Saturday, 04 February 2012 13:05

ምስኪኗ ኢኳቶሪያል ጊኒ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

የአገሪቱ የነዳጅ ሃብት የፕሬዚዳንቱ ነው

የፕሬዚዳንቱ ልጅ 23 የቅንጦት አውቶሞቢሎች አሉት

ባለፈው ሰሞን በጋቦንና በኢኳቶርያል ጊኒ ጣምራ አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለውን የአፍሪካ የእግር ኳስ ዋንጫ በማስመልከት ሁለት አስገራሚ ዜናዎች ተሰምተዋል፡፡በኢኳቶሪያል ጊኒ የተደለደሉት ሀገራት የተዘጋጀላቸው ሆቴል እዚህ ግባ የሚባል ደረጃ የሌለው መናኛ ሆቴል በመሆኑ የተነሳ፣ የረባ የመፀዳጃ አገልግሎት እንኳ ለማግኘት እንደተቸገሩ በተለይ ደግሞ የምግብና የውሃ አገልግሎቱ ከሁሉም በላይ ፈታኝ እንደሆነባቸው በምሬት የገለፁት አንደኛው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኢኳቶሪያል ጊኒ የመጀመሪያ ጨዋታዋን በድል በማጠናቀቋ የሀገሪቱ የግብርና ሚኒስትር የአንድ ሚሊዮን ዶላር ቦነስ ለብሔራዊ ቡድኑ አባላት በግላቸው የመስጠታቸው ዜና ነው፡፡

እነዚህን ዜናዎች አስገራሚ ያደረጋቸው በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀውና ባለፀጋ የሆነችው ኢኳቶሪያል ጊኒ፤ እንግዶቿን በወጉ ለማስተናገድ የሚያስችል ሆቴል ማዘጋጀት አቃታት ቢባል ለሰሚው ግራ ስለሚሆንበትና አንድ ሚኒስትር እንዴት ያለ ባለፀጋ ቢሆን ነው ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን አንድ ሚሊዮን ዶላር ቦነስ መስጠት የቻለው ወይም በሌላ አነጋገር ገንዘቡን ከየት አመጣው የሚለው ነው፡፡

በ1968 ዓ.ም ከስፔን ቅኝ አገዛዝ ነፃነቷን የተቀዳጀችው ኢኳቶሪያል ጊኒ፤ ተፈጥሮ ባደላት የተፈጥሮ የነዳጅ ሀብት የተንበሸበሸች ባለፀጋ ሀገር ናት፡፡ ይህቺው ሀገር በነዳጅ ምርቷ ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ከናይጄሪያና ከአንጐላ በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ የምትገኝ ስትሆን በቀን ሦስት መቶ አርባ ስድስት ሺ በርሜል ነዳጅ አምርታ ትሸጣለች፡፡ በቀን የምታወጣው ነዳጅ ስድስት መቶ ሀምሳ ሺ ለሚሆነው ጠቅላላ ህዝቧ ብታከፋፍለው እያንዳንዱ ዜጋዋ ከሞላ ጐደል በቀን ግማሽ በርሜል ነዳጅ ይደርሰዋል ማለት ነው፡፡ አንድ በርሜል ነዳጅ በአንድ መቶ ዶላር ይሸጣል በሚል ሂሳብ ብናሰላው ደግሞ እያንዳንዱ የኢኳቶሪያል ጊኒ ዜጋ በየቀኑ ሀምሳ ዶላር ማግኘት ይችላል ማለት ነው፡፡

ይህ ስሌት ማናችንንም ሳያከራክር ኢኳቶሪያል ጊኒን በአለም እጅግ ከፍተኛ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ያስቀምጣታል፡፡

አሳዛኙ ነገር ይህ ሁኔታ በስሌት ደረጃ እንጂ በገሀድ አለም እውነት አለመሆኑ ነው፡፡ መዲናዋን ማሳቦን ጨምሮ ባታንና ሌሎች ትላልቅ ከተሞቿንና በእዚያ የሚኖሩትን ህዝቦቿን አኗኗር ያየ የኢኳቶሪያል ጊኒን የነዳጅ ሀብት ባለፀግነት ይጠራጠራል፡፡ አለበለዚያም የነዳጁን ሽያጭ ገንዘብ መዳረሻ ለማወቅ ጥያቄውን ያነሳል፡፡

እውነታው ግን እንዲህ ነው፡፡ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከላይ የጠቀስነውን ቁጥር ያህል በርሜል ነዳጅ ለአለም ገበያ ታቀርባለች፡፡ የሽያጩ ገንዘብ መዳረሻ ግን የሀገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ሳይሆን የፕሬዚደንቱና የወዳጅ ዘመዶቻቸው ኪስ ነው፡፡ ባላት የነዳጅ ሀብት ከፍተኛ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ የምትመደበው ኢኳቶሪያል ጊኒ፤ አሁን የምትገኘው በአለም እጅግ አነስተኛ የነፍስ ወከፍ አመታዊ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ነው፡፡

ሦስት አራተኛ የሚሆነው የኢኳቶሪያል ጊኒ ህዝብ እጅግ አሰቃቂ ከሆነ የድህነት ወለል በታች ይኖራል፡፡ በየአመቱ ከሚወለዱት ህፃናት መካከልም አስራ አምስት በመቶ የሚሆኑት የአምስት አመት የልደት በአላቸውን ሳያከብሩ ይህችን አለም በሞት ይሰናበታሉ፡፡

በጤና በትምህርትና በሌሎች የመሰረታዊ አገልግሎት አቅርቦቶች፤ በመሰረተ ልማት መስፋፋት በኩልም እድገቷ በጣም ደካማ ከሚባሉት ተርታ ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት እንደ ቅንጦት ከሚታይባቸው ሀገራት አንዷ ኢኳቶሪየል ጊኒ ናት፡፡

ኢኳቶሪያል ጊኒ ያለችበትን ጠቅላላ ሁኔታ በአንድ አረፍተ ነገር አጠቃልላችሁ ተናገሩ ብትባሉ ማለት ያለባችሁ የስፔን ቅኝ ገዢዎች እንደገና መጥተው ቢያዩዋት የዛሬ አርባ አራት አመት ትተነው የሄድነው ነገር ሁሉ አንድም ሳይነካና ሳይቀየር እንዳለ አገኘነው ብለው ተናገሩ የሚለውን ብቻ ነው፡፡ ኢኳቶሪያል ጊኒ ትናንትም ዛሬም ያው ናት፡፡

የኢኳቶሪያል ጊኒ ነገረ ስራ እንዲህ ከሆነ ቀጣዩ ጥያቄ የነዳጅ ሽያጩ ሀብት የት ገባ? የሚለው ነው፡፡

ናይጄሪያውያን ሁሌም ለሚያጋጥማቸው እንዲህ ያለ ተመሳሳይ ጥያቄ የሀገራቸውን ፕሬዚደንት ቤተመንግስት፣ የፓርላማ አዳራሹንና የየክልል መሪ ቺፎችን ቤተመንግስት በጣታቸው እያሳዩ፣ የነዳጅ ገንዘባችንን ሰይጣኑ በላብን ይላሉ፡፡ ናይጄሪያውያን እንዲህ የሚሉት ሀብታችንን መሪዎቻችን በዘረፋ አራቆቱን ለማለት ነው፡፡

ኢኳቶሪያል ጊኒዎች ደግሞ “የሀገራችን ፕሬዚዳንት ብርጋዴር ጀነራል ቴዎዶር ንጉዌማ ሞባሶጐና ቤተሰባቸው እንጂ ኢኳቶሪያል ጊኒ ነዳጅ አታመርትም” በማለት የነዳጅ ሽያጩ ሀብት የት ገባ ለሚለው ጥያቄ በጨዋ ደንብ መልስ ይሰጣሉ፡፡ ኢኳቶሪያል ጊኒዎች መሪያቸውን በተመለከተ መስጠት የሚችሉት ጠንካራ መልስ ይህ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ማለፍ የፈንጂ ወረዳውን ማለፍ ማለት ነው፡፡

ይህንንም ቢሆን የሚናገሩት በግልፅ ሳይሆን ግራ ቀኙን ቃኝተው በሹክሹክታ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ማለፍ አይችሉም፡፡ ይህ ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ለእኛ እንጂ ለእነሱ ተጨማሪ ማብራሪያ የማያስፈልገው ግልፅ ነገር ነው፡፡ እርግጥ ነው እንደ ሌሎቹ ሀገራት ህዝቦች ሁሉ ኢኳቶሪያል ጊኒዎችም ህግ አላቸው፡፡ ህጋቸውም ፕሬዚዳንታቸው ብቻ ናቸው፡፡

ኢኳቶሪያል ጊኒዎች ነዳጅ አምርቶ የሚሸጠው ፕሬዚዳንቱ እንጂ ሀገራችን አይደለችም በማለት ሲናገሩ ማሽሟጠጣቸው ሳይሆን እውነተኛውን ነገር ፍርጥ አድርገው መናገራቸው ነው፡፡

በ1979 ዓ.ም አጐታቸውና የመጀመሪያው የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚደንት የነበሩትን ፍራንሲስኮ ማስያስ ንጉዌማን በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ገልብጠው ስልጣን የያዙት ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ንጉዌማ፤ እሳቸው እንጂ ሀገራቸው ነዳጅ አምርታ እንደማትሸጥ ለህዝባቸውም ሆነ ለእኛ ያሳዩን የሀገሪቱ ነዳጅ ተመርቶ ለገበያ መቅረብ በጀመረ በሦስት አመታት ውስጥ ራሳቸውን ከተራ ቺስታ ፕሬዚደንትነት በአለም ታዋቂ ወደሆኑት ሚሊየነር ባለፀጋ ፕሬዚደንትነት በመቀየር ነው፡፡ ከዛሬ ስድስት አመት በፊት በ2006 ዓ.ም የወጣ የፎርብስ መፅሄት፤ በስድስት መቶ ሚሊዮን ዶላር በባለቤትነት በማስመዝገብ ፕሬዝደንት ኦቢያንግ ምባሶጐን ከአለም ስምንተኛ ሀብታም መሪ አድርጐ መዝግቧቸው ነበር፡፡ ግን ልብ ቢሉ ፕሬዚደንት ኦቢያንግ ምባሶጐ ከአለም ስምንተኛ የነበሩት የዛሬ ስድስት አመት ነው፡፡ ያኔም ሆነ ዛሬ ሳትቀየር በድህነት ትዳክራለች ያልናት ሀገሪቱን እንጂ የነዳጅ ሽያጩን አይደለም፡፡ ኢኳቶሪያል ጊኒ በቀን ሦስት መቶ አርባ ስድስት ሺ በርሜል ነዳጅ ለአለም ገበያ ታቀርባለች፡፡ ባለፈው አመት ብቻ እንኳ አራት ቢሊዮን ዶላር ከነዳጅ ሽያጭ አግኝታለች፡፡ ይህንን ገንዘብ ፕሬዚደንት ኦቢያንግ፣ እሳቸውን ጨምሮ ለመላው የሀገራቸው ህዘብ አካፍለውት ቢሆን ኖሮ እያንዳንዱ የኢኳቶሪያል ጊዜ ዜጋ የሰላሳ ሰባት ሺ ዘጠኝ መቶ ዶላር ቀጭን ጌታ መሆን ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን አላደረጉትም፡፡ ለምን? ቢባል ደግሞ የነዳጅ ምርቱም ሆነ ከሽያጩ የሚገኘው ገንዘብ የእሳቸው እንጂ የህዝቡ አይደለም፡፡

ፕሬዚዳንት ንጉዌማ ምቦሶጐ ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በአምባገነን መሪነታቸው ሁሌም ይከሀሳሉ፡፡ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ተቃዋሚዎቻቸው አምባገነንትንና ጨካኝነትን የወረሱት ከቤተሰባቸው ነው እያሉ ያሟቸዋል፡፡ በ1979 ዓ.ም በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው ያስወገዳቸው አጐታቸው ፍራንሲስኮ ማስያስ ንጉዌማ የለየላቸው ነፍሰ ገዳይ ነበሩ ይባላል፡፡ “ወደርየለሽ የነፃነት ሀዋሪያ”፣ “የኢኳቶሪያል ጊኒ ብቸኛው ተአምር” እያሉ ራሳቸውን ይጠሩት የነበሩት ማስያስ ንጉዌማ፤ ያኔ ወደ አራት መቶ ሺ አካባቢ ይገመት ከነበረው ዜጋቸው ውስጥ ሀምሳ ሺ ያህሉን ተቃዋሚዎች በሚል ረሽነዋል፡፡ በአሁኑ ፕሬዚዳንት ከስልጣናቸው በተገለበጡበት እለት በጥይት ደብድበው የገደሏቸው የገዛ ወንድማቸው ልጅ ናቸው፡፡ ያኔ የሰላሳ ሰባት አመት ወጣት የነበሩት የአሁኑ ፕሬዚዳንት፤ የማን ዘር ጐመን ዘር እንዲሉ የአጐታቸውን ችሎታ መውረሳቸውን ያሳዩት፣ የክብር ዘበኛ ወታደሩንና ከማላቦ ዳርቻ የሚገኘውን የብላክ ቢች ወህኒ ቤትን ቀጥ አድርገው በመምራት ያለ አንዳች ተቀናቃኝ ስልጣናቸውን በጥቂት ወራቶች ውስጥ በማደላደል ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ኦቢያንግ ንጉዌማ ባለፉት ሰላሳ አመታት ሶስት ጊዜ ምርጫ አካሂደው በፕሬዚዳንትነት ተመርጠዋል፡፡ ምርጫውን የታዘቡት ሁሉ “ምርጫ ሳይሆን ምርጫ የሚመስል ትርኢት ነበር” ብለው ትዝብታቸውን ተናግረዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ያሸነፉት ዘጠና አምስት ነጥብ አራት ከመቶ አግኝተው ነው፡፡

በዚህ ውጤት ፕሬዚዳንቱ ደስተኛ አልነበሩም ተብሎ ተወርቶባቸው ነበር፡፡ ብቸኛው እጩ ተወዳዳሪ ስለነበሩ ግን ምርጫው ተጭበርብሯል ማለት አልቻሉም፡፡ የተከፉት ግን በ1996 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ካመጡት ውጤት የአሁኑ አንሶብኛል በሚል ነው፡፡ ያኔ ያመጡት ዘጠና ሰባት ነጥብ ሰማኒያ አምስት በመቶ ነበር፡፡ ይህ መከፋታቸው ግን ብዙም አልቆየም፡፡ በዚያው አመት ያለቅጥ ባሻቀበው የነዳጅ ዋጋ ሳቢያ ያገኙት የደለበ ፔትሮ ዶላር ንዴታቸውን ያስረሳቸው ወዲያውኑ ነበር፡፡

የፎርብስ መጽሔት በ2006 ዓ.ም ባወጣው የሀብት ደረጃ፣ እንዴት አድርጐ እንደዘገባቸው ነግሬአችሁአለሁ፡፡ አሁን 2012 ዓ.ም ነው፡፡ በስድስት አመት ውስጥ የሚያስመዘግቡትን እድገት መገመት መቸም አያቅታችሁም፡፡

ባለፈው ሳምንት የወጣ አንድ የፋይናንስ መረጃ፤ ባለፈው አመት ብቻ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በአንጐላ የገባበት ሳይታወቅ ተሰውሯል ብሏል፡፡ መረጃውን ያቀረበው ተቋም ይህን ይበል እንጂ አንጐላውያን ገንዘባቸውን የሚበላውን ቀበኛ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡

እንደ ኦቢያንግ ንጉዌማ አይነት የአፍሪካ መሪዎች በሀብታምነታቸው በፎርብስ ዝርዝር ውስጥ ሊገቡ የሚችሉት በሁለት ምክንያቶች ብቻ ነው፡፡ አንድም የነዳጅ ማውጫ ጉድጓድ ሲኖራቸው አሊያም የሀገራቸውን ብሔራዊ ባንክ ትራሳቸው ስር ማድረግ ሲችሉ ነው፡፡ እንዲህ አይነት የከበርቴነት እድል የማይኖራቸው እንደጠቅላይ ሚኒስትራችን መለስ ዜናዊ አይነት መሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አሁን የሚያገኙት ደመወዝ በወር መቶ ሺ ብር ቢሆንላቸው እንኳን በሀብታም መሪነት በፎርብስ ዝርዝር ውስጥ ለመግባት ጨርሰው አይችሉም፡፡

አሁን መግቢያችን ላይ ወዳነሳናቸው ሁለት ጉዳዮች እንመለስ፡፡ ኢኳቶሪያል ጊኒ ላዘጋጀችው የአፍሪካ የእግር ኳስ ውድድር እንግዶቿን በወጉ ማስተናገድ የሚያስችል የረባ ሆቴል ማዘጋጀት ያልቻለችው የነዳጅ ዘይት ሀብት የእሷ ስላልሆነ ነው፡፡ የፕሬዚዳንቱ ልጅ በግሉ ለእግር ኳስ ቡድናቸው አባላት የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት መስጠት የቻለው ደግሞ የኢኳቶሪያል ጊኒን የነዳጅ ዘይት ሀብት እያወጡ የሚሸጡት አባቱ ፕሬዚዳንት ኦቢያንግ ንጉዌማ ስለሆኑ ነው፡፡

በጓደኞቹ ዘንድ ቴወዶሪን እየተባለ የሚጠራው የፕሬዚዳንቱ ልጅ የሰጠውን ገንዘብ ሲሰሙ ብዙዎች ተገርመው ነበር፡፡ የተገረሙት ማንነቱን ስላላወቁት ብቻ ነው፡፡ እንዴ! እሱ እኮ የፕሬዚዳንቱ ልጅ ነው፡፡ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ማሊቡ አካባቢ ተገኝተው የልጁን ሀብትና ነገረ ስራ ቢመለከቱ ኖሮ ግን አይገርማቸውም ነበር፡፡

የሀገሪቱ የግብርናና ደን ሚኒስትር የሆነው ቴወዶሪን፤ በሚኒስትርነቱ የሚያገኘው የወር ደመወዝ አምስት ሺ ዶላር ብቻ ነው፡፡ የልጁ አኗኗር ግን ልክ እንደ አንድ አልጋ ወራሽ ልዑል አይነት ነው፡፡ እንዲህ አይነት የልዑል ኑሮ የሚኖረው ደግሞ በሀገሩ ሳይሆን በአሜሪካ ነው፡፡

የፕሬዚዳንቱ ልጅ ቴወዶሪን፤ በካሊፎርኒያ ማሊቡ ውስጥ አስራ አምስት ሺ ስኩዌር ጫማ ስፋት ባለው የተንጣለለ ግቢ የመዋኛ ገንዳ፣ የቴኒስ ሜዳና ባለ አራት ጉድጓድ የጐልፍ መጫወቻ ሜዳ ያካተተ ባለስምንት መኝታ ቤት የተንጣለለ ቪላ ውስጥ ይኖራል፡፡

ይህንን ቤቱን ለማስዋብና ለሌሎች አገልግሎቶች ለምሳሌ ለምንጣፍ ሀምሳ ዘጠኝ ሺ ስምንት መቶ ሀምሳ ዶላር፣ ለቤት ውስጥ ቲያትር ሀምሳ ስምንት ሺ ዶላር ሲያወጣ ሁለት የወይን ጠጅ ብርጭቆዎችን ደግሞ በአንድ ሺ ሰባት መቶ ሰላሳ አራት ከአስራ ሰባት ሳንቲም ዶላር ገዝቷል፡፡ የአባዝራው ልጅ ማለት ይሄ ነው፡፡ በዚህ በማሊቡ ጐረቤቶቹ ብሪትኒ ስፒርስ፣ ሜል ጊብሰንና ሌሎች ዝነኛ የሆሊውድ ተዋናዮች ናቸው፡፡

ቴወዶሪን ከዝነኛ የዲዛይነር ልብሶች ውጪ ሌላውን ልብስ ቢሞትም ንክች አያደርጋትም፡፡ ከዲዛይነር ልብሶች ውስጥ ደግሞ የሚወደው የዶልትና ጋባናን ዲዛይነር ልብሶችን ነው፡፡

ለዚያውም ደግሞ ልዩ ሰፊ ተመርጦ ወደ ቤቱ እንዲለከው እየተላከለት፡፡ ዶልትና ጋባና ለዚህ ምርጥ ደንበኛቸው በየጊዜው የተለየ የፋሽን ትርኢት ያዘጋጁለታል፡፡ በዚህ የፋሽን ትርኢት አንዴ አብራው ለሄደችው የሴት ጓደኛው ሰማኒያ ሺ ዶላር የሚያወጣ ልብስ ገዝቶላታል፡፡ ቴወዶሪን የሚያደንቀው ምርጥ የዲዛይነር ልብሶችን ብቻ አይደለም፡፡ የቅንጦት መኪናዎችም ነፍሱ ናቸው፡፡ ሰባት ፌራሪ፣ አምስት ቤንትሌይ፣ አራት ሮልስሮይስ፣ ሁለት ላምቦርጊኒስ፣ ሁለት መርሴዲስ ቤንዝ፣ ሁለት ፓርሽ ሁለት ሜይባሽና አንድ አስቶን ማርቲን በድምሩ ሃያ ሶስት የቅንጦት መኪናዎች አሉት፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ለይቶ የሚያደንቀውና የሚወደው መኪና ግን ሁለት መቶ ሃምሳ ማይል በሰአት የሚከንፈውንና በሁለት ሚሊዮን ዶላር የገዛውን ባለሰማያዊ ቀለሙን ቡጋቲ ቬይሮን የተሰኘውን የቅንጦት መኪናውን ነው፡፡

ቴወዶሪንን ከሚደብሩት ነገሮች አንዱና ዋነኛው ትምህርት ነው፡፡ ትምህርት መማር ድብርቱን ያመጣበታል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ዶርም ይልቅ የሚመርጠው ቢቨርሊ ዊልሻየር ሆቴልን ነው፡፡

በ1991 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ እንደመጣ ለመማር የተመዘገበው በፒፐርዳይን ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ ወደ ክፍል የሚገባው ግን አንዳንዴ ለዛውም የሴት ጓደኞቹ ሳይመጡ የቀሩ ቀን ነበር፡፡

ይህንንም ከአምስት ወር በሁዋላ ከናካቴው እርግፍ አድርጐ ተወውና ከሴት ጓደኞቹ ከራፐርና የፊልም ተዋናይዋ ኢቭ፣ ከተዋናይዋ ታማላ ጆንስና የፕሌይቦይ መጽሔት ፕሌይ ሜቷ ሊንድሴይ ኢቫንስ ጋር አሸሸ ገዳሜውን ተያያዘው፡፡ ከነዚህ የሴት ጓደኞቹ ውስጥ ቴወዶሪን ለኤቫ የተለየ ልብ ነበረው፡፡ በ2005 ዓ.ም ታቱሽ የተሰኘችውን ባለሶስት መቶ ሶስት ጫማ የቅንጦት ጀልባ፣ በሰባት መቶ ሺ ዶላር ተከራይቶ ድል ያለ ፓርቲ አዘጋጅቶላት ነበር፡፡ ቴወዶሪን ከሚወዳቸው ነገሮች ሁለቱ ደግሞ እቃ መሸመትና እንቅልፍ ነው፡፡ ማታ ማታ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በየናይት ክለቡ ሲጠጣ ያመሽና ቀን እስከ ቀትር ድረስ ተኝቶ ይውላል፡፡ ሸመታ ነፍሱ ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም ፓሪስ ሄዶ በአንድ ቀን ብቻ ከሰላሳ በላይ ሙሉ ልብሶችን ሲገዛ አምሽቷል፡፡ በዚሁ አመት ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ውስጥ ያያቸውን ሁለት የመኖሪያ ቤቶችን ሰባት ሚሊዮን ዶላር ባንዴ ከፍሎ ገዝቶ ተመልሷል፡፡

የአሜሪካ ሴኔት የዚህን ልጅ ጉዳይ አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት ብታነቡ፣ እኔ ከነገርኳችሁ የበለጡ በርካታ አስገራሚ ነገሮችን ማንበብ ትችላላችሁ፡፡

የዚህ ሁሉ ነገር ሌላው ተጨማሪ ክፋት ደግሞ አንድ ነገር ነው፡፡ አባቱ ፕሬዚዳንት ኦቢያን ንጉዌማ ስልጣን በያዙ ማግስት ስልጣናቸውን እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ከሰላሳ አመት በኋላም እንኳ ባያስረክቡም ወራሽ እያዘጋጁ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ወራሻቸው እንዲሆን የታጨውም ይሄው ታሪኩን ያወጋንላችሁ ቴወዶሪን ነው፡፡ ምስኪን ኢኳቶሪያል ጊኒ፡፡

 

 

 

 

 

 

Read 5163 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 13:08