Print this page
Saturday, 04 February 2012 12:07

ጉዞ ወደ ጐንደር …ጐንደር - “ጉንደ - ሀገር”

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(1 Vote)

(የጉዞ ማስታወሻ) ክፍል ሦስት

ጨለማው ውስጥ…

ነጯ ሚኒባስ፣ 12 የታከታቸው ጋዜጠኞችን ይዛ መጓዟን ቀጥላለች፡፡ ከፎገራ እስከ ሊቦ ከምከም ለጥ ብላ የቆየች ምድር፣ ዳገት ቁልቁለት መስራት ጀምራለች፡፡ ጥቁር ጋራ፣ ጥቁር ገደል፣ ጥቁር አቀበት፣ ጥቁር ቁልቁለት፣ ጥቁር አስፓልት…ይሄ ከፊትለፊታችን የሚጠብቀን ድቅድቅ ጨለማ በውስጡ ጥቅጥቅ ደን ይዟል፡፡ “ጣራ ገዳም” ይሉታል፡፡ እዚህ ጨለማ ውስጥ ዋሻ እንድርያስና የወይን ዋሻ ተክሃይማኖት የሚባሉ ገዳማት አሉ፡፡ የጨለማ በርኖስ ደርቦ ፀጥ ያለው ዋሻ እንድርያስ፣ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት የኦሪት እምነት ይሰበክበት የነበረ ስፍራ መሆኑ ይነገራል፡፡ አለፍ ብሎ የሚገኘው ወይን ዋሻ ተክለሃይማኖት ደግሞ በአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግስት ተጀምሮ በአፄ ሰይፈ አርዕድ ዘመን የተጠናቀቀ ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ነው፡፡

መጓዛችንን ቀጥለናል…

ንጋት ላይ የጀመርነው መንገድ አልገፋ ብሎን በጨለማም እንሄዳለን፡፡ ዝም ብለናል፡፡ በየራሳችን ድካም ዝለን የየራሳችንን ሃሳብ እያብሰለሰልን ዝም ብለናል፡፡ ቢሄዱት ቢሄዱት የማይገፋ መንገድ፣ ጨለማ ውስጥ ሽቅብ ቁልቁል ያወጣ ያወርደናል፡፡

ድካም ይሰማኛል፡፡

እጅ እግሮቼ በድካም ዝለው፣ ባለሁበት መፈራረስ ጀምሬያለሁ፡፡ ልክ እንደ ጉዛራ… ወዲያ ማዶ በስተቀኝ ጨለማው ውስጥ እንደተደበቀው ጉዛራ፡፡

ያ…የማይታየኝ፣ ጋራው ላይ ጨለማ ለብሶ ዝም ያለው ጥንታዊ ህንፃ፣ በአፄ ሰርፀ ድንግል ዘመን የተገነባውና ምናልባትም በጐንደር ምድር ከተገነቡት አብያተ መንግስታት ቀዳሚው ሊሆን እንደሚችል የሚነገርለት ጉዛራ ነው፡፡

በአለም ቅርስነት የተመዘገበውን ይህን ጥንታዊ ቤተ መንግስት እርጅና ተጫጭኖታል፡፡ ከ400 አመታት በላይ የዘለቀውን ድንቅ የኪነ ህንፃ ውጤት ወደኋላችን ትተን ጥቂት እንደተጓዝን ዳገት ላይ የተከተመችው እንፍራንዝ ጠበቀችን፡፡

“እስኪ ቸር አሳድረኝ” ለማለት የተዘጋጀች… በሮቿን መዘጋጋት፣ ምንጣፎቿን መዘረጋጋት የጀመረች እንፍራንዝ፡፡

ጋደም ብላ ከድካሟ ለማረፍ ማነጣጠፍ በጀመረችው እንፍራንዝ ቀናሁ፡፡ እየቀናሁ ወደ ማረፊያዬ እሄዳለሁ…እረፍቴ ጐንደር ናት፡፡ እዚያ ነው የኔ አዳር… ጐንደር ነው የኛ እንቅልፍ! እርቃብን ተቸገርን እንጂ ተሳክቶልን ካገኘናት ጐንደር ነው መኝታችን፡፡ ለነገሩ መተኛት መቻላችንንም እጠራጠራለሁ፡፡

የእያንዳንዳችን ሞባይል ስራ በዝቶበታል፡፡ ደዋዩ በርክቷል፡፡ ይሄኛውን ደዋይ ሳናሰናብት ሌላኛው “መጣሁ” ይላል፡፡ ዝም ብለው የዋሉ ሞባይሎች ከመሸ በስራ ተጠምደዋል፡፡ ሚኒባሷ ውስጥ የጥሪ ድምፆች በርክተዋል፡፡ ሁሉም ለጥሪው ምላሽ ለመስጠት ይተጋል፡፡ ከየአቅጣጫው ይደወላል፡፡ ከሩቅም ከቅርብም፣ ከተለያዩ ቦታዎች፡፡

የሚደወለው ከተለያየ ቦታ ሊሆን ይችላል፡፡

ደዋዮች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የሞባይሎቻችን የጥሪ ድምጽም የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የደዋዮች የመደወል ምክንያት ግን አንድ ነበር፡፡

አንድ አይነት መልስ ባንሰጥም፣ አንድ አይነት ጥያቄ ነበር

ከደዋዮቻችን የምንቀበለው፡፡

“ከተሰማው ጉድ ተረፋችሁ ወይ” የሚል፡፡

ኢቴቪ በምሽት ዜና እወጃው ስለ አሰቃቂው የአባይ በረሃ የመኪና አደጋ ያቀረበውን ዘገባ የሰሙ ናቸው ደዋዮቹ፡

ሰምተው የማያምኑ ደዋዮች…”በእርግጥ ተርፈሃል?” የሚሉ፡፡

በሰሙት የደነገጡ ደዋዮች… ”አቤት ተአምር!” የሚሉ፡፡

ስለ እኛ የሰጉ ደዋዮች…”በሉ እናንተም ተረጋጉ” የሚሉ፡

እና ደግሞ

አብዝተው ጠያቂ ደዋዮች…”ኢቴቪ አሳጠረው፣ እስኪ አንተ ዘርዝረው፡፡

አውቶብሱ ሲጋይ ስንት ሰው ነበረው?”…የሚሉ ዜናው ያጠረባቸው ደዋዮች፡፡

ረሳነው ያልነውን ሰቆቃ መልሰው የሚያስታውሱን…

ጐንደር ደረስን ስንል፣ ወደ አባይ የሚመልሱን፡፡

አዘዞ ደርሰናል፡፡ ባሻገር ማዶ ተራራው ላይ ጉብ ያለችዋ ጐንደር፣ ቁልቁል እንዳትንሸራተት ደግፌያት ተብላ እግሯ ስር የተሸጐጠች ትንሽ “ታኮ” ትመስላለች…አዘዞ፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት ጐንደር ገባን፡፡

እንባዋን ስትረጭ፣ ፊቷን ስትነጭ፣ ማቅ ለብሳ እዬዬ ስትል የዋለች ጐንደር…

በአንድ ቀን ብዙ መርዶ መጥቶባት ከዳር ዳር ያዘነች ጐንደር…

እናታለም ጐንደር ከደጃፍ ደጃፍ ባይበቃት፣ ከአፋፍ አፋፍ ጥቁር የሰማይ ድንኳን ጥላ እዝን ተቀምጣለች፡፡

እኔ ተኝቻለሁ…

በተዘጋጀልኝ አልጋ ላይ ተኝቻለሁ፡፡

ተኝቼ እንሳፈፋለሁ፡፡ አልጋ ላይ እንሳፈፋለሁ… አንሶላ ውስጥ እንሳፈፋለሁ… ሚኒባስ ውስጥ እንሳፈፋለሁ…በረሃ ውስጥ እንሳፈፋለሁ፡፡

በህልምና በእውን መካከል አንዣብባለሁ፡፡ በጐንደር እና በአባይ፣ በአልጋና በሸለቆ መካከል ጋዜጠኛ ሆኜ፣ መንገደኛ ሆኜ፣ ሰው ሆኜ…

ጥር 9 ቀን 2004 ዓ.ም ተሲያት በኋላ ጐንደር በመንታ ስሜቶች ውስጥ ናት፡፡

ከየአቅጣጫው ነቅሎ ወጥቶ ፒያሳን ከአፍ እስከ ገደፏ ያጥለቀለቃት ህዝብ በደስታና በሀዘን መካከል ነው የሚገኘው፡፡ ጥምቀትን በጐንደር ሊታደም ወጥቶ መንገድ ላይ በድንገተኛ የመኪና አደጋ በእሳት የተለበለበው፣ አመድ ሆኖ አባይ በረሃ ውስጥ ከጉዞው የተገታው 40 መንገደኛ መርዶ የህዝቡን ልብ በመሪር ሃዘን ውስጥ ከቶታል፡፡

ይህ መርዶ መላ ጐንደርን ክፉኛ አስደንግጧል፡፡ የከተማዋ ነዋሪ ጥምቀትን በጉጉት ሲጠብቅ ነበር፡፡ በእልልታና በሆታ በአሉን በድምቀት ለማክበር እየተዘጋጀ ባለበት ጊዜ ግን ያልተጠበቀው መርዶ ተሰማ፡፡ ለታቦታቱ ማደሪያ ብቻ ሳይሆን ለለቀስተኞች ማረፊያ የሚሆኑ ድንኳኖች ተተከሉ፡፡ የጐንደር ህዝብ መሪር ሀዘን ውስጥ ገባ፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኖ ነው ህዝቡ ወደ ፒያሳ መጉረፍ የጀመረው፡፡ መሀል ፒያሳ ላይ ህዝቡ በጉጉት የሚጠብቀው ነገር አለ፡፡

“በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንድናደርግ እጠይቃለሁ” አለ የፕሮግራሙ መሪ፡፡

ሁሉም አንገቱን አቀረቀረ፡፡ ፒያሳ ሰጥ ረጭ አለች፡፡ ሁሉም ሟቾችን እያሰበ አቀረቀረ፡፡

ህዝቡ ሟቾችን በፀሎት የሚያስብበት አንድ ደቂቃ አልቆ ካቀረቀረበት ቀና ሲል ግን፣ ለአንድ ደቂቃ ሳይሆን ለዘመናት የሚያስበውን፣ የሚኮራባት የሚዘፍንለት ጀግናውን ነበር የተመለከተው፡፡

ፀጥ ብላ የቆየችው ፒያሳ በእልልታና በጩኸት ተናጋች፡፡ የማርሽ ቡድን ሙዚቃ፣ የአባት አርበኞች ፉከራ፣ የሴቶች እልልታ፣ የከበሮው ምት፣ የጡሩንባው ጩኸት…ሁሉም በአንድ ተቀይጦ ፒያሳን አናወጣት፡፡ ሁሉም በጀግንነት ስሜት እየተንቀጠቀጠ ፒያሳ መሃል ወዳለው አደባባይ አይኖቹን ወረወረ፡፡ መቅደላ “ላይ እጄን አልሰጥም” ብሎ ሽጉጡን ጠጥቶ በክብር የወደቀው አባ ታጠቅ ካሳ አደባባዩ ላይ ከፍ ብሎ ቆሟል፡፡ ከእነ ጐራዴው፣ ከእነ ጋሻው፣ ከእነ ወኔው ባለ ሁለት ምላስ ጦሩን ጨብጦ ደረቱን ነፍቶ ቆሟል፡፡ ያቀበጠው ፈረንጅ “እጅ ስጥ” ሊለው መጣ የተባለ ይመስል፣ በቁጣ ነድዶ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ አሻግሮ ይመለከታል፡፡

ህዝቡ በሆታና በእልልታ ዙሪያ ገባውን እየቀወጠ፣ እየተጋፋ፣ አንዱ በሌላው ላይ እየተነባበረ አሻግሮ የሚመለከተው ባለሙያ ብዙነህ ተስፋ ብዙነህ የቀረፀውን “ሀውልቱን” ቴዎድሮስ አይመስልም፡፡ ራሱን ቴዎድሮስን እንጂ፡፡ ሰውዬው ቴዎድሮስን… አባታጠቅ ካሳ... የቋራው አንበሳ…አደባባዩ መሀል እንደ ሀውልት ሳይሆን እንደ ሰው ከእነ ጀግንነቱ ቆሟል፡፡

እምዬ ጐንደር ጀግናዋን እያየች “እልል” ትላለች፡፡

የጥምቀትን በአል መሰረት በማድረግ የውጭ ጐብኝዎችን ቆይታ ሊያራዝም የሚችል፣ የአገሪቱን መልካም ገጽታ በመላው አለም የሚያስተዋውቅና ባህልን የሚያበለጽግ፣ የባህል ትስስር የሚፈጥር “ኢትዮጵያን በጐንደር ብሔራዊ ትዕይንት” የተሰኘ ድግሷን ለታዳሚዎቿ ማቋደስ ጀምራለች፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ብሔራዊ ትዕይንት፤ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ መከበሩን ይቀጥላል፡፡

እንኳን እንዲህ ድርብ በአል ኖሮባት ድሮም ጐንደር በዚህ ሰሞን ሙሽራ ሆና ነው የምትታየው፡፡ ደምቃና አጊጣ፡፡

እንዲህ ተውባ ሊያዩዋት የሚጓጉቱ፣ በተለይ ጥምቀት ሲደርስ በርከት ብለው ነው ወደ ጐንደር የሚመጡት፡፡

ፒያሳን ከአፍ እስከ ገደፏ ሞልቶ ከቆመው ህዝብ መሀል፣ ወደ አደባባዩ ከተወረወሩ፣ አባ ታጠቅ ካሳ ላይ ካረፉ የህዝብ አይኖች መካከል ብዙ የሩቅ አገር አይኖች አሉበት፡፡

ከአለም ዙሪያ የመጡ በርካታ ቱሪስቶች ጐንደርን ያጣጥሟታል፡፡

እልልታና ሆታ ሆኗል፡፡ እዚህም እዚያም ይዘፈናል፡፡

“እምዬ ጐንደር …ጐንደር

የፋሲል መዲና የቴዎድሮስ አገር” ይባላል፡፡

በየመንገዱ ላይ፣ በየጥጋጥጉ እስክስታ እሚመቱ፣ እሚውረገረጉ…

የጐንደር ሹርቢት፣ የጐንደር ኮበሌ…ትላለች “በቴዲ”፣ ይላል

“በአባ ጃሌ”…

“አረጀች እያሉ ሰዎቹ ሲያሙሽ

ሙሽራ ነሽ ጐንደር ይሰፋል ልብስሽ” ከወዲህ ይላታል አዝማሪው፣ ውበቷን መስካሪው፡፡

ይህቺው እማማ ጐንደር፡፡ ዘመን ቀለሟን የማያደበዝዘው፤ እርጅና የማይነካካት፣ ሙሽሪት ጐንደር፣ ፀአዳ ቀሚሷን በተራራ መቀነት ሸብ አድርጋ እስክስታ ትወርዳለች፡፡

ከአንገረብና ከቀሃ ወንዞች መካከል ከዘመናት በፊት የበቀለች ትንሽዬ መንደር፡፡ የነገስታት አምባ፣ የታሪክ ማህደር፡፡

ጐንደር…

“ጐንደር - ሃገር”

“የሀገር ግንድ”፣ “የሀገር መሰረት”፣ “ርዕሰ - ሀገር”፣ “የሀገር ራስ”…እንዲህ ማለት ናት በግዕዝ አፍ - ጐንደር፡፡

(ይቀጥላል)

 

 

Read 18381 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 14:07