ ኦባማ ሂላሪን ከረቱ በኋላም ሪፐብሊካኑን ጆን ማኬይንን በላቀ የድምፅ ልዩነት ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡ባራክ ኦባማ ራሳቸው ካሳዩት ጥንካሬ በተጨማሪ የሪፐብሊካኖች ድክመት እንዲያሸንፉ እንደረዳቸው የሚጠቀስ ሲሆን፣ በተለይም ጥሩ ተናጋሪ (orator) መሆናቸው፣ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ይልቅ የመራጮችን ቀልብ ሊገዙ የሚችሉበትን ፍቅር ለሁሉም በማሳየታቸው፣ የመጀመሪያው ጥቁር ተወዳዳሪ በመሆናቸው፣ ‘Yes we can’ የምትለውን አባባል በስፋት በመጠቀማቸው እንዲሁም ወደ መነጋገሪያው መድረክ ሮጥ ሮጥ እያሉ መሄዳቸውና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ነገር ግን በ2012 ዓ.ም ምርጫ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡ የመራጮችን ቀልብ መግዛት ወይም በንግግር መማረክ ብሎ ነገር በዚህ ምርጫ ላይ አይሰራም፡፡ በ2012 የሚያስፈልገው ቀጥተኛና ግልፅ የሆኑ ንግግሮች መናገር እንዲሁም እውነታን ፊት ለፊት ማስቀመጥ ዋነኛው ሲሆን ይህም አሜሪካ ከገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስና ዜጐቿን አሳር እያበላ ከሚገኘው የስራ አጥነት ችግር ሊያላቅቅ የሚችል እጩ ተወዳዳሪ መሆን አለበት፡፡ የሚገርመው ዘንድሮ ሃይማኖተኝነትም እንደመስፈርት እንዲታይ አፍቃሪ አሜሪካዊያን (Pro-Americans) እየለፈፉ ይገኛሉ፡፡

በዘንድሮው ውድድር ከዲሞክራትም ሆነ ከሪፐብሊካን ፓርቲዎች በርካታ እጩዎች የቀረቡ ሲሆን ኦባማ የዲሞክራት ፓርቲን ወክለው ለሚቀጥለው አራት አመት በድጋሚ ለመመረጥ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ይሁን እንጂ ከወራት በፊት የሪፐብሊካን እጩዎች አሜሪካ ዛሬ ለገባችበት ቀውስ ተጠያቂው እርሶ (ኦባማ) ነዎት በማለት በተለያዩ መድረኮች ባራክ ኦባማን ማብጠልጠላቸው ይታወሳል፡፡በ2012 ምርጫ ከሁሉም እጩ ተወዳዳሪዎች ጐልተው እየታዩ ያሉት ሁለት ሃያላን ሰዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም ደግሞ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተፎካካሪዎች ሲሆኑ አንዱ ሌላውን በመንቀፍ የጀመሩት እሰጥ አገባ የአለም አቀፉን ሚዲያ ትኩረት ስቧል፡፡ ሁለቱም ሰዎች የቀድሞው የምክር ቤት አፈ ጉባኤ (House of speaker) የነበሩት ኒውት ጊንግሪች እና የማሳቹሴትስ ገዢ የነበሩት ሚት ሮሚኒ ናቸው፡፡ባለፈው ሰኞ በፍሎሪዳ በተካሄደ የቪዲዮ ክርክር ሚት ሮሚኒ ምስጢር ያሉትን የኒውት ጊንግሪች ማንነት ይፋ አድርገዋል፡፡ ኒውት ጊንግሪች ለ15 አመታት በአፈ ጉባኤነት ካገለገሉ በኋላ ’ፍሬዲ ማክ’ ለተባለ ድርጅት አማካሪ በመሆን ሲሰሩ፣ ድርጅቱ አግባብ ያልሆነ ትርፍ ወደ ካዝናው እንዲያጋብስ አድርገዋል፡፡ጊንግሪች ይህንን የሚያደርጉት የመንግሥት ሕግ አውጪ አካላት ላይ ተፅእኖ በመፍጠር ሲሆን፣ ለዚህ ውለታቸውም ’ከፍሬድ ማክ’ በየዓመቱ 1.6 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ አላቸው በማለት ሚት ሩማኒ ጉዳዩን አፍረጥርጠውታል፡፡ሚት ሩማኒ ሲቀጥሉ ታዲያ፣ እንዴት አድርገን ነው እንደ ጊንግሪች አይነት ሰው ፓርቲያችንን ወክሎ ወደ ዋይት ሐውስ እንዲገባ የምንፈቅደው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ሚ/ር ጊንግሪች ከሚ/ር ሮማኒ ለሚዘንብባቸው ትችት ፊታቸው በቁጣ የተለዋወጠ ሲሆን፣ በእልህ ምላሽ ለመስጠት ሲሞክሩም ተስተውሏል፡፡ ይሁንና ሚ/ር ጊንግሪች “ሮሚኒ የሰሜን ምዕራብ አክራሪ ነጮችን ትኩረት ለመሳብ ፈለገው እንጂ ያቀረቡት ክስ ሁሉ ሀሰት ነው፡፡ እኔ በመንግስት ላይ ተፅእኖ በማሳደር ለፍሬድ ማክ ሽፋን አልሰጠሁም” በማለት መልሰዋል፡፡ “ይህ አስቀያሚ የፖለቲካ ጭቅጭቅ ነው፡፡ ምንም ዋጋ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ሚ/ር ሮሚኒ የተዛባ መረጃ ይዟል” ብለዋል ሚ/ር ጊንግሪች የረቀበባቸውን ውንጀላ ሲከላከሉ፡፡

ይሁን እንጂ ሚ/ር ጊንግሪች ሚ/ር ሩሚኒ ከተናገሩት ሌላ በደቡብ ካሮሊና በተካሄደ ምርጫም ከታዋቂው የቁማር ከበርቴ ለምርጫ ቅስቀሳ የ 5 ሚሊዮን ዶላር መቀበላቸው ይጠቀሳል፡፡ከክርክሩ በኋላ በአንዳንድ ጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ከዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ከካራን ቱሙሊቲ የቀረበላቸው ጥያቄ “ከተመረጣችሁ ሰው በማርስ ፕላኔት ላይ እንዲያርፍ ታደርጋላችሁ?” ሲባሉ ሁለቱም አዎን! የሚል ምላሽ ወዲያው ሰጥተዋል፡፡ ይህ ጥያቄ ኦባማን ለመንቀፍ ጥሩ አጋጣሚ ስለፈጠረላቸው፣ ኦባማ በፍሎሪዳ ለሚገኘው ’ናሳ’ ከፍተኛ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ የመንግስትን በጀት እንዲቀንስ በማድረጋቸው የፍሎሪዳዊያንን ድጋፍ አያገኙም በማለት ሁለቱም ተናግረዋል፡፡ የሸንኮራ አገዳ ምርት ላይ የመንግስት በጀት መቀነሱን ጊንግሪች ሲናገሩ፣ ሩሚኒ ደግሞ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ በቂ የሸንኮራ አገዳ ምርት ስላለ ለሸንኮራ ምርት ተጨማሪ ድጋፍ አያስፈልግም በማለት ጊንግሪችን አጣጥለዋል፡፡የNBC ጋዜጠኛ ብራያን ዊሊያምስ ያቀረበው ጥቄ ደግሞ ስለ ኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራም ምን አስተያየት አላችሁ? የሚል ነበር፡፡ ሁለቱም እጩዎች ኢራን የኒውክሊየር ባለቤት ለመሆን ከመቃረቧ በፊት እርምጃ መወሰድ ሲገባው አሁን ባለቀ ሰዓት መሯሯጡ ፋይዳ የለውም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በኢራን ጉዳይ ላይ አስተየየት የሰጡትን ሌላኛው የሪፐብሊካን እጩ የሆኑትን የሮን ፓውልን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ‘Don’t hurt me and I won’t hurt you’ በእኛ አገር አባባል ’አትድረስብኝ እኔም አልደርስብህም’ የሚል ነው፡፡ጋዜጠኛ ብራያን ለሚት ሮሚኒ ካቀረበላቸው ጥያቄ አንዱ፣ “ዋይት ሐውስ ቢገቡና ፊደል ካስትሮ መሞቱን ቢሰሙ ምን ይላሉ?” የሚል ሲሆን ሚት ሮሚኒ ሲመልሱ “እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን ካስትሮ አሁንም መቃብር አፋፍ ላይ ነው” ብለዋል፡፡ ለጊንግሪችም ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ “ኦባማ በአረብ አብዮት ላይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ጊዜ ያጠፋሉ፡፡ ነገር ግን ከአሜሪካ 90 ማይልስ ርቀት የምትገኘውን ኩባን ዘንግተዋል፡፡ ከኩባ ወደ አሜሪካ በሕገ ወጥ መንገድ የሚፈልሱ ዜጐች ለአሜሪካ ትልቅ ስጋት ናቸው” ብለዋል፡፡ባራክ ኣባማ በሥልጣን ዘመናቸው የተለያዩ ስህተቶችን የፈፀሙ ቢሆንም፣ የሪፐብሊካን እጩዎች በሚያሳዩት እርስ በእርስ መወነጃጀል ሊያሸንፉ ይችላሉ ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ኦባማ በሙስና ውስጥ ያልተዘፈቁ መሆናቸው ሌላው ድምፅ ሊያገኙ የሚችሉበት ነጥብ እንደሆነም ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ ምናልባት ኦባማ በድጋሚ ከተመረጡ የአሜሪካን ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በገባበት ወቅት በድጋሚ እንደተመረጡት 32ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፍራክሊን ዲላኖ ሩክቬልት ቀጥሎ ሌላኛው ጥቁር ተመራጭ ይሆናሉ ተብሏል፡፡በደቡብ ካሮሊና እና ፍሎሪዳ ከተካሄዱት የሪፐብሊካን ውድድሮች በፊት ሃይማኖታዊ አጀንዳዎችም በስፋት ተዳስሰዋል፡፡ ባራክ ኦባማ በልጅነታቸው የሙስሊም ሃይማኖት ተከታይ እንደሆኑ ቢታወቅም በፕሮቴስታንት ውስጥ የትሪኒቲ ዩናይትድ ቸርች ኦፍ ክራይስት እምነት ተከታይ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ኦባማ በእምነታቸው አጥባቂ እንዳልሆኑ ይገለፃል፡፡ ይህም አሜሪካ በክርስቲያን መሪ እየተመራች ነው ለማለት አያስችልም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሃይማኖታዊ ባልሆነ (Secular) አስተዳደር እየተመራች ነው በማለት አፍቃሪ አሜሪካዊያን የሃይማኖት ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

አንዲት አፍቃሪ አሜሪካዊት በጉዳዩ ላይ እንዲህ ብለዋል፤ “አሜሪካ መሰረቷ የክርስቲያን አገር ነች፡፡ መሪዎቻችንም ጠንካራ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን ጠንካራ ክርስቲያን ነበሩ፡፡ ሁሉንም ነገር ሲያደርጉም ሆነ ሲናገሩ ኢየሱስን እንደ ምሳሌ በመጠቀም ይጠቅሱ ነበር፡፡ ጆርጅ ዋሽንግተን የአንጀሊካን ሃይማኖት (የእንግሊዝ ቤተክርስቲያን የምትከተለው) አማኝ ነበሩ፡፡ ይሁንና ከአንጀሊካን ውጪ የሆኑ የክርስትና እምነቶች እንዲሁም አይሁዶች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበራቸው፡፡ በእነዚህ ሃይማኖቶች መንፈሳዊ አገልግሎት ላይም ተጋብዘው ይሄዱ ነበር፡፡ በመሆኑም ዋሽንግተን አማኝ በመሆናቸው ጥሩ ዲፕሎማት እንዲሆኑ ረድቷቸዋል” በማለት ይገልፃሉ፡፡

ሌላው ሶስተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቶማስ ጀፈርሰን ናቸው፡፡ ቶማስ ጀፈርሰን፣ ለኢየሱስ ትልቅ ክብርና አድናቆት ነበራቸው፡፡ ጀፈርሰን መፅሐፍ ቅዱስን በየጊዜው የሚያነቡ ሲሆን መፅሐፍ ቅዱስን በተለያየ ጊዜያት የተረጐሙ ፀሐፊዎች ትክክለኛውን የኢየሱስን ሥራዎች አዛንፈዋል የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የፕሉቶንና ሌሎች የግሪክ ፈላስፎችን አስተሳሰብ አንፀባርቀዋልም ባይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ጀፈርሰን በብዙ የክርስትና አማኞች ዘንድ እግዚአብሔር አንድም ሦስት ነው የሚለውን የስላሴ (Trinity) እምነትን አይቀበሉም፡፡ለአሜሪካ ሃይማኖት የሚቆረቆሩ አፍቃሪ  አሜሪካዊያኑ  አሜሪካን የቆረቆሩት ክርስቲያኖች ሆነው እያለ ዛሬ ግን አሜሪካዊያን ሃይማኖት አልባ እየሆኑ እየመጡ ነው በማለት ሲገልፁ፣ ከእንግዲህ በአሜሪካ ሃይማኖቱን የማያጠብቅ መሪ ሊመረጥ አይገባም የሚል እምነት አላቸው፡፡በ2012 በሚካሄደው ምርጫ ሪፐብሊካንን ወክለው በቀዳሚነት የተሰለፉት ሚ/ር ሚቲ ሩሚኒ፤ የሞርሞንስ (Church of Jesus Christ of Latter Days of Saints) አማኝ ናቸው፡፡ በመሆኑም ሮሚኒ ምናልባት ከተመረጡ የመጀመሪያው የሞርሞንስ ፕሬዝዳንት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ሚ/ር ኒው ግንግሪች ደግሞ ተወልደው ያደጉት የማርቲን ሉተርን አስተምህሮ በሚከተሉ የሉተራኒዝምን እምነት ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ በመሆኑ የመጀመሪያው እምነታቸው ሉተራኒዝም ነበር፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ከወጡና ወደ ስራው ዓለም ከገቡ በኋላ ደግሞ ሃይማኖታቸውን በመቀየር በደቡብ አትላንታ በሚኘው የባፕቲስት ቸርች እምነት ተከታይ ሆኑ፡፡ ነገር ግን በቤተክርስቲያኑ ሴቶች ፓስተር በመሆን ማገልገል ሲጀምሩ ከባፕቲስ ቸርች ራሳቸውን አገለሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2001 ለሶስተኛ ጊዜ ሃይማኖታቸውን በመቀየር የሮማ ካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ሆነዋል፡፡ጊንግራች በሉተራኒዝም ውስጥም ሆነ በባፕቲስት ቸርች እያሉ የዘወትር ተከታታይ እንዳልነበሩ ተገልጿል፡፡ እርሳቸው ራሳቸው ሃይማኖት በፖለቲካ ውስጥ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም የሚል አመለካከት አላቸው፡፡

በ2012 ምርጫ ላይ ለሚወዳደሩት የሁለቱም ፓርቲ እጩዎች መንፈሳዊ ጥያቄዎችም ቀርቦላቸዋል? ከእነዚህም ውስጥ በቀን ምን ያህል ጊዜ ትፀልያላችሁ? ከአምላክ ጋር ያላችሁ ግንኙነት እንዴት ነው? መፅሐፍ ቅዱስ በየቀኑ ያነቡ እንደሆነ፣ ኢየሱስ በሕይወታቸው ውስጥ ስላለው ሚና፣ ኢየሱስ ለምን እንደሞተ ክርስቲያን ላልሆኑ ሰዎች ስለማስተማራቸው፣ እንዲሁም ግብርን በአግባቡ መክፈል አለመክፈላቸውን እና ሌሎችም ጥያቄዎች ቀርቦላቸዋል፡፡ለአብዛኞቹ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ ቢሆንም መንፈሳዊ ጥያቄዎች በመሆናቸው ከሚናገሩት ውጪ ሌላ ማረጋገጫ አይኖርም፡፡ በየዓመቱ ለመንግስት የሚከፍሉትን ግብር በተመለከተ ግን መረጃው ይፋ ሆኗል፡፡በ2010 ሚት ሮሚኒና ባለቤታቸው አና ሮሚኒ አመታዊ ገቢያቸው 21,661,425 ዶላር ነበር፡፡ ለመንግሥት መክፈል የሚገባቸው ታክስ 3032588.16 የነበረ ሲሆን የከፈሉት ግን 3009766 ብቻ ነው፡፡ የኒውት ጊንግሪች የ2010 ዓመታዊ ገቢ 3162425 ዶላር ነው፡፡ ለመንግሥት መክፈል የሚገባቸው ታክስ 1011976 የነበረ ሲሆን፣ የከፈሉት ግን 994708 ዶላር ብቻ ነው፡፡ ባራክ ኦባማና ባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ በ2010 አመታዊ ገቢያቸው 1795614 ዶላር ነው፡፡ መክፈል የሚገባቸው ታክስ 466859.64 ሲሆን የከፈሉት ግን 453770 ብቻ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ባለው ጊዜ የበለጠ እየተጠናከረ በሚሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሂደቱንና አሸናፊውን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡

ምንጭ :- (The daily Telegraph, The Gurdian, The Economist)

 

 

 

Read 4687 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 13:39