Saturday, 19 September 2015 09:28

የአዲስ አበባ ተከራዮችና የዘላን ኑሮአቸው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ዘላኖች (አርብቶ አደር የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል) በተፈጥሮአዊ የአኗኗር ዘይቤያቸው የተነሳ በአንድ አካባቢ ወይም ቦታ ረግተው አይቀመጡም. . .አይቆዩም፡፡ በየጊዜው ጓዛቸውን ተሸክመውና  በግመል አሸክመው መሄድ ነው-- ...መሄድ...መጓዝ....፡፡ የበረሃውን ሀሩር ሽሽት፤ ምግብና ውሃ፣ ለከብቶቻቸውም መኖ ፍለጋ .....ይሄዳሉ፣ይጓዛሉ፡፡የአዲስ አበባ ቤት ተከራዮችም እንዲሁ ናቸው፡፡ በአንድ ቤት ወይም ሰፈር አይረጉም...አይቆዩም፡፡ በየጊዜው እቃቸውን በአይሱዙና በፒክአፕ ጭነው መሄድ...ነው----መሄድ..መሄድ...ብቻ፡፡ የኑሮ ውድነቱን ሽሽት፤ ዋጋው ጣራ ያልነካ ወይም ከጣራው በላይ ያልዘለለ ቤት ፍለጋ---መጓዝ፡፡
ዘላኖች ቋሚ መንደር ወይም ቀዬ አልባ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ተከራዮችም ሰፈር አልባ ናቸው፡፡ የሥነልቦና ጫና ሰለባም ይሆናሉ፡፡ አንድ ቦታ ተረጋግቶ መኖር እንደማይቻል ማሰቡ የሚፈጥረው የስነልቦና ተፅእኖ፣ በየጊዜው እቃ ማስጫን ማስወረዱ፣ አዲስ ሰፈር የመላመዱ ፈተና፣ በተለይ ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸውን በየጊዜው ከአንዱ የሰፈር ትምህርት ቤት ወደ ሌላ ሰፈር ትምህርት ቤት በማዘዋወር የሚያዩት ፍዳ ቀላል አይደለም፡፡
የአዲስ አበባ #ዘላኖች” ፤በአኗኗራቸው ሁኔታ ምክንያት ቤት ጎረቤት፣ እድርና  ማህበር አልባም ጭምር ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ የማህበራዊ ህይወት ወጎች ለተከራይ ቅንጦት ናቸው፡፡
በነገራችን ላይ የቤት ተከራዮች ዋንኛ አመታዊ ጭንቀት፣ኪራይ ይጨምር ይሆን ወይንስ አይጨምር ይሆን የሚለው ሳይሆን ስንት ይጨምር ይሆን የሚለው ነው፡፡ መጨመሩማ አይቀሬ ነው፡፡ እንደውም በነጋ በጠባው ኪራይ አለመጨመር በህግ ያስቀጣል ተብሎ የተደነገገ ነው የሚመስለው፡፡ ቤቱ ምንም ሳይለወጥ በየጊዜው ኪስን የሚያራቁት ኪራይ መቆለል፣ ለአከራዮች ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል ነው፡፡
ቆዳህን የላጡህ ያህል የሚሰማህ ግን አንተ ነህ - ተከራዩ. . . የአዲስ አበባው ዘላን!!
ደግሞ ለምን እንደሁ እንጃ፣ አከራዮች ሲባሉ የቤት ኪራይ መጨመሩን የሚገልፁት ወይ ጠዋት አልያም ማታ ላይ ነው፡፡ ጠዋት ወይም ማታ ላይ በር አንኳኩተው ወይም ስልክ ደውለው ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ይሄን ያህል ጨምሩ፡፡ አለቀ በቃ፡፡ ከቻልክ ትከፍላለህ፤ ካልቻልክ ትወጣለህ፡፡ ጭማሪው ከተሰማ በኋላ ቀኑ አንዴት እንደሚያልፍ ወይም ሌሊቱ እንዴት እንደሚነጋ አስቡት፡፡ ያው በጭንቀት ይዋላል፤በጭንቀት ይነጋል፡፡
ከገቢያችሁ በላይ የሆኑ  የቤት ኪራይና መሰል የኑሮ ጉዳዮች የሚፈጥሯቸው የወጪ ቀዳዳዎች መስፋት እንዴት ናላ እንደሚያዞር ለእናንተ መንገር ለቀባሪው እንደማርዳት ነው፤ ኑሯችሁን ታውቁታላችኋ፡፡
አንዳንድ አከራይ ደሞ አለ፡፡ መጨመሩ ላይቀር ከጭማሪው ጋር የሰበብ መዓት አግተልትሎ የሚመጣ፡፡ ትንሽ እያመመኝ ስለሆነ ለህክምና ብር ያስፈልገኛል ኪራይ ጨምር፤ ጤፍ፣ ምስር፣ ዘይትና በርበሬ ተወዷል ኪራይ ጨምር፤ እንዲህ ስለሆነ ነው ኪራይ ጨምሪ፣ እንዲያ ስለሆነ ነው ኪራይ ጨምሩ....ጨምሩ...ጨምሩ......፡፡ ኤዲያ ምንድነው በተከራይ ጫንቃ ላይ መወዘፍ (ጠብቆም ላልቶም መነበብ ይችላል) እኔ የህክምና ወጪ ደረሰኞቼን ባሳይ፣ የወሩን ኪራይ ይቀንሱልኛል? ጤፍ፣ ምስር፣ ዘይትና በርበሬ የሚጨምረውስ በአከራይ ላይ ብቻ ነው? ግርም እኮ ነው የሚለው፡፡
አንድ አከራይ ነበሩኝ፡፡ ግቢያቸው ተከራይቼ እንደገባሁ ከሰጡኝ ማስጠንቀቂያዎች መካከል መብራት እያበሩ (ቴሌቪዥን እያዩ፣ እያነበቡ ወይም ስራ እየሰሩ--) ማደር፣ ቤት ውስጥ ተጨማሪ ሰው ማስገባት አይደለም እግር የሚያበዙ ሌሎች ሰዎች መመላለስ ከጀመሩ ያለምንም ማስጠንቀቂያ የቤት ኪራይ እንደሚጨምር እወቅ-----የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡ ማስጠንቀቂያውን ሰጥተውኝ፣ ዱሮ ጠዋት ጠዋት በሬዲዮ በምንሰማው የቡናና ሻይ ማስታወቂያ ዜማ ስልት፤
የኢኮኖሚ ዋልታ ኪራይ ኪራይ
የገቢ ምንጫችን ኪራይ ኪራይ ...
የእድገታችን ገንቢ ኪራይ ኪራይ ..... እያሉ በኪራይ ሰብሳቢነታቸው እየተኩራሩ ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ እኔም ማስጠንቀቂያውን በሚገባ ነበር ተግባር ላይ ያዋልኩት፡፡  ሌሊት ማንበብ ካለብኝ በሞባይል ባትሪዬ፤ ፊልምም ካየሁ በላፕቶፕ፣ ጓደኞቼም ካስፈለጉኝ፣ ሄጄ ቤታቸው ነበር የማገኛቸው፡፡
ሰውየው ኪራይ መጨመራቸው ላይቀር ሰበብ ይፈልጉ ነበርና አንድ ቀን ማታ ከስራ ስገባ ሳሎን ቤታቸው አስጠሩኝ፡፡ አየኸው!?»
ወደ 32 ኢንች ቴሌቪዥናቸው ዞር ስል፣ በቅርቡ የተመረቀ አንድ ትልቅ ህንፃ ማስታወቂያ ይተላለፋል፡፡ እሳቸው ቀጠሉ ማብራሪያቸውን፡-
«አለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት ቀውስ በሁሉም ሀገራት ላይ ተፅእኖውን እያሳደረ ነው፡፡ ሰሞኑን ዜናው ሁሉ እሱ ነው፡፡ እውነቱን እኮ ነው፡፡... የኑሮ ወድነቱማ ሀገራችን ከገባ ቆይቷል፡፡ የሰሞኑ ደሞ ባስ ያለ ነው፡፡ አሁን በቀደም ዕለት ለልጆቼ ጫማና ልብስ ልገዛ መርካቶ ሄጄ . . . . . . »
ሰውየው ይሄን ሁሉ ለምን እንደሚነግሩኝ ቢያንስ ለጊዜው አልገባኝም ነበር፡፡ ድክም ብሎኝ ስለነበር ወሬያቸውም ከኑሮው ጋር ተዳምሮ ስልችት ስላለኝ ከልቤ አልነበረም የማዳምጣቸው፡፡ መጨረሻ ላይ ግን ያሉት ነገር የመጀመሪያውን አሰልቺ ልፍለፋቸውን ዳርዳርታ ግልፅ አደረገልኝ፡፡ በል እስኪ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ኪራይ ጨምር፡፡ ከገባሁ ገና 3 ወር እንኳን አልሞላኝም ብዬ ለመከራከር ባስብም የትም እንደማያደርሰኝ ስለገባኝ  እሺ ብዬ ወጣሁ፡፡
አስቡት እስኪ ኪራይ ለመጨመር ከምዕራቡ አለም የኢኮኖሚ ቀውስ እስከ መርካቶ የልጆች ልብስ ገበያ የሚደርስ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔን ያዘለ ሰበብ፡፡
ከጨመሩ ዝም ብለው አይጨምሩም፡፡ ተከራይ እንደሁ ከመክፈል አልያም እቃውን ሸክፎ ቤት ፍለጋ ከመሰደድ ውጪ አማራጭ እንደሌለው ያውቁታል፡፡ ሀይ ባይ የለማ፡፡ ማን የሚጠይቃቸው አለ፡፡ ከሚመለከተው አካል የሚጠበቀው የአከራይ ተከራይ መመሪያ እንደሆነ የውሃ ሽታ ሆኗል፡፡ የከተማውን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር የሚፈታ የተባለለት የቤቶች ልማትም፣ ችግሩን ማቃለል አባይን በጭልፋ ሆኖበታል፡፡ በዚያ ላይ የኮንዶሚኒየም ቤት ገዝቶ አትርፎ መሸጡ የደራ ቢዝነስ ሆኗል፡፡
በአንድ በኩል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ለህዝብ በእጣ ይከፋፈላሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነ አጅሬ (የከተማይቱ ሀብታም የቤት ነጋዴዎች) ወደድ ሲል ለመሸጥ አልያም በውድ ለማከራየት በርካታ ቤቶችን ከህዝቡ ላይ ይገዛሉ፡፡
ሰው ስንት አመት ሲጠብቅ የኖረውን ቤት የማግኘት እድል ሲደርሰው እልል ብሎ በመቀበል ፈንታ የሚጠበቅበትን ክፍያ ለማሟላት ጭንቀት በጭንቀት መሆን ከጀመረ ከራረመ፡፡ ኮንዶምንየም ቤት ደርሷቸው ቅድሚያ ክፍያውን ለመክፈል ስንት እናቶችና አባቶች ልመና እንደወጡ፣ እራሱ ኮንዶምንየም ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ይሄን ማድረግ ባለመፍቀዳቸው ወይም እርዳታ ለምነውም ስላልተሳካላቸው የመጣላቸውን እድል በውክልና ስም ለነጋዴ የሸጡትን ደግሞ ውልና ማስረጃ ይቁጠራቸው፡፡
እነዚህ ሰዎች የመክፈል አቅም አንሷቸው የሸጡትን ቤት ነገ መልሰው በውድ ዋጋ ተከራይተው ለመኖር ይገደዳሉ፡፡ አንዱ ሰፈር ሲወደድባቸው ወደ አንዱ፣ከዚያም ወደ ሌላው እያሉ እንዲሁ እንደ ዘላን ሲንከራተቱ ይኖራሉ፡፡
አንዱ የቤት ችግር ከአንዱ ሰፈር ወደ አንዱ ሰፈር የሚያላጋው አርቲስት፤ #ለምን ልጅ አትወልድም?; ተብሎ ሲጠየቅ፤ “እኔ ሰፈር የሌለው ልጅ መውለድ አልፈልግም” አይደል ያለው፡፡ ሸጎሌ ይረገዛል፣ ኮልፌ ይወለዳል፣ ሳሪስ ያድጋል (ቤተሰቦቹ ኪራዩን መቋቋም ከቻሉ እስከ 2 አመቱ)፣ ከዚያ አሁን ባለው ሁኔታ ጭማሪውን ችሎ አንድ ሰፈር ውስጥ ከሁለት አመት በላይ መቆየት ስለማይቻል ከቤተሰቡ እቃዎች ጋር በአይሱዙ እየተጫነ የዘላን ኑሮውን ይገፋል፡፡ ይሄንን ልጅ ሰፈርህ የት ነው ብሎ መጠየቅ፣ ውጤቱ ልጁን ማወዛገብ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ምን ብሎ ሊመልስ ይችላል?
እንደው ግን ለአዲስ አበባ ተከራይ የዘለቄታ መፍትሄው ምን ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ እኔ ግን በቀጣዩ የአዝማሪዎች የቅብብሎሽ ግጥም ልሰናበታችሁ፡-  
ፈረንሳይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ አስኮ
ምን ታርግ ትልቀቅ እንጂ....
የዘንድሮ ኪራይ ያሳቅቃል እኮ
አስኮ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ ገርጂ
መንግስትና አከራይ ለሰው እዘኑ እንጂ
ገርጂ ላይ ባስጠይቅ ሄዳለች አቡዋሬ
እዛ ይቀንሳል የሚል ሰምታ ወሬ
አቡዋሬ ባስጠይቅ ሄደች አሉ ሰሚት
ኮንዶሚኒየም ግቢ ይሻላል ብለዋት
ሰሚት ላይ ባስጠይቅ ሄዳለች ኮተቤ
እንክርቱዋን ሲያስብ ተሰበረ ልቤ
ኮተቤ ባስጠይቅ ገባች አየር ጤና
የገቢዋን እጥፍ ክራይ ከወሰደው ምን ሰላም አለና
አየር ጤና ስደርስ ሄዳለች ሰበታ
ከራቀ ቅናሽ ነው የሚል ወሬ ሰምታ
ሰበታ ባስጠይቅ ሄደች አሉኝ ገላን
መቼም ቋሚ የለው የከተማ ዘላን፡፡

Read 4060 times