Saturday, 04 February 2012 12:47

የሶማሌውን ስደተኛ መነሻ ያደረገው “ቡም” ፊልም ሊሰራ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ፊልሙ 1.5 ሚ. ብር ይፍጃል ተብሏል

አያልነህ ሙላት ፊልሙን ዲያሬክት ያደርጉታል

በመላው አፍሪካ እንዲታይ ታስቦ የሚሰራ ፊልም ነው

ዓለም በቀዝቃዛው ጦርነት የምትታመስበት ዘመን ነበር፡፡ የታሪኩ ዋና ገፀ ባህርይ ሶማሊያዊ ፓይለት ሲሆን በወቅቱ በአገሩ ሶማሊያ ሰተት ብሎ የገባውን የሶቭየት ህብረት የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም በመቃወም አውሮፕላን እያበረረ ኢትዮጵያ አረፈ፡፡ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቆም የኢትዮጵያ መንግስት ፈቀደለት፡፡ ንጉሱ ያዘዙት አይነት ባይሆንም ሥራና ቤት ተሰጥቶት ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ጀመረ፡፡ ተክለሃይማኖት አካባቢ፡፡ ፓይለቱ መጠጊያ ባያጣም ደህንነቱ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ከሶማሊያ መንግሥት የተላኩ ደህንነቶች ይከታተሉት ነበረ፡፡ አንድ ቀን በመኪና ገጭተውት ሆስፒታል ገባ፡፡ ኢትዮጵያ ከገባ ከሁለት ዓመት በኋላ ንጉሱ ወርደው ደርግ ተተካ፡፡ ሶማሊያዊው ከዚህ በኋላ ነው ፈታኝ ህይወት የሚገጥመው፡፡

ይሄ እውነተኛ ታሪክ በሸገር ሬዲዮ ላይ ተቀነጫጭቦ ቀርቦ እንደነበር የሚናገረው ደራሲ ብሩክ ከበደ፤ በአንድ የአፍሪካ ጥናት ማዕከል የግዢ ጥያቄ ቀርቦለት እንደነበር ያወሳል፡፡ እሱ ግን ወደ ፊልም ተቀይሮ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአህጉሩም እንዲታይ ፍላጐት ስለነበረው ሳይሸጠው ቀረ፡፡

የአፍሪካ አምባገነኖች በየጊዜው በሚፈጥሩት ፖለቲካዊ ፍርሃት የተነሳ በተማሩ ዜጎቻቸው መጠቀም አልቻሉም የሚለው ብሩክ፤ አፍሪካውያን መሪዎች በራሳቸው ምሁራን አለመጠቀማቸው የሚያመጣውን ዘርፈ ብዙ ችግር ታሪኩ ይጠቁማል ብሏል፡፡ ይሄን ታሪክ አንጋፋው የጥበብ ባለሙያ አያልነህ ሙላት ወደፊልም ፅሁፍ እንደሚቀይሩት የገለፀው ደራሲው፤ ፊልሙ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካን፣ ላቲን አሜሪካንና እስያን ጭምር ያነቃቃል የሚል እምነት አለው፡፡ ፊልሙ ስደት እንዲገታ፣ ዜጎች በአገራቸው ሰርተው እንዲኖሩና እውቀታቸውንም ለህዝባቸው እንዲያካፍሉም ያነሳሳል ብሏል - ደራሲው፡፡

የብሩክ ከበደን በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመረኮዘ ልቦለድ  ወደ ፊልም በመቀየር “የመጨረሻው ምርጥ ስራዬ አደርገዋለሁ” ብለዋል የአዘጋጅነቱን ሃላፊነት የወሰዱት ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላት፡፡ ታሪኩን ሲያነቡ ሁለት ነገሮች ስሜታቸውን እንደነካው የሚናገሩት አያልነህ፤ የመጀመርያው አፍሪካውያን በራሳቸው ጭንቅላት አገሮቻቸውን ሊመሩ አለመቻላቸውና የአፍሪካን ኢኮኖሚ፤ ባህልና ፖለቲካ መምራት የነበረባቸው ምሁራን በስደት ላይ መሆናቸው እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ሁለተኛው ስሜታቸውን የነካው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ ለስደተኞች በሮቿን ከፍታ በሰላምና በፍቅር የምታስተናግድ ሰላማዊ ሀገር መሆኑዋ ነው ብለዋል - የታሪኩ ዋና ገፀ ባህርይ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ብር ቤት ተከራይቶ ከገባበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን መኖሩን በመግለፅ፡፡

የፊልሙ ታሪክ ወጥ መሆኑን ወድጀዋለሁ የሚሉት አቶ አያልነህ፤ መሪ ገፀባህርይው ለውጭ ተፅእኖ የማይሸነፍ ሆኖ መቀረፁ ጭብጡን አሪፍ በማድረጉ ፊልሙን ለመስራት አነሳስቶኛል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለስደተኞች ሁለተኛ አገር እንደሆነችና ስደተኛን በየትኛውም ሁኔታ በመቀበል፤ እንደኢትዮጵያዊ ሆነው እንዲኖሩ እስከመፍቀድ በሚያደርስ አክብሮት የምታስተናግድ መሆኗ ይታወቃል ያሉት ፀሐፌ ተውኔቱ፤ በታሪኩም ውስጥ ይሄው ጭብጥ መንፀባረቁ እንዳስደመማቸው ተናግረዋል፡፡

“ፊልሙ ከተሰራ እየተረሳ ያለውን ኢትዮጵያዊነት እና ያልተነካውን ቱባ ባህል ማንፀባረቂያ ይሆናል” ይላሉ - ባለሙያው፡፡

በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ የሚሰሩ ፊልሞች በአገሪቱ ቱባ ባህልና በእውነተኛው ኑሮአችን ላይ ከማተኮር ይልቅ በውጫዊ የባህል ተፅዕኖዎች በስፋት እየተበረዙ መምጣታቸውን ለመግታት እንዲህ አይነት የፊልም ስራዎች ፈርቀዳጅ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል ባለሙያው እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ባህላቸውን ተንተርሰው የኪነጥበብ ሥራቸውን እያጐለበቱ እንደሆነ በማውሳትም የኢትዮጵያ ባለሙያዎች በዚህ ረገድ በቂ ትኩረት ሰጥተው አለመስራታቸውን ይተቻሉ፡፡ አቶ አያልነህ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት እና የተለያዩ ዲፕሎማቶችና አለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ እንደመሆኗ በሰሜን፤ በደቡብ፤ በምእራብና በምስራቅ አፍሪካ ያሉ አገራት ቱባ ባህሎቻቸውን በኪነጥበብ መሳርያነት በመጠቀም የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በአርዓያነት ተከትላ ለመስራት መንቀሳቀሷ እድገቷን እንደሚያፋጥን ሙሉ እምነት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ በፊልም ኢንዱስትሪው፤ በሙዚቃ፤ በቲያትር እና ተያያዥ የኪነጥበብ ዘርፎች መስራት የምትችልበት ምንም ያልተነካ ባህል እንዳላት የሚናገሩት አያልነህ፤ ‹ቡም› በሚል ርዕስ የሚሰራው ፊልም በዚህ ረገድ ፈርቀዳጅ ይሆናል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኪነጥበብ ዘርፎችም የአፍሪካዊነት ስሜት የተቀዛቀዘ መሆኑ ያሳስበኛል የሚሉት የኪነጥበብ ባለሙያው፤ በኬንያ፣ አልጄርያ እና ናይጄርያ ጉብኝታቸው ወቅት የተመለከቷቸው ፊልሞች፤ ሙዚቃዎችና ቲያትሮች ጭብጣቸው አፍሪካዊነትንና የየሀገሮቻቸውን ቱባ ባህሎች እንደሚያንፀባርቁ በመጥቀስ፤ በእኛም አገር ተመሳሳይ አቅጣጫ መከተል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

በአፍሪካ የኪነጥበብ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ልምድ እንዳላቸው የገለፁት አቶ አያልነህ ሙላቱ፤ ናይጄርያ ውስጥ “ፌስት ቴክ” በተባለው የጥቁር አፍሪካዊያን የፊልም ፌስቲቫል ላይ “ትግላችን” የተባለ “ማይም ድራማ” አሳይተው አድናቆት በማግኘታቸው ፊልሙ በመላው ናይጄርያ እንዲታይ መደረጉን፣ በኩባም ተጋብዘው ለማሳየት መቻላቸውን አስታውሰዋል፡፡

ባለሙያው ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው የ”ህዝብ ለህዝብ” ትርዒት አዘጋጅ እንደነበሩም ይታወቃል፡፡

የታሪኩ ደራሲ ብሩክ  ከበደ ገብረፃዲቅ፤ የፊልም ስክሪፕቱን የሚፅፉትና ዲያሬክት የሚያደርጉት አቶ አያልነህ ሙላቱ እንዲሁም ፊልሙን የሚሰራው የቲ - ደብሊው ሻሎም  አድቨርታይዚንግ ሃላፊ አቶ ጥላሁን ወልደ ሰንበት ፕሮጀክታቸውን እውን ለማድረግ ከበርካታ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ ጥላሁን እንደተናገሩት፤ ፊልሙን ለመስራት የወሰኑት የዘርፉ አንጋፋ ባለሙያ የሆኑት አያልነህ ሙላቱ ስክሪፕቱን ለማዘጋጀትና ፊልሙን ዲያሬክቲንግ ለማድረግ ሙሉ ፍላጎት እንዳላቸው በመግለፃቸው ነው፡፡ “ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ እና ተቀባይነታችንን የሚያጠናክርልን ሙሉ ታሪክ መሆኑም የመስራት ፍላጎታችንን ጨምሮታል” ብሏል፡፡ ”ቡም” የተሰኘው ፊልም በጭብጡ ፍፁም ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊነትን የሚያንፀባርቅ መሆኑን መረዳታችን በሙሉ ትጋት ለመስራት አነሳስቶናል የሚለው አቶ ጥላሁን፤ ሃሳባችን ፊልሙ በመላው አፍሪካ እንዲታይ ነው ብሏል፡፡ፊልሙ የ1.5 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚፈጅ መገመታቸውን የተናገሩት የቲ ደብሊው ሻሎም  አድቨርታይዚንግ ሃላፊ፤ ፊልሙን ለመስራት አንድ ዓመት ሊወስድ ይችላል ብለዋል፡፡ ድርጅታቸው ከሰራቸው ፊልሞች መካከል “ስውር ችሎት”፤ “ብራ”፤ “የቆየ ሰው”፤ “ታጋቹ” እና “ወደ መጣሁበት” (እየሩስ) ተጠቃሽ ናቸው፡፡ “ቡም” ለአፍሪካና ለዓለም ገበያ እንዲመጥን ተደርጎ እንዲሰራ አቅደናል ያሉት አቶ ጥላሁን፤ ፊልሙ በአማርኛ፤ በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ስለሚዘጋጅ ሰፊ ትኩረት እንደሚያገኝ አክለው ተናግረዋል፡፡ የሶማሊያዊውን ስደተኛ ህይወት መነሻ አድርጐ የተፃፈው የፊልም ታሪክ፤ ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚንና ማህበራዊ ህይወትን የሚዳስስ ሲሆን የታሪኩ ጭብጥ በመሃል አዲስ አበባ ያጠነጥናል፡፡ በሶማሊያና በኢትዮጵያ ድንበር ላይም የሚሰሩ ትእይንቶች ይኖሩታል ብሏል - ደራሲው፡፡ ታሪኩ ከተፃፈ 15 አመት እንደሞላው የገለፀው ደራሲ ብሩክ፤ በየጊዜው የሚጨመረው እየተጨመረ፣ የሚቀነሰው እየተቀነሰ ቆይቶ አሁን ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን አስታውቋል፡

 

 

Read 2501 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:54