ሰሞኑን በአወሊያ ትምህርት ቤትና በአንዳንድ መስጊዶች የተነሣውን ውዝግብ አስመልክቶ ከአዲስ አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ውዝግቡ በአንዳንድ አክራሪ አስተሳሰብ ባላቸውና ህገወጥ ተግባራትን ለማራመድ በተዘጋጁ ሰዎች የተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው እነዚህ ግለሰቦች የግል ጥቅሞቻቸው የተነኩባቸውና በህገወጥ መንገድ ፍላጐታቸውን ለማስፈፀም የተዘጋጁ ናቸው ብለዋል፡፡ ተቃዋሚ አካላቱ የሚያነሱት የምርጫ አለመኖር ወይም ለአመታት መዘግየት ምክንያቱ ምንድነው በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም፤ ጠቅላይ ምክር ቤቱ በየወቅቱ ምርጫዎችን እያከናወነ መሆኑንና እሣቸውም በ2001 ዓ.ም በተካሄደ የምክር ቤቱ ምርጫ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን፣ የተሰጣቸው ኃላፊነት በምርጫ እንጂ በሹመት አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቀጣዩን ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ ለማድረግ የበጀት ማሰባሰቡ ሥራ መጀመሩንም ፕሬዚዳንቱ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ት/ቤቶችና በአንዳንድ የክልልና የአዲስ አበባ መስጊዶች አስተዳደሩን በመቃወም የፊርማ ማሰባሰብ ተግባር በማከናወን ላይ የሚገኙ ቡድኖች መኖራቸውን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህም ሙስሊሙን ከሌላ እምነት ተከታዮችና ከመንግስት ጋር ለማጋጨትና በሙስሊሞች መካከል ልዩነትን ለመፍጠር የሚደረግ ዘመቻ በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ ሊያወግዘው ይገባል ብለዋል፡፡ በአወሊያ ት/ቤትና በአንዳንድ መስጊዶች የጠቅላይ ምክር ቤቱን አስተዳደር በመቃወም ባለፈው ሳምንት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡