Saturday, 28 January 2012 14:25

ታላቁ ሩጫ ነገ በሐረር ይካሄዳል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ሉሲ የሚባለው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም የግብፅ   አቻውን በመልስ ጨዋታ ይገጥማል፡፡ በጨዋታው ሉሲዎች ግብፅን 2ለ0 እና በሁለት ንፁህ ጎል ልዩነት ካሸነፉ ወደ መጨረሻው የማጣርያ ምእራፍ መሸጋገር ይችላሉ፡፡  ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለ8ኛው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ከግብፅ አቻው ጋር ተጋጥሞ 4ለ2 ተሸንፏል፡፡ በካይሮ ከግብፅ አቻው ጋር የተፋለመው ብሄራዊ ቡድኑ በአጭር ቅብብል ማራኪ እግር ኳስ ማሳየቱን የዘገበው የካፍ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ለሽንፈት የዳረጉት ጎሎች በራስ ሜዳ ላይ በሚያደርጋቸው አደገኛ ቅብብሎች መግባታቸውን አመልክቷል፡፡ ለሉሲ ጥሩ  ከተጨዋቱት መካከል አምበል ብዙሃን እንዳለን የጠቀሰው ዘገባው የብዙዎቹን የሉሲ ተጨዋቾች ስም አዛብቶ ማቅረቡንም ለማስተዋል ተችሏል፡፡

በመጀመርያው ጨዋታ የሉሲን ሁለት ጎሎች ያስቆጠሩት  ረሂማ ዘርጋውና ሽታዬ ሲሳይ ናቸው፡፡ ለግብፅ ሴቶች ብሄራዊ ከተመዘገቡት አራት ጎሎች  ሁለት  ያስቆጠረችው አምበሏ ኢንጊ አትያ ስትሆን የተቀሩትን ሁለት ግቦች ሳልማ ተሬቅ እና ሃያም አብድ ኤልሃፊዝ አግብተዋል፡፡ በጨዋታው የሉሲ የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች በራሳቸው ግብ ክልል መቀባበል ማብዛታቸው በተደጋጋሚ አደጋ ላይ እንደጣላቸውና ለሽንፈታቸው ምክንያት መሆኑን ካፍኦላይን በዘገባው አመልክቷል፡፡ በቅድመ ማጣርያው  ላይ 10 ግጥሚያዎች ሊደረጉ ፕሮግራም ቢወጣም ባለፈው ሳምንት የተደረጉት 8 ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ከቅድመ ማጣርያው ኬንያና ብሩንዲ ራሳቸውን በማግለላቸው ተጋጣሚዎቻቸው የነበሩት ሞዛምቢክና ሴኔጋል በቀጥታ ወደ ቀጣዩ ምእራፍ በፎርፌ ተሸጋግረዋል፡፡  ከኢትዮጵያና ግብፅ ያሸነፈው በቀጣይ ምእራፍ የሚገናኘው ከታንዛኒያ ወይም ከናሚቢያ ነው፡፡ ከሳምንት በፊት በመጀመሪያው ጨዋታ ናሚቢያ በሜዳዋ በታንዛኒያ 2ለ0 ተሸንፋለች፡፡ የትዊጋ ኮከቦች ለሚባለው የታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን ከናሚቢያ አቻው ጋር ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ድጋፍ እንዲሆን ከ150ሺ ብር በላይ በአንድ ኩባንያ ተሰጥቶታል፡፡   በቅድመ ማጣርያው የመጀመርያ ዙር ሌሎች ጨዋታዎች ኮትዲቫር ጊኒን 5ለ1፤ ዛምቢያ ማላዊን 7ለ0፤ ሞሮኮ ቱኒዚያን 2ለ0፤ ቦትስዋና ከሜዳዋ ውጭ ዚምባቡዌን 1ለ0፤ እንዲሁም ማሊ ከሜዳዋ ውጭ ጋናን 3ለ0 ሲያሸንፉ ኡጋንዳና ዲሪ ኮንጎ በካምፓላ 1 እኩል አቻ ተለያይተዋል፡፡ የመልስ ጨዋታዎች ዛሬና ነገ በመላው አህጉሪቱ ተካሂደው የመጨረሻው ዙር ማጣርያን የሚያደርጉ ተጋጣሚዎች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡

የ2012 የሚሊኒዬሙ የልማት ግቦች ሩጫ በሚል ስያሜ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  ነገ በሐረር ከተማ የ6ኪ.ሜ ውድድር አዘጋጀ፡፡ ከሳምንት በፊት የውድድሩ የመጀመርያ ምእራፍ በአፋር ሰመራ 1200 አዋቂ እና 400 ህፃናትን በማሳተፍ ተከናውኗል፡፡ ነገ መነሻና መድረሻውን በሃረር ጀጐል በር በሚያደርገው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር 50 የክልሉ አትሌቶች የሚከፈሉበትን ዋና ውድድር ጨምሮ 2250 አዋቂና 5000 ህጻናት ስፖርተኞች ይሮጣሉ፡፡ የሩጫ ውድድሩ በተለያዩ መዝናኛዎችና የሚሊኒዬሙ የልማት ግቦች መልዕክቶችን በማስተላለፍ ሁሉም ሰው የድርሻውን ይወጣል የሚል መርህ አንግቦ ከዛሬ ጀምሮ የሐረር ከተማን ያደምቃታል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ውድድሮችን ማካሄድ የጀመረው ባለፈው አመት በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ፅህፈት ቤት ጋር በመተባበር ነበር፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስምንቱን የሚሊኒዬሙ ልማት ግቦች ለማሳካት በሚያደርገው ድጋፍ በሁሉም ውድድሮች ተመሳሳይ መርህን በማንበብ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ውድድሩ በየክልሉ ለሚገኙ ስፖርተኞች የተሳትፎ እድል በመፍጠርም እጅግጠቃሚ ሆኗል፡፡ አምና ውድድሩ በጋምቤላና ጅማ የተደረገ ሲሆን ዘንድሮ ከሳምንት በፊት በአፋር ሰመራ ተካሂዶ ነገ ደግሞ በሃረር ከተማ በመካሄድ ይቀጥላል፡፡11ኛውን የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በ35ሺ ስፖርተኛ በማሳተፍ በአዲስ አበባ በስኬት ያካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከከተማው ውጭ ተመሳሳይ ውድድር ሲያዘጋጅ የነገው የሐረር ሩጫ 11ኛው ይሆናል፡፡

 

 

Read 2223 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 14:28