Saturday, 04 February 2012 13:00

ሆሄያትን ያስዋጠ የኑሮ ውድነት- የኑሮ ወግ

Written by  ቢኒየም ሐብታሙ
Rate this item
(0 votes)

እኔ የምለው… ነገሩ ሁሉ በየጊዜው ሲጨምር ሲጨምር… መጨመር የሚለው ቃል የአስደንጋጭነት ሃይሉ ቀንሶ በግርምተ-እልፈት ተተካ አይደል፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት የመጨመር አባዜ ገና ሲጀማምር “እንዴ!” እያልን ከፊሎቻችን ስናጉረመርም፣ ሌሎቻችን ስናማርር፣ ምሁሮች ስንመራመር የቆየን ቢሆንም አሁን አሁን ግን ጭማሬው የማናችንንም ማማረርና መመራመር ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ይባሱኑ በመጨመሩና ለውጥም ስላልመጣ ማማረራችንም እየቀነሰ መመራመራችንም እየታከተ መጥቷል፡፡ በሌሎች አገራት እንዲህ አይነት የዋጋ መናርና የሸቀጦች ጭማሪ ሲኖር የደሞዝ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችም ጭማሪ በማድረግ የግብይይት ስርአቱን ለጊዜውም ቢሆን ለማረጋጋትና ክፍተቱን ለመሙላት የሚሞከርበት ስርአት ቢኖርም በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግን የጨመረው ነገር የህዝቡ ሃሳብ እንጂ ደሞዝና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች አይደሉም፡፡

የሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው ሲጨምር የሰው እንቅስቃሴና አኗኗር ግን እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ሰው አሁን አሁን መብላት ብቻ ሳይሆን የቀነሰው ማውራትም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ የሆነ ነገር ጨመረ ሲባል በጣም የተለመደችው የማማረሪያ ቃላችን “እንዴ!” እንኳን የኋለኞቹ ሆሄያቷ ተውጠው በ”እ!” ተቀይራለች (ደግሞ ጨመረ በሚል ቅላፄ)፡መቼም ኑሮ ካሉት… ነውና የማይለመድ ነገር የለም፡፡ በየጊዜው በጫንቃችን ላይ የሚከመረው የሸቀጦች እና የአገልግሎቶች ጭማሪ አስጐንብሶን ሁላችንንም አንገት ደፊ አስመስሎናል፡፡ ከሌላ አገር ለመጣ ዜጋ መቼም ኢትዮጵያውያን እንዴት ያሉ አንገት ደፊዎች ናቸው ሳያሰኘው አይቀርም፡፡ አሁን አሁን የሆነ ነገር ጨመረ ሲባል መደንገጥ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ይልቁንም “መቼ ጨመረ ደግሞ!” ብሎ ከዚያም ጭማሪውን ከፍሎ  ለነገር የማትበቃ አጭር አረፍተ ነገር ጣል አድርጐ ማለፍ የብዙዎቻችን የቀን ተቀን ዳዊት ሆኗል፡፡ ባለሱቁ ላይ እናጉረመርማለን፣ ባለታክሲው ላይ እናጉረመርማለን፣ ባለ ዳቦ ቤቱ ላይ እናጉረመርማለን፣ ባለወፍጮ ቤቱ ላይ እናጉመርማለን… የማናጉረመርምበት ጉዳይ የለም፡፡

በየመንገዱ የስንብት ወይም የጠላሁሽ መንፈስ ያለው ዘፈን እያንጐራጐሩ የሚሄዱ የሚመስሉ ፊቶችን ቀረብ ብለው ጆሮ ቢሰጧቸው ከሩቁ ማንጐራጐር የመሰልዎት ማጉረምረም ሆኖ ያገኙታል፡፡ “የደላህ!” አትሉኝም፡፡ በዚህ ሰዓት አሁን ማነው ከሃሳብ የተረፈ ጊዜ አግኝቶ የሚያንጐራጉረው? እንደውም ሳስበው ሰሞኑን በቅጂ መብት የተነሳ ከገበያ ወጣን ያሉ አሳታሚዎችም ሆኑ ሙዚቀኞች “የመጨረሻው!” ተብለው ምክንያታቸውን ቢጠየቁ ትክክለኛውና ያሳሰባቸው ምክንያት የቅጂ መብት ጉዳይ ሳይሆን የገዢ መጥፋት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ኑሮ ለቅሶ በሆነበት ጊዜ ማነው እስቲ ዘፈን ገዝቶ የሚሰማው? ህዝቤው በአጋጣሚ በሙዚቃ ቤት ሲያልፍ ወይም በሬዲዮ የሚሰማውንም ዘፈን በ”እያነቡ እስክስታ” ዘይቤ እንደሚያዳምጥ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ያው እሱንም ውስጡ የሚጮኸው ሃሳብ ላፍታ ዝም ካለለት ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን ውጪው ጩኸት ውስጡ ጩኸት… ኢያሪኮ፡፡

በሃሳብ ናውዘው በየመንገዱ የሚጋጩ ሰዎች፣ ብቻቸውን የሚለፈልፉ፣ የሚያጉረመርሙ (የሚያንጐራጉሩ አላልኩም)፣ በየታክሲው መውረጃቸውን የሚረሱ፣ መልሳቸውን የሚረሱ፣ (መልሳቸውን እንኳን የሚረሱ ጥቂት ናቸው፤ ምክንያቱም ድፍኑ በአሁኑ ጊዜ እንዲህ በቀላሉ አይገኝምና ነው) ድፍኑ ስል ለአንድ መቶ ብር  የተፃፈ ደብዳቤ ትዝ አለኝ፤ ላጫውታችሁ… “ለተከበርከው መቶ ብር፤ ለጤናህ እንደምን አለህ፣ እኔ ካንተ ሃሳብና ናፍቆት በስተቀር በጣም ደህና ነኝ፡፡ ታናሽ ወንድምህን ሃምሳ ብርን አልፎ አልፎ አገኘዋለሁ፣ አስር ብርን እና አምስት ብርን ስለጤንነትህ ስጠይቃቸው ‘እሱንማ ተወው የውሃ ሽታ ሆኗል’ አሉኝ፤ ውይ የኔ ነገር! ረስቼው የመጨረሻ ልጅህን አንድ ብርን ብታየው አታውቀውም፤ ተሻሽቶ ተሻሽቶ ምን እንደመሰለ” ሁሉም ኪስ ይገባላ፡፡

መቼም በፅሁፌ ውስጥ የተጠቀምኩባቸውን ማነፃፀሪያዎች አይታችሁ አካበድክ እንደማትሉኝ እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም ሰው ባሁኑ ሰዓት የሚያካብደው ነገር ሳይሆን መቶ ብርን ሆኗል፡፡ “ምነው አካበድክ!” የሚለው ቃል እራሱ “ምነው እራስህን እንደ መቶ ብር ቆለልክ!” በሚል ተቀይሮ የለ፡፡

አሁን አሁን አብዛኛው ነዋሪ ከብዙ ነገሮች እራሱን እየገዛና እያራቀ እንዲሁም ብዙ ነገሮችን እየቀነሰና እያቆመ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ በቀን ሦስቴ ከመብላት እንደምንም ብሎ ሁለት ጊዜ በመብላት በተቀረው በሃሳብ መብላላት፣ ከማውራት ይልቅ አለማውራት፣  ከሳቅ ይልቅ ሳግ… ወዘተ ቅጥ ያጣው የኑሮ ውድነት ያመጣቸው ችግሮች ናቸው፡፡ የምግብ ወጪን ለመቀነስና የምግብ ፍላጐትን ለማጥፋት ሲባል ከጠዋት ጀምረው ጫትን የሚቅሙ ወጣቶች መበራከት ሌላው ትኩረት የተነፈገው ጉዳይ ነው፡፡

ሰሞኑን በስራ የምንተዋወቅ አንድ ጓደኛዬን በተደጋጋሚ ወደ ባንክ ሲመላለስ ስላስተዋልኩት በጣም ከነከነኝና ልጠይቀው ወሰንኩ፤ “ምን!” አትሉኝም? ብድር አይደለም፤ አልበደርምም ለማለት አይደለም፤ ችግሩ ከዚህ ባልደረባዬ ጋር የብድር ግንኙነት የሌለን መሆኑ ነው፡፡ ለማንኛውም ወደ ባንክ እንዲህ አዘውትሮ የሚሄድበትን ጉዳይ ለማወቅ ሀይለኛ ጉጉት ወጥሮ ያዘኝ፡፡ እስከማውቀው ድረስ ይህ ባልደረባዬ በውጪ የሚኖሩ የቅርብ ዘመዶች ወይም ጓደኞች የሉትም፤ ብር እየተላከለት ነው እንዳልል፤ ወይ ደግሞ በቅርብ አንድ ዘመዱ ወደ ውጭ ሄዷል እንዳልል ወርቅ የሚያወጣ ነጋዴ ካልሆነ በስተቀር በሳምንት ሁለት እና ሦስት  ቀን ብር ሊልክለት አይችልም… ብቻ በሃሳቤ እንግሊዝና ጃፓን እየረገጥኩ፤ (በሃሳብ እዚህና እዚያ እያልኩ ማለቴ ነው) አሳቻ ሰዓት ጠብቄ ጥያቄዬን ሰነዘርኩ፡፡

“አንበሳው! ሰሞኑን ወደ ባንኮች እግርሽ ረዝሟል፤ በሰላም ነው?” አልኩት በቀረቤታዊ አጠያየቅ እንስታዊ ዘይቤ ተጠቅሜ “…በሰላም ነው?” የምትለው ሀረግ ሌላ ሃሳብ አዕምሮዬ ላይ ጫረችብኝ “ባንክ ለመዝረፍ የባንኮቹን የጥበቃ ሁኔታ እያጤነ ይሆን እንዴ ብዬ” አሰብኩ… ነገር ግን ሃሳቤን ሳልጨርስ ንግግሩን ቀጠለ “ባክህ ምን ይገኛል! ደግሞ እንዴት አስተዋልከኝ? ይሄኔ ሌላውም እንዳንተ አይቶኛል ማለት ነው?” አለ  በሃፍረት ፀጉሩን እየፈተለ “…ምን መሰለህ፣ እንዴት ማንበብ እንደምወድ ታውቃለህ አይደል? በተለየ ትኩስ መረጃዎችን ሳልሰማ መዋልና ማደር አይሆንልኝም፤ ታዲያ ይሄ የኑሮ ውድነት ያልጨመረው የሸቀጥ ዋጋ ባለመኖሩ በስስትና በደንበኝነት እየተከታተልኩ የማነባቸው ሁለትና ሦስት ጋዜጦች እንዲሁም ጥቂት መፅሄቶች ዋጋ ኪሴ የማይደፍራቸው እየሆነ መጥቷል፡፡ ታዲያ በአንድ አጋጣሚ ከጓደኛዬ ጋር ለእርሱ ጉዳይ ወደ ባንክ ሄጄ እሱ ጉዳዩን እስኪፈጣጥም በባለጉዳይ ወንበር ላይ ቁጭ ብዬ  ከምወዳቸው የህትመት ውጤቶች አንዱን እያነበብኩ አንድ ሃሳብ ብቅ አለልኝ፤ ምን አትለኝም?”

“ምን?” ለማለት እንኳን ፋታ ሳይሰጠኝ ንግግሩን ቀጠለ “በቃ ልክ እንደ ባለጉዳይ ወንበር ላይ ቁጭ እያልኩ ኪሴ ያልቻላቸውን ጋዜጣና መፃህፍት ማንንም ሳላስፈቅድ በነፃ መኮምኮም፡፡ ታዲያ ምን አለፋህ ከዚያ ወዲህ ባንክ ለጉዳይ የሚሄድ ሰው እየተከተልኩ በመቶ ሜትር ሩጫ ፍጥነት ጋዜጦቼን… ይቅርታ ጋዜጣቸውን መኮምኮም ሆኗል ስራዬ እልሃለሁ፡፡ ጉዳይ ኖሮት ወደ ባንክ የሚያቀና ሰው እንኳን ካጣሁ ብቻዬን እየሄድኩ ያልተላከልኝን ብር እየጠበኩ፣ ጋዜጣዬን እኮመኩማለሁ እልሃለሁ፡፡”

ነገሩ ጨርሶ ወደ አእምሮዬ ሽው ያላለ ጉዳይ በመሆኑ በግርምት “ወይ አንተ! አያልቅብህ” ስለው “ኑሮ በዘዴ” ብሎኝ ሳቀ፤ እኔም ለወደደው ነገር የከፈለውን መስዋእትነትና ድፍረቱ አስገርሞኝ በሳቅ አጀብኩት፡፡ ትንሽ ተሳስቀን እንዳበቃን “ባንክ ብቻ ነው ሳዘወትር ያየኸኝ ማለት ነው?” አለኝ “ምነው ኢንሹራንስም ትሄዳለህ እንዴ?” አልኩት እየሳቅሁኝ፤ እሱም በሳቅ እያጀበኝ “ሌላው ሱሰ-ንባቤን የማስታግስበት ቦታ የት እንደሆነ ታውቃለህ?” አለኝ “የት?” አልኩት ሌላ ጉድ ለመስማት ቸኩዬ “ፀጉር ቤቶች፤ ጓደኞቼ በሙሉ ፀጉር ሲቆረጡ እየተከተልኩ እሄድና ቁጭ ብዬ መኮምኮም ነው” ሌላ ብዙ ደቂቃዎች የፈጀ የግርምት ሳቅ! “እንደውም…” አለኝ በመቀጠል “ወንዶቹ ጓደኞቼ ፀጉራቸውን ቶሎ ቶሎ ስለማይቆረጡ ከሴት ጓደኞቼ ጋር ሁሉ የውበት ሳሎን የምሄድበት ጊዜ አለ” ብሎኝ ሳቁን ለቀቀው፡፡ እኔም የዚህ ጉደኛው ጓደኛዬ ጉድ እያስገረመኝ ረጅም ሳቆችን አብረን ሳቅን፡፡

አሁን እንዲህ አይነቱን ሰው ምን ብለን ነው የምንጠራው “ሌባ?” መስፍን  ሀብተማሪያም እንዳለው ከሆነ መፅሃፍት የሚሰርቁ “ሌባ” አይባሉም ይልቁኑም “የመፅሃፍት ቀበኛ” ወይም ለኔ ጓደኛ እንዲስማማ “የጋዜጣ ቀበኛ” ልንለው እንችላለን፡፡ ለነገሩ ጓደኛዬ በላቡ ጥሮ ግሮ ያልገዛቸውን ጋዜጦች በነፃ አነበበ እንጂ አልሰረቀም፤  ይህም “ኪራይ ሰብሳቢ” እንጂ “ሌባ” አያስብለውም፡፡ እንደውም ለአዲስ አዋጅም እንዲስማማ ይህን አይነቱን ኪራይ ሰብሳቢነት “አንብቦተ-ኪራይ ሰብሳቢነት” ብለን ልንፈርጀው እንችላለን፤ የቅጣት ዝርዝሩ ውስጥም ለ5 ዓመት ከማንኛውም ህዝባዊ ባንኮች፣ ፀጉር ቤቶች እንዲሁም የውበት ሳሎኖች እንዲታገድ የሚል ነገር ሊገባበት ይችላል፡፡

ኑሮ በዘዴ አለ ጓዴ! እውነቱን ነው፡፡ ዝነኛው ፈላስፋ አፍላጦን “Necessity is the mother of invention” ያለው ትዝ አለኝ (በርግጥ ይህችን አባባል አፍላጦን ተናግሯታል ይባል እንጂ በውል በፅሁፎቹ ውስጥ አልተገኘችም) ለማንኛውም ከላይ የጠቀስኳት የእንግሊዝኛ አባባል ደረቅ ትርጉሟ “ችግር የፈጠራ እናት ናት” እንደማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ “ብሶት የወለደው…” ልንለው እንችላለን (ይሄ ሃረግ ወደ ግንቦት 20/1983 ሊወስደኝ ሆነሳ… ሆ!)

መቼም እንደዚሁ እንደኔ ባልደረባ ስንት ብሶት የወለዳቸው ብልሃቶች በየጓዳው እንደተፈጠሩ ጓዶች ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ ”እንዴ!” ማለቴ “እ!”… በዚህ አጋጣሚ የቀጣይ ፅሁፌን ርእስ እዚሁ አገኘሁ ማለት አይደል… “የጓዳዎች ጉድ!” አሪፍ ርእስ ናት አይደል? ፅሁፍህ ጓዳና ጉድ በዛበት እንደማትሉኝ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

ባለፈው ሳምንት “ካዛንቺስ ቶታሉ ጋር ጠብቂኝ?” በሚል ርእስ የተነበበችው የዮናስ ኪዳኔ ፅሁፍ ላይ ስለ ኑሮ ውድነት የተጠቀሰችው መጠይቃዊ አባባል ትዝ አለችኝ (እንስታዊ የገለፃ ዘይቤ ያበዛሁ አልመሰላችሁም?) ግለ-ሂስ ስላወረድኩ ያው ለሚቀጥለው አስተካክል ብላችሁ እንደምታልፉኝ እርግጠኛ ነኝ (አይደለሁም፡፡)

ለማንኛውም ወደ አባባሏ… “ደስ የማይልን ነገር ስለምን ወደ አዕምሯችን እንዲመላለስ ፈቀድን?” ትላለች፡፡ ዮናስ በፅሁፉ እንደ መፍትሄ በመጠቆም የኑሮ ውድነትን ለመርሳት ብቸኛው አማራጭ ብሎ ያስቀመጠው “የኑሮ ውድነትን መርሳት፤ እስከነመፈጠሩ መርሳት…” በማለት ነበር፡፡ በሉ እኔም የኑሮ ውድነቱን ወደምረሳበት ቦታ ልመርሽ፤ እናንተም ቀሪ ንባባችሁን ቀጥሉ፡፡ (ገዝታችሁም ይሁን በባንክ ቤት አሊያም በፀጉር ቤት የምታነቡ አንባቢያንን ሁሉ ያካትታል ቂቂቂቂ…)

 

 

Read 3200 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 13:03