Saturday, 04 February 2012 12:55

የኃይለሥላሴ ደስታ “ዲግሪዎች”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

አንድ ወዳጄ የደራሲ ኃይለሥላሴ ደስታ ሥራዎች ናቸው ብሎ ሦስት መፃህፍት አንብቤ እንድመልስለት አዋሰኝ፡፡ እጄ የገቡትን ጥራዞች ሳገላብጥ ደራሲው “ዲግሪዎቼ” የሚላቸው ስድስት የድርሰት ሥራዎች እንዳሉት ተረዳሁ፡፡ በመጀመሪያ ያነበብኩት “የካሣ ትዝታዎች” በሚል ርእስ በክፍል አንድና ሁለት በተለያየ ጥራዝ የቀረቡትን መፃህፍት ነው፡፡በአንድ ሰው ታሪክ ላይ የቀረቡት ሁለቱ የልቦለድ ጥራዞች ስለ ደራሲው ማንነት የማወቅ ፍላጐቴን ቀስቅሰውታል፡፡ በሁለቱም መፃህፍት የመጀመሪያ ገፆች ላይ “ይህ መፅሐፍ ከታተመ በኋላ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፅሁፌን ሳይቀንስ አሳትሞ ለመጠቀም ይችላል” የሚለውና የደራሲውን ወይም የሕጋዊ ወራሾቹን ባለመብትነት “ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ” መስጠቱን ያሳወቀበት መግለጫ ስለ ደራሲው ማንነት እንዳስብ አንድ መነሻ ሆኖኛል፡፡

ሁለተኛው ምክንያቴ በ”ካሣ ትዝታዎች” ሁለቱም መፃህፍት ላይ ከልደት እስከ ሽምግልና ያለው ታሪካቸው የቀረበው ገፀ ባህሪ፤ ከሴቲት ሁመራ እስከ አብደራፊ ባለው የ80 ኪሎ ሜትር ርቀት በላንድሮቨር መኪና ሲጓዙ በወሰደባቸው ሁለት ሰዓት ተኩል ጊዜ ለሹፌሩ እያጫወቱት ነው ታሪኩ የሚነገረው፡፡ በሌላ አገላለፅ በምልሰት ትረካ ሁለት የተለያዩ ጥራዞች የወጣው ታሪክ፤ በ80 ኪሎ ሜትር ጉዞ ከሦስት ሰዓት ባነሰ ጊዜ (መቼት) ውስጥ የተከናወነ ነው፡

ሦስተኛው የደራሲው መፅሐፍ “የሚያቃጥል ፍቅር” የሚል ርእስ ተሰጥቶታል፡፡ የመፅሐፉ ባለታሪክ እግረ ፀሀይ ትባላለች፡፡ 212 ገፆች ያሉት ይህ መፅሐፍ፤ ስለ ደራሲው ማንነት ለመጠየቅ የሚጋብዝ አቀራረብ አለው፡፡ ሦስቱም መፃህፍት በ1960ዎቹ አጋማሽ የታተሙ ናቸው፡፡ ደራሲውና ሥራዎቹ ለታተሙበት ዘመን ብቻ ሳይሆን አሁንም ቢሆን በስፋት ሊያነጋግር የሚችል ነገር ያላቸው ይመስላል፡፡ “የሚያቃጥል ፍቅር” መፅሐፍ ውስጥ የተለያዩ ሰዎችንና ቦታዎችን የሚያመለክቱ 12 ያህል ፎቶግራፎች አሉት፡፡ ከፎቶዎቹ ግርኔ ከሰፈሩት መግለጫዎች መሃል ጥቂቱ ይህንን ይመስላል፡፡

እግረፀሐይ ለትምህርት ውጭ አገር ስትሄድ ቤተሰቦቿና የአባቷ ጓደኞች የሸኟት በዚህ መልኩ ነበር፡፡

በፓሪስ እያለሁ በህይወቴ ወስጥ ደስ የሚለኝ እስፖርት፣ ሙዚቃ፣ ውሃ ዋናና መፃህፍት ማንበብ ነበር፡፡

ከተፈራ (ከመጀመሪያ ፍቅረኛዋ) ጋር ስንገናኝ የነበረኝ ሰውነት ይህንን ይመስል ነበር፡፡

ከዘመዶቼ ተለይቼ (ተጣልታ) ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ምሳ የበላነው አዋሽ ላይ ነበር፡፡

የልጄ አባት አሌኔክስ (ፎቶ)

ሕንዳዊ ወዳጄ ታጁ (ፎቶ)

የሴተኛ አዳሪነት ኑሮዬ (ፎቶ)

ልጄ መቅደስ አሌኔክስ (ፎቶ)

ባልታወቀ ምክንያት የሞተው የጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ ልጅ የኔነህ መንግሥቱ መካነ መቃብር

ዮሴፍ የሚገኘው የእግረፀሐይ መካነ መቃብር

ማንም ሰው እጁ የገባውን መፅሐፍ ማንበብ ከመጀመሩ በፊት ጥራዙን አገላብጦ እንደሚመለከተው ሁሉ እኔም “የሚያቃጥል ፍቅር” መፅሐፍን ከማንበቤ በፊት ሳገላብጥ ያየኋቸው ፎቶግራፎችና የግርጌ ማስታወሻቸው ስለ መፅሐፉም ስለ ደራሲውም የማወቅ ጉጉቴን ጨመረው፡፡ መፅሐፉን ሳነበው ይህ ታሪክ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተፃፈ ሳይሆን አይቀርም ብዬ እንዳስብ የሚያደርግ ተጨማሪ መረጃ አገኘሁ፡፡

በመፅሐፉ የመጀመሪያ ገፆች “ይድረስ ከወንድሜ ከአቶ ኃይለሥላሴ ደስታ” በሚል ርእስ በቀረበ ፅሁፍ “አስቀድሜ የማክበር ሰላምታዬን አቀርብልሃለሁ፡፡ ምናልባት ይህ በዛ ያለው ደብዳቤ ሲደርስህ ማነች ብለህ ተጨነቅ ይሆናል… ይህ እውነተኛ የሆነው የሕይወት ታሪኬን ያዘለውን ፅሁፍ ከራስህ አንድም ሳትጨምር አሳትም… በኑሮዬ የተለዋወጠ መከራና ደስታ፣ ሐዘንና ልእርድ የደረሱብኝ በመሆኔ ለታሪኬ አርእስት ይሆነኝ ዘንድ “የሚያቃጥል ፍቅር” ስል ሰይሜዋለሁ የሚል ደብዳቤ ሰኔ 22 ቀን 1962 ዓ.ም እግረፀሐይ ለደራሲው መላኳን መፅሐፉ ያስነብባል፡፡ እነዚህ ነገሮች በራሳቸው መፅሐፉን ለማንበብ ጉጉት ይፈጥራሉ፡፡ የመፅሐፉ ታሪክ በአጭሩ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

የመፅሐፉ ባለታሪክ እግረፀሐይ ከፊውዳል ቤተሰብ ኢትዮጵያ ወስጥ በቀድሞው ሐረር ክፍለ ሀገር ተወልዳ የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ ወደ አሜሪካ፣ ፈረንሳይና ጀርመን በመሄድ በሕክምና ዶክትሬቷን ይዛ እንደተመለሰች በሐረር ሆስፒታል በሙያዋ ማገልገል ትጀምራለች፡፡ በዚህ መሃል አባቷ ለአንድ ነጋዴ ሊድሯት ያስባሉ፡፡ ሆኖም ግን በሙያው ወታደር ከሆነውና የመጀመሪያ ፍቅረኛዋ ከነበረው ከተፈራ በማርገዟ ምክንያት ከአባቷ ጋር የተፈጠረው ግጭት እስከ ሞት አደጋ የሚያስከትልባት ስለሆነና ፍቅረኛዋም በተመደበበት ግንባር ስለሞተ ከሐረር ተሰዳ ወደ አዲስ አበባ ትመጣለች፡፡

ወደ መሐል ከተማ ከመጣች በኋላ በሙያዋ ሥራ ለማግኘት ብትሞክርም የቢሮክራሲ ሰዎች የሐረር ሥራዋን የተወችበትን ምክንያትና በመሰል የልግመት አሰራራቸው አልሳካ አላት፡፡ ለጊዜው መጠለያ የሰጧት ሰዎች ከውቤ በረሃ ሴቶች አንዷ እንደትሆን ገፋፏት፡፡ በመጀመሪያው የሴተኛ አዳሪነት ዘመኗ ብዙ ችግሮችን አሳለፈች፡፡ በቡና ቤቱ ያገኛት አንድ ወንድ በእርግጫ መትቷት ከተፈራ ያረገዘችው ፅንስ እንዲጨነግፍ ምክንያት ሆነ፡፡ በተለያየ ምክንያትም ለእስር ተዳርጋለች፡፡

እግረፀሐይ ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ያህል በሴተኛ አደሪነት ስትቆይ ከሦስት ወንዶች ጋር አስደሳች የፍቅር ጊዜ አሳልፋለች፡፡ ሴት ልጅ የወለደችለት አሜሪካዊው አሌኔክስ አንዱ ነው፡፡ ቡና ቤት በተፈጠረ ግጭት በሰው ሞት በመጠርጠሩ ምክንያት ከኢትዮጵያ ሲወጣ የጋራ ልጃቸውምንም ይዞ ወደ አሜሪካ ሸሸ፡፡ የእግረፀሐይ ሁለተኛ የልብ ወዳጅ በሕንድ ኤምባሲ የሚሰራው ታጁ የሚባል ሰው ነበር፡፡ ሦስተኛው ከመሳፍንት ቤተሰብ የሚወለደው አለማየሁ ነው፡፡

በእነዚህ አምስት አመታት ከሦስቱ ጋር ፍቅር በሚባል ደረጃ ልባዊ ወዳጅነት መሥርታ እንደነበር የምትተርከው እግረፀሐይ፤ ከተራ የቡና ቤት አሻሻጭነት ተነስታ የግሏን ቡና ቤት እስከከፈተችበት ጊዜ ደረስ ባለው የሴተኛ አዳሪነት ህይወቷ በተለያየ ጊዜ ያስተናገደቻቸው 247 ወዳጆች እንደነበሯትም ትገልፃለች፡፡

በተለይ የራሷን ቡና ቤት ከከፈተች በኋላ በሐረር ሆስፒታል በዶክተርነት ታገለግል በነበረበት ጊዜ ታስተምር እንደነበረው በሥነ ተዋልዶና በግል ንፅህና አጠባበቅ ዙሪያ በቡና ቤቷ ለሚሰሩ ሴተኛ አዳሪዎች ሰፊና ጥልቅ ትምህርት ስትሰጥ እንደነበር ተፅፏል፡፡ የመፅሐፉ ባለታሪክ፤ አለማየሁ በሚባለው ሦስተኛ የልብ ወዳጇ በተተኮሰባት ጥይት ስትሞት ነው ታሪኩ የሚያበቃው፡፡

ደራሲ ኃይለሥላሴ ደስታ በመፅሐፉ የመጨረሻ ገፅ ላይ የእግረፀሐይን ገዳይ ለመጠየቅ ማረሚያ ቤት መሄዱን ይነግረንና ከአቶ አለማየሁ የሰማሁት ነው ብሎ ባለ 26 ስንኞች ግጥም ያስነብበናል፡፡ በመቀጠልም ግጥሙ “ቆንጂትዬ” የሚል ርእስ ተሰጥቶት አበበ ኃይለሚካኤል በሬዲዮ ሁለቱን ፍቅረኞች ለማስታወስ ይረዳ ዘንድ እንዲዘፈን አደረኩት ብሎ ያበቃል፡፡

“የሚያቃጥል ፍቅር” ከመነሻ እስከ መድረሻ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተፃፈ መፅሐፍ መምሰሉ እግረፀሐይ ማን ትሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህ ጥያቄ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የደራሲውን ማንነት እንዲጠየቅ ያስገድዳል፡፡ ስለ ኃይለሥላሴ ደስታ ለማወቅ ያደረግሁት ጥረት ግን ብዙ ቢደክሙም እየተረሱ ከመጡት ደራሲያን አንዱ መሆን ደረጃ ላይ መድረሱን ነው ያመለከተኝ፡፡የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር፤ ኢትዮጵያዊያን ፀሐፍትን ለማስተዋወቅ በሦስት ተከታታይ አመታት ባሳተመው ሦስት አጀንዳዎች ውስጥ ስለ ደራሲ ኃይለሥላሴ ደስታም ሆነ ስለሥራዎቹ ምንም አለመግለፁን አስተዋልኩ፡፡ ፍለጋዬን ስቀጥል አንድ አንጋፋ ፀሐፊ “በደራሲ ኃይለሥላሴ ደስታ ላይ የተሻለ መረጃ ሳይኖረው አይቀርም” ብለው ወደ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ መሩኝ፡፡ ጋዜጠኛውም ያለውን መረጃ በመስጠት ተባበረኝ፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ “ኦ! ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሰራ?”፣ “ጥቁር ሆኖ መፈጠር ወንጀል ነው ወይ?” እና “በገነት ውስጥ ያለ ሲሆል” የሚሉ ርእሶች ያላቸው ስድስት መፃህፍት ያሳተመው ደራሲ ኃይለሥላሴ ደስታ፤ በ1941 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ቢወለድም ቤተሰቦቹ የሐረር ነዋሪዎች ነበሩ፡፡

ሐረር፣ አዲስ አበባ፣ ሴቲት ሁመራ፣ አስመራ፣ ጐንደር፣ አለታ ወንዶ፣ ወደ መሳሰሉት ቦታዎች በመንቀሳቀስ በመምህርነት፣ በህዝብ ደህንነት መሥሪያ ቤት አባልነት፣ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት፣ በቴአትር አሰልጣኝነት፣ በ”ጐህ” መፅሄት ዋና አዘጋጅነት፣ በወረዳ አስተዳደሪነት አገልግሏል፡፡

በ1979 ዓ.ም ደራሲ ኃይለስላሴ ደስታ ታሞ በተኛበት ስለ ህይወትና የሥራ ታሪኩ ደምመላሽ አለሙ ለተባለ ሰው ተናግሯል የሚለው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፤ በ1963 ዓ.ም የታተመው “የሚያቃጥል ፍቅር”፤ 40 ሺህ ኮፒ ታትሞ መሸጡን ይገልፃል፡፡ መፅሐፉ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተፃፈ ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄ ጋዜጠኛው የሚከተለው ምላሽ አለው፡፡

“በህይወቴ ከተጫወቱብኝ ደራሲያን መካከል ዋነኛው ኃይለስላሴ ደስታ ነው፡፡ ምክንያቱም የዶ/ር እግረፀሐይ ፍቅሬ መቃብርና ሐውልት ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ይገኛል ብሎ ስለፃፈ ለብዙ ጊዜ ሐውልቱን ስፈልግ ኖሬያለሁ፡፡ እውነት መስሎኝ” ብሏል፡፡

“የሚያቃጥል ፍቅር” ልቦለድ ታሪክ ከሆነ መፅሐፉ ውስጥ ያሉትን ባለታሪኮች እንዲወክሉ ስለቀረቡት እውነተኛ ፎቶግራፎች ምን መልስ መስጠት ይቻል ይሆን? ደራሲ ኃይለሥላሴ ደስታ በመፃህፍቶቹ ላይ የራሱን ወይም የመፃህፍቱ ሕጋዊ ወራሾችን መብት “ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ” የመስጠቱ ጉዳይስ ሕጋዊ ትርጉም ምን ይሆን?

 

 

Read 2678 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:59