Saturday, 04 February 2012 12:10

የላሊበላው የጉዞ ማስታወሻ ነአኩቶ ለአብ ቤተክርስቲያን ደረስን - ተመስገን ነው!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(0 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)

የደሴን ቅዝቃዜ ሳስብ ሁለት ነገሮች ይመጡብኛል፡፡ አንደኛው “ደሴ ሲገቡ አልቅሶ፣ ሲወጡ አልቅሶ” የሚለው መሠረታዊ አባባል ነው፡፡ ሁለተኛው፤ በሥራ አጋጣሚ የማውቃት ያች ሞቃት ከተማ፣ ደሴ፣ ምን ነካት? የሚለው የራሴ አግራሞት ነው፡፡ ዱሮም ደሴ’ኮ ለመጀመሪያ ሲገቡባት ታስለቅሳለች፡፡ ትደብራለች፡፡ ከዳገቱ ላይ ቁልቁል ወደ ደሴ ሲገቡ የሚታየው የዛገ የሚመስል ቆርቆሮ ጣራ ያስደነግጣል፡፡ (ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስ”፣ ውስጥ “እግዜር ሠርቶ ሠርቶ የተረፈውን ዕቃ ሁሉ ያከተባት፣” የሚለው ደሴን ነው ደብረ - ሲናን ያሰኛል) እያደር ግን ከደሴ ጋር በፍቅር መውደቅ አይቀሬ ነው፡፡ ሰው ፍቅር ያስይዛል፡፡ ሙዚቃው ፍቅር ያስይዛል፡፡ ጀበናው ፍቅር ያስይዛል፡፡ አዝማሪው ፍቅር ያስይዛል፡፡ ጉራንጉሩ ፍቅሩ ያስይዛል፡፡

“ዝንጀሮው ከዳገት ይመስላል አረንዛ

በይ ቶሎ ጨርሺኝ ጣረ - ሞቴ አይብዛ” የሚባለው ከዚያ በኋላ ነው፡፡

ከዚያ እንግዲህ ከደሴ ለመውጣት ጣር ይሆናል፡፡ ይሄኔ ነው በቃ “አይ ደሴ! ሲገቡ አልቅሶ፣ ሲወጡ አልቅሶ” የሚለው ነገር የሚፈጠረው፡፡

ያም ሆኖ አንድ ሌሊት ያደርንባት ደሴ ግን ቅዝቃዜው እየጠዘጠዘን ነው፤ እስከ 8፡30 ከሌሊቱ ያቆየችን፡፡ እናም የተሰናበትኳት በሚከተለው ግጥም ነው:-

ጣራው ቆርቆሮ ነው፣ ግድግዳው ቆርቆሮ

በሩም ያው ቆርቆሮ፤

እንዴት ይዘለቃል፤ ብርድ ተነባብሮ፡፡

ብዬ ደሴን ጠየኩ፣ ገባኝ ትርጉሙ አድሮ

መነሻው ቢከፋ

መሄጃው ቢከፋ

መድረሻው ነው ፋታ

ብረት መንፈስ ካለ፣ ሁሉን የሚረታ

እንኳን መደዴው ብርድ፣ ይገፋል ጐልጐታ!!

ታህሳስ 27/2004

(ለመንፈሰ - ጠንካሮች)

ዕቃችን ተጫነና አውቶብሱ ላይ ተሳፈርን፡፡

“ከጐናችሁ ሰው ቀርቶ እንደሆነ ተናገሩ” አሉ አባ፡፡

“ሁለት ሰዎች ቀርተዋል” አለ አንዱ ከኋላ፡፡

“ይደወልላቸው” አለ ሌላኛው፡፡

“ከእኛ ጋር አላደሩም ቢደወልላቸው ነው የሚሻለው”

“ታክሲ አጥተው ይሆናል” አለች አንዷ፡፡

“ሰው ሰዓት ተነግሮት እንዴት ይዘገያል?”

“የተባለው አሥር ሰዓት ነው ገና 15 ደቂቃ ይቀራል፡፡ ለምን ለወቀሳ ትቸኩላላችሁ?” አሉ እማሆይ፡፡

“ዞሮ ዞሮ ጥፋቱ የአውቶብሱ ማህበር ነው፡፡ ስልክ ጠይቀውን ሰጥተናል፡፡ እንዴት የስልኩን ዝርዝር ረስተው ይመጣሉ?”

እንሥራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች፤ ማለት ይሄ ነው፡፡

አባ ሌላ መፍትሔ ሰነዘሩ፡፡ “ስም እጠራለሁ” አሉ፡፡ የአበሻ ነገር መጣ “ከአንበሳና ከዝሆን ማን ያሸንፋል?” ቢሉት “ከሁሉም ከሁሉም አሣ ሙልጭልጭ ነው” አለ፤ እንደሚባለው፡፡ “አሁን ስም ባይጠራ ቢጠራ ያረፈዱትን ሰዎች ላያመጣ ይልቅ ስልካቸውን ባገኙና በተደወለላቸው”

አባ ስም ጠሩ፡፡ የሌሉት አሁንም የሉም፡፡ አዲሳባ ስልክ ተደወለና የስልካችን ዝርዝር ተጠየቀ፡፡ የአዲሳባው ሰው በዚህ በሌሉት ስልኩ በእጁ እንደማይገኝ ገለፁ፡፡

“በቃ እንጠብቃቸው” ተባለ፡፡ ንጭንጩና ሀሳብ መስጠቱ ግን አላቋረጠም፡፡ “ዘመድ አቆይቷቸው ነው…አንድ አንድ ስኒ ቡና፤ ሲሉ ነው”…

“ታክሲ አጥተው ነው”…

የገረመኝ አበሻ ዕድል ከተሰጠው የጨረባ ተስካር ለመፍጠር አፍታም የማይፈጅበት መሆኑ ነው፡፡

ሁለቱ ያረፈዱት ሴቶች በ10 ሰዓት ከሩብ መጡ፡፡

“መጡ…መጡ…መጡ” ተባለ፡፡ ገቡ፡፡ እየሳቁ ነው የገቡት፡፡

ከጀርባችን ያሉት አሮጊት፤

“ኧረዲያ ከማርፈዳቸው የመሳቃቸው” አሉና አማረርን፡፡

መንገድ ቀጠልን፡፡ መርሳ ደረስን፡፡ ለንፋስ ወረድን፡፡ መርሳ - አባ ጌትዬ ነው የሚሉት አንዳንዶች፡፡

ወልዲያ ለቤንዚን ቆምን፡፡ ቤንዚን ማደያው ውስጥ ፈትል ጥበብ የሚሸጡ ሴቶች በየመስኮቱ መጡ፡፡ ሴቱ ስንት ስንት ነው ማለት ጀመረ፡፡ ሻጮቹም የላሊበላ ተጓዥ እንደሚገዛ ይገምታሉ፡፡ ገዢዎቹም ነዋሪው ሊሸጥ እንደሚመጣ ያቃሉ፡፡ ድር በድር ባለሰፊ ጥለት አለ፡፡ ግን ማንም አልገዛም፡፡ በኋላ አንዲት እናት፤

“እነሱኮ ለፈረንጅ ሊሸጡ ነው ያመጡት፡፡ ይሄ ለቱሪስት የሚሸጡበት ዋጋ ነው፡፡” አሉ፡፡

“ታዲያ እኛ ነና ጥፋተኞች! ለፈረንጅ እንደሆነ እያወቅን ዋጋ እምንጠያየቀው” አሉ ሌላኛዋ፡፡

እንግዲህ ጉዞ ወደላሊበላ ነው፡፡

በመጀመሪያ የደረስነው ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ቤተክርስቲያን ነው - ተመስገን ነው!

“በሉ እንግዲህ በ15 ደቂቃ ነአኩቶ ለአብ ቤተክርስቲያንን ተሳልመን እንመለስ” አሉን ከአመራሮቹ አንዱ፡፡ ይሄ የመንገድ ርቀት ጉዳይ እስከመጨረሻው ያስገረመኝ ነገር ነው - እናየዋለን፡፡

መንገዱን ስንጀምረው እንኳን 15 ደቂቃ አንድ ሰዓትም አይበቃው

“የቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ቤተክርስቲያን ከላሊበላ በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ስድስት ኪሎ ሜትር ወደ አየር መንገድ በሚወስደው የአስፓልት መንገድ በመኪና ከተጓዙ በኋላ ወደ ውስጥ ከአንድ ኪሎ ሜትር ያላነሰ ያስገባል፡፡ ገባ ብሎ በተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ የተሠራ ድንቅ ጥበብ የተከናወነበት ቤተክርስቲያን ነው” ይላል ስለቤተክርስቲያኑ የተፃፈው ጽሑፍ፡፡

አንድ አዛውንት መቋሚያቸውን ይዘው አብረውኝ ወደዋሻው ይጓዛሉ፡፡

“ባለአውቶብሶቹ ቅርብ ነው ይላሉ እንጂ ሩቅ እኮ ነው” አልኳቸው፤ ገና ከአስፋልቱ ማሳውን ስናቋርጥ፤ በከተምኛ ቃና፡፡

“ተወው፡፡ በላሊበላ ዙሪያ ያሉ ገዳማትና አድባራት ቅርብ የሚባል የለባቸውም፡፡ ግን መንፈሱ ያቀርባቸዋል” አሉኝ ፍርጥም ብለው፤ በልበ ሙሉነት፡፡

የመጀመሪያ ትምህርቴን ከእኒህ አዛውንት አገኘሁ ማለት ነው፡፡

“ነአኩቶ ለአብ ማነው?” አልኳቸው ዘና ብዬ፡፡ ቀና ብለው አዩኝና፤

“የዚህ ዘመን ሰው ነህ መሰል፡፡ ለዚህ ቦታ አዲስ ነህ?” አሉኝ በዐይናቸው ዕድሜዬን ለመገመት እየሞከሩ፡፡ መልስም ሳይጠብቁ ቀጠሉ፤

“ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ፣ አባቱ የቅዱስ ላሊበላ ታላቅ ወንድም ቅዱስ ገብረማሪያም ነው፡፡ እናቱ መርኬዛ ትባላለች፡፡ በ13ኛው ክፍለ ዘመን ነው የተወለደ፡፡”

“የት አድጐ ነው?” አልኳቸው፡፡ “በአጐቱ በቅዱስ ላሊበላ ቤተመንግስት ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥበብን እየተማረ፣ እየከወነ” አሉ፡፡

ልበ - ሙሉነታቸው ይገርማል፡፡ ብዙዎቹ የታሪክ ባለሙያቻችን እንዲህ ያለ ፍርጥምታ አይታይባቸውም፡፡ (“ምሁር አንፃር ያበዛል” እንዳሉት ነው፡፡ ጓድ ደበላ ዲንሣ በአንድ ወቅት ሶማሊያ ላይ ደርግ 300ሺ ሚሊሺያ ለማዝመት እንዳሰበ ለምሁራኑ ገልፀን ብናማክራቸው “በኢኮኖሚ አንፃር፣ በአንትሮፖሎጂ አንፃር፣ በሶሺዮሎጂ አንፃር በፖለቲካ አንፃር በጂኦ ፖለቲክስ አንፃር እያሉ ዘመቻውን ሊያስተጓጉሉት ሆነ፤ ምሁር አንፃር፣ ያበዛል እኛ በአንድ ጊዜ 300ሺ ሚሊሺያ መልምለን አዘመትን… ድል መታናት!”)

ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ከዚያ እንዴት ወዲህ መጣ?” ሳቅ አሉ፡፡ “ማንም ጅል የማይስተውን አንተ እንደምን አጣኸው” በሚል አስተያየት ነው ያዩኝ፡፡

“እንዴ! እንዳልኩህ ባማረ ወግ ትምርቱን ከከወነ በኋላ ንጽህት የምትባል ቆንጂት የካህን ልጅ አገባ፡፡ ከዚያ ቅዱስ ላሊበላ አጐቱ በላስታና አካባቢዋ አገረ ገዢ አደረገው”

“አገረ ገዢ? ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ በዛሬው ማለት ነው?”

“አዬ ልጄ! ሰው እንጂ ቃላቱ አይገዛ! ከገዛ ማስተዳደሩ ይቀራል? አዘለም አልከው አንጠለጠለም አልከው፤ ያው ተሸከመ አደል? ሾመውና ኋላም ከላሊበላም እረፍት በኋላ ክህነትን ከመንግሥት አንድ አድርጐ ገዛ፡፡”

“ከዛስ?”

“ንግሥናውን ለቅዱስ ላሊበላ ልጅ ለይትባረክ አስረከበው”

“ለምን ማስተዳደሩን አልቀጠለም? አባቴ ዛሬ’ኮ እንደዚህ አገረ ገዥነት ዝም ብሎ አይለቀቅም!?”

“ዋዘኛ ነህ! ይህኛው አየህ የመንፈስ ግዛት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ተገልፆ ወደ ቤተክርስቲያን እነፃው መራው”

“በጽሑፉ እንዳየሁት - “በዘመንህ ሁሉ የኔን መከራ እያሰብህ እንዳላቀስህ ከቤተ - መቅደስህ በዕንባህ ምሳሌ ለፈውስ የሚሆን ፀበል ይፈልቃል፤ የኔን ጌትነት የአንተን አማላጅነት አምነው የሚጠጡና የሚፀበሉ ድውያን ይፈወሳሉ” ባለው መሠረት” የሚለው ነው?

“እንግዲያ! ይሄን እያወቅህ ነው ልቤን የምታደርቀኝ?” በጣም ተደስተው ነው የተናገሩት፡፡ ወተት የመሰሉት ጥርሶቻቸው በግራጫ ጢማቸው መካከል የዳመና ፀሐይ ይመስላሉ፡፡ ደስ የሚሉ አዛውንት!

“ይሄ ፀበል በወሬ እንደሰማሁት”

አቋረጡኝ፡፡ “የምን ወሬ በዐይንህ ልታየው አደል? ዐይንህ የሚያየውን ልብህ የሚቀበለው ግን፣ ልብህ ንፁህ ሲሆን ብቻ ነው” አሉና መለስ - ቀለስ እያሉ ወደ ዋሻው ፈጠኑ፤ ፀበሉን ሊያሳዩኝ የቸኮሉ ይመስላሉ፡፡ እኔ ሁለተኛ ትምህርቴን አገኘሁ፡፡

“ከዋሻው ፈልፍሎ ነው ቤተክርስቲያኑን ያንፀው?” ስል ጠየቅሁ፡፡

“እንዴታ! ይሄኛውን ብቻ መሰለህ ያነፀው? አሸተን ማርያምን እዚያ (በመቋሚያቸው እየጠቆሙኝ) ወዲያ ማዶ ቂርቆስ አምባ ተራራ ሥር ናት… እሷንም ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ነው ያነፃት፡፡ ከዚህ ዋሻ ከአሸተን ማርያም የሚያገናኝ ዋሻ እንዳለ ካህናቱ ይናገራሉ፡፡ የተሰወሩ ቅዱሳን የእሷን መቅደስ ምሥጋና እያቀረበ እያጠነ ያገኙትና “እንዴት አገኛችሁኝ?” ብሎ ጠየቃቸው ይላሉ፡፡

“የከበረ ዕጣኑን መዓዛ አሸትተን!” አሉት ይባላል፡፡ ለዚህ ነው አሸተን ማርያም የተባለችው፡፡ ታዲያ አየኸው… በዕንባው ምሳሌ ጠብ ጠብ የሚለው ፀበል እስከዛሬ ምዕመናንን እየፈወሰ ይገኛል፡፡

በተራራ ጥግ የሄድን በሚመስል መንገድ ልዩ ልዩ የፀሎት መጽሐፍት በሚሸጡበት ቦታ አድርገን፣ ቁልቁል የሚያወርዱ ደረጃዎችን ወርደን ወደ ዋሻ ፍልፍሉ ቤተክርስቲያን ቀረብን፡፡ አንዲት ከእኛው ጋር በአውቶብስ የመጣች፤ አውስትራሊያ አገር ነዋሪ ልጅ እዚያ አገኘሁ፡፡

“እንዴት አገኘሽው”

“ኧረ ተዓምር ነው በማርያም፡፡ እኔ ዕድሜ ልኬን ስመኘው የኖርኩትን ነገር እኮ ነው እያየሁ ያለሁት፡፡ ቆይ ፎቶ ላንሳው” ብላ አነሳች፡፡

እኔም ከየአቅጣጫው አነሳሁት፡፡

የዋሻው ፍልፍል እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ እንዴት አስቦ እንደፈለፈለው ሲታሰብማ አንጐል ያዞራል፡፡

እኛ አዛውንት ይጠብቁኝ ኖሯል፤

“ከመቅደሱ አናት ጠብ ጠብ የሚለው ፀበል ያውልህ” አሉኝ!! የፊታቸው ፀዳል ድል አድራጊነትን ያንፀባርቃል፡፡ “ንፅህይት” የተባለች ፀበል ናት” አሉ አክለው፡፡

ደስ አለኝ፡፡ ነአኩቶ ለአብ ማለት ህዝቡ ነው፡፡ ላሊበላ ማለት ህዝቡ ነው የሚል የግጥም ጽንስ በውስጤ አቆጠቆጠ፡፡

ውስጡም እንደዚያው ተአምር ነው፡፡ ወደ ዋሻው ስንዘልቅ ቅኔ ማህሌቱም ቅድስቱም ጣሪያቸው አንድ ነው፡፡ ቋጥኝ ሥር ነው ያሉት፡፡ በውስጣቸው ወደፊት በብዛት እንደምናያቸው ሁሉ፤ አያሌ የሥዕል ጥበቦች አሉ፡፡ ነገሥታት በገፀ - በረከትነት ለዚህ ገዳም ያበረከቷቸው ውድና ውብ ቅርሶች፣ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ የወርቅ ቅብ ከበሮዎች፣ የወርቅ ካባዎች፣ የብር ከበሮ፣ መስቀሎች፣ አክሊሎች እና 6 መቶ ዓመትና ከዚያም በላይ የቆዩ የብራና መፃሕፍት ይታያሉ፡፡ በተለይ የዐይን መስህብነት ያለው አፄ ነአኩቶ ለአብ ከጦርነት መልስ ይዞ እንደመጣ የሚነገረው እና “ስማ ጐንደር” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ከበሮ ድንቅ ነው!

እኒያን አዛውንት “ተሰወረ የሚባለውስ?” አልኳቸው፡፡

“እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ድንግል፤ እንደ ነቢዩ ኤልያስ የተሰወረ እና ሞትን ያልቀመሰ መሆኑ የታወቀ ነው’ኮ! ያካባቢው ነዋሪ ሲምል ሥውሩን የሚለው ወዶ መሰለህ በዕውነት’ኮ ነው፤ ህዳር 3 ቀን፣ የተሠወረበትን ዕለት ታከብረዋለች ቤተክርስቲያናችን”

የእኒህ ሰው ነገር የደራሲ ከበደ ሚካኤልን ነገር አስታወሰኝ፡፡

አንዴ ደራሲ ከበደን፤

“በዚህ በእኛ ትውልድና በእርሶ ትውልድ መካከል ያለው ልዩነት ምን ይመስልዎታል?” ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡

እሳቸውም፤

“ይሄ የእናንተ ትውልድ “ነው” ማለት አያውቅም፡፡ “ይመስለኛል… ይሆን ይሆናል… እገምታለሁ… እንዲያ ይሰማኛል… እንዲህ ነው ብዬ ነው የምገምተው” ነው የሚለው፡፡ ውስጡ ጥርጣሬ እንጂ የመንፈስ ጽናት፣ የዕውቀት ጥንካሬ የሌለው ነው!”

“አየህ የሚያጠራጥርህን አለመናገር ነው፡፡ የማያጠራጥርህን ደግሞ አለመሸሸግ” አሉኝ፡፡

የእኒህ አዛውንትና የደራሲ ከበደ ሚካኤል መመሳሰል ገርሞኛል፡፡

በመጨረሻ ስለያቸው “አባቴ የትኛው አውቶብስ ውስጥ ነዎ? ቁጥሩን ያውቁታል?” አልኳቸው፡፡ ሳቁ፡፡

“እኔ አውቶቡስ የለኝም፤ ብዙ ያጠድቃል ብዬም አላምን! በእግሬ ከቤቴ ከወጣሁ አራት ቀኔ ነው፡፡ ቅዱስ ላሊበላን በቀኑ አገኘዋለሁ፡፡ በአውቶቡስ ወደቤተክርስቲያን ብሄድ፣ ከነጫማዬ ወደ መቅደሱ የገባሁ እየመሰለኝ ተቸግሬ ነው፡፡ በል ቅዱስ ላሊበላ በሰላም ያድርሳችሁ” አሉ፡፡

“አሜን እርሶንም በሰላም ያግባዎ!”

“አይ ልጄ! እኔማ በእግሬ ነኝ፤ ምን እሆናለሁ?” ብለውኝ ሄዱ!

(ይቀጥላል)

 

 

Read 3733 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:14