Print this page
Saturday, 04 February 2012 11:32

ቢ ጂ አይ ኢትዮጵያና ሦስተኛው ፋብሪካ በሀዋሳ “አምበር” ቢራ ለፋሲካ ይደርሳል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

አንድ ሔሊኮፕተር በሀዋሳ ከተማ አናት እየተሽከረከረች በራሪ ወረቀቶች ስትበትን አየን፡፡ ፋብሪካው አካባቢ ብዙ ጊዜ ዝቅ እያለች ስትበትን ወረቀቱን ለማግኘት ሲራኮቱ የነበሩ ሰዎችን በአቧራ ጐንፋለች፡፡ ፋብሪካው ግቢ ውስጥ በርካታ ቢጫ ድንኳኖች ይታያሉ፡፡ ከፋብሪካው ፊት - ለፊት የክብር እንግዳው አቶ ሽፈራው ሽጉጤና ሌሎች ባለሥልጣናት እንዲሁም የፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች የተጠለሉበት ትልቅ ድንኳን አለ፡፡ ከዚህ ድንኳን ግራና ቀኝ ጥሪ የተደረገላቸው የከተማዋ ነዋሪዎችና እንግዶች የታደሙባቸው ድንኳኖች ተተክለዋል፡፡ ከዋናው ድንኳን ፊት ለፊት ደግሞ የተለያዩ ሙዚቃዎች የሚንቆረቆሩበት መድረክ  ቆሟል፡፡ በተጨማሪም ድራፍት ቢራ የሚቀዱባቸው በርካታ ድንኳኖች በግራም በቀኝም ተተክለዋል፡፡

ይህ ትዕይንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ የዛሬ ሳምንት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል በሀዋሳ የገነባው 3ኛው የቢራ ፋብሪካ በተመረቀበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ የሚገልጽ ነው፡፡ በዚህ የቢራ ፋብሪካ ምረቃ ወቅት፣ የደቡብ ሕዝቦች ክልላዊ መስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ባደረጉት ንግግር፣ “…የቢጂ አይ ፋብሪካ ሰዎች ከዛሬ 14 ወር በፊት ወደ ቢሮዬ ሲመጡ ሊፈትኑኝ የመጡ ነበር የመሰለኝ፡፡ ምክንያቱም “7 ሔክታር መሬት ከሰጠኸን በ12 ወር ውስጥ የቢራ ፋብሪካ ሠርተን ቢራ የተሞላ ጠርሙስ እናስረክብሃለን” አሉኝ፡፡ እኔም ለምን 7 ሔክታር ጠየቃችሁ… ለምን 14 ሔክታር ወይም 4 ሔክታር አላላችሁም አልኳቸው፡፡ እነሱም የሚያስፈልገን 14 ወይም 4 አይደለም 7 ሔክታር ስለሆነ ነው” አሉኝ፡፡ “ሰባቱን ሄክታር ከሰጠኋችሁ ምን ታደርጋላችሁ?” አልኳቸው፡፡ “ለ350 ሰዎች የሥራ ዕድል እንፈጥራለን፣ ፋብሪካውን በ12 ወራት ገንብተን ቢራ ጠምቀን እናስረክብሃለን” አሉኝ፡፡ “ይህ ከሆነ ሁላችንም ራሳችንን እንፈትን፡፡ እኔም ከካቢኔ አባላቶቼ ጋር ተነጋግረን እንወስናለን፤ እናንተም ተመካክራችሁ ወስኑ” አልኳቸው፡፡ በዚሁ መሠረት ፕሮፖዛላቸውን አቅርበው በአንድ ሳምንት ተፈቅዶላቸው ወደ ሥራ ገቡ፡፡ ባሉት መሠረት በ12 ወር ግንባታውን አጠናቀው፣ ባለፈው ሰኔ ወር የመጀመሪያውን ጠርሙስ ቢራ ስላቀረቡ እናመሰግናቸዋለን፡፡

ዓላማችን ቃላቸውን ጠብቀው የወሰዱትን መሬት አልምተው ራሳቸው ተጠቅመው፣ ወገናቸውን ጠቅመው ለመንግስት መክፈል ያለባቸውን ግብር የሚከፍሉትን ልማታዊ ባለሀብቶች ማገልገል ነው፡፡ አሁንም ሌሎች ባለሀብቶችንም ለማገልገል መንግሥታችን ዝግጁ ነው፡፡ ሁላችንም ቃላችንን እንጠብቅ” ብለዋል፡፡

ፋብሪካው፣ ከቤልጅየም፣ ከፈረንሳይ፣ ከጀርመንና ከኢጣሊያ በተገዙ እጅግ ዘመናዊ የጠመቃ መሳሪያዎች የተገነባ ሲሆን ከመጠንሰሻው አንስቶ ቢራው ተጠምቆ፣ በጠርሙስ ተሞልቶና አርማው ተለጥፎበት ሳጥን እስኪገባ ድረስ የሰው እጅ አይነካውም፡፡ ሙሉ በሙሉ አውቶማቲክ ነው፡፡ ጠመቃው ከተጀመረ አንስቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ በእያንዳንዱ ክፍል የሚደረገውን የሥራ ሂደት ሠራተኞች የሚቆጣጠሩት  በኮምፒዩተር ነው፡፡

ክላሲክ ሚል የተባለው መሳሪያ በሰዓት 4.800 ኩንታል ብቅል የሚያበጥር ሲሆን ወፍጮው ደግሞ በሰዓት 2,500 ኩንታል ይፈጫል፡፡ ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በቀን 110 ሺህ (1ሺ 100 ሄክቶ ሊትር) ጠርሙስ ቢራና 300 በርሜል ድራፍት ያመርታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኮምቦልቻ ያለው የቢራ ፋብሪካ በዓመት 65 ሚሊዮን ሊትር፣ የአዲስ አበባው ፋብሪካ በዓመት አንድ ሚሊዮን ሊትር ቢራና የሀዋሳው በዓመት 50 ሚሊዮን ሊትር ቢራ በአጠቃላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ በዓመት 215 ሚሊዮን ጠርሙስ ቢራ እያመረተ ነው፡፡ የሀዋሳው ፋብሪካ ከ6 ወር በኋላ ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ በኋላ በዓመት ከአዲስ አበባው ፋብሪካ እኩል 100 ሚሊዮን ሊትር (1,000000 ሄክቶ ሊትር) ቢራ እንደሚያመርት ታውቋል፡፡

የሀዋሳው ቢራ ፋብሪካ የተገነባው በ14 ወራት ሲሆን በግንባታው 120 የውጭ አገር ባለሙያዎችና 1ሺ200 ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው 245 ቋሚ 150 ጊዜያዊና 2 የውጭ አገር በአጠቃላይ 397 ሠራተኞች አሉት፡፡ ፋብሪካው አካባቢን እንዳይበክል በ25 ሚ.ብር የተገዛ “ዌስት ወተር ትሪትመንት” መሳሪያ ተገጥሞለታል፡፡ መሳሪያው ከፋብሪካው የሚወጡ ፍሳሾችንና ዝቃጮችን ያጣራና ውሃው ንፁህ መሆኑ ሲረጋገጥ ለግቢው አትክልቶችና አበቦች አገልግሎት ይውላል፤ የተረፈው ደግሞ ወደ አካባቢው ወንዝ ይለቀቃል፡፡ የሃዋሳ ውሃ ፍሎራይድ ስላለው ለቢራ ጠመቃ፣ ለጠርሙስ፣ ለብርጭቆና ለበርሜል እጥበት ንፁህ እስኪሆን ድረስ “ሪቨርስ ኦስሞሲስ” በተባለ ዘዴ የሚያጣራ መሳሪያ ተገጥሞለታል፡፡

ድራፍትና ጠርሙስ ቢራ የሚለያዩት በካርቦንዳይኦክሳይድ ይዞታቸው፣ በአስተሻሸጋቸውና በፓስቸራይዜሽን ጊዜ ቆይታቸው ነው፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ፣ ድራፍት ቢራ ለ30 ሰኮንድ በ72 ዲግሪ ፓስቸራይዝድ ሲደረግ ለአንድ ወር ሳይበላሽ ይቆያል፡፡ ጠርሙስ ቢራ ደግሞ ለአንድ ሰዓት በ72 ዲግሪ ፓስቸራይዝድ ይደረጋል፡፡ ይህም ሳይበላሽ ለአንድ ዓመት እንዲቆይ ያደርገዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ አዳዲስ ምርቶችን ለማቅረብ ዝግጅት ላይ መሆኑን የፋብሪካው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ እርቀሰላም በለጠ ፋብሪካውን ባስጐበኙበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት “ካስቴል” ድራፍት ቢራ ለሙከራ ለአዲስ አበባ ገበያ ያቀረቡ ሲሆን፤ ወርቃማ ሆኖ ትንሽ ጠየም ያለ “አምበር” የተባለ ቢራ ለፋሲካ ለማድረስ እየሠሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ቢ ጂ አይ ኢትዮጵያ፤ ለሠራተኞቹ የ24 ሰዓት የክሊኒክ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከዚህ በላይ የሕክምና አገልግሎት የሚፈልግ ሠራተኛ፣ በአቅራቢያው ባለ ሆስፒታል እንዲታከም ይደረጋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሠራተኛው ከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልገው ከሆነ ከሠራተኛው የደሞዙን አንድ በመቶ፣ ከድርጅቱ ዘጠኝ በመቶ ተቀማጭ እየተደረገ ይታከማል፡፡ ዝዋይን ጨምሮ የኩባንያው ሠራተኞች ባሉበት ቦታ ሁሉ ከአፍሪካ ሰርቪስ ኮሙኒቲ ጋር በመተባበር የኤችአይቪ ሕክምና፣ የምክር አገልግሎትና መድኃኒት ያቀርባል፡፡ በስፖርት ታዋቂውን ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ ከመመሥረቱም በላይ የተለያዩ ከነማዎችን በማደራጀት አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ለኅብረተሰቡ ደግሞ ት/ቤቶችንና ቤተ - መጻሕፍትን በማስገንባት፣ መንገድ በመሥራት እንደሚሳተፍ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ አስረድተዋል፡፡

 

 

 

 

Read 10419 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 14:02